አጭር ልብወለድ

“መቀመቅ”

ዘሬ ዕለቱ ምን እንደሆነ አላወቅም፤ ዕለቱ በቻ ሳይሆን ቀኑ ራሱ ስንት እንደሆነም አላውቅም። ወሩንም ቢሆን ልነግራችሁ አልችልምና እንዳትጠይቁኝ።

ዛሬ ላይ ለመድረስ ያለፍኩበት መንገድ ብዙ ነገሮችን ነጥቆኛል። እርግጥ የማስታወስ ችሎታዬ እንደነበረ ነው። በሆነውና በገጠመው አበሳ ሁሉ አንዳች ሳንካ አልገጠመውም። አልፎ አልፎ በቻ ጥቂት በብዥታ ከተሞሉ ደንገረጋራ ትውስታዎች በስተቀር እያንዳንዷን ሁኔታ በደንብ አስታውሳሁ። ያለ ብዥታና ግርታም ፍንትው ኩልል ብሎ ይታዬኛል።

ታዲያ ለምን ቀኑን ማወቅ ተሳነኝ?… ወሩስ እንደምን ተሰወረብኝ?… ሰዎችን ብጠይቅ በቀላሉ እንደሚገላግሉኝ አውቃለሁ። ግን እጅ የመስጠት ያህል ቀፈፈኝ።

ትውስታዬን ድሮ “መቀመቅ” ሲባል አይገባኝ ከነበረውና ከኖርኩት፣ ኖሬም እንደገና ከመጣሁበት፣… ማዶ ካለው ጊዜ መጀመርን መርጬ እንደምንም ከትራሴ ቀና ብዬ ዐይኔን በስሱ ገለጥኩ። ላላወቅኩት ጊዜ ያህል ከቆዬሁበትና መቀመቅ መሆኑ ከገባኝ ቦታ በከረምኩበት ወቅት ዐይን አያስፈልግ ነበርና ዓይኔን አላዬሁበትም። ስሜትን ኖርኩት እንጂ አልነካሁትም። አሰብኩት አሰላሰልኩት እንጂ አላወራሁትም።… አዎ!… ዐይን ብቻ ሳይሆን አፍም ጆሮም አያስፈልግም ነበር። እና አሁን ፈራ ተባ እያልኩ ዐይኔን በስሱ ገለጥ ሳደርግ በአጥበርባሪ የብርሃን ጎርፍ ተጥለቀለቅኩ… ጎርፉን ልሸከመው ሰላልቻልኩ ከመቀፅበት መልሼ ጨፈንኩት… እና የውጭውን ዓይኔን ጨፍኘ የውስጠኛውን ዐይኔን አበራሁት።
ጊዜው 2012 ወሩ መጋቢት ቀኑ 15 ነበር።

“በቤታችሁ ተወሰኑ” የሚለውን ወቅታዊ ምክር ሰምቼ ከሞላ ጎደል በቤት ሆኛለሁ… እና በመቀመጥ ብዛት እንዳልዝግ ብዬ የዘወትር አካላዊ እንቅስቃሴዬን ሠርቼና ሰውነቴን አፍታትቼ፣ በቀዝቃዛ ውሃ ተለቃልቄ፣ የስፖርት ቱታዬን ለብሼ፣ ያጋመስኩትንና “When I Woke Up” የተሰኜውን በፖል ኢቫንስ ህይወት ላይ ተመስርቶ በካሮሊን ኮ የተተረከውን ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ይዤ ተደላድዬ ሳሎን ለንባብ ተቀመጠኩ።

መጽሐፉ ግለታሪክ ነው ቢባልም አነዳች የግለ ታሪክነት ምልከት የለውም። ከገጽ ገጽ ልብ እያንጠለጠለ ስሜትን ሰቅዞ በመያዝ ፋንታ የሚነሳ ግሩም ልቦለድ የሚመስል መጽሐፍ ነው።
ባለታሪኩ ፖል ኢቫንስ በህይወቱ ያለፈባቸውን መሰናክሎችና ከሞት ጋር የፈጠረውን ግብ ግብ ጸሐፊዋ በግሩምና ቀላል ቋንቋ ውብ አድርጋ ጽፋዋለች። ተመቻችቼ ተቀምጬ መጽሐፉን ማንበብ ጀመርኩ::

