ጥበብ በታሪክ ገፅ

ነገረ-ሳንሱር ወሙዚቃ

ሳንሱር የትም አለ። መልኩ ይቀየር፣ ሁኔታው ይለያይ ይሆናል እንጂ ሳንሱር ያልነበረበት የዓለም ጥግ ማግኘት ይከብዳል። ዛሬም ቢሆን የለም ማለት አይቻልም። ከዘመን ጋር እየዘመነ፣ ገጹን እንደ እስስት እየቀያየረ፤ ጊዜን እና ስልጣኔን መስሎ ይኖራል። ስለ ታሪክ ሲነሳ- “ታሪክ የአሸናፊዎች ድርሰት ነው” ሲባል እንደምንሰማው ሁሉ፤ ሳንሱር ደግሞ የአሸናፊዎቹ በትር ሆኖ የኖረ መሳሪያ ነው። በዚህ መሳሪያ ብዙዎች ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። በተለይ የኪነቱ ዓለም ሰዎች ቀዳሚዎቹ ገፈት ቀማሽ ናቸው። በሳንሱር መቀስ እየተከረከሙ ከተሽቀነጠሩ ስራዎቻቸው፤ ህይወታቸውን ለአደጋ እስከማጋለጥ የደረሱ አያሌዎች ናቸውና።

ሳንሱር ሲባል?

አንዳንድ ሰዎች ሳንሱርን በተዛባና በተሳሳተ መንገድ ሲረዱት አልፎ አልፎ እንሰማለን። ግምገማን፣ አርትኦትንና ሂስን እንደ ሳንሱር በመቁጠር “ስራዬ ሳንሱር ተደረገብኝ” የሚሉ ሰዎች ወይም ተቋማት ያጋጥማሉ። ይህ በመሰረቱ ትክክል አይደለም። የአንድን ስራ ኪነ-ጥበባዊ ለዛና ከፍታ ለማስጠበቅ ሲባል የሚደረግ ሙያዊ ግምገማና ሂስ ፈጽሞ ሳንሱር ነው ማለት ተገቢ አይደለም።

ሳንሱር ስለ ኪናዊ ውበትና ከፍታ ቅንጣት ደንታ የለውም። ውግናውም ለጥበብ አይደለም። የሳንሱር ዝምድና ከአሸናፊዎቹ ነው። ለቆመለት ገዢ ወይም ተቋም የተሰመረ ቀይ መስመር ነው። ለገዢው ወይም ለተቋሙ ያልተመቹትን ቆርጦ ይጥላል፣ የሚመቹትን ይቀጥላል። ካልጣመውም ይወረውራል። የጸሐፊያንን፣ የሙዚቀኞችን፣… ስራ ይመረምራል። ይበረብራል። መንግሥት ወይም ሳንሱር አስደራጊው ተቋም፣ ለመንግሥቴ፣ ለአገዛዜ፣ ለአስተዳደሬ አይመችም፤ ህዝብን ያሳስታል፣ ያሳምጻል፣ ወዘተ ብሎ ያመነበትን ስራ ያግዳል። ይከለክላል።

የሳንሱር ሕግ የተጻፈም ያልተጻፈም ሊሆን ይችላል። አንዱ ሕግ ተረቅቆለት አንቀጽ ተጠቅሶ የሚያስቀጣ ሲሆን፤ ሌላው በልማድ፣ በማኅበረሰቡ ይታወቃል።

የዓለም ቋንቋ ነው የሚባልለት ሙዚቃ በሳንሱር ምክንያት አበሳውን ያየ ጥበብ ነው። በግጥሞቹ በሚያነሳቸው ሀሳቦች ህዝብን አሳስተሀል፣ መንግሥታትን ተቃውመሀል፣ እምነትን ነክተሀል፣… እየተባለ በየማዕዘናቱ  ስራዎች ሲቃጠሉ፣ ድምጻውያን ሲሳደዱ ተኖሯል።

