ፍልስፍና

ሰው የመሆን እዳ

እና ውጫዊ መሰናክሉ ውስብስብ፣ ጠልፎ የሚያስቀረው መረቡ ሰፊ ነው። ከባህል የሚቀዳ ልጓም አለ፤ ሰው የመሆን ጉዞ አቅጣጫውና ትብታቡ ብዙ ነው ብለን ነበር። ሰው የመሆን ጉዞ ፈተናው ከባድ ነው፤ ውስጣዊ ከሃይማኖት የሚመነጭ የጠባቧ መንገድ ሕግና ተዕዛዝ አለ፣ ከሳይንስ የሚመጡ ትሩፋቶች ያማልሉታል፣ ራሱን አድራጊ ፈጣሪ እንደሆነ ያስባል፣ ዕብሪት። የፍልስፍና ጥሪ አለ፤ የቴክኖሎጂው “ምሉዕ በኩለሔነት” ተቃርኖዎች ያባክናሉ። ሰው የሰማያዊውም የምድራዊውም ዓለማት አማካኝ ፍጥረት የሁለቱም ዜጋ ነውና ከነፍስ በሚመጣ ጥሪ ከሥጋ በሚመነጭ ፍትወት ይባክናል። “ሰውን ሰው ያደረገው ስራው ነው” እንዲሉ አበው ሰው ራሱ ካገኘበት ህልው ሁኔታ ተነስቶ መሆን በሚፈልገው ልክ ራሱን ለመስራት በሚኳትንባቸው መንገዶች ሁሉ አያሌ መስመሮችን ሊያልፍ ግድ ይለዋል። ሰው የሚያደርገውን ሥራ ለመስራት፣ ሰው ሆኖ ለመገኘት ደግሞ ከራሱ ከተፈጥሮው በሚመነጩ እና ከማኅበረሰባዊ ቅቡልነት (Social Conventions) ሕግጋት ተወጥሮ ይባትላል። ሰው የመሆን ጉዞ እዳ አለበት፤ ሰውነት በቀላሉ የማይፈቱ ቋጠሮዎች ትብታብ ነው። አንዱን ቋጠሮ ፈታሁ ሲል ሌላው ብቅ የሚልበት የምስጢር አኮፋዳ ይመስል አለቀ ደቀቀ አይባልም፤ ብዙ ጊዜ ሰው ጉዞዬን ጨርሻለሁ ሲል አይስተዋልም። እንዲያውም የሰው ልጅ ጉዞ መቋጫ የሌለው፣ ፍላጎቱም ሽንቁር አቁማዳ ይመስል የማይረካ፣ እንደ ወንዝ ውሃ የሚነጉድ፣ ቢጨመርበት የማይሞላ እንደ ሐይቅ ውጦ ዝም ነው፤ ሰውነት ባህር ነው፣ ሰውነት ዱር ነው፣ ጥቅጥቅ ደን ነው ብለን እንድናስብ እንገደዳለን።

ባለፉት እትሞች ሰው የመሆንን ጉዞ ቅያሶች ለማየት ሞክረናል። የሰውነትን ፈትለ ነገር ብያኔ የሰጠ፣ ይህ ነው ብሎ እቅጩን የተናገረ ጠቢብ አልገጠመንም። ነገውን በእርግጠኝነት የሚናገር ነብይም እንዲሁ አልተገኘም። የቢሆን ዓለምን እያስመለከቱ፣ ይህንን አድርግ ያንን አታድርግ የሚሉ የባህል፣ የሃይማኖት፣ የፍልስፍና፣ የሳይንስ መካሪዎች ግን በርካታ ናቸው። በርግጥ ስለ ሰው ከተነገሩ ድምዳሜዎች ውስጥ ሦስቱ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።

እነሱም፦ (1) ሰው ምክንያታዊ እንስሳ ነው፣

(2) ሰው ፖለቲካዊ እንስሳ ነው፣ እና

(3) ሰው ማኅበራዊ እንስሳ ነው የሚሉት ናቸው።

የሰው ልጅ በሆነው ዓለም ውስጥ ሲዋኝ፣ ወይም የቢሆን ዓለሙን ሲመኝ ለእንደዚህ ዓይነቶቹ ባሕርያቱ ተገዥ በመሆኑ የሚነካካቸው ስስ ብልቶች አሉ። እነዚህን የተፈጥሮ ባህርያቱን ጥሪዎች በአግባቡ ካልከወነ ደግሞ ኃጢአት፣ ወንጀል፣ ነውር ውይም “ስህተት” (“ፋውል”) የሚያሰሩት፣ በእዳ ሊያስጠይቁት የሚችሉ ጉዳዮች ናቸው። ሦስቱን የሰውነት ባህርያት ተንተን አድርገን ሰው ከመሆን ጉዞ ጋር ያላቸውን ፍትጊያ፣ የአንዳቸው ወይም የሁሉ መጓደል ወደ ሰውነት ክብር ከፍ እንዳንል ጠፍረው የሚይዙባቸውን ወጥመዶች እንመለከታለን። ሦስቱ ባህርያት የየራሳቸውን ግዴታ በሰው ላይ ስለሚጭኑ እንዲያውም ሰው መሆን ራሱ እዳ ነው እንዴ? ብለን እንድንጠይቅ እንገደዳለን። በማን በያኝነት፣ በማን ፈራጅነት /በየትኛው ዳኛ፣ በምን ዓይነት ሚዛን ነው እዳው የሚለካው፣ ወይም ሽልማቱ የሚቸረው? ሰው የመሆን እዳዎች ከየት የመጡ ናቸው? የሚሉ ጥያቄዎች ለዛሬው ወጋችን መነሻ ሆነዋል።

