ጥበብ በታሪክ ገፅ

ነገረ ዓባይ

የፍጻሜው መጀመሪያ

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ግዙፍ የግድብ ፕሮጀክት ለመገንባት አስባ በይፋ ሥራ ከጀመረች ዘጠኝ ዓመት ሞላት። “የታላቁ ህዳሴ ግድብ” የተሰኘው ግንባታዋ ከብዙ ውጣ ውረድና ፈተናዎች በኋላ ግንባታው ተጠናቆ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌቱን በመጪው ክረምት እንደሚጀምር ይፋ ሆኗል።

ኢትዮጵያ ከግንባታው ጥንስስ አንስቶ ተግባሯ ከናይል ወንዝ የግርጌ ተፋሰስ አገራት /ሱዳንና ግብፅ/ ጋር ሲያወዛግባት መቆየቱ አይዘነጋም። ሦስቱ አገራት በጥምረት በግድቡ ግንባታ ዙሪያ የሚነሱ ስጋቶችን ለመቅረፍ ሞክረዋል። ባዘጋጇቸው የተለያዩ የውይይት መድረኮች ተደራድረዋል። ምንም እንኳን በ2015 ሦስቱን አገራት የሚያግባባ ገዢ የመግባቢያ ሰነድ ላይ ተስማምተው ለመፈረም ቢበቁም እስከ አሁንም ጉዳዩ ከውዝግብ ሊድን አልቻለም።

በተለይም ግብፅ ለሺህ ዓመታት ይዛው በቆየችው በብቻ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ አለመላቀቋ የግንባታውን የፍትሐዊነት አመክንዮ እንዳትቀበል አድርጓታል፡፡ በአሁን ሰዓት የግድቡ ግንባታ የፍፃሜው መጀመሪያ ላይ ደርሷል። ግብፅም ሁኔታው ይበልጥ ስጋቷን አንሮት ኢትየጵያን ከተግባሯ ለማደናቀፍ እየተጣደፈች ትገኛለች።

ይህ ፅሑፍ ከዓባይ ወንዝ አንፃር የኢትዮጵያና የግብፅ ግንኙነት ገፅታና የውዝግቦቻቸቸው ምንጭ የሆኑ ጉዳዮችን ይዳስሳል። ከዚህ ዳሰሳ በመነሳት ቀጣዩ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ምን አይነት ገፅታ ሊላበስ እንደሚችል በአጭሩ ይቃኛል።

ይህንን ጽሑፍ ለማሰናዳት ‹‹The Cross and the River›› የተሰኘውን በሃጌ ኤርሊች የተፃፈ መጽሐፍ እና ‹‹Ethiopia’s Renaissance Dam: – From conflict to cooperation›› በሚል ርዕስ በጄሲ ቬይሊ የተካሄደ ሰፊ የጥናታዊ ምርምር ወረቀት ተጠቅሜአለሁ፡፡ የዘመን አቆጣጠሩም በጎርጎሪሳውያኑ የዘመን ቀመር ነው፡፡

ታሪካዊ ዳራ፤ ከውሃ ፖለቲካ አንፃር

ግብፅና ኢትዮጵያን ከናይል ወንዝ የፍላጎት ተቃርኖ ግጭት አንፃር ታሪካዊ ዳራቸው ሰፊ ነው። ይህ ጽሑፍ ምልከታውን በማጥበብ በተለይም የግብፅ ብሔርተኛ አመለካከት ከተፈጠረበት 19ኛው ክ/ዘ አጋማሽ ወዲህ ያሉትን አንኳር ክስተቶች በቅንጭቡ መቃኘትን መርጧል። በዚህ ረገድ ተጠቃሽ የሚሆነው ዐቢይ ክስተት በግብፁ ካህዲቩ የሚመራው ሠራዊት በናይል መፍሰሻ አገራት ላይ ለመንሰራፋት ወረራ ያካሄደበት ነው። የዚህ እንቅስቃሴው ዋና ትኩረት የነበረችውም ኢትዮጵያ ናት።

የካሀዲቭ ሠራዊት ኢትዮጵያን ለመውረር ያካሄዳቸው የሁለት ጊዜ ጦርነቶች በ1876 ሙሉ በሙሉ ሽንፈት አከናንቦት ሳይሳካለት ቀርቷል። ከሽንፈቱ በኋላ በነበሩት ቀጣይ አስርት ዓመታት ግብፅ ኢትዮጵያን በተመለከተ እርስ በእርሱ የተቃረነ አመለካከት ማራመዷን ሰነዶች ያረጋግጣሉ። በመጀመሪያዎቹ ቀጣይ ዓመታት የግብፅ ሠራዊት ኢትዮጵያ ያልሰለጠነችና አረመኔ፣ የናይል ተፋሰስ ምድርን ለማዋሃድ በያዙት አቋም ላይ የተጋረጠች ጠላት፣… አድርገው ሲመለከቷት ቆይተዋል።

ግብፃውያን በዚህ አቋማቸው ብዙ አልዘለቁም። ከ1920ዎቹ ወዲህ አመለካከታቸውን በመቀየር ኢትዮጵያ የኮፕቲክ ክርስቲያን አገር፤ የፀረ ኢምፔሪያሊስት ሥርዓት አራማጅ፤ ልዩነትን እና ብዙኃነትን ማስተናገድ የምትችል ወዳጅ አገር አድርጎ የመቀበል አካሄድ መከተላቸው ይወሳል።

በ1930ዎቹ በግብፅ የተነሳው ስልጡናዊው የአረብ ብሔርተኝነት አብዮት ዳግመኛ ዋና ትኩረቱ ያደረገው ኢትዮጵያን ሆኖ ተገኝቷል። በአንድ በኩል ኢትዮጵያ የፀረ ቅኝ ግዛትና ነፃነት ዋቢ ማሳያ አድርገው በክብር የመመልከት አዝማሚያ ታይቶባቸዋል። ይህ አቋማቸው ግን በአረቦቹ የእስልምና ፅንፈኛ ተከታይ ህዝቦችና ታጣቂዎች ተፅዕኖ ተለውጦ አሉታዊ ጥላቻ ላይ የተገነባ አመለካከት ወደ ማራመዱ ተለውጠዋል።

