አድባራተ ጥበብ

እኛነታችንን በ“9ኛውሺህ” መነጽር

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሲችዌሽናል ኮመዲ (ሲትኮም) ስራዎች ቁጥር እየተበራከተ መጥቷል። ለፊልሙ ዓለም አዲስ የሆነው ይህ ዘውግ በርከት ያለ ቁጥር ባላቸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እየተዘወተረ ነው። ለበርካታ ዓመታት (ከ900 ክፍል በላይ) የሄዱትን ጨምሮ በቅርብ ዓመታት እስከተጀመሩት ድረስ እያዝናኑ ለማስተማር፣ እያሳቁ እንከንን ለመንቀስ እየጣሩ ይገኛሉ። ከነዚህ መካከል አንዱ “9ኛው ሺህ” ነው።

 ‹‹9ኛውሺህ›› በአብርሆት ኢንተርቴይመንት ኤክሰኪዩቲቭ ፕሮዲውሰርነት፣ በወንድማገኝ ለማ ደራሲና ዳይሬክተርነት እየተዘጋጀ የሚቀርብ የአንድ ቤተሰብ /የአቶ ብርሃኑ/ የሰርክ ውሎና አዳር የሚያሳይ ተከታታይ ድራማ (ሲትኮም) ነው።

የድራማው ቋሚ ገፀ-ባህርያት

  • መምህር ብርሀኑ – አበበ ተምትም፣
  • ረድኤት – ስንናፍቅሽ ተስፋዬ፣
  • ወርቁ (ጩባው) – ሚሊዮን ብርሃኔ፣
  • አቡ – ሱራፌል ብስራት፣
  • ውሮ – ሜላት ወልዴ

ሲሆኑ እነዚህ ቤተሰብ ላይ ተመሰርቶ በሚዘልቀው ታሪክ ውስጥ የተለያዩ ገፀ-ባህርያት፣ እንደየታሪኩ ተገቢነት ወጣ ገባ ይሉበታል።

‹‹9ኛውሺህ›› በየሣምንቱ በአቶ ብርሀኑ ቤተሰብ ውስጥ አዳዲስ ታሪክ እየፈጠረ የሚጓዝ፣ ከየሣምንቱ የእኛ /የሀገራችን/ አበይት ክስተቶች መካከልም ለነቁጥ ያህል እየመዘዘና የታሪኩ አካል እያደረገ የሚቀጥል ሲሆን ከተከታታይ ድራማው ታሪክ፣ ከገፀ-ባህሪያቱ ማንነት ጋር የተሰናሰለ የመግቢያ፣ የመሸጋገሪያና የመዝጊያ ዜማ አለው።

የ‹‹9ኛውሺህ›› ተከታታይ ድራማ ዜማ ዘመናዊ ቃና ያረበበበት፣ የገፀ ባህርያቱ ማንነት የተገለፀበት የተከታታይ ድራማው ጭማቂነው።

