ቀዳሚ ቃል

ቀዳሚ ቃል

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ “ገነትን ያጠጡ ዘንድ ከኤደን ይወጣሉ” ከተባለላቸው ወንዞች ውስጥ አንዱ ዓባይ ነው። ግሪካዊውን ሊቅ ሄሮዶቱስን ጨምሮ ስለ ኢትዮጵያ እና ስለወንዟ ዓባይ ብዙዎች ብዙ ብለዋል። የዓለማችን ቀደምት ስልጣኔ ታሪክ በሚወሳበት ጊዜም የኤፍራጥስና የጤግሮስ፣ ያንጊቲዝና የቢጫ፣ አማዞን እና ዓባይ (ናይል) በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። የሜሴፖታሚያ፣ የፋርስ፣ የባቢሎን፣ የቻይና፣ የአሲሪያን፣ የግብጽን ጨምሮ የእኛይቱ ኢትዮጵያ ሥልጣኔዎች መነሻ ወንዞች እንደሆኑ የሚስማሙ ምሁራን በርካታ ናቸው።

ዓባይ ሲነሳ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በተለይም ግብጽ ቀድማ ትነሳለች። ቀደምት ታሪክ ጸሐፊዎች የ“ዓባይ ስጦታ” በሚል ቅጽል የሚገልጹዋት “የበረሃዋ ገነት” ግብጽ፤ ዓባይ የግሏ እንደሆነ ይሰማታል። እንደብቻ ንብረቷ ትመለከተዋለች። “የዓባይን ውሃ አንድ ጭልፋ ለመንካት ፈቃዴን ጠይቁ፣ ካለኔ ይሁንታ ውልፊት የለም” የሚለው አስተሳሰቧን አርጅቶም አልተወችውም።

 የሰጥቶ መቀበል፣ የጋራ ተጠቃሚነት ዘመን የሆነው 21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ደርሳም የአያቶቿን ትርክት አልተወችም። እኛስ የት ላይ ነን? ምን ላይ ነን? መንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ በሂደቱ ውስጥ ያለፉ ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ፣ እያንዳንዱ ግለሰብ ለየራሱ ሊመልሰው የሚገባ ጥያቄ ነው።

 በዛሬው የታዛ መጽሔት ቅጽ 3 ቁጥር 33 ዕትማችን ዓባይን እና ግድቡን፣ በተፋሰሱ ሐገሮች መካከል ያለውን ውይይት እና ክርክር፤ የሕግ እና የታሪክ ፍላጎት እና መብትን፣… የተመለከቱ ጉዳዮችን ሰፋ ባለው ገጻችን እንመለከታለን። በታሪክ ሰሪነት እና በታሪክ ተወቃሽነት መካከል የቆመው የዛሬው ኢትዮጵያዊ ትውልድ የነበረ ብቻ ሳይሆን ያለውን፣ ያለ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም የሚቀጥለውን፣… የዓበይ ጉዳይ እንደምን ባለ መላ ሊይዘው እንደሚገባ የሚያሳዩ የውይይት መነሻዎችን ሰፋ ባሉ ገጾች እናስነብባለን።

በዚህ ቅጽ የተካተቱት ጽሑፎች እንደ ቀደሙት የመጽሔታችን ቅጾች ሁሉ ከአንድ ጊዜ በላይ የሚነበቡ፣ ለማመሳከሪያ የሚቀመጡ፣… መሆን እንዲቻላቸው በመረጃ ብቻ ሳይሆን በማስረጃ የተደገፉ እንዲሆኑ ጥረት ተደርጓል።

በወግ፣ በቃለ መጠይቅ፣ በስነ-ግጥም፣ በፍልስፍና፣ በልብወለድ፣ በታሪክ፣… እና በሌሎችም ዘውጎች እየተከፋፈሉ የተሰናዱት ጽሑፎችም ከተዝናኖት እስከ ቁምነገር ያሉ ጉዳዮችን የሚያነሳሱ ናቸው።

ከወቅታዊ እስከ ጥንታዊ ያሉ የታሪክ እና የጥበብ ጭብጦችን የሚያነሳሱ ናቸው። በንባባችሁ ላይ ቅር የተሰኛችሁበት ጉዳይ ካለ፣ በንባባችሁ ላይ ያልተስማማችሁ ሐሳብ ካለ፣ በንባባችሁ ላይ ደስ ብሎአችሁ እንዲቀጥል የምትሹት ጉዳይ ካለ ንገሩን። በቀና ልቡና ተቀብለን፣ ደስ እያለን ስህተታችንን ለማረም፣ በርትተን ጥንካሬአችንን ለማጎልበት ቆራጥ ነን። ሐሳባችሁን ከአጭር አስተያየት እስከ ረዥም ሐተታ ጽሁፎች ድረስ ያለ አድልዎ ተቀብለን እናስተናግዳችኋለን።

  በወዳጅነት እንሰንብት! መልካም ንባብ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top