ፍልስፍና

የድህረ-ዘመናዊነት ንጽረተ ዓለም ፍልስፍና እየበጀን ወይስ እየፈጀን?

“ከዉስጥ ሲያስተጋባ የወንጀሉ ትዕዛዝ ሥርዓትና ወጉ

አሜን ብቻ ሆኗል የመሃይም (ን) ወጉ”

(ጸገየ ወይን ገብረ መድህን) (ናስተማስለኪ)

ፃናት ጥያቄ የሚጠይቁበትን መንገድ አስተውላችሁ ታውቃላችሁ? ብዙዎቹ ጥያቄ መጠየቅ የሚጀምሩት ገና አፋቸውን እንደፈቱ ነው፡፡ ለማወቅ ካላቸው እጅግ በጣም ከፍተኛ ጉጉት የተነሳ ዓይን ዓይናችንን እያዩ ’ሰማዩ መጨረሻው የት ጋር ነው? ኮከቦች የሚያበሩት ለምንድን ነው? ወፎች መብረር የቻሉት እንዴት ነው?’ እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎችን ይጠይቁናል፡፡ መልስ ለመስጠት የተቻለንን ያህል ጥረት እናደርግ ይሆናል፤ ሆኖም ይህን ማድረጉ ሁል ጊዜ ቀላል አይሆንም፡፡ የተሻለ ነው ብለን የምናስበው መልስ እንኳ ’ለምን?’ የሚል ሌላ ጥያቄ ሊያስከትልብን ይችላል፡፡

ይሁንና ጥያቄ የሚያነሱት ሕፃናት ብቻ አይደሉም፡፡ ካደግንም በኋላ የተለያዩ ጥያቄዎች እናነሳለን፡፡ የምንሄድበትን አግጣጫን ለማወቅ፣ ልንርቃቸው የሚገቡ አደገኛ ሁኔታዎችን ለመለየት ወይም ደግሞ የማወቅ ፍላጎችንን ለማርካት ስንል እንጠይቃለን፡፡ ሆኖም ብዙዎቻችን ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ጥያቄዎችን መጠየቅ የተውን ይመስላል፡፡ አልያም ደግሞ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ጥረት ስናደርግ አንታይም፡፡

ይሁን እንጂ በሕይወታችን ለሚነሱ እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት እንደምንፈልግ እሙን ነው፡፡ እኔ ማን ነኝ? ከየት መጣሁ? እንዴት ተገኘሁ? የመኖር አላማዬ ምንድን ነው? ለመኖር ነው የምበላው ወይስ ለመብላት ነው የምኖረው? የሕይወት ዓላማው ምንድን ነው? መወለድ፣ ማደግ፣ ማርጀትና መሞት ብቻ ነው? እውነት ምንድን ነው? ደስታ ምንድን ነው? አስደሳች ሕይወት ሊኖረኝ የሚችለው እንዴት ነው? ከጋብቻ በፊትም ሆነ ከጋብቻ በኋላ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ወሲብ መፈጸም እውነተኛ ደስታ ያስገኛል ወይ? ብዙ ሰዎች የአንድ ሰው ደስታና ስኬት የሚለካው በሀብቱ ወይም በንብረቱ ብዛት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይህ ምን ያህል እውነትና ትክክል ነው? እውነት ከየት ይገኛል? ሞት ምንድን ነው? ሥልጣኔ ምንድን ነው? መሰልጠን እንደ ምዕራባውያን መሆን ነው? ከሞት በኋላ ዘላለማዊ ሕይወት አለ የሚባለው ምን ያህል የተረጋገጠ እውነት ነው? ገነት እና ሲዖል፤ መንግሥተ ሰማያት እና ገሃነመ እሳት ስለመኖራቸው እውነተኛ እና ትክክለኛ ማረጋገጫችን ምንድን ነው? አምላክ ምን ዓይነት አምላክ ነው? የፈጣሪ አምላክ እውነተኛ እና ትክክለኛ ስሙ የትኛው ነው? ያህዌ ነው? ይሖዋ ነው? እግዚአብሔር ነው? አላህ ነው? በዓለም ላይ ካሉ ሃይማኖቶች ሁሉ እውነተኛው እና ትክክለኛው መለኮታዊ ሃይማኖት የትኛው ነው? እውነተኛው እና ትክክለኛው መለኮታዊ መጽሐፍ የትኛው ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ነው?  ቅዱስ ቁራን ነው?  አምላክ የሚያስብልን ቢሆንማ ኖሮ ዓለማችን አሁን ባለችበት በጦርነት፣በሽብር ፣በጥላቻ፣ በረሃብ፣ በበሽታ፣ በወረርሽኝ ወዘተ ባልተሞላች ነበር? መከራ የማይኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? እያልን ማሰባችን አይቀርም፡፡ እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን ማንሳት  እጅግ በጣም ተገቢ ከመሆኑም በላይ ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢና አስተማማኝ መልስ እስክናገኝ ድረስ መጠየቃችንን ፈጽሞ ማቆም የለብንም፡፡ ሆኖም ግን ያገኘነው ወይንም የደረስንበት መልስ በድህረ-ዘመናዊነት ንጽረተ ዓለም (Post modernism world view) አስተምህሮት የተቀመረ ከሆነ  ፍጹም እውነተኛ እና ትክክለኛ አይደለም፡፡ እዚህ ጋር ’ድህረ-ዘመናዊነት’ ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል ድህረ-ዘመናዊነት ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ ከመመለሴ በፊት ስለዘመናዊነት (Modernism) እንመለከታለን፡፡

