ታሪክ እና ባሕል

ምርጫ እና የፖለቲካ ባህላችን …?

“ታሪክ ራሱን ይደግማል። መጀመሪያ አሳዛኝ ሆኖ፤ ሁለተኛ ጊዜ ግን ቧልት ሆኖ” እንዲል ካርል ማርከስ፤ የሃገራችን የፖለቲካ ባህልም ተሻለው ሲባል ወደቀድሞው ህመሙ እየተመለሰ፣ እየተመላለሰ ከእኛ ዘመን ደረሰ። ከአያት ቅድመ-አያቶቻችን ቀና ቀናውን በመውረስ ፈንታ፤ መጠላለፍ፣ መጠፋፋት፣ ሴራ፣… የሚያመዝንበት የፖለቲካ ልማድ ተረክበን፤ አሁን ደግሞ ለቀጣዩ ትውልድ ልናስተላልፈው መንገድ ጀምረናል።

በነገሥታቱ ዘመን መሳፍንቶቻችን “በእኔ እነግስ፤ በእኔ እገዛ” ሰበብ እርስ በእርስ እየተጣሉና ጦር እያዘመቱ በመጨራረስ፤ በስልጣኔ የዓለም ራስ የነበረችውን ኢትዮጵያ ከድሆች ተርታ አሰልፈዋታል። ከሐገራት ቁንጮነት ወደ ጭራነት አውርደዋታል። ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ብርቅ የሆነበት የፖለቲካ ባህላችን፤ በዘመነው ዘመንም የመሻሻል አዝማሚያ ዕንደማይታይበት አካሄዱን ያዩ ታዛቢዎች ገምተዋል።

ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ልጅ ኢያሱን የተኩት በሰላማዊ መንገድ አይደለም። ደርግም ቢሆን መንበረ ሥልጣኑን ሲረከባቸው ሰላማዊ ያልሆነውን መንገድ ተከትሎ ነው። ኢህአዴግ ደርግን ለመጣል ነፍጥ ማንሳት ግድ ብሎታል። አሻጋሪ መንግሥቱ ኢትዮጵያን ሲያስተዳድርም የሚጎረብጥ ነገር አልጠፋም። በሽግግር መንግሥቱ ከፍተኛ ድርሻ የነበረው ኦነግ ከሃገራዊው ስብስብ ተገፍቶም ይሁን በራሱ ምርጫ መውጣቱ፤ የሽግግር መንግሥቱ ያመጣቸውን ውጤቶች ምሉዕነት አጉድሏል።

የሽግግር መንግሥትን ተከትሎ የመጣው የኅብረ-ፓርቲ ስርዓትም ቢሆን፤ መጠፋፋትና መበላላት የሚታይበትን የሃገራችንን የፖለቲካ ባህል ከማከም ይልቅ አባብሶ ገፋበት። ድህረ-ሕገመንግሥት የተመሰረተው አዲሱ የኢፌዲሪ መንግሥትም እስካለንበት ጊዜ ድረስ አምስት ያህል ምርጫዎችን ቢያካሂድም፤ በምርጫዎቹ ሂደትና ውጤት ላይ መተማመን እና ስምምነት የለም። ከእነዚህ እውነታዎች ድምር ውጤት የፖለቲካ ባህላችን እንኳን አካሄዱን መርገጫ ጫማውን እንኳ መቀየር እንዳልቻለ እንገነዘባለን።    

የቅድመ እና ድሕረ ምርጫዎቹ ድራማ እንዳለ ሆኖ፤ ተመርጫለሁ ብሎ ሃገር ሲገዛ የነበረው ኢህአዴግ፤ ራሱን በራሱ ሰዎች አጥፍቶ፤ አልከስምም ያለው ኃይል ተገፍቶ፤ ‘ብልጽግና’ የተባለ አዲስ ፓርቲ አበርክቶ፤ እዚህ ደርሰናል።

የዲሞክራሲ ዐይነተኛ መገለጫ የሆነው ምርጫ ፊቱን ወደ አፍሪካ ሲመልስ የግጭት መንስኤ ነው። እውነታው ሃገራችንንም የሚያካትት ነው።

ምርጫ በጥንት ግሪካዊያንና ሮማዊያን ዘመን የነበረ ልምምድ መሆኑን የታሪክ ሰነዶች ያረጋግጣሉ። በመካከለኛው ዘመንም በተለያዩ ቦታዎች ህዝቦች ተወካዮቻቸውን በመምረጥ የተመሰረቱ መንግሥታት ነበሩ። ለዚህ ትልቅ ምሳሌ የሚሆነው የሆሊ ሮማን ኢምፓየር ነው።

