ጣዕሞት

አንጋፋው ጋዜጠኛ ተሸኙ

የጋዜጠኝነት ትምህርት በኢትዮጵያ በተደራጀ መልክ እንዲጀመር በማድረግ፤ የመጀመሪያውን የማስሚድያ ማሰልጠኛ ተቋም (Mass Media Training Institute) መስርተው ለዓመታት መርተው እና አስትዳድረው፤ በኋላ ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር እንዲጠቃለል ያደረጉት አቶ ፀሃዬ ደባልቀው፤ በተወለዱ በ69 ዓመት ዕድሜያቸው አርብ የካቲት 26 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

በስራ ዘመናቸው በባልደረቦቻቸው የሚወደድ ባህሪ የነበራቸው አቶ ፀሃዬ ደባልቀው፤ በተለይም በማስሚዲያ ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ እያሉ፤ ተቋሙ አዳዲስ ጀማሪ ወጣቶችን ተቀብሎ እንዲያስተምር የወቅቱን ባለስልጣናት ተከራክረው በማሳመን፤ 15 ልጆችና በስራ ላይ የነበሩ ሌሎች ተማሪ ጋዜጠኞችን ተቀላቅለው እንዲማሩ እድል ከፍተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ተቋሙ አስመርቆ ያወጣቸውን ጀማሪ ወጣቶች የመቅጠር አቅም ያላቸው ድርጅቶች ያኔ በቁጥር ውስን ስለነበሩና ድርጅቶቹ የራሳቸውን ሰልጣኝ ስራተኞች ብቻ መልሰው ስለሚቀጥሩ፣ በአዲስ ክፍት የስራ ቦታዎች ለመቀጠር ደግሞ የቅጥር ማስታወቂያዎች ሲወጡ በሁሉም የትምህርት ዘርፍ ለተማሩ በመሆኑ፤ ለጀማሪ  አንጋፋው ጋዜጠኛ ተሸኙ  የማሰልጠኛው ተማሪዎች ስራ ማግኘት ፈተና ነበር። እናም አቶ ፀሐዬ የተቋሙ ተማሪዎች ተወዳዳሪነታቸው እንዲጨምር ሌሎችን ባልደረባዎቻቸውን ሳይቀር እርዳታ እየጠየቁ የስራ ቅጥር ቃለምልልስ ያሰለጥኑ ነበር።

 ከሌሎች ከተሞች መጥተው የተማሩ ልጆች ስራ በማጣት ተስፋ በቆረጡ ጊዜና ወደመጡበት በተመለሱ  ጊዜ እንኳን ደውለው በመጥራት በኢንስቲትዩቱ ውስጥ በተለያዩ ስራዎች ተቀጥረው የኪስ ገንዘብ እያገኙ ስራ እንዲያፈላልጉ አድርገዋል፣ አብዛኞቹ ተማሪዎቻቸው ዛሬ በጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ አንቱ የተባሉ ሆነዋል።

ከጋዜጠኝነት ሞያ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ተቋማትን ያስተዳደሩት አቶ ፀሃዬ ደባልቀው፤ ለሃገራቸው ቁጥራቸው ብዙ የሆኑ የሁለት ትውልድ ጋዜጠኞችን በሙያ ከመውለዳቸውም በላይ፤ ለተከበረው የጋዜጠኝነት ሙያም በግለሰብ ደረጃ መስዋዕትነት ከፍለዋል። በሙያቸው ሳቢያም በደርግ ዘመን ለሰባት ዓመታት በወህኒ ቤት ታስረው አሳልፈዋል። ለጋዜጠኝነት ሙያ በከፈሉት ተኪ-የለሽ ሚና፤ በወዳጆቻቸው ብቻ ሳይሆን በተቺዎቻቸውም ጭምር ከፍተኛ አድናቆት እና ክብር የተሰጣቸው ሰው ነበሩ።

 በ1942 ዓ.ም. ከአባታቸው ከአቶ ደባልቀው ተሰማ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ብርነሽ ተክሉ በአክሱም የተወለዱት አቶ ፀሃዬ ደባልቀው ባለትዳር እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበሩ፡፡ የታዛ መጽሔት ዝግጅት ክፍል፤ ለአቶ ፀሃዬ ደባልቀው ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች፣ እና አድናቂዎች መጽናናትን ይመኛል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top