ታዛ ስፖርት

ሳንጠግበው ያጣነው አጥቂ

በአስመራው ሳባ ስታድዬም የገባው ተመልካች በድምፅ ማጉያ የሚተላለፈውን ሙዚቃ እየሰማ የውድድሩን መጀመር ሰዓት እየጠበቀ ነው። ነገር ግን ጨዋታው በሰዓቱ ሊጀመር ባለመቻሉ ማጉረምረም ጀምሯል። የኡጋንዳ ቡድን አሟሙቆ ጨርሶ ተጋጣሚውን እየጠበቀ ነው። ተመልካቹም የኡጋንዳን ተጋጣሚ  “ግባ በለው” እያለ ይጎተጉታል። ዳኛው ፊሽካ ነፍተው ሁለቱም ቡድኖች ወደ ሜዳው ይዘው መዝለቅ አልቻሉም። ዳኛው ፊሽካ ባይነፋም ተመልካቹ በብስጭት የራሱን ፊሽካ እያሰማ ነበር። ፉጨት።

ተመልካቆች የኡጋንዳ ተጋጣሚ የገጠመውን ቢያውቁ “ግባ በለው” ሲሉ ባልተንጫጩ ነበር። አዘጋጅ ኮሚቴው በነገሩ ግራ በመጋባቱ አንደኛውን ቡድን ለማስመጣት ወደ ሆቴል ሰው ቢልኩም መልዕክተኛው የማላዊን ቡድን ይዘው አልተመለሱም።

ተመልካቹ ሜዳ ገብቶ የጨዋታውን መጀመር እየጠበቀ ባለበት ሰዓት ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ አንድ ስልክ ተደወለ። በቀጭኑ ገመድ የመጣው ወሬ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንንም ሆነ አዘጋጅ ኮሚቴውን ያሳዘነ ነው። መልዕክቱን ያደረሱት የማላዊ ቡድን አሰልጣኝ ነበሩ። መልእክቱ “የቡድን መሪያችን ስለሞተ ውድድሩን አቋርጠን እንሄዳለን” የሚል ነበር። መርዶውን ያልሰማው ተመልካች ማላዊን አምጡልን እያለ ማፏጨቱን አላቋረጠም።

በ1980 ዓ.ም. የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ ውድድር በኢትዮጵያ ሲዘጋጅ በአዲስ አበባ ቡድኖችን ከታንዛኒያ፣ ኬንያ፣ ዛንዚባር ጋር ተደለደለ። የእነማላዊ ቡድን ከእነዙምባቡዌና ኡጋንዳ ጋር አስመራ ነበር የተመደበው። በመጀመሪያ ግጥሚያ የማላዊ ቡድን አንድ ተጫዋቻቸው በሜዳ ላይ ተገጭቶ ወደ አዲስ አበባ ሰደዱት። ጉዳቱ ከፍተኛ በመሆኑ ወደ ሀገሩ ተላከ። በሁለተኛው ቀን ቡድን መሪያቸውን በሞት አጡት።

በዚያን ወቅት የኢትዮጵያ ቆይታቸው በጥሩ ሁኔታ የሚያስቡት አልነበረም። ይሄኛውን የሴካፋ ዋንጫ የኢትዮጵያ ቡድን ወሰደው። በቀጣዩ በ1981 ውድድሩ ማላዊ ላይ ተካሄደ። ለነርሱ አዘጋጅነቱ የተሰጣቸው ለሟቹ ቡድን መሪ መታሰቢያነት ሊያውሉት ስለፈለጉ ነበር።

በማላዊ ውድድር ከኢትዮጵያ ሙሉጌታ ወልደየስ የነገሰበት እና ባስቆጠራቸው ግሩም ግቦች በማላዊ ጋዜጦች ሳይቀር አድናቆት ያገኘበት ነበር።

ሙሉጌታ ፈጣን ባይመስልም ቁመቱ ረጅም ስለሆነ ሳብ ሳብ እያለ በመሮጥ ለተከላካዮች አስቸግሮ ነበር። በተለይ ከኡጋንዳ ጋር ተከላካዮችን አምልጦ ያስቆጠረው ኳስ  ወሬው አዲስ አበባ ደርሶ አድናቆቱ የርሱ ብቻ ነበር።

