አድባራተ ጥበብ

ዮፍታሔ ንጉሤ “ተወርዋሪው ኮከብ”

ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ በኢትዮጵያ ቴአትር ታሪክ ውስጥ ከፍ ያለ ስፍራ ካላቸው የኪነ-ጥበብ ሰዎች መሀል ዋነኛው ናቸው። እርሳቸው በተለሙት መንገድ ብዙዎች ተጉዘውበታል፣ ብዙዎችም ህልማቸውን ዕውን አድርገዋል። በሙያቸው በቴአትር፣ በስነ-ግጥም እንዲሁም በጋዜጣ ላይ ጽሑፎቻቸው የብዙዎቹን ሀሳብ ለመግዛት እና ለማሸነፍ ሆኖላቸዋል። ቀኝ ጌታ  ዮፍታሔ ንጉሤ በሥራዎቻቸው የየወቅቱን ሃሳቦች እና ማኅበረሰባዊ አመለካከቶች ለማንፀባረቅ ሞክረዋል። በዚህም ወጤታማ ከሆኑ ጥቂት ሰዎች አንዱ ናቸው። የቴአትር ደራሲ፣ አዘጋጅ፣ ባለቅኔ፣ አርበኛ፣ የመንግስት ሹመኛ…ብዙ ነገር። ዮፍታሔ ንጉሤ ብዙ ነበሩ።

ከቴአትሩ ባሻገር በተለይ ከ1917-1920ዎቹ መጨረሻ ድረስ ዮፍታሔ እና ዘመነኞቻቸው በተለይ በወቅቱ ዝነኛ በነበረው ብርሃን እና ሰላም ጋዜጣ ላይ በጊዜው አንገብጋቢ የነበሩትን ጉዳዮች በመመርመር ተከታታይ ጽሑፎችን ይጽፉ ነበር። እነዚህ ጽሑፎች የዮፍታሔን የጽሑፍ ብቃት ማሳየት ብቻ ሳይሆን ዮፍታሔ ምን ያህል ጉዳዮችን አርቆ መመልከት የሚችል ልቦና እና ማስተዋል እንደነበራቸው የሚያሳዩ ናቸው። በዚህ አጭር ዳሰሳ፣ የዮፍታሔን የጋዜጣ ላይ ጽሑፎች ሀሳብ፣ የቴአትር ጽሑፍ መነሻ፣ የመጀመሪያዎቹን ሴት ተዋንያን ስለማስተዋወቃቸው እና ስለ አርበኝነታቸው ለማንሳት እሞክራለሁ።

አጀማመር

በ1918 ዓ.ም. ገደማ በወቅቱ ተከፍተው በነበሩ የሀገሪቱ ትምህርት ቤቶች አማርኛ እና ግዕዝ የሚያስተምር ሰው ይፈለግ ነበር። በዚህ ጊዜ በነዚህ ትምህርት ቤቶች በመምህርነት ይሰሩ ከነበሩት የውጪ ዜጎች መካከል ግብፃውያን ይገኙበታል። እነዚያ መምህራን ግዕዝን እና አማርኛን ማስተማር አይችሉም። በዚህም የተነሳ በኋላ በኢትዮጵያ ቴአትር ከፍ ያለ ስም የሚኖራቸው ዮፍታሔ ንጉሤ እና መላኩ በጎሰው የግዕዝ እና የአማርኛን ቋንቋዎችን እንዲሁም የግብረ-ገብ ትምህርትን እንዲያስተምሩ ተቀጠሩ። የውጪ ሀገር፣ በተለይ የግብፅ ተፅዕኖ ወድቆበት የነበረው የማስተማር ስርዓት ቀስ በቀስ በአማርኛ እና በግዕዝ ቋንቋዎች እየተተካ መጣ። ከማስተማሩ ጎን ለጎንም ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ በተለይ በማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ጽሑፎችን በመጽሔት ላይ ማውጣት ጀመሩ። ድራማ እና ሙዚቃን ደግሞ እንደ ማስተማሪያነት ተጠቅመውበታል። ዮፍታሔ ንጉሤ የውጪ ሀገር ቋንቋ መጻፍም ሆነ መናገር ባይችሉም በምኒልክ ትምህርት ቤት ያስተምሩ ከነበሩት ግብፃዊ መነኩሴ ጋር በመሆን ድራማ እንዴት እንደሚጻፍ እና እንደሚዘጋጅ እውቀቱን በመውሰድ ድራማ መጻፍ እና ማዘጋጀት ጀመሩ።