‹‹ህይወት በየፈርጅዋ መልኳ ጉራማይሌ፣

ደምቆ እየፈዘዘ የዘመናት ቆሌ፣

ቅኝት አልባ ምሬት ምንአገባኝ ጌታ፣

ሆነው እየመሩት የጊዜውን ቦታ፤

      ህልሙ ጠባብ ሰፊ ሜዳው፣

      መንቃት ብርቁ መቆም ዕዳው፣

–     –

ሁሉም ሣለ መሬት ጠበ ለማነስ ይለፍል፣

ቦታ ሳይሰጥ ለምርኩዙ ለመንገድ ይጋፋል፣

በየመስኩ በደጃችን አረሙ በዘበት፣

ዘርን ለናይ ተጠምደናል አሻግሮ በማየት፣

ከአይምሮ በላይ ልቀን ርቀን ሄደናል

8ሺን ጭልት አርገን ዘጠኝ ከትመናል

            ወይ — 9ኛውሺህ

ወይ — 9ኛውሺህ

ወይ — ወይ — ወይ — !››

****

ገፀ ባህሪያት

ብርሃኑ /ብሬ/፡- የቤተሰቡ አባወራ፣ የረዥም ዓመት የማስተማር /የመምህርነት ልምድ ያለው፣ ከጠመኔ ቡናኝ ጋር ሲታገል የኖረ፣ በቀደመ ታሪኩ የ1960ዎቹ ትውልድ በመሆኑ በሶሻሊስ ርዕዮተ ዓለም ፍቅር ወጣትነቱን ያነደደ፣ የትዳር አጋሩን በሞት የተነጠቀ፣ የአብራኩ ክፍይ የሆኑ 2 ሴትና 2 ወንድ ልጆች ያሉት፣ ከዛሬ ጋር አብዝቶ የሚጣላ፣ በት/ቤት በሚያስተምራቸው የዛሬ ልጆችና በገዛ ልጆቹ የዛሬ ማንነት የሚብሰለሰልና የሚበግን፣ ግን ደግሞ ከእነዚህ የዛሬዎቹ ጋር አብዝቶ በመዋሉ… ቀልድና ፌዝ… ቄንጠኛ ስታይልና የአነጋገር ፈሊጥ /ፋሽን/ የተዋሰ፣ ነገረኛ የሚባል ሆኖ ቀልድና ቁምነገርን አዋዝቶ የሚያሸሙር ባተሌ… አባት!

ረድኤት /ረዱ/፡- የብርሃኑ የክቡር ልጅ፣ በእናቷ ሞት ሰበብ የእማወራነት ኃላፊነትን የተሸከመች /የእህት እናት/… ምግብ አብሳይ፣ ልብስ አጣቢ፣ አስተዳዳሪ ናት፤ የፍራፍሬ (የአትክልት) መሸጪያና ጭማቂ ቤት ከፍታ የምትታትር፣ በአንድ የግል ኮሌጅ የትምህርት ደረጃዋን ለማሻሻል የምትጥር፣ ገራገር፣ እንደ አንድ ወጣት ሴት እጮኛም ሆነ ትዳር የማትሻ፤ እኩዮችዋ ያዩት ያላየች ሞቃታማው ሴትነቷ እየመሸባት ያለ!

ወርቁ /ጩባው/፡- የአቶ ብርሃኑ 2ተኛ ልጅ፣ የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን በተገቢው ሳይማር የተመረቀ፣ ለድምፃዊነት (በራሱ አባባል ‹‹ጥበብ የጠራችው››) እንደሆነ አብዝቶ የሚያምን፣ በተወላገደ ግጥም፣ በተፋለሰ የዜማ ስልት ያለ አንዳች ምንተህፍረት ወደ ሙዚቃ ስቱዲዮ የሚዘልቅ፣ የመጠጥ፣ የሴትና የእግር ኳስ ውርርድ ‹‹ቤቲንግ›› ሱሰኛ የሆነ… ፌዝ አብዥ፣ ሳቅ አፍቃሪ…!

አቡ፡- የአቶ ብርሃኑ 3ተኛ ልጅ ሥራ አጥ፣ … ትምህርቱን ያቋረጠ፣ ለክብደት ማንሳት ስፖርትና ለህንድ ፊልም ልዩ ፍቅር ያለው የእጅ አመል ያለበት፤ የአሽከርካሪነት ፈቃድ አውጥቶ በታክሲ ሹፌርነት ተቀጥሮ ለመስራት አብዝቶ የሚሞክርና የማይሳካለት። ትንሽዋን ታክሲ (ላዳ) ገዝቶ የመኖር ህልሙ ላይ የሚንሳፈፍ፤ የታናሽ እህቱን የውሮን የት/ቤት ጓደኛ አፍቅሮ አብዝቶ በሚመለከታቸው የህንድ ፊልሞች ላይ የሚያየውን የፍቅር ታሪክ በእውኑ ለመኖር የሚሟሟት!

ውሮ፡- የአቶ ብርሃኑ አራተኛና የመጨረሻ ልጅ፣ 20ኛ ዓመቷን ያልደፈነች፣ ቅንጡ የቴሌግራምና የፌስ ቡክ ልክፍተኛ… የቀን ጭፈራ (ዴይ ፓርቲ) እና ዳንስ አዘውታሪ የመጀመሪያ ዓመት የጋዜጠኛነት ተማሪ፣ የውጭ ሀገር ዜጋ አሊያም ዲያስፖራን አጥምዳ በማግባት ለመሰደድ ያቆበቆበች፣ ቤተሰቧ፣ ት/ቤቷ፣ ሀገሯና ቀዬዋ የሚያንገሸግሻት!

