ታሪክ እና ባሕል

ከተራ ሕመም እስከ ቸነፈር

የሥነ ፍጥረት ምርምር ከቀን ወደ ቀን እየጠለቀ ሲሄድ የሳይንስና የቴክኒዮሎጂ ምሁራንም ጊዜ የሚወልዳቸውን ተውሳኮች እንደየአካባቢው ሁኔታ እየፈተሹ መፍትሔዎቻቸውን ይሻሉ።

የሕክምና ጥበብን ርቅቀት ለመገንዘብ ያህል ያለንን የማሰላሰል ጉልበት ወደ ሸመገለውና ለድርሳን መዘክርነቱ ወደር ወደማይገኝለት ዘመን አሻግረን ብንመልሰው ብዙ እንገነዘባለን። “እንዴት ነበር?” ማለት ጠቃሚ ነው።

በኢትዮጵያችን የነበረውን ባህላዊ የሕክምና ብልሃት ለአንድ አፍታ ዘወር ብሎ ዓይነ ኀሊናችን እንዲቃኝ ብንፈቅድለት እኛ የደረስንበት ሰዎች ሆንንም መጪው ትውልድ በተረትነት መሳለቂያ ከማድረግ አልፎ በርግጥ ታይቶ የታወቀ መሆኑን እንደ ሚጠራጠረው እሙን ነው።

ድሮ ከእናቱ ማሕፀን ወጥቶ ወደዚህ ዓለም ዜግነት የተለቀጠ ሕፃን እንዳይታመም “ለባለ ውቃቢ” በአደራ ተሰጥቶ ባነጠሰው ቁጥርና ትኩሳት ሽው ባለበት ሰዓት ቡና ተፈልቶና ወዳጃ ተይዞለት ይፈወሳል ይባል ነበር። ከበሽታው ሊፈወስ የሚበቃውም በደም ሥሩ በሚሰርጽ ወይም ተበጥቶ ደም በሚያልፈቅ ዘዴ ሳይሆን “በጫት እንትፍታ እና በምርቃት ተአምር” መሆኑ ይነገር ነበር።

“የሚጥል በሽታ (ኤፒሊፕሲ)፣ መጋኛ” እየተባሉ ስም የተሰጣቸው በሽታዎች በሰው ልጅ ሰርጸው ለአነዋወር ጉስቁልና የሚዳርጉትና ለሕልፈተ ሕይወት የሚያጋልጡት በሰይጣናት ኃይል መሆኑን የሚጠራጠሩ ብዙ አልነበሩም።

ምንም እንኳ ድብትርና የአባይ ጠንቋይነት ተግባር መታወቂያ ባይሆን ላቲናችን በሆነውም ግዕዝ ድርሳናትን ተመራምረው ለዝክር ከማንቆርቆራቸውና በማኀሌት ወረብ ከማሸብሸባቸው ጎን ዐውደ ነገሥት ማገላበጥ፣ መጽሐፍ መግለጥ፣ መፍትሔ ሥራይ ማድረግንና የመሳሰሉትን ሁሉ ደብተሮች ተክነውብት ኖረዋል።

ጽንስ የሚያስወርዱትና ልጅ የማያድግላት እናት ስትገኝ ከደብተሮች የተጻፈና የተጠለሰመ ብራና በቆዳ አሰፍታ በወገቧ ስትታጠቀው “ጽንሱም ይወለዳል፤ ውሉዱም ያድጋል” የጨሌ አቴቴና የግንቦት ቦረንትቻም ከበሸታ ይከላከላሉ ይባል ነበር።

“የሰው ዐይን” የሚፈራውን ያህል አንበሳና ነብር እንደማያስበረግጉ የእድሜ ባለጸጎች ከሚያወጉን ባሻገር ለምስክርነት የበቃንም ጥቂቶች ስላልሆንን የጉዳዩን እንግድነት ከቁም ነገር አግብተን አንጨነቅበትም። ሰው ሰውን በዐይኑ ወግቶ ሊያሳምመው ወይም ከዚያም አልፎ ተርፎ ለሞት ሊያደርሰው እንደሚል በሀገራችን የሚነገረው ከጥንት ነው። ዛሬም አንዳንዴ ይሰማል።

