መጽሐፍ ዳሰሳ

“ሩህናማ” የአምባገንኑ መሪ ምርጥ የፍልስፍና መጽሐፍ

ዓለማችን በርካታ አምባገነን መሪዎችን አፍርታለች። በአስገራሚ ተግባራቸው ጎልተው ከሚጠቀሱ መሪዎች አንደኛው የቱርክሜኒስታኑ ፕሬዝዳንት ሳፖርሙራት ንያዞቭ እንደሚሆን አይጠረጠርም።

ይህ ሰው በዕድሜ ልክ ማአረግ ሀገሪቱን ከ1985 እስከ ሞተበት 2006 ድረስ መርቷል። በዚህ ቆይታው ውስጥ የሚያስደነግጡም የሚያስገርሙም ተግባራትን አከናውኗል። የራሱን ስም ቱርክሜንባሲ ወይም የቱርከሜን መሪ የሚል ስያሜ ካሰጠ በኋላ የቀን መቁጠሪያን መቃኘት ጀመረ። አንድ ሃሳብ ፈለቀለት፤ ጥር የተባለውን ወር በራሱ ስም የመተካት። ግኝቱ አሪፍ ስለነበር ቀጠለበትና ሚያዚያን ጉርባንሶልታን አለው – በእናቱ ስም። መስከረምን ሩህናማ ለማለት አላመነታም – ባሳተመው መጽሐፍ ስም። በመንፈሳዊ መሪነቱ እና በፍልስፍና ነክ ግጥሞቹ የሚታወቀውን ማግቲሙሊ ለመዘከር ይረዳ ዘንድ በስሙ የሽልማት ድርጅት ካቋቋመ በኋላ ምርጥ የቱርክሜን ገጣሚ እኔ ነኝ ብሎ በቀኝ እጁ ለግራ እጁ ሽልማት ሰጠ። በጣም አጫሽ ነበር- በ1997 ማጨስ እንዳቆመ ግን በሀገሪቱ ውስጥ ማጨስን/ በህዝባዊ ቦታዎች/ የሚከለክል ህግ አወጣ። ከተማ ውስጥ የሚታዩ ውሾች ሽታቸው ደስ አይልም በሚል ሰበብ ውሻ ማሳደግን ከልክሏል። ሴቶች ራሳቸውን በማስዋቢያ ነገር እንዳይጠቀሙ አግዷል፣ ምነው ሲባል የቱርክሜን ሴቶች በተፈጥሮ ውብና ሳቢ በመሆናቸው። አንድ የውጭ ሀገር ዜጋ የሀገሪቱን ሴት ማግባት ከፈለገ በቅድሚያ መንግስትን ለስነስርዓቱ ለማስፈቀድ 50 ሺህ ዶላር መከፈል እንዳለበትም በላዩ ላይ አክሎበታል። ሽልማት ያገኘው መጽሐፍ በየትምህርት ቤቱና ቤተ-መጻህፍት ውስጥ እንዲቀመጥ የተደረገ ሲሆን ተማሪዎችም እንደ አንድ የትምህርት ኮርስ የግድ እንዲያነቡት ተድርጓል። ሰዎች መንጃ ፈቃድ ሲያወጡና ስራ ሲቀጠሩም ከመጽሐፉ የወጣ ጥያቄ መመለስ ይኖርባቸዋል። ፕሬዝዳንቱ በአንድ ወቅት በመንግስት ቴሌቪዥን ብቅ ብሎ መጽሐፉን ከጫፍ እስከ ጫፍ ለሶስት ግዜ ያነበበ ሰው መንግስተ ሰማያት የመግባቱ ጉዳይ አውቶማቲክ መሆኑን ገልዿል። በከተማዋ መሃል 50 ጫማ ቁመት ያለው የመጽሐፍ ሐውልት የተገነባ ሲሆን ልክ ከምሽቱ 2 ሰዓት ጀምሮ ሐውልቱ እየተከፈተ ከመጽሐፉ ገጽ የተቀነጨቡ ንባቦች ይታያሉ። ለመሆኑ እንደዚህ የተንቆጠቆጠ ክብር የተሰጠው ሩህናማ ምንድነው? ሩህናማ የነፍስ መጽሐፍ እንደማለት ነው። አምስት ክፍሎች ያሉት ሲሆን ፍልስፍና፣ የህይወት መመሪያ፣ መንፈሳዊና ሞራላዊ ስብከቶች፣ ታሪክና ግጥምን አካቶ የተሰራ ነው። በክፍል አንድና ሁለት የቱርክሜን አፈጣጠር እና የሀገሪቱ ታሪክ በዝርዝር ተጽፏል። ረጅም የዘር ግንድ ተዘርዝሮ ያየሁት በመጽሐፍ ቅዱስ ኦሪት ዘፍጥረት ነው።

