ታሪክ እና ባሕል

ከእንስሳት ወደ ሰው የተዛመቱ ተህዋሳት

ዓለም አንድ ቋንቋ እየተናገረች ነው፡፡ ድሃ ሀብታም፣ ሶሻሊስት ኮሚኒስት፣ ሰሃራ ሳይቤሪያ ሳይል ስለ አንድ ነገር ብቻ እያሰበ፣ እየተጨነቀ፣ የመፍትሔ ጫፍ እያሰሰ ነው፡፡ እጃችሁን ታጠቡ፣ ርቀታችሁን ጠብቁ፣ ከቤት አትውጡ፣ ያልበሰለ አትመገቡ፣ በሁሉም ቋንቋዎች በሁሉም የመገናኛ መሳሪያዎች የሚነገር ሆኗል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ የሰዎችን ምድራዊ ልዩነት ሁሉ አጥፍቶ በሰው ቋንቋ አነጋግሯል፡፡

የኢኮኖሚ ውድድር፣ የቴክኖሎጂ ፉክክር፣ የእኔ እበልጥ አንተ ታንስ እልህ እና ሙግት የሐገራት አጀንዳ መሆን እያቆሙ ነው፡፡ የቫይረሱ ስርጭት የተስፋፋባቸው የሞት ዜናቸውን ለመቀነስ፣ ጥቂት የታማሚ ቁጥር ያላቸው ስርጭቱን ለመግታት በመስራት ላይ ናቸው፡፡

ሳኒታይዘር፣ አፍ መሸፈኛ ጭምብል፣ ጓንት፣ የንፋስ መስጫ ቬንትሌተር፣ የንጽሕና መጠበቂያ መሳሪያዎች፣… ከቅንጦት ወደ መሰረታዊ እቃነት ተሸጋግረዋል፡፡

ደረጃው ይለያይ እንጂ የሰው ልጆችን በአንድ ቋንቋ ያነጋገሩ በርካታ ደዌዎች በታሪክ ጥቁር መዝገብ ላይ ሰፍረው ይገኛሉ፡፡ አስገራሚው ነገር የአብዛኛዎቹ መነሻ እንስሳት ናቸው፡፡ በምድር ከሚመላለሱ እንስሳት የተጋቡበት ተህዋሶች ባህሪያቸውን ቀይረው፣ አደገኛነታቸውን ጨምረው፣ ተዛማጅነታቸውን አባብሰው የጭንቅ ባህር ውስጥ ዘፍቀውታል፡፡ መፍትሄአቸው እስከሚገኝ ድረስ ክቡሩን የሰው ልጅን ሕይወት ያለ ርህራሄ ቀጥፈዋል፡፡

ዓለምን ካጠቁ በሽታዎች ዝርዝር ውስጥ የሚገኙ ከ100 በላይ ህመሞች መነሻቸው እንስሳት ናቸው፡፡ በቀላሉ ከእንስሳት ወደ ሰው፣ ከሰው ወደ ሰው የሚዛመቱት እነዚህ ተህዋስ ወለድ በሽታዎች Zoonotic Disease የሚል መጠሪያ አላቸው፡፡ ከእንስሳት፣ ከአራዊት እና ከአእዋፍት ጋር በሚኖር ቀጥተኛ ንክኪ ተጋብተው የሰው ልጅን እውቀት፣ እና እምነት ፈትነዋል፡፡ ጭንቅ እና መከራውን አብዝተዋል፡፡

በዓለም ላይ ከተከሰቱት 10 ታላላቅ ወረርሽኞች ውስጥ በዘግነናኝነቱ ቀዳሚ የሆነው ጥቁር ሞት (ብላክ ዴዝ) በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ከ1346-1353 የተነሳው ጥቁር ሞት ከ75-200 ሚልዮን የሰው ልጆችን ቀጥፏል፡፡ አስያ ላይ መነሻውን አድርጎ በመርከበኞች አማካኝነት ወደ ሌሎች አህጉሮች የተዛመተው ህመም መነሻው አይጦች ናቸው፡፡ አይጥን ከሚያጠቁ ተባዮች ተነስቶ ዓለምን ጥቁር አልብሶ አልፏል “ጥቁር ቀን”

ሲኤንኤን መጋቢት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰራው ዘገባ ለኮሮና ቫይረስ ተጠያቂዎቹ የለሊት ወፎች ሳይሆኑ ሰዎች ናቸው ሲል ተደምጧል፡፡ ወረርሽኙ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከስቶበታል ተብሎ የሚታመነው ህዋን ገበያ ነው፡፡ የእንስሳት፣ የአእዋፍ፣ የአሳ ምርቶች በብዛት በሚቀርቡበት ግዙፍ ገበያ ከሌሊት ወፎች ወደ ሰው ልጆች እንደተላለፈ ምሁራን ገምተዋል፡፡ ነገሩ አስግቶናል ያሉ ምሁራንም የምክር ቃላት ሰንዝረዋል፡፡ “እባካችሁ ቻይናውያን የሚንቀሳቀሰውን ሁሉ አትብሉ”

“መርስ” የተባለው ኮሮና መሰል ህመም የተከሰተው በ2015 ነው፡፡ አሁን ባለበት ደረጃ የጉዳት መጠኑ ቀንሷል፡፡ የሚፈውስ መድሃኒት እና ክትባት ባይኖረውም የስርጭት ስፋቱ አነስተኛ ነው፡፡ ይህ ከ850 በላይ ኤሲያውያንን የገደለ ሕመም ወደ ሰዎች የተጋባው ከሌሊት ወፍ እና ከአውስትራሊያ ግመል መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