በምርጫ ሥልጣን የጨበጡ ሁሉም መንግሥታት ዴሞክራሲያዊ ነበሩ ወይ? ለሚለው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ግን ለስህተት ይዳርገናል። ምርጫ የዴሞክራሲያዊ መንግሥት አንዱ መለያ እንጂ ብቸኛ ግብአት አይደለም። የሥልጣን ዘመናቸውን ሕጋዊ ሽፋን ሰጥቶ ለማራዘም የተጠቀሙበት ግለሰቦች እና መንግሥታት ድሮም አሁንም አሉ። 

በቅጡ ባልተሰነደው የአፍሪካዊያን ታሪክ ውስጥም ምርጫ እንግዳ ተግባር አይደለም። የጎሳ መሪዎቻቸውን ከዘርሃረግ ውርስ ውጭ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚመርጡ አሉ። ጋና እና ኢትዮጵያ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ።

የእኛን ሃገር ብቻ እንኳ ብንወስድ የኦሮሞ የገዳ ስርአት፣ የትግራይ የባይቶ ስርአት፣ ወዘተ. መሪን በባህላዊው ዴሞክራሲ የሚመርጡ ቀደምት ልማዶቻችን ናቸው።

በተቀረው የአፍሪካ ክፍልም እንደነኚህ ዓይነት የቆዩ ስርዓቶች አሉ። ዘመናዊው የምርጫ ስርዓት በአፍሪካ የታየው በድህረ- ቅኝ አገዛዝ ጊዜ ነው። እነዚህ በአፍሪካ የሚደረጉ ምርጫዎች አልፎ አልፎ ዲሞክራሲያዊ፤ አብዛኛውን ጊዜ የግጭት ምንጮች እየሆኑ እዚህ ደርሰናል።

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በጅቡቲ ምርጫ ላይ አተኩሮ ሰነዳዊ ፊልም (ዶክመንተሪ) የሰራው አልጀዚራ፤ የመንግሥት ደጋፊ ግለሰቦች ለመራጮች ከምርጫ ጣቢያው 200 ሜትር ራቅ ብለው ጫት ሲያድሉ እንደነበር አሳይቷል። ይህንን አዝናኝ የጫት ጉቦ ታሪክ የሰማ ሰው፤ ምርጫ የሚያጭበረብሩት የመንግሥት ደጋፊዎች ብቻ ሊመስሉት ይችላሉ። ነገር ግን በተቃራኒው ደግሞ ጎረቤት ሃገር ኬኒያ ላይ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ራይላ ኦዲንጋ በአንድ ቃለመጠይቃቸው “እኔ ካላሸነፍኩ ምርጫው ተጭበርብሯል” ሲሉ መደመጣቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ናቸው።

በአፍሪካ የተደረጉ ምርጫዎች የመንግሥት ተፅዕኖ ብቻ ሳይሆን የውጭ ጣልቃ-ገብነት ስለነበረባቸውም ጭምር፤ የምርጫ ውጤቶች በአብዛኛው የግጭት መንስኤ ሆነዋል። ይህን የውጭ ተፅዕኖ የተመለከተ ማስረጃም ‘ዊኪሊክስ’ የተሰኘው ድህረ ገጽ ለዓለም ህዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። በአፍሪካና በላቲን አሜሪካ ያሉ መንግሥታት በምዕራባውያን ጫና፤ የምርጫ ጊዜዎቻቸውን እንደ ልዩ አጋጣሚ በመቁጠር መንግሥት የመቀየሪያ ሰበብ ማድረግ የተለመደ ነው። በቦሊቪያ ምርጫውን ያሸነፈው መሪ በምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት በሌላ እንዲተካ እንደተደረገ የያዝነው ዓመት የቅርብ ትዝታችን ነው። በቬንዝዌላም አልሳካ አለ’ንጂ ከፍተኛ የህዝብ ተቀባይነት ያለውን ፕሬዝደንት ማዱሮ በተቃዋሚው ፓርቲ መሪ ሁዋን ጉዋይዶ ለመተካት ጥረት ተደርጎ ነበር።

የኢትዮጵያ ምርጫም ልክ እንደተቀረው የአፍሪካ ክፍል ለውጭ ጣልቃ-ገብነት የተጋለጠ መሆኑ ለሁለም የተገለፀ እውነት ነው። የአሁኑን ምርጫ ይቆየን ብንል እንኳ ባለፉት ምርጫዎች የውጭ ኃይሎች አንዴ ለመንግሥት አንዴ ለተቃዋሚ ድጋፍ እየሰጡ ማሊያ ሲቀያይሩ ታዝበናቸዋል። የዚህ ሀገር የፖለቲካ ባህል ቀውስ የማያጣው እንደ አውሮፓ ሀገራት ሀገራዊ ረባሾች እንጂ ሀገራዊ ፈላስፎች ስለሌሉን ነው የሚሉ አስተያየቶች አሉ። ፖለቲካው እንደ ሄራክሊተስ፣ ፕሌቶ፣ አርስቶትል ወይም ሄግል ያለ አሰላሳይ ጭንቅላት የለውም። ህዝብን የሚመራ ሳይሆን የሚያደናግረው ይበረክታል። በፖለቲካው ውስጥ ግራ ገብ ፈላሰፎች ሲበዙ በሰለጠነ መንገድ መነጋገር አቃተን።

