ታሪክ እና ባሕል

የአፄ ኃይለ ሥላሴ የስደት ህይወት በሀገረ እንግሊዝ (1928-1933) ክፍል ፪

ከዚህ በቀደመው ክፍል ከማይጨው ጦርነት በኋላ የአፄ ኃይለሥላሴን የስደት ጉዞ፣ በየጉዞ ጣቢያው ያጋጠሟቸውን አንዳንድ ሁኔታዎችና በመጨረሻም እንግሊዝ ሀገር ከደረሱ በኋላ የመጀመሪያዎቹን የቆይታ ቀናት እንዴት እንዳሳለፉ በአጭሩ ጠቃቅሼ ነበር። በዚህ ጽሑፍ ንጉሱ ቀሪዎቹን የስደት ዓመታት በምን መልክ እንዳሳለፉ ጥቂት ዘርዘር አድርጌ ለማውሳት እሞክራለሁ።

አቤቱታ በጄኔቭ

የአፄ ኃይለሥላሴ የለንደን ቆይታ የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት ማቅማማት የበዛበት ስለመሆኑ ለግምት አስቸጋሪ አይደለም። ሁኔታው ለተረጋጋ ህይወት፣ በራስ ለመተማመንና ለተለመደ ቆራጥ ውሳኔ የሚመች አልነበረም፤ አይደለምም። ይህን ከመሰለው ደብዛዛ የእንግድነትና የስደት ህይወት ምናልባት ትንሽ ደመቅ ብሎ ሊታይ የሚችለው ንጉሡ ወደ ስዊትዘርላንድ፣ ጄኔቭ ተጉዘው በዓለም መንግሥታት ማኅበር ጠቅላላ ጉባዔ ፊት ያደረጉት ንግግር ነው። አፄ ኃይለሥላሴ በጠቅላላ ጉባዔው ፊት ንግግር ለማድረግ ዕድሉን ያገኙ የመጀመሪያው ርዕሰ-ብሄር ናቸው።

አፄ ኃይለሥላሴ በዓለም መንግስታት ማህበር ጉባዔ አቤቱታቸውን ሲያሰሙ፣ ሰኔ 23/1928

ንጉሡ ወደ ጄኔቭ በባቡር ተጉዘው በጉባዔው ዕለት ከአዳራሹ የፊት ወንበሮች ጥቂት ተርታዎች ወደኋላ ፈቅ ብለው ከሚገኙት ባንዱ ወንበር ላይ ተቀመጡ። ተራቸው ደርሶ ንግግራቸውን ማሰማት ሲጀምሩ በአዳራሹ ይገኙ የነበሩት ጥቂት የጣሊያን ጋዜጠኞች በጩኸትና በፊሽካ እንዲሁም ወለሉን በእግሮቻቸው በመደብደብ ረብሻ ፈጠሩ። ንጉሱን ለማዋረድና በጉባዔው ፊት ለመናገር ባገኙት ዕድል የተሰማውን ንዴት ለመግለጽ ጋዜጠኛ ተብዬዎቹ በዚያ ስፍራ እንዲገኙ ያደረገው ሙሶሊኒ ነበር። ቦወርስ በመጽሐፉ እንደገለጸው ጋዜጠኞቹ ለረብሻ የተጠቀሙባቸውን ፊሽካዎች ያደለው ደግሞ በወቅቱ የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የሙሶሊኒ አማች የነበረው ጋሊያትዞ ቺያኖ ነበር። ጋሊያትዞ ኢትዮጵያን በወረረው የጣሊያን ሰራዊት ውስጥ የቦምብ ጣይ አውሮኘላን አብራሪ ነበር።

ኒኮላይ ጋሊያትዞ

ጋጠወጦቹን የጣሊያን ጋዜጠኞች ፈጥኖ ዝም ያሰኘ አንድም ሰው አልነበረም። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን የሩሜንያ ልኡክ የነበረው ኒኮላይ ቲቱሌስኩ በብስጭት ብድግ ብሎ “እናንት አረመኔ አውሬዎች፤ ውጡ ከዚህ!” በማለት በቁጣ ጮኸባቸው። ይህን ተከትሎ ጋዜጠኞቹ እየተዋከቡ በሃፍረት ከአዳራሹ እንዲወጡ ተደርጐ ለአጭር ቀናት በእስር እንዲቆዩ ተደርገዋል። ኋላም ከእስር ከተፈቱ በኋላ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ለፈጸሙት ተግባር “ክብርና ሽልማት” አግኝተዋል። በሌላ በኩል ሚስተር ቲቱሌስኩ ግን ከስራው ተባርሮ፤ እርሱም የሀገሩ መንግስት በወሰደው እርምጃ ተበሳጭቶ፣ ከቶም ወደ ሀገሩ ዳግም ሳይመለስ ቀሪ ህይወቱን በስደት አሳልፏል።

