ቀዳሚ ቃል

ቀዳሚ ቃል

የዓለም ስጋት የሆነው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ያልነካው ዘርፍ የለም። ከማኅበራዊ እስከ ኤኮኖሚያዊ፣ ከፖለቲካዊ እስከ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን ቀድሞ ከተጠበቀው አካሄድ ውጪ፣ ከተለመደው ባፈነገጠ መንገድ እንዲጓዙ አስገድዷል።
ዓለማዊ እና መንፈሳዊ፣ ሸማች እና ነጋዴ፣ አምራች እና አከፋፋይ፣ አገልግሎት ሰጭ እና ተቀባይ፣ ገዢ እና ተቃዋሚ ሳይል ሁሉም ላይ ተጽእኖውን አሳርፏል።
ይህንን በትር ከቀመሱት ውስጥ የኪነ-ጥበብ ዘርፉ በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ለታዳሚው በሕትመት ከሚደርሱት፣ በግንባር መታደም ከማይጠይቁት መጻሕፍት በስተቀር አብዛኛው የጥበብ ሥራ ታዳሚያኑ በአካል መገኘታቸውን ይፈልጋል።
የሙዚቃ ዝግጅቶች በተናጠል አይዘጋጁም። መሳሪያ ተጨዋቾች፣ ድምጻውያን፣ ተወዛዋዦች፣… እያለ በርከት ያለ ቁጥር በአላቸው ሰዎች የሚመደረኩ ናቸው። ቴአትርም ቢሆን ከጥናት እስከ አቅርቦት የሰዎችን መሰብሰብ ይጠይቃል። አንድ አርቲስት ብቻውን ስቱዲዮ ከትሞ ያዘጋጃቸው የስዕል ጥበብ ሥራዎች እንኳን ሳይቀሩ ዕይታቸው ያለ ሰዎች ግርግር አይሆንም። ሰብሰብ ብሎ መመልከትን ግድ ይላሉ፡፡ ጥግግት በሕግ በታገደበት በዚህ ዘመን፣ ከቤት መውጣት በማይበረታታበት በአሁን ሰዓት፣ የሥራ ጠባያቸው የሰዎችን መሰብሰብ የሚያስገድደው የክዋኔ ጥበባት ተጎድተዋል። ጉዳታቸው ለመድረክ አለመብቃታቸው፣ ከህዝብ ዐይን እና ጆሮ
መራቃቸው ብቻ አይደለም። ስጋ እና ደሙን ሰጥቶ ነፍስ የሚዘራባቸውን የክዋኔ ባለሙያ (አርቲስት) የመኖር ህልውና ጥያቄ ውስጥ ማስገባታቸውም ጭምር ነው። አብዛኛው ከሚባለው ቁጥር ከፍ የሚለው የኪነጥበብ ባለሙያ ኑሮውን የመሰረተው ከዕለታዊ የመድረክ ክፍያዎች ከሚያገኝው ገቢ ነው። አነስተኛ ደሞዝ ያላቸው የቴአትር ቤት ተቀጣሪዎችም ከመድረክ ክፍያ፣ ከክለብ እና ከማስታወቂያ ሥራዎች በሚያገኙት ቋሚ ያልሆነ ድንገቴ ገቢ ኑሯቸውን መደጎም ካልቻሉ ህይወት ይከብዳቸዋል። ይህ ሁኔታ ዓለማችን ከምትገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር በሁሉም ዘርፍ ላይ ያለ ችግር መሆኑ ይታወቃል። ይሁን እንጂ፤ ለሌሎች ዘርፎች የተሰጠውን ትኩረት መመልከት ይቻላል። ከታክስ እፎይታ እስከ ኪራይ ቅናሽ፣ ከብድር ድጋፍ እስከ የእዳ ክፍያ እፎይታ፣.. በመንግሥት ድጋፍ በመደረግ ላይ ነው። የኪነጥበብ ባለሙያዎችን በተመለከተ ግን ምንም ዐይነት እርምጃ አልተወሰደም። የጥበብ ክዋኔ ባለሙያዎቹ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል በሚደረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ
ላይ እንዲገኙ ከሁሉ በፊት ግብዣ ቢደረግላቸውም፣ ተሰሚነታቸውን ተጠቅመው ማኅበረሰቡን እንዲያነቁ በሚል ቀዳሚ ተፈላጊ ቢሆኑም፣ የኪነጥበብ ዘርፉ መታገዝ እንደሚገባው ግን ተዘንግቷል። ሆቴሎች እና የምሽት ክለቦች ስርጭቱን ለመግታት እንዲቻል ሥራ ሲያቆሙ (ሲቀንሱ) የሙያተኞቹ መውደቂያ አልታሰበም። ገቢያቸው መቋረጡ እየታወቀ ለሙያዊ አገልግሎታቸው ክፍያ በመጠየቃቸው ምክንያት ትችት እና ተቃውሞ የገጠማቸው በርካታ ናቸው፡፡ መፍትሔዎች ሁሉ ከመንግሥት ብቻ ይመነጫሉ የሚል ሐሳብ ባይኖርም፤ ቢያንስ መመሪያዎችን እና የድጋፍ ፕሮጅክቶችን በመንደፍ ችግር ላይ የሚገኙ ባለሙያዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን ከውድቀት መታደጊያ መላ ሊያበጅ ይገባል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top