የታዛ ድምፆች

ሰይጣን ቤት ምን ሲሰራበት ኖረ? (ከ1988-2003 ዓ.ም.)

“ዓለም የተበላሸችው ክፉ ሰዎች በመኖራቸው ብቻ ሳይሆን፤ መልካም ሰዎች እውነቱን ባለ መመስከራቸው ጭምር ነው” ይላሉ የሀሳብ ሰዎች። እውነትም ነው። ሰዎች የሚያውቁትን ባለመመስከራቸው በዓለምም ሆነ በሀገራችን ጥቂት ተብለው የማይታለፉ እውነቶች ተጣመዋል። በቅርቡ በአዲስ አበባ ከሚሰራው የፒያሳ መስቀል አደባባይ ፕሮጄክት ጋር ተያይዞ በተለምዶ “ሰይጣን ቤት” የሚባለው ህንፃ እና ግቢው ለመፍረስ አደጋ ተጋልጠው ነበር። (ለቅርሳቸው ቀናኢ በሆኑ ምላሽ በሰጡ ኢትዮጵያዊያን ተቃውሞ ጭምር) ዋናው የሰይጣን ቤት ህንፃ ባይፈርስም የግቢው አጥር በተወሰነ መልኩ እና ቀደም ሲል ሜጋ የኪነ-ጥበባት ማዕከል ያሰራው “ሜጋ አምፊ ቴአትር” ሙሉ በሙሉ ፈርሷል።

በአዲስ አበባ ከተማ የቅርስን ጉዳይ የሚመለከተው የከተማዪቱ የባሕል፣ ኪነ-ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ዘርፍን (ቅርስን ጨምሮ) በኃላፊነት እንዲመሩ የተመደቡት አቶ ሥዩም ተመስገን ታሪካዊውን የሰይጣን ቤት በፎቶ እና በቪዲዮ ቀርጾ በማስቀረት ማፍረስ እንደሚቻል (እንደሚገባ) ለአዲስ አበባ መስተዳድር ደብዳቤ ጽፏል። ይህ ሁሉ ሲሆን የባሕል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ግልጽ የሆነ የተቃውሞ ሀሳብ አላቀረበም።

ቀደም ሲል ቢሮውን ሲመሩ የነበሩት ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ከሰይጣን ቤት አጥርና አምፊ ቴአትሩ መፍረስ እና ከዋናው የሰይጣን ቤት አዳራሽ ሲፈተሸ (በሩ ሲከፈት) ከተገኘው አሥር የማይሞሉ አገልግሎት የማይሰጡ የጦር መሳርያዎች ጋር ተያይዞ ነገሩን ፖለቲካዊ ቅርጽ ለመስጠት በማሰብ “የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሲኒማ ቤት ጉድ” በሚል ርዕስ በፌስቡክ ገጻቸው ያልተገባ ጽሑፍ ያወጣሉ። በጽሑፉ ዝርዝር ውስጥ “በታሪካችን አካል ሰይጣን ቤት፣ ዙሪያውን ፈርሶ በሰነበተ ሲኒማ ቤት ምን ይሰራል? ሲኒማ ተብሎ በሩ ላይ የተለጠፈው ፊልም ማሳየት ካቆመ ሰንበትበት ያለ ቅርስ ውስጥ መሳሪያ መገኘቱ ምን ይነግረናል? በውስጡ የታጨቀው ጓዝ ምንድነው? ‘እዩልኝ የጦር መሳርያ’ ለማንኛውም ቤቱ አይፈርስም መባሉን ይዘን ፖሊስ ጉዳዩን መርምሮ ባለፉት ዓመታት ለምን አገልግሎት እንደዋለ የሚነግረንን እንጠብቃለን” ሲሉ በፎቶ አስደግፈው ጽፈዋል።

እውነት ለመናገር ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ይህን ጥያቄ ማንሳት የነበረባቸው ዛሬ ሳይሆን ለሁለት ዓመታት ገደማ የከተማዪቱን ባሕል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮን ሲመሩ በነበሩበት ጊዜ ነበር። እኚህ የቀድሞ የቢሮ ኃላፊ ዛሬ ላይ ይህ ግቢ ምንም ሲሰራበት ያልነበረ አድርገው ሊያቀርቡት ቢሞክሩም ከጥቂት ዓመታት በፊት ለመጀመርያ ጊዜ በተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ “ሀ” ብለው መስራት የጀመሩት ሰይጣን ቤት ተብሎ በሚጠራው ግቢ ውስጥ በነበረው ሜጋ የኪነ-ጥበባት ማዕከል ነው። በወቅቱ እሳቸው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆነው የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በደረሰው እና በዓለም ፀሐይ በቀለ በተዘጋጀው “ፎዚያ” የቴሌቪዥን ድራማ ላይ ከእነ ዓለማየሁ ታደሰ፣ ግሩም ዘነበ እና ሀረገወይን አሰፋ ጋር በመስራት ነበር የቴሌቪዥን ድራማን ትወና የተቀላቀሉት።

