ስርሆተ ገፅ

“በአሁኑ ጊዜ ሐገሮች ከኮቪድ-19 ጋር ብቻ ሳይሆን ከተሳሳተ የመረጃ ወረርሽኝ ጋርም ግብ ግብ ገጥመዋል።”

ዶ/ር ዮናስ ባህረጥበብ

የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ተከትሎ የዓለም ጤና ድርጅትን ካሳሰቡ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የመረጃ መዛባት ነው። የጤና ድርጅቱን ስጋት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ)ን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ይጋሩታል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል የሆኑት ዶክትር ቴዎድሮስ አድሃኖም “የሐሰት መረጃዎች የቫይረሱን ስርጭት በቀደመ ፍጥነት መሰራጨታቸው ከባድ አደጋ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። የሐሰት መረጃዎች ስርጭትን ለመግታትም ጎግል፣ ትዊተር፣ ፌስቡክ፣ ቴንሰንት፣ ቲክቶክን ለመሳሰሉ ድርጅቶች ዳሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ባለፉት ሳምንታት ዋሽንግተን ፖስት ያወጣው አንድ ጥናት እንደሚያሳየው በ3 ሳምንታት ውስጥ ብቻ ኮሮና ቫይረስን የተመለከቱ ከ2 ሚልዮን በላይ የተሳሳቱ መረጃዎች በትዊተር ተሰራጭተዋል።

የመረጃው ዓይነት እና መጠን መብዛቱ፣ የመረጃው ባለቤት አለመታወቁ እና ኃላፊነት የሚወስድ አካል አለመኖሩ፣ ለእርማት እና ለቁጥጥር ማስቸገሩ፣… ተጨማሪ ወረርሽኝ አስከትሏል ሲሉ ባለሙያዎቹ ስያሜ ሰጥተውታል ‘Info-demic’ (የመረጃ ወረርሽኝ)

ዶ/ር ዮናስ ባህረ ጥበብ በአዲስ አበባ ዮንቨርሲቲ በአዕምሮ ሕክምና ትምህርት ክፍል በተባባሪ ፕሮፌሰር ማእረግ በመምህርነት፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በኮንሰልታንትነት፣ በሕጻናት እና በወጣቶች የአዕምሮ ሐኪምነት፣ እያገለገሉ ይገኛሉ። የሐገር በቀል ትምህርት እና ሕክምናን ከዘመናዊ ሕክምና እና ትምህርት ጋር ለማስተሳሰር በሚደረጉ ጥናቶች፣ ምርምሮች እና የሙከራ ፕሮጀክቶች ላይ ይሳተፋሉ የ”ስጦታ የአዕምሮ ሕክምና እና ከሱስ ማገገሚያ ማዕከል” መስራች ናቸው። ከላይ ባነሳነው የመረጃ ወረርሽኝ ዙሪያ ከጋዜጠኛ ነቢዩ ግርማ ጋር ያደረጉት አጠር ያለ ቆይታ ለንባብ እንዲሆን አንዲህ ተሰናድቷል።

የመረጃ ወረርሽኝ ምንድነው? ከሚለው ጥያቄ እንጀምር

ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ አዳዲስ ቃላቶች እየመጡ ነው። ድሮ የማናውቃቸው ቃላቶች እየተፈጠሩ ነው። ‘ኢንፎደሚክ’ አንዱ ነው። ‘ኢንፎደሚክ’ በአጭሩ የተሳሳተ የመረጃ ወረርሽኝ ማለት ነው።

በአሁኑ ጊዜ ሐገሮች ከኮቪድ ጋር ብቻ ሳይሆን ከተሳሳተ የመረጃ ወረርሽኝ ጋርም ግብ ግብ ገጥመዋል። ይህንን በእንግሊዘኛ ‘ኢንፎደሚክ’ ይሉታል።

ለአንድ ችግር ከልክ በላይ መረጃ በመስጠት፣ ከችግሩ ፍላጎት በላይ በመረጃ በማጥለቅለቅ ችግሩን ለመፍታት የሚደረግን ጥረት ውስብስብ እና አስቸጋሪ የሚያደርግ የመረጃ አቅርቦት ነው።

መንስኤው ምንድነው?

