ጥበብ በታሪክ ገፅ

የኪነ-ጥበብ ሙያና ወቅታዊ የፈተና ገጾች

የዘንድሮ ነገር መቸም ለብቻው ነው!! የኮሮና ወረርሽኝ የዓለሙን ብዙ ነገር እንዳይሆን አድርጎታል። የእኛም ሀገር ሁኔታ ከሌላው ቢብስ እንጂ የሚያንስ አይደለም። ጉዳቱ ደረጃ በደረጃ ገና በብዙ መልኩ ይገለጣል። ከዚህ እንዳያብስብን መፀለይ እና መጠንቅቅ እንጂ የጤና አገልግሎት ዋስትና የሚሆን ነገር አለን ብለን እጅጉን ተስፋም አናደርግም። የምናውቀው ነውና።


ግሎብ ቴአትር

ሰሞኑን ተወዳጁ ጌታቸው ካሳ “በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ስራውን ስላቆመ ተቸግሯል።” መባልን በመገናኛ ብዙኃን ስሰማ እጅግ አዘንኩ፡፡ አሳዛኙ ነገር የሱ መቸገር ብቻ አይደለም፡፡ በሙያው የተገለገልን ታዳሚዎች፣ አድናቂዎች፣ ሙዚቃ ቤቶች፣… በሰንሰለቱ ያለን ሁላችን ምንም ማድረግ አለመቻላችን ብቻም አይደለም፡፡ ችግሩ የጌታቸው ብቻ ሳይሆን የሌሎችም እሱን መሰል በርካታ ብርቅዬዎች መሆኑ ጭምር ነው፡፡ በባላገሩ አይድል የምናውቀው ዳዊት ጽጌ እና ለየት ባለ አዘፋፈን ኢንዱስትሪውን የተቀላቀለው ዘሩባቤል ሞላ ሁለቱም ለበኩር አልበማቸው ያሰቡትን ኮንሰርት ሰርዘዋል፡፡ ድምጻዊት ዘሪቱ ከበደ እና ያሬድ ነጉ ደግሞ የአልበም ሥራቸው ከተራዘመባቸው ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በቀረጻ ላይ የነበሩ ፊልሞች እና ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች፣ የወራት ዝግጅታቸውን አጠናቀው የመድረክ ወረፋ በመጠበቅ ላይ የነበሩ ቲያትሮች፣ የታቀዱ ባዛሮች እና ዜግዚቢሽኖች ላይ ሊመደረኩ የታሰቡ ጥበባዊ መሰናዶዎች፣… ሁሉም ተቋርጠዋል፡፡ በወርሃዊ የኪነጥበብ መድረኮች ላይ ሥራዎቻቸውን በማቅርብ ኑሯቸውን የሚደጉሙ ከያኒያንም እጅ አጥሯቸዋል፡፡  

በርግጥ ይህ ክስተት ሐገራዊ ብቻ ዓይደለም፡፡ የግል ችግራችን ብቻ አይደለም፡፡ ዓለም አቀፋዊ ነው፡፡ በመላው ዓለም የኪነጥበብ እንቅስቃሴዎች ተገትተዋል። ከሁሉ ግን የክዋኔ ጥበቡ (ማለትም ቴአትር፣ የሙዚቃ አቅርቦቶች፣ ልዩ ልዩ የኪነጥበብ እንቅስቃሴዎች፣ የግጥም ምሽቶች…ወዘተ) እጅጉን ተጎድቷል። ምናልባትም ይህ ቅዠት መሳይ እውነታ ሲያበቃም ለረዥም ጊዜ ሊጎዳ የሚችለው ጥበብ ይኸው የክዋኔ ጥበብ ነው። ሰዎች ወደ ቴአትር እና መሰል ሰዎች የሚሰበሰብባችው የክዋኔ ጥበብ መመድረኪያ ስፍራዎች በቀላሉ አይጓዙም። ጊዜ ይፈልጋሉ። እነዚህ የኪነጥበብ ስራዎች ከፍተኛ አደጋ እንደተጋረጠባቸው በተለያዩ ዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙኃን የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። የእንግሊዙ ዝነኛ የሼክስፒር ዘመን ቴአትር ቤት የሆነው “ግሎብ ቴአትር” በገቢ ማነስ ምክንያት መንግሥት የማይደግፈው ከሆነ ሊዘጋ እና ረዘም ላለ ጊዜም ቴአትሮችን የማያቀርብ መሆኑን አውጇል። በአሜሪካም በዛ ያሉ ቴአትር ቤቶች ኪሳራ እያወጁ የሀገራቸውን መንግሥት ድጋፍ እየጠየቁ ነው። በተለይ ቴአትር ቤቶች በርካታ ባለሙያዎችን ቀጥረው የሚያስተዳድሩ በመሆኑ ለደሞዝ እና ለሌሎችመክ ወጪዎች ቋሚ ገቢ ያስፈልጋችዋል። በአብዛኛው ከቴአትር ተመልካቾች የሚሰበስቡት ገቢ በወረርሽኙ ምክንያት በመቋረጡ ብዙ ቴአትር ቤቶች በገቢ ማጣት ሊዘጉ ጫፍ መድረሳቸውን እያወጁ ይገኛሉ።


