የታዛ ድምፆች

ከጣሊያን የተጻፈ ደብዳቤ

ፍራንሲስካ ሜላንደሪ ትባላለች። እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ1964 ዓ.ም. ሮም ከተማ ተወለደች። የልቦለድ ደራሲ፣ የፊልም ጸሐፊ እና የዶክመንተሪ አዘጋጅ ናት። pzon PR apallu carige prize የተሰኘውን የጣሊያን የስነ-ጽሑፍ ሽልማት አሸንፋለች። እ.አ.አ የተለያዩ የሥነ-ጽሑፍ ሽልማቶችን በ2010 እና በ2011 ተሸልማለች። ፍራንሲስካ አደነናቆት እና ክብር የተቸራት ጸሐፊ ናት።

 አሁን ዓለማችንን እያስጨነቀ በሚገኘው የኮቢድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለሳምንታት ያህል ከቤቷ አልወጣችም። ደጇን ቆልፋ በቆየችባቸው የጥሞና ቀናት ለአውሮፓዊያን ወንድሞቿ እና እህቶቿ ደብዳቤ ጽፋለች።

ደብዳቤዋን “ይኸንን ደብዳቤ የምጽፈው በቅርቡ ከምትደርሱበት የወደፊቱ የናንተ ዕጣ ፈንታ ከጣሊያን ሮም ከተማ ነው” ብላ ትጀምራለች።

“ይኸንን ደብዳቤ የምጽፈው በቅርቡ ከምትደርሱበት የወደፊቱ የናንተ ዕጣ ፈንታ ከጣሊያን ሮም ከተማ ነው። አሁን እኛ ጣልያናዊያን ያለንበትን ሁኔታ እናንተም በቀናት ዕድሜ ትደርሱበታላችሁ። የወረርሽኑ ሰንጠረዥ ዕንደሚያሳየን ከሆነ ርቀቱ ጎን ለጎን እየተወዛወዙ እንደመደነስ ያለ ነው።

ቢሆንም ከጊዜ ልኬት አንጻር ጥቂት እርምጃ ቀድመናችኋል። ልክ የቻይናዋ ህዋን ጥቂት ሳምንታት ከኛ እንደቀደመችው ማለት ነው። እኛ ህዋን ስትታመስ ነገሬ ብለን ትኩረት አልሰጠንም፤ እናንተም እንደኛ ናችሁ። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለክፉ ለማይሰጥ ደዌ ይህ ሁሉ ሸብረብ ስለምንድነው? በሚሉ እና የነገሩ ክብደት በገባቸው መካከል የተደረገውን ክርክር ዐይነት እናንተ ላይ እየታዘብን ነው።  

ከወደፊት መዳረሻችሁ ላይ ቆመን እንታዘባለን። ቤታችሁን ዘግታችሁ እንድትቀመጡ ሲነገራችሁ ገሚሶቻችሁ የኦርዌልን የተቀራችሁት የሆብሰንን ጥቅስ ታነበንባላችሁ። የማረጋግጥላችሁ ነገር ዛሬ የተጠየፋችሁትን፣ ያልተቀበላችሁትን እና የተመጻደቃችሁበትን ድርጊት ነገ በሁኔታዎች አስገዳጅነት በጥድፊያ ታከናውኑታላችሁ።   

ልክ እቤት እንደተከተታችሁ መጀመርያ ትበላላችሁ። ከምትሰሯቸው የመጨረሻ ጥቂት ነገሮች ውስጥ አንዱ ስለሆነ ብቻ።

ጊዜያችሁን ጠቃሚ በሆነ መንገድ ለማሳለፍ ቱቶሪያል የምታገኙበት በብዙ ደርዘን የሚቆጠር የማኅበራዊ ሚድያ ቡድኖችን ትቀላቀላላችሁ። ከትንሽ ቀናት በኋላ ደግሞ እርግፍ አድርጋችሁ ትተዉታላችሁ። ከመጽሐፍት መደርደሪያችሁ ላይ ትሄዱና ትንቢት ነጋሪ መጽሐፍትን ትሰበስባላችሁ። ይሁን እንጂ አንዱንም ለማንበብ ጉጉት አያድርባችሁም። እንደገና ትበላላችሁ፣ ጥሩ እንቅልፍ የላችሁም፣ ራሳችሁን ምን እየሆነ ነው ብላችሁ ትጠይቃላችሁ፡፡ ማቋረጫ የሌለው የማኅበራዊ ሚድያ ግንኙነት ታደርጋላችሁ። በሜሴንጀር፣ በዋትስአፕ፣ በስካይፒ ወዘተ…