በአምስት ዓመቱ የጣሊያን ወረራ ወቅት ከ1928-1933 ዓ.ም. ድረስ ዮፍታሔ በርካታ ቴአትሮች ጽፈዋል። ከነዚህም መካከል ስለወቅቱ ፖለቲካ እና ማኅበራዊ ህይወት የሚያነሳው ዝነኛውን ‘አፋጀሽኝ ‘ን ጨምሮ በርካታ ተውኔቶቻቸው የአብዛኛውን ተመልካች ቀልብ ገዝተዋል።

ጊዜው

ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ባለቅኔ እና የቴአትር ባለሞያ ብቻ አልነበሩም። የዘመኑ የሀሳብ ተሟጋች፣ አርበኛ፣ በኢትዮጵያ ቴአትር ታሪክ የመጀመሪያዎቹን ሴት ተዋንያን አስተዋዋቂ እንዲሁም አስተዳዳሪ ነበሩ። ስለ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ስራዎች ጥልቀት እና የአስተሳሰብ መጠን ለመረዳት እንዲሆን የጊዜውን ሁናቴ ወይም የዘመኑን መንፈስ መረዳት ተገቢ ነው። በተለይ ዮፍታሔ ብዛት ያላቸውን የኪነጥበብ እና ማኅበራዊ ሂሶችን የሰሩበት ጊዜ ከ1918-1928 ወይም የጣሊያን ወረራ እስከተከሰተበት ጊዜ በመሆኑ ይህንን ወቅት ወይም ጊዜ ማጥናቱ የጸሐፊውን ሀሳብ እና ፍልስፍና እንዲሁም ጥልቅ ምልከታን ለመረዳት ይጠቅማል። ዮሐንስ አድማሱ በሰኔ 25፣ 1961 ዓ.ም. መነን መጽሔት ላይ “ለማስታወስ ያህል” በተሰኘ ርዕስ በጻፈው መጣጥፍ ወቅቱን እንዲህ ይገልፀዋል፦

“ዘመኑ የጥድፊያ ነበር። ዘመኑ የሀገር ፍቅር የገነነበት ዘመን ነበር። ዘመኑ ኢትዮጵያ በብዙ ፈተና የተፈተነችበት ዘመን ነበር። እንደ ዮፍታሔ ያሉትም የኪነት ሰዎች ስለ ሀገራቸው በፅኑ መዋግደ-ህሊና የተጠመዱበት ዘመን ነበር። ለሀሳባቸው፣ ለስሜታቸው፣ ለጭንቃቸው መክፈያ የሆናቸው የተውኔት ጽሑፍ እና የመድረክ ዓለም ነበር። ይህ ሁሉ ተዳምሮ ይሆናል የቴአትር ስራ በዚያ ዘመን ከታላቅ ከፍታ እንዲደርስ የረዳው። የቴአትር ስራ በጣም የተወደደ፣ የተከበረ፣ የታፈረ ጥበብ ነበር።”

በተጨማሪም ዶ/ር ዮናስ አድማሱም ያንን ዘመን የጸሐፊዎቹን ውስጣዊ ስሜት “What were they writing about anyway? Tradition and Modernization in Ethiopian Literature” በተሰኘው ጥናታዊ ጽሑፋቸው እንዲህ ገልፀውት ነበር፦

“በአንድ በኩል ጠንካራ እና አክራሪ በሆነው የፊውዳል ገዢ መደብ እና ከዚያ በላይ አክራሪ በሆነው የቤተክርስቲያን አመራር፤ በሌላ በኩል ደግሞ ያልተማረው እና ለአዲስ ጉዳይ ከቶም ትኩረት በማይሰጠው ህዝብ መሃል ተገኙ። በተለይ የወቅቱ ማኅበረሰብ አለመማር እና ለአዲስ ጉዳዮች ፍፁም ትኩረት አለመስጠት፣ ምሁራኑን ምን እንደሚጽፉ ከማስጨነቅ አልፎ ለማን እንደሚጽፉ ያስቸገራቸው ወቅት ነበር።”

