የታዛ ድምፆች

የባልንጀራ ወግና የሊሙ ኢናሪያ ትዝታ

ዐረቡ ቦሩ የሊሙ ኢናሪያ ሰው ነው። በልጅነት ነው የተለያየነው፣ የዛሬ 45 ዓመት ገደማ። የልጅነት ጓደኛን እንደማግኘት የሚያስደስት ነገር የለም። ትዝታው ብዙ ነውና። በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዘመን፣ ከዚያም በኋላ ስላለፈው ረዥም የህይወት ውጣ ውረድ ብዙ አንስተን ጣልን። መቼም የሊሙ ኢናሪያን ጫካዎች፣ ሜዳዎች፣ የቡና መፈልፈያዎችና ማሣዎችን አካለልን ማለት ይቻላል። እንደ ጊቤ ወንዝ እየተጠማዘዝን ያልነካነው ነገር አልነበረም።

ዐረቡ ከእኔ የተለየው ከ1966 ዓ.ም. አብዮት በኋላ ነው። እኔና እሱ የ6ኛ ክፍል ‹ሚኒስትሪ› ተፈትነን ወደ ሊሙ ገነት አለፍን። ያኔ እንደዛሬው ዘመን ት/ቤት በቅርብ ስለማይገኝ ከወላጅ ተለይቶ፣ ስንቅ ሸክፎ ወደማያውቁት ወረዳ መሄድ የተለመደ ነበር። መቼም የደረሰባችሁ ታውቁታላችሁ። ዐረቡ ግን አባቱ በድንገት በመሞታቸው በመሃል ትምህርቱን አቋርጦ ተመለሰ። አባቱ የሊሙ ሠቃ አንድ የታወቁ ቆሮ (ባላባት) ነበሩና ሀብታቸውን መሰብሰብ ነበረበት። መቼም የሊሙ ሀብት ህልቆ መሳፍርት  የለውም። ቡናው፣ ኮረሪማው፣ ዝባዱ፣ ጥምዙ፣ ዝንጅብሉ፣… ተዝቆ አያልቅም። ከዚያ በኋላ ወደ ትምህርቱ ዓለም አልተመለሰም። አንዴ ጅማ እያለሁ በጻፈልኝ ደብዳቤ ቁጭቱን ከአንጀቱ ገለፀልኝ። “ከሠጋር በቅሎ ላይ የወደቀ አንካሳ ሆኜልሃለሁ” ሲል ልብ የሚነካ ደብዳቤውን ላከልኝ። ያኔ ገንዘብ እየሸመጠጡ፣ ለትምህርት ግን አለመታደል ፍፁም የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። ልብ የሚሰብር አጋጣሚ።

      ዐረቡን አሁን ሳገኘው ያ ቱርክ የሚመስል ገጽታው ተለውጧል። ገርጥቷል። ግንባሩ የሰሜን ሸንተረሮችን መስሏል። ካለዕድሜው ዕድሜ ተሸክሟል። ጉፍጣውን አናቱ ላይ ጥሎ፣ ዘባተሎ ልብሱን እንደምንም ለብሶ ሳገኘው ማመን ነው ያቃተኝ።

      ማምሻውን ትዝታችንን ለመኮምኮም ስለፈለኩ በጊዜ ተገናኝተን አብረን ለማደር ወሰንን። ከዚያን ቀን በፊት ከሌላ የልጅነት ጓደኛችን የሺ ከበደ (ኩራዝ) ቤት አድሮ ነበር። ዛሬ ደግሞ በሊሙኛ ሀድራው ሞቅ እንዲል አነጣጥፈን ተቀመጥን። ቡናው እየተቀዳ፣ ቀንበጡ እየተቀጠፈ፣ ዕጣኑ ቤቱን እያወደ፣ ምርቃቱ እየወረደ የሊሙ ኢናሪያን ድባብ አመጣነው። ሊሙ ከነ ሙሉ ክብሯ ወደ ጉለሌ መጣች። ሀድራው ሞልቷል። ቤቱ ሞቅ ብሏል። የሊሙኛ ጨዋታችን መስመር መስመሩን መያዝ ጀምሯል።