በታዛ መጽሔታችን በተደጋጋሚ ለማንሳት እንደሞከርነው ፖለቲካዊ ባህላችን ቅርፅ-አልባ (Formless) ሆኖ ቀርቷል። ያሳዝናል። አሁን በምርጫ ጉዳይ በምናነሳው ግልፅ ሕገ-መንግሥታዊ ጉዳይ እንኳ ጠባብና ኋላ-ቀር (parochial) አመለካከት ስለምናራምድ ልንግባባ አልቻልንም፤ እንዲያው እንደናቆራለን።

እርግጥ ነው ሕገ-መንግሥቱ ቀንደኛ ተቃዋሚ እንዳለው ሁሉ ቀንደኛ ደጋፊም አለው ብለን ለመነጋገር እንነሳ። አቶ ክፍሌ ወዳጆ ሕገ-መንግሥቱ በ1987 ዓ.ም. ሲፀድቅ አንድ የተናገሩት አባባል እንደነበር ላስታውስ፤ “ሕገመንግሥት በዲንጋይ ላይ ተፃፈ ሰነድ አይደለም። ሊሻሻል፣ ሊለወጥም ይችላል” ነበር ያሉት። ሁሌም ስንነጋገር ከሕገ-መንግሥቱ ስር እንጂ በላይ ሁነን መነጋገር ይቅር። ፖለቲካዊ መፍትሄ ከሕገ-መንግሥቱ ውጪ አይደለምና። የገባንበትን ቀውስ ለመፍታት በሰከነ መንገድ እንነጋገር።

የሃገራችን የምርጫ ባህል እንዳያድግ ምክንያት የሆኑ ብዙ ጉዳዮች ያሉ ቢሆንም፤ ለመፍትሄው ከመሯሯጥ ይልቅ የራስን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በፖለቲካው ተዋናዮች ሲፈፀሙ ዐይተናል፣ አሁንም ዕያየን እንገኛለን። የየግል ጥቅሞቻቸውን ለማሳካት የሚተጉት የፖለቲካ ኃይሎች እንወክለዋለን የሚሉትን ህዝብና ሃገር ጥቅም ባይረሱ፤ በተዘዋዋሪ ዋነኛ ተጠቃሚ የሚሆኑት እነሱው ናቸው። ይህንን ለማገናዘብ ግን ሩቅ አሳቢ መሆንን ይጠይቃል።

አራተኛ መንግሥት የሚባሉት ሚዲያዎች ኃላፊነታቸው ምን እንደሆነ እንኳን ለእነሱ ለታዳሚሆቻቸውም ጭምር የተረሳ ጉዳይ ሆኗል። ሙያቸውን አክብረው፣ ስነ-ምግባሩን ተከትለው፣… በመስራት ፈንታ ለፖለቲካ ፈረሰኞች ምቹ መጋለቢያ ሜዳ ከሆኑ ሰነባበቱ። በምርጫ ምክንያት የሚነሱ እሳት-ለበስ ንትርኮችን ከማለዘብ ይልቅ፤ በወገንተኝነት ጋዝ አርከፍካፊ፣ ክብሪት አቀባይ ሆነዋል።

የሚዲያዎች ነገር አቀጣጣይነት ላይ የፖለቲከኞችን መሰሪነት ታክሎ፤ የሃገራችን የፖለቲካ ባህል አካሄድ፤ አሁን ያለንበትን የኮሮና ወረርሽኝና ቀጣዩን 6ኛ ሃገር አቀፍ ምርጫ፤ ለሃገር በማይጠቅም አሻጥር አገማምዶ አንድ አድርጓቸዋል።

በኮሮና ቫይረስ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ምክንያት መንግሥት መጋቢት 30 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ይታወሳል። የመጀመሪያው የኮሮና ተጠቂ ዜና ከተሰማ ከ26 ቀናት በኋላ የታወጀውን አዋጅ በ8 ቀናት የቀደመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መግለጫ ነው። ቦርዱ መጋቢት 22፣ 2012 ዓ.ም. ኮሮና ቫይረስ በፈጠረው ስጋት ምክንያት 6ኛውን ሐገራዊ ምርጫ በታቀደለት ጊዜ ማካሄድ እንደማይችል አሳውቋል።

