ጥበብ በታሪክ ገፅ

፪ ተጻራሪ የባህል ገጽታዎች፤ በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ወቅት

የአምስት ዓመቱ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ በአገራችን ከተከሰቱ ታላላቅ ታሪኮች መካከል አንዱ ነው። ይህ ወቅት አዳዲስ አመለካከቶች፣ ባህሎችና እምነቶች የተንጸባረቁበት ነው። አገሪቱ የነበረችበትን የእድገት ኋላ ቀርነት ፍንትው አድረጎ ያሳየ ነው። ፋሽስት ጣሊያን በዓድዋ የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል ለአርባ ዓመት ያህል የተዘጋጀበትና በዘመናዊ የጦር መሳሪያ እራሱን አስታጥቆ፣ የአገሪቷን ደካማ ጎን በሚገባ ለይቶ ሲመጣ ኢትዮጵያ በተቃራኒው በሁለንተናዊ መስክ በዓድዋ ወቅት ከነበረችበት ሁኔታ ምንም ለውጥ ሳታመጣ የጠበቀችበት ነው።


የጣሊያን ሰራዊት

ይህ ወቅት በርካታ ኢትዮጵያዊያን የነበራቸው ጽኑ የአገር ፍቅር ስሜት የተፈተነበት ነው። በመሆኑም የአምስት ዓመቱ የፋሽስት ወረራ ከታሪክ ጥናት መስክ በተጨማሪ ከባህል፣ ከኢኮኖሚ፣ ከስነ-ልቡና እና መሰል የጥናት መስኮች አንጻር በጥልቀት መመርመር የሚገባው ይመስለኛል። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በአምስት ዓመቱ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ወቅት የነበሩትን ሁለት ተጻራሪ የአስተሳሰብ ባህሎች በጥቂቱ ማውሳት ነው።

በወቅቱ የተስተዋሉ የአስተሳሰብ ባህል ገጽታዎች ሁለት ናቸው። አንደኛው፣ የአርበኝነት ባህል ነው። ሁለተኛው ደግሞ የባንዳነት ባህል ነው። ሁለቱ ተቃራኒ ባህሎች የወቅቱን የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳዩ ናቸው። በታሪክ ሚዛን ላይም በሁለት ጫፍ  የሚቀመጡ ሀቆች ናቸው። ስለ አምስት ዓመቱ የአርበኝነት ዘመን ስናወሳ ሁለቱን ተቃራኒ ጽንፎች ማውሳት አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም መልካሙም ሆነ እኩዩ የእኛ ታሪክ አካል ናቸውና።   

አርበኝነት

በ1928 ዓ.ም. ፋሽስት ጣሊያን አገራችንን በወረረ ወቅት በርካታ ኢትዮጵያውያን ለሀገር ክብር ሲሉ በተለያየ አውደ ውጊያዎች ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል። ሀገር በጠላት በተወረረ ወቅት ሕዝቡ ቀፎው እንደተነካ ንብ ከየአቅጣጫው በመትመም ጠላትን ድባቅ ለመምታት ዘምቷል።


አጼ ኃይለሥላሴ በማይጨው ጦርነት ላይ

በወቅቱ የነበረው ትውልድ ይህን የአርበኝነት ባህል ከአባቶቹ የዓድዋ ድል የተቀበለውና የወረሰው ነው። እስከ ከ1928ቱ የጠላት ወረራ ወቅት ድረስ ጎልቶ ይንጸባረቅ የነበረው የአርበኝነት አስተሳሰብ ማንም ወራሪ ኃይል ቢመጣ እኛ ኢትዮጵያውያንን ማሸነፍ አይችልም። የሚለው ነበር። ይህ አስተሳሰብ የመነጨው ከታሪካችን ነው። ከወረራው በፊት የነበረው ታሪካችን የድል እንጂ የሽንፈት አይደለም።  

