መጽሐፍ ዳሰሳ

ተሰርቆ የታሰረው ልጅ ታሪክ

ጥቅል ታሪክ

«My name is Why» የተሰኘው የለምን ሲሳይ መጽሐፍ በራሱ የልጅነት ህይወት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ስራ ነው። መንግስት ልጅ ሰርቆ እስር ቤት ከቷል፣ የህይወት ታሪኩም እንዳይታወቅ ደብቋል ይላል ደራሲው ገና ከመነሻው። የለምን እናት እንግሊዝ ሀገር ለትምህርት የደረሰችው በ1966 ዓም ነበር። በወቅቱ ነፍሰ ጡር ነበረች፣ መውለጃዋ ሲደርስ ዊጋን አካባቢ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ደራሲውን ተገላገለች። ብዙም ሳይቆይ አባቷ ስለታመሙ ወደ ኢትዮጽያ መመለስ ነበረባት፤ ያኔ ነው እንግዲህ ህጻኑ ለአሳዳጊ ተላልፎ የተሰጠው። ኖርማን ግሪንውድ የተባለ ስምም አገኘ።

ለለምን ሲሳይ ህይወት ፈተና ነበረች። ገና በ12 ዓመቱ አሳዳጊዎቹ ከቤት ያባረሩት።  ከ12 እስከ 17 ዓመቱ ደግሞ በአራት የተለያዩ ማሳደጊያ ቦታዎች በተለያዩ ምክንያቶች ተወርውሯል። በግራ እጁ ላይ NG /Norman Green wood/ የሚል ንቅሳት ቢያጽፍም እውነተኛ ስሙ ይህ ንቅሳት አለመሆኑን የተገነዘበው በ17 ዓመቱ ነበር።

ደራሲው ለ30 ዓመታት ከእንግሊዝ መንግስት ጋር ትግል ገጥሟል። ትግል የገጠመው ከልጅነት እስከ እውቀት ሲመዘገብ የቆየው የህይወቱ ታሪክ /ማንነት/ ተላልፎ እንዲሰጠው ነበር። በ2015 የዊጋን ካውንስል ኃላፊ አራት ትላልቅ ዶሴዎችን አስረከቡት። ከዚህ በኋላ ነበር ይህ መጽሐፍ የተወለደው። ማንነቱን ለዓለም ለማብሰር ስሙ ኖርማን ሳይሆን ለምን መሆኑን ለማስረዳት ይደክማል …MY Name is Why…

ስለ ልጅነቱ፣ ስለትምህርቱ፣ ስለ አሳዳጊዎቹ ስብእና፣ ስለ ባህሪው፣ እናቱ ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር ስለተፃፃፈቻቸው ደብዳቤዎች  ምን አለፋችሁ እያንዳንዱ ትንፋሹ ዶሴው ውስጥ እየተመዘገበ ነው የቆየው። ደራሲው ደብዳቤዎቹን አባሪ በማድረግ ነው እንግዲህ ታሪኩን በቅደም ተከተል የሚተርክልን።

ለአሳዳጊዎቹ ስለመተላለፍ

ህፃኑ ለምን ሲሳይ ሆስፒታሉ ውስጥ ለ228 ቀናት ብቻውን ተኝቶ ነበር። የዚህ መሰረታዊ ምክንያት ደግሞ ዘረኝነት ነው። ህፃኑን የጎበኘ ሁሉ ጥቁር መሆኑን በማየት ብቻ ቀኝ ኋላ ዙር ይላል። መጨረሻ ላይ የግሪንውድ ቤተሰቦች እያመንቱ “እስኪ ለማንኛውም በጥልቀት እንፀልይበት” ሲሉ መከሩ፣ ከቆይታ በኋላም ፍቃደኝነታቸውን ገልፀው ህፃኑን ተረከቡ።

ይህ ሁሉ ፍጥጥም ጥር 3 ቀን 1968 የተደረገው ያለእናቱ ስምምነት ነው። እናቱ ለአጭር ግዜ ትምህርት ስትመጣ ችግር ላይ ነበረች። በመሆኑም የምትማርበት ኮሌጅ እርግዝናዋን አስመልክቶ ወደ ቅዱስ ማርጋሬት ነበር የላካት። ለምንን በሰላም ከተገላገለች በኋላ የማደጎ ስምምነቱን ትፈርማለች ተብሎ ይጠበቅ ነበር። ነገር ግን ማደጎ ምን እንደሆነ በሚገባ ታውቅ ስለነበር ስምምነቱን አልፈረመችም። ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ አባቷ በፀና በመታመማቸው ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ነበረባት። ቆይቶም ለምንን ጥላ በመሄዷ ልጁ በመንግሽት ኃላፊነት ስር መውደቁን የሚገልፅ ደብዳቤ በምትከታተልበት ቤተክርስትያን በኩል ተላከላት። ተቃውሞ ካላትም በ30 ቀናት ውስጥ ብቻ እንድታቀርብ ያስጠነቀቀ ነበር መልእክቱ።