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፊት ምርጫ ቦርዱ አቅቶኛል ማለቱን፣ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም የሚሉ አካላት ድምጽ “እኔ አሻግራችኋለሁ” በሚል አረፍተነገር መታለፉን፣ እስከ ነሐሴ 30- 2012 ዓ.ም. የተራዘመውን አዋጅ (በሕገ-መንግሥቱ መሰረት መንግሥት ከዚህ ጊዜ በላይ ማወጅ አይችልም)፣ በምርጫ ሥልጣን የጨበጠው ኢህአዴግ ዘመኑ ሳይጠናቀቅ መክሰሙን፣ ጠቅላይ ምኒስትሩ በዚህ ዓመት መጀመሪያ በተደረገ አንድ ንግግራቸው ምርጫውን ማራዘም እንችላለን ማለታቸውን፣… እና ተያያዥ ጉዳዮችን ገጣጥመው በሴራ መነጽር የተመለከቱትም አልጠፉም። ኮሮና ጥሩ ሰበብ ሆነ እንጂ ቀድሞውንም ጠቅላይ ሚንስትሩ ምርጫ የማድረግ ፍላጎት የላቸውም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።

በዘመነ ደርግ አንድ ግለሰብ ብቻውን ተወዳድሮ እንዲያሸንፍ ከተደረገበት ምርጫ የታሪካችን አካል መሆኑን ሳንዘነጋ ከ1987 ዓ.ም. አንስቶ 5 ምርጫዎችን ያካሄደው የኢፌዲሪ መንግሥት በቅድመ ግምቱ መሰረት የዲሞክራሲ ልምምዱን የሚያዳብር ምርጫ ማድረግ አልቻለም። 6ኛው ሃገራዊ ምርጫ መካሄድ የለበትም ከሚሉት፤ እስከ ምርጫው መደረጉ ግድ ነው እስካሉት ድረስ የ2012ቱን ሃገራዊ ምርጫ አንዳንዴ የመወያያ፣ አለፍ ሲልም የመነታረኪያ ርዕስ ሆኗል። ጉዳዩ ተራ ውይይት ብቻ ሳይሆን አገርን የመበታተን ወይም አምባገነንን የማንገስ ከባድ ስጋትም በውስጡ ይዟል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ሥልጣን በተቆጣጠሩበት የመጀመሪያ ሰሞን እና ወ/ት ብርቱኳን ሚደቅሳ ምርጫ ቦርድን በተረከቡበት ጊዜ የነበረው ተስፋ ተሟጧል የሚሉ ድምጾች መሰማት እየጀመሩ ነው። የብር-ኢዮቤልዩውን የደፈነው የሐገሪቱ ሕገ-መንግሥት በሚያንቋሽሹት ዘንድ ሳይቀር በተደጋጋሚ መጠቀስ ጀምሯል።

በሦስት ሺህ ዘመን ታሪካችን ውስጥ የዳበረ የፓለቲካ ባህል ልምምድ አለመኖሩ የችግሮቹ ምንጭ ነው የሚሉ ምሁራን፤ በልዩነት ውስጥ አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ብሎ በጋራ መኖር፣ የተረኛ እና የአሳዳጅ ተሳዳጅ ትርክቶችን መጣል፣ ታሪክን ባለፈ ማንነት ብቻ እንጂ በዛሬ ወሳኝነት አለመመልከት፣… የችግሩ መፍቻ ቁልፍ ነው ብለው ያቀርባሉ።

በሕገ-መንግሥቱ ዙሪያ

የሕገ-መንግሥትን ጽንሰ ሐሳብ መለማመድ የጀመርነው 1923 ዓ.ም. ነው የሚለው አከራካሪ ነው። ጥቂት የማይባሉ ምሁራን ከዚያ ቀደም ባለው ጊዜ በነበሩ ነገሥታትም ኢትዮጵያ የምትመራበት ሰነድ ነበራት በማለት ይከራከራሉ። ሁለቱም ወገኖች ግን በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን የተዘጋጀውን የመጀመሪያው ሕገ-መንግሥት የዘመናዊት ኢትዮጵያ ጅማሬ እንደሆነ ይስማማሉ።

አንድ ጊዜ የመሻሻል እድል ያጋጠመው የመጀመሪያው ሕገ-መንግሥት ጅማሮው የሚደነቅ ቢሆንም አብዛኛውን ሥልጣን እና መብት ለንጉሠ-ነገሥቱ የሚሰጥ ነው የሚል ትችት ይቀርብበታል። በደርግ ሕገ-መንግሥት እስከተተካበት ጊዜ ድረስም አንድ ጊዜ ተሻሽሏል። የሕገ-መንግሥት እና ሕገ-መንግሥታዊነት ባህላችንን ለማዳበር ብዙም አስተዋጽኦ ሳያበረክት ሙሉ ለሙሉ ተቀዶ በአዲስ ተተክቷል። ከትላንት የተሳሳተ ሕገ-መንግሥታዊ ባህል ያልተማረው የዘመነ ደርግ ሕገ-መንግሥትም እንዲሁ በግልጋሎት መድረኩ ላይ አነስተኛ ሚና ነበረው። በወቅቱ ሕገ-መንግሥት በሚል ተጸውኦ የሚጠራ የሕዝቦች መግባቢያ ሰነድ ስለመኖሩ የማያውቁ ኢትዮጵያዊያን ጥቂት አልነበሩም።

ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለው የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ከቀደሙት ብዙ የተሻሻሉ ነገሮች ቢኖሩትም ከጅማሬው አንስቶ ሙሉ ዕድሜውን ያሳለፈው በሙግት ነው። አይወክለኝም፣ አልተወያየሁበትም፣ አልስማማበትም፣ የሚሉ በአንድ ወገን ሆነው ሲነቅፉት፤ የህልውናችን መሰረት ነው ያሉት ወገኖች በሌላ ወገን ድጋፋቸውን ሲቸሩት ሩብ ክፍለ-ዘመን ያህል ዘልቋል።

በተለይ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ ግን በርከት ያሉ ድምጾች ሕገ-መንግሥት ይከበር ሲሉ ተደምጠዋል። በቀደመው ጊዜ የሕገ-መንግሥቱን አንቀጾች አብዝተው በመቃወም እና አብዝተው በመደገፍ የሚታወቁት ቡድኖች “ፌደራሊስት ኃይሎች” በሚል የጋራ አጀንዳ ውይይቶችን ከፍተዋል። በእርግጥ ይህ ውይይታቸው ጊዜያዊ የፖለቲካ አሰላለፍ ወይስ ዘላቂ መፍትሔ ፍለጋ የሚለውን የዛሬ እና ነገ ኑሯን የሚመሰክሩት ይሆናል። ሕገ-መንግሥቱ ስለምርጫ ያስቀመጣቸው መመሪያዎች ከተፃፉበት ዕለት አንስቶ ዛሬም ድረስ አሉ። በአግባቡ ይተገበራል ወይ? የሚለውን ለሌላ ጊዜ አቆይተን፤ ሕገ-መንግሥቱ ምን እንደሚል እንመልከት።

በአንቀጽ 102 የምርጫ ቦርድን አመሰራረት አስመልክቶ ዝርዝሩ በሕግ እንደሚወሰን ያወሳል። በአንቀጽ 102 (2) ላይ በጠቅላይ ሚንስትሩ አቅራቢነት የቦርዱ አባላት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማሉ ከማለቱ በፊት በአንቀጽ 102 (1)

“በፌደራል እና በክልል የምርጫ ክልሎች ነጻ እና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኝነት እንዲካሄድ ከማንኛውም ተጽእኖ ነጻ የሆነ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይቋቋማል”

ይላል። “ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቋቁማል” የሚለውን የአንቀጹን ሐረግ የሚያነሱት ወገኖች አንቀጽ 52 (ሀ)ን ጨምረው ለሙግት ያቀርቡታል።

አንቀጽ 52 (ሀ)

“ራስን በራስ ማስተዳደርን ዓላማ ያደረገ ክልላዊ መስተዳድር ያዋቅራል፤ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርአት ይገነባል፤ ይህንን ሕገ መንግሥት ይጠብቃል፤ ይከላከላል”

ሰክኖ የመነጋገር፣ ከራስ ጥቅም ይልቅ የሕዝብን ጥቅም የማስቀደም ባሕል የማዳበሩ ፈቃደኝነት ካለ የማይፈታ ችግር እንደሌለ እምነታችን ነው።

6ኛውን ሐገራዊ ምርጫ በተመለከተ ሕገ-መንግሥቱን ተንተርሰው እየተደረጉ የሚገኙት ክርክሮች በዋነኛነት 3 የሕገ-መንግሥቱን አናቅጽት ይመዛሉ።

ምዕራፍ 3 ውስጥ ከሚገኘው አንቀፅ 38 እንጀምር። ይህ አንቀፅ የመምረጥና የመመረጥ፣ በግልም ይሁን በፖለቲካ ፓርቲ የመደራጀት መብትን ለዜጎች ያጎናፅፋል። ለአንቀጹ ማሰሪያ ሆኖ የተደነገገው ደግሞ አንቀፅ 13 ነው። በዚህ አንቀፅ የሚገኘው ንኡስ አንቀፅ 1 እንዲህ ይላል።

“በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ የፌደራል መንግሥትና የክልል ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈፃሚ እና የዳኝነት አካሎች በዚህ ምዕራፍ የተካተቱትን ድንጋጌዎች የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት እና ግዴታ አለባቸው”

ስለዚህ በአንቀፅ 38 የተጠቀሰውን የመምረጥና የመመረጥ የዜጎች መብት እንዲፈፀም የክልልና የፌደራል መንግሥታት ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ግዴታ እንዳለባቸው በአንቀጽ 13 ተደንግጓል። ሕገ-መንግሥቱም በግልፅ ቋንቋ ምርጫ ማድረግ ለፌደራልም ይሁን ለክልል መንግሥት አማራጭ ሳይሆን ግዴታ እንደሆነ ይነግረናል።