ከ17 ዓመታት በፊት የተከሰተው የ”ሳርስ” በሽታ ሌለው ከእንስሳት ወደ ሰው በተጋባ ተህዋስ ሰበብ ዓለምን ያመሰ ህመም ነው፡፡ የቤት ውስጥ እንስሳት ከሆኑት ከድመት እና ከውሻ የተነሳው ሳርስ ብዙም ውድመት ሳያስከትል በቁጥጥር ስር መዋል ችሏል፡፡

መጋቢ ሃዲስ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ “መጽሐፍ ቅዱስ እና የሕክምና ሳይንስ” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ ካልታረምን አደጋ ይከሰታል ሲሉ ጽፈዋል፡፡ የሰው ልጆች ከእንስሳት ጋር ያላቸው አግባብነት የሌለው ግንኙነት ካልታረመ፣ ሰዎች ከማይበሉ እንስሳት እና አእዋፍት ጋር ቀረቤታቸውን ካላራቁ ወረርሽኞች በዓለም ላይ ይከሰታሉ ያሉት ዶ/ር ሮዳስ መፍትሔው የምንበላውን እና የማንበላውን፣ የምንቀርበውን እና የምንርቀውን ጠንቅቀን ማወቅ ነው ብለዋል፡፡

ከ20 እስከ 50 ሚልዮን ሰዎችን የገደለው ኢንፍሉዌንዛ በመላው ዓለም የተስፋፋው በ1918 ዓ.ም. ነው፡፡ አስከ 25 ሺ የሚገመቱ በርካታ ሰዎችን በክስተቱ የመጀመሪያ ሳምንታት ብቻ ቀጥፏል፡፡ የኢንፍሉዌንዛ መነሻ ከላይ እንዳነሳናቸው አደገኛ ደዌዎች ሁሉ እንስሳት ናቸው፡፡ የተነሳው ከአሳማ መሆኑን ተመራማሪዎች ተስማምተዋል፡፡

የሞት መጠኑን መቆጣጠር የተቻለው የኤች አይ ቪ ቫይረስ መድሃኒት ባይገኝለትም ተጓዳኝ ሕመሙን ማከም ተችሏል፡፡ የመተላለፊያ መንገዶቹን መቀነስ የሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ግንዛቤ እንዲኖር በትጋት ተሰርቷል፡፡ አዝጋሚ ሂደቱን ቢቀጥልም አስፈሪ ከሚባለው ክልል ውስጥ የወጣው ኤች አይ ቪ ቫይረስ ወደ ሰዎች የመጣው ከዝንጀሮ መሆኑ ተነግሯል፡፡ ተገቢ ባልሆነው የእንስሳት እና የሰዎች ግንኙነት የተከሰተው ኤል አይ ቪ ወደ ሰዎች ተዛምቶ ራሱን ወደ ኤች አይ ቪ ቀይሯል፡፡

ዶ/ር ኤንድሬል እና ዴቪድ አይ ማችት የተባሉ ተመራማሪዎች ነባር የሐይማኖት መጻሕፍትን መሰረት በማድረግ ለሰው ልጆች ተገቢ የሆነ የምግብ ሕግ ለማውጣት ጥረት ያደረጉ ተመራማሪዎች ናቸው፡፡ ከ3500 ዓመት በፊት የተዘጋጁትን የምግብ ሕግጋት ያጠኑት ተመራማሪዎቹ በድምዳሜአቸው የቀደሙት ሕግጋት ከዛሬ ሳይንሳዊ መመሪያ ጋር የሚጣረስ ነገር እንደሌላቸው አረጋግጠናል ብለዋል፡፡ በዚህም የአሳማ እና የጥንቸል ስጋ የሰው ልጆች ላይ የሚያስከትሉትን የጤና እንከን እና ጉድለት ዘርዝረዋል፡፡

ዶ/ር ቫድሌን የተባሉ ተመራማሪ በበኩላቸው እ.ኤ.አ በ1969 ለንባብ በበቃው ጥናታቸው ፈረሶች እና ጥንቸሎች ለምግብነት መዋላቸው ጉዳት እንደሚያስከትል አብራርተዋል፡፡ ጥንቸሎች “ቱላሬሚያ” ለተባለው ተላላፊ በሽታ አጋላጭ ናቸው፡፡ የፈረስ ስጋም ቫይረሶችን እና ጥገኛ ሕዋሳትን ይዟል፡፡

ሜዲካል ዶክተሩ ዶን አልበርት ከነሀሴ-ጥቅምት ወር 1978 የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ መነሻ ሲያስረዳ

“አፋጣኝ ተቅማጥ፣ ራስ መሳት፣ መጠን ያለፈ ውጥረት፣ ይስተዋልባቸው የነበሩት ታማሚዎች የአሳማ ሾርባ፣ የአሳማ ደም ከኮምጣጤ ጋር፣ ብራይን ሺረፕ (ውሃ ውስጥ የሚኖር አሳ መሰል እንሰሳ) ተመግበው ነበር” ሲል መነሻው ከእንስሳት እንደነበር አብራርቷል፡፡

የአንድ ክስተት መደጋገም ለእርግጠኝነትም ባይሆን ለምርምር በር የሚከፍት አጋጣሚ መሆኑን ጠቁመን ከልዩ ልዩ ምንጮች የሰበሰብናቸውን ከእንስሳት ወደ ሰው የተላለፉ ሕመሞች ታሪክ እናጠቃልላለን፡፡ መረጃው ወደ ማስረጃ ተቀይሮ እውቀት እስከሚሆን ድረስ እና አንድ የተረጋገጠ እውነት እስክናውቅ መጠንቀቁ አይከፋም!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top