ታዛ ወግ

የፖለቲካ ባህል እና ሕገመንግሥታዊነት

የፖለቲካ ባህል ማለት አንድ ኅብረተሰብ በረጅም ዘመናት ውስጥ ካካበተው የአስተዳደር ልምድ የተነሳ የሚኖረውን ፖለቲካዊ ግንዛቤና ዕይታ የሚያመለክት ፅንሰ ሀሳብ ነው። በሌላ በኩል ሕገመንግሥታዊነት (Constitutionalism) ማለት ደግሞ ከበዘፈቀደ አገዛዝ (Arbitrary rule) ወጥቶ በሕገመንግሥት የመተዳደርን ባህል የሚያመለክት ሲሆን፤ ማን? ለምን ዓላማ? ከመቼ እስከ መቼ ማስተዳደር እንዳለበት የሚወስን በአስተዳዳሪውና በሚተዳደረው ህዝብ መካካል የሚደረግ የቃል ኪዳን ውል ነው። የሕገመንግሥታዊነት ዋና ዓላማ ደግሞ የሚያስተዳድረው አካል ፈላጭ ቆራጭ እንዳይሆን ስልጣኑን የሚገድብና አንዱን በሌላ የሥልጣን ቁጥጥርና ሚዛን እንዲኖር የሚያደርግ፣ ለድርጊቶች በቀጥታ የህዝብ ወይም የህዝብ ተወካዮችን ይሁንታ የሚጠይቅ የአስተዳደር ባህል ነው። ለምሳሌ በሕግ አውጪ፣ በሕግ ተርጓሚና በሕግ አስፈፃሚ መካካል የሥልጣን ድልድል፣ ቁጥጥር እና ሚዛን መኖር አንዱና መሰረታዊው የሕገመንግሥታዊነት መገለጫ ነው።

በአገራችን ኢትዮጵያ፣ ስለነበረውና አሁንም ስላለው የፖለቲካ ባህል ለመፃፍ ምናልባት ከአክሱም ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ያለውን የአስተዳደርና የሥነ መንግሥት ባህል መፈተሽ ያስፈልግ ይሆናል፤ ሕገመንግስታዊነትን በተመለከተ ደግሞ ከክብረ ነገሥት እና ፍትሀ ነገሥት ጀምሮ እስከ አፄ ኃይለሥላሴ የጀመረው ዘመናዊ ሕገመንግሥት፣ የደርግና የኢህአዴግ ሕገመንግሥቶች መፈተሽና መተንተን የሚያስፈልግ ጉዳይ ነው።

ነገር ግን እነዚህን ሁሉ ለመዳሰስ ሰፊ ሃተታ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ በዚህ ፅሁፍ ዘመናዊው ሕገመንግሥታዊ ስርዓታችንና የፖለቲካ ባሕላችን ምን እንደሚመስል እንመለከታለን። ነገርን ሁሉ ከባህላዊ ትውፊታችን በሚቀዳ ምሳሌ ወይም ታሪክ መጀመር ጥሩ ነው፤ የፖለቲካ ባህላችን ምን እንደሚመስል ከሚያሳይ አንድ የቆየ ታሪክ እንነሳ፦

በአንድ ገዳም ውስጥ ብዙ መነኮሳት አብረው ይኖራሉ፤ ከእነርሱ አንድ አስተዳዳሪ ይመርጣሉ፣ ሌሎቹ መነኮሳት በገዳሙ ያሉትን ሥራዎች ማለትም ምግብ ማዘጋጀት፣ እህል መፍጨት፣ እህል መዝራት፣ አትክልት መኮትኮት፣ የመስኖ ውሃ ማጠጣት፣ የመነኮሳቱን መኖሪያ መገንባት ወይም መፈልፈል፣… የመሳሰሉትን ስራዎች በየዕለቱ የሚያከናውኑ ሲሆኑ፣ የአስተዳዳሪው ዋና ሥራ እነርሱን ማስተባበርና ከተራራ ላይ ቁጭ ብሎ ሥራቸውን መቆጣጠር ነው፤ የጉልበት ሥራ አይሰራም።