ዘመናዊነት በአውሮዻ ከኢንደስትሪ አብዮት መፈንዳት ጋር በታየው ሥልጣኔ ሳቢያ በጊዜው የነበረው አመለካከት እና እምነት ማለትም ’የቪክቶሪያን ዘመን’ በመቃወም በህብረተሰብ፤ በሳይንስ እና በቴክኖሎጂ፤ በባህል፤ በኪነ-ጥበብ፤ በሥነ-ጥበብ፤ ወዘተ፡፡ በሰው የኑሮ መስክ ሁሉ ለውጥን ለማምጣት የጀመረ እንቅስቃሴ ነበር፡፡ ዓለማችን ዛሬ ለደረሰችበት ከፍተኛ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሥልጣኔ ከ1760-1840 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት ውስጥ በእንግሊዝ ከፈነዳው የኢንደስትሪው አብዮት ዘመን በፊት የሰው ልጆች በስፋት በግብርና ሥራ የተሰማሩና በአብዛኛው የገጠራማ ዘይቤ የነበራቸው ሲሆን፣ በመጠኑም ቢሆን የቁሳቁስ ምርት ይከናወን የነበረው በባለሙያ ግለሰቦች ቤት ውስጥ በእጅ እና አነስተኛ በሆኑ የማምረቻ ቁሶች በመታገዝ ነበር፡፡ ይህ ዘመን ሰዎችን ከአነስተኛ የእጅ ምርት አውጥተው የገፍ ምርትን (Mass production) እውን የሚያደርጉ ማሽኖችን እና ፋብሪካዎችን ይዞ ብቅ አለ፡፡ በዚሁ ዘመን ከተፈለሰፉ እና ለትላልቅ ፋብሪካዎች መወለድ ምክንያት ከሆኑ አዳዲስ ፈር ቀዳጅ የፈጠራ ስራዎች መካከል፤ በእንፋሎት ኃይል የሚሰሩ ሞተሮች፤ እንዲሁም በውኃ ኃይል የሚሰሩ የማግ ማጠንጠኛዎችና ዘመናዊ የልብስ መሸመኛዎች ጥቂቶቹ ሲሆኑ፣ የኢንደስትሪው መስፋፋት ከተሜነትንም (Urbanization) ይዞ በመምጣት የሰው ልጆችን የአኗኗር ዘይቤ በዘመናዊ መልኩ መለወጥ ችሎ ነበር፡፡ ዓለም በኢንደስትሪ እንድታድግና እንድትበለጽግ ከተፈለገ ሃይማኖትን በተለይም የክርስት እና እምነትን እና ነባር ባህላዊ አስተሳሰቦችን ሁሉ በዘመናዊ አመለካከት ጨርሶ ለመተካት ትኩረቱ አድጓል፡፡