በእነዚህ የተከታታይ ድራማው ቋሚ /መደበኛ/ ገፀ ባህሪያት ዙሪያ ከቤተሰቡ ግቢ ውስጥ ቤት ተከራይ፣ ጎረቤትየው /ሱዳን/ ጓደኛዎቻቸው የት/ቤት ተማሪዎችና መሰል ገፀ-ባህሪያት እንዳየ ሣምንቱ የድራማው ታሪክ ተካተውበት ከ40 ሣምንታት በላይ ዘልቋል።

**

ምን ነገረን?

‹‹9ኛውሺህ›› የአንድ ቤተሰብ የሰርክ ውሎና አዳር ተከታታይ ድራማ ቢሆንም ዓለምን በከፊል፣ የእኛይቱ ኢትዮጵያን ደግሞ በጉልህ ያሳየናል፤ የቤተሰቡ አባላት በአንድ ጉዳይ ላይ አባሪ /የበላይ/ ለመሆን ሲፍተረተሩ በአሜሪካና በቻይና ግብግብ ይመሰላል፣ የግብግቡን ውጥረት ለማርገብ ሌላኛው የቤተሰብ አባል ሲውተረተር አቅም አጥነቱ /ተሰሚ ባመሆኑ/ በተባበሩት መንግሥታትነት ይፈረጃል።

የአቡ ሥራ ማጣት፣ የመብራት በተደጋጋሚ መጥፋት፣ የረዱት /የረዱ/ ጭማቂ ቤት መታሸግና ከቀበሌ ጋር የሚከሰት ተዘውታሪ ውዝግብ፣ የብርሃኑ /የብሬ/ የመምህርነት ወርሃዊ ደመወዝ ማነስ… የኢትዮጵያችንን ገበና ፀሐይ ያሞቀዋል።

ይህ የምንገኝበት የእኛው የፖለቲካችን አተካሮና ቅጥ አጥነት በተከታታይ ሣምንታት የድራማው ኢፒሶዶች ይወቀራል፣ ይነቀሳል፣ ይሸሞርበታል…!

አክቲቪስትነት፣ የነፃ አውጪ ፓርቲነት፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችነት፣ የዲያስፖራ ፖለቲከኛነት፣ ጋዜጠኝነት ወዘተ… እንደየ ሰሞንኛ ሁኔታቸው ከቤተሰቡ ታሪክ ጋር በተጣጣመ መልኩ እየተሰናሰሉ ይተቹበታል።

ኢትዮጵያችን ከመጋቢቱ 2010 መንግሥታዊ የአመራር ለውጥ ጀምሮ የሰነበተችበት ክራሞት ከሌሎች የዓለምና ከራሷ ጎረቤት ሀገራት ጋር የነበራትና ያደረገችው ግንኑኝነት ይፈተሽበታል።

ምንም እንኳን ተከታታይ ድራማው ቧልት ቢያይልበትም እንደ ቤተሰብ፣ እንደ ማኅበረሰብና እንደ ሀገር የምንገኝበትን ሁኔታ ፈትሾ የማማዎቻችንን መንጋደድና መዝመማቸውን “እንካችሁ” ይለናል።

ተሰጥኦ አልባ “ድምጻውያን ነን” ባዮችን በወርቁ /ጩባው/ ዘፋኝ የመሆን ቀቢጸ ተስፋ እና የከሸፈ የዜማ የግጥም “ደራሲነት” ገሃድ ያወጣል።

የጥንትና ቀደም ያሉ ዘፋኖችን “ሪሚክስ አደረኩት” በሚል ያልተገባ ሙከራ ‹‹አሻሻልኩት እና አዘመንኩት›› ብለው ከቀደመውና ጥበባዊ ለዛውን ከጠበቀው ኦርጅናሌ ፈፅሞ የራቀ (የካና መካ የሆነ) ጩኸት አይሉት ኳኳታ ነገር እንካችሁ ባዮች በወርቁ /ጩባው/ ተወክለው በ9ኛው ሺህ ተከታታይ ክፍሎች ይገኛሉ።