ዐይኔ ከመስመር መስመር ከታሪኩ ፍሰት ጋር አብሮ እየፈሰሰ በስሜትና በተመስጦ ከገፁ ጋር አብሬ እየተገለጥኩ የፖል ኤቫንስን የህይወትና ሞት ግብግብ ትንፋሽ እስኪያጥረኝ ድረስ ተቸክዬ ሳነብ የስልኬ ጥሪ አናጠበኝ።

“ኤጭ! በዚህ ሰዓት የሚደውለው ደግሞ ማነው?”

በሚል የማመናጨቅ ስሜት ደዋዩን ለማወቅ ዓይኔን ወደ ስልኬ ጣል ሳደርግ ህብስት ናት። ህብስት የወዳጄና ጥና ጓደኛዬ ሚስት ናት። ጥሪዋን ቸላ ልለው አይቻለኝምና አነሳሁት። የተለመደውን የንግግር ሠላምታ ስንለዋወጥ ለስለስ ባለው የህብስት ተፈጥሯዊ ድምጽ ውስጥ የማላውቀው ዐይነት ዕንግዳ ስሜት ሰማሁባት። በድምጿ ውስጥ ያለውን ያልተለመደ የስሜት መሻከር  ለማጣራት ስታትር ፈራ ተባ በሚልና በከባድ ትንፋሽ በሚቆራረጥ ድመፅ፤


“እ… ይፍሩ… ዳዊትን ወሰዱት…” አለች።

ምን እንደምትል አልገባኝም። ዳዊት ባሏና ለእኔ ደግሞ ወንድም አከል ጓደኛዬ ነው።


“ዳዊትን ወሰዱት?!….የት?”

አልኳት የራሷን ቃል ደግሜ……መልስ መስጠት አቅቷት ከስሜት ሲቃ ጋር እየታገለቸ ትንፋሿን ውጣ ዝም  ስትል ግራ ገባኝ::

በግርታዬ ፋታ ውስጥም ‘ምን ወንጀል ሠርቶ ይሆን?’ በሚል ድንግር የጥያቄ ወጀብ ተላግቼ ስመለስ

“የትነው የወሰዱት!? እነማን ናቸው የወሰዱት ህብስት ንገሪኝ እንጂ”

በማለት ያለፋታ የመገረም ጥያቄየን አዥጎደጎድኩባት።


“እኔ ምና’ባቴ አወቄ ብለህ ይፍሩ… ኧረ እኔ እንጃልኝ… ምባናቴ ይውጠኛል…”

ብላ እዬዬዋን ለቀቀችው። ደነገጥኩ።

“አንዴ ህብስት ምንድን ነው እሱ?!… የተፈጠረውን ገልጠሽ ንገሪኝ እንጂ”

ብዬ የቁጣ ያህል ሳምባርቅባት፤


“ኳራንቲን” አለችኝ።


“እ…!”

ብዬ ከመቅፅበት ቅዝቅዝ… ብርድ… ችስ… ትንፍስ አልኩ። ሰውነቴ ላይ በረዶ የተቸለሰብኝ ያህል ደነዘዝኩ:: እናም ያለችውን ደግሜ በሞተ ደካማ ድምፅ

“ኳራንቲን!”

      አልኳት። መልስ ሳትሰጠኝ በፊትም እንደገና ደግሜ፤

“ኳራንቲን ነው ያልሽኝ ህብስት?!” አልኳት።


“አዎ ይፍሩ አዎ!”


“እንዴት?”

ለምን እንደጠየቅኩ ባይገባኝም ጠየቅኩ:: ጥያቄዬ ይበልጥ ሆድ አስባሳት መሰለኝ በተቆራረጠ የሳግ ድምፅ ታጅባ እያለቀሰች፤


“እኔ እንጃ ይፍሩ… ኧረ እኔ እንጃ… ምና’ባቴ ነው የምሆነው?!… ምን ጉድጓድ ነው የሚውጠኝ ይፍሩ!?”