ሰው ምክንያታዊ እንስሳ ነው

ስለ ሰው ልጅ ምርምር ያደረጉ የጥንት ግሪክ ፈላስፎች ከሚት እና ተረት ሰውን ለማላቀቅ ጥረት አድርገዋል። በዚህም ሰው ራሱ ያልመረመረውን እና በማስረጃ ያላረጋገጠውን ነገር እንደወረደ መቀበሉ ከሰዋዊ ተፈጥሮ ጋር የሚስማማ አይደለም የሚል አስተምህሮ ነበራቸው። የመጀመሪያው ድምዳሜም ሰው ምክንያታዊ እንስሳ ነው (Man is rational animal) የሚለው ነው። ይህ ድምዳሜ በቅርብ ዘመን እነ ኒቼ አና ኬጋርድ እስከሚቃወሙት ድረስ ከሞላ ጎደል በቀደምት ፈላስፎች ሲወራረስ የመጣ ነው። መነሻችንን ሶቅራጥስን እናድርግና የዚህን ድምዳሜ አንድምታ ሰው ከመሆን ጉዞ ማንጠሪያ ጋር እናገናዝበው።

ሶቅራጥስ ለምናደርጋት ነገር ሁሉ እውቀት ሊኖረን ይገባል ብሎ ይምናል። ምግባራችን እውቀት የጎደለው ከሆነ ወይም እውቀታችን በምግባር የማይገለጥ ከሆነ ከሰውነት ክብር ዝቅ ብለናል የሚል እሳቤ አለው። ለዘመናት የሚጠቀስለትም “ያልተመረመረ ሕይወት ከተኖረ አይቆጠርም” የሚለው አስተሳሰቡ ነው። ይህ ምርምርም ከሁሉም አስቀድሞ ራስን ወደ ማወቅ ይወስዳል። እንዲያውም ለሶቅራጥስ የምርምር ጥበብ እውነትን ከማወቅ ጋር ይተካከላል። እንደ ሶቅራጥስ በጋራ በሚደረግ ምርምር ወደ እውነት መቅረብ ይቻላል። የሶቅራጥስ ተማሪ የነበረው አፍላጦን ደግሞ ከሰው ልጅ ስሜታዊነቱ እና መንፈሳዊነቱ ባህርያት በአማካኝ ቦታ ላይ ምክንያታዊነቱን ያስቀምጣል። ሰው ምክንያታዊነቱን በምልዓትና በአግባቡ ሲጠቀም ወደ እውነት ይቀርባል። ጠቢብነትም የምክንያታዊ ፍጡር መዳረሻ ነው። የሰው ልጅ የሚያደርጋቸውን፣ የሚያያቸውን እና የሚሰማቸውን ነገሮች ይመረምር ዘንድ ተፈጥሮ የቸረችው ጸጋ ምክንያታዊነትን ነው የሚለን ደግሞ አሪስጣጣሊስ ነው። ሰው ምክንያታዊ የሚለውም የአሪስጣጣሊስ ድምዳሜ ነው።  

በዚህ ምርምር ገፋ ስናደርግ የምናገኘው ሮማዊውን ባለ-ብዙ ክህሎት እና የፖለቲካ ሰው የነበረውን ሲሴሮን (ችቸሮ) (ከ106 እስከ 43 ቅድመ ለደተ ክርስቶስ የነበረ) ነው። የጥንት የግሪክ ፈላስፎች ፍልስፍና ተቀብሮ እንዳይቀር ወደ ላቲኑ ዓለም በማስተዋወቅ ባለ ውለታ የሆነው ሲሴሮ ነው። ሮማውያን የሕግን እና የHumanities አስተምህሮ ለዓለም ሲያስተዋውቁ በፊታውራሪነት የረዳቸው ሲሴሮ ነው። በቅድመ ማዕከላዊ ዘመን በአውሮፓ ትምህርት ቤቶች ልጆች ከመጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ የሚያነቡት ሲሴሮን ነበር ይባልለታል። ለሲሴሮ “እያንዳንዱ ውህድ እና ግዙፍ የሆነ ነገር ወስጣዊ ስሪቱን አስተባብሮ የሚገዛ ንጥረ ነገር ሊኖረው ግድ ይላል። ይህ ንጥረ ነገር በሰው ልጆች ዘንድ ምክንያት ሲሆን በእንስሳት ስሪት ደግሞ ምክንያት መሰል ኃይል ነው። እያንዳንዱ ዓላማ እና ፍላጎት የሚመነጨውም ከዚህ ገዥ የተፈጥሮ መመሪያ ንጥር ነው” ይለናል። (“Every being which is not homogeneous and simple but complex and composite must have in it some organising principle. In man this organising principle is reason and in animals it is a power akin to reason, and from this arises all purpose and desire.”)

