ጣዕሞት

“ቅኔ ነው ሀገር” እየተደመጠ ነው

ግጥም እና ዜማውን አሰናድቶ ፕሮዲዮስ ያደረገው ኢዮኤል መንግሥቱ ነው። በሙዚቃዊ እንቅስቃሴው የምናውቀው ሰርጸ ፍሬስብሃትን ጨምሮ አንጋፋ እና ወጣት ድምጻዊያን ተሳትፈውበታል። ነዋይ ደበበ፣ ጸጋዬ እሸቱ፣ ኃይልዬ ታደሰ፣ ሚካኤል ለማ ደምሰው፣ የማርያም ቸርነት፣ ማህሌት ነጋሽ፣ ማስተዋል ዕያዩ እና ይድነቃቸው ገለታን በየዘመናቸው ውክልና ለመስጠት ሞክሯል።

ይሁን እንጂ ጥቂት በማይባሉ የሙዚቃው አድናቂዎች የትውልድ ውክልናው አስተያየት ተሰጥቶበታል። ዘፈኑን ለማስተዋወቅ በተሰሩ የምስል ማስታወቂያዎች ላይ ሦስት ትውልዶችን ያስተሳሰረ የሚል ኃይለ-ቃል መኖሩ የየዘመናቱን ልከኛ ውክልና እንድንጠብቅ አድርጎናል የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ 60ዎቹ፣ 70ዎቹ፣ 80ዎቱ፣ 90ዎቹ፣… በሚል ክፍልፋይ ትውልዶችን ማግኘት ቢከብድም ስብስቦቹ ጥሩ ሙዚቃ በመስራታቸው ላይ ይስማማሉ።

“ቅኔ ነው ሐገር” ከዩትዩብ ተመካች የሚያገኘውን ገቢ ኮሮናን ለመከላከል እንደሚውል ተነግሯል።

 የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህራንን ብቁ የሙዚቃ ሰው ከማፍራት የተሻገረ ብቃት መመልከታችንን እንደ በጎ የሙዚቃው አስተዋጽኦ የቆጠሩት አስተያየት  ሰጪዎች ደግሞ፤ ለኃይሉ ዓለማየሁ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ እዝራ አባተ (ዶክተር)፣ ለሰላማዊት አርጋው፣… እና ለሌሎችም ምስጋናቸውን ይቸራሉ።

 የዘነጋነውን የሕብረት ክንድን ኃይል በግጥሙ ብቻ ሳይሆን በክዋኔውም ጭምር እንድንገነዘብ ጥረት ባደረገው “ቅኔ ሀገር” ላይ ዳዊት ፍሬው ኃይሉን እና አበጋዝ ክብረወርቅን ጨምሮ ከዝግጅት እስከ የምስል ቀረጻ ድረስ በርካቶች ተሳትፈዋል።

 በ1960ዎቹ እና 1970ዎቹ የሐገራችን ሙዚቃ ሂደት ላይ በስፋት የተለመዱትን ኅብረ ዝማሬዎች ዳግም እንዲያንሰራሩ ሊያደርግ መቻሉ ደግሞ ለሙዚቃው በበጎ አበርክቶነት ከተጠቀሱለት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነው። ከዚያን ዘመን እስከ አሁን ያሉ ድምጻዊያንን ቀለም በአንድ ከማሳየትም ባለፈ የትላንት ታሪክ ለመሆን የበቃውን የኦርኬስትራ ሙዚቃ ጣዕም አሰምቶናል ተብሎለታል። በቲያትር ቤቶቹ፣ በያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት፣ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ፣ በፖሊስ ሰራዊት፣ በክቡር ዘበኛ፣… እና በሌሎቹም እናደምጥ የነበረውን ጣእም አምጥቶልናል። ሥራው ተቀባይነት ማግኘቱም ከ1980ዎቹ ጀምሮ በስቱዲዮ ተገድቦ የነበረው ሙዚቃችን ወደቀደመ የኦርኬስትራ አበርክቶው ቢመለስ ታዳሚ እንደማያጣ ያመላክታል ተብሏል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top