ፍልስፍና

ኮሮና ያንኳኳቸው በሮች

ኮሮና ያንኳኳቸው በሮች

ስለ ኮቪድ19 አለመጻፍ፣ አለመናገር አይቻልም። የዘመናችን ትልቁ ፈተና፣ በሰው ልጆች ሁሉ ላይ የተደቀነ የህልውና ተግዳሮት ነውና ዝም የሚባልለት ጉዳይ አይደለም። የጤና ችግር ብቻ ስላልሆነ ይህንን አድርጉ፣ ይህንን አታድርጉ ተብሎ በህክምና ባለሙያዎች ምክር እና እርዳታ ብቻ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም። የፖለቲካ መሪዎች ኃላፊነት ብቻ ስላልሆን በሕግጋት፣ በተእዛዛት የሚዳኝ ጉዳይም አይደለም። እንዲሁ በታሪክ ሂደት ውስጥ በዛሬው ዘመን ላይ የሚገኙ የሰው ልጆች ሁሉ ጉዳይ፣ ጣጣ ነውና ቀልብን ሰብሰብ አድርጎ፣ በአስተንትኖት እና በማስተባቃት ሊተኮርበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ሌላው ቀርቶ “ማኅበራዊ እርቀት” (Social distancing) የሚለው የቃላት ተቃርኖ ስነ ልቡናዊ እና የረዥም ጊዜ ዳፋው እንኳ ብዙ ሊያስብል ይችላል።

ለመሆኑ ኮሮና ያልነካካቸው፣ የማይነካካቸው ጉዳዮች ይኖሩ ይሆን? በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ፣ ካለፍናቸው መንገዶች ድባቅ ያልመታቸው የትኞቹ ናቸው? የኮሮና ከባድ ክንድ ወደፊት ልናልፍባቸው ካቀድናቸው አቅጣጫዎች ጥርቅም ሊያደርግ፣ ልንወጣባቸው ያሰብናቸውን የከፍታ ማማዎች ሊያፈራርስ ያልቃጣቸው፣ ተስፋችንን ሊያደበዝዝ ቀልባችንን ገፎ የቋመጥንባቸውን ምኞቶች ከሽ ሊያደርግ ቀስቱን ያልወረወረባቸ የትኞቹ ናቸው?

በዚህ ጽሑፍ ወስጥ በታሪክ፣ በፍልስፍና፣ በሳይንስ፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በፖለቲካ፣ በሥነ ልቡና፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበረሰብ፣ በሞራል እንዲሁም በሙያዊ ጉዳዮች ውስጥ የኮሮና ጉዳይ ያስተዛዘበንን፣ ያስታወሰንን፣ ያሳሰበንን፣ ያስደሰተንን ነገሮች እያነሳን፣ ያንኳኳቸውን በሮች እየጠቃቀስን እንነጋገራለን። ጽሑፉን እያነበብን ኮሮናን እንከላከል። ቀጣዩን ገጽ ለመግለጥ ጣተዎትን ምላሰዎን እንዳያስነኩ ብሎ ማስታወስ ያስፈልግ ይሆን?

ፈጣሪ ተቆጣ ወይስ ተፈጥሮ አኮረፈች?

እስኪ ቧልት ከሚመስሉት እንጀምር። አንዳንድ ሰዎች የኮሮናን ጉዳይ ከፈጣሪ ቁጣ ጋር ሲያይዙት ይስተዋላል። የኮሮናን መከሰት እና ወረርሽኝ፣ እያደረሰ ካለው ጥፋት አንጻር የሰው ልጅ ለፈጣሪ ተገዥ ባለመሆኑ ፈጣሪ ተቆጥቶ ሊቀጣውና ሊያስተምረው አስቦ ነው ኮሮናን የላከበት የሚለው አስተሳሰብ በርካቶች የሚያራምዱት ነው። በተለይ በኛ ማኅበረሰብ ዘንድ ይህ ነገር ከፍ ያለ ቦታ የያዘ ይመስላል። እንግዲህ እንደ አማኝ ሆነን ካየነው ጉዳዩ ቅንጣት እውነት የያዘ ይመስላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፈጣሪ ተቆጥቶ የሰው ልጅን የቀጣባቸው ታሪኮች ተመዝግበዋል። የኖህ ጥፋት፣ የሰዶምና ገሞራ ጥፋት፣ የግብጾች ቅጣት፣ የእስራኤላውያን በሲና በረሃ ቅጣት ወዘተ ማሳያዎች ናቸው። እነዚያን ታሪኮች በዘመናቸው አስተሳሰብ ሚዛን ለክተን ተዓማኒነታቸውን፣ የፈጣሪን ምክንያት መመርመር ይቻላል። ይህ ለሥነ መለኮት ሰዎች የተተወ ጥናት ነው። ኮሮናን ከፈጣሪ ቁጣ ጋር ብቻ ማያያዝ ግን ጉዳቱ ትልቅ ነው። ባንድ በኩል ፈጣሪን ጨካኝ አድርጎ መሳል፣ የፈጣሪን ባህርይ በሰዋዊ ባህርይ ልኬት ማስቀመጥ ሲሆን ይህም መፍትሔው ሃይምኖታዊ ብቻ ነው ወደሚል ምክረ ሐሳብ ይወስደናል። ምንም እንኳን እምነት ላላቸው ሰዎች እንደየ እምነታቸው ይፈጸምላቸው ዘንድ የታወቀ ቢሆንም ይህ ሃይማኖታዊ መፍትሔ ብቻ የማበረታታት አዝማሚያ ሁሉን አቀፍ አይሆንም። በሌላ በኩል የሰው ልጆች ፈጣሪ በሰጣቸው የማሰብ እና የመመራመር ጸጋ ተጠቅመው፣ በኅሊናቸው ከፍተኛ የማወቅ ተፈጥሮ አማካኝነት የደረሱባቸውን የሳይንስ፣ የህክምና፣ የማሰላሰል ወዘተ ነገሮች ዋጋ የሚያሳጡ ናቸው።