በእንዲህ ያለ ጊዜ መሀል የተገኙት ዮፍታሔ፡ ሁኔታውን የተረዱት፣ ጊዜውንም ቀድመው ያወቁት ይመስላሉ። “ነገሩ አልሆነልኝም” ወይም “ምንም ማድረግ አልችልም” ብለው ዕጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም። ለማስተማር፣ ለማንቃት፣ በሀሳብ እኩዮቻቸውን ለመሟገት ሞከሩ እንጂ። ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ የቴአትር ጽሑፋቸውን ከመጻፋቸው በፊት ብዕራቸውን ያሟሹት ጠንካራ የሆነ ማኅበራዊ ሂሶችን እና ርዕሰ ጉዳዮችን በወቅቱ ተነባቢ በነበረው የብርሃን እና ሰላም ጋዜጣ ላይ በማውጣት ነበር። ቀለል ካሉ ርዕሰ ጉዳዮች ተላቅቀው ከበድ ያሉ ጠንካራ ማኅበራዊ ርዕሰ ጉዳዮችን በጋዜጣው ማውጣት የጀመሩት በተለይ በ1919 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሊቀጳጳስ የነበሩት የአቡነ ማቴዎስን ሞት ተከትሎ ነበር። በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሷን ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን ማስመጣቷን መቀጠል አለባት የለባትም በሚለው ጉዳይ ላይ በዛ ያሉ ምሁራን ጎራ ለይተው በብርሀን እና ሰላም ጋዜጣ ላይ ይሟገቱ ነበር። ከተሟጋቾቹ አንዱ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ነበሩ። እንደ ዮፍታሔ አቋም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀጳጳስ ከግብፅ ድረስ ማስመጣቷ ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ያልተናነሰ ነው። የካቲት 3 ቀን 1919 ዓ.ም. “ፍርድ ማደላደል” አሰኝተው የጻፏት መጣጥፍ ይህን አቋማቸውን ማሳያ ናት፦

“እነሆ ለህዋሳታችን መብራት ዓይን ነው። ይሁን እንጂ ለዓይን መደቡ ነጭ ሲሆን አስተካክሎ የሚያይ እና ብርሀን የሚሰጠው ጥቁሩ አይደለምን? ጥቁሩ ዐይኔ አያይልኝም የሚል ቢኖር እንዳለው ይሁንለት፣ ይደረግለት። ይልቁንም ዐይኔን ግንባር ያድርገው ብሎ የማለ ይመስላል። ሁለተኛም እንደተፃፈው ከራስህ ጠጉር አንዱን ነጩን ጥቁር ለማድረግ የሚችል ማነው አለ። ጥቁር ከነጭ ቦታ ገብቶ የጥቁርን ማዕረግ እንዳይፈልግ አይደለምን? ነጭስ ከጥቁር ቦታ ገብቶ የጥቁርን ማዕረግ እንዳይመኝ አልነበረምን? ለሁለቱም ልዩ ልዩ ማዕረግ አላቸውና ይህ ምሳሌ ከየቦታቸው እንዳይተላለፉና እንዳይበላለጡ ያሳያል። ይህም ከሆነ አምልኮ ባዕድን ያስከትላል። መጽሐፉን ዐይቶ አባይ-ጠንቋይ፣ ቡሐ በግ፣ ነጭ በግ፣ ቀይ ዶሮ ገዝታችሁ አምጡና አድናችኋለሁ እንዲል እንዲሁም እኛ በነጭ መስቀል ካልተባረክን ጥቁር አይባርከንም ማለት አባይ-ጠንቋይ መሆን ነው።”

ይህን የዮፍታሔን ጽሑፍ በተለያየ መንገድ፣ የወቅቱን ሁኔታ አካቶ መተንተን የሚቻል ቢሆንም ሦስት ዋና ዋና የሀሳብ ማዕዘናትን ግን አስቀምጦ ማለፍ ይቻላል። ይህ ጽሑፍ የወቅቱን ሀሳብ ከመሞገት ባሻገር፡

ሀ) የሀይማኖት ነፃነት ክርክር ነው።

ለ) የሀገር ሉዓላዊነት ጥያቄ ነው።

ሐ) የዘርን ጉዳይ የሚመረምር ነው።

እነዚህ ዋና ሀሳቦች በዚህ ጽሑፍ ውስጥ በዋናነት የናኙ ሲሆን ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት ለመተንተን በር ይከፍታሉ።

ከዚህም ባሻገር የነፃነትን ጉዳይ ጠንከር አድርገው ከጻፉባቸው መጣጥፎች መሀልም ዮሐንስ አድማሱ “ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ፡ አጭር የጽሑፉ እና የሕይወቱ ታሪክ” በተሰኘው መጽሐፉ በ1939 ዓ.ም. የተፃፈ ነገር ግን ያልታተመ ብሎ በገለፀው “ንጉሡ እና ዘውዱ” በተሰኘው መጣጥፋቸው እንዲህ ብለው ነበር፦

