አጭር ልብወለድ

ፕሮፌሰሩ

ለንደን እጅግ በጣም ቀዝቃዛ የምትሆንበበት ጊዜ መድረሱ ነበር። ዞር ብሎ የሀገሩን ባንዲራ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ ተመለከተ። ጅማ የምትገኝው እናቱን (ያለ አባት ያሣደገችውን) እያሰበ እንባው ሊፈስ ሲታገለው እንደምንም ተቆጣጠረው። Hethrow International Airport ሁሉንም የሚያስረሳ ሆነበት።

“አወይ መሠልጠን፣ አቤት ተዓምር፣ ወይ እንግልጣር” አለ ገና ከኤርፖርቱ ሳይወጣ። በአውሮፕላን የተሣፈረው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ኧረ እንደውም ውስጥ ሽቅብ ብሎታል። ሆስተሶቹ እንደህፃን ልጅ ባይንከባከቡት ኖሮ ሐፍረቱ ይጨምር ነበር። ባላገርነቱ ለራሱም አሳቀው። ስለ አውሮፕላን ተሳፍረው ከሚያውቁ ሰዎች መረጃ ቢወስድም አደጋው አልቀረለትም። እንግሊዝም የመጀመሪያው ከኢትዮጵያ ውጪ ያያት ሀገር ልትሆን ነው። “እንግልጣር” ይላታል። አይወዳቸውም፣ ህዝቡንም መልክዐ ምድሯንም። ወደማይወደው ሀገር የመጣው ነፃ የትምህርት ዕድል የሚጠላት ሀገር አመቻችታለት ነው፡፡ ቦርሳውን ተሸክሞ ወደ እንግዳ መቀበያው ሲሄድ በሚያየው ነገር ሁሉ ይደመማል። እቃ ማመላለሻ ጋሪው፣ ሱቆችን፣ ግዙፍ አውሮፕላንና የሠው ብዛት፣ የኤርፐርቱን ስፋት እያየ እጅጉን ተገረመ። መውጫው ወዴት እንደሆነ በመጠየቅ አብረውት የመጡትን እየተከተለ  ወደ መውጫው ደረሰ። ስሙ በነጭ ወረቀት ላይ ተፅፎ ተመለከተ። ወረቀቱን የያዘው ነጭ ሠው ”ዋቅጅራ ነህ?” አለው?

“አልተሣሣትክም” ብሎ መለሰለት፡፡

“ስሜ ዊልያም ካርኒጌ ሲሆን ከእንግሊዝ የት/ት ሚኒስቴር የስኮላርሺፕ ክፍል ሀላፊ ነኝ” አለውና

“ስለዚህ አሁን በቀጥታ ወደ መ/ቤታችን ሄደን፣ ሟሟላት ያለብህን ነገር ትከዉናለህ” ብሎ ታክሲ ውስጥ ገቡ፡፡ “ለንደንን ጥቂት እያት ነው ወይስ ደክሞሀል?” ሲል ለእንግዳው ጥያቄ አቀረበለት፣ ተስማማ፡፡

በለንደን አውራ ጎዳና ተሽሎከለኩ፣ ለንደን ብሪጅን አቋረጡ። ሳሆ አደባባይን ቃኙ። አስጎበኝው በሚያልፉበት ቦታ ገለፃ ያደርጋል። ሹፌር ዝም ብሎ ፈገግ ይላል። “የእንግልጣሮች መርዝ” ይለዋል ዋቅጅራ፣ የቴምስ ወንዝ ዳርቻ በሚያምሩ አስፋልቶች እየታከኩ ወደ መ/ቤቱ ደረሱ፡፡

ሚ/ር ዊልያም ካርኒጌ ስለሚማርበት ዩኒቨርሲቲ (ኦክስፎርድ)፣ ስለስኮላርሺፑና ስለ ት/ት አይነቱ (አንትሮፖሎጂ)፣ በወር ሁለት ሺህ ፓውንድ እንደሚከፈለው፣ ለት/ት መግዣ መሣሪያ በአመት 500 ፓውንድ እንደሚሠጠው ነገረው፣ እንዲሁም በእንግሊዝ ለመኖር ካርታ ስለሚያስፈልግ የተዘጋጀ ካርታ አቀበለው፣ ለንደን መቆየት ከፈለገ ጥቂት ጊዜ መቆየት እንደሚችል አሳወቀው፡፡ ለንደን መቆየት እንደማይፈልግ ሲነግረው በቀጥታ የመጓጓዣ እቃውን ይዞለት ወደ Paddington ጉዞ ጀመሩ፡፡ በባቡር ወደ ዩኒቨርሲቲዋ ከተማ ሊሸኘው፣ ፓዲንግተን ለንደን ውስጥ ካሉ ባቡር ጣቢያዎች አንዱ ሲሆን ኦክስፎርድ ደግሞ ኦክስፎርዲሸ ከተማ ውስጥ የሚገኝ ከአለም ገናናው ተቋም ነው፡፡