      ዐረቡ በድንገት፣ “ስማኝማ! አሁን ቄሮ፣ ቄሮ የሚሉት ያኔ እኮ እኛ ደንበኛ ቄሮ ነበርን። በግለሰብ የማንነዳ ቄሮዎች፣ የነቃን ቄሮዎች፤ ያውም የኤለመንተሪ ተማሪ ሆነን የምርጫ ተወዳዳሪዎችን ለማስመረጥ ቅስቀሳ የምናደርግ የሰላን ቄሮዎች” ብሎ ወደ ኋላ ዘመን ወሰደኝ። “አዎን! ራቢያ አብዱልቃድርን እኛ እኮ ነን ያስመረጥናት!” አልኩት።

      ራቢያ አብዱልቃድር (ልዩ ምልክትዋ- ነጭ ፈረስ) ሊሙ ሠቃን ወክላ ስትወዳደር፣ መምህሩ ጌታቸው ከበደ (ልዩ ምልክቱ- ቀይ ጨርቅ) ደግሞ ሊሙ ኮሳን ወክሎ ነበር የተወዳደረው። እንዲያውም ጌታቸው ከበደ ለውድድሩ መሪ ቃል አድርጎ የመረጠው፡-

“ውስኪና ብራንዲ መጠጣቱን ትተን፣

ልማት እናስፋፋ፣ ትራክተሩን ገዝተን!

የሚለውን ነበር። ይህች መሪ ቃል ዛሬም የምትሞት አትመስለኝም። እንዲያውም ለዛሬው ብልጽግና ፓርቲ በልኩ የተሰራች ጃኬት አትመስላችሁም ወዳጆቼ?!

***

ሌላው የሊሙ ሰው ከሆንክ በትንሹ ሁለት ስም ይኖርሃል። ዐረቡ -ቱርኩ፣ የሺ- ኩራዝ፣ ዳምጠው- ፈንጣጤ፣ እስጢፋኖስ- ጀበኔ፣ መኩሪያ- እንጐቼ፣ ናስሬ – ሽንክሪሪ፣ ጌታነህ- ጐጄ፣ ወዘተ. ስሞች ነበራቸው። በተጨማሪ የሀገሬውን ባህላዊ ስም መያዝ የግድ ነው። አባ ብያ፣ አባ ቦራ፣ አባ ዝናብ፣ አባ ሜጫ፣ ሀዳ ሲንቦ፣ ሀዳ ቆሮ ወዘተ. አይነት ስሞች የሌለው ሰው የለም። ሊሙ የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ ተቻችሎ የመኖር ወረዳ ናት። በሊሙ ሳፊ ዘር ያለው የለም፤ እንደ ሠርገኛ ጤፍ ነው። ባህታዊነት የለበትም። ይሄ የቆሮ ዘር ነው፣ እነዚያ የወርዋሪ ዘሮች ናቸው መባባል አልነበረም። አብረን ቡሄና ሆያ ሆዬ እንጫወታለን። በዚያን ጊዜ ረሽ ጠመንጃ ይዘን ለቆቆች አደን (አደሞ) እንወጣለን። ሲያሰኘን ወደ ወንዝ ወርደን እንዋኛለን። በተለይ ት/ቤታችን ዋናው አሰባሳቢያችን ነበር። ለምሳሌ ያህል አበራ የዕብየሁ የተባሉትን መምህር እኔም፣ ዐረቡም እናስታውሳለን። የመቀሌ ሰው ነበሩ። ለወላጆች ቀን የሚደርስ ትያትር ሰጥተው ያስጠኑናል። ዓርብ፣ ዓርብ የትምህርት ክፍላችንን ካፀዳን በኋላ “Gift from the American People” የሚለውን የዱቄት ወተት አፍልተን በጋራ እንጠጣለን። ከእኛ የሚጠበቀው የአስር ሳንቲሙንና ባለ ቀዩን ዝሆን ስኳር ገዝቶ መሰለፍ ብቻ ነበር። ያ ወቅት ዛሬ ካልዲስ ሄዶ ካፑቺኖ እንደመጠጣት ይቆጠራል።

