አድባራተ ጥበብ

የሸዋሉል መንግስቱ እና ህያው የጥበብ ሥራዎቿ

የችግሬ ቁስል ቢቆጠቁጠኝም፣

የመንፈሴ ሽብር ጤና ቢነሳኝም፣

ዘወትር መሳቅ እንጂ ለቅሶ አይሞክረኝም!

በ1964 ዓ.ም. “ሙዚቃ በሐረር” በሚል ርዕስ ባዘጋጀችው የሙዚቀኞችን ታሪክ በከተበችበት መጽሔት መግቢያ ላይ ያሰፈረችው ግጥም ነው። የሸዋሉል መንግሥቱ ብዙ ሰርታ ብዙ ያልተዘመረላት ከያኒ ናት። አንዳንዶች ሲጽፉ ወይ ሲናገሩ “የሸዋልዑል መንግሥቱ” ይሏታል። እሷ የራሷን ስም በምትጽፍባቸው አጋጣሚዎች ላይ ዕንዳየሁት ግን “የሸዋሉል መንግስቱ” ብላ ነው የምትጽፈው። እንግዲህ አንድም የሸዋልዑል ብሎ ስም ለሴት ስለማይወጣ (ልዑል የተባዕት ተጸውኦ በመሆኑ)፤ አንድም ከባለቤቱ ያወቀ… በሚል ብሂል በራሷ አጠራር የሸዋሉል እያልን እንቀጥላለን።

የሸዋሉል “ሙዚቃ በሐረር” የሚለውን ዝነኛ መጽሔት ስታዘጋጅ ገና የ27 ዓመት ወጣት ነበረች። አያሌ ሀላፊነቶችንም ደርባ የተሸከመችበት ጊዜ ነው። እሷ ጥቂት ኖራ ብዙ የሰራች፣ ያልኖረችውን በስራዋ ኖራ ያለፈች ናት ይሏታል። የኦሮሚፋ ቀደምት የሬዲ ዮፕሮግራም አዘጋጁ፣ የድሬዳዋው አፍረንቃሎ የሙዚቃ ባንድን ከመሰረቱት አንዱና የአያሌ ግጥምና ዜማ ደራሲው መሀመድ ቆጴ በአንድ ወቅት በደረጀ ኃይሌና አዜብ ወርቁ ይዘጋጅ ለነበረው “የደራው ጨዋታ” የሬድዮ ፕረግራም ስለ የሸዋሉል ሲናገር “አንዳንድ ሰው በቶሎ ስለምጠራህ ጉዳይህን ፈጥነህ ጨርስ የተባለ ይመስላል” ብሎ ነበር። የሸዋሉል መንግስቱ በርግጥም ቶሎ ከሚጠሩት ተርታ ነበረች። አንዳንዱ የስራን ዓለም ሀ ሁ በሚማርበት ዕድሜ እሷ ስራዋን ጨርሳ ተጠርታለች። ዛሬ በገጣሚነቷ፣ በዘፈን ግጥምና ዜማ ደራሲነቷ፣ በጋዜጠኝነቷ፣ በደራሲነቷና በጸሐፊ ተውኔትነቷ ብዙ የምንልላት ሰው፣ የምድር ቆይታዋ የተቋጨው ገና በ32 ዓመት እድሜዋ ነበር። ቀጥዬ ከተለያዩ ህትመቶች፣ በስራ አጋጣሚ ካናገርኳቸው የተለያዩ ግለሰቦችና ልዩ ልዩ ክምችቶች ያገኘኋቸውን መረጃዎች ላካፍላችሁ። የሸዋሉል በያ ትውልድ የፖለቲካ ውጣ ውረድ ውስጥ የሚነገሩ ብዙ መልኮች እንደሚኖሯት ብገነዘብም የኔው ትኩረት ግን ያልተነገሩ ኪነ-ጥበባዊ አበርክቶዋ ላይ ብቻ የተወሰነ መሆኑ ይታወቅልኝ። አንድም አልተነገሩላትም ብዬ የማስበው ኪነ-ጥበባዊ ስራዎቿ ናቸው ብዬ ስለማምን። አንድም የተሻለ መረጃው ያለኝ በዚሁ (በጥበብ) ዘርፍ ስለሆነ። በዚህ አጋጣሚ ግን ስለ የሸዋሉል መንግስቱ የተሻለ መረጃ አለን የምትሉ ካላችሁ የምታውቁትን ብታጋሩን በበኩሌ እንደ ትልቅ ውለታ ዐየዋለሁ።