ገደሙ ውስጥ ያሉት መነኮሳት የሚተዳደሩበት የራሳቸው የሆነ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ገዳማዊ ሕግ አላቸው፡፡ ሕጉ መሻሻል ቢያስፈልገው የማሻሻል ስልጣኑ የአበምኔቱ (የአስተዳዳሪው) ነው፡፡ በገዳሙ ሕግ ውስጥ ከተፃፉ ሕጎች መካካል የገዳሙ መነኮሳት ጢማቸውን ማሳጠርም ሆነ መቁረጥ የሚከለክል አንቀፅ ነበረው። የገዳሙ መነኮሳት ሲቆፍሩም ሆነ እህል ሲፈጩ ወይም ማንኛውም ሥራ ሲያከናውኑ የጢማቸው መርዘም በጣም ያስቸግራቸዋል፡፡ ከእለታት በአንዱ ቀን ሰብሰብ ብለው ወደ አበምኔቱ በመሄድ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ጥያቄው የጢም ማስረዘምን የተመለከተው አንቀጽ እንዲሻሻል የሚያሳስብ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አበመኔቱ የተጠየቀውን አንቀጽ ለመቀየር ፍቃደኛ አልሆነም፤

“በቀደምቶቹ አባቶች ተፅፎ የቆየውን ሕግ እኔ ልለውጠው አልችልም፤ ጢም ለአንድ መኖኩሴ ግርማው፣ መአርጉ በመሆኑ ይላጭ ወይም ይቆረጥ ዘንድ አልፈቅድም” አላቸው፡፡

መነኮሳቱ አለቃቸው ችግራቸውን ሊረዳላቸው ባለመቻሉ ሌላ አስተዳዳሪ ለመምረጥ ተስማሙ፡፡ ከመካከላቸው በዚህ ጉዳይ ላይ አብዝቶ ይከራከር የበረውን መነኩሴ የገዳሙ አስተዳዳሪ (አበምኔት)  አድርገው መረጡት። አዲሱ አበምኔት የተመረጠበትን የጫጉላ ጊዜ ካበቃ በኋላ መነኮሳቱ ተሰብስበው የቀደመ ጥያቄአቸውን አነሱ፡፡  

“በል አሁን ጢም ማሳጠር ወይም መቁረጥ የሚከለክለውን አንቀፅ ቀይርልን” አሉት፡፡

አዲሱ ተሿሚ በቆየባቸው አጭር የስልጣን ሳምንታት ውስጥ ተራራ ላይ ቁጭ ብሎ ጢምን እየደባበሱ መነኮሳቱን መመልከት ያለውን አዝናኝነት ወዶታል፡፡ ጢም ለስራ ባይመችም ለእልቅና እንደሚመች ተገንዝቧል፡፡

ቆጣ ብሎ “እ… እናንተ! እኔ አበምኔት ስሆን ነው እንዴ ፂም ይቅር የምትሉት?!”

በማለት ጥያቄአቸውን በጥያቄ መለሰ፡፡ የለፉለት ለውጥ በእርሱ የስልጣን ዘመን እንደማይሳካ ነግሮ አሰናበታቸው፡፡

የእኛ አገር የፖለቲካ ባህልም ከዚሁ ታሪክ ብዙ የሚርቅ ነገር አይደለም፡፡ ከአፄ ኃይለሥላሴ ጀምሮ እስከ አሁን ያለውን የፖለቲካ ባህላችንን ከነበሩት ሕገመንግሥታት አንጻር ለማየት እንሞክር፡፡

