ስነልቦና

የ Covid-19 ወረሽኝ ስነ-ልቦነዊ ምላሾች

እ.አ.አ ከ1918 እስከ 1919 ስለ ተከሰተው የህዳሩ በሽታ (የስፓኒሽ ፍሉ) እ.አ.አ. በ2018 ያየርአድ ቅጣው እና መገርሳ ካባ ባሳተሙት የጥናት ጽሑፍ ላይ የሚከተለውን ብለውናል።

በሽታው በዓለም ደረጃ በሁለት ዓመት ውስጥ ብቻ ከ 20 እስከ 50 ሚልዮን ሰዎችን፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ከ50,000 በላይ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል። በአዲስ አበባ ብቻ እስከ 10,000 ሰዎች ሞተዋል።

ወረሽኙን ለመከላከል እና በበሽታው የተያዙትን ለማዳን በሚል አረቄን እና ነጭ ሽንኩርትን እንደ መድሐኒትነት ተጠቅመውት ነበር የሚለን ደግሞ ፍሬው ጌታቸው ነው፡፡ አቶ ፍሬው ከዓመት በፊት ለንባብ በበቃው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ባህላዊ ሐኪሞቹ ለየት ያለ የሕክምና ዘዴን ይጠቀሙ እንደነበር ያትታል፡፡

ይሄም ከበሽታው ያገገሙ ነገር ግን ከድካሙ (ከድብታው) ያልወጡትን ታካሚዎች የደረቀ የበሬ ቆዳ በድንገት በማስጮህ ከእንቅልፋቸው ያባንኗቸው ነበር፡፡ ድንጋጤው ሰበብ ሆኖ ከድብታቸው ተላቀው ጤነኝነታቸውን ይቀበላሉ ይለናል፡፡

በተጨማሪም በጆሮ ግንዳቸው ጠመንጃ በመተኮስ፣ ጦርነት መጥቷል የሚል የሐሰት ወሬ በማስወራት፣… ሊፈውሷቸው ሞክረዋል፡፡ ህዳር 11 የጠላት ጦር ወሮናል በሚለው የሐሰት ወሬ ምክንያት አዲስ አበባ ከተማ ሌሊቱን በተኩስ ስትናጥ አድራለች፡፡ የቀኑን ወሬ እና የሌቱን ተኩስ የሰማ የወረሽኙ ተጠቂ ዘራፍ ብሎ ተነሳ…

እንዲህ ያለው ታሪክ ውስጥ አንድ ታላቅ ነገር እናገኛለን። ለመሆኑ በወረሽኙ በጠቅላላ የሞቱትን ማን ገደላቸው? የህዳሩ በሽታ ብቻውን ገደላቸው ወይስ ስነ-ልቦናዊ ተፅዕኖ ተዳምሮ ወረሽኙ ገደላቸው? ከበሽታው በቆዳው ጩኸት፣ በወሬው እና በጥይቱ እሩምታ ዳኑ የተባሉትንስ ወረሽኙ እንደምን ማራቸው?

እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ የተለያዩ የእውቀትምንጭ-ዕሳቤዎችን መጠቀም ይቻላል። አንዳዶች የመዳናቸው ምንጭ እምነታቸው እንደሆነ ሲገልፁ፤ ሌሎች ደግሞ ከወረሽኙ ጋር የነበራቸው ተነካኮት-ግንኙነት መቀየሩ ለመዳናቸው ምክንያት እንደሆነ ሊያስቡ ይችላሉ። በተለየ መልኩም የታማሚዎቹን መዳን ያመጣው የተቀሩት (ያልታመሙት) ሰዎች መላ እንደሆነ ይታሰባል፡፡

ሁሉም በራሳቸው ምህዋር ላይ የትክክለኛነታቸውን ማረጋገጫ ያስቀምጣሉ። ታዲያ የስነ-ልቦናው ዓለምስ ስለ ወረሽኝ በሽታዎች እና ስነ-ልቦናዊ የመከላከል አቅም ምን ይላል?