እንድግዲህ እንደነ ሲሴሮ ዓይነቶቹ ሁማኒስቶች የሰውን ልጅ ትናንትናውን የሚያስታውሰው፣ ዛሬውን የሚበይነው፣ ነገውን የሚተነብየው በዚህ ምክንያታዊ ተፈጥሮው እንደሆነ፣ ፍላጎቱ እና ምኞቹ፣ ዓላማውና ተግባሩ ከዚሁ ምክንያታዊነቱ እንደሚመነጭ ነግረውናል። የመካከለኛው ዘመን ሰዎችም የተቸገሩት ሰው በምክንያታዊነቱ እና በአማኝነቱ መካከል ያለውን ተቃርኖ ማስታረቅ ላይ ነበር። እንደነ ዴካርት ዓይነቶቹ የዘመናዊ ፍልስፍና መስራቾችም እንደ የነፍስ ኢመዋቲነት፣ የእግዚአብሔር ህልውና እና የነፍስና የስጋ አብሮነትን በምክንያት ማረጋገጥ ይቻላል ይሉናል። ይህም የሰው ልጅ የኅሊናውን የመመራመር አቅም በምልዓት ተጠቅሞ መረዳት (Understanding) ላይ መድረስ ይቻላል ይላሉ። የነፈላስፋው ዘርዓ ያዕቆብም በዚሁ የሰው ልጆች ለባዊ (Rational) ባህርይ ላይ የማያወላዳ አቋም አላቸው።

የሰው ልጅ ምክንያታዊ እንስሳ መሆኑ ምን ማኅበራዊ፣ ሞራላዊ እና ፖለቲካዊ አንድምታ አለው? በዘመነ አብርሆት (Enlightenment) የነበረው ጀርመናዊ ኢማኑኤል ካንት የሰው ልጆች የሞራሊቲ ምንጩ ምክንያታዊነትታቸው ነው ይላል። ለሁሉም ምክንያታዊ እንስሳት በእኩልነት እና በምልዓት የተሰጣቸው አንድ ጸጋ ቢኖር በጎ ኅሊና መልካም ፈቃድ (Good Will) ነው። ለሰው ልጆች በራሳቸው ስለራሳቸው ያስቡ እና ይወስኑ ዘንድ ምክንያታዊነት ተሰጥቷቸዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ለስዎች ሁሉ የማይጓደል ክብርን እና ነጻነትን ይሰጡ ዘንድ ይህ ምክንያታዊ የኅሊና ተዕዛዝ ያስገድዳቸዋል። ይህም ስነ ምግባራዊ ግዴታ ነው። ለሚያደርጓት፣ ለሚያስቧት፣ ለሚመኙት ሁሉ ሚዛናቸው ይኸው የምክንያታዊነት ባህርያቸው ነው። ይሕንን ሊቁ እጓለ ገብረ ዮሐንስ “ብርሃነ ኅሊና” ያሉት ነው።

ወደ ማኅበረ ፖለቲካዊ እንድምታ ስንገባ ከፊት ለፊታችን የምናገኘው የቅርብ ዘመናችንን አሜሪካዊ የፖለቲካ እና የሞራል ፍልስፍና መንገድ ቀያሹን ጆን ራውልን ነው። ለራውል ውሱን የሆነው ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ጸጋ (Scarce Resource) በሰው ልጆች ህብረት ግጭት መፍጠሩ አይቀርም። ይህንን ችግር ለመፍታት ደግሞ መለኮታዊ ወይም ከሰው የተለየ ስውር ኃይልን መጥራት ላይጠበቅባቸው ነው። የቀደመውን የማኅበራዊ ውል (Social Contract) መላምት በዘመናችን ልክ ለመስፋት ጥረት ያደረገው ራውል ሰዎች ተሰብስበው መክረው ወይም በየቤታቸው ወስነው ቢመጡ ሁሉም ምክንያታዊነታቸውን ከተጠቀሙ ለጀመዓው ወይም ለኅብረቱ ይበጃሉ፣ ተቋሞቻችን ቢመሩባቸው ይሻላል ያሏቸውን ሕግጋት ቢመርጡ ሁለት መሠረታዊ ሕጎች ከሁሉም የበለጠ ቅድምና ይኖራቸዋል። እነርሱም እንደኛው (The Equal Liberty Principle) ሁሉም ማንኛውም የሰውል ልጅ የማይገሰስ፣ በምንም ምድራዊ ኃይል ድርድር ውስጥ የማይገባባቸው የነጻነት መብቱ ሊከበርለት ይገባል የሚለው ነው። ይህ ሕግ ሁሉም ተቋሞቻችን ይህንን የተፈጥሮ ጸጋ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲያከብሩ የሚደነግግ ነው። ሁለተኛው ደግሞ (The Principle of Inequality) በማንኛውም የክፍፍል ጉዳዮች ላይ አድልዎ የማይቀር ከሆነ ስለ ሁሉም ጥቅም ሲባል፣ ሁሉም አምኖበት፣ በአንዱ መጠቀም የሌላው መብት ሳይሸራረፍ ሊሆን ይገባል የሚለው ነው።