አስራ ሰባት ገጽ የነበረው የንጉሱ የጄኔቭ ጉባዔ ንግግር የተዘጋጀውና የቀረበውም በአማርኛ ነበር። በእርግጥ የንግግሩ የእንግሊዝኛና የፈረንሳይኛ ትርጉሞች ለታዳሚዎቹ ታድለዋል። በስምንት ክፍሎች የተከፋፈለው የንጉሱ ንግግር የጣሊያን መንግስት በኢትዮጵያና በህዝቦቿ ላይ ያወረደውን የግፍ መዓት በመዘርዝር ይጀምርና ከእንደራሴነት ጊዜያቸው ጀምሮ ባደረጉት ጥረት ስላስመዘገቡት ብሄራዊ አንድነት፣ በጣሊያን መንግስት ትንኮሳ በወልወል ስለተከሰተው ግጭት፣ ከግጭቱ በኋላ ሰላም ለማውረድ ስለተደረገው ጥረትና መፍትሄ ስለመታጣቱ ለማስረዳት ይሞክራል። በተጨማሪም በ1927 ዓ.ም የመንግስታቱ ማህበር አባል ሀገራት ለኢትዮጵያ ሰጥተውት ስለነበረው የተስፋ ቃል፣ የተስፋው ቃል በመታጠፉ የተነሳ ማህበሩ በይበልጥ አደጋ ላይ ስለመውደቁ፣ በመጨረሻም በኢትዮጵያ ላይ ለደረሰው ግፍ ምንም ዓይነት ድጋፍ አለመገኘቱን በመጥቀስ “እናንተ የዓለም መንግስታት ማህበር ተወካዮች! አንድ መሪ ሊፈጽመው ከሚገባው ተግባር እጅግ አስከፊውን ለመፈጸም ከፊታችሁ ቆሜአለሁ። እንግዲህ ለህዝቤ ምን መልስ ይዤለት ልሂድ?” የሚል ጥያቄ አቅርበው ንግግራቸውን ደመደሙ። ይሁን እንጂ አቤቱታ በማሰማት የተገኘ ምንም በጎ ነገር አልነበረም። በመሆኑም አፄ ኃይለሥላሴ ያለ አንዳች ውጤትና ተስፋ ወደ ለንደን ተመልሰው ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ቀሪውን የስደት ህይወት እንዴት እንደሚገፉት ማሰላሰሉን ተያያዙት።   ኃይለሥላሴ

የንጉሱ ጉብኝት በባዝ ከተማ

የባዝ ከተማ ሶመርሴት በሚባለው የእንግሊዝ ካውንቲ (ወይንም ክፍለ ግዛት) ውስጥ ከሚገኙት ከተሞች ትልቋ ናት። ባዝ (በእንግሊዝኛው Bath) ስሟን ያገኘችው ጥንት ሮማውያን በቦታው ከገነቡት የፍልውሃ መታጠቢያ ስፍራ ነው። የባዝ ከተማ በአቮን ወንዝ ሸለቆ፣ ከለንደን በስተምዕራብ 150 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች። በ1920ዎቹ ወደ 70,000 የሚጠጋ ህዝብ ይኖርባት ነበር። ንጉሱ ወደ ባዝ ያመሩት ለአጭር ጊዜ ጉብኝት ሲሆን በውጣ-ውረድ የደከመ ሰውነታቸውን በፍልውሃው ለማደስና ለማገገም ነበር። ነገር ግን ኋላ ላይ ግልጽ እየሆነ እንደመጣው ሁኔታዎች እያማሩ ባለመሆናቸውና ከስፍራ-ስፍራ፣ ከሆቴል-ሆቴል እየተንከራተቱ መኖሩም አስቸጋሪና የማይቻል በመሆኑ ንጉሱ ለረዥም ጊዜ ማረፊያ የሚሆን ስፍራ ማፈላለጋቸውም አልቀረም።

