ታሪክ እና ባሕል

ሀገር በቀል መድኃኒት እና ወረርሽኝ

ለፎክሎር ጥናት መሰረት የፎክ ዕውቀት (Folk knowledge) ነው። የፎክ ዕውቀት ማለት በአንድ በተወሰነ ሕዝብ፣ ማኅበረሰብ፣ ባህል ወይም አካባቢ ውስጥ ያለ ልዩ ዕውቀት ነው። ይህ ዕውቀት የተለያዩ ህዝባዊ ቴክኖሎጂዎችን፣ ክህሎቶችንና ውስብስብ ዕውቀቶችን የሚይዝ በመሆኑ ለማህበረሰቡ ህይወት መሰረት ነው።

የፎክ ዕውቀት ማኅበረሰቡ በህይወት ዘመን ተመክሮው ያጠራቀመው፣ የትውልድን ልምድ የሚወክል፣ የማኅበረሰቡን ማንነትና የእድገት ደረጃ የሚያሳይ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ የዘመን ሙከራ አሻራ ነው።

በፎክ ዕውቀት ዘርፍ ውስጥ ከሚካተቱ ልዩ ልዩ ዕውቀቶች መካከል ሀገር በቀል የህክምና ዘዴ አንዱ ነው። በተለያዩ ማኅበረሰቦች ውስጥ የሚከሰቱ የተለያዩ የጤና ችግሮች መነሻ ምክንያታቸውን ለማወቅና ችግሩንም ለመፍታት ማኅበረሰቡ ባለው ባህል መሰረት ለረጅም ዘመን የተጠቀመባቸውና አሁንም እየተጠቀመባቸው ያሉ የፎክሎር ዕውቀቶች በሀገረሰባዊ ህክምና (Folk Medicine) ዘርፍ ውስጥ ይመደባሉ።

የዓለም የጤና ድርጅት (2001) ስለሀገረሰባዊ ህክምና ብያኔ ሲሰጥ ሀገረሰባዊ ህክምና ጤና ነክ ድርጊቶችን፣ የአቀራረብ መንገዶችን፣ ዕውቀትንና እምነቶችን፣ እጽዋትን፣ እንስሳትን፣ ማዕድናትን፣ መንፈሳዊ ቁሶችንና መንፈሳዊ ክዋኔዎችን መሰረት በማድረግ ህመሞችን የማወቅ፣ የመከላከልና የመፈወስ ስርዓት እንደሆነ ይገልጻል።

በማኅበረሰቡ በሕይወት ውስጥ ለሚያጋጥሙ የጤና ችግሮች መፍትሄ ለማግኘት በሚል የማኅበረሰቡ አባላት የሚከውናቸው አጠቃላይ ድርጊቶች በሀገረሰባዊ ህክምና ውስጥ የሚጠኑ ጉዳዮች ናቸው። እነዚህ ድርጊቶችም ማኅበረሰቡ ስለ ህመምና ጤና ያለው እሳቤ፣ ስለህመምተኛው ያለው አመለካከት፣ ስለህክምና ባለሙያዎቹ ያለው አመለካከት፣ አንድን የህመም ዐይነት ለመለየት የሚጠቀምበት ዘዴ፣ ለበሽታዎቹ መከላከያ ወይም ማጥፊያ የሚሆኑ መድኃኒቶችን ከምን ከምን እንደሚያዘጋጅ፣ እንዴት እንደሚያዘጋጅ፣ መቼ እና የት እንደያሚዘጋጅ፣ የመድኃኒቶቹ የአወሳሰድ ስርዓት እና ለህክምናው የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች የመሳሰሉትን ነጥቦች ናቸው።

ሀገረሰባዊ ህክምናዎች ማኅበረሰቡ በረጅም ዘመን የህይወት ተመክሮው ባካሄደው ምርምር በአካባቢው የሚያገኛቸውን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ግብዐቶች በመጠቀም የራሱን ሕዝባዊ ዕውቀት መነሻ በማድረግ የሚያዘጋጃቸው ናቸው። ህክምናዎቹም በአካባቢው ለሚከሰቱ የጤና ችግሮች ሁሉ መፍትሄ የሚሰጥባቸው፣ የጤና ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት የሚደረጉ ቅድመ ጥንቃቄዎች፣ ችግሮቹ ዳግመኛ እንዳይከሰቱ የሚደረጉ ዘላቂ መፍትሄዎች ወዘተ. የሚሰጡበት ህዝባዊ ጥበቦች ናቸው።