የኮሮና ቫይረስ በቁሳቁሶች ላይ ምን ያህል ይቆያል?

ወረሽኝ የሚያስከትላቸው ስነ-ልቦናዊ ተፅዕኖዎች?

እንደሚታወቀው ማሰቢያ እና ማገናዘቢያ አእምሮአችን በአንጎላችን ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፤ አንጎላችን ደግሞ አንዱ የሰውነት ክፍላችን እንደመሆኑ መጠን ማናቸው በሽታዎች /ወረሽኞች የተለያዩ አካላት ክፍሎችን ሲያጠቁ በተመሳሳይ አዕምሮን ማጥቃታቸው የማይቀር ነው። በቀላሉ ብናሰብው እንኩዋን፤ በሽታው /ወረሽኙ መኖሩን ለማወቅ፣ ተይዣለሁ ወይስ ነጻ ነኝ የሚለውን ለማረጋገጥ አዕምሮአችን ለነገርዬው ንቁ፣ አዋቂ (Stimulus) መሆን አለበት። ወረሽኙ መኖሩን አዕምሮአችን ካወቀ በኋላም በቅድሚያ የሚደርስበት አሉታዊ ተጽዕኖ “በበሽታው ብያዝስ” የሚል ፍርሃት ነው።

“ብያዝ” በሚል ብቻ ሳያበቃ ከተያዝኩ በኋላ በለይቶ ማቆያ ውስጥ እቀመጣለሁ፣ ከቤተሰብ እለያለሁ፣ እገለላለሁ የሚል የፍርሃት ሰልፍ ያስከትላል። ይህንን ፍርሃት ከሚያባብሱት ውስጥም ያልተጣሩ መረጃዎችን መስማት፣ በቂ መረጃ ማጣት፣ መድሃኒቱ ተገኘ-አልተገኘ ሃሳብ፣ የቤተሰብ አባላት በወረሽኙ ተጠቁ-አልተጠቁ እና የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው። በሂደትም ሰዎችን ለጭንቀት እና ድብርት  ይዳርጋሉ። ውድ አንባቢያን እዚህ ላይ አስገራሚው ነገር በለይቶ ማቆያ ውስጥ በበሽታው ተጠርጥረው ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ ሰዎች በሂደት የወረሽኙን ምልክቶች በማሳየት በበሽታው ሳይያዙ የተያዙ ይመስላቸዋል።

በእጅ ሰላም አለመባባል!

ለምሳሌ፦ የወረሽኙ ምልክት የሰውነት ሙቀት መጨመር ከሆነ፤ ግለሰቡ(ዋ) በፍርሃትና ጭንቀት ውስጥ ስትሆን Serotonin የተሰኘው የአዕምሮ ኬሚካል ይቀንሳል፤ የኬሚካሉ መቀነስ የሰውነት ሙቀትን የማመጣጠን ስራን ያስተጉዋጉላል። በጭንቀት ምክንያት ብቻ የሰውነት ሙቀት በመጨምር-ከዋናው በሽታ ጋ ተቀራራቢ ምልክት ግለሰቡ(ዋ) ልታሳዩ ይችላሉ። በተጨማሪ የ-Serotonin ማነስ የድንገተኛ መርበትበት (Panic attack) ህመም ሊስከትል ይችላል።

