ታዛ ወግ

ቁልምጫ

በባሕር ማዶኞች ባህል “ስዊት ኸርት፣ ዳርሊንግ፣ ሃኒ፣…” እያሉ እያጣፈጡ ለፍቅረኛ ወይም ለትዳር ጓደኛ ይድረስን ማሳመር የተለመደ ነው። አልያ ደግሞ “ጆናታን” በማለት ፈንታ “ጆኒ”፣ “ጄምስ” በማለት ፈንታ “ጂሚ” ብሎ መጥራትም ያለና የነበረ ነው። ሌላው ቀርቶ የቀድሞዎቹ የአሜሪካ ዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንቶች ጄምስ ካርተር እና ዊልያም ክሊንተን ከጓዳቸውም አልፈው በአደባባይ ጭምር በመጀመሪያዎቹ ስሞቻቸው ተቆላምጠውባቸዋል። “ጂሚ” (ካርተር) “ቢል” (ክሊንተን) እየተባሉ!! ለነገሩማ በእኛስ ሀገር እነ ሳሚ፣ እነ ጂጂ፣ እነ ቲቲ ሁሉ አሉ አይደል?

ነገርን ነገር ያነሣዋልና በአንድ ወቅት “አራዳ ቡና ቤት” የተቀጠረች ኮረዳ ከገጠር ዘመዶቿ መጥተው “እባካችሁ ዓመተ ጊዮርጊስን አገናኙን” ቢሉ ያች ዓመቴ ከወዴት ትገኝ? “የለችም እንዲህ የምትባል ሴት እኛ አናውቅም” ተብለው እያዘኑ ሊመለሱ ሲሉ አንዱ ዘመድ ድንገት ብርጭቆ ስታጥብ ከሩቅ ያያትና ለባለቤቷ ያመለክታል። “ይህችማ እናንተ ያላችኋት አይደለችም” ተባሉ። ለካስ ዓመቴ “ኪኪ” ተብላ ኖሯል የተቀጠረችው!

በሀገረ ፈረንሣይ የሚታተም አንድ የሊዮን ቤተሰባዊ መጽሔት በአህጉረ አሜሪካ ከሚገኙ ሰዎች በቀር በምድረ አውሮፓ ያሉ ተጓዳኞች ፍቅረኛን አቆላምጦ መጥራትን ጥቂት ተወት እያደረጉ መሄዳቸውን በመጥቀስ ጉዳዩ ብዙዎችን እንዳሳሰበ በአንድ ወቅት ማመላከቱ ይታወሳል።

እናም ወደ ጉዳዬ ልመለስና በመሠረቱ “ቁልምጫ” የመውደድ፣ የመለማመጥ፣ የማባባል፣ የማሞካሸት፣ የማወደስ አነጋገር ወይም አጠራር ነው። በርግጥም በአሜሪካ እንደሚታየው ወደ መንበረ ሥልጣኑም ዘልቆ አንድ መሪን አቆላምጦ መጥራት የተለመደ ሲሆን፤ ይህ ባህል ግን  በአውሮፓ እምብዛም አልተስተዋለም። በኮስታራነታቸው የሚታወቁት ወግ አጥባቂዎቹ እንግሊዞች በመጠኑ በአደባባይ ሲሞካሹ መታየታቸው ባይቀር እንኳ፤ ሲቆጡም ከዜማ መሰል የአነጋገር ስልታቸው በዘለለ ፊታቸውን ለማጨማደድ በብርቱ የሚሳናቸው ፈረንሣዮች፤ በአንፃራዊ መልክ እጅግም በአደባባይ ሲቆላመጡ ወይም ሲያቆላምጡ አይታዩም።

በፈረንሣይ ታትሞ ለገጸ-ንባብ የበቃው ቤተሰባዊ መጽሔት ግን ይበልጡን ያተኮረውና አሳሳቢነቱን የገለጸው በተጓዳኞች የእርስ በእርስ አጠራር ነው። ይህ ደግሞ እንዲሁ ያለአንዳች ምክንያት እንዳልሆነ ልንገነዘብ ይገባናል። አንድ ተመራማሪ ያደረበትን ስጋት ሲናገር እንዲያው ለመናገር ሲል ብቻ አይደለም የሚናገረው። ይህን ልብ ማለት ያሻል።

