ስርሆተ ገፅ

ጣፋጭ ወግ ከአዛውንቱ ‘ዲዛይነር’ ጋር

በአዲስ አበባ እምብርት ፒያሣ ተገኝቻለሁ፣ የቀጠርኳትን እንስት ለማግኘት አምፒር ሲኒማ ፊት ለፊት የሚያስገባውን መንገድ ተያያዝኩት። ሠራተኛ ሠፈር ጋር ከሚገኝ አንድ የልብስ መሸጫ ሱቅ ውስጥ አገኘኋት። ንቁ ዓይኗ ብዙ እንደጠበቀችኝ አሳብቆባታል። ሰላምታ ተቀያይረን በኢትዮጲያ ሠማይ ስር ብሩህ የነበሩትን፣ በብርቱ ጥረት ነጭ አምላኪነትን የቀየሩ፣ አልባሳትን እድሜ ዘመናቸውን ሲለኩና ሲቆርጡ ከገናና መሳፍንት እስከ ታዋቂ ነጋዴዎች፤ ግርማ ሞገስ ከነበራቸው ጦር ጄነራሎች እስከ የንጉሥ ልጅ፣ ከጉምቱ ደራስያን እስከ ታዋቂ ዘፋኞች፤ በጥበባቸው ሲያደምቁ ከነበሩት ዲዛይነር አባቷ ጋር ልታገናኘኝ ነበር ቀጠሯችን።

የሠራተኛ ሰፈርን ቁልቁለት፤ ‘መጣሁባችሁ’ እያለ የሚያስፈራራንን ዝናብ ለመሸሽ ፈጠን ብለን ተጓዝን። ከሰፈሩ አንፃር ሲታይ ዘመናዊ የሚባል የጋራ መኖሪያ ቤት (ኮንደሚንየም) ደረስን። ፊቱን ለፍልውሃ ጀርባውን ለአራዳ የሰጠው ህንፃ ውስጥ እንድገባ አመለከተችኝ። ጥቂት ተጉዘን ገባን።

አባዬ ያልኩህ እሱ ነው፤ተጫወቱ” ብላ ወደ ማዕድ ቤት ገባች።

የክብር ዘውዳቸው ይበልጥ አሳምሮአቸዋል። ከተቀመጡበት ሶፋ አጠገብ ክራንች አለ። መንቀሳቀስ እንደማይችሉ እግራቸው ላይ የታሰረው ጀሶ ያስታውቃል። የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ ሱዳንን ያሸነፈች ቀን በጭፈራና በደስታ የሰከሩ ወጣቶች እየጨፈሩ ላያቸው ላይ እንደወጡና አጥንታቸው መሰበሩን ወደ ቤታቸው ከወሠደችኝ ልጃቸው ተነግሮኛል።

ብቻቸውን ነበሩ። ፋና ቴሌቪዥንም ብቻውን ይደሰኩራል። 1950ዎቹን፣ 1960ዎቹንና 70ዎቹን እንዲሁም እስከ 2000 ዓ.ም. ፒያሳን አባወራውን ሆነ ወይዛዝርቷን እንዳላደመቁላት፤ በዚህ ክፍል ያላቸው ስልጣን የሪሞት ብቻ ይመስላል። ትልልቅ የመንገድ መብራት የነበራት ከተማ፤ ያለእኚህ ጉምቱ ዲዛይነር የምሽት አበቦቿ ባልደመቁ ነበር። በጦርነት ሜዳ ላይ እምቢ-ባይነታቸውን ያሳዩ ጄነራሎች ዓይን ውስጥ የሚገቡትና ግርማቸው የሚንርላቸው እኚሁ ጥበበኛ ልብስ ሰፊ ጋር መጥተው የሸመቱትን ጨርቅ ሲለኩ፣ ሲያስቆርጡና ሲያሰፉ ነው። ሙዚቀኞች በቪድዮ ክሊፕ ላይ ለመድመቅ ሙሉ ልብስ ያሻቸዋል። ከዚያ ወደ ጠቢቡ ጨርቁን ይዞ መሄድ ብቻ በቂ ነው። ገበርዲኑን ተጠቦበት የሰመረ ቪድዮ መስራት እንድትችል ያደርግሀል። ፈገግ ብለው በእጃቸው የተቀመጥ ምልክት አሣዩኝ። ተቀመጥኩ። ጠይም፣ ረዥምና መልከ-ቀና ሲሆኑ፤ ውብ ዓይናቸው ጥልቀት እና ውስብስብ የህይወት ድርና ማግ እንዲሁም የቆዳቸው ሽብሸባት የጀብዱአቸውን ከፍታ ይናገራል። እንደ አብዛኞቹ ባለከባድ አእምሮዎች ቀለል ባለና ለጨዋታ ጋባዥ በሆነ ስብዕና “ስለመጣህ ደስ ብሎኛል” ብለው ሀድራችንን አደመቁት።