በዚህ ረገድ የባህል ሃኪሞችም ሆኑ ዘመናዊ የህክምናው ቴክኖሎጂ ያስገኛቸውን ትሩፋቶች በሙሉ ልብ እንዳንቀበል ደንቃራ ይሆንብናል። በአምሳሉ የፈጠረውን ሰው ማናናቅ ፈጣሪን ማስቆጣት እንዳይሆንብን ያሰጋል። ለዚህም ይመስላል የሃይማኖት መሪዎች “ወደ ፈጣሪም እየጸለይን መንግሥት እና የህክምና ባለሙያዎች የሚሰጡንን መመሪያዎች እነከተል” የሚሉ ምክሮችን የሚያስተላልፉት። “አላህንም እመን ግመልህንም እሰር” እንዲሉ…

የኮሮና ጉዳይ ያንኳኳው አንዱ በር የአብያተ እምነቶችን በር ነው። አንዳንዶቹ ምክሮች ተሰብስቦ ፈጣሪን ከማምለክ እና አንዳንድ ሃይማኖታዊ ዶግማና ቀኖና ለመከወን አመቺ አይሆኑም። ኮሮና ለአማንያንና የእምነት መሪዎች አንዱ ከባድ ፈተና ነው።  

ሁለተኛው መላምት ደግሞ ምናልባትም የሰው ልጆች ተፈጥሮን ከመጠን በላይ በመበዝበዛቸው ተፈጥሮ አኩርፋ እንዳይሆን? የሚለው ነው። ይህ አስተሳሰብ ከየት ይመነጫል? አንዳንድ አደገኛ በሽታዎች፣ የንፋስ፣ የጎርፍ፣ የማዕበል እንዲሁም የእሳተ ጎመራ አደጋዎች ምንጫቸው የሰው ልጅ ተፈጥሮን ከሚገባው በላይ በመበዝበዙ ነው ወደሚል መላምት ያመራል። ኤች አይ ቪ ኤድስ፣ ኮሮና፣ ኢቦላ መነሻቸው እንስሳት ናቸው። ምናልባትም የሰው ልጅ ከእንስሳት ጋር ባለው ያልተገባ ግንኙነት እንስሳቱ ጦርነት ከፍተውበት ይሆን? ላይቢንዝ የተባለ ፈላስፋ ከሰው ልጅ አቅም በላይ ስለሆኑ የተፈጥሮ ክስተቶች እና መቅሰፍቶች ሲያትት “በተፈጥሮ ሂደት ውስጥ ተፈጥሮ ራሷን የምታስተካክልበት፣ የሚቀጡትን የምትቀጣበት፣ የሚሸለሙትን የምትሸልምበት የራሷ መንገድ አላት” ይላል።