በ1950ዎቹና 60ዎቹ በተከሰቱ አካባቢያዊ ግጭቶችና አደጋዎች ጀርባ የግብፅ አብዮተኛው ዐረባዊ አመለካከት ኢትዮጵያን በተመለከተ ያራምድ የነበረው አስተሳሰብ እጅ እንደነበረበት ተረጋግጧል። በኤርትራ ውስጥ የነበረው የነፃነት ታጣቂዎች ግጭትና ከሱማሊያ ጋር የተደረገው ጦርነት ለዚህ አባባል አስረጂ ሆነው ይቀርባሉ። በተጨማሪም እስራኤል በአፍሪካ ቀንድ ስታካሂድ የቆየችው የጣልቃ ገብነት እንቅስቃሴ ውስጥም የግብፅ ድጋፍ በግልፅ መታየቱ ይነገራል። እስራኤላውያኑ የወቅቱ የግብፅ መሪ ጋማል አብዱል ናስር ያራምደው የነበረውን ኢትዮጵያ በናይል ላይ አንዳችም ተፅዕኖ እንደሌላት የሚቆጥር አቋምና፤ አገሪቱን ከመጤፍ ሳይቆጥር ‘አስዋን’ ግድብን ለመገንባት በወሰደው ዕርምጃ ውስጥ ደጋፊው ሆነው ተሰልፈዋል። 

የአስዋን ግድብ ግንባታ ግብፅ በናይል ወንዝ ላይ አድሮባት የቆየውን የተፋሰሱ አገራት ተጠቃሚነት ስጋት ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚፈታ ተስፋ ተደርጎ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። ነገር ግን ግድቡ ለአንድ ወገን ጥቅም ያዳላና የዐረብ ግብፅ ብሔርተኛ አብዮተኞች ግድቡ የተፋሰሱ አገራት ጉዳይን በሙሉ የሚያካትት መፍትሔ እንደሚሆን ያሰቡበት አካሄድ በአድሎ የተመሰረተ መሆኑ ተስፋውን አጨልሞታል።

“የአስዋን ግድብ ግንባታ ግብፅ የናይል የብቻ ተጠቃሚነት አቋሟን አጠናክራ ለማስቀጠል ከዚያ ቀደም ከወሰደቻቸው ዕርምጃዎች ሁሉ የከፋ ስህተት የሰራችበት ነው” ይላል ኤርሊች።

“በተሳሳተ ቦታ የተገነባ የተሳሳተ ግድብ” ብሎ ሃሳቡን ያስረዳል። በውጤቱም ግብፃውያን እስከዚህ ጊዜ ድረስ የዘለቀ የፍርሃትና ስጋት ዋጋ ሲከፍሉ እንዲኖሩ እንዳስገደዳቸው ፀሐፊው ያትታል። የፈሩት የሚደርስበትና የጠሉት የሚወረስበት ዘመን ደረሰና ኢትዮጵያ በናይል ግዙፍ ገባሪ ወንዝ ዓባይ ላይ ግድብ ለመገንባት ዐቅዳ ወደ ስራ ገባች። ግብፅም በብቸኝነት የናይል ውሃ ተጠቃሚነት አባዜዋ ግንባታውን ለማደናቀፍ ሳትታክት የምትንቀሳቀስበት ሁኔታ ውስጥ እንድትገባ አስገደዳት። በአንድ በኩል የኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግሮችን በማባባስና በተለይም ብሔር ተኮር ግጭቶች እንዳይረግቡ ለማድረግ፤ እንዲሁም ቀጥተኛ ወታደራዊ የኃይል ጣልቃ ገብነትን እንዳማራጭ በማሰብ ግንባታውን ለማስተጓጎል ጥረት ስታደርግ ተስተውላለች። በሌላ ጎኑ ደግሞ ወዳጃዊ ግንኙነትን በማጥበቅና ወደ ውይይት ጠረጴዛ በመምጣት ፍላጎቷን ለማሳካት ጥረት ስታደርግም ታይታለች። ሁሉም አካሄዷ ስልታዊ በሆነ መንገድ ኢትዮጵያ ከዓባይ ወንዝ ላይ ዐይኗን እንዳታነሳ ማስቻል መሆኑን ያረጋግጣል።

“ግብፃውያኑ በራሳቸው መግለጫ ‘የከበደ የድርድር ውይይት’ ብለው የሚጠሩትን ወዳጃዊ አካሄድ የመምረጥ አዝማሚያ ይታይባቸዋል። ኢትዮጵያን በቀጥታ ውይይት በማባበል ለማግባባትና በተዘዋዋሪ መንገድ ዓለምአቀፍ ጫና እንዲያርፍባት ውስጥ ለውስጥ በመስራት ከናይል ገባሪ ውሃዎች አንዱንም እንዳትጠቀም ማድረግን ግባቸው አድርገዋል” የሚለው ኤርሊች ግብፅ ለዚህ የበቃችው “ታሪካዊ መብቴ” በሚል የመከራከሪያ አስተሳሰብ ላይ ተመስርታ እንደሆነ ይገልፃል። “ይህ አስተሳሰብ አዲስ አይደለም። ከጥንታውያኑ ግብፃውያን አቋምና አስተሳሰብ የማይለይ አሮጌ መርሆ ነው” ይላል።

የ”ታሪካዊ መብት” አመክንዮ

በናይል ወንዝ ላይ የመጠቀም ብቸኛ ሕጋዊ ባለመብትነትን ማረጋገጥ ግብፃውያን ቅድሚያ የሚሰጡት ሕጋዊ መከራከሪያ ነጥባቸው ነው። ግብፅ የናይል ውሃን ያለ አንዳች ገደብ በብቸኝነት ስትጠቀምበት ኖራለች። ከታሪክ መረዳት እንደሚቻለው ቢያንስ አራቱ ጥንታውያን ገናና /የቻይና፤ ህንድ፤ ሜሶፖታሚያ እና ግብፅ/ ሥልጣኔዎች ያደጉት ትላልቅ ወንዞችን ተከትለው ነው። ግብፃውያን ይህንን የጥንት ባህል፤ የምንነት እና የሥርዓት ዕድገት ሥልጣኔ በናይል ተፋሰስ ዳርቻ የመሰረቱ መሆናቸውን እንደ ዋና፣ ዘላቂ የማንነታቸው መመስረቻ ቁልፍ ይመለከቱታል።