በአደባባይ ዘወትር የሚደሰኮሩት፣ አንዳንዴም “ፍልስፍና አከል” የሆኑት “ኦፊሲዬላዊ ዘይቤዎች” የሚባሉት የአነጋገር ዘዬዎች በፍቅር ጭውውት፣ በወሲባዊ ግንኙነት ሰዓት ዋጋ ቢሶች ሊሆኑ እንደሚበቁ መገንዘብ ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል “አንተ! አንቺ!” ብለው በትዕዛዝ አከል ቋንቋ ጠርተው ለጭውውት የሚጋብዙትና “አንቺዬ፣አንተዬ” ብለው እንደ ነገሩም “የሸነገሉት” ሰው ፈጽሞ አንድ አይደሉም።

የሥነ ልቡናና የሥነ አእምሮ ሊቃውንት እንደሚያስረዱት የአንድ ሰው አጠራር ሁኔታና መልክ ያ የተጠራው ግለሰብ ለተጠራበት ጉዳይ በሚኖረው አስተሳሰብና ምላሽ አሰጣጥ ላይ የተለየ ትርጓሜ እንዲጨብጥ ያበቃል።

በሌላ በኩል ደግሞ የጠሪውን ፍላጎትና አካሄድ፣ ዝንባሌና አቅጣጫ በማወቅ ረገድ “አጠራር” ሲባል እራሱ ዓይነተኛ ጠቃሚነት ብቻ ሳይሆን ዓይነተኛ ጠቋሚነትም እንዳለው ጠበብት ሳያሰምሩበት አልቀረም። ምክንያቱም አቆላምጦ መሳደብ፣ አሞካሽቶ መደባደብ እጅግም ሊታይ የሚችል አይደለምና፤ ለምሳሌ “ፍቅሬ!” ብሎ ወዲያውኑ ደግሞ “የትአባክ” ማለቱ ይቸግራል። እንደ ሊቃውንት የፍተሻ ሰነዶች አገላለጽ በተለይ ባልና ሚስት የሚጠቀሙባቸው የቁልምጫ አጠራሮች መልካቸውን ለወጥ አድርገው ሲገኙ በባል ወይም በሚስት ላይ አንድ የሆነ፣ በአሉታዊ ገጽታ የደነደነ ነገር መኖሩን የሚያመለክቱ ይሆናሉ።

በዛሬ ጊዜ አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር የሚታይ ባለመሆኑ የ“ተረት” ያህል ለመወራት ዳርዳር አለው እንጂ ባልና ሚስት እርስ በእርሳቸው “አቶ እገሌ፣ ወይዘሮ እገሊት” በመሰኘት አንዱ ሌላውን የትዳር ተጓዳኝ በእነርሱ አስተሳሰብ በ“አክብሮት” ይጠራ ነበር። ይሁን እንጂ ይህን መሰል ይድረስ “በአክብሮት ላይ የተመሠረተ ፍቅር” ብለው ሽንጣቸውን ገትረው የሚሟገቱ ዛሬም አንዳንዴ ባይጠፉም አንዱ በሌላው ላይ የተወሰነ፣ ጊዜያዊም ሆነ ዘላቂ ቅያሜ ቢኖረው ያ ተጠሪው ፈጥኖ ለማወቅ የሚችልበት ብልኃት የለውም። ወትሮውንም በቁልምጫ ሲጠራሩ የኖሩ ከሆነ ግን አሞካሽቶ መጥራቱ ሲቀር ወዲያውኑ “አንድ ነገር” እንዳለ ፍንጭ ይሰጣል። ቁልምጫው በሚቀርበት ጊዜ ኩርፊያውም ተከትሎ ብቅ ይላል። እንዲህም ሲሆን ያኔ “ሁሉም ነገር” ታወቀ ማለት ነው።

ጊዜ ያዘመነው የሥልጣኔ አኗኗር ምስጋና አይነፈገውና እራሱንም ከአንዳንድ “እዚህ ግባ” ከማይባል ውዳሴ-ከንቱ ያነፃ ሰው ሁሉ “አበጀህ” የመሰኘት ዕድል ይደርሰውና ዛሬ ለወጥ ብሎ ስናይ ደስ ይለናል። በኢትዮጵያችን ቀደም ባለው ጊዜ የነበረውን የባልና ሚስት የእርስ በእርስ አጠራር ዘዬ ጥቂት ዘወር ብለን ብንቃኝ ባል “ጌቶች” ተብሎ የባሪያ አሳዳሪ ያህል ይጎበደድለታል። ሚስት ደግሞ ዕድለኛ ከሆነች “የማሞ እናት” ተብላ ትጠራለች። ይህን መሰሉ አጠራር “የትዳር ባልንጀርነት ምስክር ነው” ብለው የሚሟገቱ ካሉ አባባላቸው የተሳሳተ መሆኑን ሊረዱ የተገባ ይመስለኛል።