ማለፊያ ቁመናዋ በዐይነ ግቡነት አማላይ ሆኖ የውብት ጸጋ የተጎናጸፈች እመቤት ስትበላ ተጋርዶላት፣ ቤተ ክርስቲያን ስትሳለም ተጀቧቡና፣ ሰው እንዳያያት ተሸፋፍና እንደነበረ የከረሙ ወረቀቶች ይናገራሉ። እኛም የደረስንበት ለምስክርነት እንበቃለን። 

በተለይም ለዐይን ውግ የሚጋለጡት ሕፃናት መሆናቸው በብርቱ ስለሚታመንበት ጻዕዳ አልብሶ አደባባይ ማውጣትና በግልጽ እንዲታዩ ማድረግ “በቡዳ” የመበላቱን አደጋ ከፍ ስለሚያደርገው አዳፋ ማልበስ፣ ጥላሸት መቀባባት፣ በሻሽ ጠቅልሎ መደባበቅ የተለመደ ነበር።

በዐይን ወግቶ የመግደል ኃይል ያለው “ቡዳ” ጉልበቱ በዐይን ጦረኝነት ብቻ ተገድቦ የሚቀር ሳይሆን በነባራዊነት የደነደነበትን ሰብዓዊነት ወደ ፍጹም አውሬነት ለውጦ ቀን ቀን ሰው፣ ማታ ሲመሽ ደግሞ ጅብ እንደሚሆን ይነገር ነበር። ከመቅጽበት አራት እግርና ጅራት አውጥቶ ከሰውነት ወደ ጅብነት መለወጡ የማይመሰል ቢሆንም “ተእምር” ብለው በዝና ያደነቁ አልጠፉም።

በቡዳ “ተበልቶ” የሚቃትተው በሽተኛም የሚደረግለትን መፍትሔ የተጠበቡበት እነዚያው  “ደብተሮች” እንደሆኑ ይተረካል። “የወይራ እንጨት ከሰባት የጃርት ወስፌ ቅንጣቢና በዕለተ ሐሙስ ከተገደለ የእባብ ጭንቀላት ጋር ሆኖ መሬቱ ሲወጋ የቡዳው ሰው ጥላ ተወጋ” ማለት ይሆናል። በዐይን የተወጋው በሽተኛም “ደብተራው” የሚያስጠጉለትን መድኃኒት በማሽተት የወጊውን ስም እየጠራ እንደሚያጋልጥ ይወራል። ዛሬ በዘመናዊ የሕክምና ዘዴ የመከላከያ ክትባት እንዳለ ሁሉ “አሳጱራስጰስ- አስቆራስቂስ” የተሰኙትን ቃላት ያቀፈ የብራና ጽሑፍ አሰፍቶ በክንድ ማሰር ወይም በአንገት አጥልቆ መያዝ በቡዳ ከመወጋት ያድናል እየተባለ “የቡዳ መድኃኒት” ያልተሸከመ ሕፃን በጣት የሚቆጠር ነበር። ዛሬም አለ።

የምች መድኃኒት ቆረጣውም በዚያው ልክ አንድ ራሱን የቻለና የድርሳን ምዕራፍ ሊቸረው የሚገባ መሆኑን አንክድም። የስኳር በሽታ፤ የደም ብዛት (የደም ትርታ ማሻቀብ) ኢንፍሎዊንዛ” እየተባሉ የመታወቂያ ስማቸውን በኢትዮጵያ ከማጽደቃቸው በፊት በትኩሳት በራሰ ምታትና በመሳሰሉት የታጅቡ በመሆናቸው “ምች” በመባል የጥቅል መጠሪያ ተሰጥቷቸው ዘመናትን ለጡረታ አብቅተዋል።

የደም ፍተሻና የራዲዮ (ኤክስሬይ) ምርመራ እየተደረገ የበሽታው ዓይነት እንደሚታወቅ ዘመናዊ አሠራር የምች ሕመም መረጋገጥ የጠለቀ ምርምር ሳያስፈልገው በደፈናው ሲታመንበት ቆይቷል። በጠራራ ፀሐይ ቡና መጠጣት፣ በልቶ በውሃ ሳይጉመጠመጡ መውጣት፣ የቅባት እህል (በተለይም ተልባ) በልቶ ለአየር መጋለጥ፣ ጥላ ሳይበርድ ወዲያ ወዲህ ማለት “ያማታል” ይባላል። የሚማታውም ያው ርኩስ መንፈስ (ሰይጣን) መሆኑን ሳያወላውሉ ያምኑበታል።