“የማንም መንግሥት ሕዝብ የመንፈስ ተገዢነት ከሌለው መንፈሱ በበጎ ተግባር ታሽቶ ሳይለዝብ የዘገየ ነውና የአንድነቱን መንፈስ ተቀዳሚ አድርጎ የንጉሠ ነገሥቱን መንግሥት ለማገልገል የሚወጣበትን መሰላል ጀርባ ጠባቂ ያደርገዋል። የመንፈስ ተገዢነትሳ በምን ላይ ሲገኝ፣ ማን ያመጣዋል? ትለኝ እንደሆነ የሚገኘው በቤተ ክህነት የሚያመጣው አስተማሪነት ነው፤ አስተማሪውም እውነተኛ አስተማሪነቱን የሚገልጠው የመንፈስ ነፃነት ብቻ ሳይሆን የአካል ሙሉ ነፃነት ሲኖረው ነው።”

የቴአትር ጉዞ

በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ የመጀመሪያው የቴአትር ጸሐፊ የሆኑት ተክለሐዋርያት ተክለማርያም በቴአትራቸው መግቢያ ባሰፈሩት ጽሑፍ ከሳቸው በኋላ ስለሚመጡ ቀጣይ ጸሐፊያን ሁኔታ እንዳሳሰባቸው ሳይገልፁ አላለፉም። ተክለሐዋርያት የቴአትርን ሀሳብ ከአውሮፓውያን ሕይወት እና ኑሮ ጋር ብቻ በማያያዝ “አውሮጳን ያየ ሰው ቴአትር ምን እንደሆነ ያውቀዋል።” ማለታቸውን እና በኢትዮጵያ ይህ ሀሳብ የሚገባው አይኖርም ብለው በመስጋታቸው እንዲህ ሲሉ ጻፉ፦

“ሀሳባችንን በትክክል የሚቀበሉን ሰዎች ከተገኙ ደግሞ እውቀታቸው ለዚህ የሚስማማ በተፈጥሮ ለዚህ ዓይነት ስራ የታደሉ ደራሲዎች አውቀው ብቅ ማለታቸው አይቀርም። ጊዜ ላመሉ ይጠራቸዋል።”

‘ጊዜ ላመሉ’ ከጠራቸው መሀል ዮፍታሔ አንዱ ሆኑ!! ከዋነኞቹ የቴአትር ጀማሪዎች መሀል ዮፍታሔ አንዱ መሆናቸውን እና የቴአትርን ጥበብንም ከፍ ማድረጋቸውን ከተክለሐዋርያት ሀሳብ በመቀበል በለጠ ገብሬ “በዕድሜ ጎዳና ላይ የጉዞ ትዝታ” በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዲህ ያስታውሳሉ፦

“ቀደም ሲል በዳግማዊ ምኒልክ እና በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤቶች አንዳንድ ቴአትሮች ማሳየት ተጀምሮ እንደነበር ስንኳ ባይዘነጋ፣ በሰፊው የታሰበበት እና ስራ ተብሎ የተያዘው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የንጉሠ ነገሥትነት ዘውድ ከተቀዳጁበት ዘመን ከ1923 ዓ.ም. በኋላ ነው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በየትምህርት ቤቱ አካባቢ ያሉ መምህራን እና መዘምራን በዓሉን በማወደስ እና አዲሱን መሪ በማሞገስ፣ ልዩ ልዩ ቴአትር እና ድርሰት እያዘጋጁ የንጉሠ ነገሥቱን ስሜት ለመማረክ ሲሽቀዳደሙ እና ሲፎካከሩ ይታዩ ነበር። ከነዚህ መካከል በቴአትር ዝግጅት እና አቀራረብ፣ በሰም እና ወርቅ ግጥም አደራረስ እና ዜማ በማቀንቀን እስከ ዛሬ ተወዳዳሪ ያልተገኘላቸው ዝናማው ሊቅ ዮፍታሔ ንጉሤ ገና በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የአማርኛ መምህር ሳሉ ባሳዩአቸው ሁለት ቴአትሮች ችሎታቸውን አስመስክረው የቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት ቤት ዲሬክተር ለመሆን በቅተዋል።”