በፍልስፍናው መስመር በ17ኛው እና በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአውሮዻ የጀመረው ዘመነ አብርሆት (Era of Enlightenment) (የነበረው የሳይንስን እውቀት፣ የገብረገብን እና የፍትህን ሐሳቦች በማሰራጨት የኀብረተሰብን ድክመቶች ለማረም የአስተሳሰብን፣ የኑሮ ዘዴን፣ የፖለቲካ አመለካከትን ለመቀየር ይቻላል የሚል ማኀበራዊ ፖለቲካዊ አመለካከት ነው፡፡ የአብርሆት መሠረታዊ እምነት በኀብረተሰብ ዕድገት ውስጥ ኀሊና ወሳኝ ሚና ሊጫወት ይችላል የሚል ሐሳባዊ አመለካከት በመሆኑ ማኀበራዊ ችግሮች ከሰዎች ድንቁርና እና ከዕውቀት ማነስ እንደሚመነጩ አድርጎ የሚሞግት ነው፡፡ አብራህያን ችግሮችን ሊያስወግድ የሚችል ትምህርት ብቻ ነው የሚል አመለካከት ነበራቸው፡፡ ፍልስፍናው የተስፋፋው በኢንደስትሪ አብዮት ፍንዳታ አጥቢያ ሲሆን ቮልቴር፣ ሩሶ፣ ሞንተስኪዬ፣ ሄርደር፣ ቪለር፣ ጎቴ ወዘተ… የታወቁ የፍልስፍናው አራማጆች ነበሩ፡፡ አብራህያን የፊውዳልን ርዕዮት ዓለም ያዳከሙ በመሆናቸው በቀጥታ ቤተክርስቲያንን ሃይማኖታዊ ቀኖናዎችን ተምህሮኣዊ (ተምህሮ ማለት በቃል፣ በጽሁፍ ማጥናት፣ መቀጸል ማለት ነው፡፡) አስተሳሰቦችን ተዋግተዋል፡፡) ወደ ዘመናዊነት ተለወጠ፡፡ እውነት የሚገኘው በሳይንሳዊ ምርምር እና በፍልስፍና ምክኑያዊነት (Philosophical reason) ነው ብሎ አሰበ፡፡ ሁሉም ነገር በሳይንስ እና በሒሳብ ስሌት የሚለካ፤ የሚዳሰስ፤ መሆን ስላለበት እውቀት ወይም እውነት የሚገኘው በሒሳብ ስሌት (Matimatical calculation) ነው የሚል ነው፡፡

በዚህ ዘመን በሥነ ሕይወት (Biology) እና በሥነ መንግሥት አስተዳደር (Political science) ዘርፎች አስተሳሰቡን ይመሩ እንደነበር የሚታሰቡት እንግሊዛዊው ቻርልስ ዳርዊን እና ጀርመናዊው ካርል ማርክስ ነበሩ፡፡ ሰው ከአነስተኛ እንስሳ በተፈጥሮ መረጣ (Natural selection) ተገኘ የሚለው የዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ኃልዮት እና የካፒታሊስቱ ሥርዓት የውስጥ ተቃርኖዎች ስላሉበት ሠራተኛው ከከበርቴው አገዛዝ ነፃ መውጣት አለበት የሚለው የማርክስ ዲያሌክቲካዊ ቁስ አካልነት (የማርክሲዝም ፍልስፍና መሠረትና ሳይንሳዊ ንጽረተ ዓለም ነው፡፡ ዲያሌክቲካዊ ቁስ አካልነት በማርክስና በኤንግልስ ከተመሠረተ በኋላ በሌኒንና በሌሎች ማርክሳውያን ሊዳብር ችሎአል፡፡ ዲያሌክቲካዊ ቁስአካልነት የተከሰተው በ1840ዎቹ ሲሆን አመሰራረቱ ከሳይንሳዊ ዕውቀትና ከሠራተኛው መደብ አብዮታዊ ንቅናቄ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡) ርዕዮተ ዓለም ይጠቀሳሉ፡፡

ዘመናዊነት ዓለም ሥርዓት አላት፤ ተጨባጭ የሆኑ እውነቶች ስላሉባት ይህን በሳይንሳዊ ምርምር ማግኘት ይቻላል በአሁኑ ጊዜ በሳይንሳዊ ምርምር የማይደረስባቸው እውነቶች ወደ ፊት ሊደረስባቸው ይችላሉ፤ ያለዚያም ጨርሶ የማይታወቁ ሊሆኑ ይችላሉ ይላል፡፡ ስለዚህ የዓለምን (ተፈጥሮን) ጠቅላላ ምንነት ማወቅ ወይም መረዳት ይቻላል፡፡

