ጣዕሞት

ንጋት የሙዚቃ አልበም

የሙዚቃ ዘርፎች ማኅበራት ኅብረት በርካታ አርቲስቶች የተሳተፉበት የሙዚቃ አልበም ለአዲስ አበባ መስተዳድር አስረከበ። ማኅበሩ በምርቃት እና በርክክብ ፕሮግራሙ ወቅት እንዳሳወቀው በአልበሙ ውስጥ አስራ ሦስት ድምጻዊያን የተሳተፉባቸው አስራ አምስት ዘፈኖች ተካተዋል።

 አልበሙ እንዲሰራ የማነሳሻ ሐሳቡን ያነሳችው ድምጻዊት ዘሪቱ ከበደ ስትሆን በቅንብሩ ላይ ሚካኤል ኃይሉ፣ አበጋዝ ክብረወርቅ፣ ካሙዙ ካሳ፣ ማሩ፣… እና ሌሎችም ተሳትፎ አድርገዋል። በግጥም እና ዜማ ረገድም አሉ የተባሉ በርካታ ባለሙያዎች መሳተፋቸው  ተነግሯል። ዘሪቱ ከበደ፣ ሄኖክ መሀሪ፣ ሞገስ ተካ፣ ጌቴ አንለይ፣ ጆኒ ራጋ፣ ቤቲ ጂ፣ ዘሩባቤል ሞላ፣ ፍቅርአዲስ ነቅአጥበብ፣… በድምጽ ከተሳተፉት ውስጥ ይገኙበታል።

የአልበሙ ሙሉ ገቢ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ዓላማ የሚውል ሲሆን በአውታር የበይነመረብ ግብይት አማካንነት በመላው ዓለም ለሚገኙ ታዳሚያን ለሽያጭ ይቀርባል ተብሏል። የአዲስ አበባ ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ዑማ የአልበሙን ቅጂ በተረከቡበት ወቅት አርቲስቶቹ በሙያቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

ዓለም አቀፋዊነት ፎረም ምስረታ

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዓለማቀፋዊነት ላይ የሚሰራ ፎረም ምስረታ ላይ ውይይት ተካሄደ። የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዓለማቀፋዊ መሆን የሚያስችሏቸው ሁኔታዎች ላይ የተካሄደውን ውይይት የመራው የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ነው። የአዲስ አበባ፣ ሃዋሳ፣ መቐለ፣ ጅማ፣ ጅግጅጋ፣ ባህርዳር እና ሰመራ ዩኒቨርሲቲዎች የዓለም አቀፍ ቢሮ ዳይሬክተሮች እና አመራር አባላት፣ የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት በውይይቱ ላይ መሳተፋቸውን የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል። 

የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ውይይቱን በንግግር በከፈቱበት ወቅት፤ በከፍተኛ ትምህርት ዓለም አቀፋዊነት ዙሪያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከዓለም አቀፍ፣ ቀጠናዊ እና ሃገራዊ ምልከታዎች ጋር አያይዘው አቅርበዋል። በከፍተኛ ትምህርት ዓለም አቀፋዊነት ዙሪያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በሃገራዊ ምልከታዎች እንዲሁም በቀጣይ ሂደቶች ላይ መኖር የሚገባቸውን አቅጣጫዎችን ከማስቀመጣቸው በተጨማሪ በዓለም አቀፋዊነት ላይ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እየተከናወኑ ያሉ የፖሊሲ እና ስትራቴጂ የማርቀቅ ሥራዎች ያሉበት ሁኔታ መቅረቡን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የፀሐይ ግርዶች በኢትጵያ

የፊታችን ሰኔ 14 በሃገራችን የፀሐይ ግርዶሽ ይታያል። እንደ Space.com መረጃ ከሆነ ባለንበት የፈረንጆቹ 2020 ላይ ሁለት ፀሐይ ግርዶሾች በዓለማችን ላይ የሚታዩ ሲሆን፤ ጁን 21 እና ዲሴምበር 14 እንደሚታዩ ይጠበቃል። ከሁለቱ የፀሐይ ግርዶሽ በኢትዮጵያ ሰማይ የሚታየው የእሳት ቀለበት ተብሎ የሚታወቀው የግርዶሽ ዓይነት ነው። ሰኔ 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ከንጋቱ 12፡45 – 6፡33 ባለው ጊዜ ውስጥ ይታያል ተብሏል፡፡

 የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እንደተናገሩት ተቋሙ ከአማራ ክልል ጋር በመተባበር ተቋሙ በላሊበላ ከተማ የዕይታ ፕግራም ይዘጋጃል። የዓይን መከላከያዎችን ሳያደርጉ ለመመልከት መሞከር በፍጹም እንደማይገባ ያሳሰቡት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የመመልከት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች  እንደ መነጽር ያሉ መከላከያዎችን እንዲያደርጉ መክረዋል፡፡

በ2020 የሚታየው ሌላኛው የፀሐይ ግርዶሽ በዲሴምበር 14 በደቡብ አሜሪካ ደቡባዊ ጠርዝ ላይ የሚታይ ሲሆን፤ በእኛ ሃገር በጁን 21 ከታየው የሚለየው፤ ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ በመሆኑ ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top