ተፈጥሮ አኩርፋ ነው የሚለው መላምት ከዓለም ሙቀት መጨመር ጋር፣ ከኢንዳስትሪ ከሚመጣ ብክለት የሚዘንብ መርዛማ ዝናብ፣ ከመብረቅ ጋር በተያያዘ የሚከሰት መቅሰፍት፣ የአድባር ቁጣ ወዘተ ይያያዛል። እንደዚህ ዓይነቶቹ አስተሳሰቦች ከሳይንሳዊ ይልቅ ማኅበረሰባዊ እውቀት እና እምነት ላይ ይመሰረታሉ። ለምሳሌ ለአንዳንድ አፍሪካውያን ማኅበረሰቦች የተፈጥሮ ጫካዎች የአያት ቅድመ አያቶች መናፍስት ማረፊያዎች ናቸው። ጫካውን መመንጠር ወይም ዛፍ መቁረጥ መናፍስቱን ያስቆጣል ብለው ያምናሉ። በቅርቡ ቢቢሲ በሰራው አንድ ዶክመንተሪ የሴኔጋል ሰዎችን ቃለ መጠይቅ ሲያደርግ “ይህ ደን የአባቶቻችን መንፈስ ማረፊያ ነው፤ ጫካው ወይም ድኑ ከሌለ ዝናብ አይዘንብም” የሚሉ አስተያየቶችን ሰምተናል። ተመሳሳይ አመለካከቶች በኢትዮጵያም እንደ አኙዋክ እና ቦረና ኦሮሞ ማኅበረሰቦች ዘንድ እንዳለ ጥናቶች ያሳያሉ። እንደዚህ ዓይነት አስተሳሰቦች ሰው ተገቢውን እንክብካቤና ክብር ካልሰጣት ተፈጥሮ ራሷን ለመከላከል አስባ እና አቅዳ ከሰው ልጆች ጋር ጦርነት እንደምትገጥም የሚሞግት አዝማሚያ ነው። አጥፊዎቹንም በመናፍስቱ ቁጣ ወይም ዝናብ በመከልከል በድርቅና ረሃብ ትቀጣቸዋለች። ከዚህ ጋር በተያያዘ የተፈጥሮ ቁጣ የሰው ልጅ ከሌላው ተፈጥሮ ጋር በሚያደርገው መስተጋብር በሙሉ እውቀት ላይ የተመሰረተ ካለመሆኑ የመነጨ ነው የሚል ሙግትም አለ። የሚበላውን ከማይበላው፣ የሚነካውን ከማይነካው፣ መርዛማውን ከመድኃኒቱ አለመለየት የራሱ ጉዳት አለው። የሰው ልጅ ከሌላው ተፈጥሮ ጋር ያለውን ግንኙነት በሰለጠነ እና የጋርዮሽ ጥቅም (Enlightened self interest) ላይ የተመሰረተ እንዲያደርግ ለአካባቢ ተቆርቋሪ የሆኑ ሰዎች ይመክራሉ። ካልሆነ ተፈጥሮ ታኮርፍና  በሰው ልጆች ላይ የበቀል እርምጃ ትወስዳለች (ጸጋዋን ለሰው ልጅ ትነፍጋለች፣ ወይም ያላት ጸጋ ያልቃል፣ ወይም ጦሯን ትመዛለች)። ያም ሆነ ይህ እንደዚህ ዓይነቶቹ ገጠመኞች የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር የሚያደርገው ግንኙነት በእውቀት እና በምግባር ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል የሚል እንድምታ አላቸው። ወይም ሰው ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲያስብበት የማንቂያ ደውል ነው። ለመሆኑ ሰውስ የተፈጥሮ አካል አይደለም ወይ ሰውና ተፈጥሮ የሚል ክፍፍል ውስጥ የገባነው?

ሰው መሆንን ታዘብ ወይስ አወቅ?

የኮሮና ጉዳይ የሚያስታውሰን አንድ የፍልስፍና ጉዳይ አለ። በፖለቲካ ፈላስፎች ዘንድ አገር ወይም የፖለቲካ ማኅበር የሚመሰርተው ሰው ምን ስለሆነ ነው? የሚል ጥያቄ አለ። እንደ ጆህን ሎክ እና ቶማስ ሆበስ ያሉ ፈላስፎች የሰው ልጆች ሕግና መንግሥት በሌለበት ዘመን ለሕይወታቸው መቀጠል ዋስትና አይኖራቸውም። በተለይ ሆበስ የሰው ልጅ ራስ ወዳድ እና ብቸኛ ከመሆኑ የተነሳ በመንግሥት አልባ ጊዜ አንዱ አንዱን በጥርጣሬ ይመለከታል። ጉልበት ያላቸው ሳይቀሩ ጉልበት የሌላቸውን ይፈሯቸዋል፣ ተደብቀው ውይም ተባብረው ሊያጠቋቸው ይችላሉና። ለዚህም የሁሉን ደህንነት የሚያስጠብቅ የፖለቲካ መሪ ያቋቁማሉ። ለሎክ ይህ የፖለቲካ አካል እያንዳንዳቸው ግለሰቦች በተፈጥሮ ከተለገሳቸው ያልተገደበ መብት አዋጥተው ጉልበት ይሰጡታል። ያኔ ሁሉም ይገዙለታል፤ እርሱም የሁሉን መብት በእኩልነት ያስከብራል።