ሰይጣን ቤት ከተሰራ መቶ ዓመት አልፎት በቅርስነት የተመዘገበ ቢሆንም በተለያዩ ዓመታትና ሥርዓቶች ትኩረት ተነፍጎት ከጥበብ ጋር ባልተያያዘ መሥሪያ ቤትነትም፣ በመጋዘንነትም ማገልገሉ እውነት ነው። ይሁንና የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዎች አንዳቸውም እንኳን ሊመሰክሩለት ያልፈለጉት በርካታ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ሲሰሩበት እንደቆዩ ደግሞ ከብዙዎች ህሊና ሊጠፋ አይችልም።

ሜጋ የኪነ-ጥበባት ማዕከል ቀደም ሲል (ከ1987-2003 ዓ.ም.) የኢህአዴግ ኢንዳውመንት ከተቋቋሙት ድርጅቶች አንዱ እና በኪነ-ጥበብ ረገድ የማይዘነጋ ሀገራዊ አስተዋጽኦ ያበረከተ ማዕከል ነው። በአቶ ዕቑባይ በርሀ ሲመራ የነበረው ይኸው ሜጋ የኪነ-ጥበባት ማዕከል በዚሁ “ሰይጣን ቤት” በሚባለው ህንፃ እና ግቢው ውስጥ በ1987 ዓ.ም. ሂደቱ ጀምሮ ከ1988 እስከ 2003 ዓ.ም. የቀጠለ ማዕከል ሲሆን እንደ ስያሜው በሁሉም የኪነ-ጥበባት ዘርፍ ሲሰራ የነበረ ነው። ማዕከሉ ዛሬ ድረስ ከተመልካች ህሊና የማይጠፉ የኪነ-ጥበብ ሥራዎችን ሲያሳይ አዳዲስ ከያንያንን ለጥበብ ያበረከተ እና ቀደም ሲል እውቅና የነበራቸውንም ይበልጥ በዝና ከፍታ ላይ ያስቀመጠ ነው።

በዚያው በሰይጣን ቤት ግቢ ውስጥ በተሰራው እና ለሀገራችን በጥበብ ማሳያነት የመጀመርያው በሆነው “ሜጋ አምፊ ቴአትር” ዛሬም ድረስ በክብር የሚታወሱ የትያትር እና ሙዚቃ ሥራዎች ተመድርከውበታል። “አንቲገን”፣ “ጓደኛሞቹ”፣ “የአዛውንቶች ክበብ”፣ “አብሮ አደግ”፣ “የብሩክታዊት ስጦታ” እና “እንቁላሉ”ን የመሳሰሉ በጥበባዊ ዋጋቸው ከፍ ያሉ የመድረክ ሥራዎች ቀርበዋል።

በህፃናት ትያትርም ቢሆን “የወፍ አፍ” እና የተባባሪ ፕሮፌሰር አቦነህ አሻግሬ ድራማዎች ለህፃናት የቀረቡት በራሱ በሰይጣን ቤት አዳራሽ ነው። በኪነ-ጥበብ ቤቱ ከህፃናት ትያትሩ ጋር ሙዚቃ በታዳጊ ድምጻውያን እና ሙዚቀኞች እያቀረበ የህፃናቱን ትኩረት የሳበ ግቢ ነበር። በሰይጣን ቤት በሚቀርቡ የታዳጊ ሕጻናት ሙዚቃዎች ላይ በድምጽ ይሳተፉ ከነበሩት መሀል ዛሬ አድገው እውቅ ድምፃውያን ለመሆን የበቁም ይገኙበታል። አበባ ደሳለኝ፣ ጥበቡ ወርቅዬ፣ ትዕግስት ወይሶ፣ ግዛቸው ተሸመ ከእነዚህ መሃል ተጠቃሽ ናቸው።

ሜጋ የኪነ-ጥበባት ማዕከል እንደ ኪነ-ጥበብ ቤትነቱ በተለያዩ ርዕሶች ላይ ጥበባዊ የውይይት መድረኮች የሚዘጋጅ ሲሆን እነዚህ በሀገሪቱ አሉ የተባሉ የጥበብ ሰዎች የሚሳተፉባቸው ጥበባዊ ውይይቶች ይካሄዱ የነበረው በሰይጣን ቤት አዳራሽ ነው። አምፊ ቴአትሩ ከመገንባቱ በፊትም ሆነ በኋላ ሰይጣን ቤት ለራሱ ለማዕከሉ ተዋንያንም ሆነ ለውጭ አማተር የኪነ-ጥበብ ቡድኖች የትወና መለማመጃ ሆኖ አገልግሏል።

