አድባራተ ጥበብ

መንዙማ እና ኪነ-ጥበብ

የምትከተላቸውን ሃይማኖቶች በቀደምቶቹ ነቢያት የተሰበከች ሀገር ናት ኢትዮጵያ። ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ አጥምቆ ክርስትናን ሰብኮ የላከው ከመጀመሪያዎቹ ነቢያት አንዱ ነው። ነቢዩ መሐመድ እስልምናን ከማስፋፋታቸው በፊት የምእመናኑን ህይወት ከሞት ጠብቀው፤ የአማኞችን ቁጥር ያበዙት ወደ ሀበሻ ንጉሥ አስሐባዎችን ልከው ነበር። ከዓለም ቀድመው እስልምናን ከተቀበሉት ዋነኞች ተርታ የምትነኝ ሀገር ህዝቦች ነን። ቀድማ እስልምናን የተቀበለችው እሙ አይመን ኢትዮጵያዊት ናት። የአዛን ጥሪን ለዓለም ያስተማረው ቢላል የሐበሻ ደም ያለው ቆራጥ አማኝ ነው።

ኢትዮጵያ የሁሉም ሃይማኖቶች ቀደምት መኖሪያ ትሁን እንጂ፣ ተቀባይ ብቻም አልነበረችም። የተቀበለችውን ከማንነቷ ጋር ቀይጣ የራሷን ቀለም ትሰጠዋለች። የሐበሻ ሙስሊም የራሱ ቀለም አለው። የራሱ ብቻ የሆነ፣ ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ብቻ ከቀረው ሙስሊም ወንድሙ የሚለይበት ማንነት አለው። የራስ ብቻ ባህርይ ባለቤት ነው።

መንዙማ የዚህ ነባራዊ እውነት ማሳያ እንደሆነ የሚያምኑ ጥቂቶች አይደሉም። እንደ ሁሉም የራሳችን እሴቶች ሁሉ በቅጡ ካልተጠኑት፣ በትኩረት ካልተመረመሩት መካከል የሚመደበው መንዙማ ‘ኢትዮጵያዊ ብቻ ነው’ ብለው የሚከራከሩ እንዳሉ ሁሉ፤ የለም ሁሉም ሙስሊም የሚጋራው ሀይማኖታዊ ተግባር ነው የሚሉም አሉ። ምሁራዊ ክርክሩን ለመስኩ ባለሙያዎች እና ለእምነቱ ልሂቃን ትተን በመንዙማ እና የመንዙማ ባህርይ ባላቸው የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ዙሪያ ጥቂት ለማለት እንሞክር።

ትርጓሜ

መንዙማ ቃሉ አረብኛ ነው። ‘ነዘመ’ ከሚለው የአረብኛ ሥርወ-ቃል የመጣ ነው። ነዘመ ማለት ገጠመ ማለት ነው። መንዙማ ዝርው ያልሆነ፣ (ግጥም) ማለት ነው። በአረቦች መንዙማ ትምህርታዊ ጉዳዮችን ለማስተላለፍ የሚያገለግል ግጥም ማለት ነው። በእንግሊዝኛ ‹Deductive Poetry› የሚለው ነው። ለምሳሌ ሰዋሰውን ለማወቅ በግጥም ቢጠቀሙ መንዙማ ይባላል።

በሃገራችንም ለነብዩ ሙሐመድ ፍቅር፣ ክብር፣… ማሳያ የሚገጠሙ ግጥሞች ናቸው። አላህን ለማወደስ የሚደረገውም ይካተታል። ደጋግ ሰዎችን ለማወደስ የሚደረገውም በዚሁ የሚካተት ነው።

በአብዛኛው ወንዶች ሲከውኑት ይስተዋል እንጂ ሴቶችም ተሳትፈውበታል። ከከበሮ ወይም ድቤ በስተቀር የሙዚቃ መሳሪያ እንደማያጅበው ደጋግመን ብንሰማም በበገና ሳይቀር የታጀቡ መንዙማዎች መኖራቸውን አጥኚዎች ይገልጻሉ። ባህሩ ሰፊ ነው። ለማወቅ የሻተ ከቆፈረ ብዙ የሚያፍስበት…

ለስለስ ያለ ዜማ ያለው መንዙማ በርካታ መልእክቶች ይተላለፉበታል። ሐይማኖታዊ ትምህርቶች፣ አፈንጋጭን ከስሁት ተግባሩ እንዲታቀብ የሚገስጹ ኃይለ-ቃሎች፣ የማጽናኛ-የማበረታቻ ሐሳቦች ይካተቱበታል። ከበድ ያሉ ሐይማኖታዊ ፍልስፍናዎች እና ነቢዩን፣ ፈጣሪን እና በእምነቱ ትልቅ ቦታ ያላቸውን ለማወደስ ጥቅም ላይ ይውላል።

