ታዛ ስፖርት

ድራማ በራባት

የቴአትሩ ርዕስ- የእኛ ሰው በራባት

ደራሲ-…

አዘጋጅ- ፊፋ

ተዋንያን– ጠንክር አስናቀ፣

         ክፍሉ መብራህቱ፣

         ተስፋዬ ኡርጌቾ እና ሌሎችም ….

ቦታ– ራባት ስታዴም

የመግቢያ ዋጋ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ማጣርያ ከሞሮኮ ጋር ለመጫወት ተጓዘ። የሄዱት በጣሊያን በኩል ነው። አዳራቸውን ሮም አደረጉ። በነጋታው ልምምድ ለማድረግ ሜዳ አስፈቀዱ። ትሬኒንግም ሰሩ። እራት ላይ እንገናኝ ተባባሉ።

የተወሰኑ ተጫዋቾች እዚያ ያሉትን የታክሲ ሾፌሮች አገኙ እና አነጋገሩ።

“ታክሲ ፈልገን ነው” አሉ።

“ስፖርተኞች ናችሁ አይደል?”

“አዎ… በምን አወቃችሁን?”

“ትወስዱናላችሁ?”

“የት?”

(ቦታውን ነገሯቸው)

“መታወቂያ አላችሁ?”

“መታወቂያ ምን ያደርጋል?”

“ማንነታችሁን ለማወቅ”

ተጨዋቾቹ መታወቂያቸውን አሳዩዋቸው። የታክሲ ሹፌሮቹ “በዚህ መታወቂያ እናንተ ጥገኝነት ማግኘት ብቻ ሳይሆን ገነት ትገባላችሁ” አሏቸው። ፎርጅድ ቢሆንም መታወቂያቸው በጣም የሚፈለግ ነበር። የሦስቱ መታወቂያ ላይ በሻለቃ ማእረግ በወታደር ልብስ የተነሱት ፎቶ ተለጥፏል። ጥያቄያቸውን የሚያቀርቡት “ተፈናቃይ ወታደሮች ነን” በሚል ነው።

እንዴት እንደሚኮበልሉ ተነጋገሩ። ከልምምድ በኋላ ምሳም ሳይበሉ የቡድን መሪዎቹና አሰልጣኞቹ ዞር እስኪሉ ጠበቁና 6 ተጫዋቾች ኮበለሉ። ፋሲል አድማሱ (መብራት) መለሰ አካለወልድ (አየር ኃይል)፤ ሙሃባ ሳሎ (ጊዮርጊስ)፤ ፀጋው የማነ (መብራት) መሀመድ ቢን ሸሪፍ (ጊዮርጊስ) አብርሃም ብስራት (መድን) ናቸው። ተጫዋቾቹ የጠፉት ለጨዋታ ሁለት ቀናት ሲቀረው ነው። የተጓዙት 16 ሰዎች ናቸው። 6 ሲጠፉ 10 ይቀራሉ። ወደ ሜዳ የሚገባ ቡድን ለመሆን አንድ ሰው ይጎድላቸዋል። ቡድን መሪው ወደ አዲስ አበባ ደወሉ። ውድድሩ የዓለም ዋንጫ ማጣርያ በመሆኑ ፌዴረሽኑ ለፊፋ ጉዳዩን አሳወቁ።

ለፊፋ ያቀረቡት ጥያቄ “የጨዋታው ቀን ይራዘምልኝ” የሚል ነበር። ከሞሮኮ ጋር ተስማሙ ተባለ። ሞሮኮዎች በሌላ ቀን ለመጫወት ተስማሙ። ጨዋታውን ለማድረግ ከተስማሙ በኋላ የእኛ ፌደሬሽን በአስቸኳይ ተሰበሰበ። ቡድኑ ይመለስ አይመለስ የሚል ጭቅጭቅ አስነሳ። አባላቱ መከራከር ጀመሩ። አንድ አባል ጥያቄ አስነሳ። “ቡድኑ ተመልሶ መምጣት አለበት እንዴ?” አለ።

“አዎን?”

“ድጋሚ ለመጓዝ ገንዘብ አለ?”

“የለንም።… በዚያ ላይ የአየር መንገድ እዳ አለብን።”

“ታድያ መሄድ ምንድ ነው ጥቅሙ?”

“አሁን ተስማምተናል። ካልሄድን እንቀጣለን”

“ድጋሚ ለመሄድ እኮ ገንዘብ የለንም”

“ስለዚህ ምን ይደረግ?”

