አድባራተ ጥበብ

“ነገሮች ሲሳኩ ብቻ አይደለም ተመስገን የምለው፤ ሳይሳኩም ተመስገን እላለሁ።”

ከ1970ዎቹ ጀምሮ በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ውስጥ ቆይታለች። “እንኳን አደረሳችሁ” የተሰኘውን የበዓል አድማቂ ዜማዋን ጨምሮ ስደት፣ እርሳኝ፣ ጊዜ ሚዛን፣ ያደላል፣ ይዳኘኝ ያየ፣… በተሰኙት ተወዳጅ ዜማዎቿ ብዙዎች ያስታውሷታል። ከሙዚቃ ሥራዋ በተጨማሪ “አመል ፕሮዳክሽን” የተሰኘ ተቋም መስርታ ተንቀሳቅሳለች። የቅጂ መብትን ለማስከበር በተደረገ እንቅስቃሴ ላይም የጎላ ተሳትፎ ካደረጉት ድምጻዊያን መካከል ትጠቀሳለች። ድምጻዊት ሐመልማል አባተ በወቅታዊ ጉዳዮች እና በግል ሕይወቷ ዙሪያ ከጋዜጠኛ ነቢዩ ግርማ ጋር ቆይታ አድርጋለች። ቃለ መጠይቁ ለንባብ እንዲመች እንዲህ ተሰናድቷል።   

 • ከሰሞኑ እንጦጦ አካባቢ ለሚገኙ እናቶች የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) አበርክተሻል። ሐሳቡ እንዴት መጣ?

አንድ ጊዜ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን በተላለፈ ፕሮግራም ላይ እንጨት ከጫካ በመልቀም ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩ እናቶችን ሕይወት ለማሳየት ሞክረን ነበር። እና እስቲ አሁን ያለው ሁኔታ እንዴት ነው የሚለውን ነገር በማሰብ ሄጄ ነበር። ስሄድ በጣም በሚገርምህ መልኩ ልጆቻቸውም ሆነ እነሱ ማስክ የሚባል ነገር የላቸውም። እንዲያውም በዛን ጊዜ በኢቢኤስ የበዓል ፕሮግራም የሰጠናቸው ስጦታ ጠላት ሆኖባቸዋል። ብዙዎቹ የሚኖሩት ተከራይተው ነበር። ለእርዳታ የተሰራላቸውን ኩሽና ከእነሱ ለማስቀረት አከራዮቻቸው ከቤት እንዳስወጧቸው ነው የነገሩኝ። በጣም ብዙ ድርጅት እንደሚመጡ እና በቪድዮ ቀርፃዋቸው ብቻ እንደሚሄዱ፤ ምንም ነገር እንዳልተደረገላቸው፤… ነገሩኝ። በአንዳንድ ኤንጂኦዎችም ሚዲያዎችም እንደታዘብኩት በችግራቸው ማትረፍ ነው እየታየ ያለው እንጂ፤ ሰዎቹ በትክክል ተጠቅመዋል የሚለው እያስተዋልነው አይደለም። እና አሁን በዚህ ጊዜ ድርብ ጦርነት ነው እንግዲህ፤ ከችግራቸው ጋራ ወረረሽኙ ሲደረብ… አዘንኩ። ከዚያ ሦስት መቶ ለሚሆኑት ማስክ ሰርቼ ሰጠኋቸው።

ስለኮሮና ምንም ነገር አያውቁም። ማስክ ለምን ያገለግላል ስላቸው ራሱ መረጃ የላቸውም። በዛውም የማውቀውን አስተምሬ ተመለስኩ።

ብዙዎቹ እናቶች ህይወታቸው ከባድ ነው። ተሸክመው ያመጡትን ይቀሟቸዋል። እዛው ጫካ ውስጥ ይደፍሯቸዋል። አውሬ አለ። “ጅብ አትፈሩም ወይ?” ብዬ ስጠይቃቸው “እኛ የምንፈራው ሰው ነው” ይሉኛል።

 • ከዚያ ቀደም ብለሽ ደግሞ ቤትሽን ለማቆያ እንዲሆን ሰጥተሻል። እሱንስ እንዴት አሰብሽው?