ደራሲው ይህ ደብዳቤ ተፈፃሚ ሊሆን እንደማይችል በማስላት የተላከ ነው ባይ ነው።ምክንያቱም ፍርድ ቤት ጉዳዩን ለማስረዳት ብቻ 14 ቀናት ያስፈልጋል፣ የተላከው መልእክት ኢትዮጵያ ለመድረስ አንድ ወር ወስዶበታል ይህ ማለት የእሷም ምላሽ ወይም አቋም እንግሊዝ ለመድረስ አንድ ወር ይፈጅበታል። በሌላ በኩል በግዜው ከአዲስ አበባ ለንደን ቀጥታ በረራ አልነበረም። ቦታው ለመድረስ ከአዲስ አበባ አቴንስ፣ ከአቴንስ ደግሞ ለንደን መብረር ያስፈልጋል፣ ይህ ማለት በተሰጠው የግዜ ገደብ መድረስ የማይቻል ነው በማለት። ለምን ቅዱስ ‘ማርጋሬት ሃውስ’ን ከሚሰጠው ተግባር አንጻር በሚከተለው መንገድ ያጣጥለዋል

 «በመሰረቱ ይህ ቦታ የልጆች እርሻ ነው። እናቶች መሬት ሲሆኑ ልጆች ደግሞ ሰብል ናቸው። ቤተክርስቲያንና መንግስት ገበሬዋች ሲሆኑ የማደጎ አሳዳጊዎች ደግሞ ተጠቃሚዋች ናቸው»

ሰቆቃና መከራ

መምህርና ነርስ የሆኑት አሳዳጊዎቹ ሁለት ልጆች አላቸው። ክርስቶፈርና ሄለን የተባሉ።ለምን ክርስቶፈርን በአንድ ዓመት ይበልጠዋል-  ሄለን  በጣም ትንሽ ናት። ክወንድሙ ጋር ጠረጴዛ ቴንስ ሲጫወቱ አውቆ ይሸነፍለት ነበር- እንዳይናደድ።

ለምን በሰባት ዓመቱ ጠያቂ መሆን ጀምሯል። ቤተክርስቲያን ሲሄድ ያልገቡትንና ቅር የሚሉትን ነገሮች ሁሉ እንዴት እያለ ይጠይቃል። ጥያቄዋቹ ምላሾች ነበራቸው «ሁላችንም ሃጢያቶች ስለሆንን» የሚል። ትምህርት ቤት አካባቢ ለሚፈጠሩበት የዘርና የቀለም ጥያቄ ግን ምላሸ አላገኘም።

«እናትህ ጥላህ ሄደች… አትፈልግህም… እኔ ባገኘት ዐይኗን እቦጫጭረው ነበር… እንዴት አይነት ክፉ እናት ናት…» በትንሸ ጭንቅላቱ ይህን ጥያቄ ቤት ይዞ ይሄዳል- ምላሸ ለማግኘት። የአሳዳጊው እናት መልስ ግን ወላጅ እናቱን አበክራ እንደምትጠላት የሚያስረዳ  ነበር።

የህይወት ፋይሉ ላይ እንደተመዘገበው በስምንት ዓመቱ ብስኩት ሰርቆ በልቷል፣ ቁራጭ ኬክ ሲወስድም ‘እባክህ’ እና ‘አመሰግናለሁ’ ሳይል ነው። ሰርቆ መብላቱ ወላጆቹን ያበሳጫቸው ሲሆን ሰይጣን ውስጡ እንደገባ ያምኑ ነበር። ደራሲው ኋላ ላይ High Profiles ለተባለ መጽሔት በስጠው ቃለመጠይቅ  «እጃቸውን ጭንቅላቴ ላይ ጭነው ሰይጣን ከዚህ ልጅ ላይ ውጣ!» ይሉ ነበር ብሏል።

አይወደንም፣ ሰይጣናም ሆኗል ከሚሉ ምክንያቶች በተጨማሪ በ12 ዓመቱ ለመባረሩ ምክንያት የሆነው የትንሿን ሄለንን ወሬ በመስማታቸው ነው። ሄለን ለወላጆችዋ