ዘመናዊነት ምንም እንኳ ስለ እውነትና ስለሕይወት ማወቅ ይቻላል ቢልም የማወቂያው መንገድ ብሎ ያስቀመጠው መንገድ ከመለኮታዊ መገለጥ (አስተርዮ) ውጪ ነበር፡፡ የእውነትን ወይም የግብረገብን ልክ የሚወስን ሁሉ ቻይ አምላክ (Omnipotinet) የሚባል የለም ብሎ ከመካድ አንስቶ በሳይንስ ምርምር እራስን ማወቅ ይቻላል፤ ስለዚህ እውነት በሳይንስ ነው የሚገኘው ይል ነበር፡፡ መለኮታዊ መገለጥ ኢ-ፍጹማዊ ስለሆነ ከሰው አስተሳሰብ እድገት ጋር እየታየ በየጊዜው የሚሻሻል እና የሚዳብር ነው ይላል፡፡

ድህረ-ዘመናዊነት የሚለው ቃል እ.ኤ.አ. ከ1930ዓ.ም. ጀምሮ የሚታወቅ ሲሆን በተለይ እንደ ንጽረተ ዓለም መታወቅ የጀመረው እ.ኤ.አ. በ1970ዎቹና በ1980ዎቹ ነው፡፡ ድህረ-ዘመናዊነት ስለእውነት፤ ስለሰው፤ ስለሕይወት ምንነትና ዓላማ በዘመናዊነት ንጽረተ ዓለም ውስጥ የነበሩ አመለካከቶችን በመቃወም የተነሳ ንጽረተ ዓለም ነው፡፡ የተከተለበት ስልት የዘመናዊነትን ዋና ዋና አመለካከቶች በማፍረስ ወይም በመበተን በውስጡ ያለውን አስተሳሰብ መመርመር ነበር፡፡

ድህረ-ዘመናዊነት በሳይንስ እና በሒሳብ ስሌት ላይ የተመሰረተው የዘመናዊነት ንጽረተ ዓለም አስተሳሰብ ሁሉን ነገር በሒሳብ ስሌት ማወቅና መቆጣጠር አልቻለም ብሎ ተነሳ፡፡ ለዚህም የተፈጥሮ አደጋዎች እንደሚደርሱ አለመታወቁና የሁለቱ የዓለም ጦርነቶች መምጣት በሒሳብ ስሌት ማወቅ አለመቻሉን እንደ ምሳሌነት ይጠቀሳሉ፡፡ ሁሉ ነገር በሳይንሳዊ ጥናት ወይም ምርምር ይገኛል የሚለው የዘመናዊነት ንጽረተ ዓለም አስተሳሰብ በድህረ-ዘመናዊነት ንጽረተ ዓለም እንደኋላ ቀር አስተሳሰብ እየታየ እና ቅቡልነት እያጣ ነው፡፡

የድህረ-ዘመናዊነት ንጽረተ ዓለም ዋናው አስተሳሰብ ’ለአንተ ጥሩ የሆነ ለአንተ ጥሩ ነው፤ ለእኔ ግን አይደለም ወይም ላይሆን ይችላል’ የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም አመለካከት ትክክል ነው፤ ሁሉም እውነት ነው ብሎ ያስባል፡፡ በድህረ-ዘመናዊነት ንጽረተ ዓለም በጊዜ፣ በቦታ እና በሁኔታ የማይቀየር ፍጹም እውነት የሚባል ስለሌለ የአንድን ነገር ትክክለኛነት ወይም ስህተትነት ማነፃፀርና መመዘን አይቻልም፡፡ ስለሆነም የድህረ-ዘመናዊነት ንጽረተ ዓለም ሁሉ ነገር ’ነውና አይደለም’ ነው፡፡ የድህረ-ዘመናዊነት ንጽረተ ዓለም ክፍል የሆነው አውዳሚነት (Nihilism) (ያለፈውንና አሮጌውን፣ አሁንም ያለውን ሁሉ በጥቅሉ የሚቃወም ኢዲያሌክቲካዊና ሐሳባዊ አዝማሚ ነው፡፡ በዚህ አመለካከት መሠረት የሰው ልጅ በዕድገት ሂደቱ ያካበተው ሥልጣኔ እና ባህል ሁሉ ፋይዳ የለውም፡፡ ይህ አመለካከት በህ.ወ.ሓ.ት መራሹ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ስም በስፋት ይቀነቀናል፡፡) ምንም እውነት የለም ሁሉ ከንቱ ነው (አልቦ እውነት) የሚለው ይህን የበለጠ ይገልጸዋል፡፡