በአገራችን የመጀመሪያ የሆነው ዘመናዊ ሕገመንግሥት የፀደቀው በ1923 ዓ.ም አፄ ኃይለሥላሴ የነገሱበት 2ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ለህዝቡ በአዋጅ ያስነገሩት ሕገመንግሥት ነው። ጃንሆይ በዕለቱ ያደረጉትን ንግግር መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንዲህ ዘግበውታል

እኛ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ፣

በእግዚአብሄር ቸርነት ለሕዝቡ ኅብረት ለኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትነት ተመርጠን ዘውዱንና ዙፋኑን በሕግ አገባብ ተቀብለን ስንበቃ ለዚህ ታማኝ ልንሆን ለመረጠን ፈጣሪያችን የምመልሰው ወረታ የተቀበልነውን አደራ እኛም ሰርተን ጠብቀን ተከታያችንም በሕግ እንዲቀበለንና በደንብ እንዲሠራ ለአገራችንም በመልካም አስተዳደር በሕግ የሚጠበቅበትን ደንብ ከማቆም በቀር ሌላ የምንመልሰው ወረታ ስለሌለን ለኢትዮጵያ ልማት ለመንግሥታችን ፅናት ለምንወደው ሕዝባችንም ጥቅምና ሀብት ሆኖ ደስ እንዲያሰኝ ተስፋ ስላደረግን አሳባችንን ገልጸንና አስረድተን የመንግሥት ሕግ እንዲቆም ቆረጥን…።

ስለዚሁም ሁሉ ነገር በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዙፋን ላይ ከተቀመጥን ጀምሮ ከእግዚአብሄር እጅግ ታላቅ የሆነ አደራ ስለተቀበልን መንግሥታችን የሚፀናበትን፣ የሕዝባችን ኑሮ የሚሻሻልበትንና ሕዝባችን ወደ ታላቅ የሥልጣኔና የደስታ መንገድ ተመርቶ ነፃ የሆኑና የሰለጠኑ ህዝቦች ያገኙትን መልካም ነገር ሁሉ የሚያገኝበትን ማወጅና ማሠራት የሚገባ መሆኑን አስተውለን፤ ይህንንም ለማድረግ የሚያስፈልገው ፍሬ ነገሩ ወደፊት ያለውን የመንግሥት ሕግ አቋቋም አጣርተን የመንግሥት ሥራ ሁሉ እንዲያከናውን፣ የሕዝቡም የደስታ ኑሮ እንዲረጋገጥ፣ ለልጅ ልጅም የሚያልፍ ክብር እንዲገኝበት መንግሥቱም በሰለላምና በጸጥታ እንዲኖር ለማድረግ መሆኑን አስተውለን ይህም እጅግ ከፍ ያለው አሳባችን መንግስታችንንና ሕዝባችንን ከታላቁ ታሪክ ከፍተኛ ማዕረግ ለማድረስ ስለሆነ ንጉሠ ነገሥቱ ዙፋን ተቀምጠን በነገሥንበት በሁለተኛው ዓመት በ1923 ዓ.ም. ማንም ሳይጠይቀንና ሳያስገድደን በፈቃዳችን ይህንን የመንግሥት ሕግ በአዋጅ አቁመናል።

ንጉሠ ነገሥትቱ በተሰበሰበው ህዝብ ፊት ሕገመንግሥቱን በወርቅ ብዕራቸው ፈርመው ያፀደቁት ሲሆን፣ መሳፍንቱና መኳንንቱ ከአልጋ ወራሹ ጀምሮ እንዲሁም ጳጳሳትና የተፈቀደላቸው ሚኒስትሮች፣ ሹማምንትና ሊቃውንት በሕገመንግስቱ ግርጌ ላይ “እኛም የኢትዮጵያ ጳጳሳትና መሳፍንት፣ መኳንንት፣ ሹማምንትና ሊቃውንት ይህን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ያቆሙልንን ሕግ ወደን ተስማምተን ተቀብለናል።” ብለው እንዲፈርሙ ተደርጓል።   

