ማዕደ ስንኝ

ግሼ አባይ ግዮን…

የክርስቲያን አምላክ እንሆ ማተብ ክር

ምንም አላጠፋሁ … ልሳሳት አልሞክር …

     እንኳን ጥርኝ አፈር …

           ነውርም ይዠ አልነጎድኩ …

     እኔ ራሴ ብቻ …

           እኔው ራሴ ነኝ ወድጄ የታጎድኩ

እነሱም አልጠሩኝ … እነሱ አልቀጠሩኝ …

ብቻ በውዴታ በሙሃባ አጠሩኝ … ያንጀት አናገሩኝ

አለመዱ ገሩኝ … አልፌም እንዳልሄድ … ድምበር አሻገሩኝ

            ሄድኩበት አለቀ

            ልብ ተጠለቀ …

            ነፍስያ ወለቀ …

     እንደየናፍቆቱ እንደመቃተቱ ይሰፈርለታል …

     ማንስ ቢሆን ማንም … ያው ያመነው እንጂ

            ማን ይደርስለታል …?

አታመካኙብኝ … በላይ እንደገዳይ ጥላዬ አትናኙብኝ

ዋኝታችሁ ላትዘልቁኝ … አታላዝኑብኝ

     አፈር አልነካሁም …

     ምንም አልወሰድኩም …

     ሰጥቼ አልወደድኩም …

     ደሞም ደጅ ልጠና አላጎበደድኩም …

     እኔም አላበድኩም

     እኔስ ምኔ ድኩም …

     ፈስሻለሁ እንጂ … ቀልጫለሁ እንጂ እንደበጋ ቅቤ

     አንድ እንዳልተነፍስ ታፍኜ ታቅቤ …

     ወዴት ነህ የማነህ የሚል በሌለበት …

     ለመቼ ሊውል ነው ሃሞትና ጉልበት

     አዎና … ሄድኩበት

ልደታ ማርያም

ጥር – 1996 ዓ.ም.

ለግሼ አባይ ግዮን

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top