የድህረ-ዘመናዊነት ንጽረተ ዓለም የራሱ የሆነ አቋም፣ ተከታዮች እና ባህላዊ መገለጫዎች ያሉት በመሆኑ የእኔ የሚላቸው ምሶሶያት (Pilars) አሉት፡፡ እነርሱም፡-

  1. ምክንያታዊ ወይም አመክንዮአዊ አስተሳሰብ፡- ይህ አመለካከት የሰው አዕምሮ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ብቻ ሁሉንም ነገር ፈጽሞ ሊያውቅ ይችላል የሚል ሲሆን ተአምራታዊ ነገሮችን ሁሉ ውድቅ የሚያደርግ አስተሳሰብ ነው፡፡
  2. ሳይንሳዊነት፡- ሰው ሁሉንም ነገር በሳይንሳዊ መንገድ ተመራምሮ ሊደርስ ይችላል የሚል ነው፡፡
  3. ወደፊት የሚሄድ አወንታዊ እርምጃ፡- ሰው በእድገት ወደፊት መገስገሱ አይቀሬ ነው፡፡ አዳዲስ ሳይንሳዊ ግኝቶችን እያገኘ ወደተሻለ ኑሮ እና አስተሳሰብ ይገሰግሳል፡፡ ባለፉት ዘመናት የሰው ልጅ ያስመዘገባቸው ህልቆ መሳፍርት ሥልጣኔዎች ለዚህ በቂ ማስረጃዎች ናቸው፡፡
  4. ተጨባጭ ወይም ፈጹም እውነት የለም፡- መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ እውነት አንጻራዊ ነው፡፡ በአስተሳሰቦች መካከል ምንም ዓይነት መበላለጥ ፈጽሞ የለም ወይም ሁሉም አስተሳሰቦች እኩል ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት እንደ አንዱ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ብንቀበል እንኳን ማናችንም እንደመሰለንና እንደገባን መተርጎም እንችላለን፡፡
  5. እውነት እና እውነታ፡- ስለምናየው ነገር በሙሉ ፍጹም እውቀት የለንም፡፡ ስለዚህ ስለ አንድ ነገር በድፍረት ይህ ነው ብለን ትርጉም መስጠት ወይም መናገር ፈጽሞ አንችልም፡፡ ምክንያቱም የምናየው ነገር ሁሉ ብዥታ ነው፡፡ በሁሉም ነገር ላይ ተመሳሳይነት (ተዛማጅነት) ስላለ ስለነገሮች ልዩነት ማውራት አንችልም፡፡ በመጨረሻው ዘመን ተሻጋሪ እውነት የሚባል ነገር የለም የሚል አቋም አለው፡፡
  6. አምላክ፡- አብዛኛዎቹ የድህረ-ዘመናዊ ንጽረተ ዓለም አራማጆች ፈጣሪ የለም ሲሉ (Atheists) ሌሎቹ ደግ ፈጣሪ እንዳለ ወይም እንደሌለ ለማወቅ ፈጽሞ አይቻልም (Agnostics) ይላሉ፡፡