“ይጫወቱ”

“አልተሟሉም”

“በዕዳ ከመዘፈቅ ጉዳዩን እዚያው እንጨርስ”

“ይሄ ሀሳብ ጥሩ ነው። በዚሁ ብንስማማ ይሻላል”

“ፌዴሬሽኑ ለቡድን መሪው ደውለው “እንዳትመለሱ እዚያው ጨርሱ” አሏቸው። ሞሮኮ የገቡት 10 ተጫዋቾች ናቸው። አሰልጣኞቹ ካሳሁን ተካ እና ጌታሁን ገ/ጊዮርጊስ ናቸው። ወደ ሜዳ ለመግባት 11 መሆን አለባቸው። አሰልጣኞቹ በካፍ የተመዘገቡ ስለሆኑ እኛ መጫወት አንችልም ብለው አሰቡ።

አንዱን ክፍተት ቡድን መሪው እንዲሞላ ታዘዘ። እሱ ተጠየቀ። ነገር ግን ቦርጩ ገፋ ስላለ እና የሰውነቱ ሁኔታ ተጫዋች ስለማያስመስለው እሱም ፈቃደኛ ባለመሆኑ ለመጫወት ሳይችል ቀረ። በመጨረሻም ታኬታ ስለሌለኝ እንጂ በክንፍ በኩል እሮጥ ነበር (መጫወት ሳይሆን) አለ።

የጠፉት ተጫዋቾች አብዛኞቹ ተከላካይ ነበሩ። ራባት የደረሰው አጥቂውና አማካዩ ነበር። ለጊዜው ያለው የሜዳ ተጫዋች 9 ብቻ ነው። ሁለቱ በረኞች ናቸው። በረኞቹ ደሳለኝና ይልማ ከበደ (ጃሬ) ነበሩ። በረኛ መሆን የፈለገ የለም። ምክንያቱም ብዙ ጎል መቆጠሩ አይቀርም። በእከሌ ላይ ነው የገባው እንዳይባሉ በታሪክም ተጠያቂ እንዳይሆኑ ሁለቱም መግባት አልፈለጉም። ሞሮኮዎች በአየር ላይ ስለሚጫወቱ “እኔ ቁመት ስላለኝ በቴስታ እመታለሁ፣ በሸርተቴም ኳስ አስጥላለሁ” በሚል ደሳለኝ ተከላካይ እሆናለሁ ብሎ እራሱን እዚያ ቦታ ላይ መደበ። ጃሬም በረኛ ገባ። በአጥቂ ቦታ የሄዱት ጠንክር እና ተስፋዬ ኡርጌቾ በ‘ሊብሮ’ና በተመላላሽ ቦታ ተሰለፉ። አማካዩ ኤርሚያስ ግራ ‘ስቶፐር’ ሆነ። አንዱን ክፍት ቦታ ከአሰልጣኞቹ አንዱ ይተካ ተባለ። ጌታሁን ቀደም ሲል ለ“አባት ገበሬ” ቡድን ተጫውቷል። ካሳሁን ደግሞ ለብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ ነበር። ሁለቱም ኳስ ቀመስ ናቸው።

እኔ ልግባ… እኔ ልግባ ሳይሆን “አንተ መግባት አለብህ” በሚል መከራከር ያዙ። ሁለቱም ቦርጭ ስላላቸው ቦርጫቸውም ከኳስ ተለቅ ያለ በመሆኑ ዘጥ ዘጥ ለማለት ካልሆነ በስተቀር ለመጫወት ብቁ አልነበሩም። ዋናው አሰልጣኝ ካሳሁን ስለሆነ ምክትሉን ገብተህ ተጫወት ብሎ ማዘዝ ጀመረ። ተጨዋቾቹ ግን ካሳሁን ጠንካራ ምት ስላለው መሯሯጥ እንኳ ባይችል ቅጣት ምት ላይ ያግዘናል በሚል እሱ እንዲገባ ተደረገ።

ለመግባት ግን ኮሚሽነሩን ማስፈቀድ ነበረበት። ኮሚሽነሩም ተስማማ። የሞሮኮው አምበልም ካሳሁን ለመጫወት ተገቢ እንዳልሆነ ቢያውቅም ጨዋታው ከዚህ የተነሳ እንዳይቋረጥ በሚል ተስማማ። የሞሮኮ ተጫዋቾችም ቢሆኑ የኛ ወጌሻ እና ቡድን መሪውም ተጨምረው ቢገቡና ቁጥሩ ከፍ ቢልም ቅር እንደማይላቸው ነው። ፎርፌ እንዳይሆን ብቻ ነው የፈለጉት።

