ታሪክ እና ባህል

ታሪከ ወረርሽኝ

የወረርሽኝ በሽታዎች ከሰው ወደሰው፣ ከእንስሳ ወደሰው፣ ከሰው ወደእንስሳት እና ከእንስሳት ወደ እንስሳት በፍጥነት የሚተላለፍ እና ለመቆጣጠሩም በጣም አዳጋች የሆኑ ህመሞች ናቸው። የሰው ልጆች በመላው ዓለም ላይ እየተስፋፉ ሲሄዱ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችም በዛው ልክ ሊስፋፉ ችሏል። አሁን ባለንበት ዘመን እንኳ ወረርሽኝ ሊያስብል በሚችል ስፋት የሚስፋፉ በሽታዎች ብዙም ባይኖሩም፤ ከቅርብ ወራት ወዲህ ግን የኖቭል ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) በሽታ በዓለማችን ላይ በፍጥነት እየተስፋፋ እና ብዙዎችን ለሞት እያደረገ፤ የዓለም ህዝብ ራስ ምታት ለመሆን ችሏል።

የክስተት ዘመናት

በሽታዎችና ወረርሽኞች ከቅድመ-ታሪክ ዘመን አንስቶ የሰው ልጆችን የሚያጠቁና ለሚሊዮኖች ሞትም ምክንያት ነበሩ። ሆኖም ግን የሰው ልጅ ተሰባስቦ የእርሻና እንስሳት እርባታ ከጀመረ ወዲህ ነው የወረርሽኞቹ ቁጥር በአስፈሪ መጠን እየተበራከተ የመጣው።

የጥንቱ ዘመን ዓለማቀፍ የንግድ ልውውጦች በሰዎችና በእንስሳት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲበራከት በማድረጉ ሳቢያ የወረርሽኝ በሽታዎችም ተስፋፉ። ወባ፣ ቲቢ፣ ኢንፍሉዌንዛ፣ ኩፍኝ እና ሌሎች ወረርሽኞች በጥንት ዘመናት የተለመዱ ነበሩ።

የሰው ልጆች እየሰለጠኑ ሲመጡና ሰፋፊ ከተሞች፣ ረጃጅም የንግድ መስመሮች፣ እና የተለያዩ የዓለማችን ህዝቦች እርስ በርስ እንዲሁም ከእንስሳትና ከተለዋዋጭ የአየር ንብረቶች ጋር ግንኙነታቸው ሲጨምር፤ የወረርስኝ በሽታዎችም በዛው ልክ ሊጨምሩ ግድ ይላል።

ከስር ባለው ሰንጠረዥ ዓለማችንን ያጋጠሟት ዋና ዋና ወረርሽኞች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡-

የወረርሽኙ  ስም ያጠቃበት ዘመን ዓይነት/ ከሰው በፊት  የተሸከመው እንስሳ የሟቾች ቁጥር
የአንቷኒን ወረርሽኝ 165-180 በሳይንቲስቶች ኩፍኝ ወይም ደግሞ ፈንጣጣ ነው ተብሎ ይታሰባል 5 ሚሊዮን
የጃፓኑ የኩፍኝ ወረርሽኝ 735-737 ቫርዮላ ማጆር ቫይረስ 1 ሚሊዮን
የጁስትኒያን ወረርሽኝ 541-542 የርሲኒያ ፔስቲስ ባክቴሪያ / በአይጦች እና ዝንቦች የመጣ ከ30 እስከ 50ሚሊዮን
ጥቁሩ ሞት 1347-1351 የርሲኒያ ፔስቲስ ባክቴሪያ / በአይጦች እና ዝንቦች የመጣ 200 ሚሊዮን
የዘመናዊው ዓለም የኩፍኝ ወረርሽኝ ከ1520 – እስከአሁን ቫርዮላ ማጆር ቫይረስ 56 ሚሊዮን
ታላቁ የለንደን ወረርሽኝ 1665 የርሲኒያ ፔስቲስ ባክቴሪያ / በአይጦች እና ዝንቦች የመጣ 100,000
የጣሊያን ወረርሽኝ 1629-1631 የርሲኒያ ፔስቲስ ባክቴሪያ / በአይጦች እና ዝንቦች የመጣ 1 ሚሊዮን
የኮሌራ ወረርሽኞች ከ1-6 1817-1923 ቪ. ኮሊሬ ባክቴሪያ ከ1 ሚሊዮን በላይ
3ኛው ወረርሽኝ 1885 የርሲኒያ ፔስቲስ ባክቴሪያ / በአይጦች እና ዝንቦች የመጣ 12 ሚሊዮን (በቻይና እና በህንድ)
ቢጫ ወባ ከ1800ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ቫይረስ/ የወባ ትንኝ ከ100,000-150,000 (አሜሪካ)
የሩስያው ጉንፋን 1889-1890 ኤችቱ ኤንቱ ነው ተብሎ ይታመናል 1 ሚሊዮን
የስፔን ጉንፋን 1918-1919 ኤች ዋን ኤን ዋን ቫይረስ/ አሳማ ከ40 እስከ 50ሚሊዮን
የእስያ ጉንፋን 1957-1958 ኤችቱ ኤንቱ ቫይረስ 1.1 ሚሊዮን
የሆንግ ኮንግ ጉንፋን 1968-1970 ኤች ስሪ ኤንቱ ቫይረስ 1 ሚሊዮን
ኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ ከ1981-እስከአሁን ቫይረስ/ ቺምፓንዚ ከ25 እስከ 35 ሚሊዮን
የወፍ ጉንፋን 2009-2010 ኤች ዋን ኤን ዋን ቫይረስ/ አሳማ 200,000
ሳርስ 2002-2003 ኮሮና ቫይረስ/ የለሊት ወፍ 770
ኢቦላ 2014-2016 ኢቦላ ቫይረስ/ የዱር እንስሳት 11,000
መርስ ከ2015-እስከአሁን ኮሮና ቫይረስ/ የለሊት ወፍ/ ግመል 850
ኮቪድ-19 ከ2019-እስከአሁን ኮሮና ቫይረስ 27,000 (ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ እስከ ማርች 27 ድረስ ባስታወቀው)