በወቅቱ ሕገመንግስት ማውጣት ያስፈለገበት ዋና ምክንያት ሊግ ኦፍ ኔሽን ይባል የነበረው የዓለም መንግሥታት ማኅበር አባል ለመሆን ሀገራት ሕገመንግሥት ያላቸው መሆን የግድ ይል ስለነበረ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በወቅቱ አባል ለመሆን አመልክታ በመጀመሪያ የባሪያ ንግድ እንድታስወግድ እንደቅድመ ሁኔታ ተቀምጦላት የነበረ ከመሆኑም በላይ አገሪቱ የምትተዳደርበት የራሷን ሕገመንግሥት እንደሚያስፈልጋትም እንደዚሁ ግልፅ ነበር። በዚህ ምክንያት ነው ልዑል ራስ ካሳ በሕገመንግሥቱ ምርቃ ዕለት ባሰሙት ንግግር እንዲህ ያሉት

“የማኅበር ጓደኝነት ያበጀ ሰው ያንኑ ማኅበርተኛውን መምሰል በግድ የሚያስፈልገው መሆኑን በዘመኑ ያለነው ሁላችን ስለተረዳነው ይህ ሕግ እንኳን እኛ ተጠቃሚዎቹን ለሰው ነፃነት የቆመውንም ማኅበር ደስ የሚያሰኝልን በመሆኑ ደስ እያለን በኢትዮጵያ መሳፍንቶች፣ መኳንንቶች፣ በራሴም ስም ሆኜ ለሚገባቸው ንጉሠ ነገሥታችን ጤና ለአገራችንም ልማት ጽዋዬን አነሳለሁ።”

ምክንያቱ ምን ይሁን ምን፣ በወቅቱ ኢትዮጵያ ዘመናዊ ሕገመንግሥት እንዲኖራት ሆኗል። ሕገመንግሥቱ በሚለው መሰረት በወቅቱ የነበሩትን ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች ራሳቸውን ችለው በተቀመጠላቸው ሕግ መስራት ጀመሩ። በዚህ ምክንያት ንጉሡ ቤተ መንግሥት ሄዶ አቤቱታ የሚያቀርብና እጅ የሚነሳ ዜጋ እየቀነሰ መሄድ ጀመረ። ንጉሠ ነገሥቱ በራሴ ወድጄና ፈቅጄ ያቆምኩት ሕገመንግሥት ባሉት ሕግ ምክንያት ተፈላጊነታቸው እየቀነሰ የሚሄድ ስለመሰላቸው “ሕዝቡ የንጉሡን ዓይን ማየትና በረከታቸውን መካፈል ይፈልጋል፤ ስለዚህ እንደበፊቱ እየመጣ እጅ ይንሳ፤ ተዉት አትከልክሉት” በሚል ምክንያት ነገሮች ሁሉ ቀስ በቀስ ወደ ቀድሞው አሰራር መልሰው ሕገመንግሥቱ የይስሙላ ሕግ ሆኖ እንዲቀር ፈረዱበት።

“ሕዝባችን በማነኛውም ረገድ ወደ ሥልጣኔ ደረጃ እየገፋ ስለሄደ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀድሞ ነገሥታቱ ብቻቸውን ይደክሙበት የነበረውን ከባድ የሆነ የመንግሥት ሥራ ተካፋይ እንዲሆን ይደረጋል” ያሉትን ቃላቸው አጥፈው፣ እንደ ድሯቸው ከሕግ በላይ ሆነው በፈላጭ ቆራጭነታቸው፣ በአድራጊ ፈጣሪነታቸው ቀጠሉበት። ይሄም ነገር ባህል ሆኖ ከእርሳቸው በኋላ የመጡት መሪዎችና መንግሥታትም ለታይታ ብቻ፣ ከፈረንጅ ጋር ለመመሳሰል፣ “ሕገመንግሥት የላቸውም” እንዳይባሉ ለራሳቸው በሚጠቅም ይዘትና ቅርፅ ለራሳቸው የሚስማማቸውን ሕገመንግሥት እያወጡ ነው የቀጠሉት።