  7. በዓለም ውስጥ እጅግ በጣም ዝነኛ የሆኑ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ አንዳንዶች ታዋቂነትን ያተረፉት በራሳቸው ማኀበረሰብ፣ ከተማ ወይም ሀገር ውስጥ ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ ዓለማቀፋዊ ዝናና ክብር አትርፈዋል፡፡ ይሁን እንጂ የአንድን ዝነኛ ሰው ስም እናውቃለን ማለት ግለሰቡን በሚገባ እናውቃለን ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ ስለ አስተዳደጉም ሆነ ስለ ሰውየው ማንነት ዝርዝር ጉዳዮችን ላናውቅ እንችላለን፡፡ ምንም እንኳ ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ የኖረው ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት ቢሆንም እርሱ ልክ እንደ ፈላስፋው ሶቅራጠስ (Socrates) ታላቅ አስተማሪ እና ላመነበት ነገር ለመሞት የቆረጠ ሰው ነበር እንጂ አምላክ ወይም የአምላክ ልጅ አይደለም፡፡ ሆኖም አንዳንድ ትምህርቶቹ እጅግ በጣም የነጠሩ የምግባር መሠረቶች መሆናቸውን መቀበል ይቻላል ብለው ያምናሉ፡፡ ለምሳሌ አምላከኛው (deist) የአሜሪካ ፕሬዘደንት ቶማስ ጃፈርሰን፣ ቤንጃሚን ፍራንክሊን፣ ሒንዱው የነጻነት መብቶች ታጋይ ማሐተማ ጋንዲ፣ ሊባኖሳዊዉ  ሰዓሊ ፣ ባለቅኔ እና ፈላስፋ ካኻሊል ጂብራን ፣ፈረንሳዊው ፈላስፋ ኢያን ጃኩስ ሩሶና ሌሎችም ዝነኞች በሕይወቱ እና በትምህርቱ  እጅግ በጣም ከተመሰጡት መካከል ይመደባሉ፡፡
  8. ደህንነት፡- ኃጢአት የሚባል ነገር ፈጽሞ የለም፡፡ ሰው ራሱን መርዳት ሲችል ያንጊዜ ’ደህንነት’ ነው፤ ራስን ማወቅ ነው፡፡ ሰው ራሱን ሲያውቅ የራሱን ነጻነት ያገኛል፤ ይህ የሚሆነው ከራሱ ሌላ ምንም ዓይነት ሥልጣን እንደሌለ ሲገነዘብ ነው፡፡ ደህንነት ሰው ራሱን ማወቁ ነው፡፡ ሰው እራሱን ’በሙላት’ ሲያውቅ እራሱን ነፃ ያደርጋል፤ ይህ ነው ደህንነት፡፡ ኃጢአት ስለሌለ ንስሐ አያስፈልግም፤ ውድቀት ስለሌለ አዳኝ ወይም የሚቤዥ ፈጽሞ አያስፈልግም፡፡ ኃጢአት ኀብረተሰብ በተለይም ደሃው የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ያመጣው ሃሳብ ነው፡፡ ለምሳሌ ታዋቂዋ የቴሌቪዥን የመዝናኛ መርሃ ግብር አዘጋጅ እና አቅራቢ እንዲሁም ሞጃዋ ኦፕራ ዊንፍሬይ፣ ታዋቂው የአዲስ ምድር እና የአሁንነት ኃይል (New Earth,and The Power of Know) መጻሕፍት ደራሲ ኤካርት ቶሌ፣ የአልኬሚስቱ (The Alchemist) መጽሐፍ ደራሲ ፓውሎ ኮሆሊዮ፣ ታዋቂው የፊልም ተጫዋች ቶም ክሩዝ እና የብልጽግና ወንጌል (Prosperty gospel) ሰባኪያን የዚህ ንጽረተ ዓለም አቀንቃኞች ናቸው፡፡
  9. ዘላለም፡- የሚባል ነገር ፈጽሞ የለም ሰው አንድ ጊዜ ከሞተ፤ በቃው፡፡  ከሞት በኋላ ትንሣኤ ሕይወት የሚባል ፈጽሞ የለም፡፡

