መጽሐፍ ዳሰሳ

የዘር ፍጅት ማስታወሻ

ደራሲ፡ IMMACULEÉ ILIBAGIZA

ርዕስ፡ Left to Tell (ለወሬ ነጋሪነት የተረፍኩ)

ጭብጥ፡ በሩዋንዳ የዘር ፍጅት ላይ የተመሰረተ

የገፅ ብዛት፤ 240

የተፃፈበት ቋንቋ፤ እንግሊዝኛ

እንደመነሻ

ከዛሬ አስራ አምስት አመት በፊት አንድ ሩዋንዳዊ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል። በጊዜው ይኖር የነበረው ፈረንሳይ ሀገር ነበር። የመጣበት ዋና ምክንያት የፒ.ኤች.ዲ ዲግሪው ጥናት ከኢትዮጵያ ጋር የተያያዘ ስለነበር ነው። ባጋጣሚ ለጥናቱ መነሻ የሆኑ ግብአቶችን ለማግኘትና ሰዎችን ለማነጋገር ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይመጣል። ሩዋንዳውያን በቤልጂግ ቅኝ ተገዝተው ስለነበር አብዛኛው ከተሜና የተማረው ወገን በብዛት የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ናቸው። ለመግባባት የሚያስችል የፈረንሳይኛ ቋንቋ ክህሎት ስለአለኝና እኔ ወደምሰራበት ተቋም ስለመጣ በቀላሉ ተዋወቅን፤ ቆይተንም ተግባባን። በሌላ በኩል ቀደም ብሎ በአንድ ኢትዮጵያ ተካሂዶ በነበረ ዓለም-አቀፍ ሴሚናር ምክንያት አንድ የዩኒቨርስቲ ምሁር የነበረ ሩዋንዳዊ አውቅ ነበረና ወጣቱን አጥኚ ዶ/ር ሙጋሴራ ሊዮንን ታውቀዋለህ ብዬ ጠየቅኩት። እርሱም እሱን በማወቄ ተገርሞ፤ የዚያ ሁሉ እልቂት (የ1994ቱ) አንዱ መሀንዲስ እርሱ እንደሆነ ነገረኝና ያንን በምንነጋገርበት ወቅት ከሩዋንዳ አምልጦ ጠፍቶ በካናዳ በጥገኝነት ይኖር እንደነበረና የፖል ካጋሜ መንግስት ወደስልጣን ከመጣ በኋላ በጦር ወንጀለኝነት ወደሩዋንዳ ሊያስመጣው እየተነጋገረ እንደሆነ አስረዳኝ። ያ ለጥናት ወደኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው ወጣት እልቂቱ በተፈፀመበት ወቅት ፈረንሳይ ሀገር በትምህርት ላይ ስለነበር፤ ትምህርቱን አገባዶ ወደሀገሩ ሲመለስ ወላጆቹ፤ ወንድሞቹና እህቶቹ፤ ሌሎች የቅርብ ዘመዶቹ በሙሉ በዘር ፍጅቱ አልቀው ስለነበር እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ ሀዘን ገጥሞት እንደነበረና የራሴ የሚላቸው ወገኖች በህይወት ባለመኖራቸው ባዶነት እንደተሰማው በቁጭት ገለፀልኝ። እሱም ባጋጣሚ በትምህርቱ ምክንያት ከሀገሩ ውጪ ስለነበረ ለወሬ ነጋሪ መትረፉን አወጋኝ። ለወገኖቹ ማለትም ለቱትሲዎቹ እልቂት እንደዋነኛ ምክንያት ተደርጎ በአክራሪ ሁቱዎች ተወስዶ የነበረው ምክንያት ቱትሲዎች ቀደም ባለው ጊዜ ከኢትዮጵያ ወደሩዋንዳ የፈለሱ “መጤዎች” ናቸው ተብሎ ይታመንና ይነገር ስለነበረ፤ እስቲ ይህቺን የኛ ምንጭና መነሻ የሆነችን ሀገር ማየት አለብኝ ብሎና የፒ. ኤች. ዲ. ጥናቱንም ከኢትዮጵያ ጋር አያይዞ ወደሀገራችን እንደመጣ አውግቶኝ ነበር። ያ ሁኔታና የገጠመው ተግዳሮት እስከዛሬ ከምናቤ አልጠፋም። ከዚያ በኋላ ይህን መፅሀፍ ሳገኝ፤ ሌሎች ቢጋሩት የሚል ሀሳብ መጣልኝ፤ እነሆ ስለመፅሀፉ!  