ስለ ፖለቲካ ስልጣን የሚያወራው አንቀፅ 56 ደግሞ

“በምክር ቤቱ አብላጫ ድምፅ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅቶች የፌዴራሉን መንግሥት የሕግ አስፈፃሚ አካል ያደራጃል/ያደራጃሉ ይመራል/ይመራሉ።”

ይላል። በዚህ አንቀፅ መሠረት የፖለቲካ ሥልጣን የሚያዘው በምርጫ ከፍተኛ የምክር ቤት መቀመጫን በማግኘት እንደሆነ እንረዳለን።

ምርጫን እና የፖለቲካ ስልጣንን ከሚመለከተው አንቀጽ በተጨማሪ አንቀጽ 9 (3) ላይ ይሕ ኃይለ-ቃል ይገኛል።

“በዚህ ሕገ-መንግሥት ከተደነገገው ውጭ በማናቸውም አኳኋን የመንግሥት ስልጣን መያዝ የተከለከለ ነው።

ኮሮና

የዓለም ስጋት የሆነው ኮሮና ሁሉንም ሰብአዊ እንቅስቃሴዎች አቅቧል። ከአፍሪካ ጋና እና ብሩንዲ ከእስያ ኮሪያ በኮሮና ስጋት ምርጫቸውን ካላራዘሙት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ ወረርሽኙን ሰበብ አድርገው ምርጫቸውን ያራዘሙ፣ የማራዘም ጥያቄ አቅርበው የተከለከሉም አሉ፡፡ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 93 (ለ) ላይ እንዲህ የሚል መልስ እናገኛለን፡-

“የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን፥ ማናቸውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት፥ የፌደራሉ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ስልጣን አለው።”  

በዚህ ድንጋጌ መሰረት የኮሮና ወረርሽኝ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማሳወጅ በቂ ምክንያት ነው። ምርጫ ለማራዘምስ? ምርጫ ማራዘምን በተመከለከተ ከሁለቱም ወገኖች የተቃረኑ አስተያየቶች እናደምጣለን፡፡ ችግሩ ተቃርኖ ሐሳቦችን መያዙ ሳይሆን የኔ ሐሳብ ብቻ ነው ትክክል ማለቱ ነው፡፡

ተቃራኒ ሐሳቦችን አቻችሎ፣ ለሐገር የሚበጀውን ሐሳብ አቅርቦ በሐሳብ አሸንፎ እና ተሸንፎ መስማማትን ነባሩ የፖለቲካ ባህላችን አላስተማረንም። ስለሆነም ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ራሳቸውን ወይም ቡድናቸውን መጥቀም የሚችሉበት ጥግ ላይ ቆመዋል። ለሐገር አንድነት፣ የሕዝቦች ደህንነት፣… ቅድሚያ ያልተሰጣቸው ሁለተኛ ተግባራት መስለዋል። የዛሬው የምርጫ ሙግት እና ሕገ-መንግሥታዊ ክርክር ወዴት ያደርሰናል? የሚለው ግዘፍ የሚነሳ ጥያቄ ነው። እንደ ቀድሞው ወደ መጠፋፋት ወይስ አዲስ የፖለቲካ ባህል ወደ መገንባት?

የመንግሥት አቋም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ማካሄድ እንደማይችል ካሳወቀ በኋላ መንግሥት አማራጮችን አቅርቧል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ፣ ሕገ-መንግሥቱን ማሻሻል፣ የሕገ-መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ የሚሉት እነኚህ አራት አማራጮች አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት የሥልጣን ጊዜ ለማራዘም ያደሉ ናቸው ከሚል የታዛቢዎች ትችት አላመለጡም። ቀሪ አማራጮች አልተካተቱም፣ መንግሥት ፓርቲዎችን ያነጋገረው በራሱ ወስኖ ካበቃ በኋላ ነው፣… እና መሰል አሉታዊ ሐሳቦች አስተናግዷል።

ለረጅም ጊዜ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋነኛ ሰዎች አንዱ ሆነው ለመዝለቅ ከቻሉ ጥቂቶች መሃል አቶ ልደቱ አያሌው ተጠቃሽ ናቸው። አቶ ልደቱ መንግሥት ባቀረባቸው አማራጮች ላይ እንዲህ ሲሉ ተደምጠዋል፡-