የልጄ ጓደኛ አሜሪካን ተጉዞ ሲመለስ ኳራንቲን ገብቶ ነበር። ለሁላችንም ይሄ ነገር አዲስ ነው። ለዓለምም አዲስ ነው። መጀመሪያ ያሳረፏቸው ቦሌ ትምህርት ቤት አካባቢ ነበር። እና ለልጄ ያለበትን ሁኔታ ልኮላት ዐየሁ። ከዚያ ቢያንስ ይሄ መታጠቢያ ቤትም፣ መጸዳጃም አለው፣ ንጹህ ነው፣ ከዚያ ይሻላል ብዬ ለመስጠት ወሰንኩ። ምክንያቱም ይሄ በጣም ከባድ ያልታወቀ ነገር ነው ዐይተነው ሰምተነው የማናውቀው ጦርነት ነው። ያለህን ነገር ምንም ቢሆን መስጠት ነው። ለምን ከተባለ፤ አንተ ከዳንክ ነው እኔ የምድነው እኔ ከዳንኩ ነው አንተ የምትድነው።

 • አንቺስ ራስሽን እንዴት ነው እምትጠብቂው?

በተቻለ መጠን ከቤት አልወጣም። መውጣት ካለብኝ ደግሞ እንዳየኸኝ ማስኬን አድርጌ፣ መኪናዬ ውስጥ ብዙ ‘ሳኒታይዘር’ አለ። ወንበሩ ሁሉ እየፈሰሰ ተበላሽቷል። ሳኒታይዘር፣ እጄን በመታጠብ፣…

 • ሳሎንሽም ስፖርት ቤት እየመሰለ ነው

አዎ ፍራሼም እዚህ ጋር መጥቷል። እኔም አንተምኮ ልክ እንደ ሀኪሞቹ ጦር ሜዳ ላይ ነን። ጦርነት ውስጥ ነን። እና በተቻለ መጠን ራሴን እጠብቃለሁ። ሆስፒታል ከመሄድ ጥንቃቄው ላይ ብንሰራ በጣም ይሻላል። በተቻለ መጠን ርቀቴን እጠብቃለሁ። ሳኒታይዘር እጠቀማለሁ። እሱ ነው ዋናው ነገር። ርቀትህን ከጠበቅክ፣ ማስክህን ካደረክ፣ እጅ መታጠብ ደግሞ ለዘላለም መቀጠል ያለበት ነገር ነው።

 • አሁንም እያወራን ያለነው ከሁለት ሜትር በላይ ተራርቀን ነው። በተጨማሪም ከራስ ጋር ለመገናኘትም እድል ይሰጣል::

ልክ ነው። እስከዛሬ የኖርኩት ለእኔ ነበረ፣ ለሰው ነበረ፣ በእውነት ነበረ፣ በይሉኝታ ነበረ፣ እያልክ በጣም ብዙ የምታስተውልበትም ጊዜ ነው። ለራሳችን ጊዜ ሰጥተን አናውቅም። ዝም ብለን በሚረባውም በማይረባውም ስንበር ነው የምንውለው፤… ብዙ ባልና ሚስት አይተዋወቅም ይሄ እንዳዲስ የመተዋወቂያ ጊዜ ሊሆናቸው ይችላል።

 • የህዝቡንስ ጥንቃቄ እንዴት አገኘሽው?

አሁን ተዝረክርከናል። መጀመሪያ የነበረው ጥንቃቄ የለም። አንዳንድ ቦታዎች አርቲስቶች ሲነግሩኝ ሙዚቃ ተከፍቶ በደንብ ጭፈራ እንዳለ ነግረውኛል። እና ይሄ ልክ አይደለም። መጠጥ ያዘናጋል። በዚህ ጊዜ ሁሉም ስራ ተጎድቷል፤ ነገር ግን በተቻለ መጠን ሌላ ሰውን የምንጎዳበትን መንገድ ባናደርግ ጥሩ ነው።  

 • በሚድያዎች የሚተላለፉት የማስጠንቀቂያ መልእክቶችስ?

