ቀዳሚ ቃል

ቀዳሚ ቃል

በአጭር ጊዜ ውስጥ የዓለምን ተለምዷዊ አካሄድ ባልተጠበቀ መንገድ ያስጓዘው ኮቪድ-19 (ኮሮና ቫይረስ) የሐገራችንም ስጋት መሆን ከጀመረ ሳምንታት ተቆጥረዋል። ትላንት በሩቁ ስንመለከተው የነበረው ጥፋት ዛሬ ደጃችን ላይ ነው። የጤና እና የማኅበራዊ ደህንነት ፖሊሲያቸው የጠነከረውን አገራት ያብረከረከው ተህዋስ የምንተነፍሰው አየር ላይ ናኝቷል። የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የቴክኖሎጂ፣ የስፖርት፣ የባህል፣ የኪነጥበብ፣… ዜናዎች በኮሮና እና ኮሮና ነክ ወሬዎች ተተክተዋል። እንቅስቃሴአችን ብቻ ሳይሆን ሀሳባችን እና አስተሳሰባችንም ጭምር ተህዋሱን በመከላከል ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው፡፡

 ይሁን እንጂ በፍጥነት መላቀቅ የማንችለው የቀደመ ልማዳችን ለተህዋሱ መዛመት ምቹ ሁኔታን እያመቻቸ ነው፡፡ የሐኪሞችን ምክር እያደመጥን አይደለም፡፡ ምላሻችን አዝጋሚ ነው፡፡ የዘገየው ምላሽ ዋጋ ካስከፈላቸው ሀገሮች የተማርን አይመስልም፡፡ የተጠናከረ ቁጥጥር እና ስርአት ማክበር ሞትን ካስቀረላቸው ሐገሮች ተሞኩሮ የቀሰምን አይመስልም፡፡

ራሳችንን በቁጥር እያጽናናን ነው፡፡ የታማሚዎቻችን ብዛት ሁለት ዲጅት አልሞላም እንላለን፡፡ ከጠቅላላ ቁጥራችን ጋር እያካፈልን ፐርሰንት እንሰራለን፡፡ አንድ ተገቢውን ጥንቃቄ ያላደረገ ህንዳዊ የሐይማኖት ሰባኪ አርባ ሺሕ ሰዎችን ማስያዙን እንዘነጋለን፡፡ አንድ ቀድማ የመመርመር እድሏን ያዘገየች ኮርያዊት ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎችን በቫይረሱ እንዳስያዘች ለማሰብ ጊዜ አጥተናል፡፡

ራሳችንን እያሞኘን ነው፡፡ ቫይረሱ ለጥቁር ሰው፣ ለነጭ ሽንኩርት፣ ለአየር ንብረት እንደሚበገር እናወራለን፡፡ የዓለም ጤና ድርጅትን የጥንቃቄ መመሪያ ጥለን ምንጩ ባልታወቀ ሕግ እንዳኛለን፡፡ ሰፊ ምርምር እና ረጅም የፍተሻ ሂደት ባለው የመድሃኒቱ ግኝት ዜና የተጋነነ ተስፋ እናደርጋለን፡፡…

አሁንም አልረፈደም፡፡ ጥቂት የጥንቃቄ ድርጊቶች የበዛውን ኃላፊነት እንድንወጣ እድል ይሰጡናል፡፡ ጥቂት የቤት ውስጥ ትእግስት የብዙኃንን ሞት ያስቀራል፡፡ ጥቂት የመረዳዳት ድርጊት የበዛ ማኅበራዊ ኪሳራ ውስጥ እንዳንወድቅ ያደርጋል፡፡ ማንም ብቻውን ሊተርፍ ወይም ብቻውን ሊሞት አይችልም፡፡ ሁላችንም ለሁላችንም እያንዳንዳችን ለሁላችንም ስንል ተገቢውን ጥንቃቄ እንውሰድ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top