በዓለም ላይ የተነሱ ታላላቅ መንግሥታት ኢትዮጵያን በቅኝ ለመግዛት ብዙ ሙከራዎች አድርገዋል። ኢትዮጵያን የመውረር ሙከራዎች ከክርስቶስ ልደት በፊት በ336 በግሪክ ላይ ነግሶ ከነበረው ታላቁ እስክንድር ጀምሮ እስከ ዓድዋ ጦርነት ድረስ በርካታ ናቸው። ኢትዮጵያውያን ግን አገራቸውን በሌላ ባዕድ ሳያሲዙ ባላቸው ኃይል ሁሉ ጠላትን ሲከላከሉና የአገራቸውን ሉዓላዊነት ሲያስከብሩ ቆይተዋል። ይህ መሆኑ የአርበኝነት ባህል በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ስር እንዲሰድ ምክንያት ሆኗል።

በ1928ቱ ወረራ ወቅትም ይህ የአርበኝነት የአስተሳሰብ ባህል ውርስ በትውልዱ ደም ውስጥ ነበር። የጣሊያን ፋሽስት ጦር አገሪቷን ለአምስት ዓመት በወረረበት ወቅት በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የአርበኝነት እንቅስቃሴ በመካሄዱ ወራሪው ኃይል የተረጋጋ መንግሥት እንዳይመሰርት እንቅፋት ሆነውበታል። አርበኞቹ የጠላትን ዕለታዊ እንቅስቃሴ በማወክ፣ ሕዝቡ ተስፋ እንዳይቆርጥና አገር ለጠላት እንዳትገዛ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል።

በወቅቱ የነበረው የፋሽስት ወረራ ከዓድዋው ዘመን የተለየ የሚያደርገው ከጠላት በኩል በጦር ኃይል፣ በፕሮፓጋንዳ፣ በስነልቡና፣ በወታደራዊ ዝግጅት ጠላት ሙሉ ለሙሉ የበላይነት የነበረው መሆኑ ነው። በተቃራኒው ከኢትዮጵያ አንጻር ደግሞ የአገሪቷ ማዕከላዊ መንግሥት ሙሉለሙሉ በፈረሰበት፣ በዘመናዊና በበቂ የጦር መሳሪያ ያልተደራጀ ሠራዊት የነበረበት፣ ንጉሠነገሥቱ የተሰደዱበት፣ በመንግሥት ባለሥልጣናት፣ በባላባቶችና በታላላቅ ግለሰቦች አልፎ አልፎም በሕዝቡ መሃል የነበረው የአንድነት መንፈስ የላላበት ወቅት መሆኑ ነው።


ራስ ደስታ ዳምጠው

ከሁሉም በላይ “እኛ ኢትዮጵያውያንን ማንም አያሸንፈንም የሚለው ለዘመናት ስር የሰደደ አስተሳሰብና በራስ የመተማመን መንፈሳዊ ጸጋ ፈተና ውስጥ የወደቀበት መሆኑ ነው። በዚህ ከባድና ተስፋ አስቆራጭ ወቅት ነበር በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ለሀገር ክብር መስዋዕት ለመክፈል የአርበኝነት እንቅስቃሴ የተደረገው። የአርበኝነቱ እንቅስቃሴ ይደረግ የነበረውም ፍቃደኛ የሆኑ ግለሰቦች በግል የነበራቸውን ኋላ ቀር ጠመንጃ፣ ሽጉጥ፣ ጦር፣ ጎራዴና ጩቤ በመያዝ ጫካ በመግባት ነበር።

አርበኞች በሀገር ፍቅር ጠላትን በሚፋለሙበት ወቅቱ ማዕከላዊ መንግሥት በመፍረሱ አይዞህ ባይ የለም። ሿሚና ሸላሚ የለም። የምግብና የመሳሪያ አቅራቢ የለም። ለታመመ መድኃኒት የለም። የቆሰለን አካሚ የለም። የጠላት ጦር በአጭር ጊዜ ተደምስሶ ሀገር ነጻ ትውጣ ወይም ኃይሉን እያጠናከረ ለረጅም ዘመን ይቆይ መገመት አይቻልም። ይህን ስናስብ አንድም የአርበኞቹን ልዩ ጽናት ከልባችን እናደንቃለን፤ አንድም የሁኔታው አሳዛኝነት ልባችንን ያደማዋል።     