ግሎብ ቴአትር

ይህ እውነት የኛንም ሀገር ይመለከታል። ምንም እንኳ የኛ ቴአትር ቤቶች (ጥቂትም ቢሆኑ) በመንግሥት ደሞዝ የሚቆረጥላቸው ሰራተኞች ያሏቸው ቢሆኑም፤ በቴአትር ቤቶቹ የሚሰሩ ተዋንያን እና የቴአትር ባለሞያዎች ግን ቋሚ ሰራተኛ ሳይሆኑ በአብዛኛው ከመድረክ ክፍያ ከሚያገኙት ገቢ የሚተዳደሩ ናቸው። የቴአትር ቤቶቹ ሰራተኞችም ያለ ተጨማሪ ገቢ ኑሯቸውን ሊመሩ የሚችሉበትን ደሞዝ ከቲያትር ቤቶች አያገኙም፡፡ ደሞዛቸው ይህን ያህል እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ በየቴአትሩ ከሚያገኙት ተጨማሪ ገቢም ይተዳደራሉ። በመሆኑም በአሁን ሰዓት ከቋሚ ደሞዛቸው ባሻገር ከልዩ ልዩ የመደረክ ስራዎች የሚያገኟቸው ገቢዎች ተቋርጠዋል። በሰፊው የክዋኔ ጥበብ ውስጥ የሚሳተፉ ባለሞያዎች ግን ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ከዕለት ገቢያቸው ተገልለዋል።      

መንግሥት በተቻለው አቅም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዳይዳከም፣ ዜጎች በገቢ ማጣት እንዳይጎዱ፣ ወጣቶች በስራ ማጣት አሁን ካሉበት የከፋ ደረጃ እንዳይደርሱ እና በሽታው የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ የሚችለውን እያደረገ መሆኑ ግልፅ ነው። የሚበረታታም ነው። ነገር ግን በየዘርፎቹ እየነጠለ፣ ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያ እየሰጠ፣… ድጋፍ ማድረጉ እንዳለ ሆኖ ባልተገባ አመለካከት ምክንያት የኪነጥበብ እንቅስቃሴው እና ባለሞያዎቹ እንዳይጎዱ የሚያደርገውን ድጋፍ ገሸሽ እንዳያደርገው ያሰጋል። “ባልተገባ አመለካከት” ያልኩበት ምክንያት በሀገራችን የኪነጥበብ ስራ “የማዝናናት” እና “የትርፍ ሰዓት ስራ” ከመሆን ያለፈ ድርሻ ያለው ተግባር መሆኑን በመንግሥትም ሆነ በዜጎች ዘንድ ግንዛቤ ያለመኖሩን በማስመር ነው። በመሆኑ የመንግሥት የስራ ሀላፊዎች በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ለስራ ዘርፎች እና ለዜጎች የሚያደርጉትን ድጋፍ ሲወስኑ የኪነጥበብ ዘርፉንም እንደ አንድ አሳሳቢ አካል ሊመለከቱት ይገባል።

