ጣዕሞት

…ሿ ፍትግ እጄን አላምን

ሰሞንኛ…

ዘፈኖቻችን ከጊዜው ጋር ተመሳስለው ኮሮና ኮሮናን መሽተት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። መሰንበትም ደግ ነው። ከህንድ እሰከ ሰሜን አሜሪካ፣ ከናይጄሪያ እስከ ኢትዮጵያ… በኢትዮጵያም በተለያዩ ሀገራዊ ቋንቋዎች እየተዜመ ነው፡፡ እኛም እያዳመጥን፣ እየሰማን እንገኛለን። እንዲህ ያሉ ሙዚቃዎች ወይም ሌላ ዓይነት ሙዚቃዎች ይሰማሉ ይደመጣሉ ስንል፤ በአንጻራዊነት በመጀመሪያ ሰሞን ቃል-በቃል ዜማ-በዜማ የሚደመጡ ሲሆን፤ ወይም ከጊዜ ቆይታ ወደ መሰማት ብቻ ሲያመሩ ነው። ይህም በበዙ ምክንያቶች ይከሰታል። ለአዕምሯችን ለአዲስ ከሌሎች ቀድመው ከነበሩ ነገሮች በተለየ ትኩረት ይሰጣል። በሂደትም ዘፈኖቹ ከአዕምሮቻችን ሲላመዱ ከመስማት (ድምጹን) በዘለለ፤ ድምጹን ወደ ድምጽ ተቀባዩ እና ድምጽ ተርጓሚው የአንጎል ክፍል በሚገባ ባለመላክ የተሟላ ትኩረት ይነፍጋቸዋል። ለዚህም ነው፤ ለነገሮች ትኩረት ለመስጠት ስንሻ “ሰሚ ብቻ ሳይሆን አድማጭም መሆን አለብን” የሚባለው።

ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፤ ስለወቅቱ ተላላፊ ህመም “በአፍ እና በአፍንጫ በሚወጡ ፍንጣሪዎች እና በመነካካት የሚተላለፍ” በርከት ያሉ የዘፈን ስራዎች በመላው ዓለም ተቀናብረዋል። በተለይም ከወደ ህንድ የተቀነቀነው “My name is Corona” የተሰኘው ሙዚቃ በብዙ እያዝናና በጥቂቱ የሚያስተምር ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ለዛሬው ዘርዝር ወጋችን የመረጥኩት ሃገርኛው ‘እጅ እንንሳ’ የተሰኘው ሙዚቃ ያብዛኛዎቻችንን ጆሮና የመገናኛ ብዙሃን አየር ሰዓትን መያዝ ችሏል (በስራው ያልተደሰቱትን ሳንዘነጋ) ለመሆኑ ይህ የጋራ ዜማ በሆዱ ምን ቢያዝል ነው፤ በልዩነት እንዲህ የተወደደውና እየተደመጠ ያለው? የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡

የሙዚቃዊ ቅንጣቶችን ጉዳይ ለጊዜው ለሙዚቀኞቹ ተወት አድርገን፤ ዘፈኑን በስነልቦናዊ (ሳይኮሎጂካል) ገጽዎች ለመመልከት እንመክራለን፡፡ ወጋችን የጠራ እንዲሆን ጥቂት መስፈንጠሪያዎችን እንደ አብነት እያነሳሳን የሙዚቃ እና የአዕምሮ ግንኙነትን፣ የሙዚቃ-ባህርይ ትስስርን እንመለከታለን፤

“የየሃገሩ ሙዚቃ” በሃገሩ ባህል የተቃኘ መሆኑ የሚታወቅ ነው። በገጠራማው የህንድ ክፍል የሚኖሩ ህዝቦች የምዕራባውያን ሙዚቃ ከራሳቸው አንጻር ሲዳኙት “አስጨናቂ” ያሉት ሲሆን፤ አሜሪካውያኑ በበኩላቸው የህንዶቹን ሙዚቃ “አስጨናቂ” ብለውታል። በኢትዮጵያ ሙዚቃም መድረክም ዝግ ያለ ስልተ ምት ካላቸው እስከ ፈጣኖቹ ድረስ ለማድመጥ የሚያድል ነው፡፡