‹‹8ኛውሺ›› በተለምዶ የመዓትና “የጉድ ክፍለ ዘመን ነው” ተብሎ የሚነገረውን ብሂል መነሻ አድርጎ ይህ ዓይነቱን የቁጣና የክፉ ክ/ዘመንን ተሻግሮ ‹‹9ኛውሺህ›› ለተከታታይ ድራማው መጠሪያነት የመመረጡ ትክክለኛነት የሚገባን የአቶ ብርሃኑ /ብሬ/ ቤተሰብ የየዕለቱ ቤተሰባዊ ግንኙነትና የኑሮ ዘይቤን በድራማው ተከታታይ ክፍሎች በፅሞና የተመለከትን እንደሆነ ነው።

ሲጋራ በለበሰው ዩኒፎርም ኪስ ውስጥ ይዞ የሚገባና ጠላ ጠጥቶ በመማሪያ ክፍል ውስጥ “እንቅልፍን ያለሃሳብ የሚለጥጥ ተማሪ፣ የአስተማሪ /የብርሃኑ/ ልጅ ትንሿ ውሮና “F” ያመጡ ጓደኞቿ ተሰባስበው “F” ለማግኘታቸው የዳንስና የፌሽታ ድግስ ሲደግሱ፣ ውጭ ሀገር ለዓመታት የኖረ 20ኛ ዕድሜን በቅጡ ያልቆጠረ አፍላ ውሮን የውሸት አግባብቶ ወደ ነበረበት ሀገር ይዞ ለመመለስ በማሰብ ቤቷ ድረስ በድፍረት መጥቶ ቤተሰቧ ስለሚከፍሉት 6 መቶ ሺህ ብር ሲደራደር፣ ወርቁ /ጩባው/ የእህቱ የረድኤት /የረዱን/ ጁስ መጭመቂያና የገዛ አባቱ /የብሬን/ ጫማ ሸጦ የእግር ኳስ ውርርድ /ቤቲንግ/ ሲቆርጥና አረቄ ገዝቶ ሲጠጣ፣ አቡ የእህቱ /የውሮን/ ጓደኛ በማፍቀሩ ምክንያት ያፈቀራት ልጅ እጮኛዋ “ሹገር ማሚ” /ከዕድሜው በላይ ከሆኑ ሴቶች/ ጋር ወሲባዊ ግንኙነቱን አቁሞ ከእርሷ ጋር እንዲታረቅ ጉልበቱን ተጠቅሞ ይህንኑ ልጅ በመደብደብ ለሚያፈቅራት ሌላ ፍቅር ሲያመቻች…

…እና ሌላም ሌላም ስናይ እውነትም ‹‹9ኛውሺህ›› ያሰኛል…! የተከታታይ ድራማው ማስተዋወቂያ ዜማም እኮ… “ከአዕምሮ በላይ ልቀን ርቀን ሄደናል፣/ 8ሺን ጭልጥ አድርገን ዘጠኝ ከትመናል›› ነው የሚለው። 8ኛው ሺህ የነበረው እንዳልነበረ ይሆናል የሚለውን ሀይማኖታዊ ትንቢት እንደተግባባንበት ነጥብ ልለፈውና እንቀጥል፡፡

በ‹‹9ኛውሺህ›› ተከታታይ ድራማ የእኛዎቹ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና እያዘጋጁ የሚያሰራጯቸው ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችም ይተቻሉ፤ ለምሳሌ በአንዱ የድራማው ክፍል ውሮ ስፖርት አይሉት፣ መውረግረግ አይሉት መንዘፍዘፍ ሁለቱን ጅሮዎቿን በጆሮ ማዳመጫ /ኤርፎን/ ደፍና ደጃፋቸው ላይ አይሆኑ ስትሆን /ለእሷ ሳልሳ መደነሷ ነው/ ወንድሟ አቡ ‹‹አንቺ ምን ታደርጊ የእኛዎቹ ሚዲያዎች ናቸው የአካል ብቃት እንቅስቃሴን፣ ምሳ ሰዓት ላይ እያሳዩ ያበላሹሽ›› ይላታል።

ይህ የአቡ አባባል ሲያስቅ ይችል ይሆናል! ግን ደግሞ ትልቅ ትችት ነው፤ በሚዲያ ባለሙያዎች የተሰራ የመገናኛ ብዙኃንን ውስንነት የሚያሳይ ጥናትን የሚያስንቅ፣ የሚዲያ ፕሮግራሞቻችንንና የሚተላለፉበትን ሰዓት ያለመጣጣም /የአውድና ድባብ ተገቢነት/ ችግርን አመላካች!

