ታሪክ እና ባሕል

ዝኆኖችን ለምን እንታደግ?

እሱ እጅግ ደፋርና ብልጥ ነው። እርግጥ ነው ጠባቂዎቹም አያንቀላፉም። ዱሩን ነግሦበታል። ጠላቶቹን በስሙ ያባረረ ጀግና ነው። ተወድሷል፤ ደግሞም ተፈርቷል። ገድሎም ያውቃል። መጨረሻ ግን የእግዜር ሞት ሞተ።

ሹሉሬ ይሉታል ስሙን። የስሙ መነሻ የኮንታ ቃል ነው። ትርጉሙ አድፍጦ፣ አድብቶ የሚያጠቃ፤ ኮቴው ሳይሰማ፣ የሚደርስ፣… ማለት ነው። ይኽ በዚህ ወር ያጣነው የአፍሪካው ዝኆን የእድሜ ባለጸጋው የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ዝኆን ነው።

ዝኆን ተፈጥሮ የመንጋጋውን ጥርስ ስድስት ጊዜ ነቅሎ እንዲተካ እድል የሰጠችው ፍጥረት ነው። የመጨረሻው መንጋጋ ወይም ስድስተኛ ከሠላሳ ዘጠኝ እስከ ስድሳ አምስት ዓመት እድሜው ይወልቃል።

አዳነ ጸጋዬ የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ዋርደን ነው። የዚህን አንጋፋ ዝኆን ሞት ይፋ ባደረገበት ጽሑፉ የመጨረሻውን መንጋጋ ከነቀለ በኋላ የተፈጥሮ ሞት የሞተ መኾኑን ይፋ አድርጓል።

እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሀገር አንድ ዝኆን እድሜ ጠግቦ ከነጥርሱ በክብር ሞተ የሚለው ዜና የሀገር ክብር ነው። የጠባቂዎቹን ትጋት ያሳያል። የኖረበትን አካባቢ ማኅበረሰብ የተፈጥሮ ፍቅር ይገልጣል።

የጨበራ ጩርጩራ ዝኆኖች አንዳንዴ ከመኖሪያቸው ወጥተው አካባቢያቸው የሚገኝን ሰብል ያወድማሉ። ነዋሪውን ይተናኮላሉ፤ እንደ ዓለም አቀፉ የዝኆን መብት ተሟጋቾች “ዝኆን ድንበር አልባ ነው” የሚለውን ብንቀበልም፤ ያለ ሰፈሩ መጥቶ ሰፈራቸው ገብቶ የረበሻቸው ነዋሪዎች ግን ሁሉን በትእግስት እያለፉ ዛሬ በሀገራችን አንድ ብሔራዊ ፓርክ የጥይት ድምጽ ሰምተው የማያውቁ የአፍሪካ ዝኆኖች መኖሪያ ለመሆን በቅቷል።

የጨበራ ጩርጩራን ዝኆኖች እጣ ፈንታ ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ዝኆኖች አልታደሉትም። ምናልባትም የስሜኑ ጫፍ የሚባለውና በተከዜ ዳርቻ የሚገኘው የቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ ካልኾነ በስተቀር ብዙዎቹ የዝኆን መኖሪያ ፓርኮች የሕገ ወጦችም መኖሪያ ናቸው።

የሽብርተኞች የገቢ ምንጭ ከዝኆን ጥርስ ላይ መፈለጉ ግዙፉን የምድራችንን የየብስ እንስሳ አበሳ አብዝቶታል። ዝኆኖች እጅግ ሩህሩህ እንስሳ የሚባሉ ቢኾኑም ጥርሳቸው ሰው እንዳይራራላቸው አድርጓቸዋል።

እንደ POACHING FACTS ሪፖርት ለውድ ዋጋ የሚቀርቡ ጌጣጌጦች ምንጭ የኾነው የዝኆን ጥርስ የአፍሪቃ ዝኆኖችን ከምድር የሚያወድም ክስተት ኾኗል። ከዝኆን የቁጥር ምጣኔ አንጻር እየደረሰ ያለው ዝኆንን የማውደም ጠባይ አሳሳቢ መኾኑን የሚጠቁመው የCITES ሪፖርት የሰው ልጅ ዝኆኖችን ሊታደግ የሚችልበት አስራ አንደኛው ዘመን አሁን ያለንበት የታሪክ ምዕራፍ እንደኾነ አስቀምጧል።

ያም ኾኖ ምንጩ ያልታወቀ ሀብትና ለሽብር ዓላማ የሚውልን የበጀት ፍላጎት ለማሟላት ጠንካራ ደህንነት በሌለባቸው ሀገራት በሚደረጉ አደኖች የሚገኙ የአውራሪስ ቀንድና የዝኆን ጥርስ ናቸው።