ልጆቻችሁ ይናፍቋችኋል። ለመሆኑ ድጋሚ እንገናኝ ይሆን የሚለውን ስታስቡ ደረታችሁ ላይ ኃይለኛ ቡጢ ያረፈባችሁ ያህል ህመም ይሰማችኋል።

የቀድሞ ጥላቻ እና ውድቀቶች ትርጉም አይኖራቸውም። ድጋሚ ላታይዋቸው በመሃላ የተለችኋቸው ሰዎቸ ጋር ትደውላላችሁ። እንዴት እያደረጋችሁ ነው? እንዴት ነሽ? እንዴት ነህ? ትባባላላችሁ። ብዙ ሴቶች ቤታቸው ውስጥ ይደበደባሉ።

‹‹መጠለያ የሌላቸው ሰዎች ምን እየሆኑ ይሆን?›› ብላችሁ ራሳችሁን ትጠይቃላችሁ። እነዚህን የሚመላለሱ ሃሳቦችን ታመነዥጉና ትበላላችሁ። ክብደት ትጨምራላችሁ፡፡ ኦንላይን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ስልጠና ትፈልጋላችሁ። ትስቃላችሁ፣ ብዙ ትስቃላችሁ። ከዚህ በፊት ሞክራችሁ የማታውቋቸውን ቀልዶች ትቀልዳላችሁ። በአሳሳቢ ጉዳዮች ላይ፣ በሞት ላይ፣… ትቀልዳላችሁ። ከጓደኞቻችሁ እና ከፍቅረኞቻችሁ ጋር የሱፐርማርኬት ወረፋ ላይ ትቀጣጠራላችሁ። ዐይን ለዐይን ለመተያየት ያህል (የማኅበራዊ መራራቅ ሕግ እና መርህ እንደተጠበቀ ሆኖ)።

የማትፈልጓቸውን ነገሮች ትቆጥራላችሁ። በዙሪያችሁ ያሉ ሰዎች ማንነት ይገለጽላችኋል። እያንዳንዱን ታረጋግጣላችሁ። በገሚሱ ትገረማላችሁ። የሚድያ አድማቂ ምሁራን አሁን ዐይታዩም። የአዋቂዎቹ ምክር እና አስተያየት ትርጉም የለሽ ይሆናል። አንዳንዶቹ ምክንያታዊ ይሆናሉ። አድማጭ ግን አያገኙም። የበዛ ግምት የማይሰጣቸው ግለሰቦች ለጋሽ፣ አስታማሚ፣ አርቆ አሳቢ፣.. ሆነው ታገኙአቸዋላችሁ።

ይህ አጋጣሚ በዓለም አቀፋዊ ተሃድሶ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ልናየው ይገባል የሚሉት ነገሮችን ለማሰብ ዕድል ይከፈትላችኋል። በአንፃሩም ያናዷችኋል። እሺ ዓለም የተሻለ እየተነፈሰች ነው። አዎ የካርቦን ልቀቱ በግማሽ ይቀንሳል፤ ግን ደግሞ የሚቀጥለውን ወር የቤት ኪራዬን እንዴት እከፍላለሁ?

በተጨማሪም የአዲስ ዓለም ትንሳኤ ወይንም ሰቆቃ ይኑር አይኑር ለመመስከር እንደምትችሉ እርግጠኛ አይደላችሁም።

በመስኮት ወይም ከአትክልት ሥፍራ ሙዚቃ ትጫወታላችሁ። በየኮሪደራችሁ ሆናችሁ ኦፔራ ስንዘፍን እነዚህ ጣሊያኖች ምን ነካቸው ትላላችሁ። እኛ ግን ልክ እንደእኛ ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ እርስ በርስ እየተቀባበላችሁ በቅርብ ቀን እንደምትዘምሩ እናውቃለን። እናንተ ከመስኮቶቻችሁ ውስጥ ስትጮኹ እኛ ዕናያለን። ጭንቅላታችንን እናወዛውዛለን።