የኮረና ጉዳይ እና የሚሰጡን ምክሮች ይህንን ዘመን ያስታውሱናል። ምክሮቹም ማንም በበሽታው ላለመያዙ ማረጋገጫ ስለሌለን እያንዳንዳችን ተራርቀን እንቀመጥ የሚሉ ናቸው። የሰው ልጆች ሁሉ ለሌሎች የሰው ልጆች እንደ አደጋ ይታያሉ። በሕግ እስካልተረጋገጠ ድረስ ማንኛውም ሰው ከወልጀል ነጻ ነው (Presumption of Innocence) የሚለው የሕግ ብያኔ በዚህ በኮሮና ዘመን አይሰራም። እንዲያውም እየሆነ ያለው ተቃራኒው ነው። ይህም የሰው ልጆች ብያኔያቸው ሁሉ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል፣ አንዱ ሌላውን ሊረዳው ይገባል የሚለው የበበጎነት የሥነ ምግባር ምክር ስለ ራስ፣ ስለ ሌላው ደህንነት፣ ስለ ወዳጅ ሲባል መራራቅ ያስፈልጋል ወደሚል ሌላ የበጎነት፣ ግን ተቃራኒ ምክር ተቀየረ። አንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ የሰውን ልጅ ሌላኛው ገጽታ ያሳያሉ። ሰዎች ካስነጠሳቸው፣ ከሳሉ ወይም የተለየ ምልክት ካሳዩ እንደ ጠላት ይፈረጃሉ።

በኛው አገር ነጋዴዎች እና ሸማቾች ደግሞ የከፋ ቀን ይመጣ ይሆናል በሚል በስግብግብነት ነገሮችን ካለ ዋጋቸው እና ለግለሰቦች ወይም ለቤተሰብ ፍጆታ ከሚያስፈልገው መጠን በላይ ማግበስበሱ ሰው ለሌሎች የሞራል ግዴታ ያለው ሳይሆን ለራሱ ብቻ የሚያስብ ያስመስለዋል። እንደገና ደግሞ የሌሎች ሰዎች ደግነት በሰው ልጆች ተስፋ እንዳንቆርጥ ያደርገናል። ራሳቸውን ስለሌሎች አሳልፈው የሚሰጡ ባለሙያዎች፣ ንብረታቸውን በልግስና የሚቸሩ ግለሰቦች ስናይ በክፉ ዘመን ውስጥ የሰዎች ደግነት ከቦታዋ፣ ወይም ከመንበሯ እንዳልወረደች እንረዳለን።

ሌላውና አስገራሚው ነገር ደግሞ የሰው ልጆች የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነ ጥያቄ ውስጥ መክተቱ ነው። እንደ ጥንት የግሪክ ዘመን ፈላስፎች የሰውልጅ የሚኳትነው ደስታን ለማግኘት ነው። ደስታን ማግኘት የሁሉም ዓላማ ቢሆንም በምን መልኩ ትገኛለች የሚለው ላይ ግን ሁሉም የሰው ልጆች የሚስማሙበት ነገር አይመስልም። በፍርሃት፣ በተስፋ መቁረጥ፣ ወይም የቅርቦቻቸውን በማጣታቸው ሐዘን ወኔያቸውን አጥተው ራሳቸውን የሚያጠፉትን ስናይ የሕይወት ግብ  ምንድን ነች? ያስብላል። እነዚህ ጉዳዮች የሚያሳዩን ጥቁምታ ሰው የመሆንን ምስጢር፣ የሕይወት ትርጉሙ ዛሬም ድረስ በቅጡ ያልታወቀ፣ ለወደፊቱም ትኩረትን የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ነው። የኮረና ጉዳይ ያላንኳኳቸው የግብረ ገብ፣ የማኅበራዊ ደህንንነት፣ የሰው ልጆች ዝንቅ ባህርያት፣ የሥነ እውቀት እና የፍረጃ ግንኙነት፣ ባጠቃላይ ሰው የመሆን ጓዳ ጎድጓዳዎች እና የሕይወት ምስጢር ሾላ በድፍንነት የትኞቹ ናቸው?     

ሳይንስ ሆይ ጉድ ሰራሽን ወይስ ባንቺው እንታመን?