በዚሁ ዓመት መጀመርያ በ1981 ዓ.ም. ቡና ገበያ የይድነቃቸውን ዋንጫ ጨምሮ የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ሲያነሳ የሙሉጌታ ድርሻ ከፍተኛ ነበር። በተለይ በዓመቱ መጀመርያ የአሸናፊዎች አሸናፊን ዋንጫ ለማንሳት ከምድር ጦር ጋር ያደረጉት ግጥሚያ በተመልካቹ ዘንድ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ነበር። ጨዋታው የሙሉጌታ እና የምድር ጦር ፍጥጫ ይመስል ነበር። ቡና የዚህን ውድድር ዋንጫ በታሪክ አግኝቶ አያውቅም። በሙሉጌታ አምበልነት የተመራው ቡድን ታሪካዊውን ዋንጫ ለመጀመርያ ጊዜ ለመሳም አንጋፋውን ቡድን ገጠሙት። ጨዋታው ፈጣን ነበር። እንደተጀመረ ዓለምሰገድ አንቼ ለጦሩ በአምስተኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥሮ መምራት ጀመሩ። ሙሉጌታ ወልደየስ በ10ኛው ደቂቃ አቻ አደረገ። ታሪኩ መንጀታ በ17ኛ ደቂቃ ጦሩን መሪነት ላይ አቆመ። ሙሉጌታ እንደገና ተመልሶ መጣ እና በ20ኛው ደቂቃ ቡናን አቻ አደረገ። ጌቱ ማሞ በ35ኛው ደቂቃ አስቆጥሮ ምድር ጦርን ከፊት አቆመ። በ37ኛው ደቂቃ ሙሉጌታ አስቆጠረ። ግን ተሻረ። ወዲያው በ39ኛው ደቂቃ ሚሊዮን አስቆጥሮ ቡና 4ለ3 በማሸነፍ አዲሱን ዋንጫ ወደ ቤቱ አስገባ።

ሙሉጌታ በተለይ በዚህ ጨዋታ ባሳየው ድንቅ ችሎታ ደጋፊው “የሙሌ ዋንጫ ነው” እስከማለት ደርሶ ነበር። ሙሉጌታ ይሄን ዋንጫ ካነሳ በኋላ ማላዊ ላይ በተደረገው ውድድር ተሳትፎ አድናቆትን አግኝቶ ተመለሰ። በጥቅሉ ዓመቱ ለርሱ ጥሩ ከመሆኑም ሌላ ችሎታው እጅግ ገዝፎ ነበር። ከማላዊ እስከ አዲስ አበባ በአድናቆት እየተወራለትም ነበር።

የኢትዮጵያ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ግብፅን ሊገጥም ሆቴል ገብቷል። ቡድኑ ውስጥ በዚያን ወቅት ሙሉጌታ ጎልቶ በመውጣቱ ከእርሱ ብዙ ተጠብቋል። የስፖርት ቤተሰቡ ዘንድሮ ሙሉጌታን በወቅታዊ አቋሙ ብቻ ሳይሆን በፀባየ ሸጋነቱ ለተመልካቹ ባለው ክብር እጅግ ወዶት ነበር።

ብሔራዊ ቡድናችን ግብፅን ከመግጠሙ በፊት የአቋም መለኪያ ጨዋታ ማፈላለግ ጀመረ። የኬንያ ቡድን ጥሪ ተደረገለት። ለመምጣት ከተስማማ በኋላ ጥቂት ቀን ሲቀረው “ችግር ስለገጠመኝ ፕሮግራሙን ሰርዣለሁ አትጠብቁኝ” ብሎ መልዕክት ላከ። ፌደሬሽኑም ብሔራዊ ቡድኑ አቋሙን ሳይለካ ግብፅን ይግጠም ብሎ ወሰነ። ተጨዋቾቹና ጀርመናዊው አሰልጣኝ ክላውስ “ቡድን ፈልጉልን” ብለው ቅሬታ ስላቀረቡ ፌዴረሽኑ “ካገኘሁ አስመጣችኋለሁ” በሚል ቡድን ሲያፈላልግ አልተሳካለትም። በመጨረሻ ግን ማላዊን ሲጠይቅ “እንመጣለን” ብለው አሳወቁ።

ሁለቱ ቡድኖች አዲስ አበባ ላይ መጋቢት 17 ቀን እሁድ ዕለት ተጋጠሙ። ገብረመድህን ኃይሌ ባስቆጠራት ግብ ኢትዮጵያ 1ለ0 አሸነፈች። የማላዊ ቡድን እሁድ ተጫውቶ ማክሰኞ ወደ ሀገሩ ለመብረር ነው ፕሮግራም የያዘው። የእኛ አሰልጣኞች “አንድ ጨዋታ በቂ አይደለም ድገሙን” ስላሉ ፌደሬሽኑ የማላዊን ሰዎች “ወጪያችሁን እችላለሁ ማክሰኞ ድገሙንና አርብ ትሄዳላችሁ” አሏቸው። ማላዊ አንገራገረ፤ ፌደረሽኑም “ከሜዳ ገቢ አካፍላችኋለሁ” የሚል ጥያቄ ስላቀረበ የማክሰኞውን ጨዋታ ለማድረግ ተስማሙ።

ሁለቱ ወገኖች ድጋሚ ጨዋታ ለማድረግ ሲስማሙ የሙሉጌታ የኳስ ፋይል እንደሚዘጋ ማን ያውቅ ነበር?