አህፅሮተ ፅሁፍ

እ.አ.አ. በ1994 በሩዋንዳ ከፍተኛ የሆነ የዘር ፍጅት ተካሄደ። በ100 ቀናት ከ800000 የማያንሱ ቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች በአክራሪ ሁቱዎች ተገደሉ። ቀደም ባለው የቅኝ ግዛት ዘመን፤ ቱትሲዎችም ሆነ ሁቱዎች ሩዋንዳ በቤልጂግ ስር ትገዛ ስለነበር፤የጋራ ታሪክ ነበራቸው። ቤልጂጎች በፈጠሩት ልዩነት ምክንያት ማንነታቸውን የሚገልፅ መታወቂያ ለይተው ስለሰጡአቸው፤ የልዩነቱ ምንጭ ሆኖ ይታወቃል። ቅኝ ገዢዎቹ ህዝቡን በጎሳ ከፋፍለውና ሸንሽነው የጋራ ማንነቱ እንዲደበዝዝ አድርገዋል።የቅኝ ግዛት ዘመን ካበቃ በኋላ፤በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ልዩነት ይበልጥ ጎልቶ ወጣ።ቱትሲዎች የተሻለ የስራና የህይወት ተሞክሮ ስለነበራቸው፤ እነዚህ መጤዎች ናቸውና ከሀገራችን ሊወገዱ ይገባል የሚለው ስሜት ተማርን በሚሉ ሁቱዎች ውስጥ እየጎለበተ ስለመጣ፤ የራሳቸውን ወገን በዚህ ረገድ ቀስቅሰው ለበቀል አሰማሯቸው። በተለይ በመጠጥና በእፅ የሰከሩ ወጣቶች ወገናቸውን ያለምህረት ፈጁት። መፅሀፉ አንድን ቤተሰብ መነሻ በማድረግ በሀገሪቱ የደረሰውን እልቂት ለማሳየት ይሞክራል። አፃፃፉ እንደ ትውስታ የሚታይ ነው። እስከዛሬም እልቂቱ በሃያኛው መቶ ክፍለዘመን በሰው ልጅ ላይ የተካሄደ አሰቃቂ እርምጃ ተደርጎ ይዘከራል። በቅርቡ የዚህ ዘግናኝ እልቂት 25ተኛ አመት ታስቦ ነበር። ከዚህ አስከፊ እልቂት ሌሎች እንዲማሩ ይህ መፅሀፍ ተፃፈ።

ፍሬ ሀሳብ

Left to Tell (ለወሬ ነጋሪነት የተረፍኩ) የሚለው መፅሀፍ በወቅቱ ከተካሄደው የዘር ፍጅት ባጋጣሚ በተረፈች እንስት የሩዋንዳ ተወላጅ የተፃፈ፤ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የተከሰተ ጨለማ ምእራፍ ተደርጎ የሚቆጠር ድርጊት ተራኪ መፅሀፍ ነው። መፅሀፉ በ3 ኣበይት ምእራፎች የተከፋፈለ ሲሆን ፤ 23 ንኡስ ምእራፎችን ያካተተ፤ በአፍሪካ አህጉር በሩዋንዳ የተካሄደውን በማንነት ላይ የተመሰረተ የዘር ጭፍጨፋን የሚተርክ፤ ከአንዱ ምእራፍ ወደሌላው ምእራፍ በሰቆቃ የሚያሸጋግር፤ የሰው ልጅ እንደሰው ማሰብ ካቃተው ሊያደርሰው የሚችለውን አደጋ የሚያሳይ ታሪክ ነው።