የሸዋሉል መንግስቱ ብዙ ጊዜዋን ያሳለፈችው በሐረርጌ ፖሊስ ማስታወቂያ ክፍል በየሁለት ወሩ የሚታተመውን “የምስራቅ በረኛ” መጽሔት በማዘጋጀት ነበር። በዚህ ክፍል ለሐረር ምስራቃዊ ሰጎን ኦርኬስትራ አያሌ ግጥሞችንና ዜማዎችን፣ ቲያትሮችንና ዝማሬዎችን ታዘጋጅ ነበር። ካዘጋጀቻቸው ትያትሮች መካከል “ሰው መልአክ ሆነ እንዴ” የሚል ስራዋን ብዙዎች ያስታውሱታል።

በሐረር ቆይታዋ ለኢትዮጵያ ሬድዮ በትርፍ ጊዜዋ መረጃዎችን በማካፈል ታገለግል የነበረ ሲሆን፤ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣም ጽሁፎችን ትልክ ነበር። በ1962 ዓ.ም. ለመጀመርያ ጊዜ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የታተመላት ጽሁፍ “ሴቶች ብሔራዊ ስሜት ይኑራቸው” የሚል ርዕስ ነበረው።

የሸዋሉል መንግስቱ የመጽሐፍ ደራሲም ናት። በ1962 ዓ.ም. ተጽፎ በ1968 ዓ.ም. የታተመውን “እስከ መቼ ወንደላጤ” የተሰኘ ስራዋ በዚህ ዘመን እምብዛም የሚታወቅ ባይሆንም በዘመኑ ብዙ የተነበበ ነው። ከተጻፈ ከስድስት ዓመታት ቆይታ በኋላ የታተመው መጽሐፉ በጊዜው ብዙ ያነጋገረ ነበር። የማይነሱ፣ የማይደፈሩ ጉዳዮችን አንስታበታለች በሚል። የመጽሐፉ ጭብጥ በዋናነት ስለ ጋብቻና ፍቺ፣ ስለጾታዊ ግንኙነትና ስለ ወንደ ላጤነት በነጻነት ያተተችበት ነው።

ስለ ስራዋ ጥቂት ለማንሰላሰል እንዲመቸን፤ መጽሐፉን ለማዘጋጀት የተመረኮዘችባቸውን ሦስት መሰረታዊ ጥያቄዎች ከመግቢያዋ እንቀንጭብ። እነዚህም “በወንደላጤነት እስከ መቼ እንሰቃያለን? እጮኛነትን ምክንያት በማድረግ እስከ መቼ ማንዘራሾችና የሀገር ስም ሰባሪዎች፤ የወላጆቻችን አሳዛኞች እንሆናለን? እና መግባባትን ሳናውቅ ዕድልን በማማረር እስከ መቼ እንኖራለን?” የሚሉ ናቸው። በነዚህ ሦስት ጥያቄዎች ላይ ተመስርታ የራሷን ምላሽና ትንታኔዎችን ለመስጠት ትሞክራለች። አያሌ አባባሎችና ጥቅሶችም የመጽሐፉ አካል ናቸው። እንግዲህ ስለ መጽሐፍ ስራዋ ይሄን ያህል ካልኩ ቀሪውን ላንባቢዬ ትቼ ወደ ሌላ ሙያዋ ልሻገር። ሙዚቃ!

የሸዋሉል በሙዚቃው ዓለም ብዙ ሰርታለች። ዘመን ተሻጋሪ የግጥምና የዜማ ስራዎቿ ህያው ምስክሮቿ ናቸው። ለወንዶች በሰጠቻቸው ድንቅ የዘፈን ግጥሞች ምክንያት “ወንዶችን ለሴቶች የፍቅር ዘፈን የምታዘፍን” ይሏታል። ሴት ሆና ሳለ የአድን ወንድ አፍቃሪ ልብ በዚህ ደረጃ መረዳት እንደምን ቻለች? በማለት። ሴት ሆኖ በወንድ ስሜት መጻፍ፤ ወንድ ሆኖ በሴት ስሜት መጻፍ የተለመደ ቢሆንም፤ እንዲህ የልብን የሚኮረኩሩ ግን ሁሌም ጥቂቶች ናቸው። እንዲህ ዓይነቶቹ ገጣሚዎች ቶሎ ቶሎ የሚገኙም አይደሉም። በትውልዱ መካከል እንደ ሰንደቅ ድንገት ብቅ የሚሉ እንጂ። በዚህ ዘመን እንደነ ዓለምፀሐይ ወዳጆን የመሰሉ ድንቅ ገጣሚዎችን ልብ ይሏል። የሸዋሉል በትውልዱ ጅረት በአንዱ የተከሰተች ልዩ የግጥምና ዜማ ደራሲ ነበረች። የባህል ጨዋታዎችን ወደ ዘመናዊ ዘፈን ስትቀይር ደግሞ ወደር የላትም። በሀገራችን የባህል ስራዎችን በዘመናዊ ግጥምና ዜማ አድሶ የማቅረብ ብልሀትን ያሳዩ ከያኒያን በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ከዋንኞቹ ዋናዋ ደግሞ የሸዋሉል ናት። በጥላሁን ገሠሠ፣ በአሊ ቢራና በሌሎችም እውቅ ድምጻውያን ስራዎች ውስጥ የብዕር ቀለሞቿ ደምቀው ይታያሉ።