አብዛኞቹ ቁጥሮች የተመዘገቡ ታሪኮች ላይ ባለመስፈራቸው፤ የተለያዩ መረጃዎችን በመመርኮዝ ምሁራዊ የሰፊ ጥናት ግምት የተደረገባቸው ናቸው፡፡ በቅርብ ጊዜ ላይ ያሉት ግን እያንዳንዱ ቁጥሮች በአግባቡ የተመዘገቡ ናቸው።

በታሪክ ውስጥ ተከታታይነት ባለው ሁኔታ በሽታዎች እና ወረርሽኞች የተስፋፉ ቢሆኑም፤ አንድ እየተስተዋለ ያለ ዋና ጉዳይ የሟቾች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ነው። የጤና ጥበቃ በዓለማችን ላይ እየዘመነ እና እየጎለበተ መሄድ እንዲሁም የሳይንስ መራቀቅ፤ ወረርሽኞቹ ከፍተኛ ጉዳት እንደቀድሞው ዘመናት እንዳያደርሱ ገትቷቸዋል።

ቁጣ

በብዙ ጥንታውያን ማህበረሰቦች ዘንድ የወረረሽኝ በሽታዎች ሲከሰቱ፤ አማልክት አልታዘዝ ያሏቸውን ሰዎች ለመቅጣት ሲሉ ያመጧቸው ናቸው ተብለው ይታመናሉ። እንደዚህ አይነት ከሳይንሱ ጋር ያልተስማሙ አስተሳሰቦች ለብዙ ሺዎች እና ሚሊዮኖች መሞት መንስኤ ሆነዋል፡፡   

ለምሳሌ ያህል የጁስቲንያን ወረርሽኝ ሲነሳ፤ ታዋቂው የባይዛንታይን የታሪክ ፀሃፊ ፕሮኮፒየስ፤ የበሽታውን መነሻ ምክንያት ሲያጠና ከሩቅ ምስራቅ የቻይናና የህንድ ከተሞች የተነሳ በሽታ መሆኑን ደርሶበታል። በተለያዩ የንግድ መስመሮች አድርጎ በሜድሪታኒያን የግብፅ የባህር ወደብ አድርጎ ነው ወደባይዛንታይን ግዛት ሊገባ የቻለው።

ይህንን ሁሉ በምርምሩ ደርሶበት ሳለ፣ ስለንግድ መስመሮች እና ስለጂኦግራፊ ጥሩ እውቀት እያለው ግን፤ ፕሮኮፒየስ የወረርሽኙን መከሰት በቄሳሩ ጁስቲንያን ላይ ሊያሳብበው ችሏል። “ቄሳሩ እግዚአብሄርን በማስከፋቱ ወይም ደግሞ ሰይጣናዊ ተግባራትን በድብቅ ያደርግ ስለነበረ ነው ወረርሽኙ የተከሰተው” በማለት ጁስቲንያንን ወቅሶበታል። በዛን ዘመን የተከሰተው ወረርሽኝም የጁስቲንያንን ወረረሽኝ እየተባለ በህዝቡ ዘንድ ይጠራ ነበር። በዚህም ሳቢያ ይመስላል ምዕራብና ምስራቅ የሮም ግዛትን አንድ ለማድረግ ይታትር የነበረው ጁስቲንያን፤ ስሙ በወረርሽኙ ምክንያት ስለጠለሸ ሳይሳካለት የቀረው።