ጃንሆይ የመጀመሪያውን ሕገመንግሥት ሲያረቁ ከሕዝቡ ጥቅም ይልቅ ለራሳቸው ሥልጣንና መብት፣ የልጅ ልጆቻቸው ያለተቀናቃኝ ዙፋን የሚወርሱበትን መንገድ ለማረጋገጥ ታትረዋል፡፡ በዚህ ሕገ መንግስት መሰረት በኢትዮጵያ የንግሥና መንበር ለይ መቀመጥ የሚቻላቸው ከዘር ሀረጋቸው የሚመዘዙ ብቻ መሆናቸውን ስለሚደነግግ የዙፋኑ ተቃናቃኝ ሊሆኑ ይችሉ የነበሩት ከአፄ ምኒልክ በቀጥታ የሚወለዱት የልጅ እያሱ ልጆችና የአፄ ዮሃንስ ዘሮች ሁሉ ከንግሥናው ጨዋታ በሕግ እንዲሰናበቱ የሚያደርግ ነው፡፡

እንደ ልዑል ራስ ስዩም መንገሻ ያሉ መሳፍንት እና መኳንንት ደግሞ፣ በሕገመንግሥቱ ምርቃት ላይ ተገኝተው “እኛም የኢትዮጵያ ጳጳሳትና መሳፍንት፣ መኳንንት፣ ሹማምንትና ሊቃውንት ይህን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ያቆሙልንን ሕግ ወደን ተስማምተን ተቀብለናል።” ብለው እንዲፈርሙ አድርጓቸዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥ እንደምንመለከተው በሕጉ የመጽቅ ሂደት ላይ ተሳታፊዎቹ መሳፍንቱና መኳንንቱ እንደዚሁም የቤተ ክህነት ጳጳሳትና ሊቃውንት ብቻ ናቸው። ሕዝቡ ተረስቷል፡፡ ይህም ኋላ ላይ ከመጡት “ሕዝቡ ተወያይቶ አጽቆታል” ባይ ዋሾዎች ይልቅ ይሄ የጃንሆይ ሕገመንግሥት አጸዳደቅ ሽፍንፍን የሌለበት ግልፅ መሆኑ የተሻለ ያደርገዋል።

ጃንሆይ ማንም ሳይጠይቀን እና ሳያስገድደን ሕገመንግሥት አቆምን እንዳሉት ሁሉ ከእርሳቸው በኋላ የመጡት መንግሥታትም እንደዚሁ ለራሳቸው የሚጠቅማቸውና የሚሆናቸውን ሕገመንግሥት እያረቀቁ በሚፈልጉት መንገድ እያፀደቁ ነው፤ ቀጥለዋል።

የሕገመንግሥቶቹን ዋና ዓላማ በሆነ አጋጣሚ እጅ ላይ የገባውን ስልጣን ለማፅናትና ለማስጠበቅ አድርገው ይቀርጹታል፡፡ በተቻለ መጠን የስልጣን ተቀናቃኝ ሊሆኑ የሚችሉ ወገኖችን በሕግ የተገደቡ እንዲሆኑ ለማድረግ ጭምር ተዘጋጅተዋል።