“በአንቀፅ 60 (1) መሠረት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ከፓርላማው ጋር ተመካክረው አብላጫ ድምፅ ስላላቸው ምክርቤቱን መበተን ይችላሉ። አስቸኳይ አዋጅ ማወጅም ይቻላል። እንዲሁም የሕገ-መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅም ይችላሉ። ይህንን ማድረግ የሚችሉት በህዝብ ተመርጠው በተሰጣቸው የ5 ዓመት የሥልጣን ዘመን ብቻ ነው። ከዛ ውጪ ግን መንግሥት ሥልጣን ለማራዘም ተብሎ ከተሰጠው Mandate (ተልእኮ) ውጪ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ አይችልም። ስለዚህ እነዚህ አማራጮች በሙሉ የማይቻሉ ናቸው። በእኔ እምነት ሦስተኛው አማራጭ ሕገ-መንግሥቱን ማሻሻል የሚለው ይቻላል። ምክንያቱም በምክርቤቱ ከ2/3ኛ በላይ ድምፅ አላቸውና። ያም ሆኖ ግን በዚህ አካሄድ ሕገ-መንግሥቱን ማሻሻል ልክ ነው ብዬ አላምንም።”

በአንድ የግል ቴሌቪዥን ቀርበው ይህንን ንግግር ያደረጉት አቶ ልደቱ አያሌው ምንም እንኳ አብዛኛው የንግግር ክፍላቸው ላይ የገለፁትን ሐሳብ የበረታ ተቃውሞ ባይገጥመውም በሕገ-መንግሥት መሻሻል ላይ ያነሷቸው ነጥቦች የአረዳድ ክፍተት አለባቸው ለሚሉ ወገኖች ትችት አጋልጧቸዋል።

ፖለቲከኛው እንዳሉት ሕገ-መንግሥቱን ለማሻሻል የህዝብ ተዋካዮች ምክር ቤትን 2/3ኛ በላይ ድምጽ ከማግኘት በተጨማሪ ሌሎች መሟላት የሚገባቸው ነገሮች አሉ የተከራካሪዎቹ ሐሳብ ነው። በሕገ-መንግሥቱ መሰረት ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። የዜጎች የመምረጥና የመመረጥ መብት ያለው በሕገመንግሥቱ ምዕራፍ 3 አንቀፅ 38 ነውና፤ ይህንን የሕገ-መንግሥቱን ክፍል ለማሻሻል ደግሞ አንቀፅ 105 (1)ን ማየት ግድ ይለናል።

አንቀፅ 105 (1)

“በዚህ ህገመንግስት ምዕራፍ 3 የተዘረዘሩት መብቶችና ነፃነቶች በሙሉ፥ ይህ አንቀፅ 4፥ እንዲሁም አንቀፅ 104 ሊሻሻሉ የሚችሉት በሚከተለው አካኋን ብቻ ይሆናል። ሀ) ሁሉም የክልል ምክርቤቶች የቀረበውን ማሻሻያ በድምፅ ብልጫ ሲያፀድቁት። ለ) የፌዴራሉ መንግስት የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት በ2/3ኛ ድምፅ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያፀድቀው። እና ሐ) የፌዴሬሽኑ ምክርቤት በ2/3ኛ ድምፅ ማሻሻያውን ሲያፀድቀው ነው።”

የሐሳቡ መደምደሚያ መንግሥት አማራጮቹን ያቀረበው አስቸኳይ አዋጁን ለማራዘምና ምርጫውን ለመግፋት ነው የሚል ነው።  

ምርጫን በተመለከተ አሁን ያለው መንግስት ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ለማድረግ ከላይ ያየናቸውን 3 ቅድመ ሁኔታዎች ሊያሟላ ግድ ይለዋል። ምንም እንኳ በአንቀጽ 104 (ለ) እና (ሐ) የተጠቀሱትን ለሟሟላት ባይቸገርም፤  በ (ሀ) ላይ የተጠቀሰውን “ሁሉም የክልል ምክርቤቶች የቀረበውን ማሻሻያ በድምፅ ብልጫ ሲያፀድቁት”  የሚለውን ለማሟላት ግን ቀላል የሚሆን አይመስልም።  

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በፖለቲካል አክቲቪስትነቱ የሚታወቀው አቶ ጃዋር መሐመድ ደግሞ በሕገ-መንግሥቱ ማሻሻል ጉዳይ ላይ የሚከተለውን ተናግሯል፡-

