ጣዕሞት

የፈጠራ ባለሙያዎቹ ርብርብ

የዓለም ስጋት የሆነው ኮሮና ቫይረስ ሐገራችን ውስጥ መከሰቱ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያዊያን የፈጠራ ሰዎች ከመከላከል እስከ ማዳን ያለውን ሂደት ለማገዝ የየግል ጥረት አድርገዋል። ከነዚህ መካከል ወጣት ኢንጅነር ሳሮን ይገኝበታል።

 ወጣቱ የጤና ባለሙያዎች በህመሙ የተያዙ ሰዎችን በሚረዱበት ጊዜ ቫይረሱ እንዳይተላለፍባቸው የሚያደርግ የፕላስቲክ ልዩ ቱታ ሰርቷል። በምስሉ ላይ የሚታየው የሀኪሞች መገልገያ ጋዋን ከውጭ ከሚመጣበት ዋጋ 1/4ኛ ቅናሽ ያመረተው ወጣቱ የምርቱ የጥራት ደረጃ ፍተሻ በፍጥነት ተጠናቅቆ ወደ ምርት መግባቱ የበርካታ ሐኪሞችን ሕይወት እንደሚታደግ እና ልብሱን ከውጭ ለማምጣት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስቀር ያምናል።

ሌላው ወጣት የፈጠራ ባለሙያ ታምሩ ከሳ ይባላል ‹‹አንድም ሰው እጅን ባለመታጠብ ምክንያት በኮሮና እንዳይያዝ›› በሚል መርህ ተነስቶ የሰራው የጎዳና ላይ የእድ መታጠቢያ ነው። ከአዕምሮ ንብረት ጥበቃ የግልጋሎት ሰርተፍኬት የተቀበለው አዲሱ ‹‹መላ የእጅ መታጠቢያ›› የአስተጣጠብ ሂደቶችን የሚያሳዩ መመሪያዎችን በግልጽ በሚታይ ቦታ ላይ የሚያሳይ አና ለማንቀሳቀስ ምቹ የሆነ ነው። አንድ ሺህ ሊትር የሚይዝ የውሃ ታንከር ተገጥሞለታል። ከእጥበት በኋላ የሚኖረውን ፍሳሽ የሚያጠራቅምበት ታንከርም አለው።  ለአንድ ሰው የአንድ ደቂቃ የመታጠቢያ ጊዜ እና ግማሽ ሊትር ውሃ የሚመድብ ሲሆን በተገጠመለት ሴንሰር አማካኝነት የሰዎችን እንቅስቃሴ በመመልከት ቧንቧውን በራሱ የሚከፍት እና የሚዘጋ ነው። በሌሎች ቦታዎች  የሚስተዋለውን የፈሳሽ ሳሙናዎች በፍጥነት ማለቅ እና የደረቅ ሳሙናዎች መጥፋት መከላከል በሚያስችል መልኩ የተሰናዳ ሲሆን በሰዓት እስከ 1200 ሰው የማስተናገድ አቅም አለው ተብሏል።

ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ ከዚህ በፊትም ዘመናዊ የአስፋልት መጥረጊያ፣ ድምጽ እና ጽሑፍ የሚያስተናግድ ዘመናዊ የአስተያየት መቀበያ፣ የአየር ሁኔታውን ተገንዝቦ አገልግሎት የሚሰጥ እቶማክ የአትክልት ማጠጫ፣… ሰርቶ ለማኅበረቡ አቅርቧል።

በኮሮና ሕመም ለተያዙ ወገኖች የመተንፈሻ ማገዣ ማሽን ቬንትሌተር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ያሳወቀው ደግሞ ወጣት ካሚል ይባላል። የ19 ዓመቱ ወጣት ከዚህ በፊት ያስመዘገባቸው 28 የፈጠራ ስራዎች አሉት። ከነዚህ መካከል 13 ያህሉ ዓለም አቀፍ ፓተንት ያገኘባቸው ናቸው። ለመስራት ከተዘጋጀው በተጨማሪ ስራ ላይ የዋለ የፈጠራ ሥራም አለው። መክፈት እና መዝጋት የማያስፈልገው፣ በራሱ ሳሙና ጨምሮ እጅን የሚያስታጥበው መሳሪያ በወልቂጤ ሪፈራል ሆስፒታል እና በከተማዋ እየተሰራጨ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። አዲሱን የመተንፈሻ መሳሪያ በብዛት ለማምረት ሁለት ትልልቅ ማሽኖች እንደሚያስፈልጉ የሚናገረው ወጣቱ ድጋፍ የሚያደርግለት ሰው ካገኘ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰርቶ ማስረከብ እንደሚችል ተናግሯል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top