በዓለማችን ላይ በሚገኙ ህዝቦች ዘንድ በርካታ የሀገረሰባዊ ህክምና ዐይነቶች አሉ። እነዚህ የህክምና ዐይነቶች እንደማኅበረሰቡ ባህል፣ ፍልስፍና፣ ርዕዮተ ዓለማዊ ዕይታና መሰል ሁነቶች የሚለያዩ ናቸው። ሀገረሰባዊ ህክምናዎችን ማኅበረሰቡ በሰው፣ በእንስሳት እና በእጽዋት ላይ የሚከሰቱ የጤና ችግሮችን ለመከላከል ይጠቀምባቸዋል።

ዕውቁ የፎክሎር ባለሙያ ዶን ዮደር (1972) ሀገረሰባዊ ህክምናዎችን ተፈጥሯዊ የሀገረሰብ ህክምና (Natural folk medicine) እና እምነታዊ-ሀይማኖታዊ የሀገረሰባዊ ህክምና (Magico- religious folk medicine) በሚል በሁለት ይመድባቸዋል።

ተፈጥሯዊ የሀገረሰብ ህክምና የሚባሉት ከተፈጥሮ የሚገኙ፣ ለምግብነትና ለመድኃኒትነት ወይም ለመድኃኒትነት ብቻ የሚያገለግሉ የተለያዩ የእጽዋት ቅጠሎች፣ ቅርፊቶች፣ ስራስር፣ ፍራፍሬ፣ ግንዶች፣ የተለያዩ ማዕድናት፣ የእንሰሳት ተዋጽኦዎች እና ተረፈ ምርቶችን በግብአትነት በመጠቀም የሚዘጋጁ ናቸው። እነዚህን ግብአቶች በመጠቀም እንደማኅበረሰቡ ባህል ለሰው ልጅ፣ ለእንሰሳትና ለእጽዋት የጤና ችግሮች መፍትሄ ይሰጣሉ።

እምነታዊ- ሀይማኖታዊ የሀገረሰባዊ ህክምና የሚባሉት ደግሞ በተቋማዊና ተቋማዊ ባልሆኑ ሀይማኖቶች እንዲሁም በሀገረሰባዊ እምነቶች (ለምሳሌ፡- ዛር፣ ጥንቆላ፣ አስማት ወዘተ.) ውስጥ መንፈሳዊ ዋጋቸው ከፍተኛ የሆኑ መንፈሳዊ የህክምና ግብዐቶችን መሰረት በማድረግ ጤና ነክ ችግሮችን ለመፍታት የሚከወኑ ድርጊቶች ናቸው።

በተለያዩ ማኅበረሰቦች ውስጥ በሚገኙ እምነቶችና ሀይማኖቶች የአስተምህሮ ስርዓት መሰረት የተለያዩ መንፈሳዊ ቁሳቁሶች እንደመስቀል፣ የሀይማኖት መጽሐፍ፣ ጸበል፣ ዘምዘም፣ ክታብ ወዘተ. በመጠቀም፣ በቅዱስ ስፍራዎች እንደ ቤተክርስቲያን፣ መስጊድ፣ የጸበል ቦታ፣ ሀገረሰባዊ ሀይማኖቶች የሚከወኑበት ስፍራ ወዘተ. አማካኝነት፣ በሀይማኖቱ ወይም በእምነቱ ስርዓት ውስጥ ትልቅ ስፍራ በሚሰጣቸው ግለሰቦች በሚደረጉ ጸሎቶች፣ ለፈጣሪያቸው ወይም ሌላ ህመምን ያመጣል ብለው ለሚያምኑበት አካል በሚያቀርቧቸው መስዋዕቶችና መሰል መንፈሳዊ ድርጊቶች አማካኝነት የተለያዩ በሽታዎችን የመለየት፣ የመከላከልና የመፈወስ ስርዓቶች ይካሄዳሉ።