በምች መድኃኒትነት የሚታወቁት በርካታ ቢሆኑም “ዳማ ከሴ” የተባለው ዕጽ በፍቱንነቱ የተመሰከረለት መሆኑን የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም። የዳማ ከሴ ቅጠል በጣሾች ከዘር በሚወራረስ መድኃኒተኝነት የተለገሱት፤ ከሰማየ ሰማያት የወረደ ጸጋ እንጅ ማንም መንገደኛ ቢቆርጥ ፍቱንነቱ የሰመረ እንደማይሆን ስላላመኑ የምች መድኃኒት ቆራጭ በመብራት እየተፈለገ እንደሚገኝ በይፋ ይነገራል። “ከዘር የተላለፈ ዱክትርና!” ይሏል ይህ ነው።

ዳማ ከሴው ታሽቶና ተጨምቆ በአፍንጫ ሲሳብ በብርቱ ያስነጥሳል። ራስ ምታትና ትኩሳት “ተሰናበቱ” ይባላል። የተባለውም ምች ገለል ይላል። የዕጽዋቱ ፍቱን መሆን ወይም ያለመሆን በሙያው ለተጠበቡ የሕክምና ሊቃውንት እንተውላቸውና ቅጠሉ ታሽቶና ተጨምቆ በአፍንጫ መማጉ ወይም ሰውነት ማበሱ ብቻ ድርሳነ ዳማ ከሴውን በእልባት አይደመድመውም። ከቆረጣውም ነገር አለና!

በዘር ሐረጉ የኮራውና በዕፅዋቱ ፍቱንነት የተማመነው የምች መድኃኒት ቆራጭ ቅጠሉን በጥሶ ሲያሸውና ሲጨምቀው ቀይ ጭማቂ ካልሆነ ግን ምችነቱን ይጠራጠራል። በሽተኛው ሳይመረመርና ሰውነቱን እንኳ የመድኃኒተኛው እጅ ሳይዳስሰው የሕመሙ ዓይነት ሊረጋገጥ ቻለ ማለት ነው። 

ለከባድ ራስ ምታት መሐል አናትን ላጭቶና በጥቶ በቀንድ ደም ማስመጠጥ፣ እንጥል ማስቆረጥ፣ ሴት ልጅ ማስገረዝ፣ የዓይን ቆብ ማስደንቆል፣ ለእንቅርት መከላከያ ይሆን ዘንድ አንገት ማሰነቀስና እነዚህን የመሰሉቱ “የሕክምና” ዘዴዎች በባህል  “ዶክተሮች” ሲካሄዱ ትውልድ አልፎ ትውልድ ተተክቷል።

በወጌሽነት በኩል የተመለከትን እንደሆነ ግን የተሰበረው ወይም የወለቀው አጥንት ሲታሽና ሲጠጋገን እንዳያመው የሚሰጥ ማደንዘዣ ባለመኖሩና አሠራሩም ጥበብ ያዘመነው ብልኃት የታከለበት ባለመሆኑ መቶ በመቶ ተቀባይነት ለማግኘት አይብቃ እንጅ ተንቆ ሊታለፍ እንደማይገባው የመሰከሩ የዘመኑ ጠበብት ትንሽ አይደሉም። ባሕላዊ የፍወሳ ብልኃትም በወገኑ በምርምርና በጥናት ተደግፎ ሳይንሳዊ ይዘቱ ቢጠናከር ዓይነተኛ መፍትሔ ሊሆን እንደሚበቃ ለመካድ አንደፍርም።

ያለፈውን ኋላ ቀር አመለካከት በጥቂቱ ከፈተሸን ዘንድ ከዚያ ጭፍን አማኝነት አላቆ በቅን አስተሳሰብ ሥልጣኔ ያዘመነውን የሕክምና ብልሃት ተቀብሎ እንዲያጸድቅ ማሳመኑ የቱን ያህል አስቸጋሪ እንደነበረ መገመት አያቅተንም።