የሸዋሉል ግጥምና ዜማ ሰጥታቸው እጅግ ከተወደዱ ስራዎቿ መካከል የጥላሁን ገሠሠ “አካም ነጉማ” አንዱ ነው። ከላይ እንዳነሳነው ነፍስ ከዘራችባቸው የባህል ጨዋታዎች መካከል የሚጠቀስ ስራም ነው። በራሷ ግጥምና ዜማ ዘመናዊ ሸማ ያለበሰችው ድንቅ የጥበብ ውጤት። ይህ ተወዳች የኦሮሚፋ ዘፈን የተወዳጆቹ የዜማ አባቶች ተዘራ ኃይለሚካኤል እና አየለ ማሞ የዜማ ድርሰቶች የተካተቱበት እንደ “ውበትሽ ይደነቃል (የጠላሽ ይጠላ)፣ የፍቅር ሲባጎ፣ የቆለኛ ልጅ ናት” እና ሌሎች ስድስት ዘፈኖች የተካተቱበት አልበም አካል ነው። አልበሙ በ1973 ዓ.ም. ክረምት ላይ የወጣ ሲሆን አጃቢ ባንዱ ደግሞ አይቤክስ ባንድ ነበር። “እንዴት ነሽ ሰላም ነሽ” የሚል ትርጉም ባለው “በአካም ነጉማ ፈዩማ” ጥቂት ቆዝመን ወደ ሌላ የሙዚቃ ስራዋ እንለፍ።

Akkam nagumaa fayyumaa

Hiriyaa hinqabuu kophumaa

Dhuftee na laaltus gaarumaa

ሌላው የሸዋሉል መንግስቱ የግጥምና ዜማ ስራዎች ማደሪያ አንጋፋው ድምጻዊ መሀሙድ አህመድ ነው። መሀሙድ የተጫወታቸው ትዝታ (ግጥም)፣ እሆሆ ገዳማይ (ግጥም)፣ ስደተኛሽ ነኝ፣ እንዴት ነው ገዳዎ፣ አሸወይና (ዜማ)፣ ኧረ መላ መቼ ነው እና አታውሩልኝ ሌላ (ግጥም) የሸዋሉል የድርሰት ውጤቶች ናቸው። በተለይ የትዝታ ግጥሟ ልዩ ነው። መሀሙድ ብዙ የትዝታ ዘፈኖችን የተጫወተ ቢሆንም የዚህኛው ዘፈን ግጥም ግን ለየት ያለ ነው። የሸዋሉል የትዝታ ግጥም ከለመድነው “ትዝታሽ ዘወትር ወደኔ እየመጣ…”  ተለምዶአዊ ተረክ ያፈነገጠ (redefined) ነው። እንዲህ እያለ…

ትናንትናን ጥሶ ዛሬን ተንተርሶ፣

ነገንም ተውሶ አምናንም አድሶ፣

ይመጣል ትዝታሽ ጓዙን አግበስብሶ።

የሸዋሉል መንግስቱ የአንጋፋው ድምጻዊ አሊ ቢራ እና የክራሯ ንግስት አስናቀች ወርቁን ስራዎችን የመድረስ እድልም ነበራት። ከአሊ ቢራ ስራዎች መካከል “ወይ ዮቢ ዮቢ” እና “አዋሽ” የሚሉቱን ስትደርስ፤ “እህ ልበል” እና “ሰላ በልልኝ” የሚሉ ግጥሞችን ደግሞ ለአስናቀች ወርቁ ሰጥታለች።