በእንግሊዝ ካርታ ላይ የባዝ ስፍራና ከፍልውሃ መታጠቢያዎቹ አንዱ

አፄ ኃይለሥላሴ በሰኔ 1928 የጄኔቭ ንግግራቸውን ካደረጉ በኋላ ወደ ባዝ የተጓዙት በነሀሴ ወር ነበር። ጥቂት አማካሪዎቻቸውን ጨምሮ ከልጆቻቸው ሦስቱ (የ20 ዓመቱ አልጋ ወራሽ፣ የ13 ዓመቱ ልዑል መኮንን እና የ16 ዓመቷ ልዕልት ፀሀይ) አብረዋቸው ነበሩ። ጉዞውም በባቡር ነበር። በወቅቱ ይታተም የነበረው የከተማዋ ጋዜጣ (ባዝ ኤንድ ዊልትስ ክሮኒክል ኤንድ ሄራልድ) እንደዘገበው ሁለት የእንግሊዝ ነጭ ለባሽ ፖሊሶች (ዲቴክቲቮች) ንጉሱን አጅበው ተጉዘዋል። ንጉሱና ተከታዮቻቸው በባዝ የፍልውሃ ባቡር ጣቢያ እንደደረሱ ወደ ፍልውሃ ሆቴል አምርተው በዚያ አረፉ። የከተማዋ ከንቲባ ሚስተር ጀምስ ካርፔንተር ለክብራቸው የምሳ ግብዣ አድርገውላቸዋል። የክሮኒክል ጋዜጣ የእንግዶቹን ቆይታ እግር በእግር እየተከታተለ በአምዶቹ ላይ አውጥቷል። ከጋዜጣው ዕትሞች በአንዱ የፊት ገጽ ላይ የልዕልት ፀሀይ ፎቶ ወጥቶ እንደነበር ቦወርስ በመጽሃፉ ላይ ጠቅሷል።

አፄ ኃይለሥላሴና ከንቲባ ካርፔንተር በባዝ ፍልውሃ ሆቴል ደጃፍ (ንጉሱ በእጃቸው ፖስትካርድ ይዘዋል)

በባዝ የጉብኝት ጊዜያቸው በጠቅላላው ስምንት ጊዜ ወደ ፍልውሃው ተመላልሰው ተጠምቀዋል። በፍልውሃው ካገኙት አገልግሎት ውስጥ አንዱ በጭቃ ውስጥ የመነከር ወይንም የመዘፍዘፍ ህክምና ነበር። ንጉሱ ተመላልሰው ላገኟቸው አገልግሎቶች በድምሩ 7 ፓውንድ ከ6 ሽልንግ ከፍለዋል።

አፄ ኃይለሥላሴና ልዕልት ፀሀይ (ከንጉሱ በስተቀኝ ነጭ ቆብ አድርጋ) ባዝ ፍልውሃ እንደደረሱ

ከፍልውሃው ሌላ በማንቨርስ ጐዳና የሚገኘውንና በወቅቱ 200 ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረውን የፎርትስ የብስኩት ፋብሪካ ከልጆቻቸው ጋር ጐብኝተዋል። ፋብሪካው ለሪሂ በሽተኞችና ያለቅጥ ለወፈሩ ዝርጥጦች የሚሆን ብስኩት በማምረት የታወቀ ነበር። ሌላው ንጉሱ ከጐበኟቸው ስፍራዎች አንዱ በሴድሪክ ሺቨርስ ግቢ የሚገኘው ታዋቂ የመጽሃፍ መጠረዣ ማዕከል ነበር። በተጨማሪም ጥንታዊውን የሮማ ነገስታት መታጠቢያና ከሮማውያን አማልክት የሱሊስ ሚኔርቫን ቤተመቅደስ ጐብኝተዋል። ይህ ግዙፍ ቤተመቅደስ ባዝ ውስጥ ከሚገኙት የቱሪስት መስህቦች አንዱ ሲሆን በ19ኛው መቶ ከፍለ ዘመን በተካሄደ የአርኪዮሎጂ ቁፋሮ አማካይነት የተገኙ ትላልቅ የሮማ ነገስታት ሃውልቶች ዙሪያውን ቆመው ይታዩበታል። የባዝ ክሮኒክል ጋዜጣ እንደዘገበው በሌላ አጋጣሚ ንጉሱ በኦክታጎን ቻኘል የተካሄደውን የፖስታ ኤግዚቢሽን ጐብኝተዋል። በወቅቱ ዘመናዊ የተባለለት የቴሌግራም መሳሪያ እንዴት እንደሚሰራ ከተመለከቱ በኋላ ለሙከራ ለኤግዚቢሽኑ ዳይሬክተር በቴሌግራሙ መልዕክት አስተላልፈዋል። ከንጉሱ ስር የማትጠፋው ወጣቷ ልዕልት ፀሀይም በኤግዚቢሽኑ የተሰማትን ደስታ በቴሌግራሙ ለዳይሬክተሩ አስተላልፋለች። በዚያ ዕድሜ ልዕልት ፀሀይ እንግሊዝኛን አቀላጥፋ እንደምትናገር ቦወርስ በመጽሃፉ ጠቅሷል።

