ፍልስፍና

“የኢትዮጵያ ፍልስፍና”ን እንደ አዲስ ማዋቀር የክላውድ ሰምነር “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” ብያኔ

አኅጽሮተ ጥናት

ፕሮፌሰር ክላውድ ሰምነር ለኢትዮጵያ ስነጽሑፍ ያበረከተው ትልቅ አስተዋጽኦ “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” የሚባል አዲስ አካዳሚያዊ ተዋስዖ ማስተዋወቁ ነው። ሰምነር “የኢትዮጵያ ፍልስፍና”ን ያዋቀረው በመካከለኛው ዘመን ወደ ግዕዝ የተተረጎሙ የውጭ ሀገር የፍልስፍና መጻሕፍትንና ከሀገር ውስጥ ደግሞ የዘርዓያዕቆብንና የወልደ ሕይወትን ሐተታዎች በማካተት ነው። ሆኖም ግን፣ ይሄ የሰምነር “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” አቀራረብ ለሁለት “መሰረታዊ የኢትዮጵያ ፍልስፍና ጥያቄዎች” መልስ መስጠት የማይችል ነው፤


ክላውድ ሰምነር
 1. “በኢትዮጵያ ፍልስፍና” ውስጥ ዋነኛ ጭብጥ ሆኖ የተነሳው ርዕሰ ጉዳይ ምንድን ነው?
 2. በኢትዮጵያ የባህልና የምሁራን ታሪክ ውስጥ የዘርዓያዕቆብ ትክክለኛ ስፍራ የት ነው? ለሚሉት ጥያቄዎች የሰምነር አቀራረብ መልስ መስጠት አይችልም።

ከዚህም በተጨማሪ፣ ሰምነር የውጭ የትርጉም ሥራዎችን “የኢትዮጵያ” ያደረገበት መንገድና የሰጠው መልስም አጥጋቢ አይደለም። በነዚህ ምክንያቶች “የኢትዮጵያን ፍልስፍና” በአዲስ አቀራረብ እንደገና ማዋቀር ያስፈልጋል።

ይሄንን ጽሑፍ በሁለት ክፍል የማቀርበው ስሆን፣ በዚህ የክፍል- ፩ ጽሑፌ ሰምነር “የኢትዮጵያን ፍልስፍና” ያዋቀረበትን መንገድ እንመለከታለን። በክፍል- ፪ ደግሞ የሰምነር “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” አቀራረብ ያሉበትን ችግሮች በመሔስ፣ በሌላ አዲስ አቀራረብ የኢትዮጵያን ፍልስፍና እንዴት ማዋቀር እንደሚቻል እንመለከታለን።

 1. የክላውድ ሰምነር “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” ብያኔ

ከ1966 ዓ.ም. በፊት “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” የሚባል ፅንሰ ሐሳብ ኢትዮጵያ ውስጥ አልነበረም። ምንም እንኳ ከ1966 በፊት ዘርዓያዕቆብ ላይ የተለያዩ ሥራዎች የተሰሩ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የፍልስፍና ትምህርት ክፍል የተከፈተ ቢሆንም፣ “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” የሚለው ሐሳብ ግን ማንም ኢትዮጵያዊ ምሁር ሊከሰትለት አልቻለም። ሐሳቡን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ምሁራን አደባባይ ይዞት የመጣው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር የነበረው ካናዳዊው ፕ/ር ክላውድ ሰምነር ነበር።

ብዙዎቹ ኢትዮጵያ ፈላስፎች እንደነበሯት እንኳን ባልሰሙበት ወቅት፣ ሰምነር ግን በ1966 “የኢትዮጵያ ፍልስፍና ቅፅ-1 እና ቅፅ-4[a1] ” ብሎ ሲመጣ መምህሩ በኢትዮጵያ ፍልስፍና ላይ ሰፊ ፕሮጀክት ይዞ እንደመጣ ግልፅ ሆነ። ዛሬ የፍልስፍና ዲፓርትመንት በተከፈቱባቸው የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉ “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” የሚል ራሱን የቻለ ኮርስ ያላቸው ሲሆን፣ ኮርሱንም የሚሰጡት ክላውድ ሰምነር ዲዛይን ባደረገው መሰረት ነው።