መልበሻ ክፍል የነበረው የጫወታ ስትራቴጂ ስለ ማጥቃት ስለ መከላከል አልነበረም። ስለ ፎርሜሽንና ሌላ ነገር ሳይሆን “ጨዋታውን ቶሎ እንጨርሰው” የሚል ነው።

መልበሻ ክፍል የነበረው ስትራቴጂ “…15 ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንደተጎዳችሁ ትሆኑና መልበሻ ክፍል በቃሬዛ ትገባላችሁ” በሚል ትዕዛዝ ተሰጠ። ወጌሻው ወደ ሜዳው ገብቶ ተጫዋቹን ማከም የለበትም። ልጁን በቃሬዛ ይጭነውና መልበሻ ክፍል ያደርሰዋል። 5 ሰው ሲወጣ ሜዳ ላይ 6 ሰው ይቀራል።

በሕጉ መሰረት ከ7 በታች ከሆኑ መጫወት ስለማይቻል ፎርፌ ይሆናል። የኛም ሰዎች የሚፈልጉት ይሄንኑ ነው። ጉዳዩን ለማሳካት በቃሬዛ የሚወጡትን መመደብና ቅደም ተከተላቸውን ለወጪዎቹ ማሳወቅ ነው። አንደኛ፣ ሁለተኛ፣ ሦስተኛ ወጪዎች እየተባለ ተደልድለዋል። አንደኛ ወጪ ክፍሉ መብራህቱ (የዳዊት መብራህቱ ወንድም) ነው። ጨዋታው እየተካሄደ ነገሩ ተነሳ።

አንደኛው ወጪ ጥሞታል። ስለዚህ እየተጫወተ ነው። ክፍሉ ነገሩ የመሰለው የመጀመርያው ወጪ እንዲሆን ነው። ግን ካሳሁን ከወጣ በኋላ ነው እሱ እንደ አንደኛ የሚቆጠረው። ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ግልፅ መመሪያ ስላልተሰጠ አንደኛ ተሰናባች የተባለው ቶሎ ሳይወጣ ቀረ።

በዚህ መሃል ተስፋዬ ኡርጌቾ ተመትቶ ወደቀ። ወጌሻ የተነገራቸው ሰው እንደተመታ ባለቃሬዛቹን በቃሬዛ ልጁን አንከብክበው ወደ መልበሻ ክፍል መግባት ነው። ወጌሻው ተስፋዬ ጋር ደረሱ። ተስፋዬ ለማስመሰል ሳይሆን የምር ነው የተመታው።

ተስፋዬ “እግሬን ነው የመቱኝ ውሃ አፍስሱልኝ” አለ።

“ውሃ የለም ቃሬዛ ላይ ውጣ”

“እባክህ አክመኝ”

“መመሪያ ጥሰሀል”

“እኔኮ አንደኛ ወጪ አይደለሁም”

“እባክህ ታስቆጣኛለህ ቃሬዛ ላይ ውጣ” ችገር የለም።

ተስፋዬ እና ወጌሻው አልተግባቡም። (በነገራችን ላይ ተስፋዬ ኡርጌቸ በቅርቡ ግንቦት 5፣ 2012 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል) ወጌሻውም ተስፋዬም ልክ ናቸው። እሳቸው የፈለጉት የወደቀውን ሰው በቃሬዛ ይዞ መሄድ ነው። ተስፋዬ ደግሞ አራተኛ ወጪ ነህ ተብሏል። ድልድሉ ላይ አማካይና አጥቂዎች በቅድሚያ ይወጣሉ። ተከላካዮች መጨረሻ ቃሬዛ ላይ ይፈናጠጣሉ ነው የተባባሉት። ተስፋዬ ማሞ ተከላካይ ነው። ድራማው እዚህ ላይ አልሰራም። ተስፋዬም ሳይወጣ ቀረ።

በቃሬዛ የመውጣት አፈፃፀም ላይ በፍጥነት እርምጃ ባለመወሰዱ ሞሮኮዎች ቶሎ ቶሎ ጎል እያገቡ ነው። አሰልጣኞቹ የመውጣት ስትራቴጂ የቀየሱት ተጫዋች ስለሌለን በዚህ አጋጣሚ ብዙ ጎል ተቆጥሮብን አሳፋሪ ሪኮርድ እንዳይመዘገብብን በሚል ነው። ስለዚህ የቀየሱት ዘዴ ወደ ሜዳ ገብተው ጎሉ እንዳይበዛ እንደታመመ ሰው በቃሬዛ መውጣት ነው።