የአፄ ኃይለሥላሴ የባዝ ጉብኝትና በኗሪው ዘንድ የፈጠረው ግርምት የተሞላበት ትኩረት የእንግሊዝ መንግስት ባለስልጣናትን ምቾት መንሳቱ አልቀረም። የከተማዋ ከንቲባ ሚስተር ካርፔንተር ለንጉሱ ክብር በአቮን ወንዝ ዳርቻ፣ በፓራድ መናፈሻ ግብዣ እያሰናዱ መሆኑ ሲሰማ፣ ከእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “ለንጉሱ የሚደረገው አቀባበልና ቱማታ በዛ!” የሚል የክስ መልዕክት ለከንቲባው ተላከ። በተለመደው የእንግሊዝ ብልጣ-ብልጥ ዲኘሎማሲ የሀገር ውስጥ ሚኒስትሩ፣ ሰር ጆን ሳይመን፣ በይፋ ደብደቤ ከንቲባ ካርፔንተር ግብዣውን እንዲሰርዙ የሚጠይቅ ትዕዛዝ ልከው ሲያበቁ፤ ከዚሁ ደብዳቤ ጋር በሌላ ወረቀት እንደ ከንቲባ የፈለጉትን ማድረግ እንደሚችሉ ጠቅሰው ላኩላቸው። በዚህ መልክ የታሰበው ግብዣ ሳይስተጓጎል ተከናወነ። ንጉሱና እንግዶችም የተዘጋጀውን ስትሮውቤሪ-በክሬም አጣጥመው ቀማምሰው ወደየመጡበት ተመለሱ።

በዚህ የመጀመሪያው የባዝ ጉብኝታቸው ንጉሱ ድንገት ካፈሯቸው ወዳጆች መካከል አንዱ ኧርነስት ፖኘ ስሚዝ የተባለ የቆዳ ውጤቶች አምራች ነጋዴ ነበር። ንጉሱን ከሚስተር ስሚዝ ጋር ያስተዋወቃቸው አንድ የባዝ ፍልውሃ ሆቴል ሰራተኛ ነው። ስሚዝ ለመታሰቢያ እንዲሆን የአፄ ኃይለሥላሴን የፀሎት መጻህፍት በቆዳ ለብዶ ያበረከተላቸው ሲሆን ከጊዜ በኋላ ንጉሱ የገንዘብ እጥረት አጋጥሟቸው አንዳንድ የወርቅና የብር ጌጣጌጦቻቸውን ለመሸጥ በተገደዱ ጊዜ ያለምንም ኮሚሽን ዕቃዎቹን በማሻሻጥ ረድቷቸዋል። ንጉሱም የስሚዝ ሴት ልጅ ስታገባ ለመታሰቢያ የሚሆን ከብር የተሰራ የይሁዳ አንበሳ የደረት ጌጥ ልከውላታል።

ይህ በእንዲህ እያለ ነሀሴ 11 ቀን 1928 ዓ.ም. ንጉሱ የባዝ ቆይታቸውን ለጊዜው አቋርጠው ለአስቸኳይ ጉዳይ ወደ ለንደን ተመለሱ። ወደ ለንደን የተመለሱበት ዋናው ምክንያት ለማረፊያ የሚሆን የመኖሪያ ቤት ለማየትና ከተቻለም ለመግዛት ነበር። ሆኖም ጉዳያቸው የተሳካ አልሆነም። ከሦስት ቀናት በኋላ ወደ ባዝ ተመለሱ። ነሀሴ 14 ቀን በላንስዶውን ኮረብታ አካባቢ በሚካሄደው የፈረስ ትርኢት እንዲገኙ ግብዣ ቢቀርብላቸውም በፍልሰታ ጾም አሳብበው ሳይገኙ ቀሩ። ከሁለት ቀናት በኋላ ከከተማው ወጣ ብሎ ላምብሪጅ በተባለው ስፍራ በተዘጋጀ የፈረስ ዝላይ ውድድር በክብር እንግድነት እንዲገኙ ሌላ ግብዣ ቀረበላቸው። በዚህ ጊዜ ግብዣውን በአክብሮት ተቀብለው በቦታው ተገኙ። በውድድሩ ስፍራ የነበሩት ታዳሚዎች የንጉሱን መምጣት በሩቅ አይተው ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው እንደተቀበሏቸው፣ ለክብራቸውም የተለየ ድንኳን ትርኢቱን በደንብ ለማየት በሚያስችል ስፍራ ተተክሎላቸው እንደነበርና በልዩ የፖሊስ ሃይል ጥበቃ እንደተደረገላቸው የወቅቱ ጋዜጦች በዝርዝር ዘግበዋል።

