ታሪክ እና ባሕል

ኡሌ

በፎክሎር ጥናት ዘርፍ፤ ሀገረሰባዊ ሙዚቃዎቻችን ከባህርያቸው አንጻር መንፈሳዊ እና ዓለማዊ በሚል ይመደባሉ። መንፈሳዊ ሙዚቃዎች በተለያዩ የሐይማኖት አስተምህሮዎች መሰረት ለአምልኮ፣ ለምስጋና ወይም ለምህላ በሚል የሚከወኑ ወይም የሚቀርቡ ናቸው። መንፈሳዊ ሙዚቃዎች ዝማሬ (Chant)፣ ውዳሴ (Mass)፣ ዜማ (Hymn) እና ዘፈን (Song) በሚባሉ የተለያዩ ሙዚቃዊ ቅርጾች (Musical forms) ይቀርባሉ።

እነዚህን የሙዚቃ ቅርጾች መሰረት አድርገው የሚቀርቡ የአገራችን የእስልምና ኃይማኖት መንፈሳዊ ሙዚቃዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል መንዙማ እና ነሺዳ ይጠቀሳሉ። መንፈሳዊ ሙዚቃዎቹን የሚከውኑ ባለሙያዎችም የራሳቸው ስያሜ አላቸው። መንዙማን የሚከውን ባለሙያ ማዲሕ ይባላል። ነሺዳን የሚከውን ባለሙያ ደግሞ ሙንሺድ ይባላል።

በኢትዮጵያ ከመንዙማ እና ነሺዳ በተጨማሪ ባሮ፣ ሰርመዴ፣ ሹቢሳ፣ ሰላሞ፣ እንጉርጉሮ፣ አቶረራ እና ዜከራ የሚባሉ መንፈሳዊ የእስልምና ኃይማኖት ሙዚቃዎች አሉ። እነዚህን መንፈሳዊ ሙዚቃዎች የሚያቀርቡ ባለሙያዎች ኡሌ በሚል የማዕረግ ስም ይጠራሉ።

ኡሌዎች እና የመንፈሳዊ ሙዚቃ ክወናቸው በአብዛኛው የሚታወቀው ከድሬ ሼኽ ሁሴን መካነ ቅርስ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ቀረቤታና ግንኙነት ካለው የማኅበረሰብ ክፍል ዘንድ ነው። የድሬ ሼኽ ሁሴን መካነ ቅርስ በአገራችን ታዋቂ ከሆኑ የእስልምና ኃይማኖት ማዕከላት መካከል አንዱ ነው። መካነ ቅርሱ ከአዲስ አበባ በደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ በ610 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ፣ በባሌ ዞን፣ በጎሎልቻ ወረዳ በአናጂና ቀበሌ ይገኛል።

የድሬ ሼኽ ሁሴን መካነ ቅርስ ከ950 ዓመት በፊት የተመሰረተ እንደሆነ የሚነገርለት ተፈጥሯዊ፣ ሀይማኖታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶችን አጣምሮ የያዘ ልዩ ስፍራ ነው። ስፍራው ስያሜውን ያገኘው በፈጣሪ የተመረጡና ታላቅ የሀይማኖት አባት እንደሆኑ በሚታመነው በሼኽ ሁሴን ሼኽ ኢብራሂም ስም ነው። ሼኽ ሁሴን ኢብራሂም በ12ኛው መቶ ክ/ዘመን መካነ ቅርሱን መመስረታቸው ይነገራል።

በድሬ ሼኽ ሁሴን መካነ ቅርስ የተለያዩ በዓላት ይከበራሉ። በመካነ ቅርሱ በሚከበሩ በዓላት ወቅት ስምንት ዐይነት መንፈሳዊ ሙዚቃዎች ይከወናሉ። መንፈሳዊ ሙዚቃዎቹም ባሮ፣ ሰርመዴ፣ ሹቢሳ፣ መንዙማ፣ ሰላሞ፣ እንጉርጉሮ፣ አቶረራ እና ዜከራ በሚል ስያሜ ይታወቃሉ።

ድሬ ሼኽ ሁሴን የመንፈሳዊ ሙዚቃ ብዝሃነት ያለበት ስፍራ ነው። ስምንት የተለያዩ መንፈሳዊ ሙዚቃዎች በአንድ ቦታ፣ በአንድ በዓል ላይ፣ በአንድ ጊዜ… በድሬ ሼኽ ሁሴን መካነ ቅርስ እናገኛለን። ይህ መሆኑ በአገራችን ከሚገኙ መሰል የኃይማኖት ማዕከላት ድሬን የተለየ ያደርገዋል።