ስንኞቹ ሙሉ በሙሉ በአረብኛ ቋንቋ የተሰናኙ ሊሆኑ ይችላሉ። የአማርኛ እና የአረብኛ ቅይጥ የሆኑት ግን እጅግ የተለመዱት ናቸው። በተለይ ትንሽ ቀደም ያሉት መንዙማዎች በሀይማኖቱ ላቅ ያለ ደረጃ ለደረሱት የሚተዉ ነበሩ። በቅብብል ይዜማል። ከመሃል ስንኙን የሚደረድረውን ሰው የሚያደምጡት በመቀበል ያግዙታል። መልእክት ካዘሉት ስንኞች የሚከተለውን አዝማች በጭብጨባ እያጀቡ በህብረት ያዜሙታል። አጠር ያሉ ስንኞች አንድን መልእክት የሚያስተላልፉ ከሁለት እስከ አራት የግጥም መስመሮች በመንዙማ ይዘረዘራሉ።

መቼ ተጀመረ?

መንዙማ መች ጀመረ ከማለት ግጥም የሚባለው ጥበብ መች ጀመረ የሚለውን ማየቱ መቅደም አለበት። ግጥም መች ጀመረ ሲባል ደግሞ የሰው ልጅ በምድር ላይ መኖር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ወደማለት እየደረሰ ነው። ግጥም ከሰው ልጅ ጋ አብሮ ረጅም ዘመን ይኖራል።

እስልምና በመካ ከመነሳቱ በፊት አረቦች በግጥም ችሎታቸው በጣም የተደነቁ ነበሩ። በሃገራችን ደግሞ ከእስልምና ወደሀገራችን መግባት ጋር የሚያያዝ ነው። (በጥናት የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም)

በአረቡ ዓለም ጽሑፋቸው ከሃገር ሀገር የሚሸጋገር ‘ማዲሆች’ አሉ። ‘አልወራቂ’፣ ‘’ቡሰይሪ ‘ጦራኢፊ’… የታወቁ ገጣሚያን ናቸው።

ቡሰይሪ ግብጻዊ ሲሆን 13ኛው ክፍለዘመን የኖረ እስከዛሬም ግጥሙ ዘመን ተሻግሮ የመጣ ገጣሚ ነው። የግጥም ስልቱ ‹ቡርዳ› ይባላል።

በነብዩ ዘመን ነብዩን በማወደስ የታወቁ ገጣሚያን ነበሩ እነ ካእብ ኢብኑ ዙበይር፣ ሀሳን ኢብኑ ሳቢት ተጠቃሾች ናቸው።

ስንኞች

መንዙማ አልፎ አልፎ መዝናኛ ነው፤ አንዳንዴ የጸሎት ማዳረሻ ነው፤ ብዙዉን ጊዜ የማኅበረሰብን ሰንኮፍ ማሳያም ነው፤ አንዳንዴ የሃገር ፍቅር መግለጫም ነው።

ብዙዎቹ የመንዙማ ሥንኞች የሥነ-ምግባር ተምሳሌት ተደርገው የሚታሰቡትን ነብዩ ሙሐመድን ያወድሳሉ። አፈንጋጮችን ይገስጻሉ፣ ባሕል ከላሾችን ይኮረኩማሉ።

አቶ ተመስገን ፈንታው መቀለ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሥነ-ጽሑፍና ፎክሎርን ለ12 ዓመታት አስተምረዋል። በመንዙማ ዙርያ የተሠሩ በርከት ያሉ ጥናታዊ ወረቀቶችን አማክረዋል። በአንድ ቃለ-መጠይቃቸው ላይ “ሴት አያቴ በመንዙማ ነው ያሳደገችኝ” ይላሉ።

የክርስትና ሀይማኖት ተከታይ መሆናቸው መንዙማን ከማጣጣም እንዳላቦዘናቸው ሲያስረዱ።

“ወሎ ውስጥ መንዙማ ባሕል ነው። የየትኛውንም እምነት ተከታይ ሁን መንዙማን ትሰማለህ፤ በአንድም ሆነ በሌላ… አያቴ መንዙማን “የእስልምና” ብላ አይደለም የምትረዳው። እሷ የምታውቀው የወሎዬ መሆኑን ነው። መንዙማ ለእሷ ከአምላክ ጋር መገናኛ፣ መታረቂያ፣ መለማመኛ፣ ስሜቷን መተንፈሻ ነው።” ብለዋል።