በፋሲለደስ ዘመነ መንግሥት የንጉሡ የልብ ወዳጅ የነበረው ጀርመናዊው ዶክተር ፒተር ሄይሊንግ ጎንደር ከተማ በአንድ የቤተ ክርስቲያን ቅጽር የጤና ጣቢያ የቆረቆረ መሆኑን ሉዶልፍ በጽሑፍ አስፍረውታል። ይህ እንግዲህ በ1636 አካባቢ ነው። (ዓመተ ምሕረቱ እንደ ጎሪጎሪያዊው ቀመር ነው)።

ሎዶልፍ እንደጻፉት የተባለው ክሊኒክ ለንጉሡና ለቤተ ዙፋኑ ባለ ወጉች ከማገልገል በቀር ደፍሮ ለመታከም የከጀለ እምብዛም አልነበረም። የእምነት ጉዳይ አለና! ያለማወቅም እንዲሁ!

ዓመታት እያለፉ ዘመንም በአረጋዊነት ሲመደብ በወንጌል መልዕክተኝነት በነጋዴነትና በሌላውም የሙያ ዘርፍ ባሕር ማዶኞች ምድረ ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ ጊዜያት ሲጉበኙ ቀስ በቀስ ዘመናዊውንና በሳይንስ የተደገፈውን የሕክምና ዘዴ ሰው እየለመደው መሄዱን ጸሐፍት ለአንባብያን አቅርበዋል። 

እንዲያውም አንጥረኛም ይሁን ነፍጠኛ ፈረንጅ በተከሰተ ቁጥር “ሐኪም” ይባል እንደነበር ይነገራል። በዳግማዊ  አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የሕክምና ተግባር ሊሰፋፋ መቻሉን እንገዘባለን። በተለይም በአደገኝነቱ አሰፈሪ የሆነውን የፈንጣጣ በሽታ ለመከላከል ምኒልክ በ1889 እና በ1890 (እንደጉሪጉሪያዊው ዘመን አቆጣጠር) ዶክተር ሹርትስ በተሰኙ ሐኪም አማካይነት የክትባት ዘመቻ ማካሄዳቸው ተመዝግቧል። የሕክምና ጥበቡም በሰው አዕምሮ ይበልጥ እየሰረፀ መሄዱን አያሌ የብዕር አለቆች አስፍረዋል።

በ1905 (እ-ጎ-ዘ-አ) ጀርመናዊውን መራሔ ልዑክ ፌሊክስ ሮዘንን አጅበው አዲስ አበባ የገቡት ዶክተር ሐንስ ፎልብሬሽት ልዑካኑ ከአፄ ምኒልክ ጋር ተወያይተው እስኪመለሱ ድረስ ለእቴጌ ጣይቱና ለቤተ ዙፋኑ ወይዛዝርት የሰውነት ማፍታቻና ማጠንከሪያ ትምህርት መስጠታቸው ተጽፏል። “ሐኪም ይወደዳልም ይከበራልም። እቴጌይቱ በሁለት እጃቸው ሰላምታ ሰጡኝና አሰናበቱኝ። በስንብቱም ወቅት አለቀሱ” ሲሉ አትተዋል። ዶክተር ፎልብሬሽት ሕዝቡ ለሕክምና የነበረውን ጉጉትም በሚገባ ተንትነውታል።

የሕክምና ነገር እንደልብ ተዳርሶ “ነበር” ብለን ለመናገር ቋንቋ ቢያጥረንም በዚያን ዘመን ከነበረው ኋላ ቀርነት አኳያ ሲታይ ሐኪም በእርግጥ የተፈቀረ መሆኑን ለመገመት እንችላለን። አንዳንዶቹ እንደውም በቅዱስነት እንደተዘከሩ ተጠቅሷል።