አቶ ዘለቀ

ቶሎ ምግቡን አሙቂው ኤልሳ!!” አሏት። አልተግደረደርኩም። ያቀረበችልንን የበግ ወጥ አጣጥመን ቡናችንን እየኮመኮምን የህዝብ ላይብረሪ ኖት ብዬ እስካደንቃቸው ለተስማሚ ወግ ጉሮሮአቸውን እንደመጥረግ ብለው ጀመሩ። በፀዳ ጠረጴዛ ላይ መቅረፀ-ድምፄን አስቀምጬ “እህም…” “እሺ….” ብቻ ሆነ ስራዬ።

ቀይዋ ነገር

በ1932 ዓ.ም. ነሐሴ1 የካ ሚካኤል የአቤቤ ሱቅ አከባቢ ተወለድኩኝ። ዛሬ ቤቶች የተሰሩባቸው ያን ጊዜ ሰፊ ሜዳ ነበር። ሜዳው ላይ እንንከባለልበታለን፤ ሳርና ሳር እያሰርን የሚራመድን ሠው እንጥልበታለን፤ ሳሩ ላይ ማዳለጥ እንጫወትበታለን፤ እግር ኳስና የገና ጨዋታ እንጫወትበት ነበር። አንድ ቀን በለመድኩት መንገድ ስጫወት ቀይ መጫወቻ የመሠለች ዕቃ አገኘሁ። በእጄ እየዳሰስኩናእያሻሸኋት ወደ መንደሬ ስጓዝ፤ አንዲት ሴት በመንገዴ ላይ አግኝታ አስቁማ ምን እንደያዝኩና የት እንዳገኘሁት ጠየቀችኝ። ነገርኳት። ነጥቃኝ በረረች። ጥቂት እንደተራመደች በትንሽ ሜትር ርቀት ላይ ኃይለኛ ፍንዳታ ተሠማ። ፍንዳታው የተሠማው ሴትየዋ ከሄደችበት አቅጣጫ ሲሆን ነገሩ እኔን አስደነበጠኝ። ለካ ቦምብ ነበር። አጠገቤ የነበሩ አሮጊት የነገሩን ምንነት ጠይቀውኝ “ገንዘብ መስሏት ነው እኮ የወሠደችብህ” አሉኝ። በኋላ እንደተረዳሁት ሴትየዋ በእኔ ጠንቅ አንድ እጇንና ዓይኗን ማጣቷን ሰማሁ። አውቄ ያደረግሁት ባይሆንም ባሰብኩት ቁጥር “እኔ ባልይዘው ኖሮ” እያልኩ እፀፀታለሁ።

ጣልያናውያን

የካ ሚካኤል ቄስ ት/ቤት ‘ግራጁዌት’ አድርጌ እንደጨረስኩ ተፈሪ መኮንን ት/ቤት ገባሁ። ክረምት መግባቱን ተከትሎ መዋያ ስላጣሁ አንድ የሰፈራችን ሠው ልብስ የሚሰፉበት ቤት እየተመላለስኩ እሄዳለሁ፣ በየቀኑ መመላለሴን ያየው ጣሊያናዊ የልብስ ቤቱ ባለቤት ‘ቱርኮ ሎጂ’ የመመላለሴን ምክንያት ጠየቀኝ፣ “ክረምት ት/ቤት ስለተዘጋ” አልኩት፤ ህይወቴን ለዘላለም የሚቀይር ጥያቄ ጠየቀኝ፣

“ለምን ልብስ ስፌት አትማርም? እኔ ወታደር ብሆንም ቀድሜ የተማርኩት የልብስ ስፌት ሙያ ለዚህ አብቅቶኛል።”