እያለች ስታለቅስ፤


“እሺ በቃ መጣሁ… እስከዚያው ተረጋጊ!”

ብዬ መልሷን ሳልጠብቅ ስልኩን ዘግቼ እየተጣደፍኩ ወደ መኝታ ቤቴ በመሄድ ላይ እንዳለሁ ህብስት በመብረቃዊ ፍጥነት እንደገና ደወለች… አነሳሁት።


“አትምጣ ልልህ ነው ይፍሩ… አትምጣ ምንም አትሠራም እሺ…”

በግድ ለመረጋጋት አየሞከረች።


“እንዴ! እንዴት ምንም አልሠራም ህብስት… መጣሁ!”


“አይ ይፍሩ አይሆንም አትምጣ…አታገኘኝም”


“እንዴ ለምን ህብስት!…ለዚህ ለዚህ ታዲያ ለምን ደወልሽልኝ?”
“አላስችል ብሎኝ ነው እንጅ እኔንም የተለዬ መመሪያ እስክንሰጥሽ ከማንም እንዳትገናኝ… በመኝታ ቤትሽ ተወሰኝ… ከሠራተኛዋም ከማንም ሰው ጋር እንዳትገናኝ ብለው በጥብቅ አስጠንቅቀውኝ ነው የሄዱት”

ስልኩን ዘጋችው።


“ወይ ጣጣ… ወንድሜን ምን አገኘው?… ምን ጉድ ነው?”

እያልኩና ከራሴ ጋር እያልጎመጎምኩ ወደ ሳሎኔ ተመልሼ ተቀመጥኩ።


በሰሜት ሰቅዞ ከገፅ ገፅ ይጋልበኝ የነበረውን መፅሐፌን ደፍቼ ካስቀመጥኩበት አንስቼ ከቆመኩበት ንባቤን ለመቀጠል ሞከርኩ። ግን አልቻልኩም። ዐይኔ ከፊደላት አልፎ ቃላትን፣ ከቃላት አልፎ ሃረጋትንና ዓረፍተ ነገራትን ማያያዝ አልተቻለውም። መልሼ በነበረበት አሰቀመጥኩት።

ከፊት ለፊቴ ጠረንጴዛ ላይ የነበረውን የቴሌቪዥን መቆጣጠሪያ (ሪሞት ኮንትሮል) አነሳሁና አበራሁት። ይጮሃል… ድምጹን ቀነስኩት ግን ድምጹ የነበረው ወትሮ በነበረበት ልክ ላይ ነው። የሚጮኸው ቴሌቪዥኑ ሳይሆን የእኔ ውስጥ ነው። አጠፋፋሁና ተነስቼ ወደ መኝታ ቤቴ  ገባሁ።
ሌሊቱን እንቅልፍ ይሉ ነገር በዐይኔ አልዞረም። አንዱን ስጥል አንዱን ሳነሳ በአጥቢያችን ካለችው የኪዳነ-ምህረት ቤተ-ክርስቲያን የሚመጣው ቅዳሴ ኩልል ብሎ ይሰማኝ ጀመር። አዎ ዕለቱም የወሩ ኪዳነ ምህረት ነው። ከዚያ በኋላም ቢሆን መገላበጤን ቀጠልኩ እንጅ ለእንቅልፍ አልታደልኩም። ላለፉት ሰባት ዓመታት እንደዛሬ ብቸኝነቴ አስጠልቶኝም አስፈርቶኝም አያውቅም። ከአንድ ጎኔ ወደ አንድ ጎን ስገላበጥ ሌሊት 10 ሰዓት ላይ ‘አላሁአክበር’ የሚለው የሶላት ጥሪ ተረከበኝ። በቃ ከዚያም በሗላ አላንቀላፋሁም:: እንዲሁ እንደሆንኩ ወገግ ብሎ ነጋ።