በሁለተኛው ግጥሚያ ወደ ሜዳ የገባው የኢትዮጵያ ቡድን አሰላለፍ፤ ተካበ ዘውዴ፣ ደረጀ በላይ፣ ሰለሞን ኃይሌ፣ ዳኛቸው ደምሴ፣ በቀለ ብርሀኑ፣ ተስፋዬ ፈጠነ፣ ገብረመድህን ኃይሌ፣ ሙሉጌታ ከበደ፣ ሙሉጌታ ወልደየስ፣ ጌቱ ከበደ እና ዮናስ ተፈራ ነበሩ።

የማክሰኞው ጨዋታ ኃይለኛ ነበር። ካፊያ ዝናብ ይጥላል። ሹክቻ እና ጥልፊያ እዚያም እዛም ይታያል። የምሽት ጨዋታ መገለጫውም ይሄ ነበር። ኢትዮጵያ በሙሉጌታ ከበደ አማካኝነት 1ለ0 እየመራች ነበር። በዚህ ጨዋታ ሙሉጌታ ወልደየስ እና ጌቱ ከበደ ጥሩ አቋም ላይ ስለነበሩ ከተመልካቹ የአድናቆት ጭብጨባ እየተለገሳቸው ነበር።

በተለይ ሙሉጌታ ወልደየስ ከወትሮው የተሻለ ነበር። እያመለጠ በመሄድ አስደንጋጭ ሙከራ እያደረገ ነው። በረኛውን ደጋግሞ ፈትሾታል።

እኔ የተቀመጥኩት በቀኝ በኩል በሚገኘው ከማን አንሼ ስፍራ ላይ ነበር። ምሽት ነው። ጨዋታው ፈጣንና ትግል የበዛበት እንደነበር አስታውሳለሁ። ለእረፍት ጥቂት ደቂቃ ሲቀረው ሙሉጌታ ወልደየስ ተከላካዮቹን አምልጦ በረኛውን አልፎት የመታት ኳስ ለጥቂት በብረቱ ስር ወጣች። ይህች ሙከራ እንደተደረገች ዳኛው ለእረፍት ፊሽካ ነፋና ወደ መልበሻ ክፍል ሄዱ።

ተመልካቹ በእረፍት በአብዛኛው የሚወያየው በሙሉጌታ ድንቅ አቋም እና መጨረሻ ላይ ስለ ሳታት ግብ ነበር። አንዳንዱ ታዳሚ “እንዲህ ቢያረጋት እንደዚያ ቢመታት፣ ቢያጥፍ፣ ቢቆለምማት፣ ቢቆርጣት፣… ትገባ ነበር” እያለ በመሰለው መንገድ በኳስ ቋንቋ እያወራ ነበር። አንዳንዱ ከእረፍት በኋላ “ሙሉጌታ ሁለት ያስቆጥራል፣ አንድ ያገባል” እያለ ግምቱን ይደረድር ጀመር። ከዚህ ጋር አያይዞ ሙሉጌታ ለግብፁ ጨዋታ ጥልቅ ነገር ይሰራል በሚል ተመልካቹ በእርሱ ላይ ትልቅ እምነት እየጣሉ ነበር።

ወደ ሜዳ የገባው ታዳሚ ጥሩ ነገር በማዬቱ ከእረፍት በኋላም የሙሉጌታን ድንቅ እንቅስቃሴ ለመኮምኮም እየጠበቀ ነበር።

ቡድኑ ወደ መልበሻ ክፍል እንደገባ አሰልጣኙ እየመከረ ባለበት ወቅት አንድ ተጨዋች የጫማውን ክር እየፈታ ነበር። ጫማውን ካወለቀ በኋላ ካልሲውን ደገመ። ጫማ አውላቂው ተጫዋች ተቀያሪ አልነበረም። ተቀየር ያለውም የለም። አሰልጣኙ እየመከረ ድንገት ዞር ሲል ጫማውን እያወለቀ ያለውን ልጅ ተመለከተ። በልጁ ድርጊት ተገረመ። ይህ ተጫዋች ሙሉጌታ ወልደየስ ነው። አሰልጣኙ ግራ ተጋባ። መምከሩን ትቶ ሙሉጌታን ያየዋል። ሙሉጌታ አጎንብሷል። ሀሳቡ ከቡድኑ ጋር የለም። የአሰልጣኙን ምክርም አይሰማም። ምክትል አሰልጣኙ ወደ ሙሉጌታ ጠጋ አለና ጮክ ብሎ “ሙሉጌታ” ብሎ ተጣራ።

“አቤት!”