በሀገራችን የመጀመርያው ሲኒማ የታየበት ግቢ ውስጥ ያለው ሜጋ የኪነ-ጥበባት ማዕከል ሲመረቅ በሃገራችን የትያትር ታሪክ የመጀመርያው የሚባለውን የበጅሮንድ ተ/ሃወርያት ተ/ማርያም “ፋቡላ ትያትር ለዕይታ አቅርቧል። በማዕከሉ እየተመረቱ ለዕይታ በበቁ ትያትሮች ላይ የማዕከሉ ሰራተኛ በነበሩት እነ ዓለማየሁ ታደሰ፣ ሀረገወይን አሰፋ፣ ግሩም ዘነበ፣ ሽመልስ አበራ፣ አቦነሽ መንግሥቱ፣ ሸዋፈራሁ ደሳለኝ፣ አስቴር በዳኔ እና በሌሎች ተጋባዥ ተዋንያን ከላይ የተጠቀሱት ድንቅ የመድረክ እና የቴሌቪዥን ድራማዎች ተሰርተዋል። ሳህሉ ኪዳኔ በትርጉም፣ በድርሰት እና በዝግጅት በማዕከሉ የትያትር መምርያ ኃላፊ የነበረችው ገነት አጥላው እና የትያትር ክፍሉ ባልደረባ የነበረችው እመቤት ተፈራ ያላቸውን ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ፍላጎት እና አቅም ያለ ስስት ለማበርከት ችለዋል። የማዕከሉ ባልደረባ በሆኑ ሙያተኞቹ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ በማዕከሉ እና በአምፊ ቴአትሩ የሚሰሩ ትያትር እና ሙዚቃ ነክ ሥራዎች (በወቅቱ ከሌሎች የተሻለ) ክፍያ የሚከፈላቸውና በጥበባዊ ዋጋቸውም ከፍ ያሉ በመሆናቸው በየትያትር ቤቱና በግል የሚሰሩ የጥበብ ሰዎች ቀልብ ወደ ሰይጣን ቤት መሳቡ ሁሉም የሚመሰክሩት ሀቅ ነው።

እነ ጀማነሽ ሰሎሞን፣ ተፈሪ ዓለሙ፣ ጌትነት እንየው፣ ሀይማኖት ዓለሙ፣ በላይነህ አቡኔ፣ ሙሉጌታ ጃዋሬ፣ ባዩሽ ዓለማየሁን የመሳሰሉ ተዋንያን በዚሁ አምፊ ቴአትር ላይ ችሎታቸውን አሳይተዋል። የ“አንቲገን” ትያትር ተርጓሚና አዘጋጅ ሳህሉ ኪዳኔ በዕውቀት የዳበረ፣ በንባብ የካበተ ፈጣሪነቱን ያሳየውና ለከፍተኛ ዝና የበቃው በዚሁ በሜጋ አምፊ ቴአትር ነው። ዶክተር (አሁን ፕሮፌሰር) ፍቅሬ ቶሎሳ፣ በላይነህ አቡኔ፣ ማንያዘዋል እንዳሻው፣ ነጋሽ ገ/ማርያም፣ ዘከርያ መሐመድ፣ ተስፋዬ ገ/ማርያም እና በላይነህ አቡኔ በወጥ ድርሰት፣ በትርጉም እና አዛማጅ ትርጉም ሥራቸውን ለተደራሲ ያቀረቡበትን ዕድል አግኝተዋል።

ሰይጣን ቤት ራሱ አዳራሹ እና ዙሪያ ግቢው የቀደመ የጥበብ መነሻ ቤትነቱን (ሲኒማ ለሀገራችን ለመጀመርያ ጊዜ የታየበትነቱን) በማይመጥን መልኩ የተለያዩ መስሪያ ቤቶች የነበሩበትና በመጨረሻም አምፊ ቴአትሩ የተሰራበት ሥፍራ ቆሻሻ መጣያ እና ሽንት መሸኚያ የነበረ አፍንጫ ተይዞ የሚታለፍበት አካባቢ ነበር። በኋላ ላይ ሜጋ የኪነ-ጥበባት ማዕከል ከኪራይ ቤቶች በኪራይ እና በኋላም በሊዝ ገዝቶ (ከሰይጣን ቤት ህንፃ ውጭ፤ በወቅቱ ሰይጣን ቤት ሊዝ ውስጥ ያልገባው በቅርስነት የተመዘገበ በመሆኑ ነው) ሲሰራበት ከመግቢያው ጀምሮ ጥበብ ጥበብ ይሸት እንደነበር መናገር ማጋነን አይሆንም። በአምፊ ቲያትሩ የማዕከሉ ባንዶች “ራሚድ” እና “ጽንአት” ከእነ ጥላሁን ገሠሠ፣ ማህሙድ አሕመድ፣ ታምራት ሞላ፣ ዓለማየሁ እሸቴ ዓይነቶቹ ጀምሮ እስከዚያን ጊዜው ወጣትና ጀማሪ ድምፃውያን እነ ፍቅር አዲስ ነቅአጥበብ፣ ላፎንቴኖች፣ ጌታቸው ኃይለማርያም፣ አብርሐም ገ/መድህን፣ ፀደንያ ገ/ማርቆስ፣ ጥበቡ ወርቅዬ፣ ታምራት ደስታ፣ ማህሌት ገ/ጊዮርጊስ እና ዘውዱ በቀለን የመሳሰሉ ድምፃውያን በተደጋጋሚ የሰሩበት መድረክ ነው።

