የታዛ ድምፆች

ታሪክን መጥላት እንጅ መካድ አይቻልም!

ግንቦት ሃያን ብቻየን በድምቀት እያከበርኩ ነው… ምክንያቱም ታሪክን መጥላት እንጅ መካድ አይቻልማ! ብዙ ሰዎች ህወሃትን እንደሚጠሉ እያየሁ ነው! ጥላቻም ይሁን ፍቅር ሰዋዊ ነው! ችግሩ ግን ህወሃትን ለመጥላት የግድ መንግስቱ ሃይለማሪያምን ማንቆለጳጰሳቸው ላይ ነው! በደርግ ዘመን ከአምስት መቶ ሺህ (ግማሽ ሚሊየን) በላይ ኢትዮጵያዊ በግፍ ተረሽኗል! አገሪቱ ሲኦል ነበረች… አንድ ምሳሌ ብንወስድ እንኳን መላኩ ተፈራ የሚባለው ቀንደኛ የደርግ ባለስልጣን በጎንደርና አካባቢው ለአቢዮቱ አልታዘዛቸሁም በሚል ሰበብ ብዙ ሽህ ወጣቶች በገፍ እንዲረሸኑ አድርጓል! ይሄ ሰቆቃ በመላው ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ነበር… ታዲያ እናቶች እንዲህ ብለው ገጠሙ

“መላኩ ተፈራ የግዜር ታናሽ ወንድም

የዛሬን ማርልኝ ሌላ ልጅ አልወልድም”

እንግዲህ የህወሃት የትጥቅ ትግል ከሰሜን ተነስቶ የደርግን ስርዓት ጠራርጎ ካስወገደና መላኩ ተፈራንም እስር ቤት ካስገባ በኋላ ለመላው ኢትዮጵያዊ ‹‹አይዟችሁ እንደፈለጋችሁ ውለዱ ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት›› አለ! እዚህ ፌስ ቡክ ላይ ዛሬ የሚንጫጫውና መንግስቱን የሚያንቆለጳጰሰው ብዙሃኑ ከዛ በኋላ የተወለደ ነው! እንኳን ቁሞ ለመከራከር ለመወለድ እንኳን የሚበቃ ነፃነት ያልነበረው!! እውነትን አትካድ ነገ ልጆችህ አንዱ ፈረንጅ የቀረፀውን ቪዲዮ አልያም በማስረጃ የፃፈውን መጽሐፍ ማየታቸው አይቀርም! ያኔ የቅርቡን የካድክ አንተ የሩቁን አድዋ ስታወራ አያምኑህም! አባቶቻችን ውሸታም ነበሩ እንጅ ጀግና ነበሩ አይሉህም!! ምንም ማድረግ አይቻልም እውነታው ይሄው ነው! ጀግንነት የመተኮስና የመፎከር ወኔ ብቻ አይደለም… ቢመርም እውነትን የመዋጥ አቅም እንጅ!

 

እንኳን ጦርነት የመንደር ለከፋ ያስደነግጣል!

(አሌክስ አብርሃም)

ግንቦት 20 ለእኔ አዲስ አበባ ገብተው ውስኪ የተራጩ ባለስልጣናት ድል አይደለም፣ ግንቦት 20 ውስብስብ የሴራ ፖለቲካ ትርክት አይደለም! ግንቦት 20 ለእኔ ገና በአፍላነታቸው ‹‹ነፃነት›› ብለው በየበረሃው ደማቸውን የረጩ ወጣት ኢትዮጵያዊያን ድል ነው! ከምንም በላይ ግን ሁልጊዜ የሚያስደምመኝ በዚህ ትግል የሴቶች አስገራሚ ተሳትፎ ነበር!!

በእኔ ንባብ በአገራችንም ይሁን በዓለም የጦርነት ታሪክ ውስጥ በጣም አልፎ አልፎ በሆነ አጋጣሚ ለዛውም በጣም ትንሽ ሴቶች ብቻ በቀጥታ ውጊያ ውስጥ ካልገቡ በስተቀር የሴቶች የጦር ተሳትፎ ለጦረኞች ምግብ ከማብሰልና ልብስ ከማጠብ እንዲሁም ቁስለኞችን ከማከም ያለፈ አልነበረም ከአንደኛው የአለም ጦርነት በኋላ ደግሞ ሴቶች ወደጦርነት የዘመቱ ወንዶችን ቦታ በመተካት በፋብሪካዎችና መሰል ስራ መስኮች ላይ ይሰማሩ ነበር! “home front” ይሉታል! ከኛው የውስጥ ስለላ ቢለይም ቅሉ የውስጥ አርበኛ በሚል እንተርጉመው!!

