ስርሆተ ገፅ

“ሰው መጠኑን የሚያክል ነው የሚጎርሰው፤ ካልሰሩት የሰሩት ይሻላሉ!”

ድምጻዊ ትንሳኤ ጉበና

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ውስጥ መግባቱን ተከትሎ በርካታ ሙዚቀኞች ‹‹ተጠንቀቁ›› የሚል ይዘት ያለው ዘፈን አስደምጠዋል። ቀድመው ለአድማጭ ከደረሱት መካከል ‹‹እጅ እንንሳ›› ተጠቃሽ ነው። በድምጻዊት ሚሚ ሙሉቀን እና በድምጻዊ ትንሳኤ ጎበና የተዘፈነው ይህ ዜማ በህዝብ ዘንድም ከፍተኛ ተቀባይነት ነበረው። የግጥሙ ደራሲ ዓለማየሁ ደመቀ፣ አቀናባሪው አበጋዝ ክብረወርቅ ናቸው። ጋዜጠኛ በቢዩ ግርማ ዘፈኑን ከተጫወቱት ድምጻዊያን መካከል ከትንሳኤ ጎበና ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

ኮሮና እንዴት እያደረገህ ነው?

ያልለመድኳውን ነገሮች በሙሉ ዕያሳየኝ ነው። በሕይወቴ ቁርስ የማላቀውን ልጅ ቁርስ ያበላኝ ኮሮና ነው። ማታ ሦስት ሰዓት መተኛት፣ ጥዋት ተነስቶ ቁርስ መብላት፣ ከቤት አለመውጣት፣… በኔ ሰው መውደድ የማልችላቸውን አስችሎኛል። ክለብ ስለምሰራ እነዚህን ነገሮች አላውቃቸውም ነበር።  

በሽታው ብቻ አይደለም። ሁለተኛው ያልተለመደ ነገር እቤት መዋል የሚባለው ነገር ነው። ምክንያቱም ከሥራ መጣሁ፣ ተኛሁ፣ ተነሳሁ፣ ከዚያ በኋላ ሽፍት አድርጌ ወደ ስቱዲዮ ነው፤ ከጓደኞቼ ጋር… መቼም  የሙዚቀኛን ህይወት ታውቀዋለህ፤ ትላንት ምን ተሰራ፣ ያልነበርኩበትን ሕይወት እነማን ምን ላይ ደረሱ፣ ጓደኞች ማገዝ ምናምን፣… ይህንን ሁሉ ነው ያስቀረው።

ቢሆንም ግን ብዙ ማማረር አያስፈልግም። ወደ ውስጥ ዕንዳይ ረድቶኛል። ኮሮና የመጣው ለምክንያትም ይሆናል። አሁን በተገኘው አጋጣሚ ቤት ውስጥ ስንሆን ውስጣችንን ለማዳመጥ የተሰጠን ጊዜ እንደሆነ አስበን ውስጣችንን ብናዳምጥ ምን ሰርቻለሁ? ምን ይቀረኛል? እሱን ሁሉ ያሳስባል።

“አዲስ አበባ” የተሰኘው ስራህ በብዙዎች ይታወቃል። የሙዚቃ ቪድዮም አለው። ሌሎችም ስራዎች አሉህ። በስፋት ከሕዝብ ጋር የተገናኘኸው በ“እጅ እንንሳ” ነው ማለት እንችላለን?

ሰማይ ሰማይ፣ ጉዱ ካሳ የሚባሉ ነጠላ ዜማዎችንም ሰርቻለሁ። እንደኔ ፍላጎት ቢሆን ከሕዝብ ጋር የሚያገናኘኝን ሥራ የምሰራው ዛሬ አልነበረም። እንደጓኞቼ ቀደም ብዬ ነው ግን እግዚአብሄር የራሱ እቅድ አለው።

አልበም ሰርቼ ጨርሼ ከአንድም ሁለት ጊዜ ነገሮች ሲበላሹ፣ ሚክሲንግ ስል… ምናምን ስል… ነው የቆየሁት። ድንገት ግን የእግዚአብሄር ፍቃድ ሆኖ ለመልእክት ነው ያስቀመጠኝ መሰለኝ፤ በመልእክቱ እንግዲህ ብቅ አድርጎኛል።

የስራው ጅማሬ እንዴት ነበር?