ከዚህ ሃሳብ ይነሱና የወንዙ ብቸኛ የተጠቃሚነት መብታቸው በሥነ ምድራዊ ወይም በሃይድሮሎጂ መርሆ ሳይሆን በህዝቦች ታሪክ እውነታ ሊረጋገጥ እንደሚገባ ይከራከራሉ። ከዚህ በተጨማሪ የናይል ተፋሰስ ጉዳይ እንደ አንድ ህጋዊ ሰውነት ተቆጥሮ በዓለምአቀፍ ደረጃ በ20ኛዎቹ ክ/ዘ በተደረጉ ስምምነቶች በተሰጠው ዕውቅና ሊዳኝ እንደሚገባ የሚገልፅ የመከራከሪያ ሃሳብ ያነሳሉ። ለዚህ መከራከሪያቸው ይረዳቸው ዘንድ ቅኝ ገዢያቸው እንግሊዝ፤ ሱዳንና ግብፅ በ1929 እና 1959 ያደረጓቸውን የናይል ወንዝ ተጠቃሚነት ስምምነቶች አስረጂ አድርገው ያቀርባሉ።

ኤርሊች የግብፅ የ”ታሪካዊ ባለመብትነት” መከራከሪያ ሃሳብ ሞራላዊ ብያኔን በሁለት ፈርጆ ይመለከተዋል። አንደኛው ግብፅ ለህልውናዋ ሌላ አማራጭ የሌላት መሆኑ፤ ሁለተኛው ደግሞ ኢትዮጵያ እስካሁን ያለ ዓባይ ወንዝ ተጠቃሚነት የኖረች መሆኗንና በዚሁ መንገድ ህልውናዋ መቀጠል የሚችል መሆኑን።

“ወደ ተግባር ስንመለስ ግን ሁለቱም የግብፅ አመክንዮ ተቀባይነት አይኖረውም። የቅኝ ግዛቱ ስምምነት የላይኛው የናይል ተፋሰስ አገራትን ያላካተተ መሆኑና፤ አገራቱ ይህንኑ አውቀው ከጊዜ በኋላ የተጠቃሚነት ስምምነቱ አካል የመሆን ፍላጎታቸው እየጨመረ መምጣቱ የ”ታሪካዊ መብት” መከራከሪያ ሃሳቧን ውድቅ ያደርገዋል” ብሎ ያስረዳል። 

ግብፃውያንም የቆየ ልማዳቸው አልለቃቸው ብሎ እየጎተተ ቢያስቸግራቸውም እስከዚህ ጊዜ የዘለቁበት አስተሳሰብ ወደፊት እንደማያራምዳቸው ያውቁታል። ነገር ግን ዘመናት ከዘለቀ ልማድ በቀላሉ መላቀቅ አልቻል ብሎ እያስቸገራቸው ይታያል። በዚህ ስልጡን ዘመን አዋጩ መንገድ በሰጥቶ መቀበል ላይ የተመሰረተ የጋራ ተጠቃሚነት መብትን ማስጠበቅ መሆኑን ተንታኞች ያስረዳሉ። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የያዘችው “ፍትሐዊ የተመጣጠነ የተጠቃሚነት ድርሻ” የተሰኘው አቋሟ ዓለምአቀፍ ተቀባይነቱ የማያወላዳ መሆኑንም ያረጋግጣሉ።

ፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነት

“የፍትሐዊ ተጠቃሚነት” መርሆ ከ”ታሪካዊ ባለመብትነት” አስተሳሰብ ጋር በተቃርኖ ፅንፍ ለፅንፍ የቆመ አመለካከት ነው። ሮበርት ኮሊንስ የተባሉ ተመራማሪ የ”ፍትሐዊ ተጠቃሚነት” መርሆ በቻይናና በህንድ የአገር ግንባታ እንቅስቃሴ ውስጥ ለ500 ዓመታት ያገለገለ አስተሳሰብ መሆኑን ይናገራሉ። በ1966 በተፈፀመው የሄልሲንኪ ስምምነትም “ፍትሐዊ ተጠቃሚነት” ዓለምአቀፍ ተቀባይነት ለማግኘት በቅቷል።

ስምምነቱ በራሱ ምሉዕ እንዳልሆነ ልሂቃን ይናገራሉ። የ”ፍትሐዊ ተጠቃሚነት” ዓለምአቀፍ ስምምነት የውሃ ተጠቃሚነትን የሚመከቱ ዝርዝር የድርድርና መግባቢያ አጀንዳዎችን የመወሰኑን ተግባር  የስምምነቱ አካል ለሆኑ አገራት ክፍት አድርጎታል። ያም ሆኖ የትኛው የአገራት ስምምነት የተፋሰስ አገራት ተጠቃሚነትን ሊያግድ እንደማይችል ማግባቢያ ሰነዱ ዓለምአቀፍ መርሆ አስቀምጧል።

ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመን እርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ መቆየቷ ውስጣዊ አቅሟን አላሽቆታል። በዚህ ምክንያት በዓባይ ውሃ መጠቀም የሚገባትን ቅንጣት ሳትጠቀም ቆይታለች። በ21ኛው ክ/ዘ መጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያ ከዓባይ ወንዝ መጠቀም የቻለችው ከአንድ በመቶ የማይበልጥ አቅሙን እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ግብፅ ደግሞ የዚህ ወንዝ 80 በመቶን ለጥቅም አውላ ተገኝታለች። ይህ የተጠቃሚነት ድርሻ ፈፅሞ ፍትሐዊ እንዳልሆነ ሁሉም የሚያረጋግጠው ሀቅ ነው።

ባለፉት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያ በአንፃራዊ ሰላም ውስጥ የቆየች ከመሆኗ ባሻገር ኢኮኖሚዋም ተከታታይነት ያለው ዕድገት አስመዝግቧል። ከዚህ ጎን ለጎን የህዝብ ቁጥሯም በእጅጉ አሻቅቧል። በውጤቱም የአገሪቱ ውስጣዊ የልማት ፍላጎቶች አይለዋል። ይህ ደግሞ በግዙፉ ወንዟ ዓባይ ላይ ፍትሐዊ ጥቅሟን እንድታረጋግጥ ያስገድዳታል።

የዓለም ባንክ በ1997 ባወጣው ሪፖርት “የዓባይ ውሃ ለኢትዮጵያ ዕድገትና ልማት የሚውል ከፍ ያለ አቅም ይዟል። የዓባይ ወንዝ ልማት ድህነትን ለመቀነስ በምታደርገው ጥረት የሚጫወተው ሚና ወደር የለውም። የአገር ውስጥ የኃይል ፍላጎቷንና የምግብ አቅርቦቷን ከማሟላት አልፎ ለወጪ ንግዷ ስትራቴጂ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት አያጠራጥርም” ብሏል።