በነሀሴ አጋማሽ፣ ንጉሱ፣ ልጆቻቸውና ጥቂት ተከታዮቻቸው ገና ባዝን ሳይለቁ፣ ስለ ልዕልት ፀሀይ አንድ ወሬ መወራት ጀመረ። ይኸውም ልዕልቲቱ በቅርቡ ወደ ለንደን በመሄድ በታላቁ የኦርሞንድ ጐዳና በሚገኘው የህፃናት ሆስፒታል በነርስነት ለማገልገል ስለመወሰኑ ነበር። እንደተባለውም ወደ ሆስፒታሉ በመሄድ ተገቢው አቀባበል ከተደረገላት በኋላ እንደማንኛውም የሆስፒታሉ ሰራተኛ መታየት እንደምትፈልግ ገልጻ ስራዋን ጀመረች። ለመጀመሪያው ዓመት አገልግሎቷ በወር 20 የእንግሊዝ ፓውንድ ይከፈላት ነበር። ልዕልት ፀሀይ ከልጅነቷ ጀምሮ ነርስ የመሆን ፍላጎት እንደነበራት ይነገራል። የሚያሳዝነው ከስድስት ዓመት በኋላ ልዕልት ፀሀይ በወሊድ ምክንያት ህይወቷን ማጣቷ ነው። የአሁኑ የጦር ሃይሎች ሆስፒታል ቀድሞ በልዕልቷ ስም የሚጠራ መታሰቢዋ ነበር።

አፄ ኃይለሥላሴና አጀባቸው በባዝ ያደረጉትን የአንድ ወር ዕረፍት አጠናቀው በመስከረም 1929 መባቻ ግድም ወደ ለንደን ሲመለሱ በቅርቡ ወደ ባዝ እንደሚመለሱ ፍንጭ ሳይሰጡ አልቀሩም። ይህን ፍንጭ የሰማው የባዝ ክሮኒክል ጋዜጣ ንጉሱ በባዝ አንድ የመኖሪያ ቤት ገዝተዋል የሚል ወሬ ማናፈስ ጀመረ። መጀመሪያ አካባቢ የኢትዮጵያው/የንጉሱ ቃል አቀባይ ወሬው ሃሰት እንደሆነ አስተባበለ። ነገር ግን ንጉሱ በዚያን ጊዜ የሚኖሩበት ቤት ለመግዛት እያፈላለጉ እንደነበር ጥቂት ሰዎች ያውቃሉ። የማያውቁት ቦታው የት እንደሚሆን ነበር።

የስደቱ ኑሮ በባዝ ሆነ

የተወራው እውነት ሆኖ በጥቂት ቀናት ውስጥ “ፎርት፣ ሃርት እና ቢሊንግስ” የተባለ የንግድ ኩባንያ ለአፄ ኃይለሥላሴ ቤት ሲያፈላልጉ የነበሩ ሰዎችን ለንጉሱ የሚመጥን ባይሆንም የሚስማማ ቤት በምዕራብ ባዝ፣ ኒውብሪጅ ኮረብታ አካባቢ እንደሚገኝ ጥቆማ ሰጠ። ንጉሱም መልዕክቱ እንደደረሳቸው በመስከረም አጋማሽ ወደ ባዝ ሄደው የተባለውን ቤት ካዩ በኋላ ምንም ሳያመነቱ ግዢውን ፈጸሙ። የባዝ ክሮኒክል ጭምጭምታው እውነት መሆኑን በፊት ገጹ የዜና አምድ ላይ አስታወቀ።

ንጉሱ የገዙት ቤት የፌይርፊልድ ግቢ በመባል የሚታወቅ፣ (የምጸቱ ምጸት በጣሊያን የግንባታ ሞድ እ.አ.አ በ1840ዎቹ የተገነባ) በወቅቱ ግርማ ሞገስ ያለው ቤት ነበር። ግቢው ሁለት ኤክር (9680 ስኴር ያርድ) ስፋት ነበረው። በኬልስተን ጐዳና የሚገኘው ፌይርፊልድ ንጉሱ በወቅቱ ይፈልጉት ለነበረው የተገለለ የብቻ-ሰላም (ኘራይቬሲ) የተመቸ ነበር። ፌይርፊልድ ባለ አንድ ፎቅ ሆኖ አምስት መኝታ ቤቶች፣ አንድ ትልቅ የእንግዳ መቀበያ ክፍልና ከመጀመሪያው ወለል በታች በምድር ክፍሉ ውስጥ ሌሎች በርካታ ክፍሎችን አካትቶ የያዘ ቤት ነበር። ከዋናው ህንጻ ነጠል ያለች አነስተኛ ቤትና የመኪና ማቆሚያ ታዛም ነበረው። የቤቱ ባለቤት ወ/ሮ ካምኘቤል ኋይት የተባሉ ጋለሞታ ሲሆኑ በውጭ ሀገር ሲኖሩ ቆይተው እዚያው ህይወታቸው አልፎ ወራሽም አልነበራቸው። ንጉሱ ቤቱን የገዙት በ3500 ፓውንድ ነበር። (በነገራችን ላይ አፄ ኃይለሥላሴ በቢሾፍቱ የሰሩትን ቤተመንግስታቸውን ፌይርፊልድ ብለው ሰይመውት ነበር።)  