ሀሳቡ የመነጨው ከታላቁ የሙዚቃ ሰው ከአበጋዝ እና ከዓለማየሁ ደመቀ ነው። ጠርተው ይህንን ነገር እንስራ ሲሉኝ ደስተኛ ሆንኩ ምክንያቱም ለወገን መድረስ ነው። እያንዳንዱ የኪነ-ጥበብ ሙያተኛ ለወገኑ መድረስ ያለበት ሰዓት ላይ ነን። እንዲህ ተሰባስበን ነው ሿሿን የሰራነው። በመጨረሻም ውጤቱ ጥሩ ሆነ።

“ሿሿ” በአሉታዊ ትርጉም የሚታወቅ ቃል ነው እንዴት መረጣችሁት?

አስበንበት ነው። ከአሌክስም ጋር ስንማከር ለህመሙ ትክክለኛው መፍትሔ መታጠብ ነው፤ ሿሿ ያንን ይገልጸዋል። ያኛው በእኩይ ተግባር የተጠቀሰው ደግሞ በደረቅ እጥበት ነው። እኛ ደግሞ ቃሉን ከደረቅ ወደ እርጥብ እጥበት እናምጣው ብለን ተጠቅመንበታል። አሌክስ ገና ሲያመጣው ኦ ቃል አስመለስን አልን። በዚህ አጋጣሚ አንድ ቃል ከእኩይ ተግባር አስመለስን ነው የተባባልነው።

እጅ እንንሳም የነበረ ባህላችን ነው። ለአድማጩ በነባር ባህሉ ብንገልጽለት ብለን ነው። የተሳካልን ይመስለኛል

የባህላዊ ስልተ ምቱና ዜማው፣ መሳሪያዎቹ፣ የሁለታችሁ ድምጻዊያን ቅንጅት፣… ዘፈኑ እንዲወደድ ካደረጉት ነገሮች ውስጥ ይመደባል የሚሉ አሉ እንደዛ ይሰማሀል?

አዎ ልክ ነው። አሌክስ ልጅነትን፣ አሞኛልን፣ ሌላም ውብ ዘፈኖች የጻፈ ልጅ ነው። ብዕሩ ጥሩ ነው። ያንን የመሰለ ውብ ሙዚቃ አበጋዝ ባያነጥፈው፣ ማሲንቆ ተጨዋቹ፣ ክራሪስቱ፣ ዋሽንቱ፣… ባይኖሩ እዲህ ምርጥ አይሆንም። የጋራ ሥራ ነው።

አብራኝ የሰራችውን ሚሚ ሙሉቀን ረዥም ጊዜዋን የሰራችው በመሰንቆ ነው። በመሰንቆ የተገራ ድምጽ ደግሞ በጣም ‘ሪች’ ነው። በጣም ሐብታም ነው። አንድ ያለ-ማይክ ነው የሚዘፍኑት፣ ሁለት ደግሞ በመሰንቆ መገራት በጣም በምትወዳቸው እንቁ በምትላቸው ሙዚቀኞች ቃና ውስጥ ከመመላለስም በላይ ነው።

እኔ ከዚህ በፊት የምጫወተው እንደምታውቀው ዘመናዊ ዘፈኖችን ነው። ክለብ ምናምን፤… ዘፈኑን ለመስራት ስሄድ አበጋዝ ጋር ቀድማ እስዋ ነበረች። ‘ቡት’ ውስጥ ሆኜ ከርቀት ነው የሚሰማኝ። እስዋ ሌላ ቡት ውስጥ ነው የተቀዳችው፤ አሌክስዬ ምንድነው ደስ የሚል የባህል ዘፈን እሰማለሁ አልኩት። ግጥም እየጻፈልኝ ገና እያወራን ነው። እዚህ ዘፈን ላይ እኮነው የምትገባው አለኝ። ደስታዬ ወደር አልነበረውም።