ድሬ ሼኽ ሁሴን የእነዚህ መንፈሳዊ ሙዚቃ ከዋኞች በሕዝብ ፊት ጥበባቸውን አቅርበው፣ በሕዝብ ተፈትነው ዕውቅና የሚያገኙበት ስፍራ ነው።… ኡሌ የሚል ማዕረግ የሚያገኙበት ስፍራ ነው። የኡሌነት ሰርተፊኬት መስጫ ነው። የኡሌነት ሰርተፊኬት እውነተኛነት ማረጋገጫ ስፍራ ነው። የባሌው ድሬ ሼኽ ሁሴን መካነ ቅርስ

በድሬ ሼኽ ሁሴን የሚከወኑትን መንፈሳዊ ሙዚቃዎች ለመከወንና የኡሌነት ማዕረግ ለማግኘት የሚፈልግ ሰው የሚፈጽማቸው የተለያዩ ስርዓቶችና ቅደምተከተል አሉ። እነዚህ ስርዓቶችና ቅደምተከተሎች በመካነ ቅርሱ የኡሌነት ማዕረግ አሰጣጥ ቋሚ መስፈርትና ሂደቶች ናቸው። የኡሌነት ማዕረግ አሰጣጥ ሂደትም የሚከተለው ነው።

አንድ ሰው ኡሌ መሆን ከፈለገ፣ ኡሌ መሆን እንደሚፈልግ ቀደም ብሎ በስፍራው የሚከበሩ በዓላትን ለሚመሩ የኃይማኖት አባቶች፣ ለበዓላት አስተባባሪዎችና ለአገር ሽማግሌዎች ይገልጻል። እነሱም የአንድ ወይም የሁለት ቀን ቀጠሮ ይሰጡታል። በቀጠሮው ቀንም ኡሌነትን መመዘን የሚችሉ ሰዎች ተመራርጠው በአንድ ላይ ተሰባስበው ይጠብቁታል። እነሱ ፊትም ግለሰቡ ክወናውን እንዲያቀርብ ያደርጋሉ።

ግለሰቡ ክወናውን ሲያቀርብ ገምጋሚዎቹ የግጥሙ ይዘትና ውበት፣ የዜማ ቅኝት፣… ላይ በማተኮር ይገመግሙታል። ግለሰቡ የሼኽ ሁሴንን ታሪክና ገድል በትክክለኛ ግጥም ከገለጸ፣ የድምፁ ቅላጼውና የድምጹ ገልበት እንዲሁም የዜማ አወጣጡ ጥሩ ከሆነ የአገልግሎት ዘመኑ እንዲረዝም፤ መልካም ዕድል እንዲገጥመው ይመርቁታል። ነገር ግን የግጥሙ ይዘት፣ ቅኝቱና ድምጹ ጥሩ ካልሆነ በሌላ ጊዜ እንዲመለስና ድጋሚ እንዲታይ ያደርጋሉ።

በሀይማኖት አባቶች፣ በአገር ሽማግሌዎችና በበዓላት አስተባባሪዎች ፊት ክወናውን እንዲያቀርብ ተደርጎ በግምገማው መሰረት የተመረጠ ሰው ረጅም ቁመትና መካከለኛ ውፍረት ያለው የደንቄ በትር ይሰጠዋል።

ደንቄ የሼኽ ሁሴን ወዳጅ የሆኑ ሰዎች የሚይዙት በትር ሲሆን፣ አናቱ ላይ የባላ ቅርጽ (‘’Y’’) አለው። የደንቄ በትር ‘የሼኽ ሁሴን ባላ፣ ‘የሼኽ ሁሴን ዱላ፣ ‘ባላ ባልቾ እና ‘ኡሌ ሼኽ ሁሴን በሚሉ የተለያዩ ስያሜዎች ይጠራል።

የደንቄ በትር የተሰጠው ከዋኝ በሌላ ጊዜ በሚከበር በዓል ላይ እንዲገኝ ይነገረዋል። ከዋኙ በተባለው የበዓል ወቅት ወደ ስፍራው ሲመጣ፣ መጀመሪያ ከገመገሙት ግለሰቦች መካከል ለአንደኛው የሚችለውን አንድ ነገር… ጫማ፣ ጃኬት፣ ሽርጥ፣ ሸሚዝ፣ ጀለብያ ወይም ሌላ ጥሩ ነገር ሊሆን ይችላል ስጦታ ይዞ ይመጣል። ስጦታውንም ለግለሰቡ ይሰጣል። ይመረቃል፤ ፀሎት ይደረግለታል።