ከሙዚቃ ዝግጅቱ ጋር አሳቂያኑ እነ ተስፋዬ ካሳ፣ ክበበው ገዳ፣ እንግዳዘር ነጋ፣ ደረጀ ኃይሌ፣ ሀብቴ ምትኩ፣ ዋኖሶች (ቤተልሄም እና ደምሴ) እንዲሁም የባንዱ ቋሚ አባል እስኪመስል ድረስ ባንዱ በተገኘበት ሁሉ ሥራውን የሚያቀርበው ጥላሁን እልፍነህ (አሸው) የኮሜዲ ሥራቸውን በድግግሞሽ ያቀረቡበት ግቢ ነው።

በሜጋ አምፊ ቴአትር ይዘጋጅ የነበረው ራሳቸው ህፃናት ትርኢት አቅራቢም፣ ተመልካችም የሆኑበት “የህፃናት የኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል” ከሜጋ በፊትም በኋላም ያልተሰራ ነው። በፌስቲቫሉ በርካታ ት/ቤቶች ተሳታፊ ሲሆኑ ህፃናቱ በተለያዩ የኪነ-ጥበብ ዘርፎች ማለትም በሥዕል፣ በግጥም፣ በሙዚቃ፣ በትወና እና በውዝዋዜ የሚወዳደሩበት እና የሚሸለሙበት እንዲሁም የአሸናፊዎቹ ሥራዎች ለሕዝብ የሚቀርቡበት ታላቅ ፌስቲቫል በዚያው ግቢ ይካሄድ እንደነበር አይዘነጋም።

ቲያትር ቤቱ የሙዚቃ ትምህርት ቤትም አደራጅቷል። ያለማጋነን ከያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ቀጥሎ በርካታ መሳሪያ ተጫዋች የሙዚቃ ባለሙያዎችን ያፈራ ተቋም ነው።

ማዕከሉ ከተሰማራባቸው የጥበብ ዘርፎች ውስጥ የሙዚቃ ካሴት ህትመት አንዱ ሲሆን በዘርፉም በርከት ያሉ የትግርኛ፣ አማርኛ፣ ኦሮምኛ እና አፋርኛ ካሴቶች ታትመው ለገበያ ቀርበዋል። ሙዚቃን በመድረክ እና በካሴት (ሲዲ) ህትመት ብቻ ሰርቶ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብለው ባለማመኑም በተለይም የኦዲዮ ቪዥዋል አሳታሚዎች ማኅበርን የማቋቋም አስፈላጊነት ጥንስሱ እና አብዛኛው ማኅበሩን የማደራጀት ሥራ በዋንኛነት የተሰራው በሜጋ የኪነ-ጥበባት ማዕከል ግቢ ውስጥ ነው። አብዛኛው የማኅበሩ እንቅስቃሴ ከሚጻፍ ደብዳቤ ጀምሮ ስብሰባዎች በማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዕቑባይ በርሀ ቢሮ እና በጸሐፊያቸው ይካሄዱ ስለነበር ሥራ አስኪያጁ በማዕከሉ መምሪያ ኃላፊዎች እና የማኔጅመንት አባላት “የአቶ ዕቁባይ ቢሮ የማዕከሉ ነው ወይስ የኦዲዮ ቪዥዋል?” ተብለው እስከመገምገም ደርሰዋል። ሜጋ የኪነ-ጥበባት ማዕከል ባለቤቱ የፖለቲካ ድርጅት በመሆኑና በግቢው ውስጥ በተለይም በሙዚቃው ዘርፍ በትግሉ ወቅት የነበሩ ታጋዮች በአባልነት የሚገኙበት በመሆኑ ጭምር በበርካታዎቹ የኦዲዮ ቪዥዋል አሳታሚ ድርጅት ባለቤቶች ዘንድ በጥርጣሬ ይታይም ነበር። ከጥርጣሬው ባሻገርም የኮፒራይት ጥሰት ጉዳይ ለዘርፉ ቅርብ በሆኑና በተወሰነ ደረጃም በአንዳንድ የማኅበሩ መስራች አባላት ጭምር የሚፈጸም ስለነበር የማኅበሩ ምስረታ ብዙ ውጣ ውረዶችን ያለፈ ነበር። በርካታ የማኅበሩ መስራቾች ስብሰባ በዋና ሥራ አስኪያጁ፣ የሙዚቃ ባለ ሙያዎች የኮፒ ራይት ጥሰት በተቃውሞ እንቅስቃሴ ውይይት እና የሰላማዊ ሰልፍ እንቅስቃሴዎችም መነሻቸው ሜጋ የኪነ-ጥበባት ማዕከል ነው። የኋላ ኋላም “የኢትዮጵያ ኦዲዮ ቪዥዋል አሳታሚዎች ማኅበር” ሊመሰረት በቅቷል።