በርግጥም የዓለም ባንክ የተናገረው፤ በግብፅ ዘንድ የሺህ ዓመታት ስጋት ሆኖ የቆየው፤ በኢትዮጵያኑ በኩል ደግሞ ቁጭት ሆኖ ዘመናትን የተሻገረው የዓባይ ወንዝ ተጠቃሚነት ጉዳይ ጊዜው ሲደርስ እውን ሆኗል። ኢትዮጵያ ያጎለበተችው ውስጣዊ አቅም በወንዙ ለመጠቀም የሚያስችል ደረጃ መድረሱን በተረዳችበት ጊዜ የተጠቃሚነት ፕሮጀክት ነድፋ በይፋ ሥራ ጀምራለች። ይህም ባረጀና ባፈጀው የ”ታሪካዊ ባለመብትነት” መርሆ ስትመራ በኖረችው ግብፅና በ”ፍትሐዊ ተጠቃሚነት” አስተሳሰብ ውሃውን ለመጠቀም በተነሳችው ኢትዮጵያ መካከል ውጥረት ፈጥሯል። ጊዜ ያለፈበት እና ዘመነኛውን አስተሳሰብ በተቃርኖ አፋጦ ወደ ድርድር አምጥቷል።

የኢትዮጵያ እርምጃ እና የግብፅ ፍጥጫ

ኢትዮጵያ በሰኔ ወር 1996 የዓባይ ወንዝ ገባሪ በሆኑ ሁለት አነስተኛ ወንዞች ላይ ግድብ ለመገንባት መነሳቷን ይፋ አድርጋለች። መንግሥት በሰጠው መግለጫ “ኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ ድጋፍ ቢያገኝም ባያገኝም የጀመረው የማስተር ፕላን ጥናት እንዳለቀ ግንባታውን ይጀምራል” ብሎ አቋሙን ይፋ አድርጓል።

የግብፅ መንግሥት ብዙ ወራት ሳይቆይ በጥር ወር 1997 ላይ አዲስ የበረሃ መስኖ ልማት እንቅስቃሴ በማስጀመር ለኢትዮጵያ ዕቅድ ምላሽ የሚመስል ተግባር ላይ ሲሰማራ ታይቷል። የ”ቶሽካ ቦይ” የተሰኘው ይሄ የግብፅ መንግሥት አዲስ የበረሃ መስኖ ተግባር ዋና አላማው የናይል ወንዝን አቅም አሟጦ በመጠቀም ግብፅ በውሃው ላይ አለኝ የምትለውን የ”ታሪክ ባለመብትነት” መርሆ ይበልጥ ለማጥበቅ አስባ ያደረገችው መሆኑን ኤርሊች ይገልፃል።

የወቅቱ ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ይህንን የግብፅ ዕርምጃ ለመቃወም ጊዜ አልወሰደባቸውም። “የግብፅ ድርጊት በውሃው ላይ ያላትን የራስ ብቻ ተጠቃሚነት ስስታም ፍላጎት የሚያሳይ ነው” ሲሉ ዕርምጃዋን ተችተውታል።

ጠ/ሚ መለስ ግብፅ የጀመረችው የ”ቶሽካ ቦይ” ፕሮጀክት ከሌላ ቦታ የተገኘን ውሃ ለበረሃ ልማት በማዋል የቆየ የብቻ ተጠቃሚነት አስተሳሰቧን ለማጠናከር የተወሰደ ዕርምጃ እንደሆነ ተናግረዋል። ይህ ድርጊት የናይል ተፋሰሱ አገራት ፍትሐዊ የውሃ ተጠቃሚነት ድርሻቸው ላይ የመደራደር ዕድል እንዳይኖራቸው ታስቦ የተከወነ መሆኑንም ገልፀዋል። በዚህ ተቃውሟቸው የአዲሱ የ”ቶሽካ” ፕሮጀክትና አሮጌው የ1959 የቅኝ ግዛት ስምምነትን እኩል ከሰዋቸዋል። “እንደሚገባኝ ሁለቱም የውሃው ባለድርሻዎቹን ያገለሉ የግብፅ ጉዳዮች ብቻ ናቸው። ስለዚህም ፍትሐዊነት ይጎድላቸዋል” ማለታቸው ይታወሳል።  

የኢትዮጵያ መንግሥት የግብፅን ድርጊት በመቃወም ብቻ አላበቃም። በወርሃ ግንቦት 1998 በዓባይ ወንዝ ላይ 175 የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታን በይፋ ጀምሯል። “እንዲህ ዐይነቱ የላይኛው ተፋሰስ አገራት ተግባራት የታችኛው ተፋሰስ አገራት የውሃ አቅርቦትን በሂደት እየቀነሰው ይመጣል” ሲሉ ጠ/ሚ መለስ ግብፅ የምትወስዳቸው የግል ዕርምጃዎች አፀፋዊ ምላሽ መልሶ እራሷን የሚጎዳ እንደሚሆንም አስጠንቅቀዋል።

የናይል ውሃ ጉዳይ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በተፋሰሱ አገራት ይበልጥ መነጋገሪያ አጀንዳ ለመሆን በቅቷል። በውጤቱም ሁሉንም የተፋሰሱ አገራት ያካተተ የ”ናይል ቤሲን ኢንሼቲቨ” በፌብሩዋሪ ወር 1999 በዳሬ ሰላም ሊመሰረት በቅቷል። ዘጠኙ የተፋሰሱ አገራት ኤርትራን ታዛቢ አድርገው በታደሙበት በዚህ ስብሰባ ማብቂያ ላይ ያወጡት የጋራ መግለጫ “በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁሉም የናይል ተፋሰስ አገራት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ በትኩረት ተወያይተዋል። የጋራ ራዕያችንም ቀጣይነት ያለው የማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ልማትን በጋራው የናይል ወንዛችን ላይ ፍትሐዊ የውሃ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ የጋራ ራዕይ አንግበናል” ይላል። ግብፅም የዚህ የጋራ መግለጫ አካል መሆኗን ልብ ይሏል።