ፍርሃቱ ላይ ተመስርቶ ሌላኘው ተጽዕኖ የሚሆነው፤ ማኅበራዊ ትስስሮሽን ማላላት እና በቀናት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ማቋረጥ ነው። እርስ በእርስ ያለንን መተማመን የሚሰብር፤ “ያንተ ቤት ሲንኩዋኩዋ ይሰማል የኔ ቤት” የሚለውን ብሂል በሚያስዘነጋ ዓይነት። በተለይም ማህበራዊ ድጋፍ የሚሰጡ እንደ እምነት ተቁዋማት እና በሃገራችን የቡና ጠጡ ስርዓቶች ላይ የሚገኘው ሰው ወረሽኙ እንዳይስፋፋ በሚል ስለሚገደብ የባሰውኑ ማህበራዊ ትስስሮሹ እየላላ ይሄዳል። ይሄ አይነቱ መላላት ውስጥ የወረሽኙ ተጠቂ የተባሉትን ግለሰቦች እንዳንዴም ሃገራት አንዳንዴም የተወሰኑ ቦታዎችን የማግለል ነገር ይከሰታል። በቅርቡም በሎንደን ከተማ ውስጥ ቻይናውያን ጥንዶችን “Covid-19 ወረሽኝን እናንተ ናችሁ ያመጣችሁት” በሚል ጥቃት እንደደረሰባቸው ይታወሳል።

ሌላኛው ተጠቃሽ ስነ-ልቦናዊ ተጽዕኖ የሚከሰትባቸው የጤና ባለሙያዎች ናቸው። ባለሙያዎቹ ረጅም ሰዓት በስራ ላይ ከመቆየታቸው፣ በወረሽኙ የተነሳ ሰዎች ሲሞቱ እና በህመም ሲሰቃዩ በተደጋጋሚ በማየታቸውና በቂ የህክምና ግብአት ካለመኖር የተነሳ የመዳከም፣ የመሰላቸት፣ የድብርት፣ ተስፋ የመቁረጥ፣… ምልክት ሊያሳዩ ይችላሉ፤ ታዲያ ባለሙያዎች በዚህ ከቀጠሉ በህክምና ስራቸው ውጤታማ ካለመሆንም በላይ በቀላሉ ወረሽኙም ወደ እነሱ ይተላለፋል፥ ግለሰብም በህክምና ስርዓቱ ላይ እምነት በማጣት የጤና ተቋማትን መጠቀም ይፈራል፤ በወረሽኙ ቢያዝም እራሱንም ከማጋለጥ ይቆጠባል ይለናል፡፡ የጤና ባለሙያው Brian Honerman። እዚህ ጋ መዘንጋት የሌለብን ግለሰብ ራሱን ሊደብቅበት የሚችልበት ሌላኛው ምክያት መገለልን ካለመፈለግም ይሆናል።

ስነ-ልቦነዊ ምላሾች

ከላይ እንዳልነው ማናቸውም ወረሽኞች ሲከሰቱ የፍሃት፣ የጭንቀት፣ የድብርት፣ ተስፋ-የማጣት፣ የመገለል ወይም የማግለል… አሉታዊ ተጽዕኖዎች ይከሰታሉ። በተመሳሳይ መልኩም በCovid-19 ወረሽኝ ላይም የሚስተዋለው ይሄ ቢሆንም ተጨማሪ ነገሮችም አያጣም።

ከሁሉ በፊት ሲያከናውናቸው ከነበሩ ተግባራት ራሱን እንዲገታ ያድርጉዋል። በፊት እቅፍ ድግፍ አድርገን፤ አገላብጠን እንስማቸው የነበረውን አሁን ላይ ለመጨበጥ እንኳን እንድንፈራ ሆነናል። ለጉንፋንም ሆነ ለተለያዩ የመተንፈሻ አካት ህመም ማሳል ከባድ ሆኗል። ካሳሉም Covid-19 እንዳልያዛቸው እና ይልቁኑም የቲቪ ህመም እንደሆነ መንገር ከመገለል እንደሚያድን ቀልድ መሰል ፌዝ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ታይቷል። ይሄም ወረሽኙን እጅግ አስፈሪ ገፅታ ያላብሰዋል።