ዮሐንስ አድማሱም “ለማስታወስ ያህል” አሰኝቶ በጻፈው መጣጥፍ ስለ ዮፍታሔ ቴአትር አጀማመር እንዲህ ብሎ ነበር፦

“ዮፍታሔ ንጉሤ ወደ ቅኔ እና ወደ ግጥም ዓለም የገባው የቅኔ እና የዜማ ትምህርት ቤት በነበረበት ጊዜ ነው። ወደ ቴአትር ዓለም ግን መቼ እና በምን ምክንያት እንደገባ ለማወቅ ለጊዜው አልቻልኩም። ይሁን እንጂ ወደዚህ ስራ ያስገባው አንዱ ምክንያት አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ለአማርኛ መምህርነት መመልመሉ ይመስለኛል። በዚያን ጊዜ በብዛት ተውኔት የሚጽፉ እና የሚያሳዩ መምህራን እና ተማሪዎች ነበሩ። የሚያሳዩትም ብዙውን ጊዜ በየትምህርት ቤቱ እና በዘመኑ በነበሩ ሆቴሎች ውስጥ ነው። ለዮፍታሔ ወደ ቴአትር ዓለም መግባት ሁለተኛ ምክንያት የሆነው የጊዜው ሁኔታ ይመስለኛል። በ1900 እና 1928 መካከል ኢትዮጵያ ብዙ ተፈትናለች። ደራሲያኑም የህዝቡን ስሜት እና ልቦና ለመንካት ለማነቃቃት ምናልባትም ዋና መንገድ የሆናቸው “የዘመኑ መድረክ” ይመስለኛል።”

ዮፍታሔ ንጉሤ ለመጀመሪያ ጊዜ ቴአትር በመናጆ (በጋራ) የጻፉት በ1919 ከአቶ በቀለ ሀ/ሚካኤል ጋር እንደሆነ መዛግብት ያስረዳሉ። ከ1920 በኋላ ግን ለብቻቸው መጻፍ ጀመሩ። የቴአትር ስራቸውንም እየሰሩ በ1924 ዓ.ም. የቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሆኑ። ከ1924 ዓ.ም. እስከ 1928 ዓ.ም. በቴአትር ተመልካች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኙባቸውን ቴአትሮች ደረሱ። በ1925 ‘ዳዲ ቱራ’ እና ‘እመት አታላይ ባላቸውን አቶ ማታለያን እንዳስታመሙ’፣ በ1926 ዓ.ም. ‘የህዝብ ፀፀት የዕመት በልዩ ጉዳት’፣ በ1927 ‘መሸ በከንቱ ስራ ለፈቱ’ እና ‘የደንቆሮዎች ቴአትር’ እንዲሁም ከጣሊያን ወረራ በኋላ በ1933 ‘አፋጀሽኝ’፣ በ1934 ‘እያዩ ማዘን’ እና ‘ዕርበተ ፀሐይን’ ጽፈዋል።

በወቅቱ ከጣሊያን ወረራ በፊት ብርሃን እና ሰላም ጋዜጣ፣ ከጣሊያን ወረራ በኋላ አዲስ ዘመን ጋዜጣ የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ቴአትርን በተመለከተ የተለያዩ ጽሑፎችን ይዘው ይወጡ ነበር። ለምሳሌ በሚያዝያ 27 ቀን 1934 ዓ.ም. አዲስ ዘመን ጋዜጣ “አፋጀሺኝ” የተሰኘውን የዮፍታሔን ቴአትር በተመለከተ የሚከተለውን ብሎ ነበር፦

“አቶ ዮፍታሔ ንጉሤ የግርማዊ ጃንሆይ የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ የፊተኛውን እና የአሁኑን አኳኋን በቴአትር ለማሳየት ከግርማዊ ጃንሆይ ፈቃድ ስላገኙ ሀዘን ተፍስሀ ያለበት ማለት የህዝቡን አዕምሮ በፍፁም በሀዘን እንዳይታወክ የሚያስቅ ነገር ቀልቀል እያደረገ ብዙ ታሪክ የሚገልፅ ሀሳብ አውጥተው ስሙንም አፋጀሽኝ ብለው ሰይመው ብዙ ወጣቶች ሰብስበው ስራውን ሲያስተምሩ ሰነበቱ።”

ስለዮፍታሔ ልዩ ልዩ ቴአትሮች፣ በተለይም ስለ ዝነኛዋ አፋጀሽኝ ሰፊ ትንታኔ መስጠት እና መወያየት ይቻላል። ነገር ግን የዚህ ጽሑፍ አላማ ስለ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ አጠር ባለ መንገድ ለአንባብያን ማስታወቅ በመሆኑ ዝርዝር ትንታኔ ውስጥ አልገባም። ነገር ግን ቴአትርን በተመለከተ በተደጋጋሚ በቴአትር ባለሞያዎች ዘንድ መከራከርያ ስለሆነው የሴት ተዋንያን ጉዳይ አንድ ሁለት ማስረጃ በማቅረብ “ማስተካከያ” መሰል ነገር ለማቅረብ ልሞክር።