የግንባታው መቼት

ኢትዮጵያ በ2011 የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በይፋ አስጀመረች። የወቅቱ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ የግድቡ መሰረት ድንጋይ በተጣለበት ጊዜ የተጋረጠበትን ዓለምአቀፋዊ ጫናና የድጋፍ እጦት በፅናት ተቋቁሞ ዕውን እንደሚሆን ተናገሩ። “የግንባታው የፋይናንስ ምንጮች እኛው፤ መሃንዲሶች እኛው፤…” ሲሉ የግድቡ ግንባታ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ አቅም የሚከናወን መሆኑን አረጋገጡ። ግድቡ ለታችኛው ተፋሰስ አገራት /ሱዳንና ግብፅ/ ስጋት አለመሆኑንም ገልፀዋል። ይልቁንም ያልተቋረጠ የውሃ አቅርቦት እንዲያገኙ በማድረግ፤ የጎርፍ ስጋትን በማስወገድ፣ የደለል ችግርን በመቅረፍ እና የኃይል አቅርቦትን ደጃቸው በማድረስ ከፍ ያለ ጥቅም እንደሚሰጣቸውም አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ከግድቡ ግንባታ ተግባሯ ማንንም የማይጎዳ እንደሆነና በ”በሰጥቶ መቀበል” መርሆ የተመሰረተ እንደሆነ በተደጋጋሚ አረጋግጣለች። ነገር ግን የታችኛው ተፋሰስ አገራትን ዕምነት አላገኘችም። በዚህ ምክንያት የግንባታ ተግባሩ ብዙ ሳይራመድ ሁለቱን የታችኛው ተፋሰስ አገራት ከኢትዮጵያ ጋር ያጣመረ “tripartite” የተሰኘ ሦስቱን አገራትና ሌሎች ውጫዊ ሙያተኞችን ያካተተ ዓለምአቀፍ የአጥኚ ሙያተኞች ፓናል ተመስርቷል። 

ጄሲ ቬይሊ የተባሉ ልሂቅ የጥናት ቡድኑ ከተቋቋመ አንስቶ በርካታ ወራትን የፈጀ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱን ይገልፃሉ። ቡድኑ የግድቡ ግንባታ በታችኛው ተፋሰስ ላይ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ በጥልቀት ለማጥናት ሞክሯል። የግድቡ ስነ-ምድራዊ አቀማመጥ ውሃን አቁሮ ከማከማቸት አንፃር ያለው ተስማሚነት፤ ግንባታው በውሃ መጠን፣ ጥራትና ተደራሽነት ላይ የሚያስከትለውን ለውጥ፤ በኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ የሚያሳድረውን አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖና በትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት የተመለከቱ ጉዳዮች በዝርዝር ተመራምሮባቸዋል።

“ቡድኑ ከበርካታ ወራት የጥናት ስራ በኋላ ግኝቱን የሚገልፅ ትንታኔ ይፋ ቢያደርግም፤ ሪፖርቱ ድምዳሜ ላይ ያልደረሰ በመሆኑ ውዝግቡን የሚያባብስ ሊሆን በቅቷል” ይላሉ ቬይሊ። በዚህ ሳቢያ የየአገራቱ ሚዲያዎች ከየአገራቸው ፍላጎትና ጥቅም አንፃር ሪፖርቱን እየቃኙ በማራገብ በህዝቦች ውስጥ ብሔራዊ ስሜትን ባልተገባና በተጋነነ ደረጃ እንዲቀጣጠል አድርገዋል። የቀድሞ የግብፅ ፕ/ት መሀሙድ ሙርሲና ካቢኔያቸው በየሚዲያው የተራገበው ወሬ ያስከተለውን ጫና መቋቋም ተስኗቸው በቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ የጦር ነጋሪት ሲጎስሙ ተደምጠዋል።

ከ2013 ወዲህ ደግሞ ውዝግቡን ያባባሰው ሪፖርትን ወደ ጎን በመተው ሦስቱ አገራት እንደ አዲስ በዚሁ ነገረ ጉዳይ ለመደራደር ተቀምጠዋል። ይህ ድርድራቸው ሁለት ዓመት ዘልቆ አንድ ደረጃ ከፍ ያለ ውጤት አስመዝግቧል። በውጤቱም በ2015 የሦስቱ አገራት ርዕሳነ መንግሥታት ተገናኝተው የጋራ መግባቢያ ላይ የደረሱበትን ሰነድ በፊርማቸው ለማፅደቅ በቅተዋል።

ስምምነቱን ተከትሎ ተደራዳሪዎቹ አገራት የግድቡ ግንባታን በጋራ ትብብር ሊያካሂዱ የሚችሉበትን ቴክኒካዊ ጉዳዮች መቅረፅ ጀምረዋል። ለዚህ አሰራር እንዲያመች የሦስቱም አገራት የውሃ ሚንስትሮች የሚመሩት ቴክኒካል ቡድን ተመስርቶ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የዘለቀ ጉንጭ አልባ ድርድር ውስጥ ቆይቷል።

የቅርብ ጊዜ ዘገባዎች እንደሚያወሱት ድርድሩ ያተኮረባቸው አበይት ጉዳዮች በውሃ አሞላሉ ሂደትና በግድቡ አስተዳደር ላይ ያተኮሩ ናቸው። ኢትዮጵያ ግድቡን ከዘንድሮ የክረምት ወቅት አንስቶ ከአራት እስከ 10 ዓመት ባለው ጊዜ የመሙላት ዕቅድ ይዛለች። ግብፅ በዚህ ሃሳብ አትስማማም። የግድቡ አሞላል ከ12 ዓመት አንስቶ እስከ 21 ዓመት /እንደ ሁኔታው ሊራዘም ይችላል/ የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲከናወን ሃሳብ አቅርባለች።

በውሃ አሞላሉ ላይ በሚነሳው በጊዜ ገደብ ላይ ባተኮረው የልዩነት ነጥብ ውስጥ የድርቅ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜያት ሊኖር የሚችለው የውሃ አጠቃቀም ሂደት አጀንዳ ሆኖ እያከራከረ ይገኛል። ‹‹foreignpolicy.com›› የተሰኘ ድረ ገፅ እንደዘገበው የተፋሰሱ አካባቢ አሰልሶ ለሚከሰት ድርቅ የተጋለጠ ነው። ይህ ሁኔታ በውሃ አቅርቦቱ ላይ ከፍ ያለ ተፅዕኖ ያሳድራል። በዚህ አይነት የአደጋ ጊዜ ላይ ውሃውን መጠቀም የሚገባው ማን እንደሆነ በሚያትተው የመደራደሪያ ሃሳብ ላይም ሰፊ ልዩነት ይንፀባረቃል።