“ምን እያደረግክ ነው?”

“በቃኝ!”

“በቃኝ ስትል ምን ማለትህ ነው?”

“ቀይሩኝ”

“ለምን?”

“ደክሞኛል”

“አልደከመህም”

“እሺ በቃኝ”

አሰልጣኙ ሙሉጌታ በሚሰጠው መልስ ተበሳጨ። በሜዳ ላይ የቡድኑ አቅም እርሱ ላይ እንዳለ ያምናሉ። ከእረፍት በኋላ ተመልካቹ ሙሉጌታ እንደሚጠበቅ ያውቃሉ። ቢወጣ እነርሱ የቀየሩት ስለሚመስላቸው ተቃውሞ እንደሚገጥማቸው ገምተዋል። ስለዚህ መውጣት የለበትም። አሰልጣኙ እንደገና ሙሉጌታን በጥያቄ ያዋክበው ጀመር። “የሆንከው ነገር አለ?” ብሎ ጠየቀው።

“የለም!”

“ታድያ ለምን ትወጣለህ?”

“መጫወት አልፈልግም!”

“ለምን?”

“አላውቅም”

“ከተጫዋቾች ጋር ተጣልተሃል?”

“አልተጣላሁም!”

“ተመልካቹ ሰድቦሃል?”

“አልሰደበኝም!”

“ታድያ ለምን ጫማህን ታወልቃለህ?”

“ሌላ ሰው ይግባ!”

“ለምን?”

“እኔ ቀፎኛል!”

“ቀፎኛል ስትል ምን ማለት ነው?”

“ደስ አላለኝም!”

“ሜዳ ላይ እኮ ጥሩ ነበርክ”

“አሁን ለመጫወት ስሜቴ ደስተኛ አይደለም”

“እንድንለማመጥህ ነው?”

ክርክሩ መቋጫ አልነበረውም። ሙሉጌታ ለሚያቀርቡለት ጥያቄዎች መልስ ስላለቀበት ዝም ብሏል። አሰልጣኙም ወደ ሙሉጌታ ዕያዩ “አዲስ ባህርይ እያመጣህ ነው። ይሄን ጉዳይ ከጨዋታ በኋላ እንነጋገርበታለን። አሁን ግን የሚቀይርህ ሰው እስኪዘጋጅ ግባና ተጫወት። ትንሽ ቆይተን እንቀይርሃለን” አሉት።

ሙሉጌታም “ጫማዬን ስላወለቅሁ አልገባም። ጊዜ ስላለ የሚቀይረኝ ሰው አሁን አሟሙቆ ይግባ” ብሎ ሊናገር ፈለገና ይሄን ቢል ጭቅጭቅ ይነሳና ሌላ ትርጉም ይሰጠዋል ብሎ አሰልጣኙ ባይሰማም ያሰበውን ለራሱ አልጎመጎመና ዝም አለ። የሚቀይረው ሰው እንዳላዘጋጁ አውቋል። እዚያው መልበሻ ክፍል ሊቀር ፈለገ። የሚመጣውን ነገር አሰበ። አሰልጣኞቹ ሪፖርት ካደረጉበት ይቀጡታል። ከቀጡት ደግሞ ለቡና አይሰለፍም። ከዚህ በፊት በብሔራዊ ቡድን ምክንያት ተቀጥቶ ቡና ለዋንጫ ሲጫወት አምልጦታል። ዛሬ ግን መጫወት በፍፁም አልፈለገም። ከፈለጉ ይቅጡኝ አልገባም ብሎ ወሰነ። ግን ውሳኔው የተደመደመ አልነበረም።