ምንም እንኳን የድህረ-ዘመናዊነት ንጽረተ ዓለም ለሁሉ የሚሆን እውነት ፈጽሞ የለም ቢልም መጽሐፍ ቅዱስ ግን ሊታወቅ የሚችል እውነት መኖሩንና ይህ እውነት አርነት የሚያወጣ እንደሆነ “እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው” (ዮሐ 8፡32) በማለት ይናገራል፡፡ እንግዲህ የድህረ-ዘመናዊነት ንጽረተ ዓለም አስተሳሰብ የፈጣሪን ህልውና በመካድ ሰውን በአምላክ ስፍራ ማስቀመጥ፤ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቶችን መቃወም ነው፡፡ የድህረ-ዘመናዊነት ንጽረተ ዓለም በኢንደስትሪ በበለጸጉ ሀገራት በጣሙን በሰሜን አሜሪካ፣ በምዕራብ አውሮዻ እና በአውስትራሊያ በሰብአዊ እና በዴሞክራሲዊ መብቶች እንዲሁም በግለሰብ መብት ሰበብ ከጋብቻ በፊት ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሔዋን ካልደረሱ ከተለያዩ ወንዶች እና ሴቶች ጋር ሩካቤ ስጋ መፈጸም፣ ወጣቶች ለገንዘብ ሲሉ በዕድሜ እጅግ በጣም ከሚበልጧቸው ወንዶች እና ሴቶች ጋር ሩካቤ ስጋ መፈጸም እና መጋባት ፣ ግብረሶዶማዊነት፣ ዝሙት፣ አምኖናዊነት (masterbetion)፣ ቁማርተኝነት፣ ሰካራምነት፣ የትምባሆ፣ የሺሻ እና የኃሺሽ ሱሰኝነት፣ ውርጃ፣ ጾታን ማዛወር (gender transplant)፣ የዘር ፍሬ ልገሳ (Sperm or egg donation)፣ ከቤት እንስሳት፣ በተለይም ከውሻ ፣ ከአሳማ እና ከፈረስ ጋር ወሲባዊ ተራክቦ መፈጸም፣ ፍቺ፣ ራስ ወዳድነት፣ ስግብግብነት፣ ከሆነው በላይ እጅግ በጣም ጠቃሚ ነኝ ብሎ ማሰብ፣ የራስን ፍላጎት ብቻ ማሟላት… ወዘተ እጅግ በጣም ከፍተኛ ሞራላዊ ልሽቀት እና ሰብአዊ ክስረት አድርሷል፡፡ በዚህም የተነሳ በኢንደስትሪ የበለጸጉ ሀገራት የዲቃሎች፣ በጭንቀት የተወጠሩ፣ ተስፋ የቆረጡ እና ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር እጅግ በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፡፡ የድህረ-ዘመናዊነት ዳፋው በምዕራቡ ዓለም ብቻ ተወስኖ አልቀረም፡፡ በቀኝ ግዛት፣ የባሕርና የአየር መጓጓዣዎች መዘመን ተከትሎ፣ በብዙኃን መገናኛዎች እና በማኀበረሰብ ብዙኃን መገናኛዎች (Social massmedia) በኪነ-ጥበብ፣ በሥነ-ጥበብ፣ በስደት፣ በቱሪዝም፣ በጦርነት እና በዕርዳታ አማካኝነት ለሦስተኛው ዓለም ሀገራትም ዳፋው ሊተርፍ ችሏል፡፡ በዚህም የተነሳ እጅግ በጣም ብዙ ኢትዮጵያዊያን ስለ ድህረ-ዘመናዊነት ንፅረተ ዓለም ያለን እውቀት እና ግንዛቤ እጅግ በጣም ደካማ ስለሆነ በድህረ-ዘመናዊነት ንጽረተ ዓለም የተቃኘ የሕይወት ዘይቤ ነው የምንከተለው፡፡ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋና የጋራ ባህል እሴቶች ልማት ዳይሬክቶሬት በ2006/7 ዓ.ም. በመጤ ባህሎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ዙሪያ ላይ ባደረገው ሀገር አቀፍ ጥናት መሠረት በቤተሰብ እና በጓደኛ ተጽኖ ፣ የትምህርት ቤት እና የቤተሰብ የጋራ ቁጥጥር መሳሳት፣ ሉላዊነት (ድህረ-ዘመናዊነት)፣ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ መረቦች፣ የአላስፈላጊ ድርጊቶች መፈጸሚያ ቦታዎች መስፋፋት፣ የፖሊሲ እና የህግ ክፍተትና ተፈጻሚነት መሳሳት፣ ስደት፣ በሃይማኖት ተቋማት የሚሰጠው የሥነ- ምግባር ትምህርት መቀነስ ምክንያት ጠቃሚ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ የሥነ ምግባር እሴቶቻችን በመሸርሸራቸው የድህረ-ዘመናዊነት ንጽረተ ዓለም አስተሳሰብ እየተስፋፋ ነው፡፡ በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በሐዋሳ፣ በመቀሌ፣ በባህርዳር፣ በድሬዳዋ ከተሞች እና በአዳሪ ትምህርት ቤቶች፣ በከፍተኛ ትምህርት ቤቶች (High schools) እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (Universities) ግብረሶዶማዊነት እና የአደገኛ እጾች ተጠቃሚነት እጅግ በጣም በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ ነው፡፡        

1 Comment

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top