በዚህ ጨለማ ወቅት የአርበኛው ብቸኛው ተስፋና ምኞት ለሀገሩ ክብር መሞትና በታሪክ መወሳት ነው። ይህ ብቸኛ ተስፋና ምኞት በአርበኛው ልብ ውስጥ እንዲሰርጽ ያደረገው የአርበኝነት አስተሳሰብ ባህል ነው። በባህላችን አርበኝነት ከክብር በላይ ክብር ነው። አርበኝነት ከግለሰብ ገጸ-ሰብዕና በላይ የዘር ማንዘር ሰብዕና ቀራጭ ነው። የኩራት ምንጭ ነው።

ይህ የአርበኝነት አስተሳሰብ ባህል የተለያዩ ግለሰቦችን ዱር ቤቴ ብለው ጫካ እንዲገቡ አስገድዷቸዋል። ለዚህም ነው በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች በርካታ አርበኞች ለአገር ክብር የተዋደቁት። ከእነዚህ ጀግኖች አርበኞች መካከል ጥቂቱን በክብር ስማቸውን እንዘክራለን። በዚህ አጭር ጽሑፍ ከምንዘክራቸው አርበኞች መካከል አንዳንዶቹ እድለኛ ሆነው ስማቸው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጎልቶ ይወሳል። አንዳንዶቹ ግን የፈጸሙት የአርበኝነት ተጋድሎ አስታዋሽ አጥቶ ከኢትዮጵያ የታሪክ መድረክ ተገፍትረዋል። በታሪክ የመወሳት ብቸኛ ምኞታቸው ቀቢጸ ተስፋ ሆኗል።

ለዚህም ምክንያቶቹ ብዙ ቢሆኑም ከወረራው በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ የተከተሉት አርበኛውን የማግለል አካሄድ ነበር። በመላው ኢትዮጵያ የነበረው የአርበኝነት ታሪክ በተደራጀ መልኩ ተጠንቶ አለመሰነዱ ነው። ለአገር አንድነት የተዋደቀውን አርበኛ በጠላትነት የፈረጀ፣ በተቃራኒው ደግሞ ከወራሪው የጣሊያን መንግሥት ጋር እንዲሁም በሱማሊያ ወረራ ወቅት ከወራሪው የዚያድባሬ መንግሥት ጎን ተሰልፎ እናት ሀገሩን ያደማ ግለሰብ ጀግና ተብሎ የመታሰቢያ አደባባዮችንና ሀውልቶችን የሚገነባ የመንግሥት ስርዓት መኖሩ ነው።  

በዚህ አጭር ጽሑፍ ለሀገር ክብር ሕይወታቸውን ከሰጡ ጀግና አርበኞች መካከል ጥቂቱን በክብር እንዘክር…

የቆራሄው ጀግና ደጃዝማች አፈወርቅ ወልደሰማዕት በኦጋዴን።  የጦር ገበሬ በሚል የሙገሳ ቃል የሚታወቀው ልጅ ባሻ ሚኮ፣ ፊታውራሪ አበበ ሽንቁጥ፣ ልጅ ኃይለማርያም ማሞ በሸዋ። ደጃዝማች ፍቅረ ማርያም አባተጫን በአርሲ። አቡነ ጴጥሮስ በአዲስ አበባ።


የኢትዮጵያ ሠራዊት በጣሊያን ወረራ ወቅት

ደጃዝማች ኃይሉ ባህታ፣ ግራዝማች በለጠ ኃይሉ፣ ልጅ አሻግሬ ተሰማ በባሌ። ራስ ደስታ ዳምጠው በቡታጅራ። ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ እና ሽመልስ ሀብቴ በጉጆቴ። ፊታውራሪ ሽፈራው በፀለምት። ቀኛዝማች ሰለባ ወልደ ሥላሴ በክብረመንግሥት።

ኮረኔል ኃይለአብ ቀለታ በወለጋ። ደጃዝማች ኃይሉ ከበደ በላስታ። ደጃዝማች ዘውዱ አስፋው በበጌምድር። ደጃዝማች በየነ መርዕድ በሲዳማ። ራስ ሙሉጌታ ይገዙ በአፋር። ፊታውራሪ ዓለማየሁ ጎሹ በጅግጅጋ…  

ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ በርካታ ኤርትራዊያን ኢጣሊያን እየከዱ ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸው ጋር ከፍተኛ ተጋድሎ ፈጽመዋል። ከእነዚህ ኤርትራዊያን መካከል ደጃዝማች አንዶም ተስፋ ጽዮን ተጠቃሽ ናቸው። ደጃዝማች አንዶም አንድ ሺኽ የሚሆኑ ኤርትራዊያን ወታደሮችን ይዘው ጣሊያንን በመክዳት ለኢትዮጵያ ነጻነት ሲዋደቁ ቆይተው በአርማጭሆ በተደረገ ውግያ ሞተዋል። እነዚህ አርበኞች በሕይወት ቆይተው ጠላት መሸነፉን፣ ሀገርም ነጻ መውጣቷን ማየት ሳይችሉ በክብር ተሰውተዋል።  

አርበኞቹ አገሪቷ በጠላት ቁጥጥር ስር ከዋለችበት ቀን ጀምሮ እስከ ነጻነት ባሉት አምስት ዓመታት ጫካ በመግባት ከጠላት ጦር ጋር ከደፈጣ እስከ መደበኛ ውጊያ በተለየዩ ወቅቶች አድርገዋል። ጠላት የተረጋጋ መንግሥት እንዳይመሰርት ቁም ስቅሉን ያሳዩ ጀግና አርበኞች በሁሉም አካባቢዎች ነበሩ። እነዚህ አርበኞች እድለኛ ሆነው ጠላት ተሸንፎ ሀገር ነጻነቷን ስትቀናጅ አይተዋል።

ከእነዚህ በርካታ የአገራችን ጀግና አርበኞች መካከል…

ደጃዝማች በላይ ዘለቀ፣ ደጃዝማች መንገሻ ጀንበሬ በጎጃም። ራስ አበበ አረጋይ፣ ባሻ ወልደ ኪሮስ ገብረ ወልድ፣ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ በሶዶ። ፊታውራሪ ገብረስላሴ ጫኬ፣ ፊታውራሪ ተገኔ ተሰማ፣ ካፒቴን አጥሬ ተሰማ፣ ፊታውራሪ መኩሪያ ተሰማ በባሌ። ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ በጉራጌ፣ ብላታ ታከለ ወልደሐዋርያት በሊሙ። ራስ አሞራው ውብነህ፣ ደጃዝማች ዘውዴ ጥላሁን፣ ፊታውራሪ ወንድምነህ በበጌምድር ወዘተ. ጥቂቶቹ ናቸው።

ወ/ሮ ሸዋረገድ ገድሌ፣ እመቤት ከበደች ስዩም በሸዋ። ወ/ሮ ዘውዲቱ ግዛው በበጌምድር። ወ/ሮ ወደርየለሽ ይፍሩ በባሌ ስማቸው ከሚታወቁ በርካታ ጀግና የሴት አርበኞች መካከል ናቸው። በወቅቱ ስማቸው ማን እንደሆነ በታሪክ ማስረጃዎች የማይታወቁ ነገር ግን አስደናቂ ጀብድ የፈጸሙ ሴት አርበኞችም ነበሩ። ለዚህ ማሳያ ጳውሎስ ኞኞ “የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት በሚለው መጽሐፉ፣ በዶሎ ጦርነት ላይ አንዲት ሴት የፈጸመችውን ጅብድ ከዊልያም ማኪን መጽሐፍ ያገኘውን ማስታወሻ አስፍሯል። ማስታወሻውም እንዲህ የሚል ነው።

“…በዶሎ አካባቢ አበሾች በየተራራው ላይ መሽገው የኢጣሊያንን መምጣት ይጠባበቃሉ። የዚያ ቦታ ጦር መሪ የሆኑት የደጃዝማች ሀብተሚካኤል ሚስት ከተራራው ላይ ሆና ስትመለከት የኢጣሊያ ወታደር ሲመጣ ዐየች። የኢጣሊያ ጦር ገፍቶ መምጣት እንዳየች፣ የኢጣሊያን ጦር መምጣት ላይ ነውና ይመታ ብላ ለባሏ ነገረች። ባልየው ግን ተጨነቀ። የተጨነቀበትም ዋናው ምክንያት ጥሩ የመከላከያ ቦታ ስለሌላቸው ከኢጣሊያ ወጥመድ እንዳይገቡ መጋጠሙን ፈሩ።