ዓለም በዕውቀት መረዳት ላይ ፈተና ገጥሟታል። በተለይ የሳይንሱ ዓለም ዕውቀት የምንፈልግበት የለመደው ‘ዩሮ ሴንተሪክ’ የሆነው አውሮፓ ተኮር የዕውቀት ፍለጋ ከሽፏል የሚል እንድምታ መፈጠሩ ዓለም ላይ ትልቅ ተግዳሮት ፈጥሯል። በዚህ ምክንያት በባህላዊም፣ በዘመናዊም፣ በሐይማኖትም፣… አዳዲስ አስተሳሰቦች መጥተዋል። እኛ እናውቃለን፣ የተሻለ ገብቶናል፣… የሚሉ ብዙ ሰዎች አዳዲስ ነገር ስለ ኮቪድ እየተናገሩ፣.. ‘ኢንፎደሚክ’ ያልነው የተዛባ የመረጃ ወረርሽኝ እንዲከሰት አድርገዋል ብዬ አስባለሁ። አንደኛው ምክንያት ይሄ ነው።

ሀገሮች የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ በማሰብ ሰዎች በሙሉ ቤታቸው እንዲቀሩ በአዋጅ መከልከላቸው በኮቪድ ላይ ለተስተዋለው የተሳሳተ መረጃ ሁለተኛው ምክንያት ተደርጎ ነው የሚታሰበው።

ዓለም ላይ ብዙ ሰው ቤቱ ነው። ሰው ደግሞ ቤቱ ሲቀመጥ ብዙ ጊዜ ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ይሰራል። ብዙ ሰው ኢንተርኔት ላይ ብዙ ጊዜ ያጠፋል። በርካታ ሰው ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ያሳልፋል። ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ብዙ ባሳለፈ ቁጥር ስለ ኮቪድ ብዙ ነገር ሊጽፍ ይችላል፣ ስለ ኮቪድ ብዙ መረጃ ሊለዋወጥ ይችላል፣ ለማሰብ ጊዜ አለው። የመሰለውን ነገር እዚያ ላይ አንስቶ ሊለጥፍ ይችላል። ይህም ለተሳሳተ የመረጃ ስርጭት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።

ሌላው ምክንያት ተብሎ የሚታሰበው ‘ኮንስፓይሬሲ ቲዮሪ’ የሚባለው ነገር ነው። የሴራ ንድፈ ሐሳቦች፣ አንድን የተፈጠረ ሁኔታ በሆነ ኃይል ሆነ ተብሎ እንደተፈጠረ፣ ሆነ ተብሎ እንደተቀነባበረ አድርጎ ማሰብ ነው።

በተለይ ከኮቪድ ጋር ተያይዞ ብዙ ‘ኮንስፓይሬሲ ቲዮሪ’ዎች አሉ።

ምሳሌ ያህል 5G የኔትወርክ ቴክኖሎጂን ከኮቪድ ጋር አገናኝተው እንግሊዝ ሐገር ሰዎች በጣም ሲሸበሩበት ደጋግመው ሲያወሩ የነበሩበት ነገር ነው። እንደውም በ5ጂ የቴሌፎን ታወሮች ላይ ሰዎች ጥቃት አድርሰዋል።

ሌላው አንድ በቅርቡ የተደረገ ጥናት አለ። ጥናቱ ከሦስቱ አሜሪካዊያን አንዱ ኮሮና ቫይረስ ሆነ ተብሎ ላብራቶሪ ውስጥ እንደተመረተ እና አሜሪካ ውስጥ እንዲሰራጭ እንደተደረገ ያምናሉ። ይህ በጣም ብዙ ቁጥር ነው።

አገራት ይህንን ‘ቲዎሪ’ ተጠቅመው የፖለቲካ አጀንዳቸውን ሲያራምዱበት ይታያል። ሕንድ ቻይናን ትከሳለች። ቻይና አሜሪካንን ከሳለች። ኢራኖች አሜሪካኖች ሆነ ብለው እኛን ለማጥፋት ቫይረስ አሰራጭተውብናል ይላሉ። አሜሪካ የዓለም ጤና ድረጅትን እና ቻይናን ስትከስ ይታያል። ስለዚህ ‘ኮንስፓይሬሲ ቲዮሪ’ው ፖለቲካል አጀንዳም አለው። ኢኮኖሚካል አጀንዳም አለው።

ሌላው አንድ ቦታ ላይ ሳነብ ያየሁት ሩስያዊያኖች ሆነ ብለው አሜሪካኖችን ግራ ለማጋባት የተዛባ የመረጃ ወረርሽኝ በኮቪድ ላይ ይለቃሉ ብለው አሜሪካኖቹ ያምናሉ።

ከዚህ በፊት የነበሩ ዓለም አቀፍ ወረርሽኞች ላይ ተመሳሳይ ነገር ታይቷል ያሁኑ በምን ይለያል?