ሩህናማን ስታዩ ደግሞ የስርወ መንግስቱ ብቻ ሳይሆን የቱርክሜን ቤተሰቦች የዘር ግንድ እንደ አባይ ወንዝ በርካታ ገጾችን እያቆራረጠ ሲፈስ ትመለከታላችሁ። በክፍል ሦስትና አራት ህዝቡ ስለሚጠበቅበት ግዴታና ሃላፊነት እንዲሁም ሰለ ጥንታዊቷ ሀገር መሪዎችና የአስተዳደር ስልት ይተርካል። ክፍል አምስት መንፈሳዊውን ዓለም ያስታክ እንጂ የጸሐፊውን ፍልስፍናም በጥልቀት የሚመረመርበት ነው። ፈገግታ ካለህ ጠላት አይኖርህም፣ ሞት እንኳ አፍጦ ቢመጣብህ ፈግግበት፣ ሳይነካህ እንደሚሄድ አምናለሁ። ፈገግታ ነፍስን ይከፍታል፣ እርካታና መዝናናትን ይፈጥራል። የውቅያኖስ ንፋስ ጭጋግን እንደሚበታትነው ሁሉ ፈገግታም ውስጥህ ያለውን ሀዘንና ጥላቻ ይገፋል። ለባህር ማዕበል፣ ለመሬት ቀዝቃዛ ንፋስ ፈገግታቸው ነው። ባህር በንፋስ ላይና ታች እያለ ካልተጫወተ ውበቱን ያጣል፣ ሃይለኛ ሽታም ይፈጥራል። የሰው ልጅም መጥፎ ጠረን የሚጸዳው በፈገግታው ነው። እናም ለዓለም ሳቅ። ወርቅን ሳይሆን መሬትን ግዛ … ውሃ አባትህ ነው፣ መሬት እናትህ … አፈር ያንተ ገላ ነው ፣ ሰማይ ደግሞ ነፍስህ … ምንም እንኳ አናትህ ሰማይን ቢነካ መሬትን አክብር የሚለው ሳፖርሙራት በእናትና አባት ዙሪያ ያሉት የፍልስፍና ተረኮች የሚመስጡ ናቸው። በእሱ አፍ ልተርክላችሁ፣ አባት ወንድ መውለድ በመቻሉ  አላህን ማመስገን ይኖርበታል። በወላጅነቱ ባለ ዕዳ በመሆኑ በጥሩ መንገድ ያድጉለት ዘንድም መጸለይ አለበት። በርግጥ  ወጣቶች በራሳቸው መንገድ እንዳደጉ በማሰብ ሲሳሳቱ ይታያል። የወላጆቻቸውን ጭንቀት የሚያውቁት አግብተው ልጅ የወለዱ ግዜ ነው። የዕድሜ እርከን ሲፈተሽ  ሰለ አባታቸው ያላቸውን እንግዳ ባህሪያት መረዳት ያስችላል። የአምስት ዓመት ልጅ አባቴ ሁሉን ነገር ያውቃል ይላል። የአሰር ዓመት ልጅ አባቱ ብዙ ነገር እንደሚያውቅ ይሰማዋል። የ 15 ዓመት ልጅ እንደ አባቴ አውቃለሁ ባይ ነው። የ20 ዓመቱ ጌታ እንደ እውነቱ ከሆነ አባቴ ምንም አያውቅም ነው የሚለው። ሰላሳ ሲደርስ አባቴ ጥቂት ሳያውቅ አይቀርም ይላል። አርባ ዓመት ሲሆን አባቴን ባማክረው እንዴት ጥሩ ነበር ማለቱ አይቀርም። አምሳ ሲደርስ ግን አባቴ ሁሉን ያውቃል ሲል ያስረግጣል። ስልሳ ከደረሰ አባቴ በህይወት ቢኖርና ስለ አንዳንድ ነገሮች ማማከር ብችል በህይወት ያደረገውን ሁሉ አመሰግነው ነበር ከማለት ይደርሳል። …ልጅ ሲፈራና እርዳታ ሲፈልግ የሚያለቅሰው እማዬ እያለ ነው። ሲያድግ የአባቱን ድጋፍ ይፈልጋል። በቱርክሜን