 1.  የኢትዮጵያ የስነጽሑፍ ዘመናት

ሰምነር “የአንድ ሀገር ፍልስፍና የዚያ ሀገር የስነጽሑፍ አካል ነው” የሚል አመለካከት አለው። ይሄንን አመለካከቱንም “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” የሚለውን ሐሳብ ካመጣበት መንገድ መረዳት እንችላለን። በዚህም መንገድ ነው ሰምነር “የኢትዮጵያ ፍልስፍና”ን ከኢትዮጵያ የስነጽሑፍ ሐብት ውስጥ ለማውጣት የሞከረው። በመሆኑም፣ ሰምነር “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” ወደሚል አዲስ አካዳሚያዊ ተዋስዖ ከመግባቱ በፊት በመጀመሪያ የኢትዮጵያ የስነጽሑፍ ዘመናትን መለየት ነበረበት። “የስነጽሑፍ ዘመናት” የሚባሉት የተለያዩ ሥነጽሑፎች በብዛት የተጻፉበትን ዘመናት ለማመላከት ነው።

ሰምነር፣ የኢትዮጵያን የስነጽሑፍ ዘመናት በሁለት ይከፍላቸዋል (Sumner 2005: 216-218)፤

 1. የመጀመሪያው የስነጽሑፍ ዘመን ከ5ኛው – 7ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ያለው ነው። ይህ ዘመን በአክሱማውያን የሥልጣኔ ዘመን ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ ዘጠኙ ቅዱሳን ወደ አክሱም የመጡበትና ቅዱስ ያሬድም የተነሳበት ዘመን ነው። በዚህ ዘመን ውስጥ የተሰሩ የስነጽሑፍ ትሩፋቶች የሚከተሉት ናቸው።
 • በርካታ የትርጉም ሥራዎች ተሰርተዋል (ለምሳሌ፣ መጽሐፍ ቅዱስ፣ የሥርዓተ ኦሪትና አዋልድ መጻሕፍት እንዲሁም የቀኖና መጻሕፍት ከግሪክኛ ወደ ግዕዝ የተተረጎሙበት ዘመን ነው።
 • የቅዱስ ያሬድ ዜማና የሙዚቃ ድርሰቶች የተዘጋጁትም በዚሁ ዘመን ነው።
 • ከፍልስፍና አንፃር ደግሞ፣ በዚህ የስነጽሑፍ ዘመን ከግሪክኛ ወደ ግዕዝ የተተረጎመው የፍልስፍና መጽሐፍ “ፊሳሎጎስ” ነው። የ”ፊሳሎጎስ” ጸሐፊ ማን እንደሆነ ባይታወቅም መጽሐፉ ግን ግብፅ ውስጥ በሚገኝ ስኬቴ ገዳም በሚኖር አንድ ኢትዮጵያዊ መነኩሴ በ5ኛው ክ/ዘ ተተርጉሟል። “ፊሳሎጎስ” የተፈጥሮ ሥርዓት እንዴት የኢየሱስን የማዳን ሚስጥር እንደሚገልፅ የሚያስረዳ መጽሐፍ ነው።
 • ሁለተኛው የስነጽሑፍ ዘመን ከ12ኛው – 18ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ ያለውን ሰፊ ጊዜ የሚሸፍን ነው። ይህ ዘመን የሰሎሞናዊ ሥርወ መንግስትን መመለስ ተከትሎ ሥነጽሑፉም ዳግም መነቃቃት የታየበት ዘመን ነው። ልክ እንደ መጀመሪያው ሁሉ፣ በዚህ ዘመንም የትርጉም ሥራዎች የሚበዙ ቢሆንም፣ ወደ ግዕዝ የተመለሱት ግን ከአረብኛ መጻሕፍት ነው። ከነዚህ የትርጉም ሥራዎች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፤
 • የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትንታኔዎች፣ የጆርጅ ሊዲያ ሥራዎች፣ አባ ዕንባቆም ወዘተ…
 • ፍልስፍና ላይ የተሰሩ የትርጉም ሥራዎች ደግሞ፣ አንጋረ ፈላስፋ (The Book of the Philosophers) እና የስክንድስ ህይወትና አባባሎቹ (The Life and Maximes of Skendes) ናቸው። ሁለቱም በመጀመሪያ በግሪክኛ የተፃፉ ሲሆን፣ በ16ኛው ክ/ዘ ወደ ግዕዝ የተተረጎሙት ግን ከአረብኛው ነው። ከ”እስክንድስ” በስተቀር ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉም የትርጉም ሥራዎች የተሰሩት አባ ሚካኤል በሚባሉና ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖሩ በነበሩ ግብፃዊ መነኩሴ ነው።
 • በ17ኛውና በ18ኛው ክፍለ-ዘመን የተዘጋጁት የዘርዓያዕቆብና የወልደ ሕይወት የፍልስፍና ሥራዎችም በዚህ ዘመን ውስጥ የሚካተቱ ናቸው።
 1. “የኢትዮጵያ ፍልስፍና”ን ማዋቀር