“ኖርማን ከእኔ በስተቀር ሁላችሁንም እገላለሁ ሲል ሰምቼያለሁ” ብላ ታወራለች።

ይህ ወቅት ገና ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የተሸጋገረበት ነበር። የስምንት ዓመት ልጅ ቤተሰቡን ሊጨርስ እየዛተ ነው ብሎ ማመን ብሎም የከፋ ርምጃ ይወስዳል ብሎ መደምደም ተቀባይነት እንደሌለው ደራሲው ይናገራል ,።

አሳዳጊዎቹ ይህ ሰይጣንም ልጅ እንደማያስፈልጋቸው ውሳኔ ላይ ደረሱ። እናም አንጠልጥለው  ለአንድ አሳዳጊ ድርጅት አስረከቡት፣ ዝም ብለው ቢሄዱም ጥሩ ነበር። ከዚህ ይልቅ የማይታይ አርጩሜ ህሊናው ውስጥ አስቀመጡ

“እየመጣን አንጠይቅህም፤ ድብዳቤም አንጽፍልህም” በማለት።

በደህናው ዘመን ወንድም፣ እህት፣ አክስት፣ አጎት እና  አያት እንዳለው እንዳልሰበኩት «አውጥተው ሲጥሉኝ ማንም ሰው እንዳይገናኘኝ አድርገው ነበር» ብሏል በቁጭት።

ጥር 3 ቀን 1968 ዓ.ም. ተግባራዊ የሆነው የማደጎ ወላጆች ስምምነት ሰባት አንቀፆችን ይዟል። አንደኛው ኖርማንን ልክ እንደራሳቸው ልጆች ማሳደግ እንደሚኖርባቸው ይደነግጋል ። ሁለተኛው ደግሞ ልጁ የራሱን ሃይማኖት እንዲከተል ማድረግን ይመለከታል። ከእነዚህ ድንጋጌዋች አንፃር በለምን ላይ የደረሰው ቅጣት ከሚታሰበው በላይ ነው። ለመሆኑ ለምን ስለአሳዳጊዎቹ ምን አስተያየት አለው የሚል ጥይቄ ቢነሳ የሚከተለውን የሚገርም ምላሸ ሲሰጥ እናገኘዋለን

«በጣም ጥሩ ሰዎች ነበሩ፣ መጥፎ ነገርን የሚያደርጉ»

የቦብ ማርሌይ ሞራላዊ ድጋፍ

በ12 ዓመቱ ውድፊልድ ወደተባለ ማሳደጊያ ተቋም ሲገባ የእድሜ አቻዎቹ ‘ቾኪኋይት’ የሚል ቅጽል ስም ሰጥተውት ነበር። በዚህ ስፍራ ሰራተኞቹ ልጆች ሲጋራ ማጨስ እንደሌለባቸው አይመክሩም ይልቁንም የማጨሻ ልዩ ስፍራ አዘጋጀተዋል- እናም ማጨስ ለመደ። በዚህ ስፍራ መጽሐፍ የለም፣ አንብብ የሚል አበረታችም አይገኝም- በተቃራኒው ግን ለመጀመሪያ ግዜ ግጥም መፃፍ ጀመረ። ግጥሙም ስለ ዛፍ የምታወሳ እንደነበረች ያስታውሳል። ባልተጠበቀ መልኩ ግን ገጣሚ መሆኑን የተረዳችው የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር «The Mersey sound» የተባለ የግጥም መጽሐፍ እንዲያነብ ሰጥተዋለች። አሁንም በተቃራኒ ዕይታ ደራሲው ስለግጥሙ ይዘት አይደለም የሚነግረን- ገጣሚው በመጀመሪያ ገጹ ላይ ስለ ሙት ልጆች መፃፉን እንጂ።

በአንድ ወቅት በጓደኛው ምክንያት ከቦብ ማርሌይ ስራዋች ጋር ተዋወቀ። ቦብ ማርሌይ የመጀመሪያው ጥቁር ጓደኛ፣ የመጀመሪያው ጥቁር መምህር ሆነለት። በርግጥ ከቦብ የወሰደው ዘፈኑን ብቻ ሳይሆን አደገኛ እፅንም ጭምር ነበር። ቦብ ለሰው ልጆች እኩልነትና ነፃነት ይጮሃል፣ ስለ ጭቆና ስለ ታሪክ ስለ ዓለም እውነት ይናገራል። ደራሲው ቦብን የወደደበት ሌላኛው ምክንያት በዘይቤያዊ አነጋገር የሚያስተላልፋቸው ውብ መልእክቶች ናቸው። በዚህ ረገድ Ride Natty Ride በሚለው ዘፈን ውስጥ ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አባባል ለጉድ ይወደዋል።

But the stone that the builder refuse

Shall be the head cornerstone

And no matter what game they play

We’ve got something they could never take away .