ባቡር ጣቢያው ደረሱ። ሚ/ር ዊልያም ትኬት ቆረጠለት። የቆረጠውን ትኬት ተቋሙ ቃል ከገባለት ደሞዝ ግማሹን ሠጠው። “ስለረዳኸኝ አመሠግናለሁ  ሚ/ር ዊልያምስ ” አለ::

“መልካም የት/ት ወራት እመኝልሀለሁ፣ ሆኖም ኦክስፎርድ እንደሌሎቹ ዩኒቨርሲቲዎች እንዳይመስልህ በተለይ ለጥቁሮች አይቻልም” ሲለው የዋቅጅራ ደም ስር ተገታተረ ሆኖም ያልተጠበቀ መልስ ሰጠ።

“ከተከበረች፣ ማንም ቅኝ ያልገዛት፣ የራሷ ፊደል ከፈጠረች፣ ዲሞክራሲ አለም ባግባቡ ሳይረዳ ካጣጣመች ሀገር የመጣሁ ነኝ። ያንተው እንግሊዝ እንኳ አሁን ከተናገርኩት  አንዱም አይመለከታትም ከዛ ደግሞ ታላቋ ምናምን ብሪታንያ ትላላችሁ” አለው።

ተኳረፉ። በእንግሊዛዊው ኩርፊያ ውስጥ ጥቂት ፈገግታ ነበረበት፣ ያው የተለመደው ለበጣቸው መሆኑ ነው። “እኔ ምን ጨነቀኝ? የምትቋቋመዉ ግን አይመስለኝም” ብሎት ጥሎት ሊሄድ ሲል፣  በንዴት የጦፈው ሀበሻ እጁን ይዞ

“እየውልህ ሂድና ቅኝ ለገዛችኋቸው ሸውዳቸው፣ ለእኔ ይህን ለማለት ግን አቅም ያጥርሃል” ብሎት እያፏጨች ወደቀረበችው ባቡር ገባ፡፡

በደስታ ባህር እየዋኘ ወደ ኦክስፎርድ አቀና። ጥቂት ቆመ፣ እንዳይዞርበት ተሽቀዳድሞ ወንበር ያዘ። አልቀረለትም ዞረበት። በተለይ ከመስኮቱ ውጪ ያለውን ሲመለከት ባሰበት፣ አይኑን ጨፈነ። “ጌታ ሆይ እባክህ ከዚህ ውርደት አድነኝ !!” አለ። አይኑን መዝጋቱ ጠቅሞታል። ባቡሩ አንድም ጥቁር አልያዘም፣ እሱ ብቻ!! ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ተሠምቶታል። የስኮላርሺፕ ክፍል ኃላፊውን  ባስታጠቀው የመልስ ምት አንጀቱ ርሷል። ለንደን ሰንብት ተብሎ ችላ ማለቱንም ወዶታል። “ጥበብ የምቀስመው ኦክስፎርድ፣ ለንደን ምን ይረባኛል?” እና ድንገት “የሌባ ሀገር” የሚል ቃል ሲወጣው ዙሪያው ያሉ የፈረንጆች ራስ ወደሱ ዞሩ። “ሠሙኝ እንዴ?” ብሎ ለብቻው ሣቀ።