ካሳሁን ከሜዳ ወጣ። አሁን የክፍሉ ተራ ነው። ክፍሉ በቃሬዛ ወጣ። ወጪዎቹ ቶሎ ቶሎ መፍጠን አለባቸው። 15 ደቂቃ ሳይሞላ ማጠናቀቅ ይጠበቅባቸዋል። ሦስተኛው ወጪ የጊዮርጊሱ ማቲያስ  ኃብተማርያም ነበር። ማትያስ ኳስ በጣም ይወዳል። በዚያ ላይ ጎበዝ ነው። አብዶ አሠራሩ ለየት ያለ ነው። ማቲያስ ተጠልፎ ወደቀ። የእሱ ተራ ነበር እና ተጫዋቾቹ ከበው “እንዳትነሳ” አሉት…

“እኔ እኮ ማስመሰል አልችልበትም፤ ኳስ ደግሞ መጫወት እወዳለሁ። ስለዚህ አልወጣም። በኔ ቦታ ሌላ ሰው ይውጣ” አለ።

ተጫዋቾቹም እዚያው አጠር ፈጠን ያለ ስብሰባ አደረጉ። ማቲያስን ተክቶ የሚወጣ ሰው ማን ይሁን? ተባለ። መጀመርያ ድልድሉን ያወጣው ካሳሁን ነው። ካሳሁን ደግሞ በታመመ ተጨዋች ስም መልበሻ ክፍል ለመግባት ኮሚሽነሩን ማስፈቀድ ነበረበት። ኮሚሽነሩም ተስማማ። የሞሮኮ አምበልም ካሳሁን ለመጫወት ተገቢ እንዳልሆነ ቢያውቅም ጨዋታው በዚህ የተነሳ እንዳይቋረጥ በሚል ተስማማ። የሞሮኮ ተጫዋቾችም ቢሆኑ የኛ ወጌሻ እና ቡድን መሪውም ተጨምረው ቢገቡና ቁጥሩ ከፍ ቢል ቅር እንደማይላቸው ነው። ፎርፌ እንዳይሆን ብቻ ነው የሚፈልጉት።

መጀመርያ ድልድሉን ያወጣው ካሳሁን ነው። ካሳሁን ደግሞ ታሟል በሚል መልበሻ ክፍል ተደብቋል። ሽግሽግ ተደረጋና ኤርሚያስ ወጣ። የሞሮኮ ቃሬዛ ተሸካሚዎች ተጫዋቾቹ ሆን ብለው እየወጡ እንደሆነ ስላወቁ ሲጠሩ አንመጣም አሉ። የኛ ልጆች እራሳቸው ቃሬዛ አምጥተው ጓደኞቻቸውን እናደርሳለን አሉ። ቃሬዛ አንሺዎቹ የማይቀር መሆኑን አወቁና ትብብር አደረጉ።

ሦስተኛ ሰው ሲወጣ የሞሮኮ ደጋፊ ድራማ እየተሰራ መሆኑን አውቆ መጮኽ ጀመረ። ሞሮኮ 5 ጎል አግብቷል። ይሄ ጨዋታ ከተቋረጠ ፎርፌ ይሆናል በሚል ተጫዋቾቹ ከግማሽ በታች እንዳይሆኑ በጥንቃቄ የቀሩትን ይዘው ለመጨረስ ፈለጉ።

የኛ ተጫዋቾች ደግሞ ከ6 በታች ከሆነ ጨዋታው ስለሚቋረጥ በፎርፌ ይጠናቀቃል በሚል 5 ሰው ከሜዳ ለማስወጣት ነው ጥረት የሚያደርጉት። 4ኛው ተጫዋች ሲወጣ የሞሮኮ ተጫዋቾች ደነገጡ። አሁን ጨዋታው ሊቋረጥ አንድ ተጫዋች መውጣት በቻ ነው የሚቀረው።

ሞሮኮዎች አንድ ዘዴ ቀየሱ። ተጨዋቾች የሚወድቁት ሆን ብለው ስለሆነ አንንካቸው አሉ። “ብልጥ ልጅ እየበላ ያለቅሳል” እንደሚባለው ጨዋታው ከሚቋረጥ አምስቱን ጎል ይዘው የቀረውን ደቂቃ ለመጨረስ ፈለጉ። ኳስ ወደ ውጭ ወጣች። የኢትዮጵያ ተጫዋቾች ኳሱን ጀመሩት።