ድምጽ ልቀዳ ስል ደግሞ መጀመሪያ የስዋን ድምጽ ስጡኝ ነው ያልኩት። ስሰማት በጣም ወግ ያለው ድርብብ ያለ፣ የሚያምር፣ ኢትዮጵያዊ ከለር ያላት፣… ዘፋኝ ነች። እኔም በዚያው ከሷ ተመሳሰልኩ። ወደ ባህሉ ተመለስኩ።

መመለስ እንዲህ ቀላል ነው?

እንደ ሙያተኛው ነው። አንድ ዐይነት ዘፈን ብቻ መዝፈን የሚችሉ ሰዎች አሉ። እኔ ደግሞ ዘፈን አልመርጥም። የነበረኝ የክለብ ልምድ ረድቶኛል። እንግሊዘኛም፣ ባህልም፣… ሁሉንም እዘፍን ስለነበር እሱ ረዳኝ። ከእስዋ ጋር እንዲቀራረብ ሞከርኩኝ።

ከዚያ በኋላ እንደውም አንድ ሁለት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለኢንተርቪው ሲጠሩኝ አደራ ትንሱ ማሲንቆህን እንዳትረሳ ብለውኛል። በዚያ ህይወት ውስጥ ያለፍኩ መስያቸዋለሁ።

ከዚህ በፊት ለማኅበራዊ ፋይዳ የሚሰሩ ዘፈኖች ላይ ተሳትፈህ ታውቃለህ?

የመጀመሪያዬ ነው። ከዚህ በፊት የሰራኋቸው ዘፈኖች የሚያመለክቱት ስለ አዲስ አበባ፣ ስለ እናት፣ ስለ መጽሐፍ ነው።

በተለይ ነፍሱን በገነት ያኑረው ‘ኤላ’ (ኤልያስ መልካ) የሰራቸው የመዝሙር ስራዎች ደስ ይላሉ። እነ ማለባበስ ይቅር፣ እኔ ነኝ ደራሽ ለወገኔ፣ አሽርክር ረጋ ብለህ፣… ጥሩ መልእክት አላቸው።

ልብ በይ ዐለሜ እንዴት ነሽ ብያለሁ

ከወገብ ታጥፌ እጅ ነስቻለሁ

ብሎ ነው የሚጀምረው አይደል? ጥሩ መልእክት ነው። ከዘፈንኩት በኋላ ግጥሙን ራሱ በደንብ አልያዝኩትም ነበር። ለጓደኞቼ የሚያምር ዘፈን ዘፈንኩ አልኳቸው።

በጣም ብዙ ኮሮናን የተመለከቱ ዘፈኖች ተሰርተዋል። ትክክል ያልሆኑም አሉ ተብለው ይተቻሉ። አንተ እንዴት መሰራት አለበት ትላለህ?

ካሉን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አራቱን ስትከፍት አራቱም የኮሮና ዜና ነው የያዙት። አንተ ቤት የተቀመጥከው ኮሮናን ፍራቻ ነው። እሱም ራሱ አስተዋጽኦ አለው። ሰዉ ሮሮ ነገር በቅቶታል። ነገሮችን በሮሮ መግለጽ በጣም አስቸጋሪ ነው። እየተዝናና ሐገራዊ በሆነ መልኩ፣ ቢገለጽ ደስ ይላል። እና ደግሞ በብዙ ብሔር ብሔረሰቦችም ቋንቋ ሲዘፈን ዐላየሁም። አልፎ አልፎ ቢኖርም በቂ አይደለም። ተወላጅ የሆኑት ልጆች በብዙ ቋንቋዎች ቢዘፍኑ ጥሩ ነው።