ባቡሩ በብርሀን ፍጥነት ይምዘገዘጋል። ከየት ተነስቶ በፍጥነት የት እንደደረሠ ለራሱም አስደንቆታል። በኩራዝ ሲያጠና፣ በእረኝነቱ ጊዜ ደብተር ሲገልጥ፣ ለእናቱ ጀፈል ለይቶላት፣ እንዲሁም የቡና ቅጠል ሲሸመጥጥላት፣ ቡናውን ሲቆላ፣ ውቀጥ ተብሎ ታዞ ከሙቀጫው የሚወጣው ድምፅ፣ ከልጅነት ጓደኞቹ ጋር ከካልሲ ኳስ አበጅቶ ቴዘር ሲጫወት፣ አዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመጣ አስፋልት መሀል ቆሞ ቴቪ እያየ የደነገጠው ነገር፣ ስሙ በታይፕ ወረቀት ላይ ተፅፎ ያየበትን ጊዜን እያስታወሰ፤ አንዴ ሲያዝን አንዴ ሲደሰት ኦክስፎርድ ደረሰ። ኦክስፎርድ ፓርክ ዌይ ሲባል ቸኩሎ ወረደ። እቃውን አንጠልጥሎ ከኦክስፎርድ ባቡር ጣቢያ ወደ መውጫው አቀና። የመውጫውን ደረጃ ሰዎችን እየተከተለ ወረደ። ዙሪያውን የሚወጡና የሚወርዱ ታክሲዎች ስለበዙለት ደስታ ተሠማው፣ ”ታክሲ” ብሎ ጮኸ። ፈረንጆች Blonde የሚሉት(ፈዛዛ ቢጫ ፀጉር ያለው) ሹፌር “ግባ” አለው። “ወደ አንትሮፖሎጂ ተቋም ውሠደኝ” አለው። ከOX2 8HA ጎዳና  ተነስተው በባንቤሪ A4165 መንገድ አድርገው ወደ ዩኒቨርሲቲው Institute of Social and Cultural Anthropology (61 ባንቤሪ መንገድ ፓርክ ታውን) አቀኑ፡፡ ከ10 ደቂቃ ጉዞ በኋላ “This is it’ አለው ሹፌሩ:: የተጠየቀውን ሂሳብ ከፍሎ ወደ ተንጣለለው ት/ቤት አዘገመ። ለመደነቅ አፍታ አልወሰደበትም። በኪነ ህንፃው ተማረከ፣ ተደምሞ ፈዝዞ ቀረ። ቀጥታ ወደ ዲፓርትመንቱ ኃላፊ አዘገመ …።

ዶክመንቶቹን አገላብጦ ያየው የዲፖርትመንት ኃላፊው፤ ከተቋሙ የሚጠበቀውን፣ ከእሱ የሚጠበቀውን፣ አስረድቶት ወደ መኝታው መራው።

የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሣምንታት የፍዘት ነበር ማለት ይቀላል። አዲስ በተዋወቀው ህንዳዊ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ጋር ታዋቂውን ቦልድያን ላይብረሪ አይቷል። ቴምስ ወንዝን በጀልባ ሄደባት። ታዋቂውን በ1071 ዓ.ም በንጉስ ዊልይም የተሠራውን የኦክስፎርድ ካስትል ጎብኝቷል። ቦታኒክ ጋርደን ላይ ከመላው አለም የተሠበሠቡ አዝርዕትን እያየ  ተመስጧል። ሳክሶን ታወር ላይ ወጥቶ ቦካርዶ እስር ቤትን አማትሯል። ትልቋን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤ/ክርስትያን 124 ደረጃዎችን በመውጣት አራቱንም የከተማዋ ክፍሎች ቃኝቷል፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ ግን እንግልጣር ደረቀችበት። ችከላውን ተያያዘው፡፡

ዩኒቨርሲቲው የከረንቡላ መጫወቻ አዳራሽ፣ አስደማሚ ላይብረሪ፣ ቴሌቭዥን መመልከቻ ሳሎን፣ የተማሪዎች መመገቢያ ሬስቶራንት አለው፡፡ እንደአመጋገብ ባህላቸው ቁርስ ላይ ኮርን ፍሌክሱን ወተት ውስጥ በመክተት ይበላል። ምሳው ላይ እንቁላል በተጠበሰ የአሣ ስጋ በባቄላ፣ ማርመላታም፣ ሳንድዊች ይበላል። እራት ደግሞ ስጋና በመረቅ የተቀቀለ አተር ከካሮትና ድንች ጋር ይመገባል፡፡ ለሚቀጥሉት አራት አመታት እነዚሁኑ እየተመገበ ይኖራል፡፡

ኑሮ በኦክስፎርድ ቀንቶለታል፣ የት/ት ውጤቱ እጅግ በጣም ጥሩ ነው። ህይወትን የምታጣፍጥለት ኤልሳቤት የምትባል ገርል ፍሬንድ አለችው። ውበት ነች እራሷ። ኦክስፎርድ ፋሽን ማስተማር ጀመረ ወይ ያስብላል ቁመናዋ፣ ወይም የዩኒቨርሲቲው ሊቃውንት የወሲብ አምሮት ለመቀስቀስ ከእንግሊዞች ሁሉ ተመርጣ ከእንግሊዝ መንግስት የቀረበች መባ ትመስላለች። ኤልሳቤት ይህ ቀረሽ የማትባል ጎበዝ የህክምና ተማሪም ነች። ፍቅሯ ለእብደት የተጠጋ ነው። የተዋወቁት እንዲህ ባለገጠመኝ ነው…