ዝኆን ከአምስት ወገኖቹ አሁን ብቻውን የቀረ የምድር እንስሳ ኾኗል። ከዚህ ቀደም ይኖሩ ከነበሩት የዝኆን ቤተሰቦች አራቱ ማለትም ሞሪተሪዴ፣ ጎምፎተሪዴ፣ ማስቶዶንቲዴና ዳይኖተሪዴ ቅሪታቸው የቀረ ነበሩ ለመባል የበቁ ናቸው።

ኤሌፋንቲድ የሚባለው ዝርያ ደግሞ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ጀምሮ ዛሬ ድረስ ለሰው ልጆች ጊዜያዊ ፍላጎትና ለማጌጥ በሚደረግ መሻት የነገሥታት እልፍኝ የሚደምቅበት ጥርስ ባለቤት በመኾኑ ሲታደን ኖሯል።

እንደ ናሽናል ጂኦግራፊ ሪፖርት አፍሪቃ በአስር ዓመት ውስጥ 64 ከመቶ የዝኆን ሀብቷን አጥታለች። በጥርሳቸው ብቻ የሚሞቱት ግዙፍ የምድራችን የየብስ ፍጡራን እ.ኤ.አ ከ2009 እስከ 2012 ባለው ጊዜ በሦስት ዓመት ብቻ ቁጥራቸው 100 ሺህ የሚደርሱ ዝኆኖች መታደናቸውን ገልጾ ነበር። የናሽናል ጂኦግራፊክ ዘገባ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር 2011 ለአብነት ወስዶ ከአስራ ሁለቱ የአፍሪቃ ዝኆኖች አንዱ በአዳኝ ይገደላል። ይኽ ቁጥር መካከለኛው አፍሪቃ ላይ ደግሞ የሚብስና የሚጋነን ነው።

የSave the Elephant ጥናት ደግሞ የዓለም የደን ዝኆኖች ቁጥር ዛሬም እየቀነሰ ነው ይላል። የሩቅ ምስራቅ ዝኆን ጥርስ ፍላጎት ለዚህ አንድ ምክንያት ነው። ውሎ አድሮ ደግሞ ዓለምአቀፍ የሽብር ቡድኖች ትልቁና ቁጥጥር አልባው የገቢ ምንጫቸው ይኽው የዱር እንስሳ ውጤት መኾን ችግሩን ይበልጥ አከፋው።

የSeptember 2015 National Geographic መጽሔት ልዩ ትኩረት የሰጠው ለዝኆን ጥርስ ነበር። በዚህ ዕትሙም ከኢትዮጵያ የሚወጣው የዝኆን ጥርስ የሕገ-ወጥ ንግድ መስመር መድረሻ እስያ እንደኾነ አስፍሯል።

ኢትዮጵያ ዝኆንን ለመታደግ ካሰበች አንድ ክፍለ ዘመን አስቆጥራለች። ዳግማዊ ምኒልክ የዝኆንን አደን በተመለከተ ያወጡት ሕግ በአፍሪቃ ጉዳዮ ያሳሰባት ቀደምት ሀገር ቢያደርገንም ከችግሩ ጋር በመኖር በእኩል ስማችን የሚነሳ ከመኾን አልዳንም።

ኢትዮጵያዊው የዝኆን ሳይንቲስት ዶክተር ይርመድ ደመቀ ዛሬ ጥቂት ቦታዎች ለመመሸግ የበቁት የኢትዮጵያ ዝኆኖች ትናንት በብዙ የሀገራችን አካባቢዎች እንደ ነበሩ በጥናት ጽሑፋቸው አስፍረዋል። ዶክተር ሰለሞን ይርጋም ይኼንኑ ይጋራሉ። “አጥቢዎች” በሚለው መጽሐፋቸው ዝኆንን በሚመለከት ስርጭቱን ሲገልጹ በቀደሙት ዘመናት ከሰሃራ በስተደቡብ ውሃና ዛፍ ባለበት ስፍራ ሁሉ ይገኙ እንደነበር ነው የሚገልጹት።

ዛሬ ዝኆን ይገኝባቸዋል የሚባሉት የኢትዮጵያ አካባቢዎች ጥቂት ናቸው። የተከዜው ዳርቻ ቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ፣ በኮንታና በዳውሮ መካከል የሚገኘው የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ፣ የባቢሌ ዝኆኖች መጠለያ፣ የማጎና ኦሞ ብሔራዊ ፓርኮች እንዲሁም ጋምቤላ ሲኾኑ ምልክቶቹ የታዩበት አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ደግሞ አለ የሚለው ተረጋግጦ ይፋ ያልኾነበት ነው።

የባቢሌ የዝኆኖች መጠለያ በአህጉራችን ቀዳሚው የዝኆን መጠለያ ቢኾንም ዛሬ ለዝኆን ካልተመቹ የዝኆን መኖሪያዎች አንዱ ሳይኾን አይቀርም። በሱማሌና በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው የባቢሌ ዝኆኖች መጠለያ ብዙ ፈተናዎች ተጋርጠውበታል። ዝኆኖች ይገደላሉ፤ ከዚያ አልፎ የዝኆን ጠባቂዎችም ሕይወት የከፋ ነው። ለዝኆን ብሎ በሰቀቀን የሚኖር ጠባቂ የሚኖርበት የዝኆን መጠለያ ነው።