ብዙ ጊዜ ዓለም ላይ የተለያየ ወረርሽኝ ሲከሰት ወረርሽኙ በመረጃ ሱናሚ ይጥለቀለቃል። ምሳሌ ኢቮላ፣ ጥቁር ሞት የሚባለው ኢንፍሉዌንዛ በተከሰተበት ጊዜም እንዲህ እንዳሁኑ በመረጃ ተጥለቅልቆ ነበር። የአሁኑ በኮቪድ የሚሰራጨው የተሳሳተ የመረጃ ወረርሽኝ የሚለየው በፍጥነቱ ነው። ልክ እንደቫይረሱ በፍጥነት ይዛመታል። ለምን ይሄ ሆነ ከተባለ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የቴክኖሎጂ ‘ኤራ’ ነው። ኢንፎርሜሽን በጣም በቀላሉ ይሰራጫል። የተለያዩ ማኅበራዊ ሚድያዎች በሰከንዶች መረጃን ያሰራጫሉ። በማኅበራዊ ሚድያ መስፋፋት ምክንያት ሁሉም ሰው ጋዜጠኛ ሆኖ የለም? ያየውን ኢንፎርሜሽን ሰዎች ጋር በቀላሉ እንዲሰራጭ ያደርጋል።

ባለፉት ስድስት ሳምንታት ብቻ ወደ 3 ቢሊዮን የሚሆኑ ኮቪድን የተመለከቱ መረጃዎች በማኅበራዊ ሚድያው ላይ ተሰራጭተዋል። 100 ቢልዮን ጊዜ ሰዎች ለኮቪድ ‘ኢንተራክት’ አድርገዋል። መረጃ ተለዋውጠዋል። ይህ በስድስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ነው። በጣም ብዙ ነው። ያ ብቻ አይደለም አገሮች በተለያየ ቋንቋ የተለያየ ሐገር ላይ ሆነው ሰዎች ስለ ኮቪድ አውርተዋል። ዓለም ላይ እንደዚህ ሆኖ አያውቅም። አንድ አጀንዳ ላይ አገሮች በተለያየ ቋንቋ ለረጅም ጊዜ ተነጋግረውበት አያውቁም። ስለዚህ አንደኛው ነገር ለተሳሳተ መረጃ ስርጭት በኮቪድ ላይ ሰዎች ቤት መቀመጣቸው ነው ተብሎ ይታሰባል።

ከቴክኖሎጂ ዘመንነቱ በተጨማሪ ሌሎች ምክንያቶች ይኖራሉ?

የመጀመሪያው ነገር ስለ ኮቪድ ብዙ አለመታወቁ ነው ብዬ አስባለሁ። የኮቪድ ሳይንስ በብዙ መላ ምቶች የታጀበ ነው። ስለኮቪድ ይሆናል የተባለ ነገር ሳይሆን ቀርቶ ያውቃል። የሳይንሱ ማኅበረሰብ የተለያዩ የተምታቱ መረጃዎች ሲሰጥ ይታያል። ሳይንስ ከዚህ በፊት እንዳደረገው ለችግሩ መፍትሔ ማምጣት ሲያቅተው አስተውለናል። መደበኛ ከሆነው ሳይንሳዊ አረዳድ ‘ዩሮ ሴንተሪክ’ ከሚባለው አውሮፓን ማዕከል ያደረገ የሳይንሳዊ አረዳድ ያፈነገጡ ሐሳቦች እየታዩ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ከመደበኛው ሳይንሳዊ አመለካከት ያፈነገጡ አዳዲስ አተያዮች እየመጡ ነው።