ወደ ምዕራባውያን

ዛሬ የዓለም ዲሞክራሲ ምስክሮች ነን፣ ከኛም በላይ ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ ነጻነት የቆመ የለም የሚሉት ኃያላን ሀገራትም ቢሆኑ በዚህ ቆርጦ የመቀጠል የሳንሱር ተግባር ውስጥ አልፈውበታል። በአውሮፓ እንደ ጀርመን ባሉ ሀገራት ገና ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በይፋ ሲሰሩበት እንደነበር እንዳለጌታ ከበደ ማዕቀብ በተሰኘ መጽሐፉ ይገልጸዋል። በሩሲያ፣ በአሜሪካና በሌሎችም ሀገራት ሳንሱር ሕግ ሆኖ አያሌ ፈጠራዎችን ሲያግድ፣ ሲከለክል የኖረ ስውር የመንግሥታቱ መሳሪያ ነበር። የሩቁን ትተን የ20ኛውን ክፍለ ዘመን የከያኒያን ውጣ ውረድ እንኳ ጥቂት ብንመለከት እነሱ ከእኛ እኛም ከነሱ የተለየ ታሪክ እንደሌለን የሚያስገነዝበን ይመስለኛል።

እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1952 በአሜሪካ ዘዊቨርስ (The Weavers) የተባለ ሀገር በቀል ባንድ በሚያቀርባቸው ግራ ዘመም የፖለቲካ መልክቶቹ ምክንያት፤ ባንዱ ዝናው እንዲቀንስና እንዲከስም የአሜሪካ መንግስት ሲሰራ እንደነበር ታሪክ ምስክር ሆኗል። ባስ ሲልም ባንዱ በሀገሪቱ ጥቁር መዝገብ (blacklist) ውስጥ እስከመካተትም ተደርሶ ነበር።  በ1950ዎቹ ውስጥ ደግሞ የአላባማ ሬዲዮ ጣቢያ የአር ኤንድ ቢ(R&B) የሙዚቃ ስልት ያላቸውን ዘፈኖች እንደማያስተላልፍ አስታውቆ ነበር። ተወዳጁ ድምጻዊ ኤልቪስ ፕሪስሊ ደግሞ መንግሥት “አላስፈላጊ” ያላቸውን መልክቶች መዝፈንህን ካላቆምክ በሚል ሰበብ ተደጋጋሚ የእስር ዛቻዎች፤ በተለይም ከፍሎሪዳ ፖሊስ ይደርሱት ነበር። ጀምስ ብራውንም በአንድ ኮንሰርቱ ላይ “ጸያፍ” ዳንስ አሳይተሀል በሚል እዛው ኮንሰርቱ ላይ ፖሊስ አቋርጦታል።

ኤልቪስ ፕሪስሊ

ጠንካራ ምት ያላቸው የሙዚቃ ስልቶች በተለይም ከጥቂሮች የሙዚቃ ስልት ጋር በተያያዘ ብዙ ብዙ ተብሏል። አውሬነትን ለህዝቡ እያስተማሩ ነው ከማለት ጀምሮ የጥቁሮች ሙዚቃ እንዲታገድ የጠየቁ ተቋማትም ነበሩ።

ጆን ሌነን (John Lennon) የተባለው እውቅ እንግሊዛዊ ሙዚቀኛ በግሪጎሪያኑ 1966 ዘ ቢትልስ (The Beatles) ስለተባለው ዝነኛ ባንድ፤ በአንድ ቃለ-መጠይቅ ላይ ሲናገር “ባንዱ ከእየሱስ ክርስቶስ በላይ ዝነኛ እየሆነ መጥቷል” በማለቱ በርካቶች ባንዱ ይታገድ ሲሉ አደባባይ ወጥተዋል። ሃያ ሁለት ሬዲዮ ጣቢያዎች የቢትልሶችን ሙዚቃ ከማጫወት ተቆጥበዋል። አንዳንድ ቤተክርስቲያኖች የባንዱን ስራዎች እንዲቃጠሉ፣ የእምነቱ ሰዎችም ሙዚቃቸውን ሲሰማ የተገኘ እንዲወገዝ ሲሉ ጽኑ ተቃውሟቸውን አሳይተዋል።