ከዚህ በፊት በታተመ የታዛ መጽሔት ላይ “ሰው የአለመሆን ጉዞ” በሚል ርእስ በቀረበ ጽሑፍ ውስጥ እንዲህ የሚል አንቀጽ አለ፦ “በዚህ ረገድ የሳይንስ ተመራማሪዎች ራሳቸው የሚፈሩት ነገር ይህ ልቅ የሆነ የሳይንስ ግስጋሴ አንድ ቀን ከሳይንቲስቱ ቁጥጥር ውጭ ይሆን እና እንደ ኒኩለር ቦምብ የሚያወድም ኃይል ሊገጥመን ይችላል ይላሉ። ለምሳሌ ፖላክ የተባለ ሳይንቲስት ለአንድ ሪፖርተር በሰጠው ቃለ መጠይቅ የባዮቴክኖሎጂ ምርምር ላይ አንዳች ስህተት ቢፈጠር የሚያስከትለውን ጥፋት ሲያብራራ በቅድመ ሂሮሽማ ዘመን ላይ እንዳንሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል ይለናል። ለምሳሌ ስለ ካንሰር ስርጭት የሚደረግ በላቦራቶሪ ሙከራ ላይ ያለው እንስሳ ሰው ቢሆን እና የሆነ ስህተት ቢፈጸም መቆጣጠር የማይቻል የካንሰር መስፋፋት ቢከሰት ሄሮሽማን እና ናጋሳኪን እንዳጠፋ ኒኩለር ቦምብ የዛሬውን የሰው ልጅ ሊያጠፋ የሚችል ኃይል አለው ይላል። በዚህም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ከላባራቶሪ ወጥቶ ተግባራዊውን የሰው ልጅ ሕይወት በሚያንኳኳበት ጊዜ የሚያመጣው ጣጣ ከባድ ነው። ምክንያቱም ከበስተጀርባው የሚዘውረው የፖለቲካ እና የገንዘብ ድጎማ ሳይንስ ራሱን የቻለ ነጻነት የለውም። በዚያ ላይ ሳይንስ ራሱን የቻለ ቢዝነስ እየሆነ ነው። ሳይንስ ከችግር ፈቺነት ወደ የንግድ እና የፖለቲካ ውድድር ከገባ ደግሞ የሰውነትን ጉዞ በእጅጉ ሊጎዳው ይችላል።”

ይህ አነጋገር ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮችን ያስታውሰናል። የመጀመሪያው በግልጽ እንደተቀመጠው የሳይንስ ልቅነት እና ሁሉን እችላለሁ ማለት አንዳች ስህተት ቢፈጠር ከሰው ልጆች ቁጥጥር ውጭ መሆኑ ነው። ሁለተኛው እና ያሁኑን የኮሮና ሁኔታ ስንታዘብ ደግሞ አንዳንድ ሰዎችን ጥርጣሬ ሚዛን የሚደፋበት ነው። ይኸውም መጀምሪያ ኮሮና በቻይና መከሰቱ ሲሰማ በቴክኖሎጂ ጦርነት ጋር ያገናኙት ሰዎች ነበሩ። ምንም እንኳ በጥናት የተረጋገጠ ይህ ነው የሚባል ተጠቃሽ ድምዳሜ ባይገኝም እዚህም እዚያም የሚሰሙ ነገሮች በሙሉ ከአሻጥር ትርጓሜ (Conspiracy Theory) ጋር የሚቀራረቡ ይገኙበታል። ቀድመው የታተሙ መጻሕፍት፣ ጥናታዊ ጽሑፎች፣ ቀድሞ ነገሩን ያስጠነቀቀ ቻይናዊ ሐኪም ጉዳይ እና ፊልሞችን (ለምሳሌ በ2011? እ.አ.አ የወጣ Contagion የተሰኘ ፊልም) እየጠቀሱ ኮሮና ሰው ሰራሽ የባዮ ቴክኖሎጂ ውጤት ነው ወደሚል ድምዳሜ ያዘነብላሉ።

እነዚህ ጉዳዮች የሳይንስን ተቃርኖዎች የሚያሳዩ ናቸው። ሳይንስ ከስኬቷ በስተጀርባ ፕሮፓጋዳዋ እንደሚያይል የሚያሳየን ደግሞ እንደዚህ ዓይነት በሽታዎች እና ፈጣን ምላሽ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ሲያጋጥሙ በዚህ በሰለጠነው የሰው ልጅ የእድገት ደረጃ ሳይንስ መታደግ አለመቻሏ ሲታይ ነው። ይህ ሐተታ ስለ ሳይንስ አቅመቢስነት ለመሞገት አይደለም። ሳይንስ ትልቅ አስተዋጽኦዎችን እያደረገች እንደሆነ፣ በሕክምናው ቴኮሎጂ በርካታ ስኬቶች እንደተመዘገቡ ሳንገነዘብ ቀርተን አይደለም። ነገር ግን ሳይንስቶች የኮረናን ጉዳይ መቆጣጠር ካለመቻላቸውም በላይ እንደ አሜሪካ ያሉ የምድራችን ልዕለ ኃያላን መንግሥታት ሳይቀሩ ሲፈተኑ ሲታይ በሳይንስ ላይ ካለን እምነት አንዳች የጥርጣሬ መንፈስ ውልብ ይልብናል።