አንዳንድ ዕውቀቶችን፣ አንዳንድ እውነቶችን ስንፈልግ በተለያየ መንገድ ሊሆን ይችላል። እንደ ማኅበረሰቡ ባህል፣ እንደ ሀይማኖቱ፣ እንደ አተያያችን፣… በተለያየ መንገድ ዕውቀቶችን ልንፈልግ፣ ልንረዳ እንችላለን። በተለያየ መንገድ ዕውቀትን ስንፈልግ፣ በተለያየ መንገድ ወደ እውነት ለመድረስ ስንሞክር የምናመጣው ውጤት የተለያየ ሊሆን ይችላል። የተለያዩ እውነቶች እና ዕውቀቶች ሊመጡ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ዓለም ላይ ‘ዩሮ ሴንተሪክ’ የነበረው አውሮፓ ተኮር ሳይንሳዊ አረዳድ ለዓመታት ተቀባይነት ነበረው፣ ችግር ፈቺም ነበር። በኮቪድ ግን ያ ሊሆን አልቻለም። በዚያ ምክንያት ሰዎች የራሳቸውን ዕውቀት ፍለጋ ጀምረዋል። በራሳቸው መንገድ ዕውቀት እየፈለጉ ነው። ከ‘ዩሮ ሴንተሪኩ’ አፈንግጠው በራሳቸው መንገድ ዕውቀት እየፈለጉ እና እውነት የሚሉትን የራሳቸውን ነገር እያገኙ ነው። ያንን ተንተርሰው የራሳቸውን መፍትሔም እያመጡ ነው። በዚህ ምክንያት የተለያዩ መረጃዎች በኮቪድ ላይ እያየን ነው። የተለያዩ ነገሮች እየሰማን ነው።

የሚገርመው ግን አገራቸው በአውሮፓ ተኮር ሳይንስ የገነቡ ታላላቅ የሐገር መሪዎች ከራሳቸው ሳይንስ አፈንግጠው፣ ዲቶል ብትወጉ ሲሉ፣ 5ዲ የኮቪድ ምንጭ ነው ሲሉ በጣም ያስገርማል። ምክንያቱም እነርሱ አገራቸውን በአውሮፓ ተኮር ሳይንስ ነው የገነቡት። በዚያ ሳይንስ ላይ ተመስርተው ነው ሐገራቸውን የገነቡት ግን ከዚያ አፈንግጠው ሌላ አተያይ እየፈጠሩ ነው ያሉት እና ያ በጣም የሚገርም ነገር ነው።

ማን ምን ማድረግ አለበት?

መንግሥት ሁሌም ተከታታይ እና ግልጽ መረጃ አሁን እያደረገ እንዳለው ለህብረተሰቡ በባለሙያዎች እንዲሰጥ ማድረግ አለበት። በተከታታይ መሆን አለበት። ሁሌም መግለጫዎች መሰጠት አለባቸው። ያ ግልጽ እንዲሆን ያደርገዋል። የተሳሳተ የመረጃ ወረርሽኝ ካለ እና ሚድዎች ላይ ከደረሰ፣ መንግሥት ጆሮ ከደረሰ ያንን መረጃ ተከታትሎ በግልጽ መሞገት ያስፈልጋል። መረጃውን የሚገዳደር መግለጫ ማጣት ያስፈልጋል

ሕብረተሰቡ በኮቪድ ላይ መረጃ ሲሰማ የመረጃውን ምንጭ ማጣራት አለበት። መረጃው ምንድነው፣ ምንጩ ከየት ነው፣… በተለይ የተማረው ማኅበረሰብ መረጃውን በተለያዩ መረጃዎች ሊሞግት ይገባል። የተለያዩ ‘ሎጂኮ’ችን ተጠቅሞ እነኚያን መረጃዎች መመርመር ይገባዋል። ከመረመረ ካወቀ በኋላ ለሕብረተሰቡ ያንን ማሳወቅ ያለበት ይመስለኛል።

ሌላው ሳይንሳዊ አካሄድን የሚከተለው ተመራማሪ ግልጽ ያለ ነገር፤ ወጥ የሆነ ነገር፤ መናገር እና ማቅረብ፣ በሳይንስ ላይ የተመሰረቱ ትንታኔዎችን ለኅብረተሰቡ ማቅረብ ከመረጃ ውዥምብሮች ሕብረተሰቡን ሊጠብቅ ይችላል።

አመሰግናለሁ!

እኔም አመሰግናለሁ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top