ሌላው ትልቁ የግጥምና ዜማ ስራዋ በዳህላክ ባንድ አጃቢነት የተሰራው የሙሉቀን መለሠ የ1969 ዓ.ም.  አልበም ነው። በዚህ አልበም ውስጥ የተካተቱ አስር ዘፈኖች ሁሉም የሸዋሉል መንግስቱ ድርሰቶች ናቸው። ዘፈኖቹም “ጀመረኝ፣ ሕልም ሆነሽ አትቅሪ፣ ጉብል ቀዘባ፣ የምንጃር ሸጋ፣ በኔ ሞት፣ ውብ አበባ፣ መወደድሽን ብታውቂው፣ ባይሽ ደስ ይለኛል፣ ከሴት እሷ ብቻ እና ትዝታ” የሚሉት ናቸው። በሸዋሉል የግጥምና ዜማ ደራሲነት፣ በጥላዬ ገብሬ አቀናባሪነት፣ በታንጎ ሙዚቃ መደብር አከፋፋይነት እና በዳህላክ ባንድ አጃቢነት በተሰራው አልበም ሽፋን ላይ የሸዋሉል መንግስቱ እንዲህ ትላለች “ህይወት፣ ሞት፣ ሀዘን፣ ደስታ፣ ፍቅር፣ ጠብ፣ ትዝታ፣ ሰላም፣ ጦርነት፣ ትግልና ድል ብሎም ዓለም ሁለንተናዋ ይስበኛል። ዜማ እንድደርስ፣ ግጥም እንድጽፍ ይጋብዘኛል። ስለሆነም እኔና ብዕሬ የትም መቼም ከሰፊው ህዝብ ጋር ነን።”

አንዳንድ ሀሳቦች ትንቢት የሚሆኑት ለዚህ ይመስለኛል። አለ አይደል በጥቂት ቃላት እንዲህ ነፍስ ዘርተው የሚያልፉ። ዓለም ከነሰንኮፏ፣ ከነአበባዋና አመኬላዋ የምትስባት የሸዋሉል በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ብዙ ለማምረት ስትጣደፍ፣ ስትተጋ…የጊዜ የለኝም መንፈስ ሽው ብሎባት ይሆን? ፈጥና እንደምትመለስ ልቧ ነግሯት ይሆን? ማን ያውቃል…

በመረመርኳቸው መረጃዎች መሰረት የሸዋሉል መንግስቱ የተወለደችው በ1937 ዓ.ም. ሲሆን ቦታው በቀድሞው ሐረርጌ ክፍለ ሀገር ኤጀርሳ ጎሮ የሚባል ስፍራ ነው። ኤጀርሳ ጎሮ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የትውልድ ቦታ መሆኗንም ልብ ይሏል። ስለ ትውልድ ቦታዋ እራሷ የሸዋሉል መንግስቱ እትብቴ ለተቀበረችበት ቦታ መታሰቢያ ትሁንልኝ ስትል የጻፈችውን ግጥም በከፊል ላካፍል።

ለምለም ወረዳ ነሽ እጅግ የተዋብሽ፣

ደስታን የምትሰጪ ውዲቱ አንቺ ነሽ፣

ወደ ዓለም ስመጣ ጎትቶኝ ተፈጥሮ፣

ምርር ብዬ አልቅሼ ሳስብ በአንክሮ፣

ምድርን ሰላም ስላት በደረቅ ለቅሶዬ፣

አንቺን ነው ያየሁት ኤጀርሳ ጎሮዬ….

ይህ ግጥም በወቅቱ በሀረሩ የአንበሳው ኦርኬስትራ ዜማ ተሰርቶለት ተዜሞ ነበር። “በዚህ ዓለም የሚጠላ ነገር ቢኖር ነገ አደርገዋለሁ ማለት ነው” የምትለው የሸዋሉል ስራዋ ከሐረርና አካባቢዋ አልፎ አዲስ አበባንና ድፍን ኢትዮጵያን ለማዳረስ በጣት ከሚቆጠሩ ዓመታት በላይ አላስቆጠረም።

ትምህርቷን እዚያው የትውልድ ቀዬዋ አካባቢ በሚገኝ ትምህርት ቤት የተከታተለች ሲሆን እሷና ሥነ- ጽሁፍ ገና ከአስር ዓመት ዕድሜዋ ጀምሮ ተዋውቀዋል። በአንድ ወቅት ለጸደይ መጽሔት በሰጠችው ቃለ-መጠይቅ ላይ እንደተናገረችው፤ በዚህ ዕድሜዋ የጻፈችው “የኢዮብ ትግስት” የተሰኘ ድርሰቷ፣ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ማለትም በ19 ዓመት እድሜዋ ጥቂት ማሻሻያ አክላበት በኢትዮጵያ ሬድዮ “የትያትር ጊዜ” በተባለ ፕሮግራም ላይ ተላልፎላታል። ይህ ስራ በድርሰት ዓለም የመጀመርያ ስራዋ መሆኑ ነው።