ይህ ታሪክ ከዚህ አሰቃቂ እልቂት ባጋጣሚ ከተረፈችው ኢሊባጊዛ በተባለች ሩዋንዳዊት የተፃፈ ቢሆንም ታሪኩ የሰው ልጅ ታሪክ እንደመሆኑ መጠን፤ ሌሎች ካለፈው ድርጊት ይማሩበታል ተብሎ የተዘጋጀ ጭምር ነው። በመፅሀፉ መግቢያ ላይ ኢሊባጊዛ ስትተርክ የህይወት ታሪኳን ከቤተሰቧ ታሪክ ጋር አጣምራ አቅርባ፤ ሀገር ሰላም በነበረ ጊዜ የነበራቸውን የተረጋጋ ህይወት ታስቃኘናለች። አባትና እናትዋ በመምህርነት ስራ የተሰማሩ፤ መማር ሰውን ነፃ ያወጣዋል ብለው የሚያስቡ፤ ልጆቻቸውም የዚያ ፍሬ ተቋዳሽ እንዲሆኑ የበኩላቸውን ጥረት የሚያደርጉ፤ መካከለኛ ገቢ ያላቸው፤ ከራሳቸው አልፈው ሌሎችን የሚረዱ የሚወደዱና የተከበሩ ባልና ሚስት ነበሩ። አራት ልጆች ነበሯቸው። 3 ወንዶችና አንዲት ሴት። ቤተሰቡ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ሲሆኑ፤ ልጆቻቸውን በስርአት ያሳደጉ ናቸው። ቤተሰቡ ይኖር የነበረው ኪቡዬ በተባለው ክፍለሀገር፤ ማታባ ተብሎ በሚጠራ፤ ከዋናው ከተማ ኪጋሊ ርቆ በስተምእራብ በሚገኝ የገጠር መንደር ውስጥ ነበር።ወላጆችዋ ከመምህርነት ስራ ባሻገር፤ ከቤተሰብ ባገኙት የእርሻ መሬት ላይ ቤተሰቡን የሚደጉም ምርትና ተጨማሪ ገቢ የሚያገኙበት አማራጭ ስለነበራቸው፤ የተደላደለ ህይወት ለመኖር አስችሏቸዋል። ቤተሰቡ የሚገለገልባቸው ከአንድም ሁለት መኪኖች እንደነበራቸውና ኑሮአቸው የተሻለ መካከለኛ ገቢ አላቸው ተብለው የሚገመቱ እንደሁኑ ትገልፃለች።

ሩዋንዳ የሶስት ጎሳዎች ጥምረት የፈጠራት ሀገር ናት። በዛ ያለ ቁጥር ያላቸው ሁቱዎች፤ የማይናቅ ቁጥር ያላቸው ቱትሲዎችና በጣም አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ትዋ ተብለው የሚጠሩ ጎሳዎች ድምር ናት። ሁሉም የሚናገሩት ኪንያርዋንዳ ተብሎ የሚታወቀውን ሀገርኛ ቋንቋ ሲሆን፤ በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ለማስረዳት እንደሚቸግር ደራሲዋ ታወሳለች። ቱትሲዎች ቁመተ ረጃጅም፤ ፈካ ያለ ገፅታ ያላቸውና፤ አፍንጫቸው ሰልካካ የሚባሉ አይነት እንደሆኑ፤ ሁቱዎች ግን በቁመት አጫጭር ሲሆኑ፤ ፊታቸው ጠቆር ያለ፤ አፍንጫቸው ሰፋ ያለ እንደሆነ ሲጠቀስ፤ ተመሳሳይ ባህል፤ እምነት የሚጋሩ፤በጋብቻ የተሳሰሩ፤ አንዳንዴም በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ለመለየት የሚያዳግት ሲሆን፤ ትዋ የሚባሉት ወገኖች ግን ቁጥራቸው እጅግ በጣም አነስተኛና በጣም አጫጫር የሆኑ ጎሳዎች እንደሆኑ ትተርካለች።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ለመማር ብዙ ችግር እንደሌለ ይገመታል። የሁለተኛ ደረጃና  የዩኒቨርሲቲ ትምህርት እድል ተጠቃሚ ለመሆን በመሰረቱ በችሎታና በክህሎት ላይ ተመስርቶ ሳይሆን፤ በማንነት ኮታ ላይ ተመስርቶ ይሰጥ እንደነበር ከራሷ ታሪከ በመነሳት ታወጋናለች። የሁቱዎች እድል እንደቁጥራቸው ብዛት ሰፋ ያለ እንደሆነና፤  በኮታ የሁቱዎች እድል ሰፋ ያለ በመሆኑ ቱትሲዎች ችሎታም ቢኖራቸውም፤ የሚመደብላቸው ኮታ ከቁጥራቸው አንፃር አነስተኛ እንደሆነና፤ችሎታ ቢኖራቸውም የመንግስት ትምህርት ድጋፍ በሚፈልጉት መጠን ማግኘት እንደማይችሉ እንደማሳያ ትነግረናለች። ሰው ፈቅዶ ባልሆነው ነገር ህይወቱ ጭምር እንደሚወሰን መፅሀፉ ይነግረናል። ባጋጣሚ የደራሲዋ ወላጆች የትምህርትን ጥቅም የተረዱ በመሆናቸው፤ ልጃቸውን ግል ትምህርት ቤት ከፍለው እንዳስተማርዋት፤ ያ ባይሆን ኖሮ ምናልባት በሀገሯ በመንግስት ትምህርት ቤቶች የመማር እድል ሳታገኝ ትቀር እንደነበር እንረዳለን።