ወንበሩ ላይ ቁጭ እንዳለ ሆዱን ማሻሸት ጀመረ። ዛሬ ምግቡም አልተስማማውም። ምሳ ላይ ትንሽ ፓስታና ስቴክ ነው የበላው። ሳይጨርስ ነበር ተነስቶ ወደ መኝታው የሄደው። ለጨዋታው እረፍት ለማድረግ ቢተኛም ከመገላበጥ በስተቀር እንቅልፍ አልነበረውም። ወደ ሰርቪስ አርፍዶ ነበር የደረሰው። በዚያ ላይ ጫማውን ረስቶ ከመኪና ወርዶ ነው ያመጣው። ወደ ሜዳ ሲመጣም አጠገቡ ካለው ተጫዋች ብዙም ሳያወራ ነበር የደረሰው። አሁን መልበሻ ክፍል ቁጭ ብሎ “ልግባ አልግባ” እያለ ከራሱ ጋር እየተሟገተ ነው። “ብገባ ይሻላል!” ብሎ ተነሳ እንደገና። “ይቅርብኝ” ብሎ ቁጭ አለ። ስሙ ሲጠራ ድንገት ብድግ ብሎ ቆመ። ሁሉም ተጫዋች ወጥቶ እሱ ብቻ ነበር መልበሻ ክፍል የቀረው። “አሰልጣኞቹ መጥተው ከመጨቅጨቃቸው በፊት ሜዳ ብሄድ ይሻላል” ብሎ በግማሽ ልቡ ወሰነ።

ያወለቀውን ጫማ አጠለቀና እየቀፈፈው በኮሪደሩ ላይ ቀስ እያለ ሄደ። በሀሳቡ ሜዳ ገብቶ መቆም ፈለገ። ነገር ግን ተመልካቹ ከርሱ የሚጠበቀው ነገር ስላለ መቆም እንደማይችል አውቆታል። አሰልጣኞቹም ቢሆኑ ሌላ ሰው እስክናዘጋጅ ግባ ያሉት ለማረጋጋት እንጂ እንደማያደርጉት ያውቃል። እነርሱ የፈሩት ተመልካቹን ነው።

ሙሉጌታ ተቀያሪ እስኪዘጋጅለት መጫወት ጀመረ። ዞር እያለ የሚያሟሙቅ ሰው በዐይኑ ይፈልጋል።

ነጋሽ ተክሊት ሙሉጌታን ቀይሮ እንዲገባ ተነግሮታል። ግን እያሟሟቀ አልነበረም። ቤንች ላይ ቁጭ ብሏል። ሙሉጌታ ግን ቀያሪውን እየጠበቀ ነው። ሰዎቹ ዝም ሲሉት አሞኛል ብሎ በራሱ ፍቃድ ሊወጣ ፈለገ። ይሄ ደግሞ አያስኬድም። ቅድም መልበሻ ክፍል ስለተጨቃጨቀ ታሞ ሳይሆን “ደብሮኛል” ባለው ጉዳይ ነው የወጣው ብለው ያስቀጡታል። ስሙም ሊበላሽ ይችላል ግን አሁን ቀያሪውን እየጠበቀ ነው። ዞር ብሎ ለአሰልጣኞቹ ምልክት ቢሰጥም “ቆይ” እያሉት ነው።

ሙሉጌታ ለምን መውጣት እንደፈለገ ሲናገር “አልደከምኩም። ደግሞም ጥሩ አቋም ላይ ነው ያለሁት። ባለኝ አቋም ሊቀይሩኝ አይችሉም። ለምን ቀይሩኝ ብዬ እንደተጨቃጨቅኩኝ አላውቅም። በወቅቱ ግን የጨዋታ ስሜቴን የሚያቀዘቅዝ ነገር በውስጤ ተፈጥሮ ነበር። ሆኖም ይሄንን ነገር መግለፅ አልቻልኩም። በእረፍት ጫማዬን ሳወልቅ ከውስጤ የሚታገለኝ አንድ ስሜት ነበር። ምን እንደሆነ ለራሴም አላውቀውም። ለመጀመርያ ጊዜ ነው በቃኝ ቀይሩኝ ያልኩት። ከዚያ በፊት እኔ ኳስ ሰልችቶኝ ወይም ሜዳ ላይ ደክሞኝ ቀይሩኝ ብዬ አላውቅም” በማለት ይናገራል።

ጨዋታው እንደተሟሟቀ ቀጥሏል። ሙሉጌታ እየቀፈፈው ይጫወታል። አሁንም ዞር እያለ የሚያሟሙቅ ተጫዋች በዐይኑ ይፈልጋል። ቢቀፈውም የማላዊን የግብ ክልል ማተራመሱን አልተወም።