ከእለታት በአንዱ ቀን አርብ ምሽት ከቅድስት ሄለን መተላለፊያ ከሚገኘው ተርፍ ከጥንታዊው ታቨርን ባር ተቀምጦ ምሽቱን በጥናታዊ ፅሁፍ ጥናት የቸከውን ህይወት በቀዝቃዛ የኢንግሊዝ ቢራ ያወራርዳል፡፡ Black Friday ለአብዛኛው የካምፓስ ተማሪ ደማቅና ተናፋቂ ነች፡፡ የኦክስፎርድና የኦክስፎርድ ብሩክስ ተማሪዎች መዝናኛ፣ የወደዷትን የሚጠይቁበት፣ ፖለቲካዊ ዲስኩሮች የሚሰማበት፣ ሙዚቃ የሚደመጥበት ፣አነቃቂ ንግግሮች የሚሠሙበት ነው፡፡

አብረዋት የሚማሩ ወንዶች ከብበዋታል። ቀልባቸው ሁሉ ወደርሷ ነበር። ሁሉም ጂንየስ ናቸው። መጠጡንና ምግቡን ተያይዘውታል። የሚወዱት ሙዚቃ ሲሰማ ይጮሃሉ። ሁሉም ብሪታኒያዊያን ናቸው። ድንገት ሙዚቃው ተቋረጠና፣ አንድ ጥቁር ዲስኩር ማሰማቱን ጀመረ። “አፍሪካ ለአለም ያበረከተችው ስልጣኔ” በሚል ርዕስ  ቀኑን ሙሉ ተነተነ። ከግብፅ እስከ ዚምባብዌ ስልጣኔ፣ ከሜሮይ እስከ አክሱም ዘረዘረ። እንግሊዝንም ወቀሰ፣ ፈረንሣይንም ረገመ፣ አሜሪካንንም አረከሠ። ከመድረኩ ሲወርድ አድናቆት ተቸረው። በተለይ ደግሞ ኤልሳቤት ተደነቀች። ፕሮግራሙ እስኪያልቅ ድረስ ስለሱ ለማወቅ ጓጓች። እርሱም እንደርሷ በሰዎች ተከብቧል። “ችርስ” ብላው ያላያት መሠለ። ደነገጠች። እልህ ያዛት። ሊወጣ ሲል ተከትላው ወጣች። “ያቀረብከውን ፅሁፍ ወድጄዋለሁ” አለችው። “አመግናለሁ” ብሏት ሄደ። እልኋ ተናንቋት ተመልሳ “ስለ አፍሪካ ማወቅ እፈልጋለሁ” ብላ፤  እየተግደረደች “እባክህን ስለ አፍሪካ ማወቅ ስለፈለግሁ ተገናኝተን ብናወራ” አለችው።

ጥቂት አሰብ አድርጎ “አርብ ግራንድ ካፌ 8፡00 ሰዓት (2፡00 PM)” ብሎ ጥሏት ሄደ።

እጅግ ደስ አላት። ተቁነጠነጠች። አዲስ ስሜት ተቆናጠጣት። “ምን እየሆንኩ ነው?” ብላ እራሷን ጠየቀች። ወደ ኮሌጅዋ እብስ አለች። ግራንድ ካፌ እንደምንግዜውም በተስተናጋጆች ጢም ብሏል። ኤልሣቤት 7፡3ዐ ላይ ቀድማ ተቀምጣለች። ሠዓቷን ደጋግማ ትመለከታለች። አርብ እሰኪደርስ እንቅልፍ አልነበራትም። እነሆ ቀኑ ደረሰ። ካፌ ውስጥ ዐይኖች እየተፈራረቁባት ነው። ጥቁር ሰው እየጠበቀች መሆኑን ማንም አልገመተም። ነጭ ቡና(በጥቂት ቴምፕሬቸር የሚቆላ ቡና) አዘዘች። እሱ እስኪመጣ ድረስ፤ እየጠጣች መንገድ ላይ የገዛችውን ዘጋርድያን ጋዜጣ ገልጣ የፊት ገፁ ላይ ተቸከለች። ብዙ ገፆችን ገለጠች። ሆኖም ቆየባት። ተረበሸች። ከመጣች አንድ ሠዓት ሆኗታል። ቡናውን ጠጣች። ጋዜጣውንም አነበበች። በርግጥ ያነበበች መሠለች እንጂ አላነበበችውም ዝም ብላ ታየዋለች። ዝር የሚል ጥቁር የለም። የሚወጣውም የሚገባውም ነጭ ነው። “ሠራልኝ” አለች። አስተናጋጁን ጠራች። ድንገት በሩ ሲከፈት ደነገጠች። እሱ እራሱ ነው። ተቁነጠነጠች። እስተናጋጁ ከመጣ በኋላ እንዲመጣ ነገረችው። ከሠላምታው በኋላ ጥቂት ዝም አሉ…