አንዳንድ የመንዙማ ተንታኞች የመንዙማን ዋጋ ከፍ ሲያደርጉ የእስልምና ምሶሶ ከሆነው ተውሂድ ጋር ያያይዙታል። ‹ላ ኢላ ሃኢለላህ ፣ ሙሐመዱ ነብይ ረሱሉላህ› ነው። አላህ አንድ ሙሐመድ መልእክተኛው ነው ማለት ነው። መንዙማ የሚጀምረው ከዚህ ነው ይላሉ።

ሌላ ገጣሚ በበኩሉ “የአርሹ ባለቤት ማሕሙድ ነው ይህም ሙሐመድ ነው። አላህ ለሙሐመድ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ ከራሱ ስም ቆርሶ ስም ሰጠው እሱ ማሕሙድ ሲሆን ወዳጁን ሙሐመድ አለው።” ብሏል። (ማሕሙድ ማለት ተመስጋኝ ማለት ሲሆን ሙሐመድ ደግሞ ምስጉን ማለት ነው)

መንዙማ በኢትዮጵያ

መንዙማ በኢትዮጵያ በዚህ ጊዜ ጀመረ የሚል መረጃ አልተገኘም። ሆኖም የተስፋፋበት ዘመን ይታወቃል። ከ896 እስከ 1280ዎቹ በሸዋና ዙርያዋ የሙስሊም ሱልጣኔቶች ባበቡበት ዘመን መንዙማ አልፎ አልፎ መታየቱ የጽሑፍ ማስረጃዎች ይገልጻሉ። በይበልጥ ግን ኢትዮጵያውያን ለትምህርት በእግራቸው ወጥተው ሲመለሱ የመንዙማን ባሕል እንዳስፋፉ ተጽፏል።

አቶ ሐሰን ካዎ ግን “ከእስልምና መነሳት ጊዜ ጀምሮ በመካ፣ ከእስልምና ወደ አክሱም መግባት ጀምሮ ነው በኢትዮጵያ መንዙማ የነበረው” ይላል። አቶ አደም ካሚልም በዚህ ይስማማሉ። ወሎ ውስጥ ንጉስ የሚባል ቦታ ከ300 ዓመታት በፊት በሰፊው ተጀመረ ይላሉ። የሃበሻ ቡሰይሪዎች በዚህ ዘመን በዝተው ታይተዋል።፡ ለምሳሌ አንይ ራያ፣ ሸኅ አሊ ጎንደር ተጠቃሽ ናቸው። በወሎ የትምህርት ማእከል የነበረች በመሆኗ ከየአካባቢው በመምጣት ለዓመታት እውቀት ሲቀስሙ የነበሩ ሰዎች በመጨረሻ ሸኽ እየሆኑ ወደየአካባቢው ሲሄዱ መንዙማውን ያሰራጩት ነበር።

እንደ አቶ አደም ካሚል ገለጻ የሃገራችን መንዙማ የትም ሃገር ካለው በቋንቋና በሃሳብ ምጥቀቱ ይለያል። ብዙ ጊዜ አረቦቹን የሚያስገርማቸውም ይኸው ነው። እኛ ቅኝ ባለመገዛታችን ከአረብኛው የተደበላለቀ ቋንቋ ያለው መንዙማ የለንም።

እንደ አቶ ሀሰን ማብራሪያ የሐረር መንዙማ አገባቡ ወሎ ካለው ይለያል ይላል። በሐረር የሚታወቀው ዚክሪ ነው መንዙማ አይደለም። ዚክሪ እራሱን የቻለ ባህል አለው፤ አረብኛና የአካባቢው ቋንቋ ጋር ተቀላቅለው ተጣጥመው የሚባል ነው።

ነባሩ ትውፊት እና ዓለማዊው ኪነ-ጥበብ

ነባሩን ትውፊት ወደ ዓለማዊው ኪነ-ጥበብ ይዘውት የዘለቁም አሉ። ከነዚህ መካከል ኑረዲን ኢሳ አንዱ ነው። በግጥሞቹ ላይ አብዝቶ ተጠቅሞባቸዋል። “ዒሻራ፣ መደድ” በተባሉት የግጥም እና የአጫጭር ልብ ወለድ መድብሎቹ አማርኛን ከአረብኛ ጋር እየቀላቀለ የመንዙማውን ዘዬ በግሩም ሁኔታ ተጠቅሞበታል። አብዲ ሚፍታህም “ኧረ!” በተሰኘው የግጥም መድብሉ ላይ በተመሳሳይ የአረብኛውን ቅልቅል ግጥሞች አስነብቦናል። ላነሳነው ጉዳይ ምሳሌ የሚሆነንን አንድ አጠር ያለ ግጥም ከአብዲ ሚፍታህ ስብስቦች እንመልከት።

ኢክቱብ

ተቀኘሁኝ ብሎ ከፍ ከፍ ብሎ

በጠረፍ ጠባቂ ማማ ላይ ተሰቅሎ

ለካስ ህላዌውን ከልሶ ቢያሰላው

ባለ ቅኔ ሳይሆን ቅኔ ኖሯል እርሱ

በ’ኻሊቁ’ ብእር ‘ምትዘርፍ ነፍሱ!