እናም ለመጀመሪያ ግዜ ከነጮች ባህር ውስጥ የተገኘ ጥቁር ሰው መሆኑን አመነ «በኔ ዙሪያ የተሰበሰቡ ሰዎች ሁሉ የኔን ዘርና ቀለም የካዱት የቀለም ዐይነስውርነት ስላለባቸው መሆኑን  አመንኩ» ብሏል፡፡

Description: C:\Users\Alemuyehu\Desktop\ውሽይዝ.jpg

ጥቅል መደምደሚያ

በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ ‘አውቶባዮግራፊ’ እና ‘ሚሞይር’ ስለ አንድ ሰው ህይወት ስለሚያትቱና በአንደኛ ደረጃ የአጻጻፍ ይትበሃል ስለሚዋቀሩ የመመሳሰል ጸባይ ያላቸው ይመስላል። ፈታ አድርገን ስንመለከታቸው ግን መሰረታዊ ልዩነት አላቸው። አውቶባዮግራፊ የደራሲውን መላ ህይወት በቅደም ተከተል የሚዳሥስ ሲሆን ሚሞይር የደራሲው የተወሰነ የህይወት ክፍል ላይ አጠንጥኖ ይሰራል። አውቶባዮግራፊ ታዋቂ ሰዎች ላይ ሲያተኩር ሚሞይር ሰው አይመርጥም። ሰዎች ለማንበብ የሚፈልጉት አጠቃላይ ህይወቱን ቢሆን ከርእሰ ጉዳዩ ወይም ከጭብጡ አንፃር በመነሳት ነው። አውቶባዮግራፊ ለእውነትና ታሪክ ልዩ ትኩረት ሲሰጥ ሚሞይር ስሜት ነክ ልምዶችን ይቃኛል።

በዚህ ረገድ የለምን ሲሳይ ሚሞይር የማንነት ፍለጋ ላይ ላይ ያነጣጠረ ነው ማለት ይቻላል። እናት ብትርቀው፣ አሳዳጊ ቢገፋው፣ ማኅበረሰቡ ቢያገለው እንኳ ያላሰለሰ የራስ ጥረት ካለ ውጤት እንደሚገኝ ያስተምራል። ለምን ሲሳይ እስከ 17 ዓመቱ አንድ ዐይነት፣ ከ17 ዓመቱ በኋላ ደግሞ ሌላ ዐይነት ሰው ነበር። በ14 ዓመቱ እጁ ላይ የነቀሰው Norman Greenwood አንደኛው ሲሆን ከ17 ዓመት ጀምሮ ያወቀው ‘ለምን ሲሳይ’ ደግሞ ሁለተኛው ማንነት ነው። ሁለተኛውን ማንነቱን ሲያገኝ የተረዳው ስሙን ብቻ ሳይሆን እውነተኛ እናቱን፣ እውነተኛ ሀገሩን፣ የጥቁርነቱን ምክንያትና የግጭቱን መሰረት ነው። ለዚያም ነው ገጽ 137 እና 138 ላይ

«የልደት ማስረጃዬ ላይ ያለው ስም ለምን ሲሳይ መሆኑን ለሚጠቁኝ ሁሉ እነግራቸዋለሁ» በማለት 90 ያህል ግዜ My name is Lemn Sisay ተደጋግሞ ተጽፎ የምናየው። የድግግሞሹ ወይም /Alliteration/ ሚና ትኩረት መጠቆሚያ ነው።

ለምን ሲሳይ እውነተኛ ስሙንና ማንነቱን ካወቀ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ያልመለሰልን አንድ ጥያቄ አለ። እርግጥ ነው በቅጣይ /Epilogue/ ምእራፍ ላይ እናቱ የማርሸት ከአማራ ህዝቦች እንደተገኘች በዚሁ ክልል ባህል ደግሞ በመጀመሪያ ልጅ መልእክት ማስተላለፍ የተለመደ መሆኑን በመጠቆም ለምን ‘Why’ የሚል ፍቺ እንዳለው ያሰረዳናል። ጥያቄው ግን ይህ አይደለም። ጥያቄው እናቱ እንዴት ‘ለምን’ አሉት የሚለው ነው። ከስሙ ፍካሬያዊ ፍቺ ከተነሳን ለምን ትምህርቴን ሳልጨርስ … ለምን በውጭ ሀገር …. ለምን ከጋብቻ በፊት … ወዘተ የተሰኙ ህሊናዊ ሙግቶች እንዳሉበት እንገነዘባለን።