የሴት ተዋንያን ጉዳይ

በዛ ያሉ የኪነ-ጥበብ ሰዎች እና ተመራማሪዎች በኢትዮጵያ የመድረክ ትወና ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት የመድረክ ተዋናይ ሰላማዊት ገ/ሥላሴ እንደሆነች ጽፈዋል። ለምሳሌ መዓዛ ወርቁ (Women and Ethiopian Theater) በተሰኘ ጽሑፏ ሰላማዊት ገ/ሥላሴ የመጀመሪያዋ ሴት ተዋናይት እንደሆነች ስትጽፍ “ብዙዎች ዝነኛዋን ድምፃዊ፣ ተወዛዋዥ እና ተዋናይት አስናቀች ወርቁን “ዘመናዊ” ተብለው በሚቆጠሩ በዛ ያሉ ቴአትሮች ላይ በመሳተፏ ምክንያት በኢትዮጵያ ቴአትር የመጀመሪያዋ ተዋናይት አድርገው ሲቆጥሯት ሌሎች ደግሞ በቴአትር ትወና ላይ በመሳተፏ ሰላማዊት ገ/ሥላሴ የመጀመሪያዋ ተዋናይት አድርገው ይቆጥሯታል። ተባባሪ ፕሮፌሰር አቦነህ አሻግሬም የእሷን ሀሳብ ይጋራሉ። ፕሮፌሰሩ The role of women on the Ethiopian stage በተሰኘ ጥናታዊ ጽሑፋቸው “በ1951 ዓ.ም. በብርሀኑ ድንቄ በተፃፈው የሳባ ጉዞ በተሰኘው ቴአትር ላይ ንግሥት ሳባን ሆና በመጫወት ወ/ሮ ሰላማዊት ገ/ሥላሴ ከዚያ በፊት የኢትዮጵያ የቴአትር መድረክ አጥቶት የነበረውን የሴት ተዋንያን ችግር ፈታለች።” ይላሉ። ነገር ግን ከዚህ ቀጥሎ የማስቀምጣቸው ሁለት ጽሑፎች ወ/ሮ ሰላማዊት ገ/ስላሴ የኢትዮጵያ ቴአትር የመጀመሪያዋ ሴት ተዋናይ እንዳልሆነች መረጃ የሚሰጡ ናቸው። በዚህም ስራቸው ዮፍታሔ ንጉሤ የመጀመሪያዎቹን ሴት ተዋንያን ለኢትዮጵያ ቴአትር በማስተዋወቅ ረገድ ከፍ ያለ ሚናን እንደተጫወቱ ማሳያ ነው። ዮሐንስ አድማሱ ወ/ሮ ሰላማዊት የመጀመሪያዋ ሴት ተዋናይ ናቸው የሚለውን መደምደሚያ አፍርሶ ዮፍታሔ ንጉሤ ሴት ተዋንያንን ለኢትዮጵያ መድረክ በማስተዋወቅ ቀዳሚ እንደነበሩ ይገልፃል።

“በ1925 ዓ.ም. በተሰራው “ዳዲ ቱራ” በተሰኘው ቴአትር ላይ ሁለት ቆነጃጅት መሪ ተዋንያን ሁነው ሰርተው ነበር። ሴቶች እመድረክ ላይ ወጥተው፣ በቴአትር ውስጥ ፍጆታ ተሰጥቷቸው ሲሰሩ እነዚህ ሁለት ቆነጃጅት የመጀመሪያዎቹ መሆናቸው ነው። በዚህ ረገድ “ዳዲ ቱራ”ም ሴቶች ከወንዶች ጋራ እኩል ተሰልፈው፣ ፍጆታ ተሰጥቷቸው የሰሩበት የመጀመሪያው ቴአትር ነበር። ለዚህ የስልጣኔ አካሄድ በር ከፋቹ ዮፍታሔ ነበር።” (ገፅ 78)

ይህንን ሀሳብ በለጠ ገብሬ “በዕድሜ ጎዳና ላይ የጉዞ ትዝታ” በተሰኘ መጽሐፋቸው በሚገባ ያረጋግጡታል። ሰፋ ያለ ትንታኔም ይሰጣሉ፦

“…ለዚሁም አብነቱ ተሰጥኦ አመራረጥ ስለሆነ፣ ለዝማሬው ለተውኔቱም አቀናባሪነት ዮፍታሔ ከየወገኑ የመረጧቸው ልጃገረዶች ወንዶች ንቃት፣ ቅልጥፍናና የአክተርነት ችሎታ በጣም የሚደነቅ ነበር። […] ከልጃገረዶች አንዲቱ ለአያሌ ዓመታት በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የርስት ክፍል ሹም የነበሩት የአቶ አንዳርጌ ሴት ልጅ ቀፀላ አንዳርጌ፣ በተሳተፈችባቸው ትርኢቶች ሁሉ “የኮከቦች ኮከብ” ለመባል የበቃች ግንባር ቀደም አርቲስት ነበረች። ይህም በአነጋገር ችሎታዋ፣ በአቀራረብ ስልቷ እና ከሊቁ ደራሲ ባጠናችው ጣፋጭ ዝማሬዋ ማራኪነት ብቻ ሳይሆን፣ ከተፈጥሮ ፀጋ በታደለችው ዐይን አገላለጧ፣ ብሩህ ጠይም መልኳ፣ ሙሉ ቅርፀ አካሏ እና ጠቅላላ እንቅስቃሴዋ የዕድምተኞችን ዓይን የሚስብ ጠባያዊ ተሰጥኦ ስላጎናፀፋት ነበር።