የሰው ልጆች ከምክንያታዊ ተፈጥሯቸው ሲያፈነግጡ ስሜት ተጭኗቸዋል ማለት ነው። በዚህ ጊዜ ታዲያ ግለስቦችን ይበድላሉ፣ ተቋማትን ያወድማሉ፣ ማኅበራዊ መስተጋብርን ያውካሉ። ባጭሩ ከሰውነት ተራ፣ ከምክኛታዊነት ወጥተው ለሰውና ለሌላው ተፈጥሮ የማይመች፣ ፈጣሪ የማይፈቅደውን ሥራ ይሰራሉ። አንዱ ሰው የመሆን እዳም እንደዚህ ዓይነቶችን ያልተፈለጉ ውጤቶች እንዳይከሰቱ ምክንያታዊነትን በምልዓት መጠቀም ነው። ይህ የምክንያታዊነት እዳ የሚለካው ከራሱ የግል ሕይወት ባሻገር ማኅበራዊነቱን በሰለጠነ መንገድ በመምራቱም ጭምር ነው። በዚሁ ወደ ሁለተኛው ጉዳይ እንሻገር።  

ሰው ማኅበራዊ እንስሳ ነው

ሁለተኛው ስለ ሰው ልጆች የተሰጠው ብያኔ ደግሞ ሰው ማኅበራዊ እንስሳ ነው የሚለው ነው። ሰው ብቻውን ተወልዶ፣ ብቻውን ኑሮ፣ ብቻውን አስቦ፣ ሁሉንም ፍላጎቶቹን ብቻውን አሳክቶ ብቻውን ይሞት ዘንድ አይቻለውም። ራሱን የሚያገኘው በሌሎች መካከል እንደ መሆኑ፣ የሕይወቱ ትርጉም የሚበየነው በዚሁ ማኅበራዊነቱ ነው። የሰው ልጅ ማኅበራዊነቱ በርካታ ጸጋዎችን ሲያጎናጸፈው ፈተናዎችም አሉበት። ማኅበራዊ እንስሳ ነው የሚለው ብያኔ ምን እንደሆነ፣ በማኅበራዊነቱ የሚያገኛቸው ጥቅሞች እና ፈተናዎችን እንመልከት።

በርግጥ የሰው ልጅ ማኅበራዊ ነው ሲባል ትርጓሜው ምንድን ነው? ሌሎች እንስሳትም በኅብረት እና በአንድነት ይኖራሉ። አብሮ መኖር ነው ማኅበራዊ የሚያሰኘው? የሚል ጥያቄ ብዙ ጊዜ ይነሳል። ነገር ግን ማኅበራዊነት አብሮ አንድ ቦታ ላይ ተሰብስቦ በመኖር ብቻ የሚገለጽ አይደለም፤ ወይም አብሮ መኖር የማኅበራዊነት መገለጫ ላይሆንም ይችላል። የእንስሳትን ኅብረት ለጊዜው እንተወውና የሰው ልጆች ኅብረት ምን እንደሆነ በአጭሩ እንመልከት።

የሰው ልጅ ትናንትናውን፣ ዛሬውን እና ነገውን ለማሰናሰል በሚያደርገው ጥረት ወስጥ የጋራ ታሪክ እና የጋራ ማንነትን ይገነባል። ሰው ማንነቱን በሚገልጽበት ጊዜ የግል ወይም የተናጠል ታሪክ አይኖረውም። ግለሰቦች ሰለራሳቸው በሚያወሩበት ጊዜ አብላጫውን ገጽ የሚወሰደው የሌሎች ተሳትፎ ነው። የሰውነት ጉዳይ አብሮ የመኖር፣ የጋራ ወይም የሕብረት ሕይወት ነው ሲባልም ይህ አንዱ ባንዱ ላይ የሚያስቀምጠው አሻራ ነው። የሙታን መንፈስ እና ፍልስፍና፣ የሕያዋን አስተያየት እና ጫና ተባብሮ የዛሬውን ሰው የሕይወት መስመር፣ የኑሮ ዘዴውን፣ የፍላጎቱን እና የምኞቱን ባህርያት ይበይነዋል። ለዚህ ነው ሰው ማኅበራዊ እንስሳ ነው የሚባለው። ሰው መሆን በጋራ መብላት እና በጋራ መሥራት ብቻ ሳይሆን በጋራ የማሰብም ጉዳይ ነው። ሰው በጋራ አስቦ፣ በጋራ አልሞ የጋራ ግብ እና የጋራ ተቋማትን መስርቶ የሚኖር ፍጥረት ነው። ማኅበራዊነቱም የሚገለጸው በዚህ የመንፈስ ትስስር እንጅ በአካላዊ መቀራረብ አይደለም።