ታዋቂ፣ አዋቂ የምትላቸው አርቲስቶች የሰሩት ነገር ‘ሶሻል ዲስታንሲንግ’ የለውም። በዚህ መልእክት ምን ዓይነት ነገር ነው ለሕብረተሰቡ የምናስተላልፈው? ተቃቅፈው ፎቶ የተነሱ ሁሉ አሉ። እኔም እንዲሁ ስንሰራ አንዳንድ ቦታ ብዙ ያጋጠመኝ ነገር አለ።

መሰራቱ ባልከፋ፤ ለምን ቢባል ሰው በሙዚቃ ሲሰማ እና ዝም ብሎ ስትጨቀጭቀውም አንድ አይደለም። ጥሩ መልእክት ካለው ጥሩ ነው ግን… አንዳንዴ አግላይ መልእክቶች ይተላለፋሉ። በድራማ ሰርተህ የባሰ ነገሩን ማቅለል ልክ አይደለም። በጣም መጠንቀቅ አለብን፣ ለቃላቶቻችን መጠንቀቅ አለብን።

 • ከኮሮና ጋር ተያይዞ ከሰሞኑን እየሰማነው የምንገኘው የሴቶችን ጥቃት ነው እሱ ላይስ ምን ትያለሽ?

በውጭው ዓለም ተመሳሳይ ወንጀል የፈጸመ ሰው እስርቤት ብቻ ቁጭ አይልም። የተለየ ልብስ አላቸው። ደማቅ ልብስ፤ እና ወጥቶ ጽዳት ያጸዳል። ሰው ያለበት ቦታ ላይ ሲያጸዳ ታየዋለህ። መልኩን ታየዋለህ። እንዲያፍር፣ ሰውም ዐየይቶት እንዲጠነቀቅ፣… የሚያደርጉት ነገር ነው። ትምህርትም ያስተምሯቸዋል። በሽታ ስለሆነ ጥብቅ ክትትል የሚፈልግ ነገር ነው ብዬ ነው የማምነው።… አርቲስቱም በዚህ ነገር ላይ መስራት አለበት።  

 • ወደ ሥራዎችሽ እንለፍና ከዚህ ቀደም እንዲህ ላለ የማኅበራዊ ጉዳይ የሰራሻቸው ካሉ እናንሳቸው።

ለምሳሌ ድሮ

አያ ዘመናዩ አያ ዘመናይ

እስኪ ልጠይቅህ እስኪ በለኝ ወይ

ማማር መልበስ መድመቅ መከበር በሀገር አይደለም ወይ

እንዲህ እንዲህ ያሉ በጣም ብዙ ስራዎች ሰርቻለሁ። እነ ስደት፣ እነ ጊዜ ሚዛን፣ በጣም በጣም የሚገርሙ ናቸው። የ“ጊዜ ሚዛን” ሐሳብ የትም ብትሄድ ከጊዜ አታመልጥም ነው። ከሰው ታመልጣለህ፣ ከዳኛ ታመልጣለህ፣ ከሐገር ታመልጣለህ፣… ከጊዜ ግን አታመልጥም። 

እንግዲህ የዐይንም ጊዜ ሆኗል። ክሊፕ ራሱ እንደ አዲስ ልሰራላቸው የምፈልጋቸው ዘፈኖች አሉ።

አሁን ይሄ አዲሱ ቅምሻ ላይ ደግሞ ሐገራችን ያለችበትን ሁኔታ ያገናዘበ፣ ለምሳሌ “ተው ስማኝ” የሚለው በክልሎች የነበረውን ነገር ያነሳል። በብዛት ቁምነገር ያላቸው ነገሮች ናቸው። በእኔ እድሜ ደግሞ እንደዚህ ያለ ሐገርን የሚጠቅም ቁምነገር ያለው ነገር፣… ድሮውንም እኔ ግጥም ዝም ብዬ ወስጄ አልሰራም። በተቻለ መጠን አስተካክለዋለሁ።

 • በ1977 ዓ.ም. የተሰራው “የብሩህ ተስፋ እሸት” ላይ አለሽበት። ይህም ከማኅበራዊ አበርክቶ ሊቆጠር ይችላል።

ያኔ የፈለጋችሁትን ዘፈን ምረጡ ግን ለዚህ ነገር አበርክቱ ተብሎ ነው “የብሩህ ተስፋ እሸት” የተሰራው። በዚያን ጊዜ ብዙ ተነጋገርንበት። የአብዮት ዘፈን ይሁን… ምናምን ተባለ። እና ያለውን ሁሉም እያመጣ የተሰራ ስራ ነው።