      አብዛኛውን ጊዜያችንን በዋዛ ፈዛዛ ሳይሆን የምናሳልፈው ወደ ተራራ ወጥተን ስንጨዋወት እንውላለን፤ ወይም ወደ ጀጀባ ወንዝ ወርደን ስንዋኝ እንቆያለን። ከራበን ዕድሜ ለሊሙ ጫካ እንጆሪውን፣ ኮኩን፣ ዘይቱናውን፣ ዶቅማና ትርንጐውን ከዝንጀሮዎች ጋር እየተባረርን ስናጣጥመው አምሽተን ከብቶች ይዘን ወደቤት እንገባለን።

      በጨዋታችን መሀል ነገርን – ነገር ያነሳዋልና ዐረቡ “የመጀመሪያውን የሊሙ ኢናሪያን መሪ ታውቃለህ?” ሲል አፋጠጠኝ። “አዎና” – አባ ቦጊቦ መሆናቸውን ከሳቸውም በኋላ ዳግማዊ አባ – ቦጊቦ እንደነገሱ ነገርኩት።

      አዎን! አባ – ቦጊቦዎች ሁለት ናቸው። ቀዳማዊና ዳግማዊ። ከዚያ በኋላ የአባ – ቦጊቦዎች ዘመን አከተመ። የራስ ደርሶ ጦር በንጉሥ ተክለሃይማኖት ትዕዛዝ ሊሙ ኢናሪያን ከተቆጣጠረ በኋላ ነው በአባ – ቦጊቦ ዳግማዊ ዘመን የሊሙ ነፃነት ያከተመው። በነገራችን ላይ ራስ ደርሶ ጎጃሜ አይደለም፤ የኦሮሞ ጦር ጄኔራል ነበር።

      ታሪክ እንደሚነግረን ቀዳማዊ አባ – ቦጊቦ በ18ዐ2 ተወልደው በ1861 (እ.ኤ.አ.) ነው የሞቱት። ሊሙ ኢናሪያ በቀደመው የጊቤ መንግሥት(Gibe State) እጅግ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታና የደለበ ሀብት ያላት መንግሥት ነበረች። (ዋ! የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ካስቀየማችሁን ለብቻችን ተገንጥለን መንግሥታችንን እንዳናቆም!?)።

አባ – ቦጊቦ በሳፓ (Sappa) መንደር ተወልደው ግዛታቸውን ግን ሰቃ በምትባል ከተማ መስርተው ይኖሩ ነበር። በነገራችን ላይ ሰቃ በጣሊያን ጊዜ ኮብል ስቶን የገባላት የመጀመሪያዋ ከተማ ሳትሆን አትቀርም። አባ- ቦጊቦ ቁመተ ዘንካታ፣ መልከ መልካም፣ ወንዳ ወንድ ተክለ ሰውነት፣ አንደበተ ርቱዕ ሰው እንደነበሩ ይነገራል። ወላጆቻችን እንኳ “የአባ – ቦጊቦ መንፈስ ያውቃል!” ሲሉ እንደነበር አስታውሳለሁ። አባ- ቦጊቦ እንደማንኛውም የሊሙ ሰው አንድ ስም ብቻ አልነበራቸውም። ሌላኛው ስማቸው ኢብሳ (ብርሃን) ነበር። ብዙ ጊዜያቸውን የጦር ስልት በመማር ነበር ያሳለፉት ተብሎ ይነገርላቸዋል። ፈረሳቸውን ቦጊቦን አስጭነው አካባቢውን አቀኑ። ሦስት ዋና ዋና ነገሮች ለአመራራቸው እንደጠቀሟቸው ዐረቡ አባቱ እንደነገሩት አወሳ። “አደረጃጀት፣ መረጃና ሀብት! ዛሬስ ቢሆን ሀገር ለመምራት ከዚህ ሌላ ምን አለ?” ሲል መልሶ ጠየቀኝ።