ኢትዮጵያ

በሀገራችን ሳንሱር በሕግ ታውቆ በይፋ የተሰራበት ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን ወዲህ ቢሆንም ተግባሩ ግን ድሮውንም ነበረ። ከጥንት ጀምሮ በመዝፈናቸው የተቀጡ፣ ሰሚያቸውን ስላላስደሰቱ ብቻ ዋጋ የከፈሉ አዝማሪዎች ብዙ ናቸው። ቀጣዩ ዝነኛ ታሪክ የጥንቱን የሳንሱር በትር በሚገባ ያስተዋውቀናል። ነገሩ እንዲህ ነው።

የቋራው መይሳው ካሳ፤ “አጼ ቴዎድሮስ” ተብለው ከመንገሳቸው በፊት- ከብዙ ነገሥታት ጋር እየተዋጉ ሁሉን ለማስገበር ቆርጠው ይነሳሉ። ነገሩን የሰሙ ነገሥታት የመሸበራቸውን ያህል ታዲያ፤ “የት ሊደርስ” በማለት አናንቀው የገመቱም ነበሩ። ይህን ያጤነው የደጃች ጎሹ አዝማሪ ታዲያ “የካሳ ህልም ህልም ብቻ ነው” ብሎ አምኖ ይመስላል፤ እንዲህ ሲል ተሰማ፡-

ዐያችሁት ቢያ የእኛን እብድ፣

አምስቱን ጋሞች ይዞ ጉራምባ ሲወርድ፣

ያንጓብባል እንጂ አይዋጋም ካሳ፣

ወርደህ ጥመድበት በሽንብራው ማሳ።

ውጤቱ ግን ያልታሰበው ሆነ። ደጃች ጎሹ በጦርነቱ ተረቱ። የአዝማሪው ነገር የከነከናቸው አጼ ቴዎድሮስም ታዲያ፤ ደጃች ጎሹን ጉራምባ ላይ ድል እንዳደረጉ፤ አዝማሪውን ፊታቸው እንዲቀርብ አስደረጉና፤ “በል እንደሰደብከኝ መጠን የሚገባህን ፍርድ በራስህ ፍረድ” አሉት። የጨነቀው አዝማሪም መቼም ጨክነው እንደማይጨክኑበት በማሰብ ይመስላል፤

አወይ ያምላክ ቁጣ አወይ የእግዜር ቁጣ፣

አፍ ወዳጁን ያማል የሚሰራው ሲያጣ፣

ፍልጥ ይገባዋል የአዝማሪ ቀልባጣ።

በማለት በራሱ ፈረደ። ሰውዬው ግን የዋዛ አልነበሩምና አዝማሪው በፍልጥ ተደብድቦ ሞተ። እንደ ብዙዎቹ የዘመኑ ከያኒያንም የሳንሱርን ጽዋ በአደባባይ ተጎነጨ።

ታሪካችን ለሙገሳ እንጂ ለነቀፋ ቀጭን እንኳን መንገድ ያለው አይመስልም። ጥቂት ማፈንገጥ እንዲህ ላለ ቅጣት ይዳርጋል። ነገስታቱ ዘፈን ቢወዱም፤ በዘፈን ቅኔ ጠላታቸው ሲሸነቆጥ አንጀታቸው ቅቤ ቢጠጣም፤ በፌሽታ ለሽልማት ቢነሱም፣ ራሳቸው የተነኩ ዕለት ግን ወዮ ለዛ አዝማሪ። በርካታ መሰል ታሪኮች የሙዚቃ ታሪካችን የዘመናት እውነታዎች ናቸው።

ወራሪው ጣሊያን

በአምስቱ ዓመታት የጣሊያን ወረራ ወቅት በርካታ አዝማሪዎች ጣሊያኖችን ተሳድባችኋል፣ ህዝቡን ለአመጽ ቀስቅሳችኋል፣… እየተባሉ በአደባባይ ተደብድበዋል፣ ተገድለዋል። በተቃራኒው ደግሞ ጣሊያኖቹ ለፕሮፓጋንዳቸው የሚጠቅማቸውን ዘፈን አዝማሪዎችን እያስገደዱ አዘፍነዋል። በአምስት ዓመታት ቆይታቸውም ከ200 በላይ የአዝማሪ ሸክላዎችን አስቀርጸው ለህዝብ ጆሮ አድርሰዋል። ይሁንና ዘፈኖቹ ለጣሊያኖቹ የተዘፈኑ ቢመስሉም፤ ብዙዎቹ በቅኔ ለበስ መልክታቸው ለሀገራቸው የሚታገሉ ነበሩና የታለመውን ግብ መምታት ተሳናቸው።