ታላቁ የዓድዋ ድል ክብረ-በዓል የሙዚቃና የጥበባት ፌስቲቫል በሜጋ አምፊ ቴአትር እና በኤግዝቢሽን ማዕከል ሲካሄድ የፌስትቫሉ አዘጋጅ ሜጋ የኪነ-ጥበባት ማዕከል ሲሆን፤ በዚሁ ዝግጅት በሀገሪቱ አሉ የተባሉ የሙዚቃ እና የተውኔት ሙያተኞች ይሳተፋሉ። ገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬም እነ “እውነት ከመንበርህ የለህማ”ን የመሳሰሉ የግጥም ሥራዎቹን የሚያቀርብበት መድረክ ነበር።

ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በፊት የኢትዮጵያ እና የኤርትራን ሕዝቦች ወንድማማችነት ለማጠናከር በማሰብ በየዓመቱ ሊዘጋጅ ታስቦ ሁለት ጊዜ የተዘጋጀው የሙዚቃ አቅርቦት አስተባባሪም የኪነ-ጥበብ ማዕከሉ ነበር። “ኢትዮ ኤርትራ የሙዚቃ ፌስቲቫል” የሚል ስያሜ ያለው ዝግጅቱ አዲስ አበባ እና አስመራ ላይ አንድ ጊዜ በድምሩ ሁለት ጊዜ ተከናውኗል “ዓድዋ አፍሪካ” በተሰኘው የዓድዋ ድልን የሚዘክር የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይም የጎረቤት ሀገራት ሙዚቀኞች ሳይቀር ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል። ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ጨምሮ ከኬንያ፣ ከሶማሊያ እና ከሱዳን የመጡ ባንዶች ሥራዎቻቸውን ያቀረቡበት፣ ለሁለት ቀናት የቆየው፣ በኤግዚቢሽን ማዕከል የተካሄደው፣ “ዓድዋ አፍሪካ” ፌስቲቫል በሚድያዎች የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ተሰጥቶት ነበር። ከሚድያዎች ጋር በፈጠረው ጥሩ ግንኙነት በቲያትር ቤቱ የሚዘጋጁ የበዓል ዝግጅቶችን ጨምሮ የሙዚቃ ፌስቲቫሎችን በቀጥታ በራዲዮ እና በቴሌቪዥን እንዲቀርብ አድርጓል።

በኢዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅትም የሰራዊቱን እና የህዝቡን ሀገራዊ ስሜት ለመቀስቀስ “ክብር ለኢትዮጵያ” የሙዚቃ ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ከማዘጋጀት አልፎ እነ ጥላሁን ገሠሠ እነ ማህሙድ አህመድን የመሳሰሉ ድምፃውያን የጦርነቱ ቀጠና ድረስ ሄደው ሥራቸውን በማቅረብ የሰራዊቱን ሞራል ከፍ የማድረግ ሀገራዊ ግዳጁን በብቃት የተወጣ ማዕከል ነው። “አንድ ብር ለአንድ ወገን” የመጀመርያው የሙዚቃ ኮንሰርትንም በመስቀል አደባባይ በተከናወነበት ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሙዚቀኞች እና ድምጻዊያን ተሳትፈዋል። የዚህ ዝግጅት አስተባባሪም ማዕከሉ ነበር።

ሠዓሊና ገጣሚ መሥፍን ኃ/ማርያም በሚመራው ክፍልም እንደ “ሴቶች በሥዕል ውስጥ” እና በአማኑኤል ሆስፒታል በአዕምሮ ህሙማን የተዘጋጀ የስዕል አውደ-ርዕዮችም ተዘጋጅተዋል። ሠዓሊ መስፍን በቲያትር ቤቱ ለዕይታ የበቁ ቲያትሮችን የመድረክ ገጽ በማዘጋጀትም ተሳትፎ ነበረው። በተለይም “አንቲገን” የተሰኘውን ተውኔት ከመድረክ ገጹ ውጭ ማሰብ ለብዙዎች ይከብዳቸዋል።