ከዋኙ ስጦታ ይዞ በመጣበት ወቅት ክወናውን ለማቅረብ ዋሬ በሚባለው መንፈሳዊ ስርዓቶች በሚከወኑበት ስፍራ ይገኛል። ከዋኙ ወደ ዋሬ ቦታ ይዞት የሚሄደው ስጦታ ያመጣለት ግለሰብ ነው። ስጦታ የተሰጠው ግለሰብ በዋሬው ላይ የሚከወኑ ስርዓቶችን ለሚመራው የፕሮግራም አስተባባሪ ስለ ከዋኙ ፍላጎትና በስፍራው ስለመገኘት ያሳውቃል።

የፕሮግራሙ አስተባባሪ ግለሰብም በስፍራው ለተሰበሰበው ሕዝብ ስሙንና መንፈሳዊ ሙዚቃ ሊያቀርብ እንደሚፈልግ ገልጾ፣ ክወናውን ሕዝብ ፊት እንዲያቀርብ ይጋብዘዋል። ግለሰቡም ክወናውን ማቅረብ ይጀምራል።

ክወናውን የሚያቀርበው ግለሰብ የኡሌነት ማዕረግ የሚሰጠው በዋሬ ላይ የተሰበሰበው ሕዝብ ነው። በመሆኑም ሕዝቡ የግለሰቡን ክወና በአንክሮ ይከታተላል።

በድሬ ሼኽ ሁሴን መካነ ቅርስ ግለሰቦች ኡሌ ለመሆን ክወናቸውን የሚያቀርቡበትና የተለያዩ መንፈሳዊ ስርዓቶች የሚፈጸምባቸው ሁለት የዋሬ ስፍራዎች አሉ። የዋሬ ስፍራዎቹ ደረጃ በደረጃ የተሰሩ መቀመጫዎች አሏቸው። የደረጃ መቀመጫዎቹም የአምፊ ትያትር ማሳያ አይነት ቅርጽ ያላቸው ናቸው።

በመካነ ቅርሱ ሁለት ቦታዎች ላይ እነዚህ የደረጃ መቀመጫዎች ተገንብተዋል። ቦታዎቹም ዶቆ ከራ እና ዶቆ ድንኩሬ በሚል ስያሜ ይጠራሉ። የደረጃ መቀመጫዎቹ በ18ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ ላይ በሼኽ መሃመድ ቲልማ ቲልሞ እና በሼኽ አባስ አማካኝነት እንደተገነቡ ይነገራል።

በበዓላት ወቅት ሕዝቡ በእነዚህ የደረጃ መቀመጫዎች ላይ በመቀመጥ የተለያዩ ስርዓተ-ከበራዎችን ይከውናል፤ ሲከወኑ ይመለከታል። ለኡሌነት የሚመዘነው ግለሰብም በእነዚህ ስፍራዎች በተሰበሰበው ሕዝብ ፊት ስራውን እንዲያቀርብ ይደረጋል።

ለኡሌነት የሚመዘነው ግለሰብ ሕዝብ ፊት ክዋኔውን ሲያቀርብ፣ ሕዝቡ ግጥሙን፣ ድምጹን፣ ዜማውን በትክክል አቅርቧል ብሎ ካመነ ሽልማት ይሰጠዋል። ግለሰቡም ክወናውን አቅርቦ ሲጨርስ ይመርቁታል፤ በዚሁ ይቀጥል ብለው ያሳልፉታል። ሕዝቡ ችሎታውን ገምግሞ የኡሌነት ማዕረጉን ሲያጸድቅለት ከወራት በፊት በተወሰነ ገምጋሚዎች የተሰጠው የደንቄ በትር በአገር ሽማግሌዎች አማካኝነት እዛው ሕዝቡ ፊት ድጋሚ ይሰጠዋል።

ለኡሌዎች የደንቄ በትር የሚሰጥበት ሁለት ምክንያቶች አሉት። አንደኛው፣ ኡሌ መሆናቸው በሕዝብ ፊት መረጋገጡን የሚገልጽ የምስክር ማስረጃ ነው። ደንቄው የችሎታው ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ኡሌዎች መንፈሳዊ ሙዚቃ ክወና ሲያቀርቡ ደንቄውን በእጃቸው በመያዝ ወዲያና ወዲህ በማወዛወዝ ስለሚከውኑ ነው።

ደንቄ የተሰጠው ግለሰብ የኡሌነት ማዕረግ ያለው፤ በበዓላት ወቅት “ዋሬ” ላይ መንፈሳዊ ሙዚቃ እንዲከውን የተፈቀደለት ይሆናል። ግለሰቡ የኡሌነት እውቅና አገኘ ማለት ነው።