“በዚህ ህገ-መንግሥት ውስጥ ምርጫን ስለማራዘም ምንም ነገር አልተነገረም። አልተጻፈም። አልተጠቀሰም። ምክንያቱም ይሄ ያለ ምክንያት አይደለም። በአፍሪካ ውስጥ በተደጋጋሚ ህገ-መንግሥትን እያሻሻሉ የሥራ ዘመናቸውን ስለሚያራዝም እስከ ሦስት እስከ መጨረሻ ከዛም በላይ እስከረጅም የሚያደርጉበት ሁኔታ አለ። ይሄን ህገ-መንግሥት የጻፉት ሰዎች ከስልሳዎቹ እንቅስቃሴ የወጡና አፍሪካ ውስጥ አምባገነኖች እንዴት ይንቀሳቀሱ እንደነበር የተረዱ ከመሆናቸው የተነሳ ያንን ዕድል በመጠቀም ህገመንግስታዊ ቀዳዳ ጭራሽ ሊፈጥሩለት አልፈለጉም። ከዚህ አንጻር ህገ-መንግሥቱ ምርጫ ፈጽሞ ለማስተላለፍ እንዳይቻል ታስቦበት ነው የተጻፈው። አሁንም ቢሆን ምርጫን ለማራዘም ህገመንግሥትን ማሻሻል እናድርግ ከሆነ ሁለት ችግር ይፈጠራል። አንደኛ ኮሮና መቼ እንደሚጠፋ ስለማናውቅ ለምን ያህል ጊዜ ነው ምርጫው የሚተላለፈው የሚለው ነው። ሁለተኛው ደግሞ ቀጥሎ እሚመጣው አመራርስ ምርጫ በቀረበ ቁጥር ቀውስ ፈጥሮ እሚያራዝመው ከሆነስ፤ ስለዚህ እሱም ያችን የህገ-መንግሥትን ክፍተት በመጠቀም በፈለገው ጊዜ እንዲከናወን ያደርጋል እንደማለት ነው። ስለዚህ ህገ-መንግሥቱን በማሻሻል ምርጫውን ማራዘም የሚለውን የሚያስኬድ መንገድ አይደለም። እንዲያውም አደገኛ ነው።”

ጃዋር የጠቀሳቸው ስጋቶች በእርግጥም እውን የሚሆኑ ከሆነ ለቀጣዩ የሃገራችን ጉዞ ትልቅ አደጋ እንደሚደቅኑ እሙን ነው።

መደምደሚያ

ፕሌቶ አንድን የፖለቲካ ችግር መፍትሄ ለመስጠት ያነሳውን ጥያቄ ማሰታወስ ያስፈልጋል። “ማን ይምራ? የማን ፍላጎት ሕግ ይሁን?” የሚለውን ተጠየቅ ጀማሪ የፍልስፍና ተማሪዎች እንኳ የሚያስታውሱት ነው። ከፈረንሳዩ ፈላስፋ ሩሶ መነሳት በፊት ለፕሎቶ ጥያቄዎች የተሰጡት መልሶች “ልዑሉ” የሚል ነበር። ሩሶ ግን አዲስና አብዮታዊ መልስ ነበር ለጥያቄዎቹ መልስ የሰጠው። እንዲህ አለ። “ልዑል አይደለም፣ ሕዝብ ነው መምራት ያለበት” ሲል የማያወላዳ መልስ ሰጠ። የአንድ ግለሰብ ፍላጎት ሳይሆን የሁሉም ዜጎች ፍላጎቶች መከበር አለባቸው አለ። በዚህ መንገድም ሩሶ የሕዝቦችን ፍላጎቶች ለማሳካት፣ እሱ እንደሚለው የአጠቃላዩ ህዝብ ፍላጎት (general will) መሳካት አለበት ሲል ያስቀምጣል። ሕገ-መንግሥትና መንግሥት የሚቆመውም ለዚህ የህዝብ ፍላጎት መሆኑን በጥልቅ እንመን።

የተሳካ ምርጫን እንደባህል ካየንና፤ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማሳለጥ ከተጋን እኛ ላለንበት ዘመን ብቻ ሳይሆን፤ ልጆቻችን ለሚኖሩበት ጊዜም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ማስረከብ እንችላለን።

ሕገ-መንግሥቱ እንዲሻሻል የሚገፉት የፖለቲካ ኃይሎችም ይሁኑ ምርጫ ይደረግ እና አይደረግ ባዮች ቅን አስተሳሰብ ሊኖራቸው ይገባል። ይህ መሆን ከቻለ መፍትሔው የሕዝቦች ስምምነት ሰነዱ ላይ ይገኛል። ጉዳዩ የሐገር፣ የሰላም እና የመረጋጋት፣ የአገር አንድነት፣… ነውና ሁሉም ፓርቲዎች እዚህ ላይ በንቃት መሳተፍ ይገባቸዋል። “ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም” ነውና የሃገራችን ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች፣ የሲቪል ማኅበረሰቡ፣ ህዝቡ፣ ሚዲያው… ተወያይቶ መፍትሔ ለማምጣት ከልብ ከታተሩና፤ ሕገ-መንግሥቱን የተከተለ አካሄድ ከመረጡ የዚህ ሁሉ ችግራችን የመፍትሔ ቁልፍ ቅርብ የተቀመጠ ይሆናል። እስካሁን በተለመደው አካሄድ፤ የመጠላለፍ ጉዟችን ይበጀናል ብለው በጥፋት መንገድ ከቀጠሉ ግን በችግር ተሞልታ በሩ ለተቆለፈባት ሃገራችን የመፍትሔ ቁልፉ በሩቁም ቢፈለግ የማይገኝ ይሆናል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top