ሙዚቃ በሐረር በተባለ መጽሔቷ ላይ ደግሞ ስለ ሙዚቃ እንዲህ ትላለች። “ለዚህ መጽሔት ዝግጅት ቁም ነገሩ ሁለት ነው። ይኸውም አንደኛ ልፋታችን፣ ድካማችን በህዝብ ዘንድ አልታወቀልንም ለሚሉት የሙዚቃ ዓለም ሰዎች የከበረ የህሊና ድጋፍ ለማበርከት፤ ሁለተኛ የሙዚቃ ሙያና ክቡርነት በመጠኑም ቢሆን ለአንባቢያን ለማስታወስ ነው።” በዚህ መጽሔት ከተካተቱ ድምጻውን መካከል ጥቂቶቹን ብንጠቅስ እንደነ መርሀዊ ዮሐንስ፣ ሲሳይ ገሰሰ፣ ወጋየሁ ደግነቱ፣ ተስፋዬ ለሜሳና ሌሎች በርካቶችን እናገኛለን። ይህ ስራዋ እስከ ዛሬ ድረስ የብዙዎች ማጣቀሻ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል።

ለዚህ ይመስላል በ1965 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ የሙዚቃ፣ የስዕል፣ የትያትር፣ የስፖርትና የሌሎች ሙያዎችን አርበኞች በጥቂት በጥቂቱ የዘከረ አንድ መጽሔት እንዲህ ሲል የሚገልጻት። “የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ፖሊስ ማስታወቂያ ክፍል ቅመም ነች። የቁልቢን በዓል የሚያከብሩ ከድንኳን በምታስተላልፈው ግሩም ማስታወቂያ፣ ማንበብ የሚወዱ ደሞ በሐረር የመጀመርያውን የሙዚቃ መጽሔት በጥሩ አማርኛ በማዘጋጀቷ ያውቋታል። እኛም ስለ ሐረር ሙዚቀኞቻችን ለማወቅ ያስቻለን የእሷ እርዳታ ነው።”

የሸዋሉል መንግስቱ በአዲስ አበባ በቆየችባቸው ጥቂት ዓመታት ውስጥ በርካታ ስራዎችን ሰርታለች። በኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቭዥን በዜና አንባቢነት፣ በፕሮግራም አዘጋጅነትና በሬድዮ ድራማ ጸሐፊነት ሰርታለች። በደርግ ዘመን በቀበሌ ሊቀ-መንበርነትም ያገለገለች ሲሆን በወቅቱ የመኢሶን አባልም ነበረች። ረጅሙን ጉዞዋን በአጭሩ የቀጨባት ይኸው የያ ትውልድ የፖለቲካ እንካሰላንትያ ነበር።

የሸዋሉል መንግስቱ የአምስት ልጆች እናት ስትሆን፤ ግንቦት 1969 ዓ.ም. ምድርን የተሰናበተችባት የመጨረሻዋ ወር ናት። “ምንም ይሁን ምንም” በሚል ርዕስ  በ1966 ዓ.ም. በጸደይ መጽሔት ላይ በሰፈረ ግጥሟ እንሰነባበት።

ጥቁሪት ጥቁሪት ምን ታስቢያለሽ በተደምሞ፣

ጥቁር ውበትሽ በጥቁረቱ ተቀልሞ፣

ጥቁሪት ሳይሽ፣

ዝም ብዬ አላልፍሽ፣

አጠናሻለሁ፣

አነብሻለሁ፣

እስቲ አንድ ነገር ልጠይቅሽ፣

ምን እንደዚህ አጠቆረሽ፣

መልክሽን ሳትነግሪኝ አውቀዋለሁ፣

ጥቁር መሬት ፍሬው ያጠግባል ሲሉ ሰምቻለሁ፣

ከጥቁር አየር፣ ከጥቁር አፈር ከጥቁር ውሃ ተቀምመሽ፣

እንዲህ ወዲህም ከጥቁር ሰው ተወልደሽ፣

ልታስመሰክሪ ችለሻል ጥቁር ውብ ነው አሰኝተሸ!

2 Comments

2 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top