ባሕር ማዶኞቹም እንዲሁ በዛሬም ዘመን ሳይቀር “ዳድ! ማም!” በመባባል ሲጠራሩ ይደመጣሉ። ያው “የማሞ አባት፣ የማሞ እናት” ከሚለው በብዙው መልኩ ተመሳሳይነት አለው። ባሕር ማዶኛም የሚጠቀምበት፣ ኢትዮጵያዊም የሚገልገልበት፣ ይህን መሰል የአጠራር ፈሊጥ ለማለፊያ ውሕደት እማኝ ሊሆን እንደማይችል በሳሎች ያመለክታሉ። “ምክንያት” ተብሎ በሚጠየቅበት ጊዜም በጉዳዩ የጠለቀ ፍተሻ ያካሄዱ ተጠባቢዎች ተገቢ ምላሽ አላጡም። “ይህን መሰሉ አጠራር የትዳር ዋስትና ፍቅር ብቻ ሳይሆን የልጅንም በጠለፋ ዋስትና መቅረብ የሚጠቁም ነውና!” በማለት እንዲህ ዓይነቱን አባባል በጽኑዕ እንደማይደግፉት ያሰምሩበታል።

የአጠራር ፈሊጥ እንደ ቋንቋውና እንደ አኗኗሩ ሥርዓትና ባህል ከሀገር ሀገር የተለያየ መሆኑን መገንዘብ የሚያቅት አይመስለኝም። ነገር ግን ባህልና ወጉን ተከትለው፣ ጊዜ በወለደው፣ ወቅት በፈቀደው ሥልጣኔ አዘምነው የራሳቸውን ቋንቋ ማደርጀት፣ መልካሙን ከመጥፎው ለይቶ ማበጀት ሲገባቸው የሰውን ሀገር ቋንቋ እንዳለ ወስደው ለመደረት፣ በነጠላ ላይ ኪስ ለመስፋት የሚመኙ፣ ባህልና ወግ እንደሌላቸው ሆነው የተገኙ መኖራቸውን በምናይበት ጊዜ ደግሞ በውኑ እጅግ አሳዛኝ ሊሆን ይበቃል። ይህ ሁኔታም በአዳጊው ክፍለ አህጉር ብቻ ህልውናውን ያስመሰከረ አይደለም። እንደ ኋላ ቀሩ ሕዝብ መጠኑ ሚዛን አይድፋ እንጂ በሚገርም አኳኋን “አድጌአለሁ፣ ጎልምሼ  ጨርሻለሁ” ባለው በአውሮፓውም አህጉር ሳይስተዋል አልቀረም።

ለምሳሌ ጥቂት ቆርፈድፈድ በማለቱ “የወታደር ቋንቋ” የመሰኘት ቅፅል ከተሰጠው ከሻካራው ጀርመንኛ ቋንቋ ይልቅ ለስለስ በሚለው በወዛሙ ፈረንሳይኛ ቋንቋ ፍቅረኛቸውን የሚጠሩ አሉ። ቋንቋውን አዳቅለው ያለሰለሱም በቁጥር ያነሱ አይደሉም። “ለምን አዳቅለው አለሰለሱ” ወይም “ለምን የራሳቸውን ትተው የሰው ቋንቋ ተዋሱ” እያሉ ምሁራን በየወቅቱ ሲከራከሩ ከርመዋል። ለሙግቱ መፍትሔ ግን አልተገኘም።