RPF (Rwandan Patriotic Front) በሚል ምህፃረ ቃል የሚታወቀው የሩዋንዳ አማፂ ቡድን በሀገሪቱ ብሄርን ተንተርሶ የሚታየውን ልዩነት ለማስወገድ እንቅስቃሴ ጀምሯል። አማፂ ቡድኑ በኡጋንዳ መንግስት ይረዳ ስለነበር፤ በስልጣን ላይ የነበረው የሁቱ መንግስት አገር ውስጥ ነበሩትን ቱትሲዎች ምክንያት ፈልጎ ለማጥቃት ሙከራ በማድረግ ላይ ነበር። ሁቱዎች ቅስቀሳውን በሰፊው ያካሄዱት የነበረው RTLM በሚል ምህፃረ ቃል በሚታወቀው የሩዋንዳ ሬዲዮ ነበር። ቅስቀሳው በግልፅ ይካሄድ የነበረና፤ ቱትሲዎችን ከሰውነት ደረጃ አውርደው በረሮዎች ናቸውና “እነዚህን በረሮዎች ማጥፋት አለብን” በማለት ሁቱዎችን ለአመፅ ያነሳሱ ነበር። የደራሲዋ ቤተሰቦች የተማሩና በምክንያታዊነት ላይ ተመርኩዘው የሚያስቡ ስለነበር ለሚደረገው ቅስቀሳ የነበራቸው ግምት የተሳሳተ ነበር። “ሁላችንም የጋራ አገር አለን ብለን አብረን ኖረናልና ሌላ ችግር አይፈጠርም” ብለው ያምኑ ነበር። ቤተሰቦቿ በሬዲዮ ቅስቀሳ የሚያደርጉትን “ቀውሶች ናቸው፤ ሰውም አያዳምጣቸውም” ብለው ያስቡ ነበር። የሆነው ግን ካሰቡት ውጪ ነው።