እንደ ጀርመናዊው ማርቲን ሃይዲገር Being and Time በተሰኘው ድንቅ መጽሐፉ ሰው (Da-sein) በዓለም ላይ ሲኖር ብቻውን ሊሆን አይችልም። መኖር የሚችለው ከሌሎች ጋር ዓለምን በመጋራት ነው። ህልውናን ከአብሮነት ውጭ መመልከት አይቻልም። ንጥል እኔነት የማይታሰብ ብቻ ሳይሆን ከመጀመሪያውም ሊኖር አይችልም። ከሌሎች ጋር መገናኘት ወደ ራስ ማንነት የመቅረብ ኑባሬያዊ ግዴታ ነው።  (“And, thus, an isolated I without the others is in the end just as far from being given initially” (p. 109) “[T]he characteristic of encountering the other is, after all, oriented toward one’s own Da-sein.” And “on the basis of this like with being-in the-world, the world is always already the one that I share with the others. The world of Da-sein is a with-world. Being-in is being-with others” (pp. 111-112).) ይህ ማኅበራዊነቱ የጋራ ባህል፣ ወግ እና ይትበሃል እንዲፈጥር ያስችለዋል። ይህንን የጋራ ባህል ወደ ጋራ አስተሳሰብ ይለውጠው እና በእውቀት ላይ የተመሰረተ፣ በሕግ እና በደንብ የሚመራ ኅብረት ወይም ጀምዓ ይኖረዋል።   

የሰው ልጅ ማኅበራዊነቱ ለምን ይረዳዋል? ሰው ማኅበራዊነትን በሁለት መልኩ ይቀላቀለዋል። ባንድ በኩል መነሻው ምን እንደሆነ በውል ባይታወቅም አንዴ የሰው ልጆች ኅብረት ተመስርቷል እና ለዘመናት ሲወራረሱ የመጡ የጋራ እሴቶችን ስለፈጠረ ማንም አሽቀንጥሮ ሊጥለው አይችልም። ሰው በሄደበት ሁሉ ይህንን ኅብረት ስለሚያገኘው ከዚህ ውጭ መሆን አይችልም። በሌላ በኩል ህጻናት ሲወለዱ ጀምሮ ለዚህ ኅብረት እንዲመጥኑ ተደርገው ስለሚሰሩ በትምህርትም በምክርም፣ በተግሳፅም በቅጣትም አማካኝነት ማኅበራዊነትን እንዲለማመዱ ይገደዳሉ። በዚህም ምንም እንኳ ሰው በተፈጥሮው ብቸኝነትን የሚፈቅድ እንስሳ ነው የሚል መከራከሪያ ቢኖርም ይህ የባህል እና የጋራ ቅቡልነት ጉዳይ ሰዎች በጋራ እንዲኖሩ ተፈርዶባቸዋል ወደሚል አዝማሚያ ይወስደናል። እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች ተፈጥሮን ሳይሆን ልምድህን ፍራ ሲሉ ሰዎች ከህጻንነታቸው ጀምረው ማኅበረሰቡ ማኅበራዊነትን ስለሚያለማምዳቸው በጊዜ ሂደት ወስጥ ማኅበራዊነትን ይቀላቀላሉ። ያልኖሩበትን ዘመን እና ያላዩትን የቀደመ ሕይወት በተረት፣ በታሪክ ይማሩታል።

በዚህ አማካኝነት የፋፋው ማኅበራዊነት የራሱ የሆነ ኢኮኖሚያዊ እና አስተሳሰባዊ ጸጋዎች አሉት።ይኸውም ሰው ሕይወቱን ከባዶ እንዳይጀምር፣ በህጻንነት ወይም በደካማነት ጊዜው ጉልበት የሚሆኑት ቁሳዊ እና መንፈሳዊ መደላድሎችን አበጅቶለታል። በመድኃኒት ቅመማ፣ በጥበብ፣ በቁስ፣ በአስተሳሰብ፣ በሕግ፣ በእምነት፣ በእውቀት፣ በራስን መከላከል፣ በምርት፣ በሐዘንና ደስታ መግለጫ ዘዴዎች ወዘተ ዓለም ተመቻችታ ትጠብቀዋለች። ለመጀመሪያ ተመልካች እና በላይ የላይ ዕይታ የሰው ልጆች ኅብረት በዘመን ሂደት ውስጥ ይህ ቀረሽ የማይባል ለኑሮ የሚሆን የተሟላ ስፍራን ያጎናጽፋል። ሌሎች አስበው በፈጠሩት ሜዳ ብዙም ማሰብ እና መመራመር ሳያስፈልግ መጋለብ የሚያስችል መንገድ ተነጥፎ ይቆይሃል።