በተለያዩ አገራት ከተፈጥሮ በሚገኙ ግብአቶች የሚዘጋጁ መድኃኒቶችን መጠቀም የተለመደ ነው። በተለይ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ሰማንያ እጅ (80%) የሚሆነው ህዝብ ከእጽዋት፣ ከእንስሳትና ከማዕድናት የሚገኙ የህክምና ግብአቶችን ለመጀመሪያ ደረጃ ህክምናዎች እንደሚጠቀሙ ጥናቶች ያሳያሉ።

ከኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥም ሰማንያ እጅ (80%) የሚሆነው ህዝብ በአካባቢው የሚከሰቱ የጤና ችግሮችን ለመከላከልና መፍትሄ ለማግኘት ሀገረሰባዊ ህክምናዎችን እንደሚጠቀም የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ።

በዓለማችን ላይ በሚልዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች ተፈጥሯዊ የመድኃኒት ግብአቶችን በመጠቀም ለህመማቸው መፍትሄ እንደሚያገኙና ከተፈጥሯዊ ግብአቶችም በአብዛኛው የእጽዋት ሀገረሰባዊ መድኃኒቶችን (Herbal lore) ይጠቀማሉ። ለዚህም ምክንያት በዋናነት ማኅበረሰቡ በእጽዋት መድኃኒቶች ላይ እምነት ስላለው፣ እጽዋቱ በአካባቢያቸው በቀላሉ ስለሚገኙ፣ የእጽዋት መድኃኒት ቀማሚ ባለሙያዎችን በማንኛውም ጊዜ ማግኘት ስለሚቻልና በህዝቡ የፍላጎት መጠን በብዛት መገኘታቸው እንደምክንያትነት ይጠቀሳሉ። 

በዘመናዊ የህክምና ሳይንስ መፍትሄ ያልተገኘላቸው ወይም ውስብስብ የህክምና ስራ የሚጠይቁ በርካታ በሽታዎች በዓለማችን ላይ አሉ። ነገር ግን የተለያዩ የአገራችን ማኅበረሰቦች ከእነዚህ በሽታዎች ለመዳን ተፈጥሯዊ መድኃኒቶችን በሀገር በቀል ዕውቀት በመጠቀም መፍትሄ ያገኙላቸዋል።

በአገራችንም በሚገኙ በተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እነዚህን ተፈጥሯዊ የመድኃኒት ዐይነቶች በመጠቀም በአካባቢያቸው ለሚከሰቱ የተለያዩ በሽታዎች መፍትሄ በመስጠት የራሳቸውን፣ የእንሰሳትንና የእጽዋትን ጤና ለረጅም ዘመን ሲጠብቁ ቆይተዋል።

የህዳር በሽታ ‹‹ስፓኒሽ ፍሎ›› ወይም ‹‹ፓንደሚክ ፍሉ›› በመባል የሚታወቅ የኢንፊሎዌንዛ ወረርሽኝ ነው። ወረርሽኙ እ.ኤ.አ ከ1918-1920 ድረስ በበርካታ የዓለም ሀገራት የተዛመተ ሲሆን ከ20 እስከ 50 ሚሊዮን የሚገመት ሰው ገድሏል። ይህ ወረርሽኝ በአገራችንም በ1911 ዓ.ም በህዳር ወር ተከስቶ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ሕዝብ ለሞት ዳርጓል።

የህዳር በሽታ በአዲስ አበባ ከተማ ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሰና የነበረውን ጭንቀት በስፍራው ተገኝተው የተመለከቱትን መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ‹‹የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ›› በሚል መጽሐፋቸው እንደሚከተለው ይገልጻሉ።

በ1911 ዓ.ም የበሽታ መቅሰፍት በኢትዮጵያ ላይ ወርዶ ብዙ ሰው አለቀ። በሽታው አዲስ አበባ ደርሶ በጣም የታወቀው በህዳር ወር ስለሆነ በህዝብ ቃል ‹‹የህዳር በሽታ›› የሚል ስም ወጣለት። ፈረንጆች ግን የበሽታውን ስም ‹‹ግሪፕ›› ብለውታል። በሀገራችንም አንዳንድ ሰዎች ‹‹ቸነፈር›› ብለውት ነበር።