ዘርፈ ብዙው የትያትር ጥበብ በመድረክ፣ በቴሌቪዥን፣ በሬድዮ እና በኅትመት (ለንባብ) ሊቀርብ የሚችል ሲሆን ሜጋ የኪነ-ጥበባት ማዕከል በተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ሥራ ላይ ከማንም የቀደመ ታሪክ ሰርቷል። ቀደም ባሉት ዓመታት የሚታዩት የቴሌቪዥን ድራማዎች ሁሉ የድራማ ጽሑፋቸው ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተሰጥቶና ተገምግመው ለቀረፃ ብቁ ከሆኑ በኋላ በቴሌቪዥን ድራማ ትምህርት በሌላቸው የጣቢያው ጋዜጠኞች እና ሥራቸውን በማቅረብ በዚያው ጣቢያ ላይ ስም ባገኙ ተዋንያን ይዘጋጅ ነበር (ጣቢያው ለተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ባለውለታነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ) በወቅቱ በትወና የሚሳተፉ ሙያተኞች ዛሬ ላይ ጊዜው ሲያልፍ እንደ ትውስታ የሚያነሱትም ብዙ ውጣ ውረድ አልፈዋል። ተዋንያን ለዜና ዘገባ በሚወጣ መኪና ላይ ከጋዜጠኞች ጋር ተጭነው ሄደው ሌላው ስራ ከተሰራ በኋላ ከዜና መልስ ትኩረት እየተነፈጋቸው እና እነሱ የመረጡበት ሳይሆን ለካሜራው ቀረብ ባለ ቦታ ጭምር በችኮላ እየተቀረፁ ነው፤ በዚያ መጠን ኅብረተ-ሰቡን ሲያዝናኑ የነበረው።

 ሜጋ የኪነ-ጥበባት ማዕከል የቴሌቪዥን ድራማን መሥራት ከጀመረ በኋላ ሙያው እንደ ሙያ ታይቶ ለራሱ ብቻ የሚመደብለት ዳይሬክተር እና የቀረፃ ባለሙያዎች አግኝቷል። ራሱ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ማንሻ ካሜራ እና ሙያተኛ እንዲመደብ በማድረግ፣ ወዲያውም የራሱን የቀረፃ እና ኤዲቲንግ መሳሪያዎች በማሟላት ለዛሬዎቹ በግል የሚሰሩ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ፈር ቀዷል። እንደ “ጎጆ መውጫ” “ክፍተት”፣ “ማን ገደላት”፣ “ፎዚያ”፣ “እንቁላሉ”፣ “በዚህ መንገድ አለ” የመሳሰሉ ተከታታይ እና አይረሴ የቴሌቪዥን ድራማዎች ሰርቶ ለህዝብ አቅርቧል።

በዚሁ የቴሌቪዥን ድራማ ዘርፍ ቀደም ሲል ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር በተወሰነ ቁርጥ ክፍያ ከመሰራት ወጥቶ ዛሬ ድረስ የተለመደ አሰራር ለመሆን የበቃውን የወጪ መጋራት (ከማስታወቂያና ስፖንሰር የሚሰበሰበውን ገቢ በውላቸው መሰረት ለአስተላላፊው ቴሌቪዥን ጣቢያ እና ለአምራቹ ሜጋ የኪነ-ጥበባት ማዕከል በፐርሰንት ማከፋፈል) የተጀመረው “ገመና” በተባለው የቴሌቪዥን ድራማ ነው። በአዶኒስ ደራሲነት እና በአሸብር ካብታሙ ዳይሬክተርነት የመጀመርያዎቹ 25 ክፍሎች በወጪ መጋራት የተቀረጸው እና የተላለፈው በሜጋ የኪነ-ጥበባት ማዕከል ሀሳብ አመንጪነት ነው። አሰራሩ አዲስ ከመሆኑ አንፃር በጣቢያውም ሆነ በሌሎች ሙያተኞች ተግባራዊ ሊደረግ የማይችል መስሎ ሲታይም ቆይቷል። በኋላ ግን ተቻለ። አሁን ደግሞ ወደ ቀደመው አሰራር መመለስ እስከማይቻልበት ደረጃ ተደረሰ። (“ገመና” የቴሌቪዥን ድራማ የመጀመርያዎቹ 25 ክፍሎች በሜጋ የኪነ-ጥበባት እና ማስታወቂያ ድርጅት ሲሰራ ከዚያ በኋላ ያሉት ክፍሎች ግን በዳ’አማት መልቲ ሚድያ የተሰራ ነው) ዛሬ ከቴሌቪዥን ጣቢያዎች መብዛት ጋር ተያይዞ በቁጥር የበረከቱት የቴሌቪዥን ድራማዎች የዘር ግንዳቸው ከሜጋ የኪነ-ጥበባት ማዕከል የሚመዘዝ ነው።

