ማዕደ ስንኝ

ከመንጋው መስማማት

ለባዶ ቢሆንስ?
ፀሎቴን ማብዛቴ
በእምነት መበርታቴ
ወደ ላይ ዕያየሁ – በታላቅ ልመና – እንባዬን መርጨቴ
ለተረት ቢሆንስ?
በሚነግሩኝ ገድል – ከንፈሬን ‘ምመጠው
በፆምና ፀሎት – ጊዜዬን ማጠፋው
መጠየቅ አቁሜ – ያሉኝን ‘ምሰማው
ወይስ ፈርቼ ይሆን?
እየተጠራጠርኩ – ለማመን ‘ምዳዳ
ለእሺታ ‘ምፈጥን – በደንብ ሳልረዳ
መፅደቁን የምመኝ – ሳይገባኝ እውነቱ
ማጎንበስ የሚያምረኝ – ሳይኖረኝ እምነቱ
የምስቅ ‘ማለቅሰው – ሳላውቀው ስሜቱ
ሰነፍ ሆኜስ ይሆን?
ነው የተባልኩትን – መመርመር ያቃተኝ
የተነገረኝን – መፈተሽ የተውኩኝ
እንዳምን ሲነግሩኝ – ያልተከራከርኩኝ
እንምራህም ሲሉኝ – መጠየቅ ያቆምኩኝ
ለምን እንዴት ወዴት – ማለት የረሳሁኝ
ይሄ – እንዴት ሆነ?
ያኛው – ከየት መጣ?
ምንድነው ምስጢሩ?
እንዴት ነው ነገሩ? በሚሉ ጥያቄዎች
ራሴን እያስጨነቅኩኝ – ብዙ ቆየሁና
መልስ መፈለጉ – አደከመኝና
እምነት ማለት – ያለእውቀት መስማማት
ሃይማኖት ማለት – ያለምክንያት መግባባት
እንደሆኑ – ተረዳሁኝና
ብቻዬን መሆኔ – ሰላም ነሳኝና
የራሴንም መንገድ – መጓዝ ተውኩኝና
በአቦሸማኔ እግር – በብርሃኑ ፍጥነት
ሮጬ ተቀላቀልኩ – መንጋው ጋር ሄድኩና።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top