ትንሣኤ ጎበና እና ሚሚ ሙሉቀን በተጫወቱት ዜማ ላይ ዓለማየሁ ደመቀ በግጥም እና ዜማ አበጋዝ ክብረወርቅ በቅንብር ተሳትፈዋል፡፡

ትኩረትን መያዝ

በሙዚቃ ሳይኮሎጂ ምሁራን ዘንድ አቀናባሪዎች ከሚመዘኑባቸው ነጥቦች አንዱ “ሙዚቃቸውን ሰዎች በሚያዳምጡበት ወቅት ቀጣይ የሚመጣውን ዜማ ወይም ግጥም መተንበይ መቻላቸው ላይና በዛው ሙዚቃ ውስጥ ባልተጠበቁ የዜማ ባህርያትና ግጥሞች ያልተጠባቂነት ስሜት መፍጠር መቻላቸው” ላይ ነው። አዕምሯችንም ለመተንበይ እንዲረዳው ቀድሞ ያውቃቸው የነበሩ አሃዞችን እና አምክንዮዎችን በግብአትነት ይጠቀማል።

‘እጅ እንንሳ’ ሙዚቃም ባህላዊ ለዛን በመላበሱ፣ የዜማውን ውጣ ውረድ፣ የቃላቱን አጣጣል እና አሰባበር፣ ስልተ ምቱን፣… ወዘተ ለመተንበይ ከዚህ በፊት ያለንን የባህላዊ ዜማዎች ዕውቀት እንድንጠቀም አስችሎናል፤ በቀላሉም አብረነው እናዜማለን ወይም ያለ ቃል እናንጎራጉራለን። በመሆኑም የሙዚቃውን ሙሉ ግጥም ባናቀው እንኳ ዜማውን ተከትሎ አዕምሮአችን ይተነብያል። በተለይም የሙዚቃው መግቢያ /የጎላ የማሲንቆ እና ክራር ድምጽ/ ለእንጎላችን ቀጣይ ምን ዐይነት ዜማ “ባህላዊ ቃና ያለው” ሊከተል እንደሚችል በሚገባ ይጠቁመዋል።

እንዲሁም ግጥሞቹን ስንመለከት፤ በአሁኑ ወቅት በሰፊው የሚወሩትን፣ ‘በተደጋጋሚ የሚነገሩትን’ አሃዛዊ ድግግሞሻቸው የበዙትን ሃሳቦችና ቃላት ስለተጠቀመ፤ የግጥም ትንበያችንን ያን ያህል አድካሚ አያደርገውም። ያም ሆኖ ከላይ እንዳልኩት በእንጉርጉሮ ተንብየነው ቀጣይ ወደምውናቀው ቃል ወይም ሐረግ እናልፋለን። ሁለተኛው ነጥብ ይህ ሙዚቃ መንበይ ብቻ ሳይሆን ያልተጠባቂነት ስሜትም መፍጠር እንደሚችል አምናለሁ። ለማሳያ ያህል፡-

በመጀመሪያዎቹ የግጥሙ ስንኞች ላይ ድምጻዊት ሚሚ ጭንቀትና ፍርሃት ላይ ያለች፣ “ለምን አትጨብጠኝም?” የምትል፣ አትራቀኝ ቀረብ በለኝ የምትል ሲሆን… ድምጻዊ ትንሣኤ በተቃራኒው የሚሚን የተሳሳቱ ሃሳቦች ለማስተካከል ይጥራል፤ አስከትሎም ሚሚ ወደ ትንሣኤ ሃሳብ ስትመጣ ያስደምጡናል። እጅ መጨበጥ ሳይሆን እጅ መንሳት ነው ሐገረኛው የሰላምታ ባህል በሚል ለአድማጮቻቸው የ“ነው እንዴ?” ስሜትና አትጨባበጡ ብቻ ብሎ ከማለፍ በዘለለ /በቀላሉ ልንተነብየው የምንችለው/፤ መጨባበጡ ያብዛኛው ሰው ባህል እንዳልነበረ በመንገር ያልተጠባቂነት ስሜት ለመፍጠር ያስችላል።