ሰምነር ከላይ በተጠቀሰው መንገድ የኢትዮጵያን የስነጽሑፍ ዘመናት ለይቶ ካስቀመጠ በኋላ፣ በእያንዳንዱ የስነጽሑፍ ዘመን የተፃፉ የፍልስፍና ይዘት ያላቸውን መጻሕፍት እንደገና ለብቻቸው በመሰብሰብ “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” በሚል ዘውግ ውስጥ እንዲካተቱ አድርጓቸዋል። በዚህ ስብስብ ውስጥም “ፊሳሎጎስ›ን› ከመጀመሪያው የስነጽሑፍ ዘመን፣ “ስክንድስ”ን፣ “አንጋረ ፈላስፋ”ን እና እንዲሁም የዘርዓያዕቆብና የወልደ ሕይወት ሐተታዎችን ከሁለተኛው የስነጽሑፍ ዘመን መርጧቸዋል። ይሄም ማለት ሰምነር “የኢትዮጵያ ፍልስፍና”ን ያዋቀረው ከአምስት የፍልስፍና መጻሕፍት ነው ማለት ነው። እነሱም፣

 1. ፊሳሎጎስ
 2. ስክንድስ
 3. አንጋረ ፈላስፋ
 4. ሐተታ ዘርዓያዕቆብ  እና
 5. ሐተታ ወልደ ሕይወት ናቸው።

ሰምነር፣ በእነዚህ መጻሕፍት በእያንዳንዳቸው ላይ የትርጉምና የትንታኔ ሥራዎችን በመስራት “የኢትዮጵያ ፍልስፍና ቅፅ 1―5” የሚል መጠሪያ በመስጠት በተከታታይ በእንግሊዝኛ አሳትሟቸዋል። እነሱም የሚከተሉት ናቸው፤

 1. Ethiopian Philosophy Vol-1: The Book of the Philosophers (1974/1966E.C)
 2. Ethiopian Philosophy Vol-2: The Treatise of Zara’e Ya’eqob and Wold Heywot: Authorship (1976/1968E.C)
 3. Ethiopian Philosophy Vol-3: The Treatise of Zara’e Ya’eqob and Wold Heywot: An Analysis (1978/1970E.C)
 4. Ethiopian Philosophy Vol-4: The Life and Maxims of Skendes (1974/1966E.C)
 5. Ethiopian Philosophy Vol-5: The Fisologwos (1976/1968E.C)