ጥቁር ቡና አዝዞ፣ የጨዋታውን ርዕስ አነሣ። ይጠይቃታል ትመልስለታለች። ይቆሰቁሳታል ትዘረዝራለች። በመጨረሻም “ምግብ ልጋብዝህ?” አለችው። እሷ ምንግዜም አርብ ምንግዜም Turf Tavern ማሣለፍ ልማዷ ነው። ሆኖም ዛሬ ለብቻዋ ጊዜ ማሣለፍ ፈልጋለች። ወደ ጥንታዊውና ደማቁ Oxford Castle Quarter ወደሚባል ሬስቶራንት ይዛው ሄደች። ሁሉም ነገር እንግሊዛዊ ነው። ማዕዱ፣ የአበላሉ መንገድ፣ ወይኑ፣ ጨዋታው እየደራ አካላዊ ቅርበታቸውም እየጨመረ መጣ። እዚህ እንደ ግራንድ ካፌና እንደመጡበት የህዝብ አውቶብስ ያፈጠጠባቸው አልነበረም። የወይኑን መገባደድ ተከትሎ በእግር ሽርሽር እንዲያደርጉ ጋበዘችው፡፡

ሳያውቁት እጃቸው ተቆላልፎ ነበር። ጉዟቸውን ወደ ሳንፎርድ ሎክ አድርገዋል። ወጋቸውም ቀጥሏል። ሆኖም የአፍሪካ ስልጣኔ ነገር አልተነሣበትም። ከሠዓታት ጉዞ በኋላ ሳያስበው  ሣመችው። ቢደነግጥም  እሱ ደግሞ ባሰበት…

ከዚያች ዕለት ጀምረው በኦክስፎርድ ተደናቂ ጥንዶች ሆኑ። ከሰኞ እስከ ሐሙስ ያጡትን ከአርብ እስከ እሁድ ያካክሱታል። አርብ ፍቅር ይሰሩባታል። ቅዳሜና እሁድ ወክ ያደርጉባታል። ታዋቂ ጋዜጦችን ያነቡበታል። የዲከንስን፣ የሼክስፒርን፣ የዶስተየቭስኪን፣ የጁልየስ ቨርኔን፣ የቮልቴርንና፣ የኤሚል ዞላን መፅሀፍት ያነበቡት እዛው ኦክስፎርድ ነው። ክረምቱን አዉሮፓን ለመንሸራሸር ተጠቅመውበታል። ሌይዥን፣ ፓሪስን ማድሪድን፣ ሚላንን፣ ሮተርዳምን ኣይተዋል፡፡

ከተማዋ፣ ኤልሳቤጥ፣ ዩኒቨርሲቲው ተመችቶታል። ሁለተኛ ዲግሪውን ሊይዝ ወራት ቀርተውታል። ሶስተኛ ዲግሪውን በዩኒቨርሲቲያቸው እንዲቀጥል የለፉለት ቢበዙም አላደረገውም። እንደተመረቀ በለንደን ከተማ አንድ ዩኒቨርሲቲ  በማስተማር ስራ ተቀጠረ። አብራው መኖር የምትመኘው ኤልሳቤጥ ለመጨረስ ድፍን አንድ አመት ይቀራታል፡፡ ኢንግሊዝ ሀገር መስራት አይሻም። እጮኛው ት/ቷን ጨርሳ ወደ እናት ሀገሩ ይዟት ለመሄድና እዚያ ለመኖር ተስማምተዋል። እስከዛው ግን እየሰራ ይጠብቃታል። ኤልሳቤጥ ዋቅጅራን ከቤተሰብዋ ጋር ለማስተዋወቅ ያሰበችው ከአመት በኋላ ነው፡፡