በሽታው ቀደም ብሎ አውሮፓ ላይ በዓለም ጦርነት ምክንያት ስለተነሳና ብዙ ሕዝብ ስለፈጀ ይኸው ወሬም ከመስከረም ጀምሮ ተሰምቶ ነበር። ወደ አገራችንም በንፋስ ተዛምቶ መጣና ከጥቅምት ጀምሮ ጥቂት በጥቂት በአንዳንድ ሰው ቤት መግባትና መጣል ጀመረ። በህዳር ወር ግን አብዛኛውን ሰው ስለነደፈው ከተማው ተጨነቀ።

በሽታው እንደ ሳልና እንደ ጉንፋን አድርጎ ይጀምርና በበሽተኛው ላይ ትኩሳት ያወርድበታል። ከዚያም ሌላ ያስለቅሳል፣ ነስር ያስነስራል፣ ተቅማጥና ውጋት ያስከትላል፣ አንዳንዱንም አእምሮውን ያሳጣዋል። እንዲህ እያደረገ በሶስት በአራት ቀን ይገድለዋል። ከአራት ቀን ያለፈ በሽተኛ ግን ከሞት ማፋረሱ ነው። ሆኖም ከግርሻ መጠንቀቅ ነበረበት።

አንዳንድ ስፍራ ቤተሰቡ በሙሉ ይታመም ስለነበር አስታማሚ በማጣት በርሃብና በውኃ ጥም ብዙ ሰው ተጎዳ። ስለዚህ በአዲስ አበባ ከተማ በየቀኑ ሁለት፣ ሶስት መቶ ከዚያም በላይ ይሞት ጀመር። በአንድ መቃብርም ሁለቱን ሶስቱን ሬሳ እስከመቅበር ተደረሰ። አንዳንዶቹንም ሰዎች ሬሳ ተሸካሚ በማጣት በየግቢያቸው ውስጥ ቀበሯቸው።

አፍላው በሽታ ከህዳር 7 እስከ 20፣ ለ14 ቀን ያህል ነበር። በተለይም ህዳር 12 ቀን የህዳር ሚካኤል ዕለት ብዙ ሰው ሞተ። ….. በዚያ ሰሞን መቃብር የሚቆፍርና ሬሳ ተሸክሞ የሚወስድ ሰው ለማግኘት ችግር ሆነ። በቤተሰብ ውስጥ ከበሽታው ያመለጡ ሲገኙ ሁለት ሰዎች ሬሳ ተሸክመው እየወሰዱ ይቀብራሉ።

ባል ሚስቱን፣ አባት የልጁን ሬሳ እየተሸከመ ወስዶ ቀበረ። ደግሞ አንዱ መቃብር ይቆፍርና ሬሳ ለማምጣት ወደ ቤት ሄዶ፣ ሬሳ ይዞ ሲመለስ ሌላው ቀብሮበት ያገኘዋል። 

ቤተሰቡ በሙሉ በታመመበትም ስፍራ ብዙዎቹ በየቤታቸው እየሞቱ አውሬ በላቸው። ለጉዳይ ወደ አዲስ አበባ የመጣ እንግዳም እየታመመ መግቢያ ቤት አጥቶ በየመንገዱ እየወደቀ አውሬ በላው።

በማለት በወቅቱ የነበረውን አሳዛኝ ሁኔታ ይገልጻሉ። በተመሳሳይም የህዳር በሽታን አስከፊነት በሐረር ከተማ ያዩት ልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ፤ ‹‹ካየሁት ከማስታውሰው›› በሚለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል።

በሺህ ዘጠኝ መቶ አሥራ አንድ ዓመተ ምህረት በሮፓና በእስያ አድርጎ የመጣው የንፋስ (የግሪፕ) በሽታ በኢትዮጵያም በመላው አገር ገብቶ ብዙ ሰው ሞተ። ያንጊዜም ሐረር ነበርኩ። እዚሁም ሐረርጌ ከህዳር ወር ጀምሮ  እስከ ጥር መጨረሻ ሰሞን ድረስ በጣም ከፍቶ በከተማው ውስጥ ብቻ እንኳን ከሰማንያ እስከ መቶ ሃያ በየቀኑ ይሞት ነበር። የታመመው ሰው ልክ አልነበረውም።