በዚህ ዘመን ለአዝማሪዎች ክልክል ከሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዱ የኢትዮጵያንና የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ስም እየጠሩ መዝፈንና በስማቸው መማል ነበር። ታዲያ በዚህ ጊዜ አንድ አዝማሪ አፍ ያመልጠውና “ኃይለሥላሴ ይሙት” ብሎ ሲምል ይያዝና ጣሊያኖቹ ፊት ይቀርባል። ጣሊያኖቹም አይቀጡ ቅጣት ሊቀጡት ተዘጋጅተው “ለምን እንዲህ አደረክ?” ቢሉት… አዝማሪው “እኔ ኃይለሥላሴ ይሙት አልኩ እንጂ መች ይኑር አልኩ” በማለት የብልጠት መልስ ሰጠ። ጣሊያኖቹም በመገረም “እውነትም ይሙት አለ እንጂ መች ይኑር አለ” ብለው በደስታ ለቀቁት።

የጥላሁን ነገር

ጥላሁን ገሠሠ ብዙ ዘፈኖችን የተጫወተ ድምጻዊ እንደመሆኑ፤ አያሌ ፖለቲካዊ ጉዳዮችም በዘፈኑ ውስጥ ተነስተዋል። ገጣሚዎቹ አስበውበትም ይሁን ያጋጣሚ ነገር በርከት ያሉ ስራዎቹ ከሳንሱር ተፋጠዋል። ከዚያም ሾልከው የወጡት ፖለቲከኞችን አስቆጥተዋል። ብዙ የተነገረላቸውን የታህሳስ ግርግሮቹን እንደ አልቻልኩም፣ ኡኡታ አያስከፋም ያሉትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ዘፈኖቹ የሳንሱር ጥላ ያረፈባቸው ናቸው። ውሻ አሳድጋለሁ፣ ዘንድሮ፣ አንድ ቀን፣ የፈርፈር ሽቶ፣ እሁድ በአስር፣ ፈልጌ አስፈልጌ፣ ሞናሊዛ እና ሌሎችም ዘፈኖቹ በሳንሱር ተከርክመውና በባለስልጣናት ግልምጫ ለትውልድ ከተሻገሩ ስራዎቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። በሳንሱር ምክንያት ንባብ አያግኛቸው ተብለው፤ ከየገበያው ተለቅመው እንደሚቃጠሉት መጽሐፍት ሁሉ፤ ጆሮ አይስማቸው ተብለው የተቃጠሉ የሙዚቃ ስራዎችም በርካቶች ናቸው። ከዚህ ጎራ የጥላሁን ገሰሰ ስራዎችንም እናገኛለን። “ያልዘፈነው የለም” የምንለው ጥላሁን- ምናልባት ያልዘፈነው ርዕሰ ጉዳይ አለ ካልንም ቀጣዮቹ ስራዎቹን ከግምት ውስጥ አስገብተን መሆን አለበት።

አልተግባባንም

ይህ ዘፈን በ1968 ዓ.ም. በሬምቦ ባንድ አጃቢነት የተሰራ ሸክላ ሲሆን በግልባጩ “ጤንነቴ” የሚል ዘፈንም ነበረው። ዘፈኑ በጊዜው የሳንሱር ሂደትን አልፎ የተሰራ ቢሆንም፤ ገና ለገበያ መቅረብ እንደጀመረ የሰሙት ባለሥልጣናት በእጅጉ ስለተቆጡ ወዲያው ታገደ። 1,500 ሸክላም እንዲቃጠል ተደረገ። የእግዱ ዋና ምክንያት “አልተግባባንም” የምትለዋ ዘፈን ናት። በግልባጩ የተካተተችዋ “ጤንነቴ” የምትለዋ ዘፈን ለእሳት የሚያበቃ እንከን ባይገኝባትም የሸክላው አካል ነችና አብራ መስዋዕት ሆነች። ይህ ሸክላ ገና ለገበያ ከመቅረቡ ስለታገደ ብዙዎች እጅ ሳይገባ ቀረ። በሙዚቀኛው አብዱቄ ከፈኔ የተደረሱትና ደርግ የተቀየማቸው የ”አልተግባባንም” ስንኞች በከፊል፡-