ወሩ የዓብይ ጾም ወር ነውና ቁርስ አላስፈለገኝም፡፡ ረፋድ ላይ ተጣጥቤና ልብሴን ለባብሼ ወደ ሳሎን ወርጄ ማታ ደፍቼው የሄድኩትን መጽሐፍ ባለበት ዐይን ዐይኑን ስመለከት የቤታችን በር ደወል ተንጫረረ። ተከትሎም ሠራተኛዬ በሩን ስትከፍት ተሰማኝ። አንገቴን አስግጌ የሚሆነውን ለመስማት ስሞክር ከሆኑ ሰዎች ጋር ታወራለች። ምን እንደሚያወሩ ስለማይሰማኝ በባለቤታዊ ኃላፊነት ምን እንደተፈጠረ ለማረጋገጥ ተነስቼ ስወጣ በቴሌቪዥን እንደምናዬው በቻይናና ሌሎች ሃገራት ያሉ የህክምና ባለሙያዎች እንደሚለብሱት ዐይነት የበሽታ መከለያ  ነጭ አልባስ ለብሰው ከራስ ፀጉራቸው እስከ እግር ጥፍራቸው የተሸፈኑ ሦሰት ሰዎች ናቸው። በቆምኩበት ውሃ ሆንኩ። በውስጤ

“ደግሞ ከእኔ ጋር ምን አመጣቸው?… ውጭ ሀገር አልሄድኩ…”

እያልኩ ሳጉተመትም አንደኛው የቡድን መሪ የሚመስል ሰው፤


“አቶ ይፍሩ!”

አለኝ ድምፁን ከፍ ጠንከር አድርጎ፤


                        “አቤት”

ድምጹን ለስለስ አድርጎ በትህትና፤


   “እ……ይፍሩ በዛብህ?!” አለ፤


“ልክ ነዎት”


“ይቅርታ እኛ ከኢትየጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ነው የመጣነው። የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል የቫይረሱ ተጠቂ ከሆኑ ሰዎች ጋር የተገናኙ ሰዎችን እየተከታተልን Contact Tracing ስንሠራ እርስዎ የቫይረሱ ተጠቂ ከሆነ ሰው ጋር ከተገናኘ ሌላ ሰው ጋር ግንኙነት እንደነበረዎ ተረድተናል። ስለዚህ ለራስዎም ሆነ ለቤተሰብዎና ለማኅረበረሰቡ ጤናማነት ሲባል ለ14 ቀናት ክትትል ወደሚደረግልዎ የለይቶ ማቆያ ቦታ እንወስደዎታለን”

ትዕዛዙን ከመቀበል ውጭ ምንም ማድረግ እንደማልችል ስለገባኝ አላንገራገርኩም:: የምለብሰውን የሌሊት ልብስና የጀመርኩትን መጽሐፍ ይዤ ተገቢውን ጥንቃቄ ከተደረገልኝ በኋላ ወደተዘጋጀልኝ ተሸከርካሪ በክብር ገባሁ።


ለእኔ መደረግ ያለበትን ጥንቃቄ ካከናወኑ በኋላ ቤታችንን በሙሉ በፀረ ተህዋስያን ኬሚካል ረጭተው ሠራተኛዬን አንዳንድ ጥያቄ ጠይቀውና መመሪያ ሰጥተው ይዘውኝ ሄዱ።


ወደ ማግለያው በገባሁ የመጀመሪያ ሰሞን ፍፁም የጤነኛነት ሰሜት ይሰማኝ ስለነበር 14 ቀናቴን ጨርሼ ለመውጣት ሙሉ ተስፋ አድረጌ ራሴን አረጋጋሁ።