ለዝኆን የተመቸ መኖሪያ መፍጠር ማለት የተፈጥሮ ሥነ ምህዳሩን አስተማማኝ ማድረግ ነው። ከዝኆኖች ምቾት ጀርባ ያለው ትርጉም ለትውልድ የሚገባውን ድርሻ ማኖር ነው። ይኼ ውሳኔ የሰው ልጅ አስተማማኝና ዘላቂ ሀብት እንዲኖረው ያደርጋል።

በአሳለፍነው የግንቦት ወር ሦስተኛ ሳምንት በማጎ ብሔራዊ ፓርክ የተደረገው አደን ስምንት ዝኆኖችን አሳጥቶናል። በአንድ ሳምንት በዚህ ቁጥር ልክ ዝኆኖችን ማጣት አሁን ሰከን ብሏል ከሚባለው የአህጉሪቱ የዝኆን አደን ወንጀል አኳያ ከፍተኛ ቁጥር ነው።

በኢትዮጵያ ዝኆን ብቻ ሳይኾን የዝኆን ጠባቂም ነፍስ መውደቂያዋ አይታወቅም። ምክንያቱ ደግሞ የዝኆኑ ጠባቂ መሳሪያ አንግቶ መግደል ተከልክሎ መሞት ግዴታው እንዲኾን የተጣለበት የሀገር ሻማ ነው። ሕገ-ወጥ አዳኙ አለማደኑ ብቻ ሳይኾን ሊያድን ሲል መታየቱ ካሳሰበው ቀላሉን ነገር ያደርጋል፤ ጠባቂውን ለመግደል መሞከር። ራሱን የሚከላከል ጠባቂ ደግሞ ዕጣ ፈንታው አንድ ነው፤ እስር።

እንዲህ ባለው የፍትሕ መዛባት ብዙ የዱር ሕይወት ጠባቂዎች የሀገር ዝኆን ለመሰብሰብ ቤተሰባቸውን በትነዋል። ተፈጥሮን ለመጠበቅ ህይወታቸውን ለግሰዋል።

በተፈጥሮ ሀብቶቻቸው የምንቀናባቸው ጎረቤት ሀገራት ሙሉ ለሙሉ እንደ ሠራዊት በሚታይ የሰለጠነ ታጣቂ ኃይል ከተፈጥሮ ሀብቱ የሚበልጥ መርህ የለም በሚል መንፈስ የታደጉትን ተፈጥሮ ህይወት እየተገበረለት ከሚጠበቀው የኢትዮጵያ ሀብት ጋር ማነጻጸር በሰው ቁስል እንጨት የመስደድ ያኽል ግዴለሽነት ነው።

እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ገና ከሰው ልጅ መብትና የህልውና ጥያቄ ያልተላቀቀች ሀገር ዝኆን መኖር አቃተው ብሎ መጮኽ ቅንጦት ስለሚመስል ልሂቃኑም የሚያውቁትን ከመናገር ዳጎስ ያለ ጥናት ጽፎ ማኖርን መርጠዋል።

እውነታው ግን የኢትዮጵያን ዝኆኖች እንታደግ ስንል ለእነሱ ብለን አይደለም። ከሚጠብቋቸው አንዳቸውም ልጃቸውን ለዝኆን አይድሩም፤ አልያም የስጋ ዝምድና የላቸውም። ዝኆንን የምንጠብቀው ለራሳችን ነው።

ዶክተር ይርመድ ደመቀ የWestern,D Ecological role of elephants in Africa ጽሑፍን ጠቅሰው በአስቀመጡት የዝኆን ጠቀሜታ ይኼ ግዙፍ ፍጥረት ለአንድ አካባቢ የተፈጥሮ እጽዋት ብልጽግና ከፍተኛ ሚና አለው ይላሉ። ዝኆን የእጽዋትን ስብጥር ለመጨመር በተቃራኒውም ጥቅጥቅ ያለ ደንን ለማሳሳትና በሌሎች እንስሳት ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ በኩል አበርክቶው የላቀ ነው ይላሉ።

ዝኆንን ጠብቀን በዱር እንስሳት ቱሪዝም መጠቀም የሚለው ዓለምን ያጠገበ የኢኮኖሚ ጥበብ አልታይ ቢለን እንኳን ተፈጥሮን ጠብቆ ለመኖር ዝኆን የሚጫወተውን ሚና ማሰብ ብልጠት ነበር። ግን አልኾነም።

ዝኆኖችና መኖሪያቸው የዚህ ትውልድ ሀብት አይደሉም። የመጪውን ትውልድ ድርሻ መንጠቅ ከወንጀል ሁሉ ይከፋል። ቀጠሎ የሚኾነውን ለማሰብ ዛሬ የምንሰራው ምልክት ነው። ዝኆኖቹም ሀገራቸው ነው።      

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top