በባዝ ንጉሱ የገዙት ፌይርፊልድ፣ በ1920ዎቹ

ፌይርፊልድ ከተገዛና መጠነኛ እድሳት ከተደረገለት በኋላ፣ እቴጌ መነን ሁለቱን ልጆቻቸውን (ልዕልት ተናኘወርቅንና ልዑል ሳህለ ስላሴን) እንዲሁም ሌሎች ዘጠኝ ተከታዮቻቸውን አስከትለው፣ ኮምፒየኝ በተባለች የፈረንሳይ መርከብ ተሳፍረው፣ ኋላም ከማርሴይ በባቡር ተጉዘው ፎክስቶን በተሰኘው የእንግሊዝ ወደብ ደረሱ። ከዚያም ወደ ባዝ ከተማ በባቡር አምርተው በባዝ የፍል ውሃ ሆቴል ምሳቸውን ከበሉ በኋላ ወደ አዲሱ ቤታቸው ወደ ፌይርፊልድ ሄዱ። ብዙም ሳይቆዩ ንጉሱ አዲስ አበባ ከሚገኘው ንብረታቸው የተወሰነውን በእንግሊዝ ኤምባሲ ድጋፍና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩት በአንቶኒ ኤደን እርዳታ ከቀረጥ ነፃ ወደ ባዝ አስመጡ። የንጉሱን ልጆችና የልጅ ልጆች፣ ጥቂት ቀሳውስትን፣ አማካሪዎችንና አገልጋዮችን ጨምሮ በአማካይ ከ20 እስከ 25 የሚደርሱ ሰዎች በፌይርፊልድ ይኖሩ እንደነበር ቦወርስ በመጽሃፉ ጠቅሷል። ከአገልጋዮች መካከል አንድ መጋቢ (አስተናጋጅ)፣ አሳላፊ፣ ወጥ ቤት፣ ሾፌር፣ አትክልተኛና ስሙ ክርስቶስ የተሰኘ የእልፍኝ አሽከር ይገኙበት ነበር። እንዲህ እንዲህ እያለ ኑሮ በባዝ መሞቅ ጀመረ። ነገር ግን አጥንት ሰርሳሪው የእንግሊዝ ብርድ ኑሮን በቀላሉ ለማሞቅ የሚያግዝ አልነበረም። እምብዛም የተሟላ ጤንነት ላልነበራቸው ንግስት የባዝ ህይወት እጅግ ከባድ ነበር።

እቴጌ መነን ባዝ ባቡር ጣቢያ እንደደረሱ

በዚህ መካከል የዓለም መንግስታት ማህበር የኢትዮጵያና የጣሊያንን ጉዳይ በተመለከተ ለሌላ ጉባዔ እየተዘጋጀ መሆኑ ተሰማ። ቀደም ሲል በማህበሩ የኢትዮጵያ ተወካዮች በማናቸውም ስብሰባ እንዳይሳተፉ ታግደው ስለነበር፣ ይህን በመቃወም ንጉሱ ፈጥነው ወደ ጄኔቭ ለመሄድ ተነሱ። ስድስት ተከታዮቻቸውን አስከትለው በልዩ የቻርተር አውሮኘላን እኩለ ቀን ላይ ከለንደን ተነስተው ወደ ጄኔቭ በረሩ። በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ ልዑካን በማህበሩ ስብሰባ ላይ ድንገት መገኘት ተሰብሳቢዎቹን ያደናገረ ቢሆንም እንደ ቀደመው ጊዜ ንጉሱ በጉባዔው ላይ ዲስኩር ለማሰማት አልተፈቀደላቸውም። የሆነው ሆኖ ጉባዔው በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ጀምሮት የነበረው ውይይትም ያለ ምንም ስምምነት አበቃ። እንደቀደመው ጊዜ ንጉሱ ያለምንም ውጤት ወደ ባዝ ተመለሱ።