ዋሽንት እና ስሎው አድርገህ አስፈሪው ምናምን ዐይነት ነገር ከሆነ ሌላ በሽታ ነው ሰው ላይ የምንጭነው። ከታመመው ሰው በፍራቻ የሚሰቃየው ሰው ነው የሚበዛው። ከዚያ ይልቅ እየተዝናኑ የሚሰሙት ቢሆን ጥሩ ነው ባይ ነኝ።

ሰው መጠኑን የሚያክል ነው የሚጎርሰው፤ ካልሰሩት የሰሩት ይሻላሉ። ግን ሲሰራ ደግሞ እንዴት ነው መሰራት ያለበት ምንድነው የሚፈልገው። ቤት ዋሉም ተብሎ፣ እቤትም ተቀምጠን፣ ዜናው እንደዚያ እያወራብን፣ እንደገና ደግሞ ዜናውን፣ ዘፈን ሐዘንህን፣… ስትገልጽ ሌላ ተስፋ መቁረጥ ነው የሚያመጣው። በተቻለ መጠን በሚያስፈራራ እና በሚያስደነግጥ መልኩ ባይሆን፣ በደንብ ታስቦበት ቢሆን ጥሩ ነው። እኔ እድለኛ ሆኜ እነ አሌክስ አስበውበት ስለጠበቁኝ ነው። የዚያኑ ቀን ልስራ ብዬ ብነሳ የዚህን ያህል ላይሆን ይችላል። በዕይታም በቃልም እያዝናና የሚያስተምር ነገር ቢሆን ደስ ይለኛል።

ከተሰሩ ስራዎች ሁሉ ከራሴ ቀጥሎ የማንን ትወዳለህ ብትከለኝ የቶማስን ነው የምልህ። ከትላንት ዛሬ ስርጭቱ እየጨመረ ነው። ከዚህ በኋላም በተመሳሳይ ሥራ የምመጣ ከሆነ የምመጣው ሊያዝናና በሚችል መልኩ ነው።

አሁንም መሰራት አለበት ብዬ እምገምተው እቤት በሚውሉ ልጆች ነው። ቤት መቀመጥ ሰዉ እንዳይቸግረው፣ እንዳይከብደው፣… የሚያደርጉ ሥራዎች መሰራት ያለባቸው። ለሕጻናት የሚሆኑ ነገሮችንም ያስፈልጋሉ።

አማካሪስ አያስፈልግም?

እርግጥ ነው አማካሪ ያስፈልጋል። እሱን አልቃወምም። የስነልቦናም የጤናም ባለሙያ የሆነ አማካሪ ቢኖር ጥሩ ነው። ስቱዲዮ ብዙ ልጆች አሉ። እኔም እየጫጫርኩ ነው። ይህንን የጠበቀ ግጥም አለኝ የሚል ካለ በፈቃደኝነት እኔ ድምጻዊያን መልምዬ፣ ስቱዲዮ ወስጄ፣ ዜማ አልብሼ ራሴም ሰርቼ በጓደኞቼም አሰርቼ፣ እንዲዘፈን አደርጋለሁ። ግጥም ካላቸው ያምጡ። ግዴታ ከአንድ ቦታ ብቻ መሆን የለበትም።

በቀጣይ ምን እንጠብቅ?

በሀዘኑ ጊዜ ሿሿ እንዳልነው እግዚአብሄር ደግሞ ከዓለም ላይ ያጥፋውና ሌላ ሥራ ይዘን እንመጣለን። አልበሜን እየሰራሁ ነው። አሁን አንድ የባህል ዜማ ማካተት ግድ ነው።

በመጨረሻ ለአድማጮችህ ምን ትላቸዋለህ?

በኮሮና ምንም እንዳይደብራቸው ፍትት ይበሉ አድማጮቼ፤

ከዚያ ደግሞ ፍትግ አድርገው…

አዎ ከዚያ በኋላ ደግሞ ፍትግ አድርገው ደግሞ በውሃ እና በሳሙና ሿሿ ነው የሚያዋጣው አባቴ

ትንሳኤ እግዜር ይስጥልኝ

እኔም አመሰግናለሁ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top