የደርግ ሕገመንግሥት የፀደቀው ከኢሠፓ ውጭ ሌላ ኃይል ወይም ፓርቲ ስልጣን መያዝ እንደማይችል የሚገልፅ አንቀፅ እንዲካተትበት ተደርጎ ነው። ጃንሆይ የዙፋን ወራሾቻቸው የልጅ ልጆቻቸው እንዲሆኑ እንዳመቻቹት ሁሉ ደርግ ደግሞ ይህን መብት የሰጠው ለራሱ ፓርቲ ብቻ ነው። ይህን ልብ የሚል ሰው በንጉሠ ነገሥቱና በፕሬዚደንት መንግሥቱ ኃይለማርያም መካከል ብዙ ልዩነት እንዳልነበረ ይረዳል፡፡ ያወጧቸው ሕገመንግስቶችም እንደዚሁ የገዥዎቹን ሥልጣንና ጥቅም ከማስጠበቅ አንፃር ተመሳሳይ ይዘትና ዓላማ የነበራቸው ናቸው።

ደርግን ድል አድርጎ ሥልጣን የያዘው የኢህአዴግ ኃይልም እንደዚሁ ሕገመንግሥት ሲያወጣ በዋናነት የታገለላቸውን ዓላማዎች መሰረት አድርጎ ያረቀቀው ሲሆን፣ ከዚህ የተለየ ዓላማና የፖለቲካ አመለካከት የነበራቸው፣ እንደነ ኢህአፓ፣ መኢሶን፣ ደርግና የመሳሰሉት ኃይሎች በሕግ፣ በአዋጅ ከፖለቲካው መስክ እንዲታገዱ በማድረግ ሕገመንግሥቱን የአሸናፊዎች ሕገመንግሥት እንጂ የሁሉም ዜጋ ሕገመንግሥት መሆን የሚችልበትን ዕድል አምክኖታል።

ከላይ በስፋት ለማየት እንደመኮርነው፣ ከከላይ ወደ ታች እነርሱ ሕግ ሰጪ ህዝቡ ደግሞ ተቀባይ ብቻ ሆኖ በመቀጠሉ መሰረታዊውን የሕገመንግስት ዓላማ ስልጣን የመቆጣጠር፣ የመገደብና ልጓም የማበጀቱ ነገር ቀርቶ የመንግሥታቱ የመጨቆኛ መሳሪያና ሕጋዊ ልባስ ማስገኛ ብቻ ሆኖ እንዲቀር ምክንያት ሆኗል። ለዚህ ነው፣ በእኛ አገር እያሳደግነው የመጣው የፖለቲካ ባህል የአንድ ሰው ማለትም የንጉሱ ወይም የመሪው አምባገነንነት፣ አድራጊ ፈጣሪነትን ያልተገደበ ሥልጣን የሚፈቅድ ሆኖ የቀረው። ሕገመንግሥት በዜጎችና በመንግሥት መካከል የሚኖር የፖለቲካ ማኅበራዊ ውል መሆኑ ቀርቶ የገዥዎች የፖለቲካ መሳሪያ ሆኖ ስለሚያገለግል እንደ ሀገርም እንደ ህዝብም ብዙ ጉዳት አድርሶብናል። ለምሳሌ ሕገመንግስቱ በአዋጅ የአገሪቱ የበላይ ሕግ ነው ተብሎ ቢታወጅም በህዝቡ ዘንድ የሚኖረው ተቀባይነትና ተፈላጊነት እጅግ በጣም አናሳ ነው፤ በዚህም የተነሳ መሪዎቹ ሲወርዱ ወይም ስርዓቱ ሲቀየር አብረው ነው የሚጣሉት። ይህም በራሱ በአገራችን ለሁላችንንም የሚያግባባ ዘላቂ የሆነ የራሳችን የምንለውና የምንኮራበት ሕያው የሆነ ሕገመንግሥት እንዳይኖረው ምክንያት ሆኗል። ይሄ በራሱ ደግሞ በአገራችን ዘላቂ የሆነ መንግሥታዊ ስርዓት እንዳይኖር፣ በሥልጣን ላይ ያለው ከያዘው ቦታ ላለመልቀቅ፣ ሌላ ደግሞ ስልጣን ላይ ለመውጣት ሲባል በአገሪቱ ውስጥ ለብዙ ጊዜያት የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በየጊዜው እንዲከሰት ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top