ሰምነር ከሁለቱ የስነጽሑፍ ዘመናት የሰበሰባቸውን እነዚህን አምስት የፍልስፍና መጻሕፍት እንደገና በሁለት የፍልስፍና ዘመናት በመክፈል “ብሉይ የኢትዮጵያ ፍልስፍና (Classical Ethiopian Philosophy)” እና “ዘመናዊ የኢትዮጵያ ፍልስፍና (Modern Ethiopian Philosophy)” የሚል ስያሜ ሰጥቷቸዋል። በውስጣቸው ያካተታቸው መጻሕፍትም የሚከተሉት ናቸው፤

 1. ብሉይ የኢትዮጵያ ፍልስፍና (Classical Ethiopian Philosophy) (ከ5ኛው―16ኛው ክ/ዘ)
 • ፊሳሎጎስ
 • ስክንድስ
 • አንጋረ ፈላስፋ

ሰምነር እነዚህን መጻሕፍት አንድ ላይ ያደረገበት ምክንያት ሁሉም የትርጉም ሥራዎች በመሆናቸው ነው። ሆኖም ግን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በየገዳማቱ የሚገኙ ፍልስፍናዊ የትርጉም ሥራዎች እነዚህ ብቻ አይደሉም። ሰምነር በፍለጋው ውስጥ ያላገኛቸው ሌሎች ፍልስፍናዊ የትርጉም ሥራዎች በየገዳማቱ ይገኛሉ፤ ለምሳሌ፣

 • መጽሐፈ ሒቃር
 • ወግሪስ ጠቢብ (መጽሐፈ አግዋሪስ)
 • መጽሐፈ ፈላስፋ ጠቢባን
 • መጽሐፈ ፍልስፍና ዘዕብራውያን
 • መጽሐፈ ፍልስፍና ዘጽርዕ
 • መጽሐፈ ፍልስፍና ዘፋርስ
 • እና ሌሎችም….

ምንም እንኳ፣ እነዚህ የፍልስፍና መጻሕፍት በማን፣ መቼና ከየትኛው ቋንቋ እንደተተረጎሙ ገና ጥናቶች ያልተደረጉ ቢሆንም፣ መጻሕፍቱ ግን ሰምነር “ብሉይ የኢትዮጵያ ፍልስፍና” በሚለው ጎራ ውስጥ የሚወድቁ ናቸው።

 • ዘመናዊ የኢትዮጵያ ፍልስፍና (Modern Ethiopian Philosophy) (ከ17ኛው ክ/ዘ ጀምሮ)
 • ሐተታ ዘርዓያዕቆብ
 • ሐተታ ወልደ ሕይወት

ሰምነር እነዚህን ሁለት መጻሕፍት አንድ ላይ ያደረገበት ምክንያት ሁለቱም ወጥ (Original) የሆኑ የኢትዮጵያውያን የፍልስፍና ሥራዎች በመሆናቸው ነው።

ከአምስቱ የፍልስፍና መጻሕፍት ውስጥ ሰምነር በአራት ምክንያቶች ለ”ሐተታ ዘርዓያዕቆብ” ትልቅ ትኩረት ይሰጣል።

 • የመጀመሪያውና ዋናው ምክንያት፣ ጥብቅ የሆነውን የፍልስፍና ትርጉም (the strict sense of the definition of philosophy) ማለትም “በግለሰብ የተጻፈ ኦሪጅናል ሥራ መሆን አለበት” የሚለውን መስፈርት ሙሉ በሙሉ የሚያሟላው ዘርዓያዕቆብ በመሆኑ ነው።
 • ሁለተኛ፣ “አፍሪካ በጽሑፍ የተቀመጠ ፍልስፍና የላትም” የሚለውን ምዕራባዊ ፍረጃ ፉርሽ የሚያደርገው የዘርዓያዕቆብ ሥራ በመሆኑ ነው።
 • ሦስተኛ፣ ኮስተር ያሉ የፍልስፍና ጥያቄዎችን (ማለትም፣ ዲበ አካላዊ፣ ሥነ ዕውቀታዊና ሥነ ምግባራዊ ጉዳዮችን) የሚያነሳ በመሆኑ ነው።
 • አራተኛ፣ መጽሐፉ አመክንዮን የመጨረሻው የስልጣን እርከን አድርጎ የሚቆጥርና የርስበርስ የሐሳብ ተቃርኖሽም የሌለው በመሆኑ ነው።
 1. ከብሉይ ወደ ዘመናዊ ፍልስፍና