በሽታውም ትኩሳቱ በጣም እየበዛ፣ እራስ እያዞረ፣ አእምሮ እያጠፋ፣ ደም እያስታወከ ነው። በቶሎም ካንዱ ወዳንዱ የሚተላለፍ በመሆኑ ብዙም ቤተሰብ እንዳለ እየተኛ አስታማሚው ብዙ ችግር ሆነ። የነበሩት ጥቂት ሐኪሞች ምንም ያህል ሰው ለማዳን አልቻሉም፤በሽታው እያጣደፈ የሚገድል ስለሆነ።

በማለት የሕመሙን አስከፊነት ይገልጻሉ። በህዳር በሽታ ምክንያት አዲስ አበባ ከተማ የሞተው ሕዝብ ቁጥር 9 ሺህ፤ በመላው ኢትዮጵያ ደግሞ እስከ 40 ሺህ ይሆናል ተብሎ እንደሚገመት መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ይገልጻሉ። በዚህ በሽታ ሳቢያ ከሞቱ ታዋቂ ግለሰቦች መካከል በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወሰኔ ዛማኔል፣ በሀረር ከተማ ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረየሱስ ይጠቀሳሉ።    

እነዚህን መሰል የዓለማችን አስጨናቂ ወረርሽኞች በርካታ ህዝብን ጨርሰዋል። ከእነዚህ ወረርሽኞች በማኅበረሰቡ የራሱን ሀገር በቀል ዕውቀት መሰረት በማድረግ በሽታዎችን ሲከላከልና ጤንነቱን ሲጠብቅ ቆይቷል። አሁንም እየተከላከል ይገኛል።

የህዳር በሽታ በ1911 ዓ.ም ተከስቶ ከፍተኛ ጉዳት ባደረሰብን በዚያ አስጨናቂ ወቅት ማኅበረሰቡ ሀገር በቀል መድኀኒትን በመጠቀም ከበሽታው ተፈውሷል። ልዑል ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ በወቅቱ ለተከሰተው የህዳር በሽታ መድኃኒት ምን እንደሆነ እንደሚከተለው ገልጸውታል።    

በሐኪሞቹም ምክር የ‹‹ካሊፕቱስ›› ቅጠል በየበሽተኞቹ ቤት እየተቀቀለ በላበቱ አየሩን በመለወጥና ትኩሱንም ውኃውን በማጠጣት ብዙ ሰው አሻለ። በየቦታውም በሞተው ሰው መቃብር ላይ ኖራ በብዙ ተረጨበት። ይኸውም በሽታው እንዳይተላለፍ የሚያግዝ ነበረ።

እሳቸው የ‹‹ካሊፕቱስ›› ቅጠል በሚል የገለጹት የባህር ዛፍ ቅጠል ነው። የባህር ዛፍ ቅጠልን በውኃ በመቀቀል በመታጠን፣ ውኃውንም በመጠጣት ከወረርሽኑ ድነዋል። የባህር ዛፍ ቅጠል፣ የሀረግሬሳ ቅጠል፣ የዳማከሴ ቅጠል በሙቅ ውኃ ቀቅሎ መታጠን ከጉንፋን ጋር ቀረቤታ ያላቸው መሰል የኢንፊሎዌንዛ ሕመሞች ፍቱን መድኀኒት ነው። ማኅበረሰቡ አሁንም ለጉንፋንና መሰል ሕመሞች እነዚህን እጽዋት ይጠቀማል።