በደርግ ጊዜ ከነበረው “ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት” በኋላ በተደራጀ ደረጃ መጻሕፍት የማሳተም ሥራን የጀመረው አሁንም ሜጋ የኪነ-ጥበባት ማዕከል ነው። በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በኅትመት ክትትል ሰራተኛነት ሥራ የጀመረባቸው የደረጀ በቀለ “ህያው ፍቅር” እና የሰርቅ’ዳ “ቆንጆዎቹ” መጻሕፍት በኋላ ላይ እነ “መንግሥቱ ለማ- ደማሙ ብዕረኛ (ግለ-ታሪክ)” (አብዬ መንግሥቱ ሳይጨርሱት በማለፋቸው በጥሩ መንገድ ጨርሶ ያሰናዳው ደራሲ እና ተርጓሚ መስፍን ዓለማየሁ ነው)፣ የሰዓዳ መሐመድ “እሾሀማ ወርቅ”፣ የስብሀት ገ/እግዚአብሄር “ሌቱም አይነጋልኝ”፣ የዮሐንስ አድማሱ “እስኪ ተጠየቁ”፣ ገነት አየለ ጓድ ሊቀመንበር መንግስቱ ኃይለማርያምን ጠይቃ ያዘጋጀችው “የሌተናንት ኮሎኔል መግሥቱ ኃይለማርያም ትዝታዎች” (በነገራችን ላይ እዚህ መጽሐፍ ውስጥ ጓድ መንግስቱ አቶ መለስ ለኤርትራ ይወግናሉ፣ በእናታቸው ኤርትራዊ ስለሆኑ የሚለው ንግግር ተካቷል) የደበበ ሰይፉ የግጥም መድበል፣ የኦሮምኛ ቋንቋ ስነ-ቃል፣ የትግርኛ ቋንቋ ስነ-ቃል፣ በርካታ የልብወለድ፣ ኢ-ልቦለድ፣ የትምህርት አጋዥ እና ሙያ ተኮር መጻሕፍት ታትመው ዛሬም ድረስ በእጃችን ይገኛሉ። በማዕከሉ ውስጥ በመምሪያ ደረጃ የነበረው አሳታሚ በኋላ ላይ “ሜጋ አሳታሚ ድርጅት” ሆኖ ራሱን ችሎ ወጥቷል።

አሳታሚው በመጀመሪያ ደረጃ ሆኖ በማዕከሉ ስር በነበረበት ወቅት በትግርኛ እና በአማርኛ ቋንቋ የተጻፉ፣ በበላይ አመራሮች ትእዛዝ የተላኩ ደራሲያን ስራዎች በወቅቱ የነበረውን የግምገማ ስርዓት ማለፍ ባለመቻላቸው ሳይታተሙ ቀርተዋል። ድርጅቱ በዚህ መጠን ከእውቂያ እና ከቲፎዞ ይልቅ ለጥበቡ ሀቅ የቆመ ነበር። አንድም የጥበብ ሰው ሜጋ የኪነጥበባት ማዕከል ውስጥ ሰው በማወቁ እና ባለማወቁ፣ በየትኛውም እጅ መንሻ መንገድ በመጠቀምና ባለመጠቀም የሚያገኘውና እና የሚያጣው ምንም አለመኖሩ በወቅቱ ሥራቸውን ይዘው ወደ ማዕከሉ ጎራ ያሉ ሁሉ ምስክር ይሆናሉ።

ብዙዎች “ዛሬ ድረስ መደገም ያልቻለች” ብለው የሚገልጹአት ብቸኛዋ የኪነ-ጥበብ መጽሔት (“ፈርጥ” የኪነ-ጥበብ መጽሔት) ለዓመታት በሜጋ የኪነ ጥበባት ማዕከል ታትማለች። “ፈርጥ” ኪነ-ጥበቡን እንድታግዝና፣ ለኪነ-ጥበብ ሙያተኞች አንደበት እንድትሆን፣ በማሰብ አንዱም እትሟ አትራፊ ሳይሆን ትታተም የነበረች መጽሔት ናት። የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ከሪፖርተርነት እስከ ምክትል ዋና አዘጋጅነት የሰራባት “ፈርጥ” መጽሔት ሙሉ ገጽዋን ለኪነ-ጥበባዊ ጉዳዮች በመስጠት በማንም አካል ድጋሚ ለዚያን ያህል ጊዜ መታተም ያልቻለች መጽሔት ናት። ይህች መጽሔት ነቢይ መኮንን እና ተፈራ መኮንን ያዘጋጇት የነበሩ ሲሆን በሀገሪቱ ያሉ አንጋፋ እና ወጣት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ሐሳባቸውን እና ሥራቸውን አቅርበውባታል።