ሰዉ ጥሩ ዜማ ጥሩ ሙዚቃ መስማትም ይፈልጋል፤ እኔ “ገዳማይ” የሚል ዘፈን ነው የሰራሁት። በጣም ውጤታማ ነበረ።

ገዳም ገደምዳማይ ገዳም ገደምዳማይ

ያንተው አይደለም ወይ የልቤ አደባባይ

ሁሉም አርቲስት ያመጣው ስራ የሚገራርም ነበር። እና ተሸጠ። እንዲህ እንዲህ ያሉ ነገሮች ገንዘብም ሊያመጡ የሚችሉ ነገሮች ናቸው።

 • “የብሩህ ተስፋ እሸት” 30 ዓመት አልፎትም እያወራንለት ነው። ዘመኑንም ያስታውሳል፣ ታሪክ አስቀርቷል፣ ገንዘብም አስገብቶ ነበር።

አዎ ሰዉኮ ትንሽ ወጣ ማለትም ይፈልጋል። ጭንቅላት በጣም ከባድ ነገር ነው። እዚያ ላይ ‘ስታክ’ አድርገን ከቀረን አንደመጥም።

አገራችን በጣም ችግር ውስጥ ነች። በዓባይ ግድብ ብትል፣ በዚህ በኮሮና፣ ብዙ ጦርነት ውስጥ ናት።

 • ሙዚቃ ቢዝነስም ነው። ማኅበራዊ የሚለውን ይዞ ለችግሩም የገንዘብ ድጋፍ ማበርከት ይቻላል።

እያንዳንዳችን በየቤታችን ቀርጸን ብናሰባስብ፣ በየክልሉ ቢላክ፣ ዝም ብለህ ሰውን ፍራንክ አምጣ ከምትለው ይሄን ግዛ ብትለው ጥሩ ይመስለኛል።

 • ለማኅበራዊ አገልግሎት ተሰርተው ከምታስታውሻቸው ውስጥ ጥቂቶቹን ንገሪኝ እስኪ

በጣም ብዙ ናቸው። ጥላሁን ገሰሰ ለምሳሌ “ዋይ ወይ ሲሉ”ን ሲሰራው ለመስራት ብቻ አይደለም የሰራው። ውስጡ ሆኖ ነው የሰራው። ውስጡ ሆኖ እያለቀሰ ነው የሰራው፤ ምክንያቱም ዐይቷቸዋል ሄዶ፣ በዐይኔ ዐይቼ ነው የሚለው። አርት ደግሞ እንደዚያ ነው። ዝም ብለህ ስትለውና ውስጥህ ሲሆን በጣም ይለያያል። ለመስራት ብለህ ስትሰራና ውስጥህ ሆኖ ስትሰራው በጣም ይለያያል።

እኔ ልጅ ሆኜ አሰበ ተፈሪ መጥቶ ትምህርት ቤት ውስጥ “ዋይ ዋይ ሲሉን” ሲዘፍን ሁሉም ሰው ያለቅስ ነበር። እንዲህ ዓይነት ስሜት የሚሰጥህ ነገር፣ ህመምህን የሚነካ ነገር እሱ አንድ ምሳሌ ነው።

ቅርብ ጊዜ ከተሰሩት ደግሞ እሱባለው የሰራው አለ “እናልፈዋለን” የሚለው፤ እናልፈዋለን ግን ተጋግዘን ነው። መተጋገዝ ግድ ይላል። በዚህ በኮረና የወጡትም በጣም ብዙ ናቸው…

 • ዛሬ ላይ ሆነሽ ነገን ስታስቢው ምን ይታይሻል?