በግጥሙ ላይ ኢክቱብ እና ኻሊቁ የተሰኙ እንግዳ ቃላት ይገኛሉ። ኢክቱብ፡- ጻፍ ማለት ሲሆን ኻሊቁ፡- አምላክ የሚል ትርጓሜ አላቸው። ከአረብ የተወሰዱ ናቸው። ግጥሙን በምልአት ለመረዳት ተርጓሚ ያስፈልጋቸዋል። በመንዙማው ላይ ግን ተመሳሳይ ጥያቄ አናነሳም የዚህም ምክንያት አብዛኛው ታዳሚ ቢያንስ ቁርአንን የቀራ ስለሚሆን ነው። ይህንን ነባር መንዙማዊ ልማድ ነው እንግዲህ ገጣሚ አብዲ ወደ ዓለማዊ ግጥሞች ያሰረገው።

ተመሳሳይ የአገጣጠም ስልትን የተከተሉ ዘፈኖችም አሉ።

እናቱ ዱበርቲ አባቱ ሼህ ናቸው

አድርገው ያሉትን የሚያደርግላቸው

ነጃ በለኝ ወሎ በል እስቲ ፈርጀኝ

እያሽሞነሞነ ይዋል ሲያበጃጀኝ

ሃና ሸንቁጤ ያቀነቀነችው ይሕ ዜማ የአካባቢውን የንግግር ዘዬ ብቻ ሳሆን ሀይማኖታዊ ስርአቱንም በሚያውቅ ሰው መሰናዳቱ ያስታውቃል። በመንዙማ ዘዬ ይገጠም እንጂ ምቱ የወሎ ነው። እርስዋም ጥሩ አድርጋ ተጫውታዋለች። መዝሙርም አልነው መንዙማ ዋነኛው ተወዳሽ ፍቅር ነው የሚል ይዘት ያለውን ተከታዩን ግጥም ስናደምጥ ደግሞ የፍቅር ባለቤት ፈጣሪ እንደሆነ ሊያስረዳን ሲጥር እናገኘዋለን።

አንዴ በመዝሙሩ አንዴ በመንዙማ

ሲያወድስ ይውላል የፍቅርን ከራማ

የዜማ መነሻቸውን ከመንዙማ ካደረጉት መካከል የቴዎድሮስ ካሳሁንን ማንሳት ይቻላል። ሼመንደፈር

አዛን አለ መስጊድ ልትነጋ ምድር

ልሂድ ሸመንደፈር ልሳፈር ባቡር

በእንግድነት መጥታ ከሸገር ሀረር

ልቤን ይዛው ሄደች ወደ ሩቅ ሐገር

እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂም) መንዙማን መነሻ አድርጋ የሰራቻቸው ዘፈኖች አሏት። የጃን ስዩም ሔኖክ ቢላል ደግሞ አረብኛን ከአማርኛ በመቀላቀል የተሰራ ግሩም ዘፈን ነው። የግጥሙ ደራሲ ሙሉጌታ ተስፋዬ ነው።

ሙሃባ ነው እንጂ ያቀናው ሃገሩን

ጃሂል ገድሎን ነበር አሳክሮት ነገሩን

ኢትዩጵያዊውን ቢላል የሚያነሳሳው የግጥሞቹ ሐሳብ የቢላልን አስተምህሮት ይሰብካል። ሐይማኖታዊውን መልእክት ከሀይማኖት ክልል ውስጥ ያወጣውና ለሰው ልጆች ሁሉ ይሰጠዋል። እንደ መንዙማው ሁሉ በተሰናሰለ ውህደት የማይጎረብጥ የአማርኛ እና የአረብኛ ድቅል ግጥም ነው። ከቁርዓን ያልተጠጋ ወይም ሁለቱንም ቋንቋዎች የማያውቅ አድማጭ በቅጡ አይረዳውም። ይህ ነው እንግዲህ ልዩ ነገር ማለት። የራስን ቀለም በነበረው ሀይማኖታዊ አካሄድ ውስጥ መጨመር እንዲህ ይገለጻል። አረብኛም አማርኛም ያልሆነ ግጥም፤ ነገር ግን የሚጥም

ይላችኋል ቢላል ይላችኋል

ሁሉንም በዙብል ሁሉንም በሃላል

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top