ከቀናት በኋላ ግን ሁኔታዎች ፈጥነው መለወወጥ ጀመሩ። የምርመራዬ ውጤት የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ መሆኔን መሰከረ። እንዴትን ሳጣራ ጓደኛዬ ዳዊት ከሥራ ባልደረባው የውጭ ሀገር ሰው ጋር በነበረው ንኪኪ የቫይረሱ ማረፊያ ሆኖ እሱ ሳያውቀው ተቀብሎ ለእኔ ሳላውቀው አቀብሎኝ ኖሯል። በቫይረሱ የመጠቃቴ ዜና በደረሰኝ ማግስት ጉሮሮዬን ይከረክረኝ ጀመር። አከታትሎም ብን ብን የሚል ደረቅ ሳል ብጤ ይመላለስኝ ገባ። ፈራሁ… በብዙ የመዳን ተስፋ እንዳለ ባውቅም ግን ከልቤ ፈራሁ… ሁለቱ ልጆቼ ውጭ ሀገር ናቸው፡፡ ሰሞኑን አልደወሉም፡፡ እኔም ልደውልና ላሰጨንቃቸው አልፈለግኩም፡፡ ከቀን ወደ ቀን ህመሙ እየበረታብኝ ሄደ፡፡ ሳሉን ተከትሎ ለመተንፈስ ተቸገርኩ። በፍጹም ልቋቋመውም አልቻልኩም። የህመም ሰሜቱን በቃል መግለፅ ይቸግራል። እናም ከነበርኩበት ክፍል አውጥተው ወደ ፅኑ ህሙማን መታከሚያ ክፍል ሲያስገቡኝ ትዝ ይለኛል።


ከዚያ በኋላ የነበረው ጊዜ መቀመቅ ካልኳችሁ ሁኔታ ጋር የተዋወቅኩበት ጊዜ ነበር። በዚያ ለስንት ጊዜ እንዴትና በምን ሁኔታ እንደቆዬሁ አላውቅም፡፡


በመቀመቅ ቆይታዬ ሁሉ ግን ብዙውን ጊዜ ባለቤቴ አብራኝ ነበረች። ዐይቻት ግን አላውቅም፡፡ በድምጿ ግን ሁሌም አብራኝ ትሆናለች፡፡ ድምጿን ተከትዬ ውዴን እስላታለሁ፡፡ በድምጿ ፈገግ ስትል በመቀመቅ ውስጥ ብቻውን የሚሰማ ጣፋጭ ብርሃን ይሆናል፡፡ እሷ እስካለች ድረስ በዚያ ቦታ እሰከሚነጋ ድረስ ብቆይ ወይም ባይነጋ ደስታዬ ነው። ውዴ ተመችቷታል፡፡ ጥሩ ነው ያለችው፡፡ ድምጿ አሁንም ልክ የመላዕክት ዝማሬ ያህል ውብ ነው፡፡ አላረጀም።

ከተለያዬን ሰባ ይሁን ሰባ ሰባት ይሁን ሰባት ይሁን ያህል ጊዜ እንኳን ሆኖን ያው ናት፡፡ እኔ ግን አርጅቻለሁ፡፡ ድምፄን ባልሰማውም ዝም ብሎ ጨለማው ላይ ይዝለገለጋል፡፡ እሰማለሁ እንጂ አልናገርም፡፡ እንሸራተታለሁ እንጂ አልቆምም፡፡ አሙለጨልጫለሁ እንጂ አልያዝም፡፡

መቀመቅ ውስጥ መውደቅም መቀመጥም የለም፡፡ መንሳፈፍ ብቻ! እና በዚያ ውዷ ባለቤቴ አንዳንዴ ትመጣና በድምጿ ታቅፈኛለች፡፡ ምኔን እንደምታቅፈኝ ግን አላውቅም፡፡ ግን ታቅፈኝና በሹክሹክታ

 “ከዚህ ልውሰድህ? ቦታ ልቀይርልህና በእኔ ቦታ እስከ ዘለዓለም እንኑር፡፡ የእኔ መቀመቅ ይመቻል…”