በአሁኑ ወቅትም ዓለምን እያስጨነቀ የሚገኘው የኮሮና በሽታ (ኮቪድ-19) ለበርካታ ሕዝብ የሕይወት ማለፍ ምክንያት ሆኗል። በአገራችንም ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል። ይህን ጽሑፍ በማዘጋጅበት ወቅት በአገራችን 35 ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል። የኢትዮጵያ ኢኖቬሽን እና ሳይንስ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ምሁራን በመሰራት ላይ ያለ ተስፋ ሰጪ ሀገር በቀል መድኀኒት በሙከራ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ትልቅ ተስፋ ነው። የራሳችንን ሀገር በቀል ዕውቀቶች ዕውቅና መስጠታችን፣ ለእኛም ሆነ ለዓለም መድህን እንደምንሆን አምነን ወደ ተግባር መግባታችን እጅግ ደስ ያሰኛል። ለኢትዮጵያም ክብር ነው።   

በአገራችን ከሚገኙ የተፈጥሮ መድኃኒቶች አማካኝነት ልክ እንደ ኮሮና በሽታ ሁሉ መድኀኒት ባልተገኘላቸው በሽታዎች የተጠቁ ሰዎች እንደሚፈወሱ ይታመናል። አረጋ እሸቱ ‹‹የእኛን ለእኛ መድኃኒት፤ የባህላዊና ዘመናዊ መድኃኒቶች ስብስብ›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት  መጽሐፍ ውስጥ ለካንሰር ህመም መድኃኒት መኖሩን ገልጸዋል። መድኃኒቱም የቀይ ስር ቅጠል ጭማቂ ወይም የካሮት ስርና ቅጠል በየቀኑ መጠጣት ወይም ጥሬ ቀይና ነጭ ሽንኩርት አዘውትሮ ከምግብ ጋር መመገብ ነው።

በማሾሌ ብሔረሰብ ለቢጫ ወባ ባህላዊ መድኃኒት የበሶቢላ (ኤፊያ) እና ‹‹ቀሸውሊታ›› ቅጠል በፀሐይ ላይ ካደረቁ በኋላ በሙቀጫ አንድ ላይ በመውቀጥ ዱቄቱን ከውኃ ጋር በማደባለቅ በሽታው የያዛቸው ሕጻናት ጠዋት በማለዳ ምንም ምግብ ሳይቀምሱ እንዲጠጡ ይደረጋል። የቢጫ ወባ የያዛቸው አዋቂዎች ደግሞ ይኸው የበሶቢላ እና የ‹‹ቀሸውሊታ›› ቅጠል በደንብ ከደረቀ በኋላ ተወቅጦ ዱቄቱ በሲጃራ መልክ እንዲያጨሱት ይደረጋል።

በጋሞ ብሔረሰብ ‹‹ደርደሬ›› እና ‹‹አክርሳ›› የሚባሉ ተክሎች ስር በአንድ ላይ በመውቀጥ ጭማቂውን በጉበት በሽታ ለተጠቁ ሰዎች እንደ እድሜያቸው በተለያየ መጠን ይሰጣቸዋል። የጉበት መድኃኒቱንም ‹‹ጠሌ›› በሚል ስያሜ ይጠሩታል።

እነዚህንና መሰል ሀገር በቀል መድኀኒቶች በሳይንሳዊ መንገድ ማጥናት አስፈላጊ ነው። የኮሮና (ሳምባ ቆልፍ) በሽታን ለመከላከል ነጭ ሽንኩርት፣ ዝንጅብል፣ ፊጦ፣ ሎሚ፣ ዳማከሴ፣ የባህር ዛፍ ቅጠል ወዘተ. ይጠቀማሉ ብሎ በስማበለው በመሻማት ከመጠቀም መታቀብ ይኖርብናል። በተቃራኒው ደግሞ እነ ነጭ ሽንኩርት ምንም ጥቅም የላቸውም ብሎ ዜና ለመስራት ከመሯሯጥ መቆጠብ ይኖርብናል።

በእነዚህና መሰል ሀገር በቀል መድኀኒቶች ላይ ሰፊ ምርምር በማድረግ ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ማወቅና መጠቀም አሁን ላይ ግዴታችን ሆኗል። አሁን የኮሮና የስጋት ደመና በአገራችን ያንዣበበት ወቅት ነው። በመሆኑም በትክክለኛ መረጃና ማስረጃ የምንመራበት እንጂ በአሉባልታ የምንተራመስበት ወቅት አይደለም።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top