ሌላይቱ ጉብል ደግሞ ትርኢት ላይ “እመየት ቸኮለች” የሚል ስም ተሰጥቷት እንደ ጠጅ ኮማሪት ሆና ስትጫወት፣ የሐር ነዶ መሳይ ክምር ጎፈሬዋን በደንብ አበጥራ፣ በጥበብ ኩታ እና በሸብሸቦ ቀሚስ ሽቅርቅር ብላ ሳብ-ረገብ ባለው ሽንጥ እና ዳሌዋ እያረገረገች በጠጭዎች መኻል ሽር-ጉድ በማለት፣ ዓይነ ገብ ዓይኖቿን ግራ እና ቀኝ ሰረቀ፣ ነጫጭ ጥርሶቿን አንዳንድ ጊዜ ፍልቅ እያደረገች ስትሽኮረመም ፍፁም ያራዳዋን የነጋድራስን ቀፀላ የልጅ ልጅ መስላ የታየችው አሰለፈች ማሞ ነበረች።”  

እነዚህ ማሳያዎች የመጀመሪያ ሴት ተዋናይ (ተዋንያንን) በማስተዋወቅ ረገድ ዮፍታሔ ንጉሤ ያደረጉትን ታላቅ አስተዋፅኦ በይፋ የሚያሳይ ነው። በዚህም ዮፍታሔ በኢትዮጵያ ቴአትር ታሪክ ከደራሲነት ባሻገር የመጀመሪያዋን (የመጀመሪያዎቹን) ሴት ተዋናይ (ተዋንያን) ለመድረክ በማብቃት ሲታወሱና ሲመሰገኑ ይኖራሉ።

አርበኝነት

የጣሊያን ወረራን ከብዕር ባሻገር በተግባርም ከተፋለሙት አርበኞች መሀል ዮፍታሔ ንጉሤ አንዱ ናቸው። በሰላም ጊዜ ማኅበረሰቡን የሚያንፅ እና የሚያወያይ ርዕሰ ጉዳይ በማንሳት በቴአትራቸው ሲሞግቱ ሰላም በጠፋ እና ሀገር በተወረረች ጊዜ ደግሞ ነፍጥ በማንገብ፣ አርበኞችን በማገዝ ለሀገር ነፃነት ታግለዋል። ደጃዝማች ከበደ ተሰማ “የታሪክ ማስታወሻ” በተሰኘው መጽሐፋቸው በአርበኝነት ሀገራቸውን ያገለገሉ ሲሉ ከጠቀሷቸው ሰዎች መሀል ዮፍታሔ ንጉሤ አንዱ ናቸው፦

“…እነዚህ ሰዎች በስደት ከኢትዮጵያ ከወጡ በኋላ እንደገና በበጌምድር እና በጎጃም፣ በወለጋ በኩል እየወጡ የግርማዊነታቸውን የፖለቲካ ትግል ለአርበኞች በማስረዳት ማበረታታት እና እንደዚሁም የአርበኞችን ተጋድሎ እና ብርታት ለግርማዊነታቸው እንዲደርስ በማድረግ ራሳቸውን መስዋዕት በማድረግ ለኢትዮዮጵያ ነፃነት የተጋደሉ ናቸው። ለተከታዩ መግቢያ በር በመጀመሪያ በእነዚህ ጀግኖች የተመሰረተ ነው።

  • አቶ ጌታሁን ተሰማ (ባርማጭሆ፣ በጭልጋ፣ በጎጃም)
  • አቶ ገ/መስቀል ኃ/ማርያም (በጎጃም)
  • አቶ ዮፍታሔ ንጉሤ (በጎጃም)
  • ባላምባራስ አሸብር ገ/ሕይወት (ባርማጭሆ) … ” (ገፅ 212)