በተጨማሪም የግድቡ አስተዳደር ላይ ግብፅ በቀጥታ እጇን የማስገባት ፍላጎት ማሳየቷ ሌላው አወዛጋቢ ነጥብ ሆኗል። የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ልዑካን በተደጋጋሚ “የሉዐላዊነታችን ጉዳይን አሳልፎ በሚሰጥ የመደራደሪያ ሃሳብ ላይ አንስማማም” ሲሉ የሚሰሙት ለዚህ ሳይሆን እንዳልቀረ ተንታኞች ይገልፃሉ።

ከ2015 አንስቶ እስከ እዚህ ጊዜ የዘለቀው ድርድር በተጠቀሱት አንኳር ጉዳዮች ላይ የሚያግባባ ሃሳብ ማምጣት ሳይችል እዚህ ደርሷል። ነገር ግን የግድቡ ግንባታ አልተቋረጠም። ይልቁንም ግንባታው ወደ መጠናቀቁ ተቃርቧል። ይህ ሁኔታ ያሳሰባት ግብፅ ለመንግሥታቱ ድርጅት ያቀረበችው የ”አሸማግሉኝ” ጥያቄን ልዕለ ኃያሊቱ አገርና የዓለም ባንክ ተቀብለው ድርድሩ ላይ ጥላቸውን አሳርፈው ቆይተዋል።

በተለይም ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ጣልቃ በመግባት የድርድሩን ሂደት ለመጠምዘዝ ጥረት አድርጋለች። ከዚህ አልፋ ሁለቱ የግርጌ ተፋሰስ አገራት ብቻ በተገኙበት የድርድር ጉባኤ ኢትዮጵያን ያላካተተ አዲስ ስምምነት አፈራርማቸዋለች። ኢትዮጵያም ስምምነቱ ከዚህ ቀደም ሦስቱ አገራት ተግባብተው ካፀደቁት መርሆ የሚጋጭና ሕገ-ወጥ መሆኑን ፈጥና በማሳወቅ ተቃውሞዋን ይፋ አድርጋለች።

የታለቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከአንድ ወር በኋላ የውሃ ሙሌት እንደሚጀምር መገለፁ ግብፅን ክፉኛ አሳስቧታል። የአገሯ ሚዲያዎች የ”ውሃችን አይነካም” ዛቻ ከማሰማት አልፈው የጦር አውርድ ዘገባ ሲያስተጋቡ ይደመጣሉ። መንግሥቷም የኢትዮጵያን ዕርምጃ ተቃውሞ እስከ ፀጥታው ምክር ቤት የደረሰ ስሞታ አቅርቧል። በዚህ ጉዳይ በተደጋጋሚ ወላዋይ ፖሊሲ ስታራምድ የቆየችው ሱዳንም በቅርቡ የቀደመ አቋሟን ቀይራ “ሦስቱ አገራት አንዳች መግባባት ላይ ሳይደርሱ ኢትዮጵያ ውሃ መሙላት መጀመሯን እቃወማለሁ” ብላለች። የዐረብ ሊግም በአንድ አብሮ ኢትዮጵያ ላይ የተቃውሞ ድምፁን አሰምቷል።

ይህ ሁሉ ኢትዮጵያን ከአቋሟ አላነቃነቃትም። ባቀደችው ጊዜ መሰረት የውሃ ሙሌቱን እንደምትጀምር አሁንም በፅናት እያሳወቀች ትገኛለች።    

ጦርነት ወይስ…?

ግብፅ በዓባይ ጉዳይ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ማሰማት የተለመደ ተግባሯ ነው። በ1979 የወቅቱ ፕሬዚዳንቷ አንዋር ሳዳት ከእስራኤል ጋር የነበረው የተካረረ ፀብ በርዶ ለእርቅ በቅተዋል። በሌላ ጎኑ በዚሁ ዓመት ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ ግድብ የመገንባት ዕቅድ እንዳላት ተሰምቷል። ሳዳት ዜናው አበሳጭቷቸው “ከዚህ በኋላ ግብፅን ወደ ጦርነት የሚያስገባት ብቸኛ ምክንያት የውሃ ጉዳይ ነው” ሲሉ ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ ዛቻ አሰምተዋል።

ከአስር ዓመት በኋላ ደግሞ የተባበሩት መንግሥታትን የዋና ጸሐፊነት ወንበር የተቆናጠጡት ግብፃዊው ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ “ቀጣዩ አካባቢያዊ ጦርነት ሊሆን የሚችለው የፖለቲካ ጉዳይ ሳይሆን ውሃ ነው” በማለት ማስፈራሪያ አዘል አስተያየት ሰጥተዋል።

መሀመድ ሙርሲም በአንድ ወቅት “ኢትዮጵያን እወጋለሁ” ሲሉ በገዛ ቴሌቪዥናቸው ታይተዋል። የአሁኑ ፕሬዚዳንት አልሲሲም የአገራቸውን የዓባይን ውሃ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ “ማንኛውንም አማራጭ እንጠቀማለን” ማለታቸው የሚዘነጋ አይደለም።

ግብፅ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከጅማሮው አንስቶ በፈጠረባት ከፍተኛ ስጋት ከዛቻና ማስፈራሪያ አልፎ ወደ ተግባር ለማሸጋገር ሞክሮ እንደነበር በ2012 ይፋ የሆነ መረጃ አመላክቷል። “ስትራትፎር” የተሰኘው የአሜሪካው የግል ስለላ ድርጅት ይፋ ባደረገው መረጃ ግብፅ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ለመደምሰስ ከሱዳን ጋር ተማክራለች። በዚህ ምክክሯ መነሻውን ከሱዳን መሬት ያደረገ የአውሮፕላን ጥቃት በመፈፀም አልያም ልዩ ኮማንዶዎችን አስርጎ በማስገባት ግንባታውን ለመምታት አሲራለች።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግብፅ የጦር ኃይል አቅሟን ለማጎልበት የተለየ ትኩረት ሰጥታ ስትንቀሳቀስም ዕየታየች ነው። ይህ ተግባሯ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር የተገናኘ ሳይሆን እንደማይቀር የሚጠራጠሩ ወገኖች ብዙ ናቸው። ምንም እንኳን ይፋ የሆነ የተረጋገጠ መረጃ ባይገኝም ግብፅ በደቡብ ሱዳን የጦር አውሮፕላን መነሻ የሚሆን ቦታ ማግኘቷ ውስጥ ውስጡን ይነገራል።

ግብፅና ኢትዮጵያ ከወታደራዊ አቅም አንፃር ደረጃቸው ሲፈተሸ ልዩነታቸው ሰፊ ነው። “ግሎባል ፋየር ፓዎር” የተባለው የጦር አቅም ማሳያ ሰሌዳ ባወጣው የ2020 የአገራት ደረጃ ግብፅ ባላት የጦር አቅም በዓለም ላይ የ9ኛ ደረጃ እርከን እንደያዘች ጠቁሟል። በዚሁ ሰሌዳ ኢትዮጵያ የ60ኛ ደረጃ ላይ ሰፍራ ትገኛለች።

“ጦር ኃይል መገንባትና ጦርነት ማሸነፍ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ግብፅ የቀደመ ታሪኳን ስህተት ለመድገም ካላሰበች በስተቀር ወደዚህ ዕርምጃ አትገባም። ከ85 በመቶ የሚበልጠው የውሃ ፍላጎቷ የሚመነጨው ከኢትዮጵያ ነው። ኢትዮጵያን መውጋት የገዛ ውሃዋን ማድረቅ እንደሆነ ልትረዳው ይገባል” ይላሉ ቬይሊ።

ኤፕሪል 23፣ 2020 ለንባብ የበቃው የ”ዘ ጋርድያን” ጋዜጣ የናይል ተፋሰስ አካባቢ ከፍ ያለ ተፈጥሯዊ አደጋ ባንዣበበበት በዚህ ጊዜ ጦርነት ትክክለኛ አማራጭ እንዳልሆነ ያትታል። ዘገባው የአሜሪካ ሥነ ምድር ተመራማሪዎችን እማኝ ባደረገበት ጽሑፉ “የተፋሰሱ አካባቢ እያሰለሰ በሚገጥመው የድርቅ አደጋ ሳቢያ በአሁኑ ጊዜ አስር በመቶ የሆኑት የተፋሰሱ ህዝቦች እጅግ ከባድ ለሆነ የውሃ እጥረት ተዳርገዋል። በዚህ ላይ በአካባቢው የነገሰው ኢ-ፍትሐዊ የውሃ ተጠቃሚነት ድርሻ ችግሩን እያባባሰው ነው” ብሏል።

እንደዘገባው ይህ አደጋ እየተባባሰ የሚመጣ ነው። “በ2040 የናይል ተፋሰስ በተከታታይ በሚገጥመው ድርቅ ምክንያት የውሃ መጠኑ በ35 በመቶ ይቀንሳል። ይህም ከ80 በመቶ በላይ ነዋሪውን አደገኛ ለሆነ የውሃ እጦት ይዳርገዋል” ሲል ሳይንሳዊ መረጃዎችን ጠቅሶ አስረድቷል።  

በዚህ አደጋ በተከበበ የውሃ ተፋሰስ ላይ የሚበጀው በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሆነ ልሂቃን ይመክራሉ። ጦርነት ያለውን ከማውደም እና ችግርን ከማባባስ በቀር ረብ አይኖረውም። በአንፃሩ የጋራ መግባባት ደግሞ ችግርን የመቅረፍ ዕድልን ያሰፋል።

እንደ ቬይሊ ምክረ ሃሳብ የተፋሰሱ አገራት ዘላቂነት ያለው ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ የሚችሉት በዚህ ሃሳብ የተቃኘ የጋራ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ነው። የተፋሰሱን የአካባቢ ጥበቃ ስራ በማጎልበት የአየር ንብረት ለውጥ ከሚያስከትልበት ጉዳት መጠበቅ። የተቀናጀ የልማት ተግባራትን በማከናወን አንዳቸው ለሌላቸው የሚተርፍ ውጤት ማስመዝገብ። አጠቃላይ የናይል ተፋሰስ ጉዳይም ሆነ በተናጠል የኢትዮጵያና ግብፅ ውዝግብ ዘላቂነት ያለው ዕልባት ማግኘት የሚችሉት በዚህ አስተሳሰብ ሲመሩ ነው። ተንታኞች “ዘመኑን የዋጃ እውነት” ብለው የሚገልፁት የመፍትሔ ሃሳብ ድምዳሜውን እዚህ ላይ ያደርጋል።

ማጠቃለያ

ኢትዮጵያ በ2015 ከሁለቱ የናይል ግርጌ ተፋሰስ አገራት /ሱዳንና ግብፅ/ ጋር በህዳሴው ግድብ ግንባታ ዙሪያ የጋራ መግባቢያ ሰነድ መፈራረሟ ይታወሳል። ይህ መርሆ በማናቸውም መንገድ ተቀባይነት ያለው እና የጋራ ጥቅምን የሚያስጠብቅ መሆኑ በዓለም መድረክ ተረጋግጧል። ኢትዮጵያ በዚህ ሰነድ ድርድሩ እንዲቀጥል የያዘቸውን አቋም በማያወላዳ ሁኔታ አጠናክራ መቀጠል ይጠበቅባታል።

የጋራ መግባቢያ ሰነዱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በሦሰት ዙር በተከፋፈለ የአሞላል ሂደት እነዲከናወን በአንቀፅ አምስት ላይ ድንጋጌ አስቀምጧል። መርሆው ሦስቱ አገራት ያዋቀሩት ዓለምአቀፍ የሙያተኞች ፓናል የሰጠውን ምክረ ሃሳብ ተከትሎ የሦስቱ አገራት የቴክኒክ ቡድን የተስማማበትን ሂደት መሰረት አድርጎ የተቀመጠ ነው።

በዚህ አንቀጽ ሁለተኛ ነጥብ ላይ “የመጀመሪያው የግድቡ ውሃ ሙሌት ከግንባታው ጎን ለጎን የተለያዩ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መንገድ የሚካሄድበት መመሪያ ላይ ተስማምተዋል” የሚል ሃሳብ አስቀምጧል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት የማካሄድ ዕቅዷን ስምምነቱ የሚደግፈው መሆኑ አያከራክርም። ከዚህ በኋላ ከናይል ተፋሰስ የግርጌ አገራት የሚመጣን ሌላ ቅድመ ሁኔታ እንድትቀበል የሚያስገድዳት ድንጋጌ የለም። ከዚህ ሦስቱንም የሚገዛ መግባቢያ ሰነድ ባፈነገጠ ሁኔታ የግርጌው አገራት በየጊዜው የሚያመጧቸውን ተለዋዋጭ የድርድር ሃሳቦች ማስተናገድ ተገቢ አይሆንም።