የእኛን አማርኛ ለምሳሌ ያህል ብንወስድ እንኳ አዳብሮ፣ አደርጅቶ ጥቂት መስመር ማስያዝ ብቻ ይቀረን እንደሆነ ነው እንጂ ለዛ ያላቸው የተዋቡ ቃላት ሞልተውናል። ግና እነዚህን ማራኪ ቃላት አዳብረን፣ አደርጅተን ስንጠቀምባቸው እንገኛለን? በቃላቱ የሚገለገሉት ለመሆኑስ እነማን ናቸው? ለዚህ ምላሹ አጭር ነው። ይኸውም በራስ ቋንቋ መጠቀምን እንደ “መሐይምነት” የምንቆጥር አልጠፋንምና!! ይህን አንቀበልም ብንል ከእውነት መሸሽ ይሆንብናል።

ዘፋኞች የሚጠቀሙባቸው ለዛ ያላቸው መልካም ቃላት ከኪነ-ጥበቡ መድረክ ውጪ ወደ ፍቅረኞች አምባ አልዘለቁም። ብዙዎቹ ቃላት ከጭራ ግርፍ ማሳመሪያነት አልፈው አልሄዱም። ዘፋኝ ብቻ እንዲጠቀምባቸው ሌላው የኅብረተሰብ ክፍል ዘወር ብሎም እንዳያያቸው የሕግ ማዕቀብ የደነደነባቸው ይመስል በዚያው ተገድበው የቀሩ መሆናቸውን ዕናያለን። በተለይ በባህል ተጫዋቾች ዘንድ ያሉት ወዛም ቃላት በአዝማሪ አንደበት ብቻ መወሰናቸው የሚያሳዝን እንጂ የሚያስደስት ሊሆን አይበቃም።

ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የባህሉ፣ የቋንቋው፣ የአኗኗሩ፣ የሥርዓቱ ምንነት እንደተጠበቀ ሆኖ ያን ፈጽሞ በማይጎዳ አኳኋን ሀገራዊው ዕድር በሚፈቅደው መሠረት አበጃጅቶ፣ አመቻችቶ መጠቀም የሚቻል ይመስለኛል። በርግጥ ፈረንጆች “ዳርሊንግ፣ ስዊት ኸርት፣ ሃኒ፣…” የሚሉትን በቀጥታ እንደ ወረደ ተርጉሞ “ማሬ፣ ስኳሬ፣…” ብሎ ለማቆላመጥ መጣሩ ስሜት የሚሰጥ አለመሆኑን እናውቃለን። ምናልባትም ጥቂት የቧልተኝነት፣ የአሿፊነት መልክ ያለበት መስሎ ሊታይም ይችል ይሆናል። “ስሜት” ስል የራሴን ስሜት ከቋንቋው ጋር አዛምጄ አቀረብኩ እንጂ ምናልባት ሲለምዱት ተቀባይ ያጣል ማለትም ላይሆን ይችላል። ሁሉም የእኔን ስሜት ይጋራ ማለትም አልችልም። ወይም ደግሞ የእኔን ስሜት ለጊዜው ይዋስም አልልም። ስሜትን ማከራየት አይቻልምና!!

ይሁንና በየወቅቱ ከዘፋኞቹ አንደበት የሚንቆረቆሩት ዜማዎች አሉ። እንደ “ሰውነት፣ አካላት ገላዬ፣ ገላ ሰው፣ አካሌ፣…” የመሳሰሉትን መጥቀሰ ይቻላል። እነዚህን አባባሎች ወስዶ ለፍቅረኛ መጥሪያ መገልገል የሚቻል ይመስለኛል። “የምወድህ የምወድሽ” መባባሉም መስተፋቅርነቱ የሚናቅ አይመስለኝም። ይህ ሲባል ግን ከልብ ለሚናፈቀው ከአንጀት ለሚፈቀረው ብቻ መዋል ያለበት እንጂ ዛሬ ለአንዱ ወይም ለአንዷ፣ በነጋታው ደግሞ ለአንዱ ወይም ለአንዷ “ፍቅረኛ” ወይም ድርብ ወዳጅ እየተመጠነ በመቁነን እንደ ድሮው የቀበሌ መኖ በራሺን መልክ የሚታደል ሊሆን እንደማይገባ ከማለዳው አውቆ መቀመጥ ያሻል።

እኔ እንደሚመስለኝ ቁልምጫው ከአዝማሪ እንጉርጉሮ አልፎ ወደ ትዳሩም ዓለም መግባት ይገባዋል። እንደ ሰውነት አካላት፣ ገላዬ፣ ገላ ሰው፣ አካሌ፣… ያሉትና ሌሎችም።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top