ምናልባትም ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሽልማት ድርጅት በኋላ የመጀመሪያው ሊባል የሚችልና ከሁለት ዙር በላይ መዝለቅ ያልቻለውን “የኢትዮጵያ የስነ-ጥበብ እና የመገናኛ ብዙኃን ድርጅት” ጥንስሱ እና ውጤቱ የሜጋ የኪነ-ጥበባት ማዕከል ነው። የኪነ-ጥበብ ሥራዎችን ከማምረት፣ በማኅበር ከማደራጀት እና ለብዙዎች እድል ከመሆን አልፎ የጥበብ ሰዎችን በመሸለም እና በማበረታታት ሜጋ የኪነ-ጥበባት ማዕከል የቻለውን ያህል ታግሏል።

ከዋናው የሽልማት ድርጅት በመለስም በዓላት እና ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ እነ አበበ ተካ፣ ዓለማየሁ ታደሰ፣ ዮዲት ዘለቀ፣ ሀዋ ታለንን የመሳሰሉ የጥበብ ሰዎች ተሸልመው በወቅታቸው ከፍ ብለው ዕንዲታዩ እና ዛሬም ድረስ ስመ ጥር የጥበብ ሰው ሆነው እንዲኖሩ የራሱን ድርሻ አበርክቷል። አበበ ተካ በወቅቱ ነባር ድምጻዊ ቢሆንም “ጭቃውን እፍ ብሎ” እስትንፋስ የዘራበት፣ ብዙ እርከኖችን ሳይረግጥ በደቂቃዎች ውስጥ ከታች ወደ ላይ ያነጠረው ሜጋ የኪነ-ጥበባት ማዕከል በኤግዚቢሽን ማዕከል አዘጋጅቶት የነበረው የልማት ፕሮግራም እንደሆነ ራሱም ሊክድ አይችልም።

“የደርሶ መልስ” የቴሌቪዥን ድራማ ደራሲ እና ዳይሬክተር መአዛ ወርቁ፣ የድራማው ፕሮዲዩሰር ዘካርያስ ካሱ፣ የበርካታ የራዲዮ ድራማዎች ደራሲ ፍቅሩ ካሳ፣ ገና ከዩንቨርሲቲ እንደወጡ (ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ጋር በነበረው ጥብቅ ግንኙነት) በወቅቱ ባላቸው ከፍተኛ ነጥብ ተመርጠው እጃቸውን ከጥበብ ጋር ያፍታቱት እና ሥራቸውን ለህዝብ ማቅረብ የቻሉት በዚሁ ማዕከል ነው። ሸዋፈራሁ ደሳለኝ በትወና ችሎታውን ያሳየበት እና ዝና ያገኘበት፣ በጥበብ ዳዴ ያለበት ቤት እዚያ ነው። በአጠቃላይ በሐገሪቱ ውስጥ በጥበብ መንገድ ላይ ሆኖ እግሩ ሜጋ የኪነ ጥበባት ማዕከልን ያልረገጠ ማን ይሆን? ይህ ታሪክ ከማዕከሉ በርካታ ተግባራት መካከል ጸሐፊው ያስታወሰው ውስን ያልተናገረ ታሪክ ነው። ይህ ትልቅ የጥበብ ማዕከል ይህን ሁሉ ታሪክ እንዲያከናውን በጀት የመደበ አካል ቢኖርም ማዕከሉን ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው የመሩት ግለሰቦች አስተዋጽ ላቅ ያለ ነው። በግል ኪነ-ጥበቡ እንዲያድግ፣ ለሀገር አንዳች ለውጥ እንዲያመጣ ብርቱ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው። ዕቑባይ በርሀ፣ ገነት አጥላው፣ ሳህሉ ኪዳኔ፣ ኢያሱ በርሄ፣ ነቢይ መኮንን፣ ሰሎሞን አያሌው፣ ፍርዱ አየለ፣ እመቤት አበራ፣… በጥበብ ሥራ ብቻ ሳይሆን በአስተዳደር፣ በፋይናንስ፣ ማርኬቲንግ ያገለገሉበት ቤት ነበር። እነኚህ ግለሰቦች በዚህች ሀገር የኪነ-ጥበብ ታሪክ ደማቅ አሻራ ያላቸውና በአመራራቸውም ብዙ የጥበብ ሥራዎችን ያፈሩ ናቸው። ይሁንና በሰይጣን ቤትም ሆነ በሜጋ የኪነ-ጥበባት ማዕከል ዙሪያ እኛ በሂደቱ ያለፍን ሰዎች ዝም ስላልን (ስላልተናገርን) ሌሎች ሰዎች ለተሳሳተ ግምት በቁ። የእኛ ጥፋት ነው

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top