የሚዲያ ፕሮግራሞች ያልተገባ /ረብ የለሽ የሆነ/ የርዕሰ ጉዳይ መርጣ፣ የአንዳንድ አዘጋጆችን የቅድመ ዝግጅትና የሙያዊ ክህሎት ውስንነት፣ በተለይ በቃለ መጠይቅ አድራጊዎችና በእንግድነት የሚቀርቡ አንዳንድ ግለሰቦች ላይ የምናስተውላቸውን ክፍተቶች ቃለ መጠይቆቹ በተላለፉበት ማግስት በሚታየው የ‹‹9ኛውሺህ›› ድራማ ላይ ሲገመገሙና ሲመዝኑ ይታያል።

በእኔ እምነት ከወቅታዊ የማኅበረሰብና የሀገራችን ጉዳይ ጋር በተያያዘ ጎላ ብለው በመነጋገሪያነት የሰነበቱ ክስተቶችና ርዕሰ ጉዳዮች ገና መነጋገሪያ መሆናቸው ከአየሩ ላይ ሳይደበዝዝ በ‹‹9ኛውሺህ›› ድራማ ላይ ከአቶ ብርሃኑ /ብሬ/ ቤተሰብ ከተረኛ /የክፍሉ/ ርዕሰ ጉዳይ (ጭብጥ) ጋር ተሰናስለው በመደበኛነት መቅረባቸው የደራሲውና አዘጋጁን ብቃትና ለተከታታይ ድራማው መሰጠትን ብሎም የተዋንያኑን አንድ ወቅታዊ ርዕሰ ጉዳይ አዋዝቶ ከራስ /ከገፀ ባህሪው/ ጋር አዋህዶ የመተወንን ጥበባዊ ክህሎትና ተሰጥኦን ያሳየናል።

ከመገናኛ ብዙኃኖቻችን ጋር በተያያዘ የ‹‹9ኛውሺህ›› አንዱ የቤተሰብ አባል ነገር መደጋገም ካበዛ፣ አሊያ ደግሞ ሌላ ግዜ (ቀደም ብሎ) የቀለደውን ቀልድና የተናገረውን አባባል ከደጋጋመ በሌላኛው የቤተሰብ አባል ‹‹ምነው አንተ ደግሞ የኛን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ይመስል ትደጋግማለህ›› ይባልና ምን ቻናሎቻችን ቁጥራቸው ቢበራከትም በዜና ይሁን በፕሮግራሞቻቸው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተደጋጋሚና ተመሳሳይ ስለመሆናቸው በሾርኔ ጠቅ ተደርጎ ይታለፋል።

ስለ ትውልዳችን!

ተከታታይ ድራማው በርዕሱ እንዳመለከተን፣ በማስተዋወቂያ ዜማውም እንደነገረን ‹‹8ኛውሺን›› ያለፉ የ‹‹9ኛውሺህ›› ትውልዶች ላይ አብዝቶ ያተኩራል፣ የቤተሰቡ አባል የሆኑ በርካቶቹ /ከጋሽ ብሬ በስተቀር/ ሁሉም “የዛሬዎቹ” የሚባሉ ናቸው፤ በየተከታታይ ክፍሎቹም እንደየ ክፍሉ ርዕሰ ጉዳይና ጭብጥም ገባ ወጣ የሚሉ ገፀ ባህሪያትም ሁሉም ሊባሉ በሚያስችል መልኩ ወጣት ገፀ ባህሪያት ናቸው።

እና… በግሌ 40ዎቹንም ክፍሎች በተደጋጋሚ ዐይቼ የተገነዘብኩት አንድ ዐቢይ ቁምነገር “9ኛውሺህ” ለእኛ ለዛሬዎቹ /ለዘመኑ ወጣቶች/ የተሰራ የቴሌቪዥን ድራማ መሆኑን ነው።