ሆኖም ስነ-ልቦና ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ፤ ወረሽኙ በተቀሰቀሰበት የመጀመሪያዎቹ ሰሞን ወረሽኙን በከፍተኛ ሁኔታ አጋኖ ማቅረብ እና በዙ ሲቆይ ደግሞ እንደ ቀላልና አሌ የማይባል ነገር መውሰድ ሰዋዊ ባህርይ ነው። HIV በኢትዮጵያ በገባበት ወቅት እና አሁን ላይ ያለውን የበሽታው ግንዛቤ ማየት ለዚህ ምሳሌ ይሆናል። እንዲህ ያሉት በወረሽኙ መከሰት የመጀመሪያ ጊዜያት የሚስተዋሉ ስነ-ልቦናዊ ከፍተኛ ሽብሮች በሰዎች ላይ ድንገተኛ መርበትበት፣ ከወረሽኙ ለማምለጥ ከመፈለግ የሚመጣ የገነነ ራስ ወዳድነት እና የተለያዩ የህክምና እና ተጉዋዳኝ ግብአቶችን ለማግኘት የሚደረግ አላስፈላጊ ግብግብ ያስከትላሉ።

ነገር ግን የስነ-ልቦና ባለሙያዋ Terri Apter /Ph.D./ እንደምትለው፦ “አሁን ላይ ያለው ዘመናዊ ሰው የሚተጋገዝ (የሚደጋገፍ) እና ርህራሄ የሚሰማው ነው” ሆኖም ያለ ቡድን ድጋፍ፣ የምግብ አቅርቦት፣ የመጠለያ እና የደህንነት መጠበቅ ወደ እዚህ በጎ ባህርይ የሰው ልጅ አይመጣም ነበር ይላሉ ሳይኮሎጂስቶች። በአሁኑ ወቅትም ከ Covid-19 ጋር በተያያዘ ሃገራት (መንግስታት)፣ ተቁዋማት፣ እና ግለሰቦች በትብብር እና በርህራሄ መንፈስ እየሰሩ እንደሆነ እንታዘባለን። በተቃራኒውም አንድንድ ወገኖች “ቫይረሱ ስራውን ይስራ፤ ሲጨርስ ሁሉ ይሻላል” በሚል መንፈስ መንግስታት እና የተለያዩ ተቋማት እየተንቀሳቀሱ ነው በሚል ይወቀሳሉ።

በወቀሳው መሐል የሚፈጠረው ስነ-ልቦናዊ ጉዳት ከፍ ሲል፥ ወረሽኙን መቆጣጠር የሚችል አካል አለ ብሎ አመኔታ መጣል መቸገር ሲያስከትል፤ ዝቅ ሲልም ሰዉ ራሱን ለመጠበቅ በሚል በተቋማቱ የሚሰጡትን አዲሶቹን የዕለት ተዕለት ተግባራት ላይ በመጠመድ እና መመሪያዎችን በአግባቡ መከተል-አለመከተሉን ደጋግሞ በማሰብ ለአላስፈላጊ መረበሾች መዳረግ እና ከላይ እንዳልነው በተደጋጋሚ ስለወረሽኙ አስፈሪነት እና ምልክት ከመስማት እና ከማውራት የተነሳ አንዳንዶች ወረሽኙ ሳይኖርባቸው የCovid-19 ምልክቶችን በሰውነታቸው ላይ ያዩ ይመስላቸዋል። ተቀራራቢ የሆኑ እንደ ጉንፋን ያሉ ህመሞች ምልክት ሲያዩም በበለጠ ይረበሻሉ።

እጃችንን መቼ እና እንዴት መታጠብ እንዳለብን የሚያሳይ መረጃ

የበሬው ቆዳ…

ስለ ስነልቦናዊው ተጽዕኖ ይህን ያህል ካልን ዘንድ የCovid-19 ለመከላከል ከአካላዊ (ስነ-ህይወታዊ) ህክምና ወይም ድጋፍ በተጓዳኝ ስነ-ልቦናዊ ድጋፎችን በምን ዓይነት መልክ መስጠት እንደሚቻል በማየት ጽሑፌን አጠናቅቃለሁ።