ባህል አባት የጥበብ፣ የአመክንዮ፣ የጀግንነት፣ የቁጣና የፍትህ ምሳሌ ነው። አባት ልጁን ሲያሳድግ ይህን አድርግ፣ ያንን አታድርግ በማለት ሳይሆን የሚፈልገውን ነገር በተግባር ያሳያል። አባት ከልጁ ጋር የሚያወራው በዐይኑ አማካኝነት ነው። በአንድ ውቅት የቸገራቸው አባትና ልጅ ሲሰርቁ ተይዘው ፍርድ ቤት ቀረቡ። በጥፋታቸውም አርባ ጅራፍ እንዲገረፉ ታዘዘ። አባት አርባ ጅራፍ ጀርባው ላይ ሲያርፍና በደም ጎርፍ ሲጥለቀለቅ ህመሙን የሚያሳብቅ ለቅሶ አላሰማም። ልጁ መገረፍ ሲጀምር ግን «ወይኔ ልጄ አይሆንም !» እያለ መጮህ ጀመረ። ይህን የሰማው ሱልጣን አርባ ጅራፍህን ስትጠጣ ቃል አልተነፈስክም ነበር፣ አሁን ምን ይሁን ብለህ ነው የምታለቅሰው ብሎ አፈጠጠበት “የተከበሩ ግርማዊነትዎ እኔ ስገረፍ ጅራፉ የሚነካው ስጋዬን ብቻ ነበር፣ ልጄ ሲገረፍ ግን ህመሙ ውስጤ ዘልቆ ገባ” ሲል መለሰ። ሱልጣኑ በመልሱ ተደስቶ እንዲህ አይነት አባት በሌብነት አይከሰስምና ፈታችሁ ልቀቁት ሲል ትዕዛዝ አስተላለፈ። … በማኅበረሰቡ ውስጥ ለአንተ መሰረት የሚሆነው አባትህ ነው። ሰዎች ያንተን አስፈላጊነትና ዋጋ በቅድሚያ የሚመዝኑት አባትህን በመገምገም ነው። እናም አባትህን በሌሎች ፊት አታሳፍረው።

አንተ የአባትህ ወራሽ ነህ። ሐብት ብቻ አይደለም የምትወርሰው፣ ዝናውን ወይንም ክብረቢስነቱንም ጭምር እንጂ። የአባት ቅርስ ለልጆች ሁሉ እኩል የሚከፋፈል ነው፣ ነገር ግን ለአንተና ለወንድምህ የሚያስተላልፈው ስልጣን የማይካፈል ነው። መቼም ቢሆን አባትህ ማን እንደሆነ እንዳትረሳ። ሌሎች ከአባቱ ይሻላል ሲሉ የምትኮራ ሌሎች እንዳባቱ አይደለም ብለው ሲያጣጥሉህ  አንገትህን የምትደፋበት መሆን የለበትም። መቼም ቢሆን ከእሱ አንዲት ጠብታ ውጪ ያልተፈጠርክ መሆኑን መርሳት የለብህም። እሱ አባትህ ካልሆነ አንተ ህልውና የለህም። እሱ ባይሆን ኖሮ አንተ አትፈጠርም ነበር። ያንተ ህልውና መሰረት የአባትህ ህልውና መሰረት ነው። ያንተ አባት ያንተ ራሱ ቀድሞነት ነው። ቱርኩሜኖች እንደሚሉት አባትህ ውሻ ከሆነ፣ አንተም ምግብህን በውሻ ማቅረቢያ ዕቃ ተጠቀም። …ህይወት መኖር ሲሆን ሞት አለመገኘት ነው። አለመኖር አንድ ሲሆን ህልውና ሶስት ደረጃዎች አሉት። አንተ ራስህ ተጨባጭ ህላዌ ነህ… ልጅህ የነገ ህይወት… አባትህ ደግሞ የትናንት መኖር። ድንገት ሞት ይመጣል። አንተ ከሶስቱ አንደኛውን ካልሆንክ ከሞት ጋር የምታደርገውን ጦርነት አታሸንፈውም። አባት አይሞትም፤ በልጆቹ ነፍስያ ውስጥ ይኖራል። እኔ ወጣትነትን ካለፍኩ በኋላ ይህ ስሜት በጥቂቱ ተሰምቶኛል። ሁሉም የበሰለ ሰው ይህ ስሜት ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ ። አንዳንዴ እኔ የራሴ ሳልሆን የአባቴ እንደሆንኩ ይሰማኛል። በእጆቹ የምነካ፣ በእግሮቹ የምራመድ፣ በአንደበቱ የምናገር ይመስለኛል። የአባቴ ባህሪ በእኔ ውስጥ ህይወት የዘራ ያህል ሆኖ ይሰማኛል። እናም ለአባት ትልቅ ክብር ያስፈልገዋል። እናት ቅዱስ ፍጥረት ናት። አንዳንዶች እናት ቅዱስ መሆኗን የሚረዱት በህይወት ካጧት በኋላ ነው። ቱርኩሜኖች እናት ምን ያህል ለልጇ ውብ ፍጥረት መሆኗን የሚገልጽ አባባል አላቸው ‘አባት ከሌለ የሙት ልጅ፣ እናት ከሌለች ምርኮኛ ነኝ› እንላለን። የሙት ልጅ የሚባለው ቃል የቁሳቁስ ፍላጎት አለመሟላትን ነው የሚያሳየው። ምርኮኛ የሚለው ቃል ግን መንፈሳዊ እጦትና ድጋፍ አለመኖርን ያሳያል። ምርኮኛ ሆንክ ማለት ከትውልድ ሀገርህ ተጥለህ በሁሉም ዓይነት ችግሮች ተሰቃየህ ማለት ነው። ዓለም ለምርኮኞች ጨካኝና ኮምጣጤ ነች። ለዚህም ነው የሙት ልጅ ከምርኮኛ ይሻላል የምለው። አባት ለልጁ የማያቋርጥ ጥረት ያደርጋል፣ እናት ግን ልቧን ነው  የምትመግበው። ልብ ውስጣዊ ስሜትና ሰብዓዊነትን ይወክላል። ቱርኩሜኖች እናትና ልብ የሚባሉትን ቃላት የሚያገናኙት ቅዱስነት ከቁሳቁስ ጥቅሞች ጋር ያልተያያዘ መሆኑን ለማሳየት ነው። ልጅ የአባቱ የአካል ክፋይ ሲሆን ከእናቱ አንጻር ግን የልቧ ክፋይ ነው።

ዕድል በእኔ ላይ ሁለት ህመሞችን ደንግጋለች። የሙት ልጅም ምርኮኛም  ነበርኩ። ይህን ጣምራ ስቃይ የሚያውቀው የተጋፈጠው ብቻ ነው። እንደ እኔ እምነት በርካታ ህመሞች የቁሳቁስን ፍቅር ፈላጊ ናቸው። ልብን የሚሰማው ስቃይ ግን ከአካላዊው ጥቃት በእጅጉ ስለታም ይሆናል። አካላዊው ጉዳት ይቀዘቅዛል፣ የልብ ግን ተጓዥ ነው። ሁሌም የሚደማ ሁሌም ከተጎጂው  ጋር የሚቀር። አባት ሲሞት የቁሳቁስ ችግር ያጋጥማል፣ እናት ስትሞት ግን የፍቅር እጦት ያስጨንቃል። ምድር ላይ ላለነው ሁሉ የመጀመሪያ መኖሪያችን ወይም ሀገራችን እናት ናት- የእናት ማህጸን። የእናት ጭን ሁለተኛው መኖሪያ ነው- ቋንቋ የምንማርበት። ርህራሄ የሚጀምረውም ከሞቃታማው የእናት ጭን ነው። የእናት ተንከባካቢው እጅ ደግሞ ከልጅነት ወደ እውቀት የሚደረገውን የዕድገት መንገድ ያደላድላል። በአጠቃላይ ለርህራሄ ውጤት የሆኑት ማህጸን ፣ ጭንና እጆች ናቸው። …ቅዱስና የማያሰጋ ቦታ ይፈልጋል። ለዚያም ነው አላህ ወደ ዓለም የሚመጣውን ፍጡር በእናት ማህጸን እንዲፈጠር አድርጎ ቅዱስነቷን ያሳየው። ምንም ዓይነት ነገር ቢያጋጥም እናት ከልጇ ጋር በፍቅርና ርህራሄ ትኖራለች። ቁርኝቷና መስዋእትነቷ በፍጹም የሚቋረጥ አይደለም። እናት ልጅን በከባድ ስቃይና ምጥ ነው የምትገላገለው። አንዳንዴ ታዲያ ክፍተኛ አደጋ ያጋጥማል። ማዋለጃ ክፍል የሚሰራ አንድ ዶክተር እንዳጫወተኝ የምጡን አደገኛነት የሚረዱ እናቶች ልጄን አድኑልኝ እንጂ ለእኔ አትጨነቁ ነው የሚሉት። አንዲት ነፍሰ ጡር እናት በጎረቤቴ ግቢ ውስጥ የተንዥረገገውን አፕል ለመብላት ጓጓች። ቅርርብ ስላልነበራት ግን መጠየቅ አልፈለገችም። ገዝታ እንዳትበላ ደግሞ ገንዘብ አልነበራትም። ወዲህ ወዲያ እያለች ብዙ አሰበች፣ ሆኖም የኔ ያልሆነው ሁሉ ለእኔ አይገባም በሚለው አቋሙ ጸናች። ልጁ ተወልዶ ካደገ በኋላ ታዋቂ ገጣሚ ሆነ። አፕሉን በተመለከተም አንድ ነገር ጽፎ ነበር ‹የጎረቤቴ አትክልት ስፍራ አፕል ለማፍራት በጣም ለም ነው። አንዳንድ ግዜ አፕሉን ለመብላት እፈልግና አላደርገውም። ምክንያቱም የእናቴን ነፍስ መጉዳት ስለማልፈልግ› የሚል። ቱርኩሜኖች እውነተኛው እንባ የእናቶች ብቻ ነው ይላሉ። እናቱን የሚያከብር በህይወቱ ውጤታማ ይሆናል። …አንዳንድ ትችቶች ደራሲው መጽሐፉን ለራሱ ግለሰባዊ አምልኮነት እንደተጠቀመበት ጽፈዋል። በተለይ አንዳንድ ግጥሞቹ ከሌሎች የተወሰዱ መሆኑንና ቱርክሜንስታን የ 5 ሺህ ዓመት ባለጸጋ መሆኗ የማይታመን እንደሆነ በማስረዳት።

በእኔ እምነት ታሪካዊ መረጃዎቹን መመጠን ስላልቻለ አሰልቺነት ፈጥረዋል። ርእሰ ጉዳዮቹም በሚፈለገው መጠን ተደራጅተው አልቀረቡም። ምናልባትም ስራውን ሌሎች እንዲያሹለት የሰጠ አልመሰለኝም። እዚህና እዚያ የሚረግጡ ሀሳቦችን በአርትኦት መስመር ቢያሲዘው የተሻለ እንደነበር ይሰማኛል። በአጠቃላይ ግን ግራ ነገር መስራት ከሚያረካው መሪ እንዴት ይህ ስራ ፈለቀ ማለቴ አልቀረም። ሩህናማ ከፕሬዝዳንቱ አምባገነንነት የተለየ ገጽታ ይዞ ነው ያገኘሁት። ከሶሻሊስት ካምፕ ፈልቆ ያለፈውን የሀገሩን ታሪክ ለማጠልሸት አልሞከረም። ቀድሞ ለነበሩ መሪዎች ትልቅ ክብር በመስጠት ስራቸውን ሲያጎላ ይታያል። ሀገራቸውን ጠብቀው ያቆዩትን፣ ሀገር ተረካቢው ትውልድ እንዲያከብር፣ እንዲያፈቅርና አበልጽጎ እንዲቀጥል ነው በትህትና የሚሰብከው። ለፍቅርና ለሰላም ያለው አስተሳሰብ ፍጽም ታላቅ ነው። ሰዎች እንዲደሰቱ፣ እንዲስቁ፣ እንዲከባበሩ፣ ሃይማኖታቸውን ጠብቀው እንዲቆዩ ምን ማደረግ እንዳለባቸው ነው የሚጎተጉተው። ለተፈጥሮ፣ ለእጽዋት፣ ለወላጆችና ለመልካም አስተዳደር ያለው ቅንነት እዚህና እዛ ተፈነጣጥቆ እንመለከታለን። ሁኔታዎችን በንፅፅር፣ በተቃርኖና በምልሰት የሚገልጽበት የፍልስፍና ምልከታው ጥልቅ ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top