ግን የሞሮኮ ተጫዋቾች ለመንጠቅ አልመጡም። የኢትዮጵያ ተጨዋቾችም የሚነጥቃቸው ስላልመጣ እዚያው ጎላቸው አከባቢ መቀባበል ጀመሩ። ሞሮኮዎች እነሱ ፔናሊቲ ክልል ውስጥ የኛም ተጨዋቾች እራሳቸው ፔናሊቲ ክልል ውስጥ ሆነው ማዶ ለማዶ መተያየት ጀመሩ።

በሁለቱ መሃል የ60 ሜትር ያህል ርቀት አለ። ዳኛው መሃል ሜዳ ላይ ቆመ። ለእሱም ግራ የሚያጋባ ነው። ነጣቂም ተነጣቂም። አጥቂም ተጠቂም የለም። በራባት ከተማ ኳስ ሳይሆን ድራማ እየታየ ነው።

ሁለቱም የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው። የኛ ተጫዋቾች ጎል እንዳይበዛባቸው ፈልገዋል። ሞሮኮዎች የኛን ተጫዋቾች ከተጠጉ ይወድቁና በቃሬዛ ይወጣሉ። የቀረው አንድ ተጫዋች በመሆኑ “አንድ ዐይን ያለው በአፈር አይጫወትም” እንደሚባለው ኳስ የያዘውን ላለመንካት ክልላቸው ውስጥ ቆመዋል። ዳኛው ደግሞ ነገሩ ገብቶታል ግን ምን ያድርግ? ሞሮኮዎች ስለቀሩ ኳሱን የያዘው ጠንክር “ለምን መሃል በገባ አንጫወትም?” በሚል ለልጆቹ ጥያቄ አቀረበ።

ሞሮኮ ይሄ ጨዋታ ከተቋረጠ ፎርፌ ስለሚሆን ሁለት ጎል ነው የሚያገኘው ብለው በማሰብ አምስቱ ጎል እንዳይመዘገብለት በሚል ተጨዋቾቹ ተነጋገሩ። ሞሮኮዎች ወደ እኛ የማይመጡት ሰዓቱ በዚሁ እንዲያልቅ ነው። ስለዚህ ወደ እነሱ ጎል እንሂድ አሉ። የመጨረሻው ወጪ ጠንክር ስለሆነ ኳስ ለጠንክር ተሰጠው።

ጠንክር በኮምበይ (በአጃቢ) መሄድ ጀመረ። መሪው እና ሙሽራው ጠንክር ነው። ሌሎቹ ሚዜ እና አጃቢ ሆነዋል። ልጆቹ ጠንክርን እንደ ሹፌር ዐዩትና “ንዳ” አሉት። እነሱ ከኋላ ናቸው። “እርገጥ በለው ሹፌሩን” እያሉ ጠንክርን እየተከተሉት ነው። ዓላማው ጠንክርን ኳሱን ሊቀማው ከሚመጣው የሞሮኮ ተጨዋች ጋር ተጋጭቶ መውደቅ ነው። ስለዚህ የሚነጥቀው ሰው ይፈልጋል። የሞሮኮ ተጫዋቾች ደግሞ የጠንክርና አጃቢዎቹ አመጣጥ ስለገባቸው ኳስ የያዘውን ተጫዋች መሸሽ ጀመሩ።

ጠንክር ፔናሊቲ ቦክሱ ጋር ደረሰና ይነጥቀኛል ወዳለው ተጫዋች እየገፋ ሄደ። ልጁ ግን ጠንክርን ሸሸና ወደ ኮርናው ጋር ሄደ። ተከላካይ ቦታ የሚጫወተው ልጅ ቦታውን ስለለቀቀለት ጠንክር ወደ ጎል ሄዶ ማግባት ይችላል። ነገር ግን ጠንክር ጎል አይደለም የፈለገው። ልጁን መጋጨት ነው። ልጁ ደግሞ ሸሽቷል።

ጠንክርም ኳስዋን እየገፋ ይከተለዋል ነገሩ “ስትሄድ ስከተላት” ዓይነት ሆነ። ልጁ ከኮርናው ጋር ተመልሶ መጣ። ጠንክርም ተከተለው። ግን ኢላማ ውስጥ ሊገባለት ስላልቻለ ሌላ ሰው መፈለግ ጀመረ። ጉዳዩ ከጨዋታ ወጣ እና በትክክል የድራማ ቅርፅ ያዘ። ይሄ ጉዳይ ኳስ ሜዳ ላይ ሳይሆን የቴአትር አዳራሽ ውስጥ መሰራት የሚችል ነው። የራባቱ ድራማ እንደቀጠለ ነው።