አቅማማሁ ግን ተስማማሁ። ለሁለት ዓመት አከባቢ መስፋትን ተማርኩ፣ ሳይታሰብ አስተማሪዬ “እናትህ ታማለችና ድረስ” በመባሉ ወደ ጣሊያን ሄደ፣ አልተመለሰም፣ 70 ደረጃ ልብስ ሰፊ ቤት ያላቸው ሌሎች ጣሊያኖች ቀጠሩኝ፣ ከምሳና ከእራት ውጪ ከጧት ሁለት ሰዓት እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ከመኪናዬ ላይ አልወርድም፣ ልብስ መለካት፣ መቁረጥና መስፋትን ተጠበብኩበት። ልብስ ዲዛይኒንግ ውስጥ የራሴን አሻራ ያገኘሁት ከጣሊያናውያን ነው።

የነጭ አምልኮና ልብስ ሰፊ ኢትዮጵያውያን

በሀገራችን ፈረንጅ የሰራውና ያደረገው ይከበራል። “የፈረንጅ ነው” ማለት ይበዛል። የኢትዮጵያ ነክ ነገሮች ለመጠቀም እራሱ ኢትዮጵያዊው የገንዘብ እጥረት ካልገጠመው በቀር፤ ፈረንጅ ሀኪም፣ ፈረንጅ መምህር፣ ፈረንጅ ሜካኒክ፣ ፈረንጅ ደራሲና ፈረንጅ ሼፍ ይመረጣል። በተለይ ልብስ ላይ እኔን ጨምሮ የእኛ ሃገር ዲዛይነሮች አይወደዱም። አማራጭ ከሌለ ብቻ ይታዘዛሉ። እኔ ለዚህ አንድ ምስክር ነኝ። በዚህ በዚህ ጃንሆይን አደንቃለሁ። እሳቸው ታደሰ ገብርዲን የሚባል ሰፊ ነበራቸው። ሌሎቹ በተለይ መሳፍንትና መኳንንት አካባቢ ለሀገር ውስጥ ጥበበኛ ቦታ አልነበራቸውም።

አንድ “አበሻ አይንካኝ” የሚሉ ጀነራል ጨርቅ ይዘው ኖባርድ ዶኖክያን የተባለ ጎረቤቴ ሰፊ ጋር ይመጣሉ። ጀነራሉ ከኔ ሱቅ ይልቅ ነጩን የመረጡት ነጭ ሁሉንም ይችላል” ከሚል አስተሳሰብ ሲሆን፤ ሰፊው ግን ስፋ ተብሎ የታዘዘውን የወታደር ሞዴል ስላቃተው እኔ ጋር መጣ። ሂድና ለካቸው!!” አለኝ። ሰውዬው ይማታሉ ተብሎ ስለሚወራ “እራስህ ለካ፤ እኔ ቆርጬ እሰፋልሀለሁ” አልኩት። ዶኖክያን ለካቸውና ጨርቁን ሰጠኝ። ዲዛይን አድርጌ ለፕሮቫ እንዲመጡ ተጠየቁ። መጥተው ፕሮቫ ሲደረግላቸው እኔ ተደብቄ ዐያለሁ። ምከንያቱ ደግሞ እኔ እንደሰራሁት ካወቁ እንደማይለብሱ መታወቁ ነው። ሴኮንዶ ፕሮቫም መተው ታዩ። ዲዛይን አድርጌ ገጥሜ ለአርሜንያው ዶኖክያን ሰጠሁት። በቀጠሯቸው ቀን ልብሳቸውን ሲለብሱት ተደብቄ ዐያለሁ።