በጥቅሉ ሁለት ዐይነት ስነ-ልቦናዊ ድጋፍ ቢሰጥ የተሻለ እንደሆነ ይሰማኛል። አንደኛው እና የመጀመሪያው የግለሰቦችን ፍርሃት ከሚጨምሩ ተግባራት ራስን መከልከል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ተጨማሪ እንደ በሬው ቆዳ እና የጥይት ተኩሱ ያሉ እንደ ያኔው እንተኩስ አለመሆኑን ልብ ይሏል፡፡ የሰውን አዕምሮአዊ ጤና ማስጠበቅ የሚችሉ እና ራስን ለማረጋጋት የሚያስችሉ ተግባራትን እንዲፈጽም ማስቻል ነው። በሌላ አነጋገር አሉታዊ ነገሮችን ማስወገድ እና አውንታዊ ነገሮችን መጨመር እንደማለት ነው።

…ራስን መከልከል

  1. ሰዎችን ፍርሃት ውስጥ የሚከቱ መረጃዎችን አለማሰራጨት እና የሚመለከታችው አካላትም በተለያዩ የግንኙነት መስመሮች የተረጋገጠ መረጃዎችን እንዲሰጡ ማድረግ።
  2. ካላስፈላጊ ግዢዎች እና ወጪዎች ራስን መጠበቅ እና ግዢዎችንም በባለሙያዎች ምክር ላይ ብቻ የተመሠረቱ ማድረግ።
  3. ከዋናው ጤና ተቋም ውጪ ይህ አድርጉ እና አታድርጉ፤ ይህ ሆነ እና ይህ አልሆነም ከሚሉ አካላት መራቅ ወይም መረጃዎችን አለመቀበል እና አለማስተላለፍ።
  4. ስለ ወረሽኙ አብዝቶ አለማውራት እና ከመረጃ ልውውጥ በዘለለ ሰፊ የመወያያ ጊዜ አለመስጠት (ለምርምር ስራ እና ለወረሽኝ ቁጥጥር ተግባር ካሆነ በስተቀር)።

…ሳይታከሙ መታከም

  1. እምነት ያለው በእምነቱ ላይ በመመስረት ውስጣዊ ሰላሙን እና እርጋታውን በየዕለቱ በጸሎት እና ሌሎች ሐይማኖታዊ ግላዊ ተግባራት ማስፈን።
  2. እርስ በእርስ በጎ (ገንቢ) የሆኑ ነገሮችን መነጋገር።
  3. በስነ-ልቦናው ዓለም Placebo effect የተሰኘ እሳቤ አለ። አንዳንድ ሰው ሆስፒታል ሄዶ ተመርምሮ ነጻ ሲሆን፤ ነገር ግን አሁንም ህመም አለኝ ሲል የውሸት መርፌ በመውጋት ሃኪሞች ወደ ቤት ይሸኙታል። ግለሰቡም መድሐኒት ይመስለው እና ከተወጋው በሁዋላ መለስ አለልኝ ይላል። ይሄ ነው እንግዲህ “ሳይታከሙ መታከም”።

አሁን ያለብን አካላዊ (ስነ-ህይወታዊ) ትንቅንቅ ብቻ አይደለም ስነ-ልቦናዊም እንጂ። “ቀናችን ከደረሰ መሞታችን አይቀርም” ብለው ከሚያዘናጉንም ሆነ አንዳች የማይገፋ ወረሽኝ አድርገው ፍርሃት ከሚዘሩብን ራሳችንን መጠበቅ እና ደረቁን የበሬ ቆዳ ሰምተን፣ የቀኑ “ወራሪ ጠላት መጥቶብሃል” ወሬ እና የሌቱን የጥይት ተኩስ ሰምተን በጥሩ ጤንነት ልንነሳ ግድ ይለናል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top