ሰው ማኅበራዊ እንስሳ ነው ሲባል ሕይወቱ ከሰዎች ጋር የመወገን ሕይወት ነው ማለት ነው። ሕመማቸውን መታመም፣ ደስታቸውን መደሰት፣ ኑሯቸውን መጋራት ነው። የአፍሪካውያን ኡቡንቱ “እኔ የኖርሁት ሌሎች ስለኖሩ ነው ወይም እኔነት የሚኖረው በእኛነት ውስጥ ነው” (I am because we are) የሰው ልጆች ማኅበራዊነት ተጠቃሽ አስተሳሰብ ነው። እኛነት ከሌለ እኔነት የለም፣ እኛነት ደግሞ እኛ የአንድ አካባቢ ነዋሪዎች ወይም የዚህ ቤተሰብ አባላት፣ የዚህ ሃይማኖት ተከታዮች በሚል አጥር የተከለለ አይደለም። “እኛ”ነት የሰው ልጆች ወደሚል ትልቅ ቤተሰብ የሚወስድ ኅብረት ነው። ውግንናችን እኛን ከሚመስሉት ሁሉ ጋር ነው። ይህ መመሳሰል ደግሞ በቀለም ወይም በባህል፣ በቋንቋ ወይም በነገድ የተወሰነ አይደለም። ከላይ እንደገለጽነው ከተፈጥሮ ቅመም፣ ከተሰራንበት ውህድ፣… በሚመነጭ የፍላጎት እና የምኞት፣ የምርጫ እና የአዝማሚያ፣… መመሳሰል ላይ የተመሰረተ ነው። ሰው ከሁለት ነገሮች ይወለዳል። ከማይነቃነቅ የተፈጥሮ ጸጋው ጋር እና በትምህርት ከሚያገኛቸው የበጎነት እና የመጥፎነት መመዘኛዎች። የመጀመሪያው የሰው ልጆች ሁሉ የሚጋሩት ቀዳሚ ውግንናቸውን የሚበይነው ሲሆን ሁለተኛው አካባቢያዊ ውቅሮችን የሚያበጁበት ባህል ወለድ ዝንባሌ ነው። በሁለተኛው በኩል ሰዎች የተወሰነ ልዩነት ይኖራቸዋል፤ የመጀመሪያው ደግሞ ልዩነታቸውን ሽረው እንዲግባቡ የሚያስችላቸው ሰንሰለት ነው።

ሰው የመሆን እዳም የሚመነጨው ከዚህ ባህል ወለድ አካባቢያዊ ዝንባሌ፣ ቁንጽል ውግንና ወይም ተቃውሞ ነው። የመጀመሪያው ወደራስ ባህል በአጽንኦት ሲመለከቱ የሚገኝ ቀዳዳ ነው። አንድ ማኅበረሰብ ባህል እና አስተሳሰብ ፍጹም የተሟላ እና እፎይ የሚያስብል ሳይሆን ሲቀር የአንዳንዶች ነፍስ ትጨነቃለች። ይህ ኅብረተሰባዊነት እና የጋራ አስተሳሰብ አልዋጥ ሲል “አነዋሪዎች” (Critics) ይነሳሉ። የሰው ልጅ አሳቢ እንደመሆኑ በነባሩ የሕይወት መስመር እንደ ወራጅ ውሃ ዝም ብሎ ለመፍሰስ ይቸገራል። የነባሩ ይትበሃል የጎደለው ነገር እንዳለ መገንዘብ ይጀምራል። ያኔ ከባህል ጠበቃነት፣ ለእምነት ዘብ ከመቆም፣ ተረቱን እና ታሪኩን እንደወረደ ውጦ ከማስቀጠል ወጣ ብሎ መተቸት ይጀምራል። ፈተናው እንዴት ልተች የሚለው ላይ ነው። ከመሳደብ እና ከማንጓጠጥ በውይይት እና በምክንያት የተደገፈ ሙግት መሠረት በማድረግ ማስተካከያ መስጠት ያስፈልጋል። ሰው የመሆን እዳም የራስን ምክንያታዊ እና ለሁሉ የሚጠቅም አስተሳሰብ ከቁንጽል ውግንና እና ጥራዝ ነጠቅ ነቀፋ ነጻ በመሆን የሁሉም ሐሳብ እንዲሆን ማድረጉ ላይ ነው።  

ሁለተኛው ፈተና የኔ ወገን ብሎ በቅርቡ ባገኛቸው ሰዎች እና ሌሎች ተብለው በጠላትነት ወይም በወዳጅነት ከተፈረጁት ጋር በሚኖረው መስተጋብር በሚፈጠር የባህል እና የፍላጎት ተቃርኖ የሚመነጨው ነው። ይህንን ተቃርኖ ደምስሶ መልካም ተግባቦትን መጻፍ ሰው የመሆን እዳ ነው። ይህም ከአካባቢያዊነት ንፍቀ ክበብ ተሻግሮ አገራዊነት ወይም ዓለምአቀፋዊነትን ለማስፈን የሚደረግ ድምበር የለሽ ውግንናን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። ፖለቲካ የሚጸነሰውም ይህንን ድንበር ወለድ በሽታ ለማከም፣ ሁሉን አቀፍ ሕግጋትን በመደንገግ፣ ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት፣ የተራራቁ ስሜቶችን በማስታረቅ፣ የጠባብ ወገንተኝነትን እንከኖች በማረም በሰዎች መካከል መደላድል ለመፍጠር ሲታሰብ ነው። ሰው ፖለቲካዊ እንስሳ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው።

“ፖለቲካችን” የጎደለው ምንድነው?