ጊዜው ይሮጣል። በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ለንደን ያሣለፈው አመት ያስደምማል። አፍሪካዊያን ተማሪዎች መመኪያው ናቸው። በሀገሪቱ ዋና ከተማ ለሀገሪቱ ታላላቅ መጽሄትና ጋዜጦች ይፅፋል። በየክርክር አዳራሾች እየተገኘ ይፋለማል። ብሪቲሽ ሙዝየምና ቤኪንግሀም ፓላስ ባየው ነገር ተበሳጭቷል። በተለይ በእንግሊዞች ሙዝየም ውስጥ የተሠረቁ ብራናዎችን ሲያይ ቆሽቱ አርሯል። ተቃጥሎም አልቀረም፣ እንግሊዝ ከመላው አለም የዘረፈቻቸውን ቅርሶች የሚያስመልስ እንቅስቃሴ ለማድረግ ማህበር አቋቁሟል። በግሉ ተማሪዎቹን ሲያገኝ እንግሊዝ ከአፍሪካ የዘረፈችውን እስከታስመልስ ለምንቀበላቸው አገልግሎቶች ክፍያ መክፈል የለብንም ይላቸዋል። በካፌቴሪያ ምግብ ይመገብና “ለተመኑበኩት አልከፍልም ምክንያቱም የአፄ ቴዎድሮስን የወርቅ ፅዋ አልመለሳችሁም” ይላል። የካፌዎቹ ኃላፊዎች እንደ አበደ ሠው ብዙ ቦታ ባይከፍልም ድጋሚ ሲገባባቸው አለመታዘዝን መረጡ። ይበጠብጣል፣ እድሉ ሆኖ አልተያዘም እንጂ፤ ቢከሰስ የእጁን ያገኝ ነበር። ታክሲም ሆነ መጠጥ ቤት ሲጠቀም አይከፍልም፤ ምክንያቱ ደግሞ “የሀገሬን ብራና ሠርቃችኋል” ነው። ከተማዋ “እብዱ ፕሮፌሰር” አለችው። ዝናውን የሠሙት የሎንደን ከንቲባ የነገሩ አካሄድ ስላላማራቸው ኮቨንት ጋርደን ቀጠሩት። የተቃጠሩበት ሬስቶራንት በዓመት 500 ፓውንድ የሚከፈልበት፣ ከፍተኛ ሀብትና ማዕረግ ያላቸው ሠዎች ብቻ አባል የሚሆኑበት ሲሆን፤ አዲስ አባል የሚቀላቀለው ጥያቄ ቀርቦ አባላቱ በምስጢር ድምፅ ሲሰጡ ብቻ ነው። አባላቱ አልፎ አልፎ ከቀናት በፊት ለተያዘ ልዩ ግብዣ እንግዳ ይዘው መምጣት ይችላሉ፡፡

ከህንፃው መግቢያ በር ላይ የቆመው ጠባቂ በክብር ሠላምታ ሠጥቶ፣ ስሙን ጠየቀውና የመኪናዋን በር ከፍቶለት ወደ የሚገርም ሣሎን መራው። ጥቁር ሱፍ የለበሱ ሠው ተነስተው ተቀበሉት፣

”ሠላም!! ሜየር ኒኮላስ” አሉት፤ እጃቸውን ዘርግተው

“ዋቅጅራ” አላቸውና ተቀመጠ። ዙሪያውን ቃኘ። ቤቱ ያስደነግጣል። የሻማ ማብሪያ ቀንዲሎቹ ውድና ቅንጡ በሆኑት የቤቱ ዕቃዎች ላይ አሸብርቀዋል። ሰሃኑ፣ ሹካውና የወይን ማስቀመጫው፤ ተደርድረው ላያቸው አቀማመጣቸው ለሰማይ ጌታ ውዳሴ፣ ለምድሩ ጌታም አሠተናጁ ለተስተናጋጁ የሚቀርብ ከፈጠረኝ ቀጥለህ ምርጡ ጌታ ‘አንተ ነህ’ የምትል ቅኔ ይመስላል።  አስተናጋጁ ከዳክዬ ጉበት የሚሰራ ውድ ምግብ ከሻምፓኝ ጋር አቀረበላቸው። ሳልመንና ጣፋጭ ቂጣዎችም ቀርበው ማዕዱን በሉት። ዋቅጅራ በልቡ “አሁን ይሄ ሊጥ በዚህ መሆን ይገባዋል?” አለ::

ከንቲባው ሻምፓኛቸውን አጋጭተው  ወሬያቸውን ጀመሩ። ከየት እንደመጣ፣ ለምን እንደመጣ፣ ስለ ህይወት ታሪኩ ጠየቁት። መለሰላቸው። አሁንም ሌላ ጥያቄ ደገሙት “አፍሪካዊ ተማሪ ለምን ታነሳላለህ? ሀገራትን በእንግሊዝ ላይ ማሳመፅስ ምን ይጠቅመሀል? ነፃ የት/ት ዕድል ላመቻቸ ሀገርስ ይህ ነው ውለታው? ተማሪዎችን ምን ብለህ እንደምታነሳሳ፣ ካፍቴሪያዎች ውስጥ ምን እንደምትል እናውቃለን” እንዳሉት ጥቂት አሰብ አድርጎ