ትለኛለች። ደስ ይለኛል፡፡ “እሺ” እላታለሁ፡፡ ግን አትወስደኝም፡፡ ሁሌ ልውሰድህ ነው…ግን አትወስደኝም፡፡ አንድ ቀን ጭክን ብላ በድምጿ እፍስፍስ እቅፍቅፍ አድርጋ እየተንከተከች ይዛኝ ልትሄድ ስትል ሟሟሁባት መሰለኝ ተሙለጭልጬ ከደምጿ ውሰጥ ተዘርገፌ ወጣሁ። ከዚያ ቀን በኋላ ውቧ ውዷ ባለቤቴ መጥታ አታውቅም፡፡ አንድ ቀን እንደለመደችው በደምጿ ሠረገላ ተሳፍራ ትመጣና በሳቋ እቅፍ ውስጥ ሽብልል አድርጋ ታሞቀኛለች፡፡ ይዛኝ ትሄዳለቸ ብዬ ሙልጭልጬን ድምጿ ላይ ተክዬ ብጠብቅ… ብጠብቅ… ብጠብቅ… የለችም፡፡ በቃ ቀረች፡፡

መቀመቅ ከገባሁ ጀመሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ። በቃ ጭራሽ የሞትኩ መሰለኝ… “በቃ እሷ መጥታ ካልመጣች ሞትኩ ማለት ነው” ብዬ ተስፋ ቆረጥኩ፡፡ ምክንያቱም በቆርቆሮ ቤት ሽንቁር ውስጥ አልፎ የመጣ ብናኙ ጎልቶ የሚታይ የብርሃን ፈርጥ መጥቶ ድምፄ ላይ ሲያርፍ የሆነ በመቀመቅ ሆኖ የማያውቅ ባዕድ ነገር ተሰማኝ፡፡ የሆነ ዐይን የሚስል ነገር ዐይኔ ላይ የወጣብኝ መሰለኝ፡፡ ለማረጋገጥ ቀስ ብዬ ገለጥ ሳደርገው ጉም የመሰለ ነገር…

“አሃ!!… ውዴ እኮ ድሮም መለኛ ናት እያሟለጭኩ ሳስቸግራት ለካ ሳትነግረኝ ቀርቶ እንጂ ቦታ ቀይራልኝ ኖሯል አልኩና…” ጉሙን ልነካ የድምፄን እጅ ሰደድ ሳደርግ አልደርስበት አልኩ፡፡ ድምፄ ሲምለገለግ ጉሙምም እየተምለገለገ ይተማል:: በእጄ ልይዘው ፈለግኩ፡፡ ለካ እጅ የለኝም፡፡

“ታዲያ ምንድን ነው ያለኝ?” ግራ ገባኝ፡፡ ብቻ ከሰሞኑ የተለዬ የሆነ ነገር አንዳለኝ ገባኝ፡፡ ቀስ ብዬ እራሴን ለማዬት ሞከርኩ፡፡ እግር ትዝ ሲለኝ እግሬን አሰብኩት፡፡ ቀጥዬ የእግሬን አውራ ጣት አሰብኩት፡፡ እንደነበረኝ አርግጠኛ ነኝ፡፡ ነቅነቅ አደረግኩት አለ፡፡ የቀኝ እግሬን ሞከርኩት አለ፡፡ በቃ ሞቻለሁ ማለት ነው አልኩና ሞቴን ለማረጋገጥ ፍተሻ ጀመርኩ::

ስሙን ያላወቅኩት የሆነ አካል ነገር እንዳለኝ ገባኝ፡፡ አሁን የማይሰማው ድምፄ የሆነ መፍለቂያ እንዳለው ጠረጠርኩ፡፡ እንደገና ብሞትም ልሙት ብዬ ዐይኔ ላይ ባረፈው ዐይኔ  በሽንቁር ገብቶ ያረፈውን ነገር ዐየሁት። ከድቅደቁ ጨለማ እምብርት በሽንቁር የገባች የብርሃን ፈርጥ የፈጠረችው ወጋገታ ዐይነት ብርሃን ጭል ጭል ይልብኝ ጀመር፡፡


የሽንቁሩን ብርሃን ተከትሎ እስከአሁን ስምቼው የማላውቀው ድምፅ ድርብ ድርብ እየሆነና እያስተጋባ ተሰማኝ፡፡ በቃ የፈለገው ይምጣ ብዬ የድምጹን ምንነት ለማጣራት ዐይኔ ላይ ያወጣብኝን ዐይን የሚመስል ነገር ቀስ ብዬ ስገልጠው በዐይኔ በኩል የብርሃን ጎርፍ ወደ ውሰጤ ፈሰሰ፡፡ …የብርሃን ሞገዱን መቋቋም ቢያቅተኝም መልሼ መጨፈን ግን ፈራሁ፡፡

”የት ነኝ!?”