የስደቱ ህይወትና የፋይናንስ ሁኔታ

በነሀሴ 1928፣ ገና ኑሮን በባዝ ማደላደል ሳይጀመር፣ አፄ ኃይለሥላሴ የፋይናንስ አቅማቸውን ኦዲት አስደርገው ነበር። የሂሳብ ምርመራውን ያካሄደው በወቅቱ የኢትዮጵያ ባንክ ገዥ የነበረው ቻርልስ ኮሊየር ነበር። በዚህ የመጀመሪያ የሂሳብ ምርመራ መሰረት ንጉሱ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ የፈረንሳይ ፍራንክና 200,000 የማርትሬዛ ብር ይዘው ወደ እንግሊዝ ገብተዋል። በዛሬው ስሌት የማርትሬዛ ብሮቹ ከአንድ ሚሊዮን ፓውንድ በላይ፣ የፈረንሳይ ፍራንኮቹ ደግሞ ከ250,000 ፓውንድ በላይ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገመታል። በተጨማሪም በዚህ የሂሳብ ምርመራ ንጉሱ ስዊትዘርላንድ ውስጥ በቬቪ ከተማ አንድ ቤት እንዳላቸው፣ በልጆቻቸው ስም ወደ 54,000 ፓውንድ (በአሁኑ ስሌት ከ3 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ)  የሚገመት በባንክ የተቀመጠ የአደራ ገንዘብ እንደነበራቸው ተረጋግጧል። ከዚህ ሌላ ሚስተር ኮሊየር በብሄራዊ ባንክ፣ በምድር ባቡር፣ በጨው ኩባንያዎችና በፊትዝማይክል ኩባንያ ውስጥ የነበሩትን የኢትዮጵያ የአክስዮን ድርሻዎች ይቆጣጠር ነበር። በየትላልቅ ሆቴሎችና የገጠር ቪላዎች የንጉሱን ዘና ያለ ኑሮና ለቀቅ ያለ ወጪ ተመልክቶ ፈጥነው ቤት እንዲገዙ አበክረው ከመከሩት ሰዎች አንዱ ኮሊየር ነበር። በእርግጥም እንዲህ ዓይነቱ የኑሮ ዘይቤ ከቤተሰቡ ስፋት፣ ከደጀጠኚው ብዛት ጋር ተደማምሮ በእጅ የነበረውን የንጉሱን ገንዘብ በፍጥነት ማመንመኑ አልቀረም። በዚህ የተነሳ በድንገት ያጋጠማቸውን የገንዘብ እጥረት ለመቋቋም ኀዳር 1929 ዓ.ም ላይ ንጉሱ ከነበሯቸው ጥቂት ከብር የተሰሩ የቤት እቃዎች መካከል የተወሰኑትን ለሽያጭ አቅርበው በድምሩ 2527 ፓውንድ ለማግኘት ችለው ነበር።

ከዚህ በተጨማሪ ዘለግ ያለ ጊዜን የወሰዱ የተለያዩ የፍርድ ክርክሮች የንጉሱን የገንዘብ አቅም ክፉኛ ተፈታትነውታል። ከእነዚህ የፍርድ ክርክሮች ውስጥ ሊጠቀሱ የሚገባቸው በግብጽ ባንክ ይዞታ ስር በነበረውና በኢትዮጵያ ባንክ ውስጥ የሚገኘው የመንግስት ገንዘብ፣ ኬብልና ዋየርለስ በተሰኘ የቴሌኮሚኒኬሽን ኩባንያ ውስጥ የነበረው የኢትዮጵያ የአክስዮን ድርሻና በፈረንሳይ ሊየዥ ከተማ ከሚገኝ አንድ ነጋዴ ጋር የነበረው እሰጥ አገባ ናቸው። የሊየዡ ነጋዴ ከአፄ ኃይለሥላሴ የቡና መሬት የተለቀመውን ቡና ለመሸጥ ተስማምቶ የሽያጩን 14,000 ፓውንድና በኪሳራ ላደረሰው ጥፋት መክፈል የሚገባውን ተጨማሪ 3000 ፓውንድ መክፈል ባለመቻሉ ነበር የፍርድ ክርክሩ የተጀመረው።

አፄ ኃይለሥላሴ በወከባ መሃል በዕለት ችግር ተጠምደው ለተወሰነ ጊዜ እጅ አጠራቸው እንጂ ለክፉ ቀን የሚሆን በአንፃራዊነት ጠቀም ያለ ሃብት በጥሬ ገንዘብና በአክስዮን መልክ እንደነበራቸው ቆቁ የእንግሊዝ መንግስት ሚስተር ዎልጌት በተባለ የእንግሊዝ ብሄራዊ ባንክ የአንድ አውራጃ ሃላፊ አማካይነት ልቅም አድርጐ አረጋግጧል። ለምሳሌ በእንግሊዝ ባንክ ከተቀመጠው ገንዘብ በተጨማሪ በሆውከር ሲድሊ የአውሮኘላን ኩባንያ ውስጥ 755 አክስዮኖች፣ በጆን ብራውንና ጓደኞቹ የኢንጂነሪንግ ኩባንያ ውስጥ 550 አክስዮኖች ነበሯቸው። በ1933 ዓ.ም ከእነኚህ አክስዮኖች 490 ፓውንድ የትርፍ ክፍያ አግኝተው 118.56 ፓውንድ ታክስ ከፍለዋል። በተጨማሪም ዎልጌት ባደረገው ክትትልና ባቀረበው ሪፖርት መሰረት አፄ ኃይለሥላሴ በካናዳ የፓሲፊክ የምድር ባቡር ኩባንያ 4500 ፓውንድ፣ በሃደርስፊልድ የግንባታ ማህበር ውስጥ 2500 ፓውንድ፣ እንዲሁም በሊድስ የግንባታ ማህበር ውስጥ 4000 ፓውንድ አክስዮኖች ነበሯቸው። ኪራዩ አነስተኛ ነበር ይባል እንጂ በስዊትዘርላንድ ቪቪ ከተማም አንድ ቤት እንደነበራቸው ከፍ ሲል ተጠቅሷል። እቴጌ መነንም በእየሩስአሌም በዓመት 90 ፓውንድ የሚከራይ ቤት ነበራቸው። የእንግሊዝ መንግስት ይህን ሁሉ ክትትልና ማጣራት ያደረገው የሚፈልገውን ታክስ በአግባቡ ለመሰብሰብ ነበር።