እኔ ጥያቄ ነው ያለኝ። ዓለም ከዚህ በኋላ እንደነበረ ይቀጥል ወይ ብዬ አስባለሁ። ተስፋም ይታየኛል። ለሐገራችንም ተስፋ ይታየኛል። ሁሌ እኔ ‘ፖዘቲቭ’ ነው የማስበው። ተስፋ የቆረጥክ ዕለት ነው ችግሩ… እኔ ተስፋ ይታየኛል። ያለንን ጉልበት በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ አድርገን የምናወራበት ቢሆን ተስፋ አለ ብዬ ነው የማስበው።

ውጭ ሐገር መጦሪያ ውስጥ የገቡ ሰዎች የሚሉትን ልንግርህ። በኋላ እንኖራለን ብለው ሰርተው ሰውተው አሁን ጡረታ ላይ ሲሆኑ የሚሉት በዚያን ጊዜ በኖርኩኝ ኖሮ ነው። ስለዚህ መኖር ለሚገባን ነገር መኖር እንዳለብን ነው ያየሁት። አንዳንድ ጊዜ የበዛ ነገሮች እናደርጋለን። እውነት ጊዜ እሰጥ የነበረው ለልጆቼ ነበረ ወይ? ለባለቤቴ ነበረ ወይ? ለሚገባው ነገር ነው ወይ? እንድትል ያደርግሃል።

 • ሙዚቀኛ በመሆንሽ ብቻ ያጣሽው ነገር ምንድነው?

ድምጻዊ በመሆኔ ያጣሁት ነገር የለም። እንደውም ያገኘሁት ብዙ ነው። ግን… አንዳንዴ ለመናገር እየፈለግክ የማትናገርበት ጊዜ አለ። እንደልብህ አትናገርም፤ ሕዝቡን በማክበር ዝም የምትለው ነገር አለ። እሱ ግን ዘፋኝ ሳልሆን በሌላ ነገር ታዋቂ ብሆንም የሚመጣ ነገር ነው።

 • ምን ቀን ነው ዘፋኝ የሆንኩት ብለሽ ታውቂያለሽ?

እኔ ነገሮች ሲሳኩ ብቻ አይደለም ተመስገን የምለው፤ ሳይሳኩም ተመስገን እላለሁ። ከሆነም ለበጎ ነው ካልሆነም ለበጎ ነው ብዬ ነው የምወስደው። አላማርርም።

 • ከአጠገብሽ እንዲርቁ የማትፈልጊያቸው ነገሮች

ቤተሰቦቼን፣ ምቾቴን፣ ሙዚቃዬን፣ ወገኖቼን፣ አገሬን እንዳጣቸው አልፈልግም።

 • ለአንድ ድምጻዊ ስኬት ቀዳሚው ነገር ምንድነው?

ዲሲፕሊን፤ በዚህ አጋጣሚ ሮሃ ባንድን በጣም ነው የማመሰግነው። ሙያው ኢንደስትሪው ከባድ ነው። እያሳሳቀ ነው የሚወስድህ። ጠንካራ ካልሆንክ ችግር ነው። እኔ ለምሳሌ ከሀረር ነው የመጣሁት። ሕይወት እንደለመድኩት ቀላል ነው የመሰለኝ።

የሥራ ዲሲፕሊን፣ የገንዘብ አያያዝ፣… ከእነሱ ነው የተማርኩት። እነሱ ‘ሼር’ ሆነው እንኳን ይከባበሩ ነበረ። አንድ ሰው ከስራው ካረፈደ አለምንም ንግግር፣ አለአንድም ቃል ይቀጡት ነበር። “ይሄም አለ እንዴ?” ትላለህ።

አሁን ድረስ የጠቀመኝ የሮሃ ባንድ የስራ ዲሲፕሊን ነው። ኮንሰርት ኖረ አልኖረ በሳምንት ሦስት ቀን ተገናኝተን ልምምድ ማድረግ ግዴታ ነበር። ስራዎች ይቀያየራሉ። አዳዲስ ዘፈኖች በየጊዜው ይኖራሉ።

ሥራው ከተሰራ ገንዘብ ይመጣል። ገንዘብ ላይ ከሮጥን ግን አስቸጋሪ ነው። በርግጥ አሁን ኑሮውም አስቸጋሪ ነው።

 • በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ስትሰሚው ደስ የሚልሽ ዘፈን ወይም ድምጻዊ ማን ነው?

በየትኛውም ጊዜ?

 • አዎ የትም መቼም ብትሰሚው ቅር የማይልሽ

ከባድ ጥያቄ ነው። በጣም ብዙ አሉ። ደስ የሚለኝ… እ… ጎሳዬ ይሁን በቃ! እንዳልኩህ ብዙ ናቸው። ሙሉቀን የኔ አንደኛ ነው።

 • አብረሽው ብትሰሪ ደስ የሚልሽ ድምጻዊስ?