በተለይ ደግሞ የሰለጠነው ዓለም የህክምና የሳይንስ ይህ ነው የሚባል የክትባት እና የዘላቂ መፍትሄ አማራጭ አለማምጣቱ፤ ቢያመጣም በሳይንቲስቶቹ፣ በባለ ሃብቶቹና በፖለቲከኞቹ መካከል ያለ ስውር ትስስር በተፈለገው ፍጥነት ለዓለም የሚደርስበት ሰንሰለት ሲታሰብ ሳይንስን በሙሉ ልብ እንዳንተማመንባት ያደርገናል። መቼስ ፈተናው የሰው ልጆች ሁሉም አይደል? ለመፍትሄውም የሰው ልጆች ሁሉ ለዘመናት ያካበቷቸውን የሕክምና ጥበባት ውርሶቻቸውን ከተደበቁበት ትቢያቸውን እያራገፉ ቢመረምሩስ? የሚል ጥሪ መሰል ማቅረባችን አልቀረም። ያም ሆነ ይህ የኮሮና ጉዳይ የሳይንስን መስኮት አንኳኩቶ “ሳይንስ ሆይ ክንድሽ የት አለ?” እያላት ያለ ይመስለናል። ዞረን ዞረን ወደ “ኋላ ቀር” (Primitive) የመከላከል ዘዴ መመለሳችን እኛም ሳይንስ ሆይ እንዲህ ታደርጊን? ሳያስብለን አልቀረም።    

ተቀምጠን እየሰቀልነው ይሆን?

የሰው ልጅ ከማን ነው መማር ያለበት? “ሰው ከሁለት ነገር ይማራል አንድም በሳር ‘ሀ’ ብሎ አንድም ከአሳር ‘ዋ!’ ብሎ” ይላሉ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን። በዚህ ረገድ የሰው ልጆች መዘናጋት ምን ያክል ዋጋ እያስከፈላቸው እንዳለ ከጣልያን እና ከአሜሪካ በላይ ምስክር የለም። በቴክኖሎጂ ምጥቀት፣ በኢኮኖሚ አቅም ካየነው ከነ ቻይና ወዲያ ላሳር ነው። የበሽታው አደገኝነት እየተስተዋለ ያለው ደግሞ በነዚህ ኃያላን ላይ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ የዓለም ማኅበረሰብ የገባው ዘግይቶ ነው። የኛው ማኅበረሰብ ደግሞ አሁንም የገባው አይመስልም። ይህንን ጽሑፍ በማዘጋጅበት ወቅት በኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙኃን እየተነገረ የሚገኘው የሰዎች ቸልተኛ እንቅስሳሴ ለዚህ ምስክር ነው።

ኮሮና ካሳየን አንዱ ነገር የሀገራት የጤና ፖሊሲዎችን ከቃል፣ ከወረቀት ባለፈ ወደ ምድር የመውረዳቸውን ጉዳይ እንድንፈትሽ ነው። ለምሳሌ የኢትዮጵያ የጤና ፖሊሲ በቅድሚያ መከላከል ላይ ያተኮረ እንደነበረ ለበርካታ ዓመታት ሲነገር የኖረ ጉዳይ ነው። መንግሥት ይህን ይበል እንጂ በህዝቡ ልቡና ውስጥ እንዳልሰረጸ ከዚህ በላይ ማሳያ የለም። ቀድሞ መከላከል ማለት አቅም በፈቀደ  ከማንኛው በሽታ ሊያስይዝ የሚችልን ነገር ራስን እና አካባቢን መጠበቅ ነው። አንድ ፖሊሲ ጥሩ ነው የሚባለው በሚመለከታቸው አካላት ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ በቀላሉ ተግባራዊ በሚሆንበት ልክ ነው። የኢትዮጵያ የጤና ፖሊሲ ከህዝቡ ጋር ባይተዋር ስለነበረ ይሆን እንዴ ኮሮናን ያክል አስጊ ነገር ሲያጋጥም ህዝቡ አልሰማ ያለው?

መጀመሪያ በቻይና ላይ ሲከሰት ዓለም ልብ ሳይለው ሲሳለቅበት ነበር። ኋላ ላይ ወደ ተለያዩ አገራት ሲዛመት አንዳንዶቹ መደናገጥ ጀመሩ። አሁንም በአፍሪካ በኩል ያለው መዘናጋት ዋጋ እንዳያስከፍል መጠንቀቅ ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ በኩል መዘናጋቱ ድርብርብ ገጽታዎች አሉት።

ማኅበራዊ እርቀት?