ሌላው ‘ሿሿ’ የሚለውን ቃል ላለፉት ጥቂት ዓመታት ከዝርፊያ ከአጭበርብሮ ዝርፊያ ወንጀል ጋር አያይዘነው የነበረ ቢሆንም፤ በዚህ ሙዚቃ ላይ ዳግም ወደ ቀደመ ስርወ-ቃላዊ ፍቺው መልሰውት /የውሃ መፍሰስ ድምፅ/ አንድም ቃሉን አክመውታል፤ ሁለትም አድማጮቻቸውን በዝርፊያ ስንጠብቀው እጅን በመታጠብ አምጥተውት ያልጠበቅነውን አቀንቅነውልናል። ሿሿ ከሚለው ቃል ውጪ ‘ምን ይመጣል ብሎ አጉል ከመጃጃል’ በሚለው ሐረግ ውስጥ ‘መጃጃል’ የሚለው ቃል በአብዛኛው በዘፈኖቻችን ውስጥ ባለመኖሩና እምብዛም የአደባባይ ቃል ባለመሆኑ እንዲሁም ቃሉ ጠንከር ያለ አሉታዊነት ስለሚታይበት በዘፈኑ ውስጥ አይጠበቄ ነው።

ልብ እንበል በቀላሉ ትኩረቱን ለሚያጣ ሰው እነዚህ ቃላትና ሐረጎች ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል ከሙዚቃው ሃሳብ ያስወጣሉ። ለዛም ነው መተንበዩ እና በተመሳሳይም ያልተጠበቀ መሆኑ በሚገባ መመጣጠን ያለበት። ከሁለት አንዱ መብዛትም ሆነ ማነስ ወይም ጨርሶ አለመኖር የሙዚቃውን ተወዳጅነት የሚያጠፉት፤ አልያም የሚያደበዝዙት። እናም ‘እጅ ከምን…’ የሚለውን ሐረግ እና ሌሎች ባልተጠበቁ መንገዶች የሰኳቸውን የግጥሙ አካላት ለእናንተ ማሰላሰያ ይሆኑ ዘንድ ተውኳቸው።    

በመግቢያዬ እንዳልኩት የባህል ጉዳይ አሌ የሚባል አይደለም። ከመጨባበጥም አልፎ አጥብቆ መሳሳም /እጅን እና ጉንጭን../ በአንዳንድ የኢትዮጵያ ክፍሎች የቀደመ ባህል ቢሆንም፤ ከወቅቱ ሁኔታ አንጻር ግን ሁሉም ወደ አንድ ‘እጅ የመንሳት ባህል’ ቢመጣ መልካም ስለሆነ ሃሳቡ አያጋጭም። በሌላ አቅጣጫ ብናየው ደግሞ፤ ከዚህ በፊት እጅ የመንሳት ባህል የሌለውም ቢሆን “ሌላው ጋር እንዲህ ነበር እንዴ?” የሚል ያልተጠባቂነት ስሜት ግጥሙ መፍጠር ስለሚችል ይሄን ሙዚቃ “የማይጠበቁ ስሜቶችን መፍጠር የሚችልና አድማጩ መተንበይ የሚችለው ነው” ልንል እንችላለን፡፡