ገባኝ፡፡ ከፊት ለፈቴ በጉም ላይ የሚንሳፈፉ የሚመስሉ ድምፅ የሚያወጡ ነገሮች ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የተለዩ ፍጡራን ናቸው፡፡ ሚስቴንም እኔንም አይመስሉም፡፡ ዐይኔ ላይ የበቀለውን ዐይኔን ላለመጨፈን ስታገል፤

“አቶ ይፍሩ”

የሚል ወፈር ያለ የሰው የሚመስል ድምፅ ሰማሁ። የጓደኛዬን የዳዊትን ድምፅ ይመስላል፡፡ አቤት ልለው ፈለግኩ ግን አልቻልኩም።


“አቶ ይፍሩ ይሰማዎታል?!”

አለኝ የሚስቴን የሚመስል ግን የታፈነ ድምፅ፤ ምን ጉድ ነው!? ተቀዣበረብኝ፡፡ ድምፅ ለማውጣት ብሞክር አልቻልኩም።

“ይሰማዎታል?!” አለኝ የዳዊትን የሚመስለው ድምፅ… ቀጥሎ የሆነ ነገር ይለኛል ብዬ ስጠብቅ ድምፁም ምስሉም እንደጉም እየተነነ ጠፋ፡፡ ተሰፋ ቆርጨ ዐይኔ ላይ የበቀለውን ዐይኔን መልሼ ከደንኩት። ከዚያ በኋላ የለመድኩትንና የኖርኩበትን መቀመቃዊ ትዕይንት ብፈልገውም፣ ሚስቴ ብትናፍቀኝም፣… ወደ መቀመቅ መመለስ አልቻልኩም።


ከዚያ በኋላ በየቀኑ በዙሪያዬ ያሉ ምስሎችና ድምፆች ቀስ በቀስ እየፈኩና እየጠሩ አካልና አምሳልን እየለዬሁ መጣሁ፡፡ .ለካ ፅኑ ህሙማን ክፍል ገብቼ ነበር… ሙሉ በሙሉ ስነቃና ሰውነቴ ላይ የተሰካኩት ሰው ሠራሽ መተንፈሻና በፈሳሽ የሚሰጡ ምግቦች ቀስ በቀስ እየተቀነሱ በመጨረሻም ወደ ሌላ ክፍል ተዛወርኩ።
በተዛወርኩበት ክፍል ኮሜዲኖ ላይ መጽሐፌ በክብር ተቀምጧል። አንስቼ ዕልባት ያደረግኩበትን ገፅ ገለጥኩት። ገፅ 151 ላይ ነበር።


Wake up call 6
PARALLEL LIVES
I began to live the day I died.

ብሎ ይጀምራል፡፡ በማገገሚያ አልጋዬ ጫፍ ላይ ቁጭ እንዳልኩ የሚቀጥለውን ከሞት ወደ ህይወት ያለውን ጎዳና ከባለታሪኩ ፖል ኢቫንስ ጋር የራሴን የሞት ሳይሆን የመኖር… የወድቀት ሳይሆን የትንሳኤ ተስፋ አክዬበት ንባቤን ቀጠልኩ!!


ግሩም መጽሐፍ ግሩም ህይወት!
መሄድ እንዳለ ሁሉ መመለስ እንዳለም ተማርኩበት፡፡ እንደናፈቀችኝ ለዘለዓም የማትመለሰው ከሰባት ዓመት በፊት በሞት የተለዬችኝ ውቧ ውዷ ባለቤቴ ብቻ መሆኗንም ተረዳሁ፡፡ ጓደኛዬ  ዳዊትስ እንዴት ሆኖ ይሆን?Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top