ስለምንነት ካወራን ደግሞ እናቱን አስታውሶ አባቱን መግደፉ መሉ አያደርገውም። ለምን ሲሳይ ከመጽሐፉ ሕትመት በኋላ በሰጣቸው ቃለመጠይቆች አበቱ የኢትዮጽያ አየር መንገድ አብራሪ እንደነበር፣ በ1973 ከኢትዮጽያ ወደ ኤርትራ እየበረረ መብረቅ ክንፉን መቶት በሰሜን ተራሮች ላይ መሰዋቱን ተናግሯል። ሰሜን ተራራሮችን ከጎበኘ በኋላም ለአባቱ ግጥም መጻፉን አስረድቷል። እነዚህ ቀጥተኛ ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች በድሉ የመጨረሻ ምእራፍ ላይ ቢዳሰሱ የበለጠ ጠንካራ ያደርገው ነበር።

ደራሲው በዚህ ስራው የተበላሸ የማደጎ ስርአት አሰራርን አጋልጦበታል። የቸልተኛ ባልስልጣናትን የተረገመ ተግባር እንዲሁም የቢሮክራሲን ጭካኔ አሳይቶበታል።  በዘር፣ በቀለምና በሞራል ላይ የሚደረገውን ልዩነት ኮንኖበታል። በ 30 ምእራፎች የተከፋፈለው ስራ ሁለት ልዩ ባህሪያት አሉት። የመጀመሪያው አብዛኛው ምእራፍ ከመረጃ ጋር ተሰናስሎ የመቅረቡ ጉዳይ ነው። ሁለተኛውና ዋነኛው ሀሳብ ሁሉም ምእራፎች የሚጀምሩት በኳትሬይን /Quatrain/ ዐይነት ግጥሞች መሆኑ ነው። ለአብነት ያህል በምእራፍ 14 ላይ የሚከተለውን ግጥም እናገኛለን

Night can’t drive out night

Only the light above

Fear can’t drive out fear

Only love

ጨለማን ጨለማ አያባርረውም

ብርሃን እንጂ

ፍርሃትን ፍርሃት አያባርረውም

ፍቅር እንጂ

ግጥሞቹ በቀጣይ ከምናነበው ታሪክ /ሃሳብ/ መረጃ ጋር እናገናኘው ካልን ሊገኛኝ ይችላል።እነዚህ ባለ አራት መስመር የግጥም ስንኞች በተለይ በእንግሊዝ ስነ ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ ላቅ ያለ ሚና አላቸው። ርግጥ ነው ይህ ስነጽሁፋዊ ዘውግ በጥንታዊ ቻይና፣ ሮም፣ ግሪክ እና ህንድ ቀደምት ልእልና ነበረው። ቀጥሎም በአውሮፓ የጨለማው ዘመን በስፋት ተሰርቶበታል። በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ ኦማር ካያም ሩባያ በሚል ስያሜ ገኖበታል። በተመሳሳይ መልኩም ኖስትራዳመስ ለዝነኛ ትንቢቶቹ መጠቀሚያ አድርጓቸዋል።

ታዲያ ለምን ሲሳይ እነዚህን የግጥም ዐይነቶች በምን አላማ ተጠቀመባቸው ብሎ መጠየቅ ግድ ይላል። ግጥም ያለውን ትልቅ ጉልበት ለማሳየት… ግጥም መጻፍ የጀመረው እስር ቤትን በሚስተካከሉ /እንደርሱ አመለካከት/  የህጻናት ማቆያ ቦታዎች መሆኑን ለመዘከር… በስቃይና ችግር ያሳለፈውን የልጅነት ህይወት ያቃለለት ኪነጥበብ /ግጥምና ሙዚቃ/ መሆኑን አስረግጦ ለማስረዳት… ጽሁፉን ተነባቢ ለማድረግ… ወዘተ ማለት ይቻላል። እንደ እኔ እምነት ግን ባለአራቱ ስንኞች ገዝፈው የተቀረጹት በአራት አስቸጋሪ ማሳደጊያ ቦታዎች ህይወቱን መምራቱን ተምሳሌታዊ ለማድረግ በመፈለጉ ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top