በርግጥ ከኪነጥበቡ በፊት የሚቀድሙ ስራዎች እንዳሉ እርግጥ ነው። ከኪነጥበቡ በፊት ዜጎች መመገብ አለባቸው፣ መታከም እና የመድሃኒት አቅርቦት ማግኘት አለባቸው፣ ደህነንታችን ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፣ ኢኮኖሚያችንም እንደዚሁ። ነገር ግን መረሳት የሌለበትም ኪነጥበቡ ውስጥ ያሉ ባለሞያዎችም እንደሌላው ዘርፍ እንዳሉ ባለሞያዎች ሁሉ ዜጎች መሆናቸውን ነው፡፡ እነዚህ ዜጎች እንደሌላው ሰው የሚያሳድጉት ልጅ፣ የሚደግፉት ቤተሰብ፣ የሚያግዙት ወገን አላቸው። በመሆኑም የዕለት ገቢ ያስፈልጋቸዋል።

በሀገራችን የኪነጥበብ መስክ ውስጥ ቋሚ ደሞዝ ተቆርጦላቸው የኪነጥበብን ስራ የሚሰሩ ባለሞያዎች (ጥናት ቢያስፈልገውም) ከመቶ አስር እጅ እንኳ አይሆኑም። አብዛኛው በየሳምንቱ በቴአትር ቤቱ በሚሰራው የመድረክ ክፍያ በሚያገኘው ገቢ ወይም በሰራው ፊልም፣ የቴሌቪዥን ድራማ፣ ማስታወቂያ እና መሰል ተግባር በሚያገኘው ቋሚ ያልሆነ ገቢ የሚተዳድር ነው። በዚህ መንገድ ከአብዛኛው ጥቂት ሻል ያለ ገቢ የሚያገኙት አጅግ ጥቂቶች ናቸው። በዛ ያሉት እዚህም እዚያም እየሰሩ ነገ የተሻለ ይሆናል በማለት ኑሮን እና የተፈጥሮን ጥሪ ለማሸነፍ የሚታትሩ ናቸው። በመሆኑም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የኪነጥበብ እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ በመቆማቸው የእነዚህ ባለሞያዎች የገቢ ምንጭ ሙሉ በሙሉ ደርቋል።

ወረርሽኙ እንደ ፈጣሪ ፍቃድ በአጭር ጊዜ ቢቋጭ እንኳ፣ ሰዎች ብዙ ሰው ወደ ተሰበሰባበቸው ቦታዎች የመምጣት እድላቸው አናሳ ይሆናል። ረዘም ላለ ጊዜም ቴአትር ቤቶች፣ ፊልም ማሳያዎች፣ የግጥም ማቅረቢያ አዳራሾች፣ የሙዚቃ ማቅረቢያ መድረኮች ባዶ ሆነው ይቆያሉ። ይህ ደግሞ የኪነጥበብ ባለሞያውን ለተራዘመ መከራ ይዳርገዋል።

ዘመናዊ የኪነጥበብ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተጀመረ ጀምሮ የኪነጥበብ ባለሞያዎች አሁን ለኮሮና ወረርሽኝ ማኅበረሰባዊ ንቃተ ህሊና ለመፍጠር እየተጉ እንዳሉት ሁሉ በሀገሪቱ ለተከሰቱ ጉዳዮች ግንባር ቀደም ተፋላሚ ባለሞያዎች ሆነው የየጊዜውን መንግሥት እና ህዝብን አገልግለዋል። አሁንም እያገለገሉ ይገኛሉ። ነገር ግን የየዘመናቱ መንግስታት በኪነጥበብ ባለሞያዎቹ እስኪበቃቸው መገልግል እንጂ ባለሞያዎቹን ማገልገልን አልተካኑበትም (እዚህ ላይ የኪነጥበብ ባለሞያዎቹ ችግር እንዳለበትም ሳይዘነጋ! ከዚህም በላይ የየጊዜውን አጋጣሚ እየተጠቀሙ ሀብት ያጋበሱ “ባለሞያ ነን” ባዮች ትናንትም ዛሬም እንዳሉ ሳይዘነጋ።)

ነገር ግን በየቀኑ ከካሜራ ፊት የማይገተሩ፣ ሰው በተሰበሰበበት እኔን ብቻ ስሙኝ የማይሉ፣ ዘወትር ስለ ሀገራቸው እና ህዝባቸው የሚጨቁ፣ ለገንዘብ ሲሉ ኪነጥበብን መሸቀጫ ያላደረጉ፣ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የቀን ተቀን ህይወታቸው ፈተና የሆነባቸው በየዘርፉ ብዙ የኪነጥበብ ባለሞያዎች አሉ። ነገር ግን እነዚህ ባለሞያዎች በጥቂት ጮሌዎች የመከለል እና የመታፈን አደጋ እንዳይጋረጥባቸው፤ በትህትናቸው ምክንያት (ከዚህ ቀደም በብዙዎች እንደሆነው!) ለብቻቸው ተጎድተው እንዳይገኙ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ሊያስቡበት ይገባል።

ምን ይደረግ?