አንድ ኳስ ወደፊት ሄደና ተበላሸ። የኛ አጥቂዎች ቶሎ ሲመለሱ ሙሉጌታ በፍጥነት ወደ ቦታው አልመጣም። እዚያው ቀረና ቀስ ብሎ መምጣት ጀመረ። ቀያሪውን ፍለጋ ወደ ውጭ ዕያየ በነበረበት ሰዓት ጌቱ ከበደ ከመሀል ያገኘውን ኳስ ራቅ ብሎ ለሚጠብቀው ለሙሉጌታ ወልደየስ ሰደደለት። ሙሉጌታ ኳሷን እንዳገኘ የሚቀበለው ሰው ሲፈልግ በማጣቱ እራሱ ለማግባት ወደ ጎሉ አቅጣጫ ገሰገሰ። ካፊያው ሜዳውን አርጥቦታል። ኳሱ እየነጠረ ስለመጣ እርጥበቱ እንዳያንሸራትተው ሙሉጌታ ሸፍኖ ይዞ ለመሄድ እያሰበ ነው። 3 ቁጥሩን አለፈው። ልጁን ሲያልፈው ኳሱ ትንሽ ረዝሞ ነበር። በዚያው ቅፅበት ከበረኛው ጋር ተገናኙ። መጀመርያ የታለፈው 3 ቁጥሩ ሙሉጌታ ላይ ፋውል ሰርቶ ለማስጣል እየታገለ ነው። ዳኛው ሊነፋ ፈለገ፤ ነገር ግን ኳሱ በሙሉጌታ ሥር ስለነበረ አድቫንቴጅ ጠብቆለታል።

ሙሉጌታ ከሚታገለው ተከላካይ ጋር ተሻሽቶ አለፈና ኳሷን አንድ ጊዜ ገፋ አደረጋት። ይቺ የገፋት ኳስ ሙሉጌታ በአዲስ አበባ ስታዲየም በኢንተርናሽናል ጌም ለመጨረሻ ጊዜ የነካት እንደምትሆን ማን ያውቅ ነበር? ከዚህች ኳስ በኋላ እግሩ በመሰበሩ ዝነኛው ሙሉጌታ የእግር ኳስ ታሪኩ ተቋጨ።

ስለ አደጋው ሙሉጌታ እንዲህ ይላል፡- “በረኛ ምንጊዜም ኳስ ይዘህ ስትመጣ ወይ በግራ አለበለዚያ በቀኝ ያመልጠኛል በሚል እጁን አስተካክሎ መወርወር ነው። ይሄ በረኛ ግን ኳሱን አይደለም የፈለገው። ልጁ ዋና በረኛ አይደለም። ተጠባባቂ ነው። ተጠባባቂ በረኛ ደግሞ ቋሚ ለመሆን ስለሚፈልግ ያልተጠበቀ ጎል ሲገባ በጣም ይናደዳል። ቅድም የገባበት ኳስ አበሳጭቶታል። እኔም ደጋግሜ ሞክሬበታለሁ። 3 ቁጥሩ እየገፋኝ እየታገለኝ ስለሆነ ባላንሴን ለማስተካከል እየሞከርኩ ነበር። እርሱን ሸፈንኩት እና ኳሱን ተቆጣጥሬ ለመምታት ፈለግሁ። የቀኝ እግሬን ተክዬ በግራ ለመምታት ተዘጋጀሁ። መረቡን ለመወዝወዝ ጠንካራ ሹት ለመምታት ስለፈለግሁ የቀኝ እግሬ በአየር ላይ እንዳለ በረኛው እየሮጠ መጥቶ እንደኮማንዲስት በሁለት እግሩ ጉልበቴን ረግጦ ጣለኝ። ያደረገው ብሎን ጫማ ነው። የጫማው ጡት ጉልበቴ ላይ ነው ያረፈው። ብሎኑ ሰርስሮኝ እየገባ ነው። ልጁ ደግሞ ሙሉ ኃይሉን ነው እኔ ላይ ያሳረፈው። እየመታኝ እያለ ኳሷን ትንሽ ነክቻት ነበር። እኔ ወድቄ ኳሷ በዝግታ ወደ ግብ እየሄደች ነበር”…ይላል።

ነገሮች እንግዲህ የሚጀምሩት ከዚህ ነው። ሙሉጌታ ወድቋል። ኳሷ ወደ ግብ እየሄደች ነው። ሙሉጌታን እየገፈተረ የነበረው 3 ቁጥሩ ሁለቱ እንደወደቁ ኳሷ እንዳትገባ ለማዳን ወደ ጎል እየሮጠ ነው። ተመልካቹ ዐይኑም ስሜቱም ኳሷ “ትገባለች ወይስ ተከላካዩ ያድናታል?” የሚለው ላይ ነበር። ተከላካዩ ኳሷ ከግቡ መስመር ላይ አድኗት ወደ ጨዋታው አስገባት። ኳሷ ባለመግባቷ ተመልካቹ ተበሳጨ። ተመልካቹ በኳሷ አካሄድ ሀሳቡ ስለተጠመደ በዚያች ቅፅበት የተፈጠረውን ነገር ልብ አላለም። ሙሉጌታ ተነስቶ ጨዋታውን እንዲቀጥል እየጠበቀ ነው። ካለበለዚያ ሌላ ኳስ ከመጣ ኦፍሳይድ ይሆናል። ከበረኛው ጋር ተገናኝቶ ተደጋጋሚ ኳስ በመሳቱ “እንዲህ ቢያረገው ኖሮ ይገባ ነበር” የሚለው አስተያየት እየተሰጠ ነው። እርሱ ግን ተኝቷል።