እኔ ላንቺ ላስብ ስሞክር- አንቺ ለራስሽ ስታስቢ፣

እኔ ለጋራ ጥቅም ስታገል- አንቺ ራስሽን ስትቀልቢ፣

ከዛሬ ነገ ይገባሽ መስሎኝ- ባቅሜ መጠን ስጥር ስለፋ፣

ባሰብሽ እንጂ አልተሻሻልሽም- እኔም ደከምኩ ቆረጥኩ ተስፋ።

አልተግባባንም!

የኔ ሀሳብ አልገባሽም፣

አልተስማማንም!

ለኔ የታየኝ አልታየሽም፣

ካልተጣጣምን፣

ካልተስማማን፣

በሀሳብም ካልተግባባን፣

ሞክረነው ካቃተን፣

ምናለበት ቢቀርብን።

ተሾመ ምትኩ

ከአማርኛ እስከ እንግሊዘኛ በርካታ ዘፈኖችን በመጫወት የሚታወቀው ተሾመ ምትኩ፤ ከእናት ሀገሩ ኢትዮጵያ የተለየው ገና አብዮቱ ሳይፈነዳ በ160ዎቹ መጀመርያ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ከዘውዳዊው መንግስት አገዛዝ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ነበር። ያለመግባባቱ ምክንያት ይህ ነው። የዘመኑ ተማሪ እነተሾመ ላሉበት ሶል ኤኮስ ባንድ ልዩ ፍቅር ነበረው። ከእለታት ባንዱ ቀንም ይኸው ባንድ ወደ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ) አቅንቶ ስራዎቹን በልደት አዳራሽ ያቀርባል። ወጣቱ ታዲያ የተለመደውን ስራሰቸውን ሳይሆን፤ ልብን የሚያሞቅ፣ ወኔን የሚቀሰቅስ ዘፈኖችን መስማት ነበር የሚፈልገው። ወቅቱ መንግስትን መቃወም፣ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄድ ብቅ ብቅ ማለት የጀመረበት ጊዜ ነበርና፤ እንደ ፋኖ፣ ቼ በለው፣… የመሳሰሉ፤ የወጣቱ የብሶት መተንፈሻ ዘፈኖችን እንዲዘፍኑ ድምጻውያኑን የሙጢኝ አሉ። ድምጻውያኑም እምቢ ማለት ስላልተቻላቸው ዘፈኑ። ጩኸቱ፣ ብጥብጡና ተቃውሞውም ቀጠለ።

እንግዲህ ይህ መነሻ ነው፤ የባንዱን መሪ ተሾመ ምትኩን መንግስት ዐይን ውስጥ የከተተው። በኋላም ሀገር ጥሎ ወደ ሀገረ ስዊዲን እንዲሰደድ ምክንያት የሆነው።

በኃይሉ እሸቴን እንደ መደምደሚያ

ሳንሱር በመንግስት ብቻ ሳይሆን በማኅበረሰብ ወይም በግለሰብ ውስጥም አለ። ተነካሁ ባዩ ማኅበረሰብ ወይም ግለሰብ ያልወደደውን ዘፈን ማስቆም፣ መቁረጥና መቀጠል ባይችል እንኳ በዚያ ማኅበረሰብ ውስጥ ዘፈኑ እንዳይሰማ መከልከል አያቅተውም። ባስ ሲልም በዘፋኙ ላይ የራሱን እርምጃ ይወስዳል። የፖሊስ ኦርኬስትራው ድምጻዊ በኃይሉ እሸቴ የተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮችን እያነሳ የሚዘፍን ድምጻዊ ነው። በሚያነሳቸው ጉዳዮች ደስ የሚሰኙ መኖራቸውን ያህል ታዲያ አብዝተው የሚበሳጩበትም አልታጡ። አንድ ጊዜ “የኪዎስኳ እመቤት” እያለ በመዝፈኑ “ተደፍረናል” ያሉ ሴተኛ አዳሪዎች ቀን ጠብቀው ጥርሱ እስኪወልቅ ደብድበውታል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top