የተቀናጀ፣ በጮሌዎች ሳይሆን ዘርፉን በሚያውቁት ባላሞያዎች እና በመንግሥት የተመራ (ጊዜያዊም ቢሆን) አንድ ተቋም ያስፈልጋል። ይህ ተቋም በተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ስልቶችን እየተጠቀመ፣ የመንግስትንም ድጋፍ እያከለ፣ እገዛ የሚያስፈልጋቸውን ባለሞያዎች በመመልመል መደገፍ ይኖርበታል። ከዚህም ተግባራት ውስጥ፦

  • በህዝብ ፊት ከሚያቀርቡት ስራ ባሻገር ሌላ የገቢ ምንጭ የሌላቸውን በጥናት እየመረጡ ማገዝ፤
  • ባለሞያዎች ከጠባብ አዳራሾች ባሻገር ትዕይንት ሊያሳዩባቸው እና ገቢ ሊያገኙባቸው የሚችሉባቸውን መንገዶች ማስላት፣ ማመቻቸት፤
  • ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ተቀያሪ (Alternative) የማሳያ መንገዶችን ማመቻቸት፤
  • መንግሥታዊ ካልሆኑ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመነጋገር ድጋፍ ለማሰባሰብ መሞከር፤ ወዘተ…

በእነዚህ እና በመሰል ስልቶች፣ ኪነጥበቡ ውስጥ ሆነው ድጋፍ ያላገኙ ወገኖችን ማገዝ የተገባ ይሆናል። ምንም ጥረት ሳያደርጉ ግን በኪነጥበብ ስም ለሚነግዱ ጥቂት ነጋዴዎች ብቻ የመንግሥትን ካዝና እያስበረበሩ፣ እንደ ጌታቸው ያሉ ታላላቅ ሰዎች በችግር ወድቀው ሲጎዱ እና ህይወታቸው ሲያልፍ ዜና ማሳወጅ፣ ቤተሰብ ለመርዳት መሯሯጥ ወይም ሌላ ተግባር መፈፀም ከታይታ ያለፈ ተግባር የሚሆን አይመስለኝም።

ይህ ወረርሽኝ ሲያበቃ ሰፊውን የኪነጥበብ እንቅስቃሴ እንዴት ማነቃቃት እና ወደነበረበት ቦታ፣ ሻል ሲልም ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር በጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ ያስፈልገዋል። የትኛው የኪነጥበብ ዘርፍ ምን ያህል እንደተጎዳ እና እንዴት መንቀሳቀስ እንደሚችል ጥናት ተሰርቶ መፍትሄ በሚሆን መንገድ ማስላት ያስፈልጋል። ሁሉም የኪነጥበብ ዘርፎች እኩል ጉዳት ደርሶባቸዋል ማለት ባይቻልም፣ ጉዳቱ ግን ሁሉንም መንካቱ አይካድም። ስለዚህ የትኛው ዘርፍ ይበልጥ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው አጥንቶ ተገቢ ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል። ድጋፉ ግን እንደተለመደው የመንግሥትን የገንዘብ ድጐማ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ልዩ ልዩ ስልቶችን፣ የፖሊሲ አማራጮችን፣ አዳዲስ ሕግ እና አዋጅ ማስፀደቅን እንዲሁም ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ፤ መንግስታዊ የሆኑ እና ያልሆኑ፤… ድርጅቶችን በማሳተፍ ጠንካራ መሰረት ለመጣል ልዩ ልዩ ተግባራትን መከወን ያስፈልጋል። እስከዛው ግን ባለሞያዎቹን ማዳን ይቀድማልና ተግባራዊ ምላሽ ቢሰጥ መልካም ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top