      ቀጠለ። “የእኛ የኢትዮጵያውያን የሥልጣን ፍቅር እንዴት ክፉ እንደሆነ ከአባ – ቦጊቦ ማወቅ ይቻላል። አባ ቦጊቦ ስልጣን ላይ የወጣው ታዋቂውን አባቱን አባ ጐምልን በመፈንቅለ መንግሥት አባሮ እንደሆነ የዛሬ ሰው ብትነግረው ምን ይል ይሆን?” ሲል ጠየቀ። “ይህ እኮ አዲስ አይደለም፣ ታሪካችን በመገዳደልና በደም የጨቀየ ነው። ለዚህስ አይደል እንደ ግመል ሽንት ሀገሪቱ ወደ ኋላ የምትነጉደው?” ስል መልስ አልባ ጥያቄዬን ጣል አደረኩለት፣ ነገር ይለውጥ እንደሆነ ብዬ።

      እሱ ግን ከአባ ቦጊቦ ራስ አልወረደም። “አሥራ ሁለት ሚስት፣ 5ዐ ልጆች፣ ነበራቸው። 2ዐ ወንደችና 3ዐ ሴቶች። ወንዶቹ ያባታቸውን ፈለግ ሲከተሉ፤ ሴቶቹ ደግሞ ለዘመኑ የጊቤ መንግሥታትና ከዚያም አልፎ ባሉ ግዛቶች ለፖለቲካዊ ጋብቻ ተሰጡ። እንዲህ ነው ያኔ ሀገር የሚቀናው። ልጆቻቸውን ብቻ ሳይሆን ሀብታቸውንም ገፀ-በረከት በማቅረብ ይታወቃሉ አባ ቦጊቦ። ሀብት ሞልቷላ! ኮረሪማው፣ዝባዱና ቡናው፣ ለጐጃም፣ ለሸዋ፣ አልፎ ተርፎም ለአፄ ቴዎድሮስ ሁሉ ይላክ ነበር አሉ። የሊሙ ሀብት ያልደረሰበት ቦታ የለም። ይህችን አዲስ አበባን እንኳን የገነባው የሊሙ ሀብት ነው፤ ዳሩ ግን ሊሙ አሁንም በሀብት ውስጥ ተኝታ የምትፎክት ድሃ ወረዳ ሆና ቀርታለች። አያሳዝንም?” እያለ እጣኑን ምድጃው ላይ ቦግ አደረገው።

      ሀድራው እንደሞቀ ነው። እጣኑ እንዳንተያይ ጋርዶናል። ትዝታችን በሁለታችን ልብ ውስጥ እየተብሰለሰለ ይዞን ወደ ሊሙ ነጐደ።

      በዚያን ዘመን ከኢትዮጵያ ወረዳዎች ሁሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እና ባንክ ቤት የነበራት ሊሙ ነበረች። ሚስተር ኦጄንስ የተባለው አሜሪካዊ ከጓደኛው ሚስተር ሊ ጋር ነበር ሊሙን ያዘመኑት። ለሊሙ ገነት መብራት ብቻ ሳይሆን ዘመናዊ ሆቴልም ሰርተው ነበር። “Clean bed excellent food” የሚል ማስታወቂያ ባለው ሆቴል። ጊዜው በመርዘሙ የሆቴሉ ስም ላይ ሁለታችንም ልንግባባ አልቻልንም። ለማንኛው የከተማው አድባር ከሆነው ዋርካ በላይ ከጅማና ከአዲስ አበባ የሚመጡ ሰዎች ያዘወትሩበት እንደነበር አይረሳንም። የሊሙ ኢናሪያ ከተሞች ሁሉም አንዳንድ ግዙፍ ዋርካዎች አላቸው። በዚህ ግዙፍ ዋርካ ሥር ነው በዓላት የሚከበሩት። የአፄ ኃይለሥላሴን የልደት በዓል አከባበር አስታወሰኝ ዐረቡ። “ይኑርልን ለክብራችን…” “በሸለቆው ውስጥ ስንጓዝ…”፣ “ኃይለማርያም ማሞ የጦሩ ገበሬ …” የሚለውን የልጅነት መዝሙር በዚያች ሞቃታማ ክፍል ውስጥ እየተቀባበልን ነጠላ ዜማችንን ለቀቅነው። በድንገት “የስንቁሬውን ጭቃ ሹም አሟሟት ታስታውሳለህ?” ብሎ ጠየቀኝና መልስ ሳይጠብቅ ገነቲ ጫንቃ ነበር የጭቃ ሹሙ ስም አለኝ። ገነቲ በጃንሆይ የልደት ክብረ በዓል የከተማው ዋርካ ሥር የቁርጥ ሥጋ አንቆት ነበር የሞተው! መቼም ሞት አዲስ እንደሆነ ሁሉ በሊሙ ጉድ ነበር የተባለው። የአሟሟቱ ወሬ ጋቲራ ተራራን አልፎ፣ ጀጀባ ወንዝን ተሻግሮ የቦሰንቴን ጫካ እየዞረ ሊሙንና ማዕዘናቷን አናወጣት። ወሬ ወሬን እየወለደ እንደ ጊቤ ወንዝ እየተጠማዘዘ ዞሮ ተጨማምሮ ወደ ከተማችን መጣ። እኛም የአንድ ሳምንት ወሬ አድርገን በመሀመድ ወርዲ ሙዚቃ እየተከዝን፣ በራድ ሻያችንን አዘን አቋሸርን። እነሆ ዛሬ ደግሞ እኔና ዐረቡ የባልንጀራ ወግ አደረግነው።