አክራሪ ሁቱዎች ቱትሲዎችንና ለዘብተኛ ሁቱዎችን እያሳደዱ ገደሉአቸው። የተወሰኑ ሁቱዎች ቱትሲዎችን ደብቀው ያንን መከረኛ ጊዜ እንዲያሳልፉ አደረጉአቸው። የደራሲዋ ቤተሰቦች ውጪ ሀገር ለትምህርት ከሄደው ታናሽ ወንድሟና ከራስዋ በቀር ሁሉም የፍጅቱ ሰለባ ሆኑ። ደራሲዋ ባጋጣሚ ባካባቢው በነበሩ የሀይማኖት አባት ቤት ገብታና ዋናውን መፀዳጃ ቤት ዘዴያዊ በሆነ መንገድ ከልለው (ደራሲዋ ባመነጨችው ሀሳብ) ህይወቷ ሊተርፍ ችሏል። ሁቱዎቹ ይጠቀሙበት የነበረው የሬዲዮ ስርጭትና ለረጅም ጊዜ የተካሄደው ፀረ-ቱትሲ ፕሮፓጋንዳ ወገኖቻቸውን በበጎ ለማየት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል። ከግድያው ጎን ለጎን ንብረት ማውደምና ማቃጠል የዘወትር ተግባር ነበር። ህይወታቸውን ለመታደግ መታጠቢያ ቤት ታፍነው በቆዩበት ጊዜ በሁለት ነገር ተቸግረው ነበር። ምግብ፤ውሀና ሌሎች ለመኖር አስፈላጊ ናቸው የሚባሉ ነገሮችና መቼ ይሆን ይህ ሰቆቃ የሚያበቃው የሚለው ሀሳብ፤ በተለይ ፍጅት አድራሾቹ እየዞሩ የሚሰሩትን ተግባር እነሱ ወዳሉበት ቤት ጭምር በተደጋጋሚ በማምራት ይበልጥ ተሳቀው ያንን አስቸጋሪ ወቅት እንዲያሳልፉ አድርገዋቸዋል።

ከወራት ቆይታ በኋላ በፖል ካጋሜ የሚመራው የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር ሀገሪቷን ተቆጣጠረና ህግና ስርአት ለማስከበር ሞከረ። በየቦታው ከእልቂቱ የተረፉ ወገኖች ከየጎሬአቸው ወጡ። ከመታጠቢያ ቤቱ ሲወጡ ብዙዎቹ ክብደት ቀንሰዋል፤ ሰውነታቸው ገርጥቷል። የንፅህና ጉድለቱ ተደምሮ የሚያውቋቸው ሰዎች ጭምር ለመለየት ተቸግረው ነበር። የእነርሱ መሳደድ ቢያበቃም፤ ብዙዎች ወገኖቻቸውን በፍጅቱ አጥተው ቤተሰብ አልባ ሆኑ። ደራሲዋም እናቷን፤ አባቷንና ሁለት ወንድሞቿን፤ ሌሎች የቅርብ ቤተሰቦቿን አጥታ የባዶነት ስሜት ተሰማት። በዘር ፍጅቱ ተዋናይ የነበሩ ሩዋንዳውያን ተራበተራ ተለቅመው ዘብጥያ ወረዱ። ዋናዎቹ የእልቂቱ መሀንዲሶች እግሬ አውጪኝ ብለው ወደሌሎች ሀገሮች ፈረጠጡ። ደራሲዋ በኋላ በግሏ ባገኘችው እድል ወደአሜሪካ አቅንታ እዚያ ትኖራለች። ከተፈፀመው እልቂት ሌሎች ወገኖች እንዲማሩበት ብላ ፃፈችው። ዛሬ በሩዋንዳ “ሁቱ ነኝ” “ቱትሲ ነኝ” የሚል ማንነት የለም፤ “ሩዋንዳዊ ነኝ” I am a Rwandese በሚል ማንነት ተተክቷል። የጋራ ማንነትን ማጎልበት የተሻለው ነገር ነው ብለው በዚያ ላይ በሰፊው እየሰሩ ነው። ሌላው ዓለም ከእልቂቱ እንዲማርም፤ የተባበሩት መንግስታት ተመሳሳይ ተግባር በሌሎች ሀገራት እንዳይፈፀም መመሪያ አወጣ፤ በዚህ መመሪያ መሰረትም ተመሳሳይ እልቂት ዓለም እንደማይታገስ፤ ችግሩም የዘር ማጥፋት ወንጀል ሆኖ የሀገር ብቻ ሳይሆን የዓለም እንደሆነ ተደርጎ እንደሚወሰድ ተነገረ። የተለያየ ቋንቋና ነገድ ያላቸው ሀገሮች ከዚህ ኣይነት ጥፋት እንዲማሩ የሚያስተምር መጽሀፍ ነውና መፅሀፉን መተርጎም፤ ማንበብና ሁኔታውን ላልተረዱት ወገኖች ማሳወቅ የዜግነት ግዴታችን ይመስለኛል። አበቃሁ!!!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top