ዶኖክያን የወታደር ልብስ በጣም ጎበዝ ነህካ!! አሉት። አዎን ጌታዬ አላቸው ያልሠራውን ልብስ፤ ብሬን ብቀበልም በሃገራችን ሠዎች ላይ ስለኛ ያለው ንቀት ያበሳጨኛል። ሌላው ገጠመኝ እዛው እኔ አከባቢ ካለ ጴጥሮስ ፓምቡክያን ከተባለ አርሜንያዊ ባለ ሱቅ የድረስልኝ ጥሪ ደረሰኝ። አንድ የንጉሡ አፈንጉሥ የነበሩ ሰው ልብስ እንዲሠፋላቸው ወደ ፓምቡክያን ገበርዲን ጨርቅ ይዘው ይመጣሉ። ሰውዬው ሐበሻ ዲዛይነር ላይ ያላቸው ጥላቻ ወደር የለውም። ገና ስለካቸው ገላመጡኝ። እየቀፈፋቸው ቁመት ወገብና ትከሻቸውን ተለኩልኝ። ፕሮቫም ላይ ገላመጡኝ። የመጨረሻው ቀን ግን ሙሉውን ሱፍ ገጭ አድርገው መስታወት ፊት ቆሙ። ፈገግ ሲሉ አየኋቸው። በልብሱ ልክክ ማለት ደስ መሰኘታቸውን ግን አልነገሩኝም። ለአርሜንያዊው ገንዘብ ከፍለው አመስግነውት ወጡ። ቅር መሰኘቴን ያየው ፓምቡክያን በማያውቅ ሰው አትናደድ ብሎኝ የሰራሁበትን ከፈለኝ። እንደዚሁ ሁለት ደንበኛዬ የነበሩ  የደጅአዝማጅነት ማዕረግ የነበራቸው ወንድማማቾች ያለቀውን ጨርቅ ለመውሰድ መጡ። አብረዋቸው በወቅቱ ለንጉሡ ቅርብ የነበሩ መሳፍንት ነበሩ። መስፍኑ የደንበኞቼ ወንድም ሲሆኑ ለወንድማቸው የሰፋሁለትን ልብስ እያሳያቸው በጣም አደነቁ። ሰፊው እኔ መሆኔን ሲነግራቸው በጣም ይገርማል ደግሞ እኮ አንድ ፍሬ ልጅ ነው አሉ። ወንድምዬው በመቀጠል እኔ ጋር ልብስ እንዲያሰፉ ሲነግራቸው እኔ እገሌ!! በማለት ከመቀመጫቸው ተነስተው

ለሐበሻ ጨርቄን አላስነካም ሲሉ በጣም ተቆጡ። ወንድምዬውም ምነው? እንዲህ ይባላል?” ብሎ በተራው ተቆጣና ሰዎቹ ወጡ። ቢወጡም ሀሳቡ ግን አሁንም ይታወሰኛል። ቅኝ ያልተገዛች ሀገር የሚል ስሰማ ይገርመኛል።

የቱባው ባለሥልጣን ድርጊት

በግሪክ ቤተክርስትያን እና ሸዋ ፋርማሲ መካከል ካለው ሱቄ ቆሜአለሁ። ከፊት ለፊቴ ህፃናት ፈረንጆቹን እየተመለከቱ እንደመልከፍና እንግሊዝኛ እንደማናገር ያለ ነገር እየፈፀሙ ነጮቹን ያስቸግራሉ። ጎረቤቴ አርመናዊ የልብስ ቤቱ ባለቤት ፈረንጆቹን የሚያስቸግሩትን ህፃናት ኢትዮጵያዊያን እናንተ ተው እነዚኮ የተከበሩ ሀገር ዜጎችና የተለዩ ናቸው ብሎ ህፃናቱን ያባርራቸዋል። ነገሩን ከጅምሩ ሲከታተል የነበረው ባለሥልጣን በእግሩ እየተንጎማለለና ሁኔታውን ቃኝቶ ስለነበር አርመኑን በጥፊ ሲለው የአርመኑ መነፅር ወደቀ። እነዚህ ናቸው ለሀገሬ ልጆች ልዩ ዜጋ? አንተ ማን ነህና ነው ኢትዮጵያውያንን የምታባርረው? እናውቃቸዋለን እኮ እነሱ ባገራቸው ተራ ሰዎች ናቸው ብሎ አስደነገጠው አርመኑም ባለሥልጣኑን ባየ ጊዜ ይቅርታ አጥፍቻለሁ አለ። በጥፊ የተማታው ባለሥልጣን በ1953 መፈንቅለ መንግሥት ከወንድሙ ጋር የተገደለው ግርማሜ ንዋይ ነበር።

የሴኔጋል አምባሳደር

 አንድ ሰው መኪናውን አቁሞ ሱቄ ገባ። እኔ መኪናዬ ላይ ትእዛዝ ለማድረስ አንገቴን አቀርቅሬ እሠራለሁ፣ የሴኔጋል ኤምባሲ ጸሐፊ ሲሆን በእንግሊዝኛ ውጪ የሰቀላችሁት ሱፍ የት ተሠራ?’” ብሎ ጠየቀኝ። እኔ ነኝ የሠራሁት” አልኩት። ውሸት ነው ይሄ እዚህ ሀገር ሊሰራ አይችልም” አለኝ። መሄድ ጀመረና ተመለሰ። የበታች ሰራተኛውን ሦስት ልብስ ሰጠኝና እስቲ በዚህ ልሞክርህ አለኝና” በፈለገው ልክ ሰራሁለት። በሚገርም ሁኔታ በስራው በጣም ስለተደሰተ ሌላም ሌላም ጨምሮ ሰጠኝ፤ ሰራሁለትና ረካ። ጭራሽ አምባሳደሩን ይዞ መጥቶ ለሳቸውም ሰራሁ። ወደዱት። እንደውም የሴኔጋል 3 ተከታታይ ኤምባሲ ሰራተኞች በሙሉ ልብሳቸውን የምሠራው እኔ ነበርኩ።