ልክ እንደ ቻይናዎቹ፤ የህዋን ነዋሪዎች የካቲት ወር ላይ በየመስኮታቸው ብቅ ብቅ እያሉ ዘመሩ። አሁን ደግሞ እኛን ዕያዩ ጭንቅላታቸውን ያወዛውዛሉ። ልክ እንደዚያ ብዙዎቻችሁ እንቅልፍ ከመተኛታችሁ በፊት ይህ የእንቅስቃሴ እቀባ እንደተነሳ የመጀመርያው ቀን ስራዬ የፍቺ ጥያቄ ማቅረብ ነው ብላችሁ ትዝታላችሁ።

ብዙ ልጆች ይረገዛሉ። ልጆቻችሁ ኦንላይን ትምህርታቸውን ይከታተላሉ። አስቸጋሪ እና አናዳጅ ይሆናሉ። ደስታ ይሰጧችኋል።

አሮጊቶች እና ሽማግሌዎች አይታዘዙም። ልክ እንደ ረባሽ ጎረምሳ ያስቸግራሉ። እውጭ እንዳይወጡ ለመከላከል ከፍተኛ ትግል ታካሂዳላችሁ።

በሆስፒታል ውስጥ ታመው በብቸኝነት በመሞት ሂደት ስላሉት ማሰብ አትፈልጉም። ሁሉም የህክምና ሙያተኞች የሚራመዱበትን መንገድ በሮዝ አበባ ማድመቅ፣ ማሸብረቅ ያሰኛችኋል።

ማኅበረሰቡ በጋራ ጥረት የተሳሰረ እንደሆነ ይነገራችኋል። ሁላችሁም በአንድ ጀልባ የምንቀዝፍ መሆኑን፤ እውነትም ይሆናል። በዚህ ተመኩሮ ራስን በአንድ ትልቅ ማኅበረሰብ ውስጥ ያለ ግለሰብ አድርጎ ማሰብ ይቀራል። አይመለስም! እስከመጨረሻው አይመለስም!!

ቢሆንም መደብ የሚባለው ነገር የመለያ መንገድ ይሆናል። በአንድ ቆንጆ መናፈሻ ባለቤት ቤት ውስጥ በብቸኝነት ከመዘጋት ወይም በጣም በህዝብ በተጣበበ የቤት ፕሮጀክት ውስጥ መኖር አንድ አይሆንም። ከቤት ውስጥ ሆኖ እየሰሩ መቀጠል አይቻልም ወይም ከነጭራሹ ሥራ አይኖርም። ወረርሽኙን ለመከላከል የምንቀዝፍበት የጋራ ጀልባ ይለያያል። ህይወት ለሁሉም እኩል አትሆንም። ሆናም አታውቅም። አንድ ነጥብ ላይ ስትደርሱ በጣም ከባድ መሆኑን ትገነዘባላችሁ። ትፈራላችሁ። ፍርሃታችሁን ከምትወዷቸው ጋር ትጋራላችሁ። ወይም ደግሞ ለምን አስጨንቃቸዋለሁ ብላችሁ ዝም ትላላችሁ። እንደገና ትበላላችሁ።

ጣልያን ውስጥ ያለን እኛ የወደፊት መዳረሻችሁን በዚህ ያህል ዝርዝር እናውቃለን። ይህ ቀለል ብሎ የተነገረ ትንበያ ነው። መከራ የመከረን ቀለል ያለ ንግርት ነጋሪዎች ነን።

ዕይታችንን የሩቁ ምንነት ላይ ካደረግነው ስለናንተም ስለኛም ልንላችሁ የምንችለው ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ የምንኖርባት ዓለም እንደ አሁኑ እንደማትሆን ነው።”

ዘለግ ያለው የደራሲዋ ደብዳቤ የተጻፈው ከማርች 25፣ 2020 በፊት ነው፡፡ ይህንን ቀን መነሻ አድርገን ስናሰላ አውሮፓውያን ጣሊያን ላይ ለመድረስ የወሰደባቸው 11 ቀናት ብቻ ነው፡፡ በዚያ ወቅት ስፔን ውስጥ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 42,058 ነበር። በአሥር ቀናቶች ውስጥ ብቻ ከሦስት እጥፍ ተዛምቶ 131,646 ላይ ደርሷል። ይህ አሃዝ ጣሊያንን በልጣ ከዓለም በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ አድርጓታል።