ነገር ግን ግለሰቡ ክወናውን ሲያቀርብ በግጥሙ፣ በድምጹ ወይም በዜማው ላይ ስህተት ከተገኘ ወይም ለኡሌነት አይበቃም ብሎ ሕዝቡ ካመነ ክወናውን ሳይጨርስ ወዲያው ያስቆመዋል። ግለሰቡ ለክወናው ብቁ ካልሆነ ሕዝቡ በጩኽት፣ በጭብጨባ ወይም አቁም በሚል ትዕዛዝ ያስቆመዋል።

በዚህን ጊዜ ግለሰቡ ለሌላ ጊዜ እንዲያቀርብ ተጨማሪ አንድ እድል እንዲሰጠው ጠይቆ፣ ክወናውን ያቆማል። ሕዝቡም የግለሰቡን የክወና ሁኔታ ከግምት በማስገባት ለሚቀጥለው ጊዜ እንዲገመገም አንድ እድል ሊሰጠው ወይም ሙሉለሙሉ እንዳይመለስ ሊወስን ይችላል።

በድሬ ሼኽ ሁሴን መካነ ቅርስም ኡሌዎች የሚያቀርቡትን ክወና ሕዝብ ፊት በማቅረብ ይገመገማሉ። ሕዝቡም ለክወናው ዳኛ እና ፈራጅ  በመሆን የራሱን ውጤት ይሰጣል። ክወናው ባህሉን መሰረት ያላደረገ፣ ክህሎትና ዕውቀት የጎደለው ከሆነ ክወናውን በተቃውሞ ያስቆመዋል። ክወናው ትክክል ከሆነ በድጋፍ እንዲቀጥል በማድረግ ያጸድቅለታል። የሕዝብ ማጽደቅ ለከዋኙ የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማግኘት ነው። 

በድሬ ሼኽ ሁሴን የሚሰጠው የኡሌነት ማዕረግ በሕዝቡ ተሳትፎ፣ ፍላጎትና ዕውቅና መሰረት ነው። ይህ መሆኑ በአገራችን ከሚታወቁ ሌሎች የመንፈሳዊ ሙዚቃ ከዋኞች አንጻር ኡሌ የተለየ ባህርይ አለው።

በድሬ ሼኽ ሁሴን መካነ ቅርስ የኡሌነት ማዕረግ ማግኘት የሚችሉት ወንዶች ብቻ ናቸው። ሴቶች መንፈሳዊ ሙዚቃዎችን አይከውኑም። ማዕረጉም የሚሰጣቸው ሰዎች ከወጣት እስከ ሽምግልና የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው።

በተለያዩ ዘመኖች በድሬ ሼኽ ሁሴን መካነ ቅርስ ታዋቂና ተወዳጅ የሆኑ ኡሌዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ሱልጣን ጎሎልቻ የሚባሉት ከታዋቂ ኡሌዎች መካከል አንዱ ነበሩ። በደርግ ዘመነ መንግሥት ደግሞ ከዲር ወሌንሶ የተባሉት ኡሌ በጣም ታዋቂ ነበሩ።

በአሁኑ ወቅት ታዋቂ የሆኑ በርካታ ኡሌዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል ሀሰን ሙሳ፣ ኢብራሂም፣ ሲታ፣ መሃመድ አልይ፣ አደም፣ ነጋሽ፣ አሚን፣ ጀማል ሰሃባ፣ ሙሸመም፣ ሱሲና ሙስጠፋ በዋናነት ይጠቀሳሉ።

መንፈሳዊ ሙዚቃዎችን የሚያቀርቡ ኡሌዎች ይህንን ሙያ የሚለምዱበት መንገድ ይለያያል። የተወሰኑት ቀደም ሲል ከሚቀርቡ መንፈሳዊ ሙዚቃዎች ግጥሞችን በመስማት፣ የድምጽ አወጣጡን (ዜማውን) በመልመድ፣ ቅኝቱን በመለማመድ ነው። አብዛኛዎቹ ኡሌዎች ሼኽ ሁሴን ለኡሌነት ሲመርጧቸውና በኡሌነት እንዲያገለግሉ ሲያስገድዷቸው እንደሆነ ይታመናል።

መንፈሳዊ ሙዚቃዎችን የሚከውኑ ግለሰቦች ችሎታውን ከመለኮታዊ ኃይል እንደተሰጣቸው ማመናቸው በተለያዩ ሀይማኖቶች አስተምህሮ የተለመደ ነው። በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አስተምህሮ ቅዱስ ያሬድ የግዕዝ፣ የዕዝልና የአራራይ ጸዋትወ ዜማዎችን እግዚአብሔር በሦስት ወፎች አማካኝነት እንደነገረው ይታመናል። በተመሳሳይም ታዋቂው ሮማዊ ፖፕ ግሪጎሪ ዜማን ከወፍ እንደሰማ ይነገራል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top