ሙሉቀን መለሰን በጣም ነው የምወደው። አሁን እሱ ያመነበት ነገር ላይ ነው አብሬው ብሰራ ግን ደስ ይለኝ ነበር። ከውጭ ሐገር እንደመጣሁ ጥቂት ጊዜ አብሬው ሰርቼ ነበር።

 • ከሙዚቃ ቀጥሎ የምትወጂው ነገር…

‘ዲዛይኒንግ’ እና ‘ጋርደኒንግ’ እወዳለሁ። አትክልቶቼ ማዳበሪያ ራሴ ነኝ እምሰራው። ብስባሽ ሰብስቤ፣ መሬት ውስጥ ቀብሬ፣… ማዳበሪያ አዘጋጃለሁ። ይሄ ኮሮና ደግሞ ብዙ አስተምሮናል። ቁጭ ስል ጎግል አድርጌ የማየው ምን እንዴት እንደሚበቅል ነው። አሁን ክረምት ሲመጣ የራሴን ጎመን የራሴን ቲማቲም ነው የምበላው። ማብሰልም እወዳለሁ።

 • በተለየ የምትመርጪው መድረክ (ክለብ)

ከትልልቅ አዳራሽ ይልቅ መድረኩ በጣም ከፍ ያላለ፣ አነስ ብሎ የሚያምር፣ ከህዝብ ጋር የሚያገናኝ ቢሆን ደስ ይለኛል።

 • የሚጎረብጥሽ የሙዚቃ ስልት አለ?

የማይመቸኝ ሙዚቃ የለም። በሙዚቃ ሰውን፣ አገርን የሚጎዳ ነገር ሲመጣ፣ በሙዚቃ ሰው ሲገዳደል፣… አይመቸኝም። በተረፈ ስልት አልመርጥም። ትውልድ ይቀየራል የድሮው ብቻ ካልሆነ አልልም። ስራው ላይ ጥራት፣ ብስለት ቢኖረው ደስ ይለኛል።

 • ከዜማ እና ከግጥም የትኛውን ታስቀድሚያለሽ?

ግጥም ነው የማስቀድመው። ጥሩ ዜማ ተሰርቶ ግጥሙ ጥሩ ካልሆነ ዘፈኑ ይወድቃል። ጥሩ ግጥም ከመጣልኝ ግን ዜማውን ራሴም እሰራዋለሁ። እዚህ ማኅበረሰብ ውስጥ ስትሆን ስለ መልእክቱ ማስብ አለብህ። ሁለቱ ደግሞ አብሮ ሲፈጠር በጣም ቆንጆ ነው። ግጥም ከሌላ ሰው ወስደህ ዜማ ሌላ ሰው ሲሰራ በጣም ይለያል። ድሮ አበበ መለሰ እና ይልማ ገብረአብ ቁጭ ብለው ሲሰሩ ይገርምሃል፤ ሁለቱም እዚያው ነው የሚፈጠረው፣ አብሮ ነው የሚፈጠረው። አሁን ሞገስ ተካ የሚገርም ደራሲ ነው በእውነት። ዜማም ግጥምም ሲሰራ ጎበዝ ነው።

እኔ ድሮ አንድ ሰው ግጥም ሰጠኝና ዜማ ራሴ እሰራበታለሁ ችግር የለም ብዬ ወደ 10 የሚሆነውን ዜማ ራሴ ሰራሁት። “እንካ ጥቅሻ” የሚለው አልበም ላይ፤ ያ ስህተት ነበር። በአንዴ ከስህተቴ ተማርኩ። ሞያውን ለባለሙያ መተው አለብኝ።

የኤፍሬም ታምሩ “ገዳም እንደገባ” የኔ ድርሰት ነው። ግን በዚያን ጊዜ ያቺን ሰራሁና አሪፍ ነኝ ልል አልችልም። ግጥሙ የይልማ ነው መሰለኝ እርግጠኛ አይደለሁም። እኔ ነገሩም ስላልገባኝ ክሬዲት አልወሰድኩም እንጂ መአት የራሴ ድርሰቶች አሉ።

 • ለሰጠሸኝ ሰፊ ጊዜ፣ ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ!

እኔም አንተን አመሰግናለሁ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top