እብዱ አቀንቃኝ

እኔ ጋር መጥቶ ሲለካ፣ ሲቆረጥለትና ሲሰፋለት የሚደንስ፣ የሚያቀነቅንና የሚቁነጠነጥ ዘፋኝ ነበር። እኔ ጋ ያልመጣ ታዋቂ ሠው አልነበረም ማለት ይቻላል። ሮሃ ባንድ፣ ዋልያስ ባንድ እና ሂልተን ሆቴል እኔ ጋር አሰፍተዋል። ከዘፋኞች መሐሙድ አህመድ፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ አያሌው መስፍን፣ ታምራት ሞላ፣ ጌታቸው ካሣ፣ ከአዲሶቹ ጃኪ ጎሲ፣ አቤል ሙልጌታ፣ ዳን አድማሱ እና ልጅ ሚካኤል ደንበኞቼ ነበሩ። በ1981 ዓ.ም. መፈንቅለ መንግሥት ተሳታፊ የነበሩና የተከበሩ እንደ ጀነራል ደምሴ ቡልቶ እና ጀነራል መርእድ ንጉሤ ደንበኞቼ ናቸው። እንደውም ጀነራል ደምሴ ቡልቶ ውጭ ደርሰው ሲመጡ ዶላር የምዘረዝርላቸው እኔ ነበርኩ። ታዲያ ቅድም ወደ ጀመርኩልህ ጨዋታ ስመለስ እየተቁነጠነጠ ሲደንስ የነበረውን ታዋቂ አቀንቃኝ ልብስ ስለካው አባቴ አብሮኝ ነበርና እብድ ነው‘ንዴ?” አለኝ። ስቄ አባዬ ይሄ እኮ ጥላሁን ገሠሠ ነው” አልኩት።

ስንብት

ስለተደረገልኝ የበዛ መስተንግዶ አመስግኜ ከእንግዳዬ ቤት ወጣሁ። ወደ አዛውንቱ ዲዛይነር ቤት የሚወስደው መንገድ ጠመዝማዛ ነው። በአንድ ዕይታ ብቻ እንግዳ ተጓዥ ሊላመደው አይችልም። ሸኚ ተመድቦልኝ ጉዞ ጀመርን። ሸኚዬ መስማት የተሳነው ነው። ጉዟችን የዐይን ንግግር በቀር ድምጽ አልባ ነው። ውስጤን ደስታ ሲወረኝ ይታወቀኛል። የቆየሁባቸው ሰዓታት ከደቂቃ አንሰው የታዩኝ በዚህ ምክንያት መሆኑ ገብቶኛል። ስሜቱ እንዲህ ያለ የህዝብ ቤተ መጽሐፍት ሳናግር ሀሴት እንደማደርግባቸው ማናቸውም ቀናት ቢሆንም ነጭ አምላኪዋን የዛን ጊዜዋን ኢትዮጵያ በሀሳብ ወደኋላ ተጉዤ ተቀየምኳት። የዛሬውን ሁኔታዋን ሳስብ ደግሞ መልሼ ፈገግ አልኩ። ቢያንስ ቢያንስ ፈረንጅ ይስፋልኝ ከማለት ሰፍቶ የላካትን በማማረጥ ላይ ናት፡፡ የራሷን ሙያተኞችም ታከብራለች፡፡ ነገ ከዚህ የተሻለ እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም። ሸኚዬ ሐሳቤን ያነበበ ይመስል ፈገግ ብሎ ጀርባዬን ነካ ነካ አደረገኝ። አሁን ከመንደር ማካፈያ መንገዶች ወጥተን ዋናው አውራ ጎዳና ላይ ደርሰናል። እንደጊዜው ወግ ሳንነካካ ተሰነባበትን። እሱ ወደመጣንበት አቅጣጫ ወደ ለይብረሪው ሲመለስ እኔ በሐሳቤ የቀደመውን ወግ መከለስ ጀመርኩ…

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top