በ1931 (እ.ጎ.ዘ.አ) አዲስ አበባ የነበሩት ዶክተር ጋብሪሎፍ የተሰኙት ሐኪም “የገብርኤል-ወፍ” ተብለው ብዙ ታካሚዎች በጻድቅነት ይመለከቷቸው እንደነበረ ገልጸው አስፍረውታል። ቅጠል በመበጠስ እና “ጠልስም አስሎ በማንገት ይዳናል” የሚባልበት፤ አባይ ጠንቋይም እንደ ፈጣሪ የሚመለክበት ጊዜ ስለነበረ የንቃተ ኀሊናን ማዘቅዘቅ ለመመስከር አያቅተንምና በዚሁ አምነን መቀበል እንገደዳለን።

በአንድ በኩል ባሕር ማዶኞች ወደ ኢትዮጵያችን መጥተው ዘመናዊ ሕክምና ማስፋፋታቸውን በይበጃል ስናጸድቀው አንዳንድ አስቂኝ የሆኑ ጉዳዮች ደግሞ ይከሰቱና ያስገርሙናል። መቼም ጥበብ ብርቅ በሆነበት ሥፍራ የማይከሰት ነገር የለምና ዶክተር ላንዳው ከተባሉ የኦስትሪያ ተወላጅ ጋር በሎሌነት የመጣ ሣእን የተባለ አንድ ጀርመናዊ ከጌታው ጋር ተጣልቶ ቢያሰናብቱት በቅዱስ ጊዮርጊስ ስም መድኃኒት ቤት መክፈቱ ይተረካል።

በድፍን ኢትዮጵያ ሁለተኛው መሆኑ የሚነገርለት የያኔው ቅዱስ ጊዮርጊስ መድኃኒት ቤት የደራ ገበያ የነበረው ከመሆኑም በቀር ከተራ ረዳትነት ወደ መድኃኒተኝነት ራሱን የሾመው ጀርመናዊ ብዙ መሰንበትም ሳያስፈልገው “ሐኪም ሣእን” እየተባለ “ብር በአካፋ” ሆኖለት በመጨረሻም ነገረ ሕክምናውን ጥሎ ለጥቂት ዓመታት በአዳሚ ቱሉ ግብርና አካሂዶ ወደ ሀገሩ ተመልሷል። ይህ ነገር የተፈጸመው በ1925 እና በ1927 (እ.ጎ.ዘ.አ) እንደ ነበረ ተጽፎአል።

ኢትዮጵያዊው ወገን ዱክትርና አግኝቶ እንደ ዛሬ ለዘመኑ ሳይንስ ምስክርነት ሳይበቃ ያፈራናቸው ሐኪሞች ብርቅዬዎች ነበሩ። ከሀገራችንም ሐኪሞች  አፄ ምኒልክን በመጨረሻው የእድሜ ማምሻቸው ያከሙት እና በኋላም በፋሺሽት ወረራ ዘመን በስደት ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጋር ሆነው ታላቁን ፖለቲካዊ ትግል አብረው ያካሄዱት ዶክተር ማርቲን ወርቅነህ በቀደምትነት ሲታወቁ በፋሺስት ወረራ አካባቢ የነበሩት ደግሞ ዶክተር መላኩ በያን አይዘነጉም።

እንግዲህ በሀገራችን ጥንት የነበረውን፣ በኋላም አንዳንዶቻችን እድሜ ሰጥቶን ያየነውን የሕክምና ብልሃት እና የሐኪሞችን ሁኔታ ዐይተናል። ስለ በሽታውም ቃኝተናል። ዛሬስ ያለው ቸነፈር ምን መልክ ይኖረው ይሆን? ይህ በመላው ዓለም የተሰራጨው ኮሮና ቫይረስ እጅግ አስጊ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑን የሚክድ ያለ አይመስለንም። ለሁሉም የመንግሥትን መመሪያና የተባበሩት መንግሥታት የጤና ክብካቤ ድርጅት የሚሰጠውን ምክር መቀበልና ተግባራዊ ማድረግ አማራጭ የሌለው ነው። በተረፈ ደግሞ ብዙ ጊዜ እኛ ሰዎች የምናጠፋው የመጣብንን መቅሰፍት በጸሎትና  በምሕላ ወደ ፈጣሪ መማጸናችንን ትተን በማሾፍ እና እንዲሁም የመጣውን ቸነፈር እንዳልመጣ በመቁጠር የምናካሂደው አጉል የጅል ቀልድ ነው። ከዚህ አጉል ድርጊት መታቀብ ይኖርብናል።  

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top