የታዛ ድምፆች

#ዝም አልልም

የህጻናቱን መደፈር ወሬ በርካታ ሰዎችን አስቆጥቷል። አርቲስቶችም #ዝምአልልም የሚል ዘመቻ ከፍተው በስሜት ቁጣቸውን እየገለጹ ነው፤ እንዲሁም ሌሎች ላለመለየት እየተመሳሰሉ ነው። ጥሩ ነው። ነገር ግን ግቡ ምንድን ነው? በእቅድ ላይ ተመስርቶ ነው? ወይስ እንዲሁ እንደለመድነው የአንድ ሰሞን ወሬ እና ጩኸት ሆኖ የሚቀር?

እንደ ማኅበረሰብ ያደረግናቸውን አስተዋጽኦዎችስ እንዴት እንመዝናቸው ይሆን? ምክንያት ተደርገው ከተነሱት መካከል ሚዲያ እና ፊልሞች ይጠቀሳሉ። እና አርቲስቶቹስ ከእንግዲህ ስራ መርጦ ከመንሳት አንስቶ የሰው ልጆች ሕይወት ላይ ምስቅልቅሎሽ የሚያስከትሉ ስራዎችን ላለመስራት ከስር ከስሩ ያስቡ ይሆን?

ይኽንን የምጠይቀው፣ ሰዉ የመቆጣቱን እና የመጮኹን ያህል፣ መጀመሪያ ወሬውን የሰማንበት የዋልታ ቲቪ ሊንክ ተመልካች ቁጥር ያን ያህል አይደለም። ይኽንን እስክጽፍ ድረስ 28,569 ሰው ብቻ ነው ያየው። በቲቪ ሲሄድ ያዩት ይኖራሉ በርግጥ። እንዲሁ ሰይፉ ፋንታሁን “65 ተጨማሪ ህጻናት ተደፈሩ” በሚል ርዕስ ያቀረበውን የሬድዮ ዝግጅት ሊንክም 12247 ሰዎች ብቻ ናቸው ያዩት። የዋልታን ብንተወው፣ የሰይፉን ከራሱ ከሌሎች ዝግጅቶቹ ጋር ካላቸው ተመልካች ጋር ስናነጻጽረው፣ በዚህ ሰሞን ከታዩት ዝግጅቶቹ ሁሉ በቁጥር አነስተኛው ይሄ ነው።

እንግዲህ ተመልካች መቁጠሬ፣ ሌሎች ዝግጅቶች ካሏቸው ተመልካቾች አንጻር ሲታይ ያን ያህል ተግባራዊ ትኩረት የተሰጠው ስላልመሰለኝ ነው።

የዋልታው ዝግጅት ላይ፥ የኢትዮጵያ ሴቶች መጠለያ ጥምረት ም/ሰብሳቢ ማኅሌት ኃይለማርያም “መጠለያ ውስጥ ያሉት ሁሉም ኬዛቸው በሕግ ተይዟል” ብላ ነበር። እንዲሁም የአ/አ/ሴቶች እና ህጻናት ቢሮ ኃላፊ አልማዝ አብርሃ የጥቃት ኮሚቴ እንዳላቸውና፣ ከምክትል ከንቲባው ጅምሮ ተባብረው ከጥቃት ጋር በደንብ እየሰሩ መሆናቸውን፤ የሕግ አማካሪም እንዳለ፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ጋርም እንደሚተጋገዙ ተናግረው ነበር። በሦስቱ ሆስፒታል ጣቢያዎች፣ በተለይ ጋንዲ ፖሊስም እንዳለ እና እዛው ማመልከት እንደሚቻል ተናግረዋል። ሰናይትም እንዲሁ “ፍርድ ቤት ጉዳዩን እናደርሳለን። የፍርድ ሂደቱንም እንከታተላለን።” ብላለች።

ነገር ግን፥ የጠቅላይ ፍ/ቤቱ ዋና ሀላፊ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ “ከአ.አ.ህ/ሴ/ቢሮ በህፃናት ላይ የሚደርስ ጥቃትን በተመለከተ ለህዝብ የተገለፀውን መረጃ መሠረት በማድረግ ባለፉት 2 ወራት የተከፈቱ የክስ መዝገቦችን ለመከታተል ባደረግነው የመረጃ ዳሰሳ ባለፉት 2 ወራት የተከፈቱ መዝገቦች እንደሌሉ አውቀናል።” ብላ በትዊተር ገጿ ገልጻ ነበር።

የቱ ነው ትክክለኛው? የደፋሪዎቹ ጉዳይ በሕግ አልተያዘም? ወይስ ተይዟል?

ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንትና የሴቶች ህጻናት እና ወጣቶች ሚኒስትር “ሴቶችና ህጻናት በኮሮና ምክንያት ከሚደርስባቸው ዘርፈብዙ ጫና እና ፆታዊ ጥቃት እንታደጋቸው!” የሚል የጽሁፍ መልእክት ልኳል።

በምን ዓይነት መልኩ ነው ከሚደርስባቸው ዘርፈ ብዙ ጫና እና ፆታዊ ጥቃት የምንታደጋቸው? እየተባለ ያለው እኮ፣ ያለው ሕግም አተገባበር ላይ ክፍተት አለበት ነው። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ሊከሱ ፖሊስ ጣቢያ ሄደው፣ ተከሳሽ ከከሳሽ ቀድሞ ቤት ይመለሳል፣ በዚህም የተነሳ ሰዉ “ምን አቀያየመኝ መፈታቱ ላይቀር” እያለ አይናገርም፣ የጥቃት ከለላ ይሆናል ነው።

ለምንድን ነው ቤተሰብ ከሚሳቀቅ፣ ደፋሪዎቹ ይፋ የማይወጡት? በመልክ የማይታዩት? የማናውቃቸው? ፎቶአቸው የማይሰራጭ እና “ተጠበቋቸው” የማይባል? ሌሎች ብዙ አገራት እንደዚያ ያደርጋሉ። የእኛ አገር ሕግ ለምንድን ነው ወንጀለኛን የሚተባበረው?

በነገራችን ላይ፥ ከተደፈሩት 101 ህጻናት ውስጥ፣ አብላጫው ማለትም 57ቱ ወንድ ህጻናት ናቸው። ነገር ግን አብዛኛው ሰው የሴት ህጻናቱን ጉዳይ ነው የሚያነሳው። ምናልባት ነገሩን በአግባቡ ሳይሰማ ስለሚቃወም ይሆን? ያው በአግባቡ ካልሰማ፣ ለምን እንደሚቃወምና ምን ዓይነት መፍትሄ እንደሚጠብቅ ያለማወቅም ነገር ይኖራል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top