ከዚህ በኋላ ሚስቲቱ ከባሏ ተለይታ ወደ ሌላ ስፍራ ሄደች። ከዚያም ልብስዋን ለዋውጣ እንደወንድ ለበሰች። ፍቃደኛ የሆኑ 150 ሰዎች አዘጋጅታ ከጨረሰች በኋላ ከበቅሎዋ ላይ ወጥታ ወደፊት ገሰገሰች። ሰዎችዋም የጦርነት ጩኀት እየጮሁ ወደሚመጣው የኢጣልያ ጦር እየሮጡ ሄዱ። የኢጣሊያ ወታደሮችም በቅሎ በምትጋልብ ሴት የሚመራ ጦር እንደመጣባቸው ባዩ ጊዜ ቦታ ቦታቸውን ይዘው ውጊያ ገጠሙ።

የአበሻው ጦር አዛዥ የሚስታቸውን ከጠላት ጋር መዋጋት እንደሰሙ ጦራቸውን ይዘው ለእርዳታ ሄዱ። ደጃዝማች ከውጊያው ቦታ ሲደርሱ ውጊያው አልቆ ረዳት ከማያስፈልግበት ደረጃ ላይ ነበር። ብዙ ኢጣሊያኖች ተገድለዋል። ብዙዎቹ ቆስለዋል። ያቺ አገሯን የምትወድ ተዋጊ ሴት ከጠላቷ ብዙ ጠመንጃ እና ጥይት ማርካ ተመለሰች።…በማለት ጽፏል።

የታሪክ ምሁራን የእኚህን ጀግና ሴት ሙሉ ስምና የነበራቸውን የአርበኝነት ታሪክ ወደፊት በጥናት እንደሚያሳውቁን ተስፋ አደርጋለሁ።   

እነዚህ አርበኞች ለመንግሥት ባላቸው ታማኝነት ወይም ለራሳቸው ዝና አልነበረም ለአምስት ዓመት መስዋዕትነት የከፈሉት። ለአገር ክብር ባላቸው ቀናኢነት እንጂ። ይህ ጠንካራ መንፈስ ምንጩ ከአባት፣ አያቶቻቸው የወረሱት የአርበኝነት ባህል ነው።

ባንዳነት

የአምስት ዓመቱ የጣሊያን ወረራ ወቅት በአገራችን እምብዛም ያልተለመዱ ባህሎች በስፋት የታዩበት ነው። ከእነዚህ ባህሎች መካከል አንዱ ባንዳነት ነው። ይህ የባንዳነት አመለካከት በወረራው ወቅት በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በስፋት የነበረ ነው። በወቅቱ የነበረው የባንዳነት ባህርይ፣ አይነትና መነሻ ምክንያቱ የተለያየ ነው። አንዳንዱ “ሀገሪቷ በእድገት ኋላ ቀር በመሆኗ በጣሊያን መገዛት ይኖርባታል። ለኢትዮጵያ እድገትን ያመጣል። የሚል አመለካከት አላቸው። በዚህ አመለካከት በባንዳነት ከሚታወቁ ሰዎች መካከል ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረየሱስ ይጠቀሳሉ።

ለአንዳንዱ ደግሞ ለፋሽስት ጣሊያን ማደር ለተሻለ ስልጣንና ሀብት ማግኛ አቋሯጭ መንገድ ነው። በዚህ አመለካከት በባንዳነት ከሚታወቁ ሰዎች መካከል ደጃዝማች ኃይለሥላሴ ጉግሳ ይጠቀሳሉ። ለአንዳንዱ ደግሞ ከንጉሱ ጋር ባላቸው ቁርሾ ለጣሊያን ያደሩ ናቸው። በቁርሾ ሳቢያ ለጣሊያን ከወገኑት መካከል ራስ ኃይሉ ይጠቀሳሉ። ለአንዳንዶቹ ደግሞ የኃይማኖትና የዘር ጭቆና ተደርጎብሃል”  በማለት ጣሊያን የሚያካሂደውን የከፋፍለህ ግዛ ፕሮፓጋንዳ አምነው በባንድነት የተሰለፉ በርካታ ሰዎች ነበሩ።