እንደጥሩ ዕድል ሆኖ የሰው ልጅ ስለበሽታዎች ያለው እውቀት እየጨመረ በመምጣቱ፤ እንደሚፈለገው ባይሆንም ለወረርሽኝ በሽታዎች በአሁኑ ዘመን አፋጣኝ ምላሽ እየተሰጠ ይገኛል።

ኳረንቲን

በ1347 እ.አ.አ. አውሮፓን ያጠቃው ‹ጥቁሩ ሞት› የሚባለው ወረርሽኝ ለ4ዓመታት የቆየ ሲሆን፤ የሰው ልጆችን ካጠቁ ወረርሽኞች ሁሉ የከፋው ነወ። በዚህ ወረርሽኝ ሳቢያ ቁጥሩ እስከ 200 ሚሊዮን የሚደርስ ህዝብ አልቋል። ወረርስኙን ለመከላከል ታዲያ ‹ኳረንቲን› የተባለ ዘዴ ተፈጠረ። ኳረንቲን ማድረግ የተጀመረው በ14ኛው ክፍለዘመን ነው። የወደብ ከተሞችን ከወረርሽኝ በሽታዎች ለመታደግ ሲሉ የቬነስ ባለስልጣናት፤ ወረረሽኝ ተከስቶባቸዋል ከሚባሉ ቦታዎች እንደመጡ የሚጠረጠሩ መርከበኞች መልሕቃቸውን ዘርግተው ወደመሬት ሳይወርዱ 40 ቀናት እንዲቆዩ ያደርጉ ነበር። ‹ኳረንቲን› የሚለው ቃልም “quaranta giorni” ከሚለው የጣሊያንኛ መጠሪያ የመጣ ሲሆን፤ ትርጉሙም ‹40 ቀናት› ማለት ነው።

የመጀመሪያው በስታቲክስ እና ጂኦግራፊ ጥናት የተደገፈ ሳይንሳዊ ምርምር በ19ኛው ክፍለዘመን በለንደን በተከሰተ የኮሌራ ወረርሽኝ ላይ ነበር የተደረገው። በ1854 ዶክተር ጆን ስኖው ወረርሽኙ የተከሰተው በተበከለ ውሃ ምክንያት መሆኑን በማሳወቅ፤ የውሃውን መስመር በመከተል የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ካርታው ላይ በማስፈር ስሎ አሳይቷል። የእሱን ካርታ በመጠቀምም የት አካባቢ ውሃው መበከል እንደጀመረ ሊታወቅ ተችሏል።

መለኪያዎች

ሳይንቲስቶች አንድ ሰው ወደ ምን ያህል ሌሎች ሰዎች በሽታውን ያስተላልፋል የሚለውን ለመለካት “R0 or “R naught”” የሚባል መለኪያ ይጠቀማሉ። ይህም አንድ ሰው በአማካይ የሚበክላቸውን ሰዎች ቁጥር የሚያሳይ ነው።  ለምሳሌ የማጅራት ገትር በሽታ ባልተከተቡ ሰዎች ላይ ያለው የመስፋፋት ልኬት ከ12-18 ነው።

አሁን ያለው የኮሮና (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ምንያህል የመስፋፋት ምጣኔ እንዳለው፤ እስካሁን ድረስ የተሟላ መረጃ ስለሌለ ለማወቅ አልተቻለም። ክትባት የሌለው በመሆኑ ግን በቀላሉ ወደብዙ ሰዎች ሊተላለፍ የሚችል መሆኑ ለመገመት አይከብድም።

ከተሜነት እና መስፋፋት

የከተሞች በፍጥነት እየበዙና እየጎለበቱ መሄድ፤ ባላደጉ ሃገራት ላይ ከገጠር ወደከተማ የሚገባውን ህዝብ ቁጥር እንዲጨምር አድርጎታል። የህዝብ እድገቱ ደግሞ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ የሚታወቅ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የአይሮፕላን በረራዎች ከየትኛውም ጊዜ በላይ ባለንበት ዘመን እየተበራከቱ መሄድ፤ ለወረርሽኝ በሽታዎች መስፋፋት አባባሽ ምክንያት ሆኗል።

ዓለምአቀፍ ተቋማት እና ቁጥራቸው የበዛ የዓለም መንግስታት፤ ሰዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ በማድረግ የወረርሽኙን መስፋፋት ለመግታት እየሞከሩ ይገኛሉ።

የዓለም የጤና ድርጅት የ‹ወረርሽኝ› ደረጃን የሰጠው የኮቪድ-19 (ኮሮና ቫይረስ) ፤ ይሄ ፅሁፍ እስከሚጠናቀርበት ሰዓት ድረስ ባለው በመላው ዓለም ላይ ከ27 ሺህ ሰዎችን ለሞት ዳርጓል፡፡  

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top