ሦስተኛው የሰነት ብያኔ ሰው ፖለቲካዊ እንስሳ ነው የሚለው ነው። አሪስጣጣሊስ የሰውን ማኅበራዊነት በሚያትትበት ወቅት ይህ ኅብረት የተሻለ ህልውና እንዲኖረው ሲመክር የሰው ልጅ ፖለቲካዊ ባህርይውን በአግባቡ መጠቀም እንዳለበት አጽንኦት በመስጠት ነው። ለአሪስጣጣሊስ ፖለቲካ ከሥነ ምግባር ጋር በእጅጉ የተቆራኘ የተግባር ሳይንስ ነው። የሰው ልጆች እውቀታቸውን በተግባር የሚያሳዩበት የኑባሬ አጽቅ ፖለቲካዊነታቸው ነው። በጎነትን ከመጥፎነት የሚለዩበት እና የጋራ እና የግል ደስታቸውን ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ፖለቲካ አለ። ይህም ማኅበራዊ የሆነው ሰው በጎ ማኅበረሰባዊ ውቅርን በመፍጠር ጥሩ ኅብረተሰብ እንዲወለድ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ጎልቶ የሚወጣ ተፈጥሮው ነው። ኒኮምኪያን ኢቲክስ በተሰኘ መጽሐፉ የሞራሊቲ ዋና ዓላማ ሰዎችን ጥሩዎች ማድረግ ነው። ይህም ከመምህሩ ከአፍላጦን አስተምህሮ ጋር ይስማማል። ሰዎች በትምህርት ካልተገሩ ከአራዊት የከፉ አውሬዎች ይሆናሉ የሚለው ድምዳሜ ሰዎችን እንዴት ጥሩዎች ማድረግ ይቻላል የሚል ዓላማ አዘል ዘዴን ያዘለ ነው። ዘዴው በትምህርት እና መልካም ፖለቲካዊ አመራር ሲሆን ዓላማውም ደስተኛ ማኅበረሰብን፣ የተረጋጋ ኅብረትን (Just Social Order) በከተማችን፣ በአገራችን ወይም በPolis ውስጥ ማስፈን ነው። ይህም የግለሰቦችን ደስታ ሳይሆን የሰው ልጆችን ሁሉ ደስታ የመሻትን ጥያቄ መልስ መስጠት ነው። የራሳችን ዓለም ሳይሆን የሁላችን ዓለም ያማረች ትሆን ዘንድ (for “the supreme end of human beings”) የሚሰሩ መሪዎች ወይም ተቋማትን ማስፈን። ያኔ ማኅበራዊው ሰው ፖለቲካዊ ቅርጽ ይይዛል፣ ወይም ፖለቲካዊው ባህርይው ጎልቶ ይወጣል።

እንደ ጃንካር (1966፣ ገጽ 193) ትንታኔ ለአሪስጣጣሊስ ምክንያታዊ እንስሳ በእውቀት መኖር እንዳለበት ያምናል፣ ይህም ኑሮው የቀና ይሆን ዘንድ በእውቀት መኖር ተገቢ መሆኑን ከሚያምኑ ሌሎች ሰዎች ጋር ይኖራል፤ ይህንን በተግባር ለመግለጽ ደግሞ ተቋማዊ ስሪት ያስፈልጋል። ያ ተቋማዊ ስሪት ደግሞ መንገሥት ወይም ሃገረ መንግሥት (State) ነው። አገር የምትመራበት ውስብስብ መዋቅራዊ ኅሊና ደግሞ ፖለቲካ ይባላል። ፖለቲካ ሰፊ ሳይንስ ሲሆን በውስጡ ሞራሊቲንም ይይዛል።

ሀገረ መንግሥት የሰው ልጆች ማኅበራዊነት ከፍተኛ መገለጫ ነው። ይህ የሀገረ መንግሥት ምሥረታ ሂደት በርካታ ፈላስፎችን ያመራመረ እና መላምታቸውን ያስቀመጡበት ጉዳይ ነው። የሰው ልጆች ያለ ሕግና ሥርዓት ክፉዎች ስለሆኑ ለሌሎች ህልውና አደጋ ናቸው የሚሉ አሉ። ለምሳሌ ሆብስ መንግሥት በሌለበት የሰዎች ሕይወት በፍርሃት የተሞላ፣ የሰቆቃ ሕይወት ነው። ለዚህ መፍትሄ ይሆን ዘንድ ሰዎች መንግሥትን ማቋቋም አስፈለጋቸው፤ በዚያም ሀገረ መንግሥት ተመሰረተ ይለናል። ሆብስ እና መሰሎቹ የማኅበራዊ ውል አቀንቃኞች የሃገረ መንግሥት ምስረታ ዋና ዓላማው ሕገ-ወጦችን አደብ ማስገዛት እና የጋራ ዋስትናን ማረጋገጥ ነው ይላሉ። ካንት የሰው ልጆች ምክንያታዊነት እና የሌሎችን መብት ለማክበር ያላቸው የሞራል ግዴታ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ ሀገረ መንግሥት ይሆናል ይላል። ወይም የሃገረ መንግሥት ዋና ሥራ ሰዎች እርስ በርሳቸው ይከባበሩ ዘንድ ያላቸውን የተፈጥሮ ግዴታ በምልዓት ለማስፈጸም ሕጋዊ ጉልበት ያለው ተቋም መሆን ነው።