ተራርቆ ከመቀመጥ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ የምንጠቀመው ሐረግ “ማኅበራዊ እርቀት” የሚል ነው። ሰዎችም ሲመክሩ “ማኅበራዊ እርቀታችሁን ተብቁ” እያሉ ነው። ይህ ነገር እንዲያው ጸጉር ስንጠቃ አይሁንብኝ እንጅ ሐረጉ ተገቢ አይደለም። ማኅበር የአካል መቀራረብ ሳይሆን የመንፈስ ትስስርን የሚገልጽ ከሰው ልጆች የአብሮነት እና የመተሳሰብ ባህርይ የመነጨ ነው። ማኅበራዊነት በራሱ መቀራረብ ነው። ማኅበራዊ እርቀት የሚለው ሐረግ እንዲሁ ትርጉም አልባ ነው። ከዚህ ይልቅ “አካላዊ እርቀት” የሚለው ኮሮናን ለመከላከል ስለሚደረገው ምክር ትክክለኛውን ይዘት ይወክላል። ከዚህ ጋር በተያያዘ እጅ ለእጅ መጨባበጥን ወይም ተቃቅፎ መሳሳምን ስለማስወገድ ሲመክሩ አንዳንዶች በዘፈቀደ “ሰላም አትባባሉ” ሲሉ ይሰማል። ይኸም ስለቃላቶቻችን እና ግብሮቻቸን ያለንን አለማስተዋል ነው።   

እነዚህን ሁሉ መዘናጋቶች ስንታዘብ ይህንን ነገር ተቀምጠን እየሰቀልነው ይሆን? ማለታችን አልቀረም።

የነገው ሰው ማን ነው?

የሰው ልጅ ከሌላው እንስሳ የሚለየው የጋራ ህልውናውን የሚመራባቸው የእምነት፣ የባህል፣ የእውቀት፣ የሕግ፣ የሥልተ መርት እና የፍጆታ፣ የልኬት እንዲሁም የቁጠባና የምጣኔ መርሆዎችን መገንባቱ ነው። ጠቅለል ብሎ ሲታይ አንድ ሙለር የተባለ ጸሐፊ እንዳለው ሰው ባህል ገንቢ እንስሳ ነው። ባህል ደግሞ የአስተሳሰብ እና የቁሳዊ ነገሮች መገለጫ፣ የአንድ ማኅበረሰብ አባላት የሚንቀሳቀሱበት ካስማ እና የኅሊና ካርታ ነው። ሰው በዘመን ሂደቱ ውስጥ ሲፈጥር፣ ሲያሻሽል፣ እንደወረደ ሲያስቀጥል፣ እንዲሁም ሲቀይራቸው የኖረ አስተሳሰባዊ እና ተግባራዊ ይትበሃሎች አሉት። የሰው ልጅ የሚገለጸው ደግሞ በነዚህ የዘመናት ክምችት መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ውርሶቹ ድምር ነው።

የኮሮና ጉዳይ ስለ ነገው ሰው ምን ይጠቁመናል? ከፖለቲካ አንጻር ካየነው አሁን ያሉ ኃያላን አገራት መፋጠጥ ዓለማቀፍ ግንኙነት ላይ አንዳች ለውጥ ማምጣቱ አይቀርም። አብዝሃኛዎቹ አግራት ድንበራቸውን ዘግተዋል፣ ወደ አገራቸው የሚገቡ ሰዎችን በጥርጣሬ ዕያዩ ነው። የቻይና እና የአሜሪካ ቃላት መፋጠጦች ይፋ ወጥቷል። ለወደፊቱ የሚኖረው የቴክኖሎጂ ፉክክር ወዘተ ማን ከማን ጋር እንደሚወግን በዓለም አቀፍ የፖለቲካ መስተጋብር ላይ አንዳች ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።

የህክምናው ጉዳይ በእጅጉ የሚያሰጋን ነው። ዓለም አሁን በአያሌው ተጨንቃለች። ዘላቂ መፍትሔም ሆነ ክትባት አልተገኘለትም። የሕክምና ተመራማሪዎች አንዳች ተስፋ ሰጭ ክትባት ቢፈጥሩ ተሽቀዳድሞ የሚጠቀመው በርካታ ነው። ፍርሃታችን እና ጭንቀታችን ምርጫችን የተረጋጋ እና የረዥም ጊዜ ጫናውን ያገናዘበ አይደለም። የመድኃኒቱ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ጊዜ ሰጥተን እንድንመረምር የሚያስችለን ሁኔታ አይደለም ያለው። ዛሬ ላይ የምንወስደው ክትባት በልጆቻችን ላይ ምን ጫና ሊኖረው እንደሚችል የምናስብበት ጊዜ የለንም። የነገው ሰው ማን ነው? የሚያስብለን አንዱ ስጋት ይህ ነው።