ያው ታሪክን መሰነድ ላይ ትልቅ ችግር ስላለብን እንጅ እንደ ህወሃትና ሻዕብያ ትግል ሴቶችን በስፋት ያሳተፈ የትጥቅ ትግል በመላው ዓለም ስለመኖሩም እርግጠኛ አይደለሁም (ካለ ወዲህ በሉ) አስባችሁታል…ዛሬ አለም ስለሴቶች መብት የተሻለ ግንዛቤ ፈጥሪያለሁ በምትልበት በዚህ ሰዓት እንኳን ሴቶቻችን እንኳን የተጨቆነ ህዝብ ጠመንጃ አንስተው ነፃ ሊያወጡ ከባላቸው ጥፊ እንኳን ራሳቸውን ማዳን አቅቷቸው በየጓዳው የሚያለቅሱትን ቤት ይቁጠራቸው! ባሉን ተውት ተምረናል ሰልጥነናል በሚለው የከተሜው አካባቢ እንኳ ዛሬ ላይ እንኳን የሚተኩስ ወታደር ፊት መቆም ባዶ እጁን የሚያፏጭ የመንደር ጎረምሳ ለከፋ አረማመዳቸውን የሚያጠፋባቸው ስንት ሴቶች ናቸው…

እንግዲህ ከአራት አስርት ዓመታት በፊት ተራራ ወጥተውና ወርደው ከወንድ እኩል ብረት ተሸክመው ፍፁም ከሰለጠነና ዘመናዊ መሳሪያ ከታጠቀ ኃይል ጋር ፊት ለፊት ተፋልመው ያንን ኃይል ያፈራረሱ ወጣት ሴቶች ነበሩ የሚል ታሪክ ለማመን የሚከብድ ነው! ግን ደግሞ እውነት ነው! ይሄ ጉድ አሜሪካ ቢሆን ሆሊውድ አርቲፊሻል ጀግኖች እያመረተ ፊልም መስራቱን አቁሞ ብዙ ሺህ ፊልም ባመረተ ነበር! የምእራብያኑ ፀሃፍት ስንት መድብል ፅፈው ቤተ መፅሃፍቶቻቸውን በሞሉት ነበር! ሙዚየሞቻቸው እነዚህ ወጣት ሴቶች በነኩት በረገጡት ሳር ቅጠል በተሞላ ነበር!

የሆሊውዱን ተውትና ህንድ ውስጥ የተፈፀመና የምታውቁትን ታሪክ ላስታውሳችሁ… ሳትፈልግ ያገባችው ባሏ ግፍና የቤተሰቦቿ ተባባሪነት አስመርሯት ጠፍታ የሽፍቶች ቡድን ጋር የተቀላቀለችና ቆይቶም የሽፍቶቹ መሪ ሁና ስትዘርፍና የበደሏትን ሁሉ ስትገድል የኖረች በኋላም አገር አቀፍ ጀግና ተብላ እስከ ፓርላማ አባልነት የደረሰች ፉላን ዴቪ /phoolan devi/ የተባለች አንዲት ጀግናቸውን በስንት መፅሃፍና በስንት የሆሊውድ ፊልም ለዓለም እንዳስተዋወቋት ስታዩ ትገረማላችሁ!

ያው ግን እኛ እኛ ነንና ብዙዎቹን በስም እንኳን ለታሪክ መመዝገብ አልቻልንም! በነገራችን ላይ በሻእቢያና ህወሃት ውስጥ ቁጥራቸው ከ15 ሺህ የሚልቅ ሴቶች ቋሚ ተዋጊ ሁነው ተሳትፈዋል! እነዚህ ሴቶች እጅግ አደገኛ ከሆነው የስለላ ስራ ጀምሮ የከባድ መሳሪያ ምድብተኛ እንዲሁም አዋጊ በመሆን ጭምር የተዋጉ ነበሩ! ከትግሉ በኋላም በከፍተኛ ሃላፊነት ላይ ተቀምጠው ያገለገሉ ብዙ ናቸው! ከጥላቻና ተራ የፖለቲካ ስንክሳር የወጣን ህዝቦች ብንሆን ኑሮ… ገና ጓዳ ለጓዳ ለሚያለቃቅሱት የኢትዮጵያ ሴቶች የመብትና እኩልነት ጥያቄ ትግል እነዚህ ሴቶች ወደር የለሽ ምሳሌዎች በሆኑት ነበር!

ዘመናት ያልፋሉ፣ አንዳንዴ የብዙዎችን ደም ያስገበረ ትግል በጥቂቶች ክፋት በሉት ስህተት ዓላማው ተቀይሮ መጥፎ ጥላሸት ታሪክ ላይ ሊያራግፍ ይችላል… የሆነ ሁኖ ግን በንፁህ ልብ የባህልንም ሆነ የአስተዳደር ጭቆናን እምቢ ብለው በአፍላነታቸው ህይወታቸውን፣ አካላቸውን ለህዝባቸው የገበሩ የእነዚህ አስገራሚ ሴቶች ገድል በታሪክ ሲወሳ ይኖራል!!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top