ለካንት የሀገረ መንግሥት ዋና ዋና ዓላማዎች የዜጎችን ነጻነት ማስከበር፣ ማንኛውንም የውጭ ወረራ መከላከል፣ እና አንድ ሀገር በምስለ ግለሰብ ቅርጽ ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚኖራትን ግንኙነት ማደረግ ነው። ይህም የካንት ዓለምአቀፍ ግንኙነት ፍልስፍናዊ መሠረት ነው። አገራት እንደ ግለሰቦች መብታቸውን አስከብረው መገናኘት ይችላሉ። የፖለቲካ ትልቁ ደረጃም ይኸው ዓለምአቀፋዊ ባህርይው ነው። ፖለቲካ ከአንድ አገር ንፍቀ ክበብ ወጥቶ አገራት ከአገራት ጋር፣ ያንድ አገር ዜጎች ከሌሎች አገራት ዜጎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ይወስናል።

ሰው የመሆን እዳ ሌላኛው ሰበዙ የሚመዘዘው ከዚህ ፖለቲካዊ ባህርይው ከሚመነጭ ግዴታው ነው። ሰው ከራሱ የግል ህልውና አልፎ ማኅበራዊ ግዴታን ይላበሳል፣ ከዚህ ተሻግሮ ደግሞ የዜግነት ጉዳይ ይሸከማል፤ ይህ የዜግነት ግዴታ ደግሞ ዓለምአቀፋዊ ክንፍ ይኖረዋል። ፖለቲካችን የጎደለው የፖለቲከኞቻችን ለሕግ፣ ለምክንያት እና ለሰው ልጆች ሁሉ አለመወገናቸው ነው። ይህ ውስብስብ አካባቢያዊ፣ አገራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ተሳትፎው እና ውግንናው የወለዳቸው ለሕግ የበላይነት፣ ለሰዎች እኩልነት፣ ለፍትሕ መረጋገጥ፣ ለዘላቂ ሰላም፣ ለሰው ልጆች ሁሉ ደህንነት ዘብ የመቆም ሰው የመሆን ግዴታ ደግሞ ትልቅ አስተውሎትን፣ ክህሎትን እና ማሰላሰልን የሚጠይቅ፣ (የልዕለ ተፈጥሮ ኃይል እርዳታ የሚያስፈልገው) የህልቆ መሳፍርት እዳዎች ጥርቅም ነው።

ሰው የመሆን እዳው የሚጎላው ደግሞ ሰው የማሰብ ክህሎቱን ተጥቅሞ በረቀቀ ጥበብ ሕግን ሲያጣምም፤ ለግል ፍላጎቱ በስሜት ተመርቶ፣ ያለውን ኃይል እና ሥልጣን ተጠቅሞ ሌሎቹን ሲጨቁን፣ ራሱን ሲጠቅም፤ ሐጋራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ሰላምን የሚያውክ፣ የሰው ልጆችን ደኅንነት አደጋ የሚጠል ነገር ሲከውን ነው። በምድራዊ ውግዘት ነውር እና ወንጀል ተብሎ ማኅበራዊ መገለል እና ቅጣት ሲጣልበት፤ በሰማያዊ ሚዛን ኃጢአት ተብሎ መለኮታዊ ቅጣት ሲዛትበት ይኖራል። ሰው የመሆን እዳ መለኪያ ሚዛኑ ማኅበራዊ ቅቡልነት፣ የሕግ መከበር ወይም ሃይማኖታዊ ጽድቅ፣ ፍልስፍናዊ እውነት እና ምክንያታዊነት፣ ወይም ሳይንሳዊ ቀመር ሊሆን ይችላል። የሁሉም ማጠንጠኛው ግን ለሰው ልጆች ሁሉ ፍላጎት መሳካት፣ ሰው የመሆን ክህሎቱን አሟጦ ለመጠቀም ባሳየው ቁርጠኝነት ላይ ይመሠረታል።  

መውጫ

ከላይ ዕንዳየነው ሰው የመሆንን እዳ ከምክንያታዊነት፣ ከማኅበራዊነት እና ከፖለቲካዊ ግዴታዎች አንጻር ተመልክተናል። ይህ ጽሑፍ እነዚህን ሰፋፊ ሰው የመሆን ጉዳዮች እና በአንጻራቸው የተዘረጉትን እዳዎች በወፍ በረር የተመለከተ ነው። እያንዳንዳቸው ጉዳዮች ሰፊ ሐተታና ጥናት የሚያስፈልጋቸው ናቸው። በዋናነት ሰው ከሰዎች ጋር በሚያደርገው መስተጋብር እና የስሜት መጋራቶች አማካኝነት የሚመነጩ ሰው የመሆን ልህቀቶች እና ከሰውነት ተራ የመውረድ ተዛንፎዎችን ለማየት ሞክረናል። ሰው የመሆን ጉዞ ፍለጋው አያልቅም። ሰውነት በብዙ ትብታብ ታስሮ የሚባትል ብኩን ፍጥረት ይመስላል። ከውስጥ በሚመጡ የማይጠረቁ ፍላጎቶች እና ከውጭ በሚመጡ አብለጭላጭ እና አበሳጭ ሁነቶች የሚዳክረውን ሰው እንዴት ነጻ ማውጣት ይቻላል? ቀጣዩ ፍለጋችን ይህ ይሆናል። እስከዚያው ለዘመናችን ሰው ትልቁ ፈተና፣ የህልቅናውን ኩራዝ ሊያጠፋ የተቃጣ ከሚመስለው ወረርሽኝ ራሳችንን እና ሌሎቹን እንጠብቅ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top