የኮሮና ጉዳይ በጋራ ሆነን የምናደርጋቸውን ባህሎች (ለምሳሌ የሰላምታ፣ የአመጋገብ፣ የአብሮነት፣ የአምልኮ) ሁሉ እርግፍ አድርገን እንድንተው አድርጎናል። ሁላችንም በየጓዳችን ተደብቀን በራሳችን ጠባብ ዓለም ውስጥ እንድንኖር፣ ሌሎቹን እንዳንነካ፣ እንድንሸሽ ተገደናል። ኳስን ጨምሮ ሁሉም ሰብሰብ ብለን የምንመለከታቸው፣ የምንጫወታቸው መዝናኛዎች በሙሉ ቀርተዋል። ለወትሮው በአንድ ወንበር ሦስት እና ከዚያ በላይ፣ በአንድ ዶርም እስከ ስምንት ተማሪዎች ባንድ ላይ የሚማሩበት፣ የሚኖሩበት፣… ሁኔታ አሁን ላይ ቀርቷል። ሁሉንም ሰዎች መፍራት እና እንደ በሽተኛ መጠርጠር የሚለው መርህ በሁላችን ዘንድ እየሰረጸ ነው። ይህ የመራራቅ ትዕዛዝ ከልምድ አልፎ ባህል እንዳይሆን ያሰጋል። በሰው ልጆች ተጠራጣሪነት እና በሳይንሱ አይታመኔነት ምክንያት ነገ ላይ ቫይረሱ ሙሉ በሙሉ ተወግዷል እና ወደ ቀደመ ነገራችሁ ተመለሱ ቢባል በቀላሉ እንመለስ ይሆን? የነገው ማኅበረሰብ ምን ዓይነት ነው?

ማጠቃለያ

በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን አንድ የአፍሪካ አገር መሪ ለዜጎቻቸው ተናገሩት ተብሎ ሲዘዋወር ያገኘሁት ሐሳብ እንዲህ ይላል “ኢኮኖሚውን እንዴት ወደነበረበት መመለስ እንዳለብን እናውቅበታለን፤ ሕይወታችሁን መመለስ ግን አንችልም። ሕይወታችሁን ጠብቁ” (ቃል በቃል አይደለም)። በኝህ መሪ ንግግር መሰረት ወደ ነበረበት መመለስ ወይም የበለጠ ተሻሽሎ ሊሰራ የሚችል ጉዳይ አለ። አንዴ ካመለጠ የማይመለስ ጉዳይ ደግሞ አለ። በኮሮና ምክንያት ያጣናቸውን መመለስ አይቻልም። ለወደፊቱ ልናጣቸው የምንችላቸውን ግን መታደግ ይቻላል። ከሕይወት ጀምሮ እስከ ባህል ማስቅየር፣ ማኅበራዊ ደንብን እና ዓለማቀፋዊ መሰተጋብርን በሙሉ ጥያቄ ውስጥ የሚከት ፈተና በሰው ልጆች ሁሉ ዘንድ እንደተደቀነ ይሰማናል። በዚህ አጭር ጊዜ እንኳን የታዘብናቸው ነገሮች ሰውነትን፣ ባህልን፣ እምነትን፣ ሳይንስን፣ የኢኮኖሚ አቅምን፣ ስልጣኔን፣ ወዘተ ትዝብት ውስጥ የሚከቱ ናቸው። በተቃራኒው ደግሞ በሳይንቲስቶች ርብርብ፣ በቁርጠኞች መስዋዕትነት፣ በባለ ሃብቶች እና በደግ ሰዎች ልግስና ብዙ ተስፋ ሰጭ ነገሮች ዐይተናል። እነዚህ ሁሉ ገጠመኞች፣ ትዝብቶች እና ተስፋዎች የሰውን ልጅ ጥበብ አቅምና ወሰኗን፣ የሰውን ልጅ ምንነት እና የሕይወቱን ትርጉም፣ ሰው ከሰው ጋር ያለውን ማኅበራዊ ግንኙነት፣ ሰው ከተፈጥሮ ጋር ያለውን መስተጋብር (Interaction)፣ ሰው ከልዕለ ተፈጥሮ ጋር ሊኖረው የሚገባውን መነጋገር እንደገና እንድንፈትሽ የሚያስችሉን የማንቂያ ደወሎች ናቸው። ለመሆኑ የኮሮና ጉዳይ ያላንኳኳቸው በሮች የትኞቹ ናቸው? በዚህ የሕይወት ጠባብ በር አልፎ የምናገኘው የነገው ሰው ማን ነው? ማኅበራዊ መስተጋብሩስ ምን ይመስላል?

ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላምና ጤናን ያብዛልን!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top