የኛ ተጫዋቾች ከጠንክር ኳስ መቀበል አልፈለጉም። ይሄ የድራማው መጠናቀቂያ ስለሆነ የቴአትሩም አክተር ጠንክር በመሆኑ፤ ቴአትሩም የሚያበቃው በጠንክር አስናቀ ስለሆነ ልጆቹ እሱን ማገዝ ነው ያለባቸው። ጠንክር ኳስ ይዞ ይጋጫል ብሎ ያሰበው ልጅ ሊያገኘው አልቻለም። ሌሎች የእኛ ተጫዋቾች እዚህኛው ጋር ሄደህ ተጋጭ …እዚያኛው ጋር ሂድ… ይሄኛው ይሻልሃል” እያሉ መንገድ ይመሩታል፤ ያስመርጡታል።

ጠንክር ሌላ ሰው ፈለገ እና ወደ እሱ ሲሄድ ኳሱ ረዘመበት። ኳሱን ማትያስ አገኘው። ማትያስ ደግሞ የድራማው አባል አይደለም። “እኔ አልወጣም በማለቱ የቴአትሩ ገፅታ አበላሽቷል። ማቲያስ ኳሱን እንዳገኘ ሊጫወት እንደፈለገ ስላወቁበት የእኛ ተጫዋቾች ከማቲያስ ነጥቀው ለጠንክር ሰጡት እና ድራማው እንዲቀጥል አደረጉት።

ጠንክርም ኳሱን ያዘ። ቶሎ በፍጥነት እንደደነበረ በሬ ወደ ተሰበሰቡት ተጫዋቾች እያተራመሰ ገባ። እነሱም ሸሹት። ነገር ግን አጠገባቸው እንደደረሰ ኳሱን ረግጦ አንደኛውን ተጫዋች ተደግፎ ወደቀና “ኡ! ኡ! ያገር ያለህ! አንገቴን!”… ወገቤን!!… ጉልበቴን!!… ሆዴን!!… ጀርባዬን!!!…

ያልተመታሁበት ቦታ የለም አለ። ተንፈራፈረ። አጃቢዎቹም ጠንክርን ከበቡት “ወይኔ ወንድሜ!!” እያሉ መጮኽ ጀመሩ። ዳኛውን ጠሩት። “ገደሉት እኮ አይታይህም እንዴ?” አሉት። ዳኛውም አዘነ ግን ሳቁን መቆጣጠር አልቻለም። “እነዚህ ኢትዮጵያውያን ለካ ድራማም ይችላሉ” በሚል እራሱን ነቀነቀ። የሚቀጥለው ነገር ምን እንደሆነ አልጠፋውም።

ጠንክር ወደቀ። ደሳለኝ የጠንክርን አንገት ቀና ሲያደርግ ይስቃል። ሌሎቹ ጠንክርን ተቆጡት። ሳቅ የድራማው አካል አይደለም። የእኛ ተጫዋቾች ጠንክርን ቃሬዛ ላይ እንዲወጣ አመቻቹት።

የሞሮኮ ተጫዋቾች ግን ጠንክር ከሜዳ አይወጣም ብለው ሙግት ያዙ። “እንወስደዋለን! አትወስዱትም!” በሚል ግብግብ ተፈጠረ። ጨዋታው የሚቋረጠው ደግሞ ጠንክር ከሜዳ ሲወጣ ነው። አረብኛ እና ፈረንሳይኛ እንችላለን የሚሉ የእኛ ተጫዋቾች ቋንቋውን በእጁም በእግሩም እያስኬዱት ድርድር ጀመሩ።

ሞሮኮዎች ከእንግዲህ ጎል አናገባም በዚሁ እንጨርስ ብለው ተማፀኑ። የእኛ ልጆች ደግሞ ኳስ ጨዋታው ሳይሆን ቴአትሩ ተጠናቋል ነው የሚሉት። ሞሮኮዎች ጠንክርን ከተኛበት አንከብክበው አነሱት። በእግሩ አቆሙት። ግን ጠንክር ተዝለፍልፎ ወደቀ። አክተሩ ከሌለ ፊልሙ ቦታ የለውም። ከብዙ ሙግት እና ድርድር በኋላ ጠንክር በቃሬዛ ወጣ። ቴአትሩም ተጠናቀቀ።

1 Comment

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top