ዮሐንስ አድማሱም የህይወት ታሪካቸውን ባሰፈረበት መጽሐፉ ይህንን ሀሳብ ያጠናክራል፦

“ዮፍታሔ ከኢትዮጵያ ተሰድዶ ወጥቶ እካርቱም ከገባ ወዲህ፣ እዚያም እንዲቀመጥ ከተፈቀደለት በኋላ፣ የቅኔ ተልዕኮውን፣ ስጋዊ እና መንፈሳዊ ተጋድሎውን መደብ አድርጎ በሚስጢር በጎጃም፣ በበጌምድር እና ሰሜን በኩል ወደ ኢትዮጵያ መልዕክት ለማድረስ፣ ኢትዮጵያም የሚያገኘውን ጠቃሚ እና ዓይነተኛ ጉዳይ ወደ ሎንዶን ለማስተላለፍ ወደ ኢትዮጵያ እየመጣ ከአርበኞቹ እና ከመሪዎቻቸው ጋር ተገናኝቷል። እንግሊዞችም ይህንን የሚስጢር ስራውን ሰምተው ስላወቁ አስረውት ነበር ይባላል።”

በጊዜው የዮፍታሔ ንጉሤ ቴአትሮች ላይ በመተወን ከሚታወቁት ወጣት ባለሞያዎች አንዱ የነበሩት አቶ በለጠ ገብሬ ስለግል ህይወታቸው በጻፉት መጽሐፋቸው የዮፍታሔን አርበኝነት እና የድርሰት ስጦታ በማስታወስ ይቆጫሉ፦

“ዮፍታሔ ከቴአትሮቻቸው ላይ ስለ ኢትዮጵያ ድቀት እና ትንሳኤ “ዓመተ ምህረት” ብለው በመሰየም የጻፉትንም ዕፁብ ድንቅ ድርሰት ሳልጠቅሰው ማለፍ አይገባኝም። እሱም ሱዳን ውስጥ ስለነበረው የስደተኞች ህይወት እና እርሳቸው ወደ አርበኞች እየተላኩ እስከ መሀል ጎጃም ተደብቀው በመግባትና በመውጣት ስለፈፀሙት ተልዕኮ ከዚያም በንጉሠ ነገሥቱ አዝማችነት ከካርቱም እስከ ደብረ ማርቆስ የተደረገውን አስቸጋሪ ጉዞ እና ጠላትን በማጥቃት የተገኘውን አኩሪ ድል፣ በልብ ወለድ ወግ የተረኩበት መጽሐፍ ሲሆን እስከዛሬ አለመታተሙ ያሳዝናል።”

ለማጠቃለል

አንዳንድ ሰው አለ ለየት ያለ፣ ድንገት የሚከሰት፣ ሊደገም ጊዜ የሚፈልግ። እንዲህ ያለ ሰው ብቅ ሲል በተሰማራበት ሙያ ቢነገር የማያልቅ፣ ቢወራ የማይሰለች ስራ ጥሎ ያልፋል። ይህም ስራው ከሱ ወዲያ ለሚመጣውም ትውልድ ፋና ሆኖ ብዙዎች እንዲረማመዱበት ይፈቅዳል። በር ይከፍታል። ይህንን ሀሳብ ጠቅለል አድርጎ፣ ቅን ልቡና በታከለበት ቋንቋ፣ ውበት በተሞላበት አንደበት ዮሐንስ አድማሱ በሰኔ 25፣ 1961 መነን መጽሔት ላይ ስለዮፍታሔ የጻፈውን ማጠቃለያ አስቀምጬ ሀሳቤን ልቋጭ፦

“ኮከብ እምኮከብ ይኄይስ ክብሩ” የሚል የኖረ የግዕዝ አባባል አለ። አንዱ ኮከብ በብርሀኑ፣ በግዝፈቱ፣ በጠቅላላ ተፈጥሮው ከሌላው ኮከብ ይበልጣል። እኔን የሚያስገርመኝ ይሄ አይደለም። አንዳንድ ከዋክብት አሉ እኛ በተለየ አጠራር ተወርዋሪ የምንላቸው። በሌሊቱ ኅዋ ውስጥ ከአንዱ ማዕዘነ ሰማይ ወደ ሌላው ተወርውረው ብልጭ ብለው ይጠፋሉ። ይህ ሁሉ የሚሆነው በቅፅበት ነው። ያንን በጨለማ ግርማ የተዋጠውን ኅዋ በብርሀን ጎርፍ ሰንጥቀው አጥለቅልቀውት ይጠፋሉ። ተመልካችም ከመገረም በሚመነጭ ዝምታ ይዋጣል። በኢትዮጵያ ስነጽሑፍ ኅዋ ውስጥ ዮፍታሔ ንጉሤ አንድ ታላቅ ተወርዋሪ ኮከብ ነበረ።”

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top