ደብዳቤው በተጻፈበት ወቅት ፈረንሳይ የነበሯት የተጠቂዎች ብዛት 22,302 ነበር። አሁን ይህ ቁጥር በአራት እጥፍ አድጓል።

ታላቋ ብርታኒያ ማርች 25፣ 2020 ላይ ከአሥር ሺህ ያነሰ የተጠቂ አሃዝ ነበራት። ወቅታዊ ቁጥራቸው ከ40ሺህ በላይ ነው፡፡ በተጠቀሰው 11 ቀን ያሳየው እድገት አምስት እጥፍ ነው፡፡ ብሪታንያ ተራ ዜጎቿን ብቻ ሳይሆን ጠቅላይ ሚንስትሯንም መታደግ አልተቻላትም፡፡    

የታላቋ አሜሪካ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የቡጢ በሽታ ነው ብለው በተሳለቁበት ጊዜ ወረርሽኙ የደረሰባቸው አሜሪካውያን ከስልሳ ሺህ አልበለጡም። አሁን በታማሚ ብዛት ዓለምን ይመራሉ፡፡

እንቅልፍ የለሽ ከተማ የሚል ቅጽል ያላት፣ የአሜሪካ ምልክት የሆነችው ኒውዮርክ አንቀላፍታለች፡፡ በቀንም ሆነ በሌሊት፣ በፀሐይም ሆነ በበረዶ፣… በሰው ጎርፍ የሚጨናነቀው ታይም ስኩዌር ጎዳና አሁን ጸጥታ ውጦታል፡፡ ሰማይ ጠቀስ የሕንጻ ጫካዋ ኒውዮርክ ሕይወት አልባ ሆናለች፡፡  

ከዓመት በላይ ወረፋ ተይዞ፣ ቅድሚያ ትኬት ተቆርጦ፣… የሚገባባቸው በዓለም ተወዳዳሪ የሌላቸው የብሮድዌይ ቲያትሮች በሰው እጦት እያዛጉ ነው፡፡  

የኛስ?

የተጠቂዎቻችን ቁጥር ከእለት እለት እያሻቀበብን የምንገኘው፣ ማኅበራዊ ርቀትን ለመጠበቅ በሚያስቸግር የአኗኗር ዘይቤ ላይ የምንኖረው፣ የሐኪሞቻችን እና የጤና ተቋሞቻችን ቁጥር ከሕዝብ ቁጥራችን ጋር የማይመጣጠነው፣… እኛ ምን ላይ ነን? እኛ ኢትዮጵያዊያን ምን እያልን ነው?

የጆርጅ ኦሮዌልን ጥቅስ እየጠቀስን ነው? ጥቁሮችን አይነካም ቢነካም አይገድልም እያልን ነው? የበርካታ ወጣቶች አህጉር የሆነችው አፍሪካ ቫይረሱን ታሸንፈዋለች የሚል ባዶ ጉራ ላይ ነን? ሙቀት አይስማማውም፡፡ ፌጦ ድራሹን ያጠፋዋል፡፡ ነጭ ሽኩርት አይወድም፡፡ ዝንጅብል፣ ጤናዳም፣ ቁንዶ በርበሬ ወዘተ… እያልን ነው?  

ከኦርዌል ተረት ይልቅ ‹‹ማስተማሪያ አያድርግህ፤ መማሪያ ግን አይንሳህ›› የሚለው ሐገር በቀል ተረት ይበልጥ የሚያዋጣ ይመስላል፡፡ ቻይናውይን- በቁርጠኝነት፣ በመተባበር፣ በዲሲፕሊን፣ ሳይንሳዊ ምክሮችን ተግባራዊ በማድረግ፣… ቫይረሱን በቁጥጥራቸው ስር አውለዋል፡፡ እኛም ከነገ ጸጸት እና ኪሳራ ለመዳን መከተል የሚገባን ብቸኛው መንገድ ይህ ነው፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top