ጨዋታው ቀጠለ። በረኛው እንደማፈግፈግ እያለ ጎሉን ጥሎ ከሜዳ ለመውጣት ጉዞ እየጀመረ ነው። አሁንም ግን ጨዋታው እየቀጠለ ባለበት ጊዜ በትሪቡን የነበረው የመስመር ዳኛ ወደ ሜዳ ለመግባት እያኮበኮበ ነበር። ሰውዬው ጌታቸው ገብረማርያም ነው። ጌታቸው ገብረማርያም ሕጉ ባይፈቅድለትም ጨዋታው እየተካሄደ ሮጦ ወደ ሜዳ ገባ። ሙሉጌታ ጋር ደረሰ። ተመልካች አሁንም ዐይኑ ጨዋታው ላይ ነበር። የአቶ ጌታቸው ሜዳ መግባት ያልተለመደ በመሆኑ ተመልካቹ “ምንድነው እዚያ ጋር የተፈጠረው?” በሚል ወደዚያ ማዬት ጀመረ።

ጌታቸው ሙሉጌታን ጎንበስ ብሎ ተመለከተው። አይንቀሳቀስም። በወቅቱ ጌታቸው ምን ዕንዳየ ማንም ሰው አያውቅም። ጌታቸው ሙሉጌታን ካየው በኋላ ቀና ብሎ ባንዴራውን መሬት ላይ ጣለና እራሱን ይዞ እዬዬውን አቀለጠው። ተጫዋቾችም በጥድፊያ እየመጡ ዐይተው እራሳቸውን ይዘው ማልቀስ ሲጀምሩ ተመልካቹ “ሙሉጌታ ሞቷል” ብሎ አጥር እየዘለለ ወደ ሜዳ መግባት ጀመረ።

ነገሮች ሁሉ ተተረማመሱ። ወደ ሜዳ የገባው ሰው ያገኘውን የማላዊ ተጫዋች በንዴት መደብደብ ጀመረ። በረኛው ግን በቶሎ መልበሻ ክፍል ገብቷል። ሙሉጌታን ምን እንዳደረገው የሚያውቀው እርሱ በመሆኑ ሁለቱም እንደወደቁ በረኛው ቶሎ ተነስቶ እያፈገፈገ ሮጦ ማምለጥ ቻለ። ሌሎቹ የማላዊ ተጫዋቾች ግን የተፈጠረውን ነገር ስላላወቁ እዚያው ተያዙ።

እኔ ባለሁበት ቦታ የነበረ አንድ ተመልካች ፊት ለፊቱ ቆሎ የምትሸጥ ሴት ቆማ ነበር። ግርግር እንደተጀመረ የያዘችውን ትልቅ ሰሀን ቀማትና ቆሎውን ዘርግፎ “ወይኔ ወንድሜ” ብሎ በሰሃኑ ሊፈነክት አጥር ዘሎ ገባ። ፖሊስ ረብሻውን ለመቆጣጠር መሳርያ ወደ ሰማይ ቢተኩስም ሊያረጋጋ አልቻለም። ሙሉጌታ ይናገራል