በሰምነር ብያኔ መሰረት ሁለቱ የኢትዮጵያ የፍልስፍና ዘመናት (ብሉይና ዘመናዊው) በሐሳብ አገላለፃቸው (Concept of Image) ተወራራሽነት ያላቸው ሲሆን (Sumner 1978: 61)፣ በይዘታቸውም ዕድገት አሳይተዋል (Sumner 1985: 7)።

ሰምነር “የሐሳብ አገላለፃቸው” የሚለው “ስዕላዊና ምሳሌያዊ” የሆነውን የሐሳብ አገላለፅ ሲሆን (ለምሳሌ፣ ጠቢብን በንብ መመሰል)፣ “ኢትዮጵያውያን ጸሐፍት በዚህ የተካኑ ናቸው፤ ይሄም የኢትዮጵያ የስነጽሑፍ ባህል ልዩ መገለጫው ነው” (Sumner 1978: 61) ብሏል። እንደ ሰምነር ግምገማ፣ “ስዕላዊ አገላለፅ” በአንጋረ ፈላስፋ ውስጥም ሆነ በዘርዓያዕቆብና በወልደ ሕይወት ሐተታዎች ውስጥ አለ (Sumner 1978: 61)።

ሌላው፣ ከብሉይ ወደ ዘመናዊ ፍልስፍና በተደረገው ጉዞ በአገላለፅ ብቻ ሳይሆን በሐሳብ ይዘትም ዕድገት አሳይቷል።

ከፍልስፍናዊ የትርጉም ሥራዎች ተነስቶ ወደ ሐተታ የተደረገው ጉዞ የ1200 ዓመታት የስነጽሑፍ ባህል ጉዞ ነው። በዚህ ረጅም የስነጽሑፍ ባህል ጉዞ ውስጥ የፍልስፍና ሥራዎች በሂደት ሁለት ዓይነት ለውጥ አምጥተዋል። የመጀመሪያው ከትርጉም ሥራ ወደ ወጥ (ኦሪጅናል) ሥራ ማደጉ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከምክርና ግሳፄ ወደ አመክንዮአዊ የሐሳብ አደረጃጀት (from wisdom to rationalism) ማደጉ ነው (Sumner 1985: 7)

ሰምነር፣ “የኢትዮጵያ የፍልስፍና መጻሕፍት በሐሳብ አገላለፃቸው ተወራራሽነት ያላቸው ሲሆን፤ በይዘታቸውም ዕድገት አሳይተዋል” የሚለው መደምደሚያው “ዘርዓያዕቆብና ወልደ ሕይወት የ17ኛው ክ/ዘ ኢትዮጵያ ድንገተኛ ክስተት ሳይሆኑ የሀገሪቱ የረጅም ዘመን የስነጽሑፍ ባህል ውጤት ናቸው” ወደሚል ሌላ ድምዳሜ አድርሶታል። ሰምነር፣ በኢትዮጵያ የብሉይና ዘመናዊ ፍልስፍና መጻሕፍት መካከል ያለውን ትስስርና ዕድገት ለማሳየት Classical Ethiopian Philosophy (1985) የሚል መጽሐፍ አሳትሟል።


 [a1]2 ነው 4? ቢረጋገጥ፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top