“ውለታ አልከው አቶ ኒኮላስ? የሃገሬን ወርቅ፣ ብር፣ መፅሀፍት ወርሳችሁ በሙዝየሞቻችሁ እየሸቀላችሁ፣ የሃገሬንና አህጉሬን ወጣት ህልም አጨናግፉችሁ፣ የራሳችሁን ወጣት እየሰራችሁ፤ ውለታ አልከው? ሀገር ወስዳችሁ ሚጢጢዬ መንደር መልሳችሁ። ነፃ የት/ት ዕድል ሠጠን ስትሉ ይሄስ የብሪታንያ ስላቅ እንበለው?” ከንቲባው ጥቂት ሳቅ አሉ

“የማታርፍ ከሆነ ወደ ሀገርህ እንሸኘሀለን። እናውቃችኋለን ኢትዮጵያውያን ውለታ ትክዳላችሁ። ለማናቸውም ይህንን ተማሪ ማነሣሣት ካቆምክ ፕሮፌሰርነት በቅርብ አመት ይሰጥሀል” አሉት

“እድገታችሁ ገደል ይግባ በጉዳዩ እገፋበታለሁ” አለና ጥሎ ወጣ፡፡

በምርቃቷ ቀን የቀድሞ ዩኒቨርሲቲና ከተማው ተገኝቷል፤ ገና ስታየው ሮጣ አቀፈችው፣ ለቤተሰቦቿ “የወደፊት ባሌ ነው አለቻቸው። “አባዬ ተዋወቀው እዚሁ በከፍተኛ ማዕረግ ከሁለት አመት በፊት ተመርቋል” አለችው። አባት በፈገግታ ”ሠላም ላንተ ይሁን” አሉት። እጅ ነስቶ “ለእርሶም” አለ። ሁሉም ቤተሰብና ጓደኞቿ ወደ ሆቴል አመሩ። ዝግጅቱ ላይ ስጦታ ሲሰጥ አመሸ። ዘመዶቿ፣ ወንድሟ፣ እህቷና ጓደኞቿ፤ ስጦታውን ሲሰጡ ይጨበጨባል። ዋቅጅራም በተራው የወርቅ ሀብል አንገቷ ላይ አኖረ። ግን ጭጭ ተባለ። ወዲያው ተረጎመው። ሸልሟት  ሲዞር የቃኘው ፊት ላይ ቅሬታ ነበር። ከነከነው። ኤልሳቤጥ “የምወደው እጮኛዬ ነው፣ ኢትዮጵያዊ ሲሆን University of London አስተማሪ ነው” ብትልም ሞራል የሚሰጥ ጠፋ። ለመጀመሪያ ጊዜ እንግሊዝ ከመጣ ብቸኝነት አንገበገበው። ወደ ወንበሩ ተመልሶ ነገር ያሻምዳል። ይደውራል። ድንገት አባቷ ወደ በረንዳው ጋበዙት። ልጃቸውንና እሱን የተመhከተ፣ ሃገሩን፣ ምን አይነት ቤተሰብ እንዳሣደገው? ጠየቁት። ተናገረ። አባትዬው ወሬያቸው ውስጥ ‘ጥቁር ባትሆን’ የሚለውን ጣልቃ እንዳስገቡ ነበር ስጦታ ሲሰጥ ለምን ደስ እንዳላላቸው በደንብ የተገለጠለት። “ልጆችን እወዳታለሁ እኔ ጥቁር ስለሆንኩ አታገባትም ማለት ግን አይችሉም፣ እንግሊዝ እንዲህ  ያለ ህግም እንዳላትም አላውቅም” ብሎ ሳያስፈቅዳቸው  ወደ ለንደን የምሽት ትኬት ቆርጦ ተጓዘ፡፡

እንግሊዝ የምትባል ሀገር በተለይ የኤልሳቤጥን አባት ሀሳብ ሠምቶ ተቀይሟል። ከቀናት መካከል ባንዱ አፍሪካዊያን ተማሪዎችን በሚሠራበት ተቋም ከት/ት ሠዓት ውጪ ሠበሠበ።