      ጨዋታው ደርቷል። “ትዝታ አያረጅም” የሚባለው አባባል እውነት ሆኗል። ከዚህ ትውስታ በኋላ ጣሊያናዊውን ባለሀብት ፓጋኖ ሳልቫቶሪን እና የቄስ መምህራችንን አባ አባተ ገላውን አስታወስን።

      ፓጋኖ ሳልቫቶሪ ሰቃ ከተማ ላይ የዳቦ ስም ወጥቶለት በታደሰ ብሩነት ነበር የሚታወቀው። ቀዳሚ ወፍጮ ቤትና የቡና መፈልፈያ በሊሙ የጀመረው ይህ ሰው ነበር። በልጅነት ትውስታችን ወ/ሮ ጣይቱ ጠጅ ቤት ተጐንጭቶና ፍም መስሎ ይወጣ ስለነበር በዕዝነ ልቡናችን መለስ ብለን ቃኘነው። በጂማ ከተማም ቢሆን ከረሙቡላ ማጫወቻ ያለው ቡና ቤት ከፍቶ ፈረንጅ አራዳን አድምቋት እንደነበር ይታወሳል።

      ዐረቡ ስለ ቄሱ አባ አባተ ገላው መታወር ሲነግረኝ በጣም አዘንኩ። እኔን፣ ዐረቡንና የአትናጐን (አትናጎን – የኦሮሚያ ሳንቲያጎ ነበር የምንላት) ልጆች ፊደል ያስቆጠሩት እኝህ ሰው ነበሩ። ለአገልግሎታቸው ከአንድ ብር ያለፈ ክፍያ አልነበራቸውም። ዳሩ ግን በምትኩ ወንዝ ወርደን ውሃ መቅዳት፣ ጭራሮ መልቀም፣ ከብቶችን በማስገባት ወረታቸውን እንከፍል ነበር። ዐረቡ ብዙ ጊዜ ስለሚያገኛቸው “መንገድ ባሻገርኳቸው ቁጥር ከምርቃታቸው በተጨማሪ አንተን ይጠይቁኛል” አለኝ። ትዝታ አያረጅምና አሁንም ልቤ በሀዘን ፈሰሰ። እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ሼህ ኦኮላ (አንካሳው)፣ የየዶዎቹ ሼሆችና ሠጋር በቅሎዎቻቸው፣ የአትናጐ ቅዳሜ ገበያ፣ የአባ አመዶ (የመናዊው ባለ ሱቅ) ፓስቲ ቤት፣ በ1963 የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በመጠለፉ ቁጭት አሊ ዐረቡ በር ላይ ወጥተን –

“የሶሪያ አረቦች ይውጡ ካገራችን፣

ከእንግዲህስ ወዲያ አልቋል ትዕግስታችን፤” ብለን የፈከርነው ሁሉ ወደ ኋላ መልሰው ዛሬም በትዝታ ያንገላቱኛል። ትዝታ አያረጅም።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top