ይሁን እንጂ የስደቱ ህይወት ንጉሱና ቤተሰባቸው ከለመዱት ኑሮ በእጅጉ የተለየ እንደነበርና በእለት ወጪ ሳቢያ ጭንቀት ውስጥ መውደቃቸው እርግጥ ነበር። በተለይ በአስቸጋሪው የክረምት ወቅት የከሰልና የኤሌክትሪክ ወጪን በሰዓቱ ለመክፈል ብርቱ ችግር ያጋጥማቸው ነበር። እንዲያውም አንድ ዕለት የአካባቢው የኤሌክትሪክ ኩባንያ ሃላፊ የንጉሱን ቤት (ፌይርፊልድን) ለመጐብኘት ሄዶ ንጉሱ በካፖርት ተጀቡነው፣ ጐልበታቸው ላይ ምንጣፍ ጣል አድርገውና በብርድ ተቆራምደው አገኛቸው። በሁኔታው ያዘነው እንግሊዛዊ የነበረባቸውን ውዝፍ ክፍያ ምህረት አድርጐላቸዋል።

በዚህ ደረጃ ድንገት ዘጭ ያለውን የስደተኛ ንጉስ ኑሮ በእንግሊዝ መንግስት ድጐማ ለመደገፍ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአንቶኒ ኤደንና በእንግሊዝ ፓርላማ የባዝ ተወካይ በነበሩት በሎዌል ጊነስ አማካይነት የተወሰነ ጥረት ቢደረግም ሁኔታው ይፋ ከወጣ ሙሶሊኒን ያስቀይምና ጣሊያንን ወደ ጀርመን ጉያ ሊከታት ይችላል በሚል ፍራቻ ዳር ሳይደርስ ቀርቷል። ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ሰር አሌክሳንደር ካዶጋን እና የገንዘብ ሚኒስትሩ ሰር ጆን ሳይመንም በጉዳዩ አልተስማሙም። ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድ ማንነቱ እንዲገለጽ ያልፈለገ በጐ አድራጊ ለንጉሱ የ10,000 ፓውንድ እርዳታ አበረከተ። የእንግሊዝ መንግስትም በጉዳዩ ጣልቃ ገብቶ በራሱ ስሌት ለንጉሱ የዓመት ወጪ 2000 ፓውንድ እንደሚበቃ ወስኖ በየሦስት ወሩ 500 ፓውንድ እንዲሰጣቸው ወሰነ። በሁኔታው ቅር የተሰኙት ንጉስ ውሳኔውን ላለመቀበል ቢያንገራግሩም በመጨረሻው ግን ውሳኔውን ተቀብለው ድርጎአቸውን በየሦስት ወሩ ለመቀበል ተስማሙ።

የንጉሱ የስደት ህይወት በዚህ መልኩ እየተንገጫገጨ እስከ 1933 ዓ.ም ድረስ ቀጠለ። ጣሊያን ጀርመንን ወግና ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ስትቀላቀል የአፄ ኃይለሥላሴ ዕጣ ፈንታም አቅጣጫውን ቀየረ። በእንግሊዞች ድጋፍ ወደ ሱዳን በድብቅ ሄደው ምዕራብ ኢትዮጵያ ጠረፍ ላይ ከነበሩ አርበኞች ጋር ተገናኝተው በብርቱ ተጋድሎ ጣሊያኖች ተሸንፈው የኢትዮጵያ ነፃነት ተመለሰ። በድጋፍና በተቃውሞ የተጀመረው የአፄ ኃይለሥላሴ ሁለተኛ የስልጣን ዘመን በክብር፣ በዝና፣ በጥላቻና በንቅት ታጅቦ በውርደት ተደመደመ።  

አፄ ኃይለሥላሴ ወደ አዲስ አበባ እየገቡ፣ 1933

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top