“እሁድ እንግሊዝ የዘረፈቻቸውን ቅርሶች (መንፈሳዊና ቁሣዊ) እንድትመለስ የሚጠይቅ ሠላማዊ ሠልፍ እጠይቃለን። ቦታው ሀይድ ፓርክ(ቦታው hንደን ውስጥ ይገኛል)። ከአካላዊ ንክኪ ውጪ የትኛውም አይነት ክርክር፣ ጭቅጭቅ፣ ስድድብና ጩኸት የሚቻል ሲሆን፤ ሁላችንም ሁለት ሠዐት ሲደርስ በሩ ላይ እንገናኝ። ወደታዋቂ ጋዜጦችና መፅሄቶች ዋና መ/ቤት እየሄዳችሁ እንዲመጡና እንዲዘግቡ ንገሯቸው። ፖስተሮችንም ያዙ!! እኔም ዛሬ ወደ ኪንግ ፓላስ ለዘጋርድያን ጋዜጣ ሀሳቤን ለማስረዳት እሄዳለሁ” አለና ሁሉንም ተማሪዎች ወደሚመለከታቸው መ/ቤቶች ሄደው ደብዳቤ እንዲያደርሱ አደረጋቸው።

እሁድ ሃይድ ፓርክ

ግቢው በሠው ተሞልቷል። መድረኩን ተማሪዎቹ አሣምረውታል። “እንግሊዝ የዘረፈችውን በአስቸኳይ ትመለስ። ቅኝ የገዛችውን ሀገር የበደል ካሣ ተክፈል። ለበደለቻቸው ሀገራት ይቅርታ ትጠይቅ!!” የሚሉ ፖስተሮች ተይዘዋል። ዘ ጋርድያን፣ ዘ ኢኮኖሚስት፣ ዴይሊ ሜይል፣ ዴይሊ ሚረር፣ ለንደን ታይምስ ወ.ዘ.ተ ተገኝተዋል። ዋቅጅራ ንግግር ለማቅረብ ወደ ተሰራለት መድረክ ወጣ። ተማሪዎቹ አፏጩለት። ያፏጩለት በተለይ የያዘውን ፓስተር አይተው ነው። ንግግሩን ጀመረ። በተመስጦ እንግልጣር ከሀገሩ በኣፄ ቴዎድሮስ ጊዜ የዘረፈችውን እየነገረ በእልህ ‘መመለስ አለበት’ ይላል። እያወራ ድንገት ኤልሳቤጥን አያት ቪቫ ምልክት አሣየችው። ፈገግ አለ። ፓስተሩን በደንብ አነሣው። ተጨበጨበ። ሌላ ድምፅ ተከተለ።

“ጥያቄ መጠየቅ ይቻላል? ከዘ ጋርድያን ነው” አለው ጭንቅላቱን በመነቅነቅ እሺታውን ገለፀላቸው። “የፃፍከውን ታውቀዋለህ?” ጋዜጠኛው ጠየቀ

“አዎ!! ‹‹ለንደንን ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘኋት እኔ ነኝ (I am the first person who discover London) ›› ይላል” አለው። ጋዜጠኛው እየሳቀ “ሠዎች ያሉበትን ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ አገኘሁ ስትል አታፍርም?” ሲለው ዋቅጅራ ተምበለበለ። “ወዳጄ ማግኘት (discover) ማለት ቀድሞ ማየት ሳይሆን ቀድሞ አየሁ ማለት ነው” አለው። ቀጠለናም “ጄምስ ብሩስ ናይልን አገኘሁ ያለውኮ አከባቢው ሠው ስላልነበረበት ሳይሆን ቀድሞ የመናገር ጉዳይ ነው፣ ማርኮ ፖሎ ቻይናን ሲያገኝ እኮ ህዝብ ይኖርበት ነበር፣ ግን በቃ ‹አገኘሁ› ብሎ ተናገረ አለ” ብሎ ንግግሩን ሲጨርስ ሞቅ ያለ ጭቅ ጭቅ ተነሣ። ጋዜጠኛውም፣ ተማሪውም፣ እንግዳውም እስኪሰለቻቸው ቀኑን በውይይት አሳለፉት፡፡

ሰኞ

በጭቅጭቁ ማግስት ሁኔታውን  ዘ ጋርድያን “እብዱ ፕሮፌሰር” ብሎ ሲዘግብ፣ ዘ ኢኮኖሚስት ደግሞ “አፄ ቴዎድሮስ በሎንዶን” የሚል ርዕስ ይዘው ወጡ፡፡ ዋቅጅራ ግን ይህ ሁሉ ሲሆን ወደ ወደ ሀገሩ የምትሄደዋ ጢያራ ውስጥ ነበር፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top