የአምስት ዓመቱ የአርበኝነት ዘመንን በጥልቀት ብንመለከት፣ አርበኞቹ በርካታ ውጊያዎችን ያደረጉት ከጣሊያን ወራሪ ኃይል ጋር ሳይሆን ጣሊያን እያስታጠቀ ከሚልካቸው ባንዳዎች ጋር ነው።  እነዚህ የባንዳ ኃይሎች አርበኞችን በቀጥታ የፊት ለፊት ውጊያ ከመግጠም ጀምሮ ትልልቅ የኢትዮጵያ አርበኞችን በመያዝ ለጠላት ጣሊያን አሳልፈው ሰጥተዋል። በበርካታ ጀግኖች አርበኞች ላይም የሞት ፍርድ አስፈርደዋል።

ከእነዚህ መካከል ራስ ደስታ ዳምጠው በጉጆቴ ጦርነት በጣሊያን ጦር ከመማረክ ለጥቂት ባመለጡበት ወቅት እሳቸውን እግር በእግር ተከታትሎ የያዛቸው የባንዳ ጦር ነው። የባንዳ ጦር መሪውም ደጃዝማች ተክሉ ነው። ይህንና መሰል መራር እውነቶች እጅግ በጣም ብዙ ናቸው። ይህን አሳዛኝ ሀቅ ለመረዳት በወቅቱ በነበረው የአርበኝነት ታሪክ ላይ የተጻፉ መጽሐፍትን ማንበብ በቂ ነው።         

የሸዋ አርበኞችን ከጣሊያን ሠራዊት ይልቅ ይፈትኗቸው የነበሩ ባንዳዎች፡- ደጃዝማች መሸሻ ባንቺ፣ ደጃዝማች መሸሻ ተወንድበላይ፣ ባላምባራስ አያሌው ጓንጉል ናቸው። የባሌ አርበኞችን ከጣሊያን መድፍ በላይ የጎዷቸው ባንዳዎች፡- ሻምበል ተፈራ በላቸው፣ ታምራት ፋሪስ፣ ተፈሪ ገብረመድህን፣ ታደሰ አበራ የተባሉ ባንዳዎች ናቸው። የልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴንና የሆለታ መኮንኖችን ጦር በነቀምትና በጎሬ ማለፊያ መንገድ እየዘጋ ይዋጋቸው የነበረው የጣሊያን ሠራዊት አልነበረም። የጣሊያንን መንግሥት ተቀብያለሁና ወደ ሀገሬ እንዳትገቡ። ይሉ የነበሩት የአካባቢው ባላባት የነበሩት ደጃዝማች ኃብተማርያም፣ ቢተወደድ ወልደ ጻድቅ፣ ደጃዝማች ዮሐንስ ጆቴ… እንጂ።

ይህ ወቅት ይበልጥ የሚገርመው አባትና ልጅ በሁለት የአመለካከት ወገን ውስጥ የነበሩበት አጋጣሚም የፈጠረ መሆኑ ነው። አባት ባንዳ ልጅ አርበኛ የሆነበት። ደጃዝማች አባውቃው በማይጨው በኩል ከአጼ ኃይለሥላሴ ጋር አብሮ ዘምቶ እዚያው ከድቶ ወደ ጣሊያኖች ይገባል። ልጁ ግን በጅማ ለነበረው የአርበኞች ጦር መሪ ሆኖ፣ ቀኛዝማች ተብሎ ከእነ ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ጋር በመሆን ከጣሊያን ጋር የተዋጋበትን ታሪክ እራሳቸው ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ በመጽሐፋቸው የነገሩን ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው።

በመሆኑም የአምስት ዓመቱን የጣሊያን ወረራ፣ የአርበኝነት ዘመንን እንዲሁም የአርበኞችን ቀን ስንዘክር ለሀገር ክብር ዘብ የቆሙ ጀግና አርበኞችን በአንድ ወገን፤ ሀገርን የከዱ ባንዳዎችን ደግሞ በሌላ ወገን መዘከር ይኖርብናል። ትውልድ ከሁለቱም ተጻራሪ የታሪክ ገጽታዎች ትምህርት ይወስድ ዘንድ አስፈላጊም፣ ግዴታም ነውና።   

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top