ማዕደ ስንኝ

አንደዛ ነውኮ!

ምን ይገርማል ይሄ በኔና‘ቺማ ‘ድሜ

ምን ያስደፋል አንገት ምን ሆነሻል እቱ

በኔናንቺ‘ኮ እድሜ…

መሳ ለመሳ ነው እምነቱ ከእብለቱ

በኔናንቺ‘ኮ እድሜ…

አድናቂው ብዙ ነው አድራቂው ብዙ ነው

ምን ያደርጋል ታዲያ…!

እንደ ክረምት አግቢ… ማታ ተፈልፍሎ ሲነጋ ጠፊ ነው

እንደዛ ነውኮ ቆንጅት ምን ሆነሻል?

ውጣ ያለው ገንዘብ ሲቆፍር ያመሻል

በኔና ‘ንቺ‘ኮ ‘ድሜ ላ‘ሳር ነው እንግዳው

በዚም በይ በዚያኛው ብዙ ነው ግድግዳው

መንገዱ መንትያ ረግረግ ነው ሜዳው

ልውጥ ውልምጥ ይላል የያዝነው ከዘራ

እርም ነው እህቴ…

በኔ‘ና‘ንቺማ እድሜ እልፍኝም አንቅም ስልቻ ብንዘራ

ይሰለብ የለን‘ዴ የያዝነው ከጃችን

እንደ ጉርጥ እንቁላል ሾልኮ በጣታችን

ይከዳንስ የለም ወይ ወንዛችንን ለምዶ ያፋችንን በልቶ

ደርሶ እንደማያውቀን ምሎ ተገዝቶ እመቤቴን ጠርቶ

እንደዛ ነው እኮ…

ያለፈው አለፈ አታስቢው ተይው

ገና ነው ፈተናው…

እስኪ ነቃ ብለሽ ነገን አስተውይው

ነገም ሰው ይመጣል ያሞግስሻልም

በእምነቱም በእናቱም ይምልልሻልም

ምን ያደርጋል ታዲያ…

በእኔ እና አንቺ እኮ እድሜ መግተልተል ነው እንጂ

የመጣው ከሄደው ብዙም አይሻልም

ይሰማሻል እቴ

ገራገር ልባችን ይሉኝታን አምቆ

አንድም ባይሄድ ደፍሮ አንድም ባይቀር ንቆ

ላይን አምላክ እንዲሉ ከጠበቀን በቀር

ከሄደስ ከቀረስ ማን ዳነ ተጨንቆ

እንደዛ ነው እኮ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top