“…በረኛው እንደመታኝ ዝርግፍ ብዬ ነው የወደቅሁት። ዳኛው ወደ ጎል የምትሄደው ኳስ ላይ ነበር ያተኮረው። ስለዚህ ፋውል ነው ብሎ ፊሽካ ባለመንፋቱ ጨዋታው ቀጥሏል። ጌታቸው መጥቶ ዐየኝ። እርሱ መሆኑን ያወቅሁት ፊልሙን ዐይቼ ካረጋገጥኩ በኋላ ነበር። ጌታቸው መጥቶ ራሱን ይዞ እየጮኸ ነበር። የኦሜድላ ወጌሻ ሙሉነህ ሮጦ ገባ እና እግሬን ይዞ ሲወዘውዘኝ ይሰማኛል ግን በድን ስለሆንኩኝ መጮኽ አቃተኝ። እግሬ ቦታው ላይ ያለ አልመሰለኝም። ተቆርጦ እንደሄደ ነው የገመትኩት። ስለደነዘዝኩኝ ምንም የህመም ስሜት  አልነበረኝም። ሰውነቴን ሞቆኛል፤ አልቦኛል እንደገናም ሌላ ላብ በሰውነቴ ላይ ሲሄድ ይሰማኛል፤ በኋላ እያለቀሱ ተሸክመውኝ ወደ መልበሻ ክፍል ወሰዱኝ። እነዚህ ሁሉ ሲሆኑ ብዥታ እንጂ ምንም አላውቅም በጭንቅላቴ ስለኳሱ እያሰብኩ ነበር። በረኛውን አልፋ እንደሄደች አስታውሳለሁ። ተደጋጋሚ ኳስ ስለሳትኩ ተመልካቹ ቅር ቢሰኝም “አይዞህ ታገባለህ” እያለ ያበረታታኝ ስለነበር ይህች ብትገባ እክሳችኋለሁ እያልኩ እያሰብኩ ነበር። ግን መግባቷን ማረጋገጥ አልቻልኩም። በወደቅሁበት ሰዎች ከበውኝ እንደነበር አስታውሳለሁ። የመሳርያ ተኩስ እሰማለሁ። ኳስ ሜዳ እንደነበርኩ ትዝ ይለኛል። ታዲያ ተኩሱ ምንድነው? ብዬ ግራ ተጋብቻለሁ። የተፈጠረውን የሚነግረኝ አጣሁ። በመሳርያው ተኩስ መሃል ህዝቡ ሲንጫጫ ጎሏ በመግባቷ ደስታቸውን በጩኸት እየገለፁ እንደነበር ነው የገመትኩት። ሆኖም ነገሮች ስለተደበላለቁብኝ የተጨበጠ ነገር ማወቅ አቃተኝ። ወደ መልበሻ ክፍል እንደወሰዱኝ ዶክተር አያሌው ህክምና አደረገልኝ እና ወደ ጦር ኃይሎች ወሰዱኝ። ጉልበቴ ወደ ቦታው ተመልሷል። ነገር ግን ሊጋሜንቱ በሙሉ ተበጥሷል። ምሽቱን ጉልበቴ እያበጠ ሄደ። እኔም እራሴን ማወቅ ስጀምር ጉዳቱን አወቅሁና አለቀስኩ። ያስለቀሰኝ አደጋው ከኳስ እንድለይ የሚያረገኝ እንደሆነ ስለገመትኩ ነው። ማን እንደሆነ ባላውቅም ከከበቡኝ ሰዎች ውስጥ “ጉዳቱ እንግዲህ ኳስ አያጫውተውም” ብሎ ሲናገር በመስማቴም ነበር። በነጋታው ህመሙ እየባሰብኝ በመሄዱ ወደ ምስራቅ ጀርመን ለከፍተኛ ህክምና ሄድኩ። እዚያ እንደደረስኩ ሦስት ሰዓት የፈጀ ቀዶ ጥገና ተደረገልኝ። ጉዳቱ ከፍተኛ በመሆኑ ሀኪሞች ወደ ኳስ መመለስ እንደሌለብኝ ነገሩኝ እዚያ ሁለት ወር ቆይቼ ተመለስኩ” ይላል።

ሙሉጌታ ዱላ ቻይ በመሆኑ ተከላካዮች ጠንካራነቱን ለመግለጽ ወይራ በሚል ስም ነበር የሚጠሩት። የማላዊ በረኛ በሕገ-ወጥ አጨዋወት በተንኮል ሰብሮ ከኳስ አሰናበተው። የማላዊ አንዳንድ ተጫዋቾች ከፍተኛ ድብደባ ደርሶባቸው ምሽት ላይ ኢትዮጵያ ሆቴል የተዘጋጀላቸውን የእራት ግብዣ ትተው፣ ኤርፖርት አድረው፣ አርብ ሊሄዱ ያቀዱትን ሰርዘው፣ ምሽቱን በናይሮቢ አድርገው ወደ ሀገራቸው ገቡ። ፊፋም የተፈጠረውን ረብሻ ሰምቶ እንዲሁም ማላዊ “ተደብድቤያለሁ” ያለውን ቅሬታ ተመልክቶ የአዲስ አበባ ስታዲምን ለአንድ ዓመት ቀጣ። በነገራችን ላይ በረኛው ከዓስር ዓመት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ከመሞቱ በፊት በሀገሩ ሚዲያ ሙሉጌታ ላይ ላደረሰው ጥፋት ይቅርታ ጠይቋል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top