የአቡ የስርቆት አመል /በነገራችን ላይ የአቡ የእጅ አመል በመንገድ ላይ የጀበና ቡና ከምትሸጥ አንዲት ደሃ እንስት በረከቦቷ ላይ ከደረደረቻቸው ሲኒዎች መካከል አንስቶ ኪሱ እስከመክተት የደረሰ ነው/፣  የወርቁ /ጩባው/ ህልመኝነት፣ ላልተፈጠረበት ዘፋኝነት ራሱን አጭቶ በቁም መቃዠት፣ የረድኤት /ረዱ/ ታላቅ /የበኩር ልጅ/ በመሆን ብቻ የቤሰቡን የጓዳ ጎድጓዳ ጣጣ ለመሸከም መታጨት፣ ብርሃኑ /ብሬ/ የሚያስተምራቸው ተማሪዎች ተስፋ ቢስነት፣ በሱስና በምዕራቡ ዓለም ባዕድ ባህላት ባህር ውስጥ መስመጥ፣ ከኢትዮጵያዊ ማንነት አብዝቶ መራቅ፣ የውሮ ትምህርት፣ እውቀትና ምክር ጠልነት፣ በቴክኖሎጂ ፍቅር አብዝቶ መውደቅ.… እኛ የዛሬዎቹን ዐያሳየን ይሆን?

የ‹‹9ኛውሺህ›› ማስታዋወቂያ ዜማ እንደሚነግረን የእኛ የዛሬዎቹ ህይወት በየፈርጁ ጉራማይሌ ነው፣ ብዙዎቻችን እናማርራለን ግን ምሬታችን ቅኝት አልባ ነው፣ ጌታችን ምን አገባኝነት፣ ምን ሰፊ ሜዳ ቢኖረን ህልማችን ጠባብ፣ በህይወታዊ ኑሮ ይሁን በሰብአዊ ማንነት ጤናማ አቋቋም አጦች መንቃት ብርቃችን የሆንን አይደለም?

በ‹‹9ኛውሺህ›› ረድኤት /ረዱ/ ትጥራለች! ጥረቷ ለፍቶ ለመሻሻል ነው፡፡ ይህ ጥረቷ በዘርፈ ብዙ ሳንካዎች የተከበበ ነውና ደስተኛ አይደለችም፤ ጥረቷ በእውቀት አይደገፍም፣ ስሜት ይበዛዋል፣ ወረት ያጠቃዋል፣ በዚያ ላይ እናታቸውን በሞት በመነጠቃቸው ምክንያት አንድም ታላቅ ሁለትም እንስት በመሆኗ ቤተሰቡን ተሸክማለች! (እንደውም በርከት በሚሉ የድራማው ክፍሎች በተደጋጋሚ ‹ወገቤ ተንቀጠቀጠ፣ ወገቤ እስኪንቀጠቀጥ…›› ማለት ታበዛለች) ምሬት የገፀ ባህሪዋ መለያ ነው።

ወርቁ /ጩባው/ ቢማር ያልተማረ ነው፤ ተመርቋል ግን ስለተመረቀበት የትምህርት (ሙያ) ምንም አያውቅም፣ ለአላዋቂነቱ እውቅና ላለመስጠት አዋቂ መስሎ ለመታየትና “አዋቂነው” ለመባል ያልተሳካ ሙከራ ያደርጋል፤ ያለ ጥሪው በ“ጥበብ ጠራችኝ” ባይነቱ ደረቅ ነው፤ አልተሳካለትም ግን ደግሞ ስኬታማነቱን ብቻ ይለፍፋል፣ ደስታ ባይኖረውም ደስተኛ ለመምሰል ፌዝና ቀልድ አዘውታሪ ነው፤ ውሸት፣ የእውነት ያልሆነ ግን ጥቅምን አብዝቶ የሚፈልግ አፍቃሪነት ምልክቱ ነው፡፡ በተከታታይ ድራማው ክፍሎች /በተደጋጋሚ ለጥቅም የሚቀርባቸው ሴቶች ይከሰታሉ /ቁማርና አረቄ ነፍሱ ነው፤ ካልሲው የሚሸት፣ የአባቱን ጫማ ወይም የቤተሰቡን አንድ የሆነ ቁስ /ንብረት/ ሸጦ የሚጠጣ፣ ካርታ ቤት የሚያመሽ፣ በዚያ ላይ ድንጉጥ… ፈሪ… ግን ድንጉጥነቱ፣ ፍርሃቱ እንዳይታውቅበት አብዝቶ የሚጠነቀቅ! በአጠቃላይ ወርቅ መሆን ያቃተው ከራሱ የተጠፋፋ… ነው። (መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ እንዲሉ ስሙ ወርቁ ነው)

አቡ… ቂል መሣይ ግን ጉልቤ… ባለው ጉልበት ምንም ማድረግ የሚሳነው የማይመሳሰለው፤ ባንድ በኩል ባለው የአሽከርካሪነት ፈቃድ የራሱን ተሸከርካሪ (ላዳ) ገዝቶ የመንዳት የገዘፈ የምኞት ባህር ላይ እየዋኘ በሌላ በኩል ግን የሚሰርቀውን እንኳን የማይመርጥ የእጅ አመለኛ… አዘውትሮ እንደሚመለከታቸው የህንዶች የፍቅር ፊልሞች ማፍቀር የሚቃጣው፣ የታናሽ እህቱን ጓደኛ፣ ያፈቀራትን “ቃጀል” ነው የሚላት፡፡ ለ“ቃጀል” ሲል፤ ከጉልቤዎቹ ጎርምሶች ጋር ብቻውን 11ዱን ግብግብ ገጥሞ /በመፋለም ድል ሲያደርግ የሚያልም ቅዠት ቅርቡ ነው… መደበኛ ትምህርቱን እንኳ በወጉ ተምሮ ያላጠናቀቀ…

ውሮ /ትንሺቷ/ የዛሬ ታናናሾቻችንን ወካይ ናት፡፡ እሷን ዕያዩ ነገን አለማሰብ፣ ነገን በእርስዋ ውስጥ ዐይቶ አለመደንገጥ፣ አለመሳቀቅ አይቻልም።

ውሮ ነገር ቶሎ የማይገባት…. ትምህርት ጠል… ዳንስ አፍቃሪ… “የዴይ ፖርቲ” /የቀን ጭፈራ/፣ የፋሽንና የጌጣጌጥ ግዞተኛ…. የቴሌቪዥን ዜና ፎቢያ ያለባት፣ ሀገር… ምናምን የማይገባት ምክር.. አለርጂኳ፣ ለነጄኔፈር ቀናኢ… ለምዕራቡ ዓለም የፊልም ተዋንያን /አክተሮች/ ውሎና አዳር ተጨናቂ… ‹‹ፈታ ማለት ነው እንጂ!›› የምንግዜም መፈክሯ ነው።

ሲጠቃለል

‹‹9ኛውሺህ›› በየሣምንቱ በፋና ቲቪ እየመጣ፣ በቀልድ እያዋዛ በአንድ ቤተሰብ ሃዲድ ላይ እያመላለሰ፣ በየፋርጎውም እኛነታችንን እያቀለመ የሚያሳየን የትውልዳችን (የዛሬዎቹ) መነፅር ነው።

ተከታታይ ድራማው ከዚህ ወግ አንፃር ለኮሜዲ ያደላ እንደመሆኑ በቀልድ እያዋዛ የሚነግረን የእኛነታችንን ህፀፆች፣ በየገፀ-ባህሪያቱን ማንነት፣ ፍላጎትና ከዚሁ ማንነታቸውና ፍላጎታቸው በመነሳት የሚሆኑት፣ የሚከውኑት ሁሉ በእኛነታችን የሚያስተላልፉት ቁም ነገር በቀልዱ ደብዝዞብን እኛም ቁምነገሩን አፍዝዘን ቀልዱን እንዳናደምቅ የሚል ስጋቴ እንደተጠበቀ ሆኖ ‹‹9ኛውሺህ›› የእኛ፣ የማኅብረተሰባችንን ብሎም እንደ ሀገር የቆምንበትና የምንገኝበትን ዙሪያ መለስ ሁናቴ ስለማሳየቱ አልጠራጠርም።

በመጨረሻም፡– አሁንም ኮሮና ስጋት ነው፤ ጥንቃቄ የሕይወት መመሪያችን ይሁን!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top