እንዲህ ዐይነቱ ተለዋዋጭ አስተሳሰቦች ኢትዮጵያ ከተፈራረመችው ሰነድ እንድታፈነግጥ መንገድ ስለሚከፍት ዳግመኛ ወደ መርሆው መመለስ ሊከብዳት እንደሚችል ዕሙን ነው። በዚህ ረገድ በተለይም ግብፅ ዓለምአቀፍ አሸማጋይ ፍለጋ የምትኳትንበት መንገድ በጥንቃቄ ሊታይ ይገባል። እንቅስቃሴዋ ሊያስከትል የሚችለውንም ጫና ለመቋቋም መዘጋጀትም ተገቢ ይሆናል።

የስምምነት መርሆው አንቀፅ 10 በግልፅ እንዳስቀመጠው ሦስቱ አገራት በመካከላቸው ሊነሳ የሚችሉ አለመግባባቶችን ለመፍታት በጋራ መመካከርና መደራደርን ቅድሚያ ይሰጣሉ። ይህ ባይሆን እንኳን ሦስተኛ አካል በጉዳያቸው መካከል ለማማከር፤ ለማሸማገልም ሆነ ለመዳኘት ጣልቃ ሊገባ የሚችለው በሦስቱም ፍቃደኝነት መሰረት እንደሆነ ደንግጓል።

ድንጋጌው በአግባቡ ሲቃኝ ግብፅ በግሏ ወደ ዓለምአቀፍ ተቋማትና ኃያላን አገራት እያቀናች የምታሰማው አቤቱታ ስምምነቱን የጣሰ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ይህ ደግሞ በማንኛውም መስፈርት ተቀባይነት አይኖረውም።  

በተለይም ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ በድርድሩ ውስጥ ጣልቃ ገብታ ተፅዕኖ ለመፍጠር የተንቀሳቀሰችበት ሂደት ከፍ ያለ ጥንቃቄ ይሻል። በርካታ ዘገባዎች የግብፅና የኢትዮጵያን ውዝግብ በአካባቢያዊ ፖለቲካ ላይ እንደሚደረግ የበላይነት ግብግብ ሲገልፁት ይስተዋላል። አሜሪካም “ይህንን ግብግብ በላቀ ዲፕሎማሲያዊ ጫና አበረድኩ” በማለት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እየዳከረች መሆኑን ይተነትናሉ። ይህ ደግሞ በተለይም ፕሬዚዳንቷ ከስድስት ወራት በኋላ ለሚጠብቃቸው የምርጫ ውድድር ደጋፊ ለማሰባሰብ ጥሩ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው ዘገባዎቹ ይገልፃሉ።

በኢትዮጵያ ጉዳይ በተለይም የምዕራባውያን አገራት የሚፈጥሩት ጣልቃ ገብነት ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚብስ ታሪክ በተደጋጋሚ አረጋግጧል። ይህ እውነታ ዛሬም ይቀየራል ብሎ ማሰብ ስህተት ነው። ግብፅ ከሥነ ምድራዊ አቀማመጧና በከረመ ወዳጅነቷ ምክንያት ለነዚያ ወገን ትቀርባለች። በዚያ ላይ በዐረቡ ምድር ያላት ተፅዕኖ ፈጣሪነት የጎላ ነው። ይህ ሁሉ ባዕዳኑ ለግብፅ ያደላ ፍርደ ገምድል እንዲያሳልፉ ዕድል ይከፍታል። 

በዚህ መካከል የዘመናት የኢትዮጵያ ህዝብ የጥቅም ቁጭት የወለደውና አገር ወገን ጥሪቱን ያሟጠጠበት ፕሮጀክት ችግር እንዳይገጥመው ጠንቃቃ መሆን ይሻል። የአገራቱ ጉዳይ በራሳቸው የድርድር መንገድ ዕልባት የማያገኝ ሆኖ የሌላ ወገን ጣልቃ ገብነትን የግድ ቢል እንኳ፤ ኢትዮጵያን የሚያዋጣት ፊቷን ወደ ናይል የራስጌ ተፋሰስ አገራትና አፍሪካውያን ወንድሞች ማዞር ነው።

ኢትዮጵያ በፖለቲካ ዲፕሎማሲውና በህዝብ ግንኙነት መስክም የታላቁ ህዳሴ ግድብን አጀንዳ አድርጋ የመንቀሳቀሷ ነገር ሲታይ ደካማ ሆኖ ይገኛል። ይህ ስራ ዓለም እየመረረውም ቢሆን የግድቡ ግንባታ ፍትሐዊነትን እንዲቀበል የማስገደድ አቅም አለው። በመሆኑም ኢትዮጵያ በዘርፉ የተጠናከረ ስራ ውስጥ ለመግባት ውላ ማደር አይጠበቅባትም።

ሲጠቃለል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ያለው ትርጉም ቁጥር ስፍር የለውም። ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት ዕቅድ መሰረት ለመጓዝ ጠንካራ አቋም ይዞ መገኘት ይገባል። የፍፃሜው መጀመሪያ ላይ በደረሰበት በዚህ ሰዓት ተግባሩ ወደ ኋላ እንዳይመለስ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረትና ቁርጠኝነት ይዞ መገኘት ይሻል። ግብፅ ለዘመናት በኢትዮጵያ ላይ ስታካሂድ የቆየቻቸው ፀረ ህልውና የግልፅና የህቡዕ ተግባራት ሁሉ ግድቡ ዕውን ሆኖ ስራ ሲጀምር ዘላቂ ዕልባት ያገኛል።

ፕሮጀክቱ እዚህ ደረጃ እንዳይደርስ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መልኩ ዘመቻ ውስጥ የገባችው ግብፅ አካሄዷን በአንክሮ መከታተል፤ አፍራሽ ተግባራቷን የሚመክት ተመጣጣኝ ዕርምጃና ዝግጅት ማድረግ፤ በተያዘው ዕቅድ መሰረት ግድቡን ወደ ስራ ማስገባት የማንም ሳይሆን የኢትዮጵያውያን ጉዳይ ይሆናል። ይህንን ፈፅሞ አለመገኘት በታሪክ ያስወቅሳል። ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት ከተቻለ ደግሞ ትውልዱ በታሪክ ስንክ-ሳር በወርቅ ቀለም ስሙ ተከትቦ የሚዘከርበት ትልቅ ዕድል ይፈጥራል።  

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top