ተንብየን ትክክል በሆንን ቁጥር አንጎል ራሱን ያበረታታል። ጥሩም ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል። ከመበረታታትና ከደስታ ጋር የተያያዘው የአንጎል መስመር ይነቃቃል። ደስተኝነትን መፍጠር የሚያስችለው አዕምሯዊ መረጃ አስተላላፊ ንጥረ ነገር በአንጎል ውስጥ ይመነጫል። ‘የተመጣጠነ ዶፓሚን ምርት ይኖረናል’። በአጠቃላይ ሙዚቃው በቀላሉ ጆሯችንን /ትኩረታችንን መያዝ ችሏል። እኛም መተንበይ በመቻላችን ስለተበረታታንበት ወደነዋል “ሁሉም ማለት እንዳይደለ እንደታወቀ ሆኖ”። ያልጠበቅናቸው ነገሮች በውስጡም በመያዙ ፈገግ ብለናል፤ ያም ፈገግታ ‘የ-Zygomatic እንቅስቃሴ’ ለደስታችን ምክንያት ሆኗል።  

ስሜትን መግዛት

ሙዚቃዎች በራሳቸው ብቻ ስሜት ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራሉ ወይ? የሚለው ሃሳብ በተወሰኑ ባለሙያዎች ዘንድ ተቀባይነት ባይኖረውም፤ አሁን አሁን ላይ ግን ሙዚቃ ስሜትን በቀጥታና ያለ ሌላ ተጨማሪ ምክንያት ተጽዕኖ ሊፈጥርበት ይችላል የሚለው ሃሳብ ተቀባይነት እያገኘ ነው። ነገሩን ግልፅ ለማድረግ ያህል፤ የመጀመሪያዎቹ ተከራካሪዎች አንድ ሰው እንቅልፉን ሊተኛ ፈልጎ፤ ነገር ግን ቤቱ ውስጥ ዘፈን ከፍ ብሎ እየተሰማ ከሆነ በዘፈኑ ሊናደድ ይችላል እንጂ፤ ግለሰቡ ከሜዳ ተነስቶ የሆነ ሙዚቃ ሰምቶ ሊናደድ፣ ሊያዝን፣ ሊደሰት አይችልም ይላሉ። ልክ ያፈቀርን ሰሞን የመፋቀር ሙዚቃ ፈገግ ያደርገናል። መግባባት ሲታጣ ደግሞ “ተበድዬስ ይቅርታ አልልም፤ የቀረው ይቅር እንጂ” የሚለው ሙዚቃ እልህ ውስጥ ያስገባናል እንጂ በሰላሙ ቀን “ተበድዬስ..” የሚለውን ሙዚቃ ብንሰማው አይሞቀንም አይበርደንም ነው ነገሩ።

ሆኖም ይህ ብያኔ የራሱ ድጋፍ ቢኖረውም፤ አሁን ላይ ያሉ የአዕምሮ ህዋሳት አጥኚዎችና ሳይኮሎጂስቶች ሙዚቃ በቀጥታ፣ ያለ ሌላ ተጨማሪ መነሻ ምክንያትም በአዕምሮ ላይ፣ በስሜት ላይ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር በጥናት እያረጋገጡ ይገኛል። ለምሳሌ አንድ ሰው ሙዚቃ በሚያዳምጥበት ጊዜ ከስሜት ጋር የሚገናኙ ተግባራትን የሚያከናውነው የአንጎል ክፍል የሚነቃቃ ሲሆን፤ በተጨማሪም ይህ ክፍል ውስጥ የሚገኙ፥ ከትውስታ፣ ከመበረታታት ጋር የሚዛመዱ ክፍሎችም ወደ ስራ ይገባሉ።

‘እጅ እንንሳ’ ሙዚቃም በዚሁ ትንታኔያችን ዕይታ ሁለቱንም ብያኔዎች አስማምቶ ይዟል። ቀዳሚዎቹ ባለሙያዎች እንዳሉት ሙዚቃው አሁን ካለንበት ወረርሽኝ የተነሳ ስሜታችንን መኮርኮር ችሏል እንጂ ያለኮሮና ዘፈኑ ምንም ነው። ይህ ምን እንደ ማለት ነው ካላችሁ፤ ከዓመታት በፊት ለኤች አይ ቪ ኤድስ የተቀነቀነውን ‘መላ በሉ’ ሙዚቃ በአሁኑ ወቅት ብናዳምጠው ‘እጅ እንንሳ’ ከሚለው ሙዚቃ ጋር ተቀራራቢ ስሜት ነው የሚሰጠን። ወይም ትካዜ ያለበት የትኛውንም ዐይነት ሐይማኖታዊ መዝሙር በአሁኑ ሰዓት ብናዳምጥ ሆዳችንን ባር ባር፣ አልቅሱ አልቅሱ፣… ሊለን ይችላል። ያከሆነ ደግሞ ሙዚቃዎቹ ወይም መዝሙሮቹ በራሳቸው ሳይሆን አንዳች ስሜት እንዲሰማን ያደረጉን ባለንበት ሁኔታ አጋዥነት ነው። ስለዚህ የ‘እጅ እንንሳ’ ሙዚቃ ወቅቱን በማገናዘቡ ስሜታችን ላይ በተዘዋወሪም ቢሆን ተጽዕኖ ፈጥሯል። 

በሌላኛው ገጽ ድግሞ አንዳንድ ሰዎችን ለማናገር እንደሞከርኩት ከሙዚቃው መልዕክት ይልቅ ከስነ ውበታዊ ‘Aesthetic’ ለዛው ጋር በፍቅር ወድቀው “እንደው ስሰማው ደስ ይለኛል ደስ አይልም?” የሚል ሃሳብ አንስተውልኛል። ‘ሿሿ’ ዘፈንም ከተለምዷዊ ስሜት “መደሰት፣ ማዘን፣ መናደድ…” በተጨማሪ ስነውበታዊ ስሜትን መጫር እንደቻለ እንገነዘባለን “የመሰንቆው ድምጽ፣ ድምጻውያኑ ቃና፣ የግጥም ምጣኔው… ወዘተረፈ”። በዚህም ሙዚቃው በራሱም ሆነ ያለኮሮና ስሜትን ቀስቅሷል። በጥቅሉ ሙዚቃው ያለኮሮናም፥ በኮሮናም ስሜታችን ላይ አንዳች ‘የመወደድ፣ የማስገረም፣ ምናልባትም ያለመውደድ’ ተጽዕኖ ፈጥሯል። ይሄ ብቻ ሳይሆን የደስታ ሙዚቃዎች ወይም ለስለስ ያሉ ሙዚቃዎች ውጥረትን የመቀነስና ፈገግታን የማምጣት አቅም አላቸው።

እንዲህ ያለው ሃሳብ ባህር ነው። በዚህ አጭር ወግ ብቻ የሚዳሰስም አይደለም። ለምን ከተባለ፤ እያንዳንዱ የድምፅ ባህርያት፣ ‘የድምጽ ውጣውረድ፣ ስልተ-ምት፣ የድምፅ ጥራት፣ ቅላጼ፣ ከፍታነ…’ ከተለያዩ ስሜቶች ጋር ይገናኛሉ፤ ይተነተናሉም። ወደ ለስላሳ ወይም የትዝታ ዘፈኖች ስንመለስ በራሳቸው ከማፍታታት በተቃራኒም የትካዜን ወይም የሃዘን ስሜትን ያመጣሉ። ‘ሿሿ’ ዘፈናችንም የፈራን፣ የተጨነቀን፣ ግብዝ የሆነን፣ መጠንቀቅ እንዳለበት የገባው፣ ግራ የገባው፣…ግለሰብ ድምጽ ያሰማናል። ሆኖም በዚሁ ጹሑፍ ላይ የሙዚቃ ባለሙያ ባለመሆኔ ቅኝቱን እና ተያያዥ ጉዳዮችን ተወት ላድርግና ጥቂት ስነ-ልቡናዊ ነገሩን ልበላችሁና የዛሬውን ጨዋታ ላብቃ።

አንድ ሙዚቃ ውጥረትን እንዲቀንስ ከሚያስችሉት ነገሮች አንዱ ድምጻውያን ካሉት፤ የድምጻውያኑ የድምጽ ጥራት ነው። በምስል የተደገፈ ከሆነ ደግሞ ምስሉ ላይ ያሉት ሰዎች እርጋታ ነው። በ‘እጅ እንንሳ’ ሙዚቃ ላይም የድምጻውያኑ የለሰለሰ ድምፅ ሃዘንና አሉታዊ ስሜት መኖሩን ለአንጎል ይልካል። እንዲሁም ከፍ ባላለ ድምፅ፤ በማይጮኽና ፈጣን ባልሆነ ምት የሚተላለፍ መልዕክት በሰሚው ዘንድ መረጋጋትን ይፈጥራል። ከሁለቱ ሃሳቦች ይልቅ ሙዚቃው ሌላም ዐይነት ድምጽ አቅፏል። የሚያወዛውዝ፣ ደግሞ ከሃዘን ጋር ያዝ ለቀቅ የሚያጫውት፣ ደግሞም የሚያስፈግግ።

የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በአንድ ጊዜ ሁለት ተቃራኒ ስሜቶችን መፍጠር የሚችሉ ‘የተለያዩ’ ሙዚቃዎችን ሰዎች ስናዳምጥ፤ ሁለቱንም ስሜቶች በአንድ ላይ እናጣጥማቸዋለን እንጂ አንዴ ካንዱ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከሌላው ስሜት ጋር አንወላውልም። ታዲያ በአሁኑ ነጠላ ሙዚቃ ውስጥ እንዲህ ዐይነቱ የስሜት መደባለቅን ምን ያህል ጊዜ ተሰምቶት ይሆን?

በመጨረሻም…

ከቅርብ ሰው ጋር ሆነን የምንሰማው ሙዚቃ አዎንታዊ ስሜት ይፈጥርልናል። እዚህ ጋር አንድ ልንረዳው የሚያስፈልግ ነገር አለ። ሙዚቃውን እኛ መርጠነው እየሰማነው ከሆነና በአጠቃላይ ከሙዚቃው ጋር ከእዚህ በፊት የምንተዋወቅ ያክል የሚሰማን ከሆነ፤ አሁንም አዎንታዊ ወይም ጥሩ ስሜት ይፈጥርብናል። ለዛሬው ወሬያችንም መነሻ የሆንን ሙዚቃ ከላይ እንደተጨዋወትነው ባህላዊ (ሐገረሰባዊ) ለዛን በመላበሱ፤ ዜማውም ሆነ ግጥሙ ለስሜታችን የበለጠ ቀርቧል። ያም ለሙዚቃው ትኩረታችንን እንድንሰጥ ወይም እንድናዳምጠው አድርጎናል። የምናውቃቸው ያልተለመዱ ፊቶችን እና ድምጾችን አበጋዝ እና ጓደኞቹ ይዘውልን በመምጣታቸው እኔም ይህንን መለስተኛ ስነ-ልቡናዊ ዳሰሳ ጻፍሁ።

እንግዲህ፥ አንዲህ ያሉ ሀሳቦችን ለመጋራት በሃገር ቤት የስነ-ልቡና ባለሙያዎች መሰል ሙከራዎች መኖራቸውን ባላውቅም፤ በቀጣይ የተሻሉ ዳሰሳዎችን በሃገራዊ ሙዚቃዎች፣ ድርሰቶች፣ የመሪዎች እና የታዋቂ ሰዎች